Wednesday, February 1, 2017

"መሿለኪያና መሿለኪያዎች"

#ሳteናw

በወራሪው ጣሊያን በተመሰረተችውና በአፍሪካ ገላጣ ገበያነት ግንባር ቀደም በሆነችው መርካቶ ውስጥ…  ሁሉንም እንደ አቅሙ በማኖር የእናትነት ሚና ተጫዋች በሆነችው መርካቶ እንብርት ተመስርታለች …ማን?   ቀስ በል ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ!!

ኪስን ሳታይ እኔ ነኝ ያለውንም ቱጃር፣ ያጣ የነጣውንም  ጠብሻም በየደረጃው አብልታ አጠጥታ በምታሳድረው መርካቶ… ውስጥ… የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መዲና አዲስ አበባ የኢኮኖሚ ሞተሯ በሆነችው መርካቶ ክልል ትገኛለች… በመሀል አዲስ አበባ በ17 ካሬ የሰፈረች በመኖሪና በሱቆች የተጥለቀለቀች በሆነችው በእምዬ መርካቶ… ወጣት አባላቶቿን [መሿለኪያዎችን] በፍቅሯ፣ ሰብስባ፣ ውስጧ በሚሰፍነው፣ መረዳዳት ናፍቆት ጫሪ የሆነች አንድ ሰፍራ ነች … መሿለኪያ።
 
… ከዳርና እስከ ዳር በተገጠገጡ ንግድ ቤቶች መሀል ድንገት የምትገኝ፣ ጣራና ግድግዳዋም ድፍን የሆነች ዋሻ፣ በመሆኗ ነው መሿለኪያ የሚለው ስያሜ በአባላቿ የፀደቀላትም ናት መሿለኪያ።

መሿለኪያ ወጣት የነብር ጣት ለሆኑ የመርካቶ ወጣቶች መሰብሰቢያ፣ ደስታም ሀዘናቸውን፣ ማሳለፊያ፣ ቢያገኙም ቢያጡም፣ መዋያ። መወያያ፣ መማማሪያና፣ መረዳጃ ማዕከላቸው ናት።

  መሿለኪያዎች በተለያየ፣ የእድሜ፣ የእምነት፣ የገቢና የትዳር ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በጠቅላላ ወንዶች ናቸው። ከመሿለኪያ ጋር በያዛቸው ፍቅር ሰበብ፣ በአዘቦት ቀናት ከስራ ቡሃላ፣ በእረፍት ቀናት፣ በበዓላት ቀናት ሳይቀር፣ ከዋሻዋ አይጠፉም፣ በዚሁ ሳቢያ ለማህበራዊ ህይወት የሚሆን ትርፍ ጊዜ ባይኖራቸውም፣  ከማህበራዊ ኑሮ የወጡም፣ ቢሆንም ቅሉ በመሿለኪያ የራሳቸውን ማህበረሰብ መስርተዋል።  በመሰረቷት መሿለኪያ ውስጥ ያለው ግንኙነት ለሌላው ህብረተሰብ አርዓያ መሆን የሚችል የኢትዮጲያዊነት ስሜት ያለውና በህረተሰቡ ውስጥ የሚታየው፣ የጠባብ ብሄርተኝነት፣ በለው የጎሳ ልዩነት፣ የሚባሉ ዝባዝንኬዎች በመሿለኪያ ጣሪያ ስር፣ ሞተው የተቀበሩ ናቸው። አንዱም ይህ ነው መሿለኪያዎችን ለየት የሚያደርጋቸው የአስተሳሰብ ልኬት። የመሿለኪያ ወጣቶች፣ እርስ በእርሳቸው፣ ያለ ልዩነት ይዋደዳሉ፣ይረዳዳሉ። ለመሰብሰቢያ ማዕከላቸው መሿለኪያም ልባዊ ፍቅር አላቸው።

በአጋጣሚ አንድ አባል አስገዳጅ ሁኔታ ገጥሞት ከመሿለኪያዋ ቢርቅ፣ በናፍቆቷ ሟች ነው። አስሬ እየደወለ በሀሳብ መሿለኪያ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት የማይቀር ጉዳይ ነው።

ይህ ቁርኝት ያለ ነገር አልሆነም። ወጣቱ በመሻለኪያ ውስጥ ነፃነት አለው፣ ሀሳቡን ለአባላት የመግለፅና የማስተላለፍ፣ የራሱን ፍልስፍና የማካፈል፣ ታመነበትም አልታመነበት የመደመጥ እድል አለው።  በመካከላቸው ያለው የእርስ በእርስ መተሳሰብ፣ አንድ አባል ሲቸገር የሚደረገው መረዳዳት፣ በደስታውም በሀዘኑም ከጎኑ የመቆሙ ባህሉም ጭምርም ነው መሻለኪያን ተፈቃሪና፣ ተናፋቂ ያደረጋት። ይህ ብቻ አይደለም፣ የመሿለኪያዎች ባህሪይ በስራ እንቅስቃሴያቸው ከተለያዩ ስዕብናዎች ጋር የሚያገኙትን ልምድ፣ በትምህርት የተደገፉ፣ ብሎም ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከመፅሃፍት፣ ከኢንተርኔት፣ የሚገኙ መረጃዎችና፣ እውቀቶች በሙሉ በመሿለኪያ ስብስባቸው አምጥተው የመወያየት ባህል በማዳበራቸው፣ መሿለኪያን፣ ሁሌ በተለያየ አጀንዳና ሁኔታ ስለሚያሳልፏት፣ የፍቅሯ እስረኛ አድርጓቸዋል። የእርስ በእርስ፣ መረዳዳት፣ መተዛዘን ለአንዱ ደስታ፣ ሌላው በደስታ መስዋዕት መክፈል፣ የመሿለኪያ ወግ ልማድ መሆኑ፣ የሰነባበተ ጉዳይ ነው።
ዛሬ በሀገራችን የተንሰራፉት የዘር፣ የሀይማኖት ወዘተ… ልዩነቶች መሿለኪያ ውስጥ አባልን ከአባል የሚለዩ ወሰኖች ሆነው በፍፁም አይገኙም። ለሀገር ለወገን ጠቃሚ የሆኑ ሀሳቦች፣ በተለያዩ ዘርፎች ልምድና እውቀት ባላቸው መሿለኪያዊያን ይብላላሉ፣ ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ የሚችሉትን ያደርጋሉ።

   ሲጠቃለል መሿለኪያ በአራት ግድግዳ የተወሰነች ስፍራ ትሁን እንጂ፣ ለመሿለኪያዎች የሚሰበሰቡባት መሰብሰቢያ አዳራሻቸው ነች። መወያያ መመካከሪያ፣ ውሳኔ በድምፅ ብልጫ የሚያፀድቁባት ፓርላማቸው ነች። መብያ፣ መጠጫ፣ ቀልድና ቁምነገር መጨዋወቻ፣ መዝናኛ ስፍራ ነች። እርስ በእርስ የሚረዳዱባት የቴሌቶን መድረካቸው ነች። ወቅታዊ፣ አለም አቀፋዊ ሀገራዊ መረጃና ዜናዎች የሚለዋወጡባት፣ የሚሰሙባት፣ የሰሙት የሚያካፍሉባት መገናኛ ብዙሃናቸው ነች። መሿለኪያ ለመሿለኪያዎች ይህ ሁሉ ነገራቸው ነች ቢባል ግነት እንዳልሆነ በቀይ ብዕር ይሰመርበት። ታዲያ መሿለኪያዎች በእረፍት ቀን፣ በበአል ቀን ሳይቀር ሁሉም ነገር  በምትሆንላቸው መሿለኪያ ከማህበረሰቡ ሸሽተው መሰብሰቡ ሱስ ቢሆንባቸው፣ የሚገርምህ ነገር ነው? አይደለም!!
ወገሬት!!