Monday, May 30, 2016

Anwar abdo yahya

Anwar abdo yahya
#ሳteናw
ስታዲየም ፊት ለፊት ከሚገኘው ላሊበላ ሆቴል እንድንገናኝ ቀጠሩኝ… አንዋርና፣የእህቱ ልጅ አዚዝ። በቀጠሮው መሰረት ልብሶቼን በትንሽዬ ቦርሳ አንጠልጥዬ፣ ካሉኝ ቦታ ቀድሜ ደረስኩ። ከሆቴሉ ገብቼ ውጪውን ከሚያሳይ ስፍራ ተቀምጬ ያዘዘኩትን ሚሪንዳ አየተጎነጨው፣ ጎዳናው ላይ አላፊ አግዳሚውን እያየው ቆየሁ። አንዋርና አዚዝ አፍታም ሳይቆዩ በጊዜው ለከተማችን የመጀመሪያ የሆነችውን ቶዮታ ያሪስ አውቶሞቢል ይዘው ከች አሉ። አዉቶሞቢሏ በአንዋር አማካኝነት ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ከገባች ገና አስር ቀን እንኳ አልሆናትም። ከአዲስነቷ ጋር አዲስ ሞዴል ስለነበረች ባለፈችበት ጎዳና ሁሉ የሰውን አይን ብቻ ሳይሆን ቀልብም ትስባለች። ከራስ ሆቴል ሂሳቤን ከፍዬ ወጥቼ ወደ መኪናዋ ገባው። አብረውን የሚሄዱ ዘመዱ ሚልዮንና… ችኳንታውን ካሉበት ፒክ አድርገን ጉዞአችንን ጀመርነው …  ወደ ሶደሬ… ዋቢ ሸበሌ ሆቴል…

  ቀጥሎ የምነግርህ ስለ አንድ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋች ወይም ታዋቂ ስለሆነ ሞዴል አይደለም። ይልቁንስ በጣም የምወደውና የማከብረው አብሮ አደግ ወንድሜ ስለሆነው አንዋር አብዶና ለሽኝቱ ስላሳለፍነው የሶደሬ ጉዞ ገረፍ ገረፍ ትውስታዎች እንጂ። ላንተ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ስላልሆነ ብታነበውም! ባታነበውም፣ ለውጥ የለውም። ምናልባት አስቂኝ ገጠመኞች ስለተካተቱበት ፈገግ ሊያሰኝህ ይችላል…

   አንዋር አብዶ ያህያ፣  ከልጅነቱ ጀምሮ ዕድል የምትከተለው ቅንነት መለያው የሆነ በአንድ ግቢ አብሮኝ ያደገ ልጅ ነው(ታላቅ ወንድሜ ነው ልበልህ አንጂ)። የየመን ዝርያ ስለነበረው፣ ገፅታው የአረብ ፀጉሩ የህንድ፣ የመሰለ፣ ውበት ያፈሰሰበት… የቷንም ሴት "ውይ ሲያምር" የሚያስብል መልከመልካምነት ተፈጥሮ የተቸረ ነው ስልህ ከምሬ ነው። ታዲያ በፊት ከመልኩ ጋር በተያያዘ ማስታውሰው…  ፒያሳ ለፒያሳ ወክ ስናደርግም አላፊ አግዳሚ ቆንጆ ሴቶች አይኑን ሊያወጡት ይደርሱ ነበር። የዚህኔ እኔ በቅናት ይሁን በቅንነት በግልምጫ አፈር ከድሜ አግጣቸውለው።  "ምኗ ደረቅ ነች! ልትበዪው ነው እንዴ!" አላታለው። እሱ አፌን በመዳፉ ለመሸፈን እየታገለኝ  ይስቃል… ተወደድኩ ብሎ ማይመፃደቅ፣ ኩራት የሚባል ነገር ጨርሶ የማይነካካው… ምርጥ ልጅ ነው አንዋር። እኔ የሱ አይነት ገፅታና ስብዕና ቢኖረኝ ኖሮ ስንቷን… ሆ! ሞቼልህ  ዛሬ ይህን ታሪክ ለመፃፍ አልበቃም ነበር kkk  ሌላው ደግሞ አለባበሱ። ብታምንም ባታምንም ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ1000 ብር ማጫ ያየሁት አንዋር እግር ላይ ነበር። ታዲያ ምን ያስገርማል? እንዳትል! ይሄ የዚህ ዘመን ሳይሆን የ80ዎቹ መጨረሻ ወሬ ነው። ዛሬ ሀይሉ ሻውል ሞል ባለ 40000 ብር ጫማ መሸጡ ስትሰማ እንደሚገርምህ ሁሉ  በጠቀስኩልህ ጊዜ የ1000ብር ጫማ አስገራሚ ዋጋ ነበር። አንዋር መልክና አለባበስ ብቻ አይደለም… ብዙ መልካም የምትላቸው ስዕብናዎች ባለቤት ነው። ለምሳሌ ባህሪው የተቸገረ ሰው አይቶ ማለፍ ፣አይችልም። "ሰላም ና! ለአከሌ ይሄን ብር እኔ እንደሰጠሁት ሳትነግረው ስጠው" ብሎ  ይልከኛል። ዛሬ ሰው አንድ ውለታ ቢውል በቱልቱላና፣በነጋሪት ላላፊ አግዳሚው እዩልኝ ስሙልኝ መከራ ነው። የእርዳታ ድርጅቶችም አንድ እጃቸው ረድተው በአንድ እጃቸው ቪዲዮ ይቀርፁሃል። አየኸው አንዋር  ሲሰጥ እንኳ በሚስጥር ነው። (ይህ ተግባሩ ሁሌም እንዳከብረውና እንድወደው የሚያስገድደኝ ነው)። በዚህም ሰበብ አንድ ቀን በገንዘብ በኩል ተቸግሮ አያውቅም። ተማሪ እያለም እንኳን።

… ስማ የአዲስ ከቴ ተማሪ ችኳንታዎች… በሱ የመጣ ሚኒ ሚዲያ ያጣብቡ እንደነበር ብነግርህስ…   ከጃሊያ ወጥቶ አዲከተማ ሃይስኩል በሚማር ግዜ ዩኒፎርም አልተጀመረም ነበርና… በዘመኑ ድንቅ የነበረ የአለባበስ ስታይል የሚከተል፣ሁሌ ንፁህ፣ዛሬ የለበሰውን ነገ የማይደግም፣ በዘመናችን ቋንቋ ፀዴ ልጅ…  ታዲያ ይህ ፅዱነቱ፣ በዛላይ መልከ መልካምነቱ የማረካቸው የአዲስ ከተማ ሀይስኩል ኮረዳ ተማሪዎች፣ ለአንዋር ሙዚቃ ለመምረጥ የትምህርት ቤቱን የሚኒ ሚዲያ ቢሮ በሰልፍ ያጨናንቁት ነበር። 15 ደቂቃው የእረፍት ጊዜ አየር ሰዓት ለሱ በተመረጡ ዜማዎች ይጠናቀቁ ነበር። ወደው መሰለህ? ከመልኩ ጋር ያለው መልካም ስነምግባር ያዩት ሁሉ የቀረቡት ሁሉ እንዲመኙት ያስገድድ ነበር።   ምነው አውቀኸው ባህሪውን ብትረዳው… ነጠላ ዘፈን ትለቅነት ነበር።
ከኔ ጋር የነበረን ቅርርብነት እንደማንኛውም የጎረቤት ልጅ ሳይሆን እንደታላቅና ታናሽ ታላቅ፣ እንደልብ ጓደኛ አይነት ነበር። አኔ እንኳ አንድ ነገር አድርግልኝ ካልኩት፣ ያለምንም ጥርጥር አድርጎታል። ከሱ ጋር በነበረን ቆይታ የገጠመኝን ልንገርህ…

  አንድ ቀን ፒያሳ ከሚገኘው እውቁ ገብረትንሳይ ባቅላቫ ቤት  ሄድን፣ አንድ አንድ አዘን በቁም መብላት ጀመርን። አንዋር ሶስቴ እንደጎረሰ ዘጋውና አቆመው እኔ አስገባዋለው። በጊዜው ተማሪ ስለነበርኩ የገንዘብ እንጂ የሀፒታየት ችግር አልነበረብኝም፣ የራሴን እንዳጠናቀቅኩ ወደ አንዋር ባቅላቫ ዞርኩ ፣አቀርቅሬ እጠበጥበዋለው…  ለተመልካች ሰዓት ሰሪ እመስል ነበር፣ ለካ አንዷ ኮበሌ በአበላሌ ተመስጣ ኖሮ ቀና እስክል ትጠብቀኛለች። አድናቂህ ነኝ ፈርምልኝ ልትለኝ አልነበረም። ቀና ስል አይን ለአይን ተጋጨን… በምልክት ና! የኔንም ጨርስልኝ አትልም!…  ንድድ አለኛ…  ሁኔታችንን ሲከታተል የነበረው አንዋር መርካቶ እስኪደርስ ሳቁን ማቆም አልቻለም። እኔም በንዴት እንደዚህ አይነት ሰርጎ ገብ ቡዳዎች እያሉ በየት በኩል እንብላ እልኩት!  የልጅቷ ድፍረት ቢያናደኝም ለአንዋር የሳቅ ምንጭ ስለነበረች ምንም የመልስ ምት ሳልሰጣት ተውኳት።

  አንዋር አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ 12ኛ ክፍልን ካጠናቀቀ ቡሃላ፣ ማይክሮሊንክ ኮሌጅ በኢፎርሜሽን ቴክኖ ዲኘሎማውን ወስዶ ወደ ህንድ በመሄድ የትምህርት ደረጃውን አሳድጎታል። የአንዋርን ስብዕና ብተነትነው ብተነትነው ማሰልቸት ስለሆነ ላቁመው። እድል የሚከተለው ልጅ ነበር ብዬህ አልነበር?  በአንድ ቀን ተደጋጋሚ ብስራት ስለደረሰው ገጠመኝ ላጫወትህ… 

  ትዝ ይለኛል በዚህ ቀን እኔና ጓደኛዬ ሄኖክ አትክልት ተራ ሽንኩርት በኪሎ ለመግዛት በዛውም ፓስታ ቤት የመጣ ደብዳቤ ካለ ለመጎብኘት ወደ ፒያሳ ሄድን… እኔ ሽንኩርቴን ገዝቼ ለጃሬ ሂሳብ እያመቻቸው ወደ ፖስታ ቤቱ ገባን። ሄኖኬ የፓስታ ሳጥኗን ከፈታት ከአንድ ብጣሽ ወረቀት በቀር አላገኘንም። ወረቀቷ አንዋር አብዶ ዲቪ ስለደረሰህ የተላከልህን ፎርም ቀርበህ ውሰድ የሚል ወረቀት ነበር። ጓደኛዬ ሄኖክ በደስታ ጩኸ። እኔ ሀሳቤ ጃሬ ላይ ስለነበር በወቅቱ ደስታዬን አልገለፅኩም። ልክ ሰፈር ስንደርስ ሽንኩርቱን ቤት አድርሼ …  ወረቀቷን ይዘን እነ አንዋር ቤት ገባን…  ብስራቱን ለቤተሰቦቹ ነግረናቸው እየተደሰትን ሳለ በዛው ቅፅበት አንዋር ከህንድ ደወለ …(አይገርምህም አጋጣሚው) አንዋር በትምህርቱ በከፍተኛ ነጥብ ማለፉን ለቤተሰብ ለማበሰር ነበር አደዋወሉ። ለብስራት ደውሎ ብስራት ተነገረው ደስታው ወደር አጣ። ከጥቂት ወራት ቡሃላ አን ዋር ግራጁዌሽኑን አጠናቆ አዲስ አበባ ገባ። የዲቪው ኘሮሰስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀቀ። ቪዛው በእጁ ገባ። ይህን ተከትሎ የደስደስ ወደ ሶደሬ… ለመዝናናት ራስ ሆቴል ተገናኝተን ጉዞውን ጀመርን…

…ደስ የሚለውን የአዲስ አበባ አየር ሰንጥቀን ቁልቁል ተምዘገዘግን ቃሊቲ፣ገላን፣ዱከም፣ እድሜ ለያሪሷ ፉት አልናቸው ደብረዘይት፣ሀይላንድ ውሃ  ለመግዛት፣ቆምን ሄድን… ደግሞ ለሽንት፣ ለፎቶ ምናምን ቆምን…  ደግሞ የሞጆን አውራ ጉዳና… አልፈን  ወደ ናዝሬት።

በረሃ ላይ የተመሰረተች የምትመስለው ናዝሬት (አዳማ) ከተማ 10:00 ሰአት ላይ ደረስን። በመኪናዋ ሰበብ የአብዛኛውን የከተማዋን ሰው አይን ተቆጣጠርነው ብልህ እትት እንዳይመስልህ የምሬን ነው። እዛው ካለ መንዲ ቤት ምሳ በልተን ወደ ሶደሬ ነካነው…  ገባን። አርብ ከቀትር ቡሃላ ስለነበር ግቢው ውስጥ እንደኛው ለመዝናናት በመጡ ሰዎች ተሞልቷል። እንደ ደረስን ቀድመን አዲስ አበባ ዋቢሸበሌ የያዝነውን ሁለት አልጋ ያሉት ሁለት ክፍል ተረከብን። ከክፍሉ ውጪ የሚታዩት ዛፎች፣አዕዋፋት፣ ጦጣዎች ነፋሻማው አየር ተደማምረው የሚሰጡህ ድባብ የነብስ ምግብ ነው ብልህ ማጋነን አይሆንም። ከሻወርና ከእረፍት ቡሃላ ቁምጣ ለብሰን ፎጣ ይዘን ወደ አባድር ፍል ውሃ ገንዳ ሄድን።

በአባድር የመታጠቢያ ገንዳ ገና ስትገባ የምታየው የቦርጭ መዓት የሀገሪቱ ሀብት በገላቸው ላይ በተሸከሙ ባለ ጊዜዎች እንደተከበብክ ይገባሃል።
የአባድር ፍል ውሃ በወፍራሙ እየተምዘገዘገ ቁልቁል ሲንዠቀዠቅባቸው ሳይ ወንድሜ  እኔ በየትኛው አቅሜ እቋቋመዋለው ብዬ ፈራው። ደግሞ ይህ እድል ድጋሚ በህይወቴ ላይገጥመኝ ይችላል ብዬ በወላፈናማው ውሃ ውርጂብኝ ውስጥ ለመግባት ወሰንኩ። ሰውነቴን የውሃውን ወላፈኑን ሳልለማምድ ዘው ብዬ ገባው። ወይኔ ጉድ ሆንኩልህ!! የውሃውን ቃጠሎ መቋቋም አቅቶኝ ድምፅ ሳላሰማ ዘልዬ እንደገባው ዘልዬ ወጣው። አይኔን ሳልከፍት ህመሜን ዋጥኩት። እግሬ በተረበበ ነገር የተሸፈነ መሰለኝ። ውሃው የጀርባ ቆዳዬን ገሽልጦ ከእግሬ የሞጀረው መስሎኝ ደንግጬ ቀስ ብዬ አይኔን ገለጥኩት። ለካ እግሬን የሸፈነው በውሃው ግፊት የወለቀው ቁምጣዬ ነበር። ቀና ስል ሰው እየሳቀ ስስ ጉተና የበቀለበት ሙርጤን ይመለከተዋል። የአንዋርና የአዚዝ ሳቅማ መርካቶ ድረስ የሚሰማ እስኪመስል ነበር…ካካካካ  እንኳን ይችን አግኝቶ… !! የማንንም ሳቅ  ከምንም አልቆጠርኩት። እንትኔ ከቁምጣው ጋር አብሮ ባለመውለቁ ፈጣሪዬን እያመሰገንኩ መልሼ ቁንጣዬን አጠለኩት።በሶደሬ መዝናኛ… ሶስት ቀን በፈረስ ግልቢያ፣ በዋና… መዝናኛ በተባለ ሁሉ አሳለፍን… የማይረሳ ደማቅ ትውስታ ፈጥረን ተመለስን። የሶደሬው የአዋሳው የወንዶ ገነቱ በሌላ ፅሁፍ ዘርዝሬ እቸከችከው ይሆናል።አሁንግን በቃኝ።

አንዋር ዛሬ ስቴት ውስጥ አግብቶና ወልዶ ይኖራል፣ ባለበት ሁሉ ሰላሙን፣ እመኝለታለው።
ወገሬት!!

Friday, May 27, 2016

"የአያቴ ድቤ"

"የአያቴ ድቤ"

#ሳteናw 
  ከቀኑ 9:30 ሲሆን ከት/ቤት ተለቀቅን። ከጓኞቼ ጋር እየተተራረብን በህብረት ግማሽ የአስፓልቱን ጎዳና ሞልተን ወደ ቤታችን እንሄዳለን። ጓደኞቼ በየቅያሳቸው ሲደርሱ አየተሰናበቱኝ እየተተሰናበቱኝ ብቻዬን ቀርቼ ወደቤት ሄድኩ።ግቢ በር ስደርስ ከቤታታችን እየተግተለተለ የሚወጣው የእጣንጭስ የቅቤ ቃና ሲያውደኝ አያቴ ከሰምንታዊ የቡና ስርዓቷ ጋር አተካኖ ማዘጋጀቷን አወኩ…

ስለ ኢትዮጲያ ሲነሳ አብሮ ቡና ይነሳል። ቡናው ሲነሳ ያየነው ያደግንበት ከሌላው አለም የተለየው ከባህላችን አንዱ የሆነው የቡና አፈላል ስነ ስርአታችን ድቅን ይላል። የኢትዮጲያን የቡና ስርአት አያየኸው ብታድግም በድጋሚ ላስታውስህ…

ረከቦት፣ሲኒ፣ምጣድ ወዘተ… ተጣጥቦ ይቀርባል፣ ቡናውን ፍሬውን ከእንክርዳዱ እስኪለይ ይለቀማል … ከሰል ይቀጣጠላል … የተለቀመው ቡና ታጥቦ … በተቀጣጠለው ፍም በጋለው ምጣድ ላይ … ቡናው ይገለጣል … ችሥሥሥ… ብሎ ሲንጫጫ ድምፁ አይደላህም?… ቡናውን እንዳያር በመቁሊያ ይማሰላል (ቡና ጠጣለው ብለህ ሬንጅ እንዳትጠጣ ስትቆላው ጥንቃቄ ያሻል) አጋም ሲመስል በመቁያው ተዝቆ…  ይወጣል … ቡናው እስኪቀዘቅዝ… በጀበና ውሃውን ትጥደዋለህ… ጥፍርህን እንዳትቀረጥፍ ተጠንቀቅና ውቀጠው… እስከዛ ውሃው ፈልቷል… የቡናው ዱቄት በፈላው ውሃ ተጨምሮ በድጋሚ ይጣዳል… ይፈላል… ይወርዳል… ሲሰክን… እየተቀዳ…ከነ ስባቱ አቦሉ ይጠጣል(level one በለው)…ውሃ ተጨምሮ…ድጋሚ ይጣዳል…  ቶናው… ከአቦሉ  ቀጥኖ… ይርሳል… በሰሶስተኛውም… በረካው… ይደርሳል…  እሱም ይጠጣል። ድሮ ነበር ታዲያ ይሄ ሁሉ ማሽሞንሞን!! አሁንማ… ጊዜው እራሱ በረካው ስለተነሳ… አስከ በረካ ብዙም አይጠጣም። በማሽን ተቆልቶ በማሽን ተወቅጦ በማሽን ይፈላል… ቶሞካ በለው!።

  ስለቡና ካነሳው አይቀር… አሳዳጊ አያቴ ታዘወትር የነበረውን የቡና ስርአት አነሳለው። አያቴ ከቡና ጋር ልዩ የሆነ ፎንቃ ነበራት። የአያቴ የቡና አፈላል ስነስርዓት ሶስት አይነት ነበር።
1/ዕለታዊ ቡና፣
2/ሳምንታዊ ቡና፣
3/አመታዊ ቡና በሚል ከፍየዋለው።

☞ ዕለታዊ ቡና:- በየእለቱ ጠዋት፣ቀን፣ማታ የሚፈላው ቡና ነው። ዶክተር እንዳዘዘው መድሃኒት ጊዜው ሳይዛነፍ ይፈላል። የቤታችን የቡና ዕቃዎች በቀን 3 ጊዜ በስራ የመሰማራት ግዴታ ነበረባቸው። ዕለታዊው ቡና ላይ የግቢ ውስጥ ጎረቤት አባም እማም ወራዎች የሚታደሙበት ነው። የቡና ቁርሱ ቤት ያፈራው ማንኛውም ነገር… ዳቦ፣ደረቅ እንጀራ በሚጥሚጣ፣ ንፍሮ ቆሎ ወዘተ… ሊሆን ይችላል። ታዲያ ተማሪ እያለው… ጠዋት ጠዋት  ከእንቅልፌ አላርም ሆኖ  የሚቀሰቅሰኝ… "የኢኮኖሚ ዋልታ
ቡና ቡና… " ከሚለው የሬድዮ ዜማ ቀጥሎ … ቡና ሲወቀጥ የሚወጣው ድም… ድም… የሚለው የወቀጣ ድምፅ ነው።

☞ ሳምንታዊ ቡና:- በሳምንቱ አንድ ቀን ለየት ባለ መልኩ በምሳ ሰዓት የሚፈላ ነው።  የቡና ቁርሱም ቆጮ በአይቤ፣አተካኖ፣3 አዚዝ ወይም በቅቤ፣ በአይብ፣ በሚጥሚጣ የተለወሰ ሩዝ ይሆናል። ጎረቤቶችና ልጆቻቸው ጨምሮ ይታደሙበታል። በዚህ ቀን የቡናው ዝግጅት ገና ከማለዳው ከሰራተኞች አንዷን ወደ መርካቶ ቆጮ ታራ ትላክና አይብና ቡላ ቄጠማ ተገዝቶ ቡላው ተቆልቶ… መጠኑ መለስተኛ ማስታጠቢያ በሚያክል ጣባ ተሰናድቶ… መደብ ላይ ከነበረው የአያቴ አልጋ ስር በትሪ ተከድኖ ይቀመጣል። የምሳ ሰዓቱ ሲደርስ የቡና ዕቃዎች ታጥበው ፀዴ ሆነው ይቀርባሉ። ቄጠማ በሸፈነው የመደቡ ወለል ላይ ሰፊና ትልቁ የስኒ ረከቦት ሲኒዎቹ እንደተገጠገጡበት ከአያቴ ፊት ለፊት ይሰየማል። አያቴ በተመስጦ ቡናውን ትቆላዋለች፣ ታስወቅጠዋለች… ቡናው ፈልቶ እስኪሰክን የግቢ ውስጥ ጎረቤት ይጠራል… (ለነገሩ የዛን ቀን የምግብ ዝግጅቱ ቃና ራሱ ይጠራል)። …በጣባ ተሞልቶ የተሰናዳው ቡላ ይቀርባል… ቡላው ሙሉ በሙሉ በአይብ ይሸፈናል። ከአይቡ በላይ ከሩብ ሊትር ያላነሰ የቀለጠ ቅቤ ይደፋበታል፣ ከዳር እስከዳር ሚጥሚጣ ተነስንሶበት ፣ እጣን ተጫጭሶ … ዱዓ ከተደረገና ካበቃ ቡሃላ… የተቀመመው ቡላ ተለውሶ ለቡና አድምተኛው ይታደላል፣ ያልተገኘው ድርሻው ይቀመጥለታል። የኔ ቢጤዎችም ከዚህ ማዕድ ተቋዳሽ ነበሩ። ታዲያ በዚህ እለት በ9:30 ከትምህርት ቤት ስመጣ… ገና ከጊቢ ቃናው ያወደኝ የቡና ስርአቱ ቢጠናቀቅም… አያቴ ለብቻዋ ተቀምጣ  የመሀመድ አወልን መንዙማ ከፍታ፣ እየቃመች… ቤቱ በእጣንና በቅቤ መዓዛ ታውዶ እደርሳለው። ቲቪ ከፍታለው ብለህ እንዳትጦልበኝ! ብላ ቶሎ ድርሻዬን ታስታቅፈኛለች። አላህ ይርሃማት።

☞አመታዊ ቡና በተለምዶ(የዳዶ ቡና) ይሰኛል። በአመት ሁለት ሶስት ቀን የሚዘጋጅ እናቶች የሚታደሙበት የቡና የዱዓ ስርአት ነው። አስፈላጊና ጊዜያዊ  ፀሎት በሚያሻ ጊዜም በእናቶች ይዘጋጃል… ይህን ስርአት ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ጎረቤት ሴቶች ብቻ ሳይሆን ሩቅ የሚገኝ ወዳጅ ዘመድ ቀድሞ ተነግሯቸው በእለቱ ስለሚገኙ ነው። በዚህ ስርዓት እናቶቻችን የተመካከሩ ይመስል ነጭ በነጭ ለብሰው ቤታችንን ይሞሏታል… የቡና ስርአቱ በመጠኑ ላቅ ብሎ  እንደ ሳምንታዊው ቡና በቆጮና አይብ ይታጀባል… ከምንጊዜውም በላይ ዱዓው በሁሉም እናቶች በየተራ ስለሚደረግ ዘለግ ያለ ጊዜ ይወስዳል። ቆጮና አይብ በሰሀን ሰሀን ተደርጎ ለደረሰው ሁሉ ይሰጣል። በሰአቱ ላልተገኘ ቆጮው እንደ አነባበሮ በአራት መዓዘን ተጠርዞ አንድ አፍኝ አይብ እየተደረገ ይቀመጥለታል። በመጣ ጊዜ ይገጨዋል።ይህ ስርአት ላይ በእናቶቻችን መንዙማ ይባላል … አያቴ ድቤዋን እየመታች ትቀበላለች፣ መንዙማ ታወጣለች…  ሁሉም እናቶች በየተራ መንዙማ ይላሉ። ዜማቸው ከግቢው አልፎ በሰፈራችን ያስተጋባል።(የአያቴ ድቤ ዛሬ አይጥ ከረታትፎት ጊዜ ጥሎታል… ባየሁት ቁጥር ትዝታ ይጭርብኛል። (አላህ የንአለክ…… አይጥ)

በዚህ የእናቶች ዱዓ ሰበብ የታመመው ይሽራል፣ የጨነቀው ይፈረጃል፣ የታሰረው…ነጃ ፈላህ ይወጣል። … ታዲያ እናቶች ያደረጉት ዱዓ እንዲሁ መሬት የሚቀር ይመስልሃል? አይቀርም

ለምሳሌ የኔን አያቴ የተረከችልኝን እውነተኛ ገጠመኝ ላጫውትህ… ነብስ ሳለውቅ መኮንን ክሊኒክ ተገረዝኩ…  በግርዛቱ በስህተት ይሁን በስፌት ሶስት ቀን ወሃ ሽንት መሽናት ተሳነኝ። አያቴ ጨነቃት ጠበባት… በመጨረሻም የዳዶ ቡና አዘጋጅታ በእናቶች ዱዓ ልታስደርግልኝ ዝግጅት ጀመረች። የተጠሩ አንናቶች በሙሉ ተገኝተዋል። ቡናው ሶስት አዚዙ ቀርቧል እኔን በትንሻ ፍራሼ ላይ በጀርባዬ እንደተኛው ከወገቤ በታች እርቃኔን አድርጋ… ከእናቶቻችን መሀል አጋደመችኝ። በየተራ ዱአ አደረጉልኝ። አላህ ሰማቸው!! ሶስት ቀን ታምቆ የሰነበተው ሽንቴ ሽቅብ ወደ ኮርኒሱ ተነፎለፎለ። ቤታችን በእናቶች እልልታ ተቀወጠች እልሃለው።

አላህዬ ለእናቶቻችን ዱዓ! ፈጣን ምላሽ እንደምትሰጠው የኛንም ዱኣ ስማን! ለዲንህ ብለው የታሰሩ ኡሰታዞቻችንን በዚህ ረመዳን ከቤተሰቦቻቸው ይቀላቀሉ እኛም የህሊና ረፍት እናገኝ ዘንድ ፈጣን ምላሽ ስጠን…  አሚን አትሉምን?

Wednesday, May 25, 2016

ለላይፍ የገቡበት ሙድ ላይፍ ይቀጫል!!!

#ሳteናw
"ሁሉንም ላይፎች አይቶ መመለስ ጥሩ ነው" እያለ ሲሰብክና በስሜት ሲያወራ ሰማሁት አንዱን ወጣት… ለማበላሸት መሞከሩን ሳያስተውል መምከሩ እኮ ነው በሱ ቤት። በጣም አናዶኛል… በጊዜው ዘርዘር ያለ መልስ ባልሰጠውም … ነቁሬዋለው። ወዲያው ግን በዚህ ዙሪያ እራሴን ስብሰባ ጠራው… ከሀሳብ ፍጭት ቡሃላ ከሱ ተቃራኒ የሆነ መደምደሚያ ላይ ደረስኩ… ከሱስ ነፃ የሆኑትን ለመምከር  መሞከር እንዳለብኝ… አሰብኩና ይህን ፃፍኩ… "አንተን ብሎ መካሪ!!" … በለኝ ከፈለክ…

   እርግጥ ነው መጥፎ ነገሮችን አይቶ መመለስ ለወደፊቱ ህይወት ልምድ ጠቃሚ ነው። ለነገሩ አዲስ ስለማትሆን፣ ስለማትጓጓ ቀድሞ ማወቅና፣ ማየትህ በተወሰነ መልኩ ይጠቅምህ ይሆናል። የነቆርኩት ወጣት ላይፎች ሲል የገለፀው ጎጂ… የጫት፣ የመጠጥ፣ የወሲብ፣ ሱሶችን ነበር።
በነዚህ ውስጥ ለሙድ ለላይፍ ብሎ ገብቶና አልፎ የወጣው ሰው ቁጥር እጅግ አናሳ ነው። ይህን መዘርዘር ለቀባሪ ማርዳት ነው።…  ግን እዚህ ጋር ልብ በልልኝ!! አይቶ መመለስና! አይቶ መቅረት! የሚባል ጉድ አለ። ይህንን መዘንጋት አይገባም።

☞ ጎጂ ሱስ የሚሆን ነገር አይቶ መመለስ፣ ኤድናሞል popcorn እየበላ ሙቪ  ከልሞ እንደ መመለስ ቀላል አይደለም።

የትኛው አጫሽ የትኛው ቃሚ የትኛው ጠጪ ነው በነዚህን የሱስ መሰናክሎች አልፎ ዛሬ ከሱስ የፀዳ ህይወት የሚመራው? ለሙድ ብሎ ገብቶ በሱሶቹ ሙድ የሚያዝበት ስንቱ ነው? ለሙድ ለላይፍ ብሎ ይቺም፣ ያቺም ጭን ውስጥ ሲገባ ከርሞ በመጨረሻም ጉድጓድ የገባው ስንቱ ነው? አላየህም?  አልሰማህም? <<ቦንብ ረግጦ ነው የሞተው>> ብለው በራሱ ለቅሶ ላይ አላንሾካሾኩልህም? ᎂቹ ይህን የጀመረው ለላይፍ ብሎ እንጂ ለመሞት ብሎ አልነበረም። ላይፍ ለማሳለፍ ነው እያለ ስንቱ ላይፉ ተበላሽ። የመውጣት እድሉ ጠባብ በሆነ ጫካ ውስጥ… ለመዝናናት ተብሎ እንዴት ይገባል? በሰላም ስለመውጣትስ በምን እርግጠኛ ይኮናል? ጫካ… ስል (wrong turn) የተሰኘውን ፊልም ታወሰኝ… ለመሆኑ ይህን ሙቪ አይተከዋል?… ለመዝናናት ብለው ጫካ የሄዱ ወጣቶች መመለሻው መንገድ ጠፍቷቸው ሲኳትኑ… በጫካው ውስጥ ሰው ሆነው የሰው ስጋ በል በሆኑ ፍጡሮች ይዘው… ስጋቸው ሲዘለዝሉት፣ ደማቸው ሲጠጡት፣ ነብሳቸውን ሲያወጡት … ሾፈከዋል? ለሙድ ለላይፍ ተብሎ የሚጀመርን ሱስ በዚህ ሙቪ መስለው። ሱስ ለመያዝ መግቢያው ሰፊ እንደሆነ ሁሉ መውጫው ሰፊ አይደለም። ለጊዜው ያዝናናኛል ብለህ ለሙድ የጀመርከው፣ በመጨረሻ ይዝናናብሃል፣ ራስህ ላይ ሙድ ይይዝብሃል። ዛሬ በቁጥጥሩ ስር ያላደረገህ ሱስ ነገ ይቆጣጠርሃል። እጅና እግርህን ያስርሃል ህይወትህን የዝባዝንኬ መንደር ያደርገዋል። ግድ የለሽና ሞራል አልባ ስብዕና ያላብስሃል። ዛሬ ለጥናት ብለህ የጀመርከው ቂማ፣ ነገ ቂያማ እንደሚሆንብህ አትጠራጠር።

ከጫትና መሰል ሱሶች የምታተርፈው ነገር ቢኖር… ጊዚያዊ ደስታን ነው… በህይወትህ ሂደት ቀስበቀስ የምታገኘውን ደስታ፣ በአቋሯጭ መንገድ ያገናኝሃል።ግን ምን ዋጋ አለው? ለጊዜው ያስደስትህና ደስታህ ወዲያው ይጨልማል። ስትጀምምረው ደስ ደስ ያሰኘህ በርጫ ምርቃናው ሲመጣብህ በሀሳብ ማዕበል ያንገላታሃል! ቁጭ አድርጎ ያስሮጥሃል ደግሞ በቀላሉ  ሆድ ይብስሃል፣ ትንሿን ቀዳዳ ያሰፋብሃል። ቸለስ ቸለስለስ አድርገህ ሞቅ ሲልህ ያስጨፈረህ ሞቅታ፣ በመጨረሻ አስክሮ አቅልህን ወስዶ ሰባተኛ ወይ ትቦ መሃል ያሳድርሃል፣ ። ለሙድ ብለህ የምትጀምራቸው ሱሶች መጨረሻቸው አያምርም። እደግመዋለው መግቢያው ሰፊ እንደሆነ መውጫቸው ሰፊ አይደለም።

ብልህ ከሰው፣ ሞኝ ከራሱ ስህተት ይማራል!! በውስጡ አልፌ እማረዋለው ካልክ ተሞኝተሃል። ምንም የዋና ችሎታ ሳይኖርህ… እዛው ዋና ለምጄ በዛው ይህን ባህር አቋርጣለው እያልክ መሆኑን… ተገንዘብ። ይህ ስህተትህ አያስተምርህም፣ ቦምብ አምካኝ እንዳትሆን!! እዛው ያስቀርሃል።

☞ አራዳ ከሆንክ ከሰው ስህተት ተማር፣ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ከተሳሳቱት ተረዳ፣ ምንም አያጓጓህ! የተለየ ነገር የለውም።… ካንተ በልጬ፣ ካንተ ይበልጥ… ተገንዝቤ እንዳይመስልህ! በዚህና በመሰል ሱሶች ተይዘው… ተወው በቃ!! እናም እልሃለው ጎጂ ሱስ ያልጀመርክ ወንድሜ ብልህ ከሆንክ ከሰው ስህተት ተማር…  ሞኝ ከሆንክ… ሂድበት…

ወገሬት!!

Friday, May 20, 2016

የትም ተወለድ መርካቶ እደግ

#ሳteናw

"የትም ተወለድ መርካቶ እደግ"

"የትም ተወለድ መርካቶ እደግ" የሚለው ብሂል ያለነገር አልተባለም። ይህን አባባል ዛሬ ፌስ ቡክ ላይ መርካቶን አውጥተው የሰፈራቸውን ስም በመተካት የሚፖስቱትን ስታይ ለየትኛው ሰፈር እንደተባለ ግር ብሎህ ይሆናል! አይዞህ ግር አይበልህ ከዚህ ፅሁፍ ንባብ ቡሃላ ግን አባባሉ ለማን እንደተባለ በራስህ ፈራጅነት ታረጋግጣለህ።

ለአንድ ሰው ዛሬ ለተላበሰው ስብዕና አስዳደጉ ወሳኝ ሚና መሆኑን ማስታወስ አይጠበቅብኝም። የዛሬ ማንነት የአስተዳደግ ፍሬ ነው። መርካቶ ሰፊ የገበያ ስፍራ በመሆኑ የማይረግጠው የማይጎበኘው የሰው አይነት የለም። አዋቂው፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ አስተማሪው፣ ተማሪው፣ ቱሪሰቱ፣ ለማኙ ፣ቀማኙ … በዚህም ሳቢያ የመርካቶ ልጅ በአስተዳደጉ ከማይገናኘው የሰው አይነት የለም እልሃለው። ይህም መስተጋብር በአስተዳደጉ የህይወትን ውጣ ውረድ ብዙ እንዲያይ፣ብዙ እንዲታዘብ፣ብዙ እንዲያውቅ ያደርገዋል የመርካቶን ልጅ።

ሌላ ሰፈር ያደገንና የመርካቶን ልጅን አቅርበህ ብታነጋግር በንቃተ ህሊናም ሆነ ብዙ አዲስ ነገር በማወቅ ረገድ የመርካቶ ልጅ ልቆ እንደምታገኘው ጥርጥር አይግባህ። ከከተማችን ሰፈሮች ሁሉ የመርኬ ልጅ በንቃተ ህሊናው ልቆ መገኘቱ ይሄው አስተዳደጉ ነው። በሌላ ስፍራ ገና ዳይፐር የሚቀያየርለት ህፃን የመርካቶ እኩያው ዳይፐር ሲሸጥ ታየዋለህ። ገና በጨቅላነቱ የኢኮኖሚ የተግባር ባለሞያ ይሆናል፣ የትኛው እቃ በየትኛው ወቅት እንደሚሸጥ ያለምንም አለማዊ እውቀት ይገነዘባል።  በልጅነቱ የህይወትን የተለያየ ገፅታ አይቶና አውቆ ያድጋል። በያንዳንዱ እንቅስቃሴው ምን ማድረግ እንዳለበት ለመርካቶ ልጅ መምከር ጊዜ ማጥፋት ነው።

በኪነ ጥበብ ዘርፍ ብትል የመርካቶ ልጅ ከ18 ቀበሌው ከሂሩት ቪዲዮ ቤት አንስቶ በዘመኑ ዘመናዊ እስከነበሩት ሲኒማ ራስ፣ አዲስ ከተማ ሲኒማ፣ የፊልምና የትያትር ጥበቦችን ገና ከህፃንነቱ አጣጥሞታል። ሀይመኖተኛነትን እንደ የእምነቱ በከበቡት ቤተ አምልኮዎች ይስተማራል። የተለያዩ እምነቶችን አስማምቶ አፋቅሮና አዋዶ እንዲያድግ … ያለማንም ኘሮፖጋንዳና አስተማሪ የራጉኤልና የአንዋር መስጊድ የጉርብትና አጥር ብቻ ማየት በቅቶታል። ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት ባሉ መንደሮች ያደገ ክርስቲያን ወጣት ከቁርአን ክፍል ፋቲሃን ቅራ ብትለው ሳያዛንፍ ያንበለብልልሃል። በተክለ ሀይማኖት ቄስ ትምህርት ቤት ተምሮ ያለፈ ሙስሊም ህፃንም የጠዋትና ማታ የዳዊትን ፀሎትን ያንቸለችልልሃል። የመርኬው ፈላ !

ይህ ብቻ አይደለም ሁለቱን የህይወት ጎኖች ማግኘትንና ማጣትን ገና ከጨቅላነቱ በከበቡት ባለ ሀብት ነጋዴዎች፣ በሌሊት ከእዳሪ ቡሃላ  መርካቶ በሚደርሱ የኔ ቢጤዎች አማካኝነት ጠንቅቆ ያውቃል። የችግርን መራራነት ለመረዳት በችግር ውስጥ ሳያልፍ በማየት ብቻ ይረዳዋል።የህይወት ዑደቷ በተለያዩ አጋጣሚዎች ህይወታቸውን የለወጠ ስብዕናዎችን በሰባተኛ ጉራንጉር፣ በአውቶብስ ተራ የምሽት ተሰላፊ እህቶች፣ በአሜሪካ ጊቢ በአልጋ ተራ ሴቶች አይቶ ግንዛቤ ይኖረዋል። አለነገር የትም ተወለድ መርካቶ እደግ አልተባለም። ፀጋዬ ገ/መድህን በቅኔው  የተቀኘለት… አብዱ ኪያር በዜማው ያቀነቀነለት… መርካቶ። ከየትኛውም ስፍራ መርካቶ የማደግን ልዩነት ይበልጥ ለማስገንዘብ በጥቂቱ መርካቶንና ክፍለ መርካቶዎቿን በስሱ ላስታውስህ

መርካቶ፣ አውቶቢስ ተራን ጎጃም በረንዳን ከራስጌው ፣ ከተክለሀይማኖት እስከ አብነት ከግርጌው አኑሮ ሰፍሯል።
ከአፍሪካ በትልቅነቱ ግንባር ቀደም መርካቶ ምንም አይነት ሰው እንደማታጣ ሁሉ ምንም አይነት ሸቀጥም እንደማታጣ ስነግርህ ከልቤ ነው። ዋና ዋናዎችን ሸቀጥ ትተህ በዙሪያህ ምንም አያገለግሉም ብለህ የፈረድክባቸው ቁሶች መርካቶ ስራ ላይ ሲውሉ ትታዘባለህ

… አገልግሎቱ አብቅቷል ብለህ በግቢህ ውስጥ ለልብስ ማጠቢያ ምጣድ ማስደገፊያነት ብቻ የምትጠቀመው የመኪና ጎማ፣ በጎማ ተራ እጆች… ወደ በረባሶ ጫማ፣ ልብስ ማጠቢያ የጎማ ሳህን፣ ዘመን የማይበጥሰው ገመድ… ወዘተ ሲሆን በአይንህ በብረቱ አይተህ በመርካቶ ጎማ ተራ ልጆች ፈጠራ ትደነቃለህ። የጥፍር ቀለም ጠርሙስ፣ የቅባት ጠርሙስ፣ አሮጌ ጫማዎች፣ የተቀዳደዱ ልብሶች፣ የተበጣጠሱ ፌስታሎች፣ የኘላስቲክ ውጤቶች፣ ብትንትናቸው የወጣ ካርቶኖች… የለስላሳ  ቆርቆረሮዎች ብታምንም ባታምንም መርካቶ የሚሸጡ እቃዎች ናቸው። ትላንት እህቶቻችን ተጠቅመው የጣሉት የጥፍርና የቅባት ቀለም ጠርሙስ ዛሬ አንዱ ምግብ ቤት የደቃቅ ጨው ወይም የቅመማ ቅመም ዕቃ የሆኑት በመርካቶ ውስጥ አልፈው ነው። ጠብሽ ከንቶህ ለቁራሌው የሸጥከው የዘይት ቆርቆሮ ወንፊት፣ ላቀች ምድጃ፣ ቀፈሻ፣ ወዘተ… አድርጎ መልሶ ለማዘርህ የሸጠልህ የመርካቶ ቀጥቃጭ ሰፈር ልጅ ነው። በስፍራው ማደጉ አይረባም የተባለን ነገር መልሶ አገልግሎት ላይ የማዋልን እሳቤ በተግባር ይማራል።የተበጣጠሱ ፌስታሎችና ስብርብራቸው የወጣ የኘላስቲክ ውጤቶች ለኘላስቲክ ፋብሪካዎች ለጥሬ እቃነት ግብዓትነት በመርካቶ እንደሚሰበሰቡ ብነግርህስ። ተሰብሯል ብለህ የጣልከው ባልዲ በሪሳይክል ኘሮሰሰህ ጆክ ሆኖ የምትጠቀመው የመርካቶ ነጋዴ ለፋብሪካዎች አስረክቦ ነው። ከየትኛውም አህጉር፣ ሀገር፣ ሰፈር ወደ ከተማህ የሚገቡ… ሸቀጣ ሸቀጦች መዓከላቸው መርካቶ ነው። ወይ መርካቶ!

አብዶ በረንዳ አለልህ ደግሞ… የከተማችን የጫት ፍጆታ በገፍ የሚያቀርብልህ የጫት ገበያ። በቅጡ ያልተነገረለት፣ ከመርካቶ የገበያ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ነው። አብዶ በረንዳ ስያሜው ከምን ከማን እንደመጣ ባይታወቅም… አብዶ በተሰኘ ሰው እንደተመሰረተ መገመት አይከብድም። ከሰባተኛ በስተቀኝ የሚገኘው አብዶ በረንዳ በጫት ቆጮና የሸክላ ውጤቶች የሚገበይበት ቦታ ነው። 24 ሰዓት ጫትና እብድ ብትፈልግ አታጣም! አብዶ በረንዳ።

ከአብዶ በረንዳ አጠገብ ወራባ ተራ አለልህ። አላቂ ምግብ ነክ ዕቃዎች በጅምላ የምትገበይበት። ወራባ በስልጢኛ፣ በሀደሪኛ በሶማሊኛ (ጅብ) ማለት ነው። ጅብ ተራ ብለህ ተርጉምልኝ ወራባ ተራን። ስፍራው ይህን ስያሜ ያገኘው ድሮ በግንትር  እቃዎች በመታወቁ ነው። ዛሬ ባይኖርም በፊት በፖሊስና ህብረተሰብ ኘሮግራም ላይ ሸክላ ፈጭተው በርበሬ፣አንዳች ነገር ጨምቀው ዘይት፣ ሙዝ አቡክተው ቅቤ ብለው ሲሸጡ ተይዘዋል ሲል ያሳወቀህ ወንጀለኞች… መሠረታቸው ከዚህ ስፍራ መሆኑንም አልዋሽህም።

ቦንብ ቦንብ የሆኑ ነጋዴዎች፣ ከዱባይ፣ ከቻይና… ሸቀጥ፣ ሀገርህ የሚያመርታቸውን ዕቃዎች አስመስለው አሰርተው አስመጥተው የሚያከፋፍሉት በመርካቶ ቦንብ ተራ መሆኑን ሳልገልፅልህ አላልፍም። ይሄንንና መሰል ሁኔታዎች ታዝቦ ማደግ ቀልድ አይደለም። ለዚህም ነው የመርካቶ ልጅ አዲስ የሚሆንበት ጉዳይ የለም ምልህ… አለ የተባለ የዘመኑ ምርጥ ምርጥ ሞዴል ሞባይልና ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ተያይዞ ለሚመጡ ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎች ቅርብነቱ ምንም ጥርጥር የሌለው ሀቅ ነው። የመርካቶ ልጅ ሀረር ሳይሄድ ስለ ሀረር ይተነትንልሃል።

ለምሳሌ:- አንተ የአምር አብዱላሂን ሀገር ሐረር ሄደህ ግንቧን ማየት ባትችል፣ የሀደሬዎችን የቤት አሰራራቸውን፣ የመጅሊስ መደቡን፣ የግድግዳ ላይ ጌጦቻቸውን፣ የእደ ጥበብ ውጤታቸውን አይተህ ለማድነቅ ባይሳካልህ፣ የፍቅር ሀገር ድሬን የአኗኗር ገሯምነቷን መጎብኘት እጅ ቢያጥርህ… ና ወደ መርካቶ። በብዛት የብሄሩ ተወላጆች የሰፈሩበት ሀደሬ ሰፈር ፣ የሀረርጌና የድሬ ፍቅርና አኗኗር ዘይቤ ድባብ በናሙናነት ቁልጭ ብሎልህ  ታገኘዋለህ።ሀረርና አጎራባቾቿ አፈራሽ የሆኑ የጫት ዘሮችን መቃም ቢያሰኝህ ሀረር ሳትሄድ እዚሁ አለልህ በመርካቶ ሀደሬ ሰፈር። ትንሽ ወረድ ብለህ… ፎዴ ተራ ግባ ደግሞ የተለያዩ ሰልባጅ ጫማዎችና ፣ የሸክላ ውጤቶች በገፍና በቅናሽ ዋጋ … ታገኛለህ፣ ካልባነንክ ትገነተራለህ።በፊት ከፊት ለፊቱ ሜዳ ሆቴል የሚሰኝ የሜዳ ላይ ምግብ ቤት ነበረ። ከአንድ ጉርሻ አንስተህ እስከፈለከው ድረስ የሆቴል፣ የኬክ ቤት የደሀን፣የሀብታምን፣ የክርስትያን፣ የሙስሊም፣ ምግቦች በአንድ ማዕድ በፍቅር ተሰባስበው ሲሸጡ ከመመልከትህ ባሻገር ልዩነት አልባ አንድነትን ትማራለህ በመርካቶ ጉርሻ ገበያ። 

  ከሀብታም መልስ ላይ ታድመህ፣ የሙሽራና የሚዜዎቹ ባህል ልብስ ውበቱ ካስደመመህ አትጠራጠር! ጥጡ ከአፋር ቢለቀምም፣ በምንጃር ተወላጅ ተፈትሎ በእንዝርት ቢሾርም ፣ በዶርዜ ልጆች ተሸምኖ ጥለቱ ቢያምርም፣ ድንቅ አድርጎ ሰፍቶ የሸጠላቸው የመርካቶ ሸማ ተራ ባለ ሱቅ ነው።

መርካቶ እንደ ቃሉ ቀላል ስፍራ አይደለም… የሌለበት ጉድ፣ የለም በዚህ ሁሉ መሀከል ማደግ ቀልድ አንዳልሆነ አሁን የተረዳህ ይመስለኛል። ሌላው ደግሞ መርካቶ ያላፈራቸው አይነት ሰዎች የሉም። ከከባድ ነጋዴዎች ጀምረህ በተለያዩ የህይወት ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ለሀገርህ እጅግ አስፈላጊ የምትላቸው ሰዎች ሞልተዋል። ከትልቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአዛውንት እስከ ጨቅላ፣ ከባለ ሀብት እስከ መናጢው፣ ከጤነኛው እስከ እብድ… ሁሉንም የህብረተሰብ ስብዕናዎች ሁሉንም አይነት ብሄር ብሔረሰቦች ጠቅልሎ የያዘ አንድ ክልል ቢኖር መርካቶ ሰፈሬ ነው።
በቃ አልነዝንዝህ እንደ ብሂሉ እኔም እደግምልሃለው… "የትም ተወለድ መርካቶ እደግ"ብዬ ተሰናብቻለው!
ወገሬት!!

Monday, May 16, 2016

"ህ ል ም"

#ሳteናw

<<ከግልገል ሱሪ(ፓንት) ውጪ እናቴ እደወለደችኝ እርቃኔን እንዴትና? በምን? መልኩ እንደተገኘው በማላውቀው ሁኔታ ዙሪያዬን በከበበኝ ፅልመት ተውጬ በሚያረገርግ አግዳሚ ጣውላ ላይ ተቀምጬ… እራሴን አገኘሁት።

ወደ ዙሪያዬ እየተዟዟርኩ ገላመጥኩ ምንም የሚታየኝ ነገር የለም። የት ነው ያለሁት? እንዴት አዚህ ፅልመት ውስጥ እርቃኔን ልገኝ እንደቻልኩ ምንም የማስታውሰው ነገር የለም። ግራ ተጋብቻለው። የተቀመጥኩበትንና በእጆቼ ዳርና ዳር የያዝኩትን ጠጣር ነገር በመዳሰስ ለማወቅ ሞከርኩ። የተቀመጥኩት ጣውላ ላይ እንደሆነ ተገነዘብኩ በቀኝና በግራ እጄ ዳርና ዳር የተደገፍኩትም በጎኑ የቆመ ጣውላ መሆኑን አወኩ። አሁንም ያለሁበት ቦታ ሚስጥር እንደሆነብኝ ነው። እግሮቼ የረገገጡትንም ወለል ቀኝ እጄን ቁልቁል ሰድጄ በዳበሳ አሰስኩ እሱም እርጥበት አዘል ጣውላ ሆነብኝ። የተሸከመኝ ቁስ መላ አካሉ ጣውላ ከመሆኑ በላይ በቆመበት በዝግታ ያረገርጋል። እንዴ? ምንድነው ነገሩ? የት ነው ያለሁት? ማን ነው እዚህ ያመጣኝ?

እዚህ ከመገኘቴ በፊት ያሳለፍኩትን ጊዜ ለማስታወስ ሞከርኩ ከማንነቴ ውጪ ያሳለፍኩት የህይወት ትውስታ ትዝ ሊለኝ አልቻለም። የተደገፍኩትን በጎኑ የቆመ ጣውላ ሁለቱንም እጆቼ ወደ ፊት አንሸራተትኩ በሄድኩ ቁጥር እየጠበበ ሄዶ አንድ ነጥብ ላይ ሁለቱም እጆቼ ተገናኙ። ምን እንደሆነ መንም ሊገፅልኝ አልቻለም! ግራ መጋባቴ ጨመረ። ባለወኩት ሰበብ በተገኘሁበት አስደንጋጭ እንቆቅልሽ በጣም ፈራሁ!

ሞቼ ተቀብሬ ነው እንዳልል… ተቀምጬ ከተደገፍኩበት  የጣውላ ዘር ውጪ ዙሪያዬ ነፃ ክልል ነው፣ ከፈን የተባለ የጨርቅ ዘርም በዙሪያዬ የለም፣ በየመሃሉም ሽው እያለ ፊቴን የሚዳብሰኝ ስስ አየር… አለ። ወይኔ ጉዴ እሺ የት ነው ያለሁት…?  ኡ… ኡ! ብዬ… መጮህ ቃጣኝ። ደግሞ ያለሁበትን ሳላረጋግጥ መጮሁ ፋይዳው አልታይህ አለኝ። እጅግ ብቸኝነት ተሰማኝ። ይህን ስሜት ከዚህ ቀደም አላውቀውም። የሰው ዘር የተባለ ናፈቀኝ። በዚህ ሚስጥራዊ ብቸኝነት ውስጥ ጠላቴም ቢሆን አጠገቤ ቢሆን ብዬ ተመኘው…!

ቀስ በቀስ አይኔ ከፅልመቱ ጋር ትንሽ ሲላመድ ለውጥ ያሳየኝ መሰለኝ… አንጋጥጬ ተመለከትኩ እንደ አከንባሎ የተከደነብኝን ፅልመተ ሰማይ እዚህም አዚያም ሸንቁረው ብልጭ ድርግም የሚሉ ኮከቦች ታዩኝ። ቀብር ውስጥ እንዳልሆንኩ አረጋገጥኩ። ይህም ትንሽ መረጋጋት ፈጠረልኝ። ከቀብር ውስጥ በማይሻል ሁኔታ መኖሬን ሳውቅ መልሶ ደግሞ ረበሸኝ። መልሼ ለመረጋጋት ሞከርኩ።

አንዳች ድምፅ ሰማው። ትኩረቴን ጆሮዬ ላይ ሰብስቤ ቀሰርኩት … አቅጣጫውን አጤንኩ… የተቀመጥኩበትን ጣውላ ከተሸከመው አረግራጊ ወለል የመጣ ድምፅ ነው። ድምፁ አዲስ አልሆነብኝም። የባህር ወጀብ ስስ ድምፅ ነው። ከዳበስኩት፣ ካየሁት፣ ከሰማሁት አንድ ነገር ብቻ ማወቅ ቻልኩ… የመሬት ዘር የተባለ ደረቅ ምድር በሌለበት በማላውቀው ውቅያኖስ ይሁን ባህር ላይ ተንሳፋ በቆመች ትንሽዬ ጀልባ እርቃኔን መቀመጤን። ይህን ብቻ አወኩ። ወደ እዚህ ከየት እንደመጣው? ለምን እንደቆምኩ? ወዴት እንደምሄድ? አሁንም አላውቅም ወይም ትዝ አላለኝም።

ያለሁበትን ነባራዊ ሁኔታ ባውቅም ቅሉ፣ መነሻና መድረሻዬን አለማወቄ ህሊናዬ እረፍት ነሳው። ግራ ተጋባው። ተስፋ የተባለ ሁሉ በዚህ ብቸኝነት ውስጥ አልታይህ አለኝ። የጀልባው ማረግረግ አንዳች ተስፋ የሚቸረኝ ይመስል… በምኞት አደመጥኩት። ከመወዝወዝ ውጪ መልስ የለውም። አይኔን ወደ ሰማዩ አንጋጥጬ ቀረው… አተኮርኩበት… ያተኮርኩበት የሰማይ ግድግዳ ላይ ሴኮንዱና ደቂቃዎቹ የሚዘውሩ ሰዓት
ከየት መጣ ሳልለው ገጭ ብሎ መቁጠር ጀመረ። ተስፋዬን ወደ ሰዓቱ አዞርኩ። የደቂቃው መዘውር ሙሉ ሰአት ላይ ሲደርስ አዲስ ነገር ሊፈጠር ይችላል በሚል ተስፋ። የመጨረሻዎቹ 5 ሴኮንዶች ላይ ደረስኩ… የልብ ምቴ ይሰማኝ ጀመረ … 55… ድው ደው… 56… ድው ደው… 57…ልቤ ይደልቃል…
58… ድው ደው… 59… ድው ደው… 00…

ልክ በዚህ ቅፅበት ይህ ሁሉ ተከሰተ…
አይኔ አይቶት የማያውቀው ብርሃን በዙሪያዬ ፈነጠቀ። እንዴት እንደሆነ ባላወኩት መልኩ ከወተት የነፃ ልብስ ተጎናፀፍኩ… ጀልባዬን የተሸከማት አረግራጊው የውሃ ሜዳ… ቁልቁል… ወደ ሚንዥቀዥቅ ፏፏቴ ተለውጦ… ከጀልባዬ ጋር ይዞኝ ቁልቁል ከነፈ። ከቀኝና ከግራዬ ልዩ ልዩ የፍራፍሬ ተክሎች ከውሃው ውስጥ ብቅ ብቅ ይሉ ጀመር… በድንጋጤ ይሁን በደስታ… ሱብሃን አላህ!! ብዬ ጮህኩ። አንደበቴን ጥሶ የወጣው ድምፄ ከእንቅልፌ አባነነኝ።>>ብሎ ዛሬ ጓደኛዬ ያየውን ህልም ነገረኝ።
ህልሙ ቅዠት ይሁን ምን እስካሁን ፍቺው አልተገኘም።
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••√
<<ሞቼ ተቀብሬ ነው እንዳልል… ተቀምጬ ከተደገፍኩበት  የጣውላ ዘር ውጪ ዙሪያዬ ነፃ ክልል ነው፣ ከፈን የተባለ የጨርቅ ዘርም በዙሪያዬ የለም፣ በየመሃሉም ሽው እያለ ፊቴን የሚዳብሰኝ ስስ አየር… አለ።>>