Sunday, September 4, 2016

ሸምስ ቡሴር

" ሸ ም ስ      ቡ ሴ ር "
#ሳteናw

   ሸምስ … ከረጅም አድካሚ ጉዞ ቡሃላ አቧቷ ቀዬ ደረሰች። ለሷ አቀባበል ለማድረግ በቅድም አያቴ ጎጆ ቤተሰብ፣ጎረቤት ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ተሰብስቦ ለቡና በተቀመጠበት ነበር… የሸምስን ቀልብ አንዲት ህፃን ልጅ የሳበችው። ሸምስ… ህፃኗን ባየች ቁጥር ልቧ ድንግጥ ድንግጥ ትር ትር ይልባት ገባ። ቢጨንቃት ቢጠባት "ያቺ አይነ ትልልቋ ልጅ  ማን ነች? ስትል አጠገቧ የነበረችውን ሴት ጠየቀች"።"ሴትየዋም እስኪ በደንብ እያት!"። አለቻት። ሸምስ አንዳች ነገር ጠረጠረች። ግን እርግጠኛ ስላልሆነች ጥርጣሬዋን ዘላ ወዸ ጥያቄዋ ገባች "እባክሽን አታስጨንቂኝ ማነች?" "እንግዲየውስ እርምሽን አውጪ ያንቺው ልጅ ነች።"……
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

እስከማውቀው ድረስ በምድር ላይ ከሰማዋቸው የእናቶች ታሪክ የአብራኳን ልጅ በእልህ ጥላ የእንጀራ ልጆቿን በእንክብካቤ ያሳደገች እናት ብትኖር የእናቴ እናት አያቴ ሸምስ ቡሴር ነች።

   አያቴ በወጣትነት ዘመኗ ለምታምንበት አቋሟ ምንም ማንም ሀይል የማይበግራትና በጣም እልከኛ በባህሪዋም ሀይለኛ የተሰኘች ነበረች። ይህ ባህሪዋና እልከኛነቷ ከኮረዳነቷ እስከ ብስለቷ ድረስ አብሯት የዘለቀ ባህሪይ ነበር። በተወረደልኝ የታሪክ መረጃ መሰረት ሀይለኛ ነች!! በሚል ምንም ባል ያላጣች ስትሆን የፈለገችውን ነገር በፈለገችው መልኩ የራሳ የማድረግ ብቃት ከመላበሷ ባሻገር በተክለ ቁመናና በመልኳ የተዋበች ነበረች።   ይህችው ሀይለኛዋ አያቴ ለእናቴ አባት ሁለተኛ ሚስት ሆና ከቤቱ ገባች። እሷና ጣውንቷ በተመሳሳይ ጊዜ ወለዱ፣ አያቴ እናቴን ፣ ጣውንቷ አጎቴን። ሁለት አራስ በአንድ ጊዜ ያስተናገደው የአያቶቼ ቤት አራስ አራስ መሽተቱ አልቀረም። አንድ ዕለት እንዲህ ሆነ። አያቴ ሸምስ በአራስነት ጊዜዋ ከአራስ ጣውንቷ ጋር እየታረሰች ባለችበት ሁኔታ ባሏ መጥቶ ቀልድ አዘል ነቆራ ጣል አደረገባቸው።  ጣውንቷ ምንም አላለችም። አያቴ ግን አፍንጫህን ላስ! አለችውና ገና አጥንቷ ያልጠነከረችው እናቴን ጥላለት ወደ አባቷ ቤት ነጎደች። ታምናለህ በቃ ልጇን ጥላ ሄደች። የእናቴ አባት ትመለስ ዘንድ ሽማግሌ ቢልክ፣ ምን ቢቧጥጥ። ሀይለኛዋ አያቴ መስሚያዋ ጥጥ። እናቴ ከአጎቴ ጋር እንደመንታ የእንጀራ እናቷ ጡት አየጠባች አደገች። አያቴ ሁለተኛ ሁለተኛ ሚስት ሆኜ ባል አላገባም! በሚል አቋሟ ፀንታ በአባቷ ቤት ከሀይለኝነቷ ጋር መኖራን ቀጠለች። ለሁለተኛ ጊዜ ተኩላ ተሞሽራ ተዳረች። ብዙም ሳይቆይ ይኸው ሁለተኛ ባሏ፣ በምታምንበት አቋም የሚፃረር ተግባር ፈፀመ። እሷ ላይ ሌላ ሚስት አገባ። "ልጅ ስላክወለድኩለት ነው አይደል የደረበብኝ ?" ብላእልህ ተናነቃት። በሆዷ ላንተ እልህ የማደርገውን እኔ አውቃለው ብላ ጠበቀች። ሁለተኛው ባሏ አዲሷን ሙሽራ ሀይሎ ጋ ሆ እያስጨፈረ በዋናው በር ሲያገባ። እልኸኛዋ አያቴ "በል እንግዲህ አልተገናኘንም!" ብላ። በጓሮ በር ነካቸው። በቃ! አፍንጫህን ላስ! አለችው። ድጋሚ  ወደ አባቷ ቤትገባች። የባል ገዷ ለሱ እልህ፣ከሱ ጋር ማይስማማ የነበረን ሰው። ለሶስተኛ ጊዜ አገባች። ሁለተኛ ባሏን በሶስስተኛ ባሏ አሳበደችው። እገድላቸዋለው አለ። በዚሁ የመጣ ከዚሁ ባሏ ጋር ለኑሮ  ወደ አዲስ አበባ መጡ።   እንግዲህ ጊዜው በንጉሱ ዘመን መሆኑ ነው። ህይወቷ በአዲስ አበባ ቀጠለች። አራት ኪሎ አካባቢ በነበረው በባሏ ቤት የሻሜታ ንግድ ጀመረች። አላዋጣትም! የአራት ኪሎ አካባቢ ኑሮም አልተመቻትም።(ለፖለቲካ ቅርብ ስፍራ ስለነበር ይሆን?) እንጃ ብቻ አልደላትም። አንድ ቀን ለዚሁ ሶስተኘ ባሏ መርካቶ ወንድሞቼ ስላሉ እነሱ ጋር ሄደን ኑሮዋችንን አናሻሽል ስትል አማከረችው። አይሆንም አላታ። እሷም አፍንጫህን ላሳታ! ብላ። ሶስተኛወንም  ጥላ ወደ መርካቶ ነካቸው። ወንድሞቿ ጋር ገባች። የግሏን ስራ መስራት ጀመረች። አያቴ ሶስት አግብታ ብትፈታም ባል አልጠጠረባትም። ብዙ ባል እየመጣ እሷን ለትዳር መጠየቅ አልተወም። ያመነችበት ሰላልገጠማት በጄ አላለችም። ከመጀመሪያ ባሏ በተጋባችው እልህ የመጣ የአብራኳን ክፋይ ልጇንን እንኳ ዞር ብላ አላየችም። የእልህኛነቷ ብዛት በአብራኳ ክፋይ እንኳ እንድትጨክን አስገደዳት።  በመርካቶ የአይብና የቆጮ ንግድ ጀመረች። (የዛሬው የመርካቶው ቆጮ ተራ በአያቴ ዘመንም ነበር አይገርምም።) እልኸኛዋ አያቴ ህይወቷን ለብቻዋ ቀጠለች። በመጨረሻም እዛው መርካቶ ሚስቱ አራት ልጅ አከታትላ ወልዳለት የሞተችበትን ሰው በዘመድ በኩል እንደ አጫት ተነገራት። መልሷ እስኪ ሄጄ አየዋለው ነበር። ተመልከትልኝ ጉዷን! ሴት ልጅ፣ ወንዱ ቤቷ ሄዶ አይቷትና መርጧት ብቻ በሚያገባበት በዛ ጊዜ፣ ማን ያግባት ማን ሳታውቅ ዝም ብላ እንደተመረጠች ተነድታ ወደ ባሏ ቤት በምትሄድበት ዘመን።  አያቴ በተገላቢጦሽ ያጫትን ሰው ቤቱ ሄዳ አይታው እራሷው እንደሚሆናት ለመወሰን ቀጠሮ አስያዘች። ይህ አድራጎቷ ተያይዞ የመጣውን ወግ ልማድ ወደ ጎን ብላ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ (አቦ ጀግና!)። አያቴ ስለሆነች አያሽቃበጥኩላት ወይም እየሞላውህ እንዳይመስልህ የምተረተርልህ ሀቅ ነው። ከፈለክ ድንጋይ ነክሼ እምልልሃለው።( አረ ሲያምርህ ይቅር ከፈለክ አትመን…ህእ)

   በቀጠሮው መሰረት ተደግሶ ወደ አጫት ሰው ቤት ሄደች። አየቸው! ወዲያወ ፎንቃ! በቃ በአንዴ ወደደችው። እናታቸው ጥላቸው የሞተችውን አራት ህፃን ልጆቹን ስታይ ደግሞ ይብስ ባባች። እሺታዋን እዛው አበሰረች። ድግሱ የተሳካለት ሆነ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ አግብታ ህይወትን  ቀጠለች። የራሳን የአብራኳን ክፋይ በእልህ ለባሏ ጥላ የባሏን ልጆች እንደ ልጆቿ በእንክብካቤ አሳደገች።   አያቴ ፈጣሪ መጀመሪያ ጥላት በመጣችው ልጇ አቄመባት መሰል ከእናቴ ቡሃላ ለልጅ አልታደለችም።

  አራስ ቤት ጥላት የመጣችው ልጇ(እናቴ) ከእንጀራ እናቷ ጋር ተስማምቶ መኖር ቢያቅታት። ወደ እናቷ አባት ቤት ጠፍታ መጣች።(በማን ትውጣ?)

   እናቴን ሲያዩዋት በወንድ አያቷ አለቀሱ። እናቴ ከዚህ ቡሃላ  በአያቷ እጅ ህይወቷ ቀጠለች። ከዘመን ቡሃላ አያቴ አባቷ ቤት የምትሄድበት አጋጣሚ ተፈጠረ። የልጇን ወደ አባቷ ቤት መምጣት የማውታቀው አያቴ አባቷ ቤት ገጠር ሄደች። በአባቷ ቤት … ቤተሰብ ሁሉ ተሰብስቦ በተቀመጠበት የአያቴን ቀልብ አንዲት ልጅ ሳበቻት። ባየቻት ቁጥር ልቧ ድንግጥ ድንግጥ ይልባት ገባ።"ያቺ አይነ ትልልቋ ልጅ  ማን ነች?" ስትል አጠገቧ የነበረችውን ሴት ጠየቀች።"ሴትየዋም እስኪ በደንብ እያት!"። አያቴ አንዳች ነገር ጠረጠረች። ግን እረግጠኛ ስላልሆነች ተወችውና።"እባክሽን አታስጨንቂኝ ማነች?" "እንግዲየውስ እርምሽን አውጪ ያንቺው ልጅ ነች።"   አያቴ በተሰበሰበው በሰው መኻል ተንደርድራ ሄዳ ልጇን አቀፈቻት። ረጅም ሰዓት እንዳቀፈቻት። አዬዬዋን አስነካችው። "እኔ ነኝ ገዳይሽ!" "አኔ ነኝ ገዳይሽ!"። ረጅም ሰዓት እናቴን አቅፋ አነባች። ትላንት በጉርምስናዋ የፈፀመችው ተግባር ዛሬ ልብ ስትገዛ ፀፀታት። ፀፀቱ የእግር አሳትት ሆኖ መላ አካሏን ለበለባት። እናቴን ከተማ ወስዳ ለማሳደግ አቧቷን ጠየቀች። ቤት ውስጥ ሌላ ልጅአገረድ ሰላልነበር አባቷም የአባቷም ሚስት በጄ አላሉም።   አያቴ ከዛ ቡሃላ ለእናቴ በርቀት የሚያስፈልጋትን ታሟላላት ጀመር። የቁስ ፍላጎቷን ማሟላቷ፣ የእናትነት ፍቅር ለልጇ አለመስጠቷ የፈጠረባት የስነ ልቦና ክፍተት ሊሞላላት አልቻለም። ዘመን አልፎ ዘመን መጣ። ልጇም (እናቴ) ተዳረች። ወለደች። ሁለተኛዋን ልጅ በእናቷ ቤት መርካቶ መጥታ ነበር  የወለደቻት። ከዚህ ቡሃላ አያቴ እንድ ነገር አሰበች። ለአንድያ ልጇ የነፈገቻትን የእናትነት ፍቀር ለልጅ ልጇ ልትሰጥ። ሲፀፅታት የኖረውን በልጇ ልትክሳት። የልጅ ልጇን ለማሳደግ እዛው መርካቶ አስቀረች። ይህም አያቴን አላረካትም። እናቴ ልጇን እናቷ ዘንድ ትታ ለመሄድ ስትሰናዳ። አስቀምጣ እንዲህ አለቻት። "ልጄ በህፃንነትሽ የነፈግኩሽን ፍቅር ዛሬ ለልችጆሽ በመስጠት ልክስሽ እሻለው። ይህች ልጅ እኔው ጋር ታድጋለች። ከዚህ ቡሃላ የምትወልጂውንም ወንድ ልጅ እንደወለድሺው ለኔው ነው የምትሰጪኝ! ብላ ቃል አስገባቻት። እናቴ ቃሏን እንደምትጠብቅ ምላ ተገዝታ ወደ ቀዬዋ ነካችው። ቃል በተጋቡ በሁለት አመቱ እናቴ ሴት ልጅ ወለደች ይህቺ ልጇ ከሳ ጋር ታድጋለች። እናቷ የገባቸው ቃሏ ወንድ ልጅ ነው። ድጋሚ በሁለት አመቱ ወለደች። አሁን ወንድ ሆነ። በቃሏ መሰረት የአራስነት ጊዜዋን እንደጨረሰች ወንዱን ህፃን ልጇን ለእናቷ ሰጠች። በደንብ እስኪጠነክር አብራው ቆየች። በመሃል ከሱ ተለይቼ መኖር አልቻልኩም ብላ መልሳ ገጠር ወሰደችው። ከተማ ለምዶ ገጠር አልስማማ አለው። ድጋሚ ይዛው ከተማ መጣች። ቀድሞ የነበረው ወዙ የገጠሩ አየር አሟጦት ነበር… በመጨረሻም ለእናቷ ጥላው ሄደች። ህፃኑም በአያቱ ማደጉን ቀጠለ። ህፃኑ ማን እንደሆነ ልንገርህ? እኔው ነኝ። በአያቴ እጅ ማደግ እጣ ፈንታዬ የሆነበትን መንስኤ አሁን የገባህ? ይመስለኛል!!
ወገሬት!!   

ኢቲቪና ሙዓመር ጋዳፊ

"ኢቲቪና ጋዳፊ"

  ኢቲቪ ድሮም ለኢትዮጲያ ህዝብ አልተፈጠረም። ቶምሰን በተባለ የእንግሊዝ ድርጅት አገዛ በ1957 ጋዳፊና የወቅቱ አንባገነኖች ደስ እንዲላቸው ሲባል ክቡርነታቸው የአፍሪካ አንድነትን ለማድመቅ ሲሉ ወለዱት። እድሜ ለጃ!። ይኸው ኢቲቪ ከጋዳፊ እኩል ኢትዮጲያን ላለፉት አርባ ምናምን አመታት የሙጥኝ እንዳለ አለ።

   አንድ ተውኔት መድረክ ላይ ሲተወን ትያትር ይባላል። ተውኔቱ ደጅ ተቀርፆ በሲኒማ ቤትና በቴሌቪዥን ስታየው ፊልም ተብሎ ይጠራል። አንድ ደረቅ ኘሮፖጋንዳ ባላዋቂ ጋዜጠኛ ወይም በአዋቂ "ዋሽቶ አደር" በሰፊ ብራና ሲፃፍ "አዲስ ዘመን" ይባላል። ያው! ፕሮፖጋንዳ ጥሩ የትወና ብቃት ባላቸው ጋዘጠኞች ተቀርፆ ሲቀርብ "ኢቲቪ" ተብሎ  ይጠራል።"ኢቲቪ"ና "አዲስ ዘመን" የእድሜ ዘመናቸው ረጅም ነው። ሁለቱም እድሜ ያጎበጣቸው አዛውንቶች ናቸው፣ ተከብረው ግን አያውቁም።

"አዲስ ዘመን" ሞኝ ሰውነት ስላለው ኩሸት ሲበዛበት ዝም ብሎ ወደ ጎን ይለጠጣል። በአንፃሩ ኢቲቪ ውሸትና ኩሸት እያሸማቀቀው በየቀኑ ይከሳል። ስንት ዲያስፖራዎች 21‘ ኢንች ቲቪ እየገዙ ወደ አሜሪካና አውሮፖ ሄደው አመት ቆይተው ሲመለሱ የገዙት ቲቪ 14’ ኢንች ሆኖ ጠበቃቸው መሰለህ።ይህ ነገር ቀልድ ሆኖ ይወራል እንጂ የየቤቱ እውነት ነው። ብዙ የኢትዮጲያ ቲቪዎች በውሸት እየተሸማቀቁ ከስተዋል። ተመሳሳይ የበሽታው ምልክቶችም በአስመራ ቲቪዎችም ላይ ይስተዋላል።

ዕድሜዬ እየገፋ ነው። የኢቲቪን ውለታ ዛሬም ድረስ አልረሳውም። በአባባ ተስፋዬ ተረቶች መልካም ስብዕናን እንድገነባ ረድቶኛል፣ አዝናንቶኛል፣ በአፍሪካ ዋንጫዎች አስቦርቆኛል። ማራዶና የተባለ የኳስ ንጉስ እንዳለ አሳይቶኛል። ጥላሁን ገሠሠ የሚባል የሙዚቃ ንጉስ ተስረቅራቂ ድምፁን አሰምቶኛል፣ እንባውን ሳይቀር አሳይቶኛል። ማይክል ጃክሰንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየኝ ኢቲቪ ነው። አለምን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት በኢቲቪ መሆኑን መቼም አልክድም። ኢቲቪ በሁሉም መልኩ አሳድጎኛል። ለዚህም አመሰግነዋለው።

  ኢቲቪ በልጅነቴ አይንና ጆሮዬ ነበር። አሁን አይንና ጆሮዬ በገዛ አገሬ በይፋ ታሽገውብኛል። ይህ የእኔ አቻ ትውልዶች ሁሉ የሚጋሩት ሀቅ ነው። እንዲያውም የኢቲቪ ውሸት ያንገሸገሻቸው ወጣቶች በማህበራዊ ድህረገፅ "I HATE ETV" የሚባል የፌስቡክ ቡድን አስከማቋቋም ደርሰዋል። ይህ ንቅናቄ… በርካታ አባላት አሉት። የአገሪቱ ዝነኛ ሰዎችም በዚህ ድህረ ገፅ ኢቲቪ እንዳንገሸገሻቸው ይናገራሉ። አንድ ወጣት በዚህ የማህበረሰብ ድህረ ገፅ ላይ እንዲህ ፅፎ አነበብኩ "ኢቲቪ እናት ኢትዮጲያ ላይ ያለ ትልቅ እባጭ ኾኖ ይሰማኛል"
ኢቲቪ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ይዋል!!
ረጅም እድሜ እንዲህ በነፃነት እንድንፅፍ ላበቃን ህገ መንግስታችን!
ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር!!

ምንጭ– ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ በመሀመድ ሰልማን

ጥቁር ሳምንት

"ጥቁር ሳምንት"
#ሳteናw

  በመሀል መርካቶ ልዩ ስሙ ስጋተራ ከቀኑ 8:30 ላይ ከፍተኛ የከባድ መኪና ግጭት ካለንበት የድብርት ሁኔታ አነቃን። ወዲያው የሰዎች የኡኡታ ድምፅ ተከተለ። በፍጥነት ወደ ጩኸቱና ግጭቱ ስፍራ ሮጠን ሄድን። አንድ fsr isuzu  ከአንድ ሱቅ ግንብ ጋር ተላትሞ ደረስን። በግንቡና በመኪናው መካከል ባለው ሰው በማያቆም ክፍተት ቅርፁን የቀየረ የራስ ቅል ተመለከትኩ። የመኪናው ስኮርት ሹፌር በግርግሩ አምልጦ ስለነበር ተጯጩኸን መኪናውን በሌላ ሹፌር ከተጣበቀበት ግንብ  ወደኋላ ተመለሰ። የተገጨው ሰው በደም ተጨማልቆ ግንቡ  እምደተጣበቀ ተንሸራቶ መሬት ላይ ወደቀ። ግራ አይኑ ጉድጓዷን ለቃ በያዛት ጅማት ጉንጩ ላይ ተንጠለጠለች። የቀኝ እጁ ሌባ ጣት እንደተቀሰረች ቀርታለች(የአምላክን አንድነት መስክሮ) ሸሃዳ ይዞ። እንደዚህ አይነት ዘግናኝ ግጭት ስመለከት የመጀመሪያዬ ስለነበር በድንጋጤ ደርቄ ቀረው። በግጭቱ ሳቢያ የፊቱ ቅርፅ በመበላሸቱ ማንነቱን  ለመለየት ደቂቃዎች ወሰዱብን። ከመኪናው ግጭት በተአምር ማን ገፍትሮ እናዳወጣት ለራሷ አጃዒብ የሆነባት ሻይ አፍልታ የምትሸጥ ልጅ በእጇ አረንጓዴ ጆግ ይዛ… በድንጋጤ አይኗ ፈጦ  ቆማለች… የተገጨው ሰው ማን እንደሆነ ብንጠይቃት ለመመለስ አንደበቷ ተሳስሮ ቃላት ከዷት…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
   ከቀኑ 7:00 ሰዓት እንደሁሌውም መርካቶ ስጋ ተራ ወደ ክፍለ ሀገር ሸቀጥ በሚጭኑ ከባድ መኪናዎች ተሞልታለች። ተራ አስካባሪዎቹ መኪናዎቹን እያሸጋሸጉ ለማብቃቃት በመዋከብ ላይ ናቸው። ከመኪናው መብዛት በተቃራኒ በሰፈሩ እንደ ወደብ መጫንና ማውረድ እንጂ ግብይቱ ከጎረቤት ተራዎች በመሆኑ የስጋተራ ልጆች የበይ ተመልካች ሆነናል። እኔም በበኩሌ የስራው አለመኖር እያበሳጨኝ እያማረርኩ ስብስብ ብለን ተቀምጠናል። በመርካቶ ምድር ስራ ፈትተን ለመቀመጥ ያበቃን የስራው አለመኖር መሆኑን ሳልነግርህ የምትረዳው ሀቅ ነው። በዛ ላይ ቀኑ ከወትሮው በተለየ ድብት ይላል። የመርካቶ ማህበረሰብ አባላችን ሙሂዲን ከስብስባችን መጥቶ፣ የኛም ስሜት የሆነውን የቀነኑ መክበድ ገልፆልንና አብሽሩ ብሎን ሄደ። ሙሂዲን በባህሪው የምትወደው አይነት ፀባይ ያለው ልጅ ነው። ሰላምታውና ለሰው ያለው መተናነስ በማህበረሰቡ የሚወደስበት ባህሪ የተላበሰ በሀይማኖቱ የጠነከረ እድሜው አርባ የሚጠጋ ጅመር ጎልማሳ ነው። ባለትዳርና የልጆች አባት ነው ሙሂዲን። ከኔ ጋር አንድ አይነት የስራ ፊልድ የምንሰራ ሲሆን በስራ አጋጣሚ የረጅም ጊዜ ደንበኛውን አስኮብልዬበት ነበር። የሚገርመው ሙሂዲን ይህን ባደርግም ሰላምታውን አላቆመም። እኔ ወይ ይወቅሰኛል ወይ ያኮርፈኛል ብዬ ብጠብቅም የሱ ተቃራኒ ሆነ። በፍቅር አሸነፈኝ። ድርጊቱ የህሊና ጫና አሳደረብኝና ያን ነጋዴውን በዘዴ ወደሱ እንዲመለስ አደረኩ። … ሙሂዲን ከተለየን ቡሃላ ስብስቡ ስለሱ ያለውን እውነታ ያወራ ጀመር። ወደ ጆሮዬ ከደረሱ መረጃዎች ውስጥ የሚከተሉት ነበሩ።
"እኔ ሀያ አመት ይሆነኛል እሱን ሳውቅ አንድ ቀን ክፉ ሲናገር ሰምቼው የማላውቅ ሰው ቢኖር ሙሄ ነው።"
"ለነኸይሬ ዘመድ ነው አይደል? "
"አረ አይደለም፣ እሱ እንደውም ድሮ ክርስቲያን ነበር ሰልሞ ነው እንደውም ስሙ ጌቾ ነበር።"
"ሰልሞ ነው እንደዛ ከከመስጊድ ሰላት የማይታጣው? ይገርማል!!
"አዎ ሰሞኑን እናቱን ዘይሮ እንደመጣ ነግሮኛል! ሚስቱም ከረጅም አመት የውጪ ሀገር ቆይታ ቡሃላ ነው የመጣችው አሁን እንደውም አራስ ነች አሉ"።
ሙሂዲንን አሰሪዎቹ በጣም ያቀርቡታ ይወዱታል። እንኳን እነሱ በሩቁ የምናውቀው እና እንኳ በትህትናው በፀባዩ እናከብረዋለን እንወደዋለን።

ሙሂዲን ከምሳ በፊት አንድ የክፍለ ሃገር ነጋዴ በአደራ  መልክ ለነጋዴዎች እንዲከፍልለት የላከለትን ብር በአደራው መሰረት አከፋፍሎ ከጨረሰ ቡሃላ ከአሰሪዎቹ ጋር ምሳውንእየበላ "የማን እንደሆነ ያል ተገለፀለት  ትርፍ መቶ ሃያ ብር ኪሱ ውስጥ ማግኘቱን ለአሰሪዎቹ ተናገረ። ለማንኛውም ለብቻው ይቀመጥ ብሎ ከደረት ኪሱ እያዩት አስቀመጠውና "ዘንድሮ እኔንጃ መርሳት አብዝቻለው" የሚል ቃል ከአንደበቱ ወጣ። በጊዜው ይህቺ ቃሉን ማንም ልብ አላለውም። ሙሂዲን ምሳውን በልቶ ከጨረሰ ቡሃላ እጁን ሊታጠብ ከሱቁ ግንብ ስር ሻይ አፍታ ከምትሸጠው ልጅ ጋር ሄደ። ስላልነበረች እቃዋን ላላመንካት ቆሞ ይጠብቃታል። ከቆመበት ትይዩ ከግንቡ ፊትለፊት የቆመውን fsr isuzu መኪና ተራ አስከባሪው ቦታ ለማሸጋሸግ ሾፌሩን ፈልጎ አጣውና ስኮርት ሾፌሩን እንዲያስጠጋው አዘዘው። ሙሂዲን ሻይ አፍይዋ ስትመጣ የእጅ ውሃ እንድትሰጠው ጠይቋት እሱ አንዳጎነበሰ በያዘችው አረንጓዴ ጆግ እጁን ታስታጥበው ጀመር… በተራ አስከባሪው ትዕዛዝ ተዋክቦ ስኮሩት ሾፌሩ ልብ ሳይል አንደኛ ማርሽ ላይ እንዳለ ሞተሩን አስነሳው። መኪናው ዘሎ ከፊት ለፊቱ ካለው የሱቅ ግንብ ጋር ተላተመ …ጓ!  የሙሂዲን እስትንፋስ ከዚህች ቅፅበት ቡሃላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆመች። ኢናሊላሂ ወኢና አለይሂ ራጂዑን።

በቃ የኛው ነገር ይሄው ነው። እንደ እንቁላል መች ፍርጥ እንደምንል አናውቅ፣  መች እንደምለያት ለማናውቃት ምድር መንገብገብ፣ መበላላትት፣በበነነ ተነነው ማማረራችን፣ በቃ ለዚሁ ነው። እስኪ እውነቱን እናውራ አሁን ባለንበት ባህሪያችን ሁኔታ ብንሞት እንወዳለን?  በጭራሽ!! ይኸው 7:00 ሰአት ላይ ጥሩነቱን ያወራንለት ሙሂዲን 8:300 ላይ ከምድርን ተለየ። ለመሆኑ  እኛ እንደሱ በመልካም የሚመሰከርልን ስራ ሰርተናልን? መች እንደምንሞት አናውቅምና … የምንለወጥበትን መንገድ እሱው ያግራልን። መጨረሻችንን ያሳምርልን፣በመካከላችን ፍቅርንም ይስጠን ለሟቹም ጀነተል ፍርደውስ ይወፍቀው። አሚን!! በሚል ፀሎት ያሳለፍነውን ጥቁር ሳምንት እንማርበት ዘንድ መልዕክቴን አስተላልፋለው።
ወገሬት!! 

ፈዋሽ ስም

"ፈዋሽ… ስም"
#ሳteናw

… ባልንጀራችሁ እንዲፈወስ ከፈለጋችሁ ትዕዛዜን በጥሞና አድምጡ። የማዛችሁን ሳታዛንፉ ፈፅሙ። የዚህ ሰው ፈውስ ከምትጠሉት ሰው ስም ጋር የተቆራኘ በመሆኑ አንድ ሺህ ጊዜ  ስሙን ጠርታችሁ በስኒው ውሃ ላይ እንትፍ ትሉበታላችሁ… በዚህ ከተስማማን ህክምናዬን መጀመር እችላለው…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  የጎንደር ትልቁ ገበያ ቅዳሜ ገበያ ይባላል። ከገበያው ጎን አንድ መስጂድ ይገኛል። ከመስጂዱ ጀርባ የኛ ሰፈርነው። አካባቢው በሙሉ ቅዳሜ ገበያ በሚል ይታወቃል። የኛ ሰፈር ደግሞ በተለየ ሁኔታ የሸህ ለጋስ መንደር ትባላለች።

  ሼህ ለጋስ የአባቴ አባት ናቸው። በ1905 ዓ/ል ሸህ ለጋስ ጫካ መንጥረው ከአካባቢው መስፈራቸውን አባቴ ሲያወራ ሰምቸዋለው። ሲበዛ ጀግና ነበሩ። በራሳቸው ስልት ለእስልምና ሰርተዋል በዛላይ ዓሊምና የባህል ሕክምና አዋቂ ናቸው። ይህን ክህሎታቸውን እስልምናን ለማገልገል ተጠቅመውበታል። በዚህ ረገድ በርካታ ታሪኮች ይነገሩላቸዋል።

  አንድ ቀን በጎንደር ታዋቂ የሆነ ቄስ በእባብ ተነድፎ ለሕክምና ከሳቸው ዘንድ መጣ። የጎንደር ቀሳውስት እስልምናን እንደሚጠየፉ ሸሁ ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተለይ መሀመድ (ሰዐወ) የሚለውን ስም በጭራሽ መስማት እንደማይፈልጉ። ሸሁ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ቄሱን ለህክምና ይዘው የመጡ ቀሳውስትን ነቢዩን ስም እንዲጠሩ ፈለጉ። ውሃ በሲኒ አቀረቡና ባልንጀራችሁ እንዲፈወስ ከፈለጋችሁ ትዕዛዜን በጥሞና አድምጡ የማዛችሁን ሳታዛንፉ ፈፅሙ። የዚህ ሰው ፈውስ ከነቢዩ ሙሐመድ(ሰዐወ)ስም ጋር የተቆራኘ በመሆኑ አንድ ሺህ ጊዜ የነቢዩን (ሰዐወ) ስሙን ጠርታችሁ በስኒው ውሃ ላይ እንትፍ ትሉበታላችሁ ፣ ሲጠጣው ይድናል፣ አሏቸው።

   ትዕዛዙ ለቀሳውስቱ መርዶ ነበር። አንድ ጊዜ መስማት የማይፈልጉትን ስም አንድሺህ ጊዜ በአንደበታቸው መጥራትና ማውሳት ከባድ ነበር። በሽተኛው ወዳጃቸው ይንገበገባል በስቃይ ይጮኻል። የሚመርጡት ቸገራቸው። የሸሁን ትዕዛዝ ባይፈፅሙ እንዲሞት የማይፈልጉት ቄሳቸው መሞቱ ነው። እየረራቸውም ቢሆን ሀላፍትናውን ተቀበሉ። መቁጠሪያውን ተቀብለው አንድሺህ ጊዜ የአሽረፈል ኸልቅን ስም አወሱ። በስኒው ላይ እንተፍ አሉበት። ሸህ ለጋስ መድሀኒቱን ከውሃው ጋር ሰጡተ። በሽተኛው ተፈወሰ። በመጨረሻም ሸህ ለጋስ ለቀሳውስቱ የሚከተለውን መልዕክት አስተላለፉ። "ወዳጃችሁ የዳነው በነቢዩ ሙሀመድና በሳቸው ጌታ በረከት ነው።"
ሸህ ለጋስ በርካታ አስታማሪ ታሪኮችን ሰርተዋል። ገድላቸው ብቻ ራሱን የቻለ ጥናት ይፈልጋል። ምንጭ የለውጥ ቡቃያ (ከሀሰን ታጁ ግለ ታሪክ መፅሀፍ)
ሰሉ አለን ነቢይ!! (ሰዐወ)
ወገሬት!!

የስራ አቦጊዳ

"የስራ …  አቡጊዳ…"
#ሳteናw

…በማዕከአዊ ስታቲስቲክ ባለስልጣን ትመና መሰረት ሀዋሳ የ119,623 ሰው መኖሪያ ስትሆን ከነሱም ውስጥ 60,378 ወንዶች 59,245 ሴቶች ሆነው ተተምነዋል።

… በኔ ግምታዊ ትመና መሰረት 25 ሺህ የሚሆኑት ጥርሳቸው ቡኒ ሲሆን 35 ሺህ የሚሆኑ የአዋሳ ቺኮች የሰውነት ቅርፃቸው ውብ ነው…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

   የአዲስ አበባው የገና ባዛር አለቀ። ቀጥሎ በአዋሳ የሚደረገው ባዛር በነበረን እቃ ላይ አንዳንድ እቃዎችን ጨምረን ወደ ደቡብ ኢትዮጲያ ርዕሰ ከተማ ሀዋሳ ነካነው። … በአዲስ አበባው ባዛር እንደኛው ባዛር ከሚሳተፉ ሰዎች ተግባብተን ስለነበር በአዋሳው ባዛር ላይ ዳግም ስንገናኝ በደንብ ተላምደን ደስ የሚል ህብረት ፈጥረን አሳልፈናል። አዋሳ ትርፋማ በሚያሰኝ ሁኔታ ባንሰራም አንዳንድ አዝናኝ ገጠመኞች አሳለፍንባት።

(በነገሬ ላይ አዋሳ ከ1998 ቡሃላ፣ ጠንካራ እድገት ያሳየች ቢሆንም፣ ስያሜዋ በንባብ ላልቶ ሀዋሳ ሆኗል። ሀዋሳ በሲዳምኛ ትልቅ ሀይቅ የሚል አቻ ትርጉም አለው።)

  ለአይኔ አዲስ ያልሆነችው አዋሳ ከዚህ ቀደም ከማውቃት የበለጠ ውብ ሆና ጠበቀችኝ። ከጥቂት አመት በፊት አሸዋማ የነበረው ውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ በኮብል ስቶን ተቀውጠዋል።(ኮብል ስቶኑን ያያሁት በባዛሩ ይሁን ከዛ ቡሃላ በሄድኩበት አጋጣሚ አርግጠኛ እይደለሁም) ብቻ የመልከዓ ምድሯ አቀማመጥ ለጥ ያለ ሜዳ የሆነችው የደቡቧ ፈርጥ  ከኮብል ስቶን ጋር በደንብ ማች አድርጋለች።

  አዋሳ ከራስጌዋ የታቦር ተራራ ከግርጌዋ ከተንጣለለው ሀይቋ ጋር በየጎዳናው መሀል የተተከሉ ዘንባባዎቿ እና  የኮረዳዎቿ ውብ የሰውነት ቅርፅ ጋር ተደማምሮ እውነትም ውብ ምድር ያስብላታል። ሌላው ደግሞ አዋሳ ከተማ ተወላጆችን፣ በመመልከት ብቻ የምትለይበትን መለያ ከተማዋ ችራቸዋለች። ጥርሳቸው፣ ሳይቅሙ ሳየጨሱበት ወደ ቡኒነት ተቀይሯል። ተወልዶ ያደገባቸውን ሰው እንደዚህ አይነት መለያ ከቸሩ ከተሞች ሌላኛዋ ናዝሬት ነች። መንሴውም በድሮ ጊዜ ለመጠጥ የሚውለው ውሃቸው ነው አሉ። አሉ ነው፣ አሉባልታ። በመርካቶ ጥርስ የሚያበላሹት ነገሮች… ጣፋጭ ነገሮች ፣ጫት መቃም፣ ሲጋራማጨስ እና፣ ከባድ ቦክስ፣ ናቸው። በማዕከአዊ ስታቲስቲክ ባለስልጣን ትመና መሰረት ሀዋሳ የ119,623 ሰው መኖሪያ ስትሆን ከነሱም ውስጥ 60,378 ወንዶች 59,245 ሴቶች ሆነው ተተምነዋል። በኔ ግምታዊ ትመና መሰረት ሀምሳ ሺህ የሚሆኑት ጥርሳቸው ቡኒ ነው። ሀምሳ ሺህ የሚሆኑ የአዋሳ ሴቶች የሰውነት ቅርፃቸው ውብ ነው። ከአዋሳ ከሚገርሙኝ ነገሮች አንዱ የሔዋንያን ቅርፅ ነው። በለው! ምንድንው ቆይ ቅርፃቸውን እንዲህ አሳ ያስመሰለው፣ ለአሳ ቅርብ ስለሆኑ ይሆን? ከየትኛውም ከተማ አይን የሚንከራትት ቅርፅ ያለው አዋሳ ነው። ወጣቱ ብቻ መሰለህ?  እነማሚም ጭምር ፍዴያቸው አስማት ነው። በአብዛኛው ጋቢናቸው ግን እንደኋላቸው አይደለም። … በአዋሳው ባዛር ከታዘብኳቸው ነገሮች ጥርሳቸውና፣ ሼፓቸው ነው።
ገጠመኝ ①
  በአንዱ ቀን ይህ ሆነ። በአዲስ አበባ ባዛር ላይ የተግባባነው አንድ ልጅ፣ በሀዋሳ ምሽት በፒያሳ… ስንዛዟር ከሩቅ ሼፗ የሚመስጥ ሴት ተመልክተን ስናደንቅ በመሃል ልጁ አፏጨላት። ሰምታው ስትዞር። በእጁ ነይ ብሎ ጠራት። አላቅማማችም ወላ አልተሽኮረመመችም መጣች። መምጣቷስ ባክከፋ!! ስትመጣ ከሩቅ በተመለከትነውና ከገመትነው ወጣትነቷ ላይ ሰላሳ አመት የጨመረች ሆና መምጣቷ ነበር።
"አቤየት!!" ብላ በምልክት ወደ ጠራት ጓደኛችን አፈጠጠች፣ማለቴ አፈጠጡ። እሳቸው ልበል እንጂ አንቺማ ክብራቸውን ማሳነስ ነው። ለነገሩ እሜትዬ እራሳቸው ናቸው  ክብራቸውን በአለባበሳቸው ያሳነሱት። (እንዲህ አይነት እምቢ አላረጅም አለባበስ በአዲስ አበባም ይታያል። እድሜ ከሄደ ቡሃላ ማጌጥ መልበስ አግባብ አይደለም ሳይሆን፣ እድሜን ያገናዘበና በወጉ ቢሆን ስታይል አለው።) ሴትየዋ አቤት ሲሉ መጡ…  ጠሪው ጓደኛችን የሚለው ቢጨንቅ ቢጠበው፣

"ታደሰ ኢንጆሪ ሆቴል፣ እግሬ እስኪቀጥን ብፈልግ ብፈልግ አጣሁት… ብሎ በሩ ላይ የቆመበትበትን ታደሰ እንጆሪ ሆቴል ቦታውን ጠየቃቸው…

"ይኸው" ብለው አጠገቡ ያለውን ሆቴል አሳዩት።

"ውይ ይቅርታ ልብ አላልኩትም ነበር።"ብሎ ተንተባተበና መለሰ። ሴትየዋ ብትፋታንም… ለተወሰነ ቀን የሳቅ ምንጭ ሆነ ጀለሱካችን።

ገጠመኝ ②

ከስራ ቡሃላ ማታውን እኛ ወደ አልጋ በጊዜ ገብተን እንተኛለን። አሰሪያችን በሁለተኛው የሌሊት አጋማሽ ሽርብትን ብሎ በተኛንበት ይገባል። ይህ ሁኔታ አንድ ሁለት ቀን ሲደጋገም አብሮኝ ከሚሰራው ልጅ ጋር እኛስ ከማን እናንሳለን? ግፋ ቢል ከደሞዛችን ቢቆረጥ ነው ብለን ከተኛንበት ተነስተን ወደ ከተማ ነካነው። የሂሳብ ብር እኔ እጅ ላይ ቢሆንም በራሳችን ብር ከአንድ መቃሚያ ቤት ገብተን ምርቅን ምንቅር ስንል አምሽተን ወጣን። ሁለታችንም ፍሬሽ ቀመቴዎች (ለጫት አዲስ) ስለነበርን ምርቃናው ጉድ ሰራን ጓደኛዬና እኔ መንገድ ላይ ለሽንት ቆምን።
ከቆምንበት ስፍራ ትይዩ፣ አንድ ጨለማ ቅያስ ነበር። ጀለስካ
በመሃል አንዳች ነገር ከጨለማው ውስጥ አየና…

"አየሃቸው እዛጋ ኪስ እየተደራረጉ ነው?" አለኝ።

"አረ! የታሉ?" አልኩት።

"ይኸው" ብሎ አንድ ፅልመት የዋጠውን ቅያስ ጠቆመኝ።

   ቅያሱ ሙሉ በሙሉ ጨለማ ሲሆኑ ከጀርባው የሚያቋርጠው መንገድ ፏ ያለ ብርሃን ነበር። ልክ ሲኒማ ቤት ቤት በለው ቅያሱን!! ተቀምጠህ ፊልም እየሾፈተርክ ከስክሪኑ አንፃር የሚንቀሳቀስ ሰው ስትመለከት ቅርፁን ብቻ እንደምትመለከው ነገር ነበር፣ ያየውን… ተቃቅፈዋል ብሎ ከግምት፣ ይሁን ከሽፍደት… 

"ያው አይታዩህም?"

"አው አው አንተ… አልኩት"። የሚሳሳሙ ሰዎች ይሁን የተቃቀፉ በእርግጠኛ አይደለሁም ብቻ ጥቁርና ሰፊ የተቃቀፉ የሚመስሉ ሰዎች ወደኛ እያዘገሙ ይቀርባሉ። ቆይ ተደብቀን እንያቸው ተባብለን። እኛ ወዳለንበት ብርሃን እስኪደርሱ ቆመን መጠበቅ ጀመርን። "ቆሙ!!" እየተሳሳሙ መሆን አለበት። አዎ አልኩት እርግጠኛ ባልሆንም። የማይደርስ የለም ወደ ብርሃኑ ደረሱ…።  ምን ዋጋ አለው እስካሁን የሚሳሳሙ ሰዎች ናቸው ብለን የጠበቅነው ጥቁሩ ነገር … ባለቤቱ የጣለውና እከክ የወረሰው ግድንግድ ፈረስ ሆኖ አረፈው። በራሳችን እየሳቅን የተደበቅንበትን ስፍራ ለቀን ጉዟችንን ቀጠልን። አለቃችን  ሳይቀድመን ቀድመን ወደ ማረፊያችን ደረስን። ፈጣሪ ሲረዳን ልክ እንደገባን መጣ። ሌላ ቀን በእንቅልፍ አቅላችንን ስተን የሚያገኘን ሰውዬ… በምርቃና ፈጠን አገኘን። እስካሁን አልተኛችሁም? … አዎ። ቢጠረጥረንም ዝሎ ስለመጣ ዘሎ አልጋውላይ ወጥቶ  ዝም ብሎን ተኛ። በማግስቱ ጠዋት አርፍደን ሲያየን ጥርጣሬው አደገ። አሁንም ምንም አላለም።
ባማግስቱ በአዋሳው ባዛር የቀኑን ስራ ጨርሰን ወደ አልቤርጎ እንደሚሄድ ሆነን… ወደ አንድ ባር ነካነው። ገባን። ብልጭ ድርግም እያለ አይን ከሚያጭበረብረው ዲም ላይት ጋር ተጨማምሮ የሙዚቃው ድምፅም ናላ ያዞራል። አዛ ፈሳሽ አየለበለብን ሳለ አሰሪያችን 4:00 ላይ በኔ ሞባይል ደወለ። "ወይኔ ደወለ"። አልኩት ለስራ ባልደረባዬ። አታንሳው አለኝ። ማንሳት ብፈልግስ በዛ ጩኸት እንዴት ላንሳው። ሳላነሳ ዝም አልኩት። ቆይቶ ደግሞ ደወለ። ባሩን ለቅቄ ድምፅ ወደማይሰማበት ስፍራ እሮጥኩ ወጣው። የባሩ አስተናጋጅ ሂሳብ ሳልከፍል የማመልጥ መስሎት ከኋላዬ ሊከተለኝ ሲል… ሰዒድ ይዞ ሁኔታውን ነገረውና ተመለሰ። ፀጥ ያለ ስፍራ ብደርስም የሙዚቃው ድምፅ የሌሊቱን ፀጥታ ሰንጥቆ በስሱ ያስተጋባል። አነሳሁት።
"ሀሎ"
"ሄለው የት ናችሁ ?"
"እ… አዛው ማለት ኳስ አያየን?"(በጊዜው የአፍሪካ ዋንጫ ይካሄድ ነበር።)
"የማንና የማንን" መስቀለኛ ጥያቄ መሆኗ ነው።
"ሴኔጋል ከኮትዲቯር" አልኩ አፌ እንዳመጣልኝ።
"ነው? እሺ መጣው ብሎ!" ስልኩን ዘጋ። ሮጬ ወደ ባሩ ተመለስሁና። ጓዴን ጠርቼ ና ቶሎ ውጣ ወደ ቤርጎ እየሄደ ነው ብዬው ሂሳባችንን ዘግተን እየተጣደፍን ወጣን። በስልክ ያወራነውን ነገርኩት።
"ጨወታዉ የማንና የማን አልከው?"
"ሴኔጋል ከኮትዲቯር"
"ወይኔ የሴኔጋል ጨዋታ እኮ 1:00 ላይ ነበር የታየው!! ይህን ያውቃል እኮ።)
"በቃ ተደገመ እንለዋለና" ልለው አልኩና ድንጋጤያችን ስላየለ ትቼው… እንደ ማራቶን ተወዳዳሪ ጭር ባለው የአዋሳ አውራ ጎዳና ሳምባችን እስኪፈነዳ መሮጥ ያዝን አልቤርጎ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረሰን። አሰሪያችን ደመቅ ደመቅመቅ ብሎ ኮንትራት በያዛት ባጃጅ ደረሰብን።
"እ! ሴኔጋል ብሎ በዛ ብራቅ ድምፁ ፀጥታ በነገሰባት የአዋሳ ምድር አንባረቀ። ቁና ቁና እየተነፈስን በድንሆነን ቀጥ አልን። "ወይኔ ገንዘቤ! ወይኔ ገንዘቤ! ብሎ ከልቡ ያልሆነ ኡኡታውን አስነካው።" እኛ ምንም አላደረግንም ብለን ምለን ተገዝተን ልናሳምነው ብንሞክርም ሊያምነን አልቻለም። ጥንድ አልጋ ባላት ቤርጎአችን ገባን። እንደገባን ወቀሰዋን ጀመረ "ሰላም ልጅ ነህ ብዬ! ምንም አታውቅም ብዬ ካሼር ባደርግህ ሮንድ ትዞርልኛለህ?  ለነገሩ ማን ይህን ሀሳብ እንዳነሳው አውቃለው። ብሎ ወደ ጓዴ አየ።
"አረ እኔ አይደለሁም" ሲል ታሱን ተከላከለ። "ዝም በል አንት አይነ ደረቅ፣አላውቀህ መስሎሃል  የአብነት ወሮ በላ፣የአብነት አይን ቀርጥፎ የበላህ ዝም በል መልስ እንዳትሰጠኝ። ሰኢድ አያጉረመረመ አንገቱን ደፋ። ከብዙ ወቀሳ ቡሃላ አለቃችን ደክሞት ሲተኛ። እኛም ተኛን። ምስኪን ነው። በማግስቱ ግን የምሽቱን ሁኔታ ረስቶት ዋለ። ምሽቱን ወደ ቤርጎ ልንሄድ ስንል አብረን ነው ምንሄደው ጠብቁኝ አለን። ቤርጎ እጃችንን ይዞ ሊያስገባን ነው ብለን ብንገምትም ልክ አልነበርንም። ምርጥ የፍየል ጥብስ እራት ጋበዘን።

   አዋሳ ምድር የክርስቲያና የሙስሊም ልኳንዳዎች ልየነታቸው ላይ ብዙም ትኩረት አይደርጉም። ለምን? ብዬ ስጠይቅ አብዛኛው የከተማው ነዋሪ የኘሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆኑ ነበር። ከእራቱ ቡሃላ አንድ ባር ይዞን ገባ። በቃ ከኔ ጋር ይዝናኑ ብሎ ነው ብለን አሰብን። የባሩ እስተናጋጅ መጣ። "አለቃ ቀድሞ ለኔ አንድ ጉዳዩና ለነሱ ሁለት ሚሪንዳ!" ሲል አዘዘ። እኔና ጓዴ ዞረን በግርምት አየነው? ምናባህ ታፈጣለህ? ልትጠ አማረህ ደረቅ!" ሲለን ለንቦጫችንን ዘረገፍን። አለቃ ባላየ ላሽ። ሚሪንዳረውን ስንጨርስ ሌላ ደግሞ ለኛም ድጋሚ ሚሪንዳ።"እንደ አራስ ሚሪንዳ ላይ በላይ አስግቶን ከባሩ ወጣን። ወደ አልቤርጎ ስንሄድ ሆዳችን እየተንበጫበጨ እንደ ውሻ በየ እርምጃው ለሽንት እየቆምን ደርሰን ገባን።

   በአዋሳ መስቀል አደበባይ በተባለው ቦታ ላይ በሸራ እንደ  በተሰራልን አዳራሽ ውስጥ ፣ በትንንሹ የተከፋፈሉ ጊዜያዊ የባዛር ሱቅ ከአዋሳ ሐሩር የአየር ፀባይ ጋር በሙቀት ተቀቅሎ መዋሉ ከባድ ነበር። ሙቀቱ በኛ በወንዶች ላይ ተፅኖው ባይጎላም እንደኛው በሸራው ውስጥ  ታምቀው የሚውሉ ሴቶችን ለከፍተኛ ሽፍደት ዳረጋቸው። ወንዶች በምርቃና ሲፈዙ፣ ሴቶች  ሲወቀጡ ሲገቡ መቅበጥበጥ፣ ማስካካት መጯጯህ አበዙ። በተለይ ከአጠገባችን ሱቅ ለሽያጭ የተቀጠረች የጥቁር ቆንጆ፣ ከኔ ጋር ተላምዳ ወደ መደብራችን ብቻዬን ስሆን ጠብቃ ከች በማለት ጀመረች። የሼፗን ቅርፅ የሚያጎሉ ልብሶች ለብሳ እየመጣች እግር አበዛች።የሰውነቷ ቅርፅ አስማት ነበር። አለ አደል ንካኝ ንካኝ እቀፈኝ እቀፈኝ የሚል ሰውነት። የመልኳን ጥቁረት የሰውነቷ ቅርፅ ደብቆታል። ነብሴ ለካ ሽፍዱ ብላ ኖሯል! እኔ መች አወኩ ባውቅም ለአቅመ  አዳም እንጂ ለአቅመ ድፍረት ገና ነበርኩ። የመርካቶ ልጅ በተለይ የኛ ሰፈር አብዛኛውን ጊዜ የሚገናኘው ከንግድ እንጂ ከቺክ ስላልሆነ ቶሎ ተላምዶ ደሽ ለማድረግ ጊዜ ይገድላል።  መቃለድ፣ መላፋት እንደ መጀመር አለች፣ ውይ ሙቀቱ እያለች ከላይ የለበሰችውን በአጠገቤ ሳታፍር ማውለቅ አበዛች። እኔ የአይን ሻወር ከመውሰድ ውጪ እጄን እንዳላነሳ እንዳልኩት ድፍረት አለነበረኝም በዛላይ እኔ የአዋሳ ስቄ ጫት ቅሜ በሁኔታዋ ስቄ ስቄ ዝም ብቻ ስላት፣ ከፊት ለፊታችን ያለው ባለ ሱቅ ሁኔታችንን ታዝቦ … ሰውነቱን አይተሽ ነው? ጩጬ እኮ ነው! ሲላት አንድ ቀን ሰማሁት። ከዛ በሁላ እሷም እግር ማብዛቷን አቆመች።"ይሄኔ ነበር የባነንኩት። ወይኔ ብዬ ተቆጨው። ምክኒያቱም ባዙሩ ወደ መቋጨቱ ነበር። ወደ አዲስ አበባ ተመለስን። ቀጣይ ጉዟችን ወደ ነቀምትና ጊምቢ ተጓዥ ባዛር ሆነ!…
ወገሬት!!

Saturday, August 20, 2016

አይ መርካቶ

አይ መርካቶ!

አገር ከየጎራው ወጥቶ
አንቺን ብሎ ነቅሎ መጥቶ
ግሣንግሱኘሡን ጓዙን ሞልቶ
ኅልቄ መሣፍርትሽ ፈልቶ
ባንቺ ባዝኖ ተንከራቶ
እንደባዘቶ ተባዝቶ
ተንጠራውዞ ዋትቶ ዋትቶ

አይ መርካቶ!

የምድር ዓለም የእንጀራ እናት
ላንዱ ርካሽ ለሌላው እሣት
ላንዱ ፍትሃት ላንዱ ምትሃት
ላንዱ ሲሳይ ላንዱ ፍርሃት
ላንዱ ተስፋ ላንዱ ስጋት
የግርግር የሆይታ ቋት

አይ መርካቶ!

ያንዱን ወስዶ ላንዱ ሰጥቶ
ያንዱን ገፍፎ ላንዱ አብልቶ
አንዱን ነስቶ ላንዱ አድልቶ
ስንቱን ፈርቶ ስንቱን ሸሽቶ
ባፈ ጮሌ ተሸልቶ

እይ መርካቶ!

ቢያዋጣ ወይ ባይዋጣ
ከስንቱ ተንጣጥቶ ጣጣ
ተነታርኮ ተገዛግዞ
ተብለጥልጦ ተበዛብዞ

መርካቶ ያገር ድግሱ
የገጠር ስንቅ አግበስብሱ
ለከተሜው ለአባ ከርሱ
በትሬንታው በአውቶብሱ
በቁሳቁስ ግሳንግሱ
ለቱጃር የጥጋብ ቅርሱ
ለኔ ቢጤው የቀን ጉርሱ
አባ መስጠት እጦት ቢሱ

አይ መርካቶ!

ተሻምቶ ተገበያይቶ
ወይ ተፈራርሶ ተጣልቶ
በእንካ ስላንቲያ ተማትቶ
አንዳንዴም ተፈነካክቶ
ተመራርቆ ተስማምቶ

አይ መርካቶ!

የኤስፔራንቶ ቋንቋ ሀገር
ያ ሲነገር ያ ሲሰበር
የስንቱ ልሳን ሲቀመር
ያንዱን ሲያከር ያንዱን ሲያቀር
ያንዱን ሲያውስ ያንዱን ሲያስቀር
ያ ሲደቀል ያ ሲፈጠር
የልሣን ሸማች ለብቻ
ከዕቃው ጭምር በስልቻ
ሲመዠርጥ እንደ ግቻ
ቶሎ በል ቶሎ በል ብቻ
ዝግ በሉ እማይባልበት
መርካቶ የአንደበት ፍላት
ግርግር እሚባልባት
ክርክር እሚሞቅባት
ደላላ እሚያውጅባት
ቸርቻሪ እሚተምባት
ሌባ ላብክን እሚያልብባት

አይ መርካቶ!

ላንዱ ምድር ላንዱ ጣራ
ያ ሲዘረፍ ያ ሲደራ
ያ ሲወስን ያ ሲፈራ
ያ ሲሸሽግ ያ ሲያወራ
የንግድ ጠፍ ወይ ያዝመራ
የነጋዴ ምጥ መከራ
የከበረ እንደመረዋ፣ረብጣ አፍኖት ሲያስገመገም
የከሰረ እንደ ፈላስፋ፣ በቁም ቅዠት ሲያልጎመጉም
የኔ ቢጤም ጠብሻ መቶት፣በየጥሻው ሲያስለመልም
ቸርቻሪ ዝርዝሩን ቋጥሮ፣ቅንጣቢውን ሲቃርም
የወር ሸማች ስንቁን ጭኖ፣ ሲመርቅና ሲረግም
ማጅራት መቺ ከጀርባው፣ ጥሻውን ዘሎ ሲያዘግም
ከዚህ በርሮ እዚያ ሰብሮ፣ ያዝ ሲባል ሲሸሽ ሲጣጣር ካማኑኤል ከራጉኤል፣ ሾልኮ ዶሮ ማነቂያ ዳር ከመስጊድ እስከበረንዳ፣ ከአራተኛ እስከ ነፍስይማር
የኡኡታው የጡሩንባው፣የጩኸቱ የፊሽካው ሳግ
የሰው የመኪና የከብት፣ የፍግ የቁሳቁስ ትንፋግ
ሲገፋተር ሲገሻለጥ፣ ላቦት ለላቦት ሲላላግ
ትንፋሽ ለትንፋሽ ሲማማግ
አባ ሽብሩ መርካቶ፣ ያለውን አጣጥቶ
የሌለውን ከሌለበት፣ እስጎልጉሎ አስወጥቶ
ስንቱን ከዳር ዳር አዛምቶ
በግድም በውድ አስማምቶ
አገር ካገር አካቶ
ሁሉን አቀፍ ባይ መርካቶ
ያቻችለዋል አሻምቶ
አይ መርካቶ!

ከክቡር ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን