Tuesday, May 10, 2016

ከሀይገሩ ጣራ ስር።

#ሳteናw
  ከአራዳ ህንፃ ጀርባ፣ ሚድሮክ ካጠረው የማዘጋጃ ሜዳ ፊት ለፊት ባለ የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ስፍራ ግራ በተጋባ ሁኔታ ቆሜያለው … የተሳፋሪዎች ሰልፍ እንደ መስኖ ቦይ በመደዳ ተደርድሯል። እድሜ ለታክሲ ማህበረሰቦች አስኮ ፣እንቁላል ፋብሪካ፣ መድኋኔአለም፣ እያሉ  በአንድ መስመር የሚጓዘውን ተሳፋሪ እንደ ፍላጎታቸው ቆራርጠው አሰልፈውታል። የከፋፍለህ ግዛ ርዕዮተ አለም በታክሲሾፌርና ረዳቶችም ጋር ስራ ላይ ይውላል!! ግድ የለም ይከፋፍሉን፣ እንደፍላጎታቸው እየዘወሩ የሚፈልጉበት ድረስ ይንዱን፣የሚፈልጉበት ያድርሱን!! ብቻ አንድ ቀን ህዝቡን አንድ ላይ ይዞ የሚዘውር እስኪመጣ!! ለወትሮው ከፒያሳ አስኮ የታክሲ ችግር ብዙም አልነበረም። ዛሬ ምን እንደሆነ እንጃ የአስኮ ታክሲ የውሃ ሽታ መሆኑ ግር ብሎኛል፣

"ዛሬ ቀን 19 ነው እንዴ?" ራሴን ጠየኩ።

አረ አይደለም  12 ነው!" አለኝ ሌላው ማንነቴ።

"እእእ ታዲያ አልሸሹም ዞር አሉ አትለኝም?" አልኩት።
በታክሲ ችግር ምክኒያት ቀኑን መገመት የኔ ብቻ ሳይሆን የመላው አዲስ አበባ ነዋሪ ግምት ነው። እያንዳንዱ ታክሲ ከኋላ መስታወቱ ላይ በትልልቁ በሚያፅፉት ቀን ቁጥር መሰረት በቀኑ ያለስራ ይቆማሉ። እንኳን በፈረቃ እየቆሙ ሁሉም ስራ ላይ ውለውም ከመጋፋትና ከመሰለፍ አልዳንን። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ!! አሉ ጋሽ አበው…

የምመርጠው ሰልፍ ጠፍቶኝ ከተወዛገብኩ ቡሃላ የሲጋራ ሱሴ እንደሆነ በከንፈሩ የተለበለበ እንጨት መምሰል ነቄ ያልኩበትን  ተራ አስከባሪ የአስኮን የሰልፍ ረድፍ ጠይቄ ከሰልፉ ተቀላቀልኩ። ተሰላፊው ሙጫ ላይ የቆመ ይመስል ሰልፉ ንቅንቅ አልል አለ። ከኔ ሰልፍ ጎን በሌላ ረድፍ የተሰለፉት ጥንዶች፣ ሴቷ ያለ ማቋረጥ ትለፈልፋለች። እትትዋን ታስነካዋለች። ስታወራ መላ አካሏ ምላስ ይመስል ዉንውን ይላል። የመለፍለፍ ሱስ እንዳለባት ወዲያው ገባኝ። ወንዱ በተሰላቸ ስሜት ይሰማታል። ትኩረት እንዳልነፈጋት ለማሳየት አስሬ እያዛጋ ጭንቅላቱን በአዎንታ ይነቀንቅላታል። አስሬ የሚስዛጋው የሱ ሱስ ደግሞ ምን ይሆን? ሰልፉ አሁንም አልተነቃነቀም። ሰዓቱን ሳየው ሄዷል ግራ ገባኝ … ሲስተር ጋር ድውዬ ለማዘር እየመጣው እንደሆነ ንገሪያት ብዬ ትንሽ  ቆምኩ።

ከፊቴ ተሰልፋ የነበረች ተሳፋሪ አንድ ነገር ያገኘች ይመስል ቱርርር ብላ ከሰልፉ ሰንሰለት ተገንጥላ ሄደች። በአይኔ የአቅጣጫዋን መዳረሻ ስመለከት አንድ ባዶ ሀይገር አፉን ከፍቶ ቆሟል። አሃ አስኮ መሆን አለበት ብዬ ሳላስነቃ ተከተልኳት … ግምቴ ልክ ነበር። ወደ አስኮ ተሳፋሪ ይጠራል ወያላው። ሀይገሮች ምንም ሰው እየለቀሙና እያንጠባጠቡ ቢጎተቱም  አማራጭ ስላልነበረኝ ገብቼ ጥግ ላይ ካለው መቀመጫ ተቀመጥኩ። የመኪናው ወንበር በሰው ሞላ፣ በሀይገሩ  ኮርኒስ ላይ ጫፍናጫፉ በተጣበቀው ሚዛን መጠበቂያ የብረት ዘንግ ተንጠልጥለው በቆሙ ተሳፋሪዎችም ሞላ አይገልውም። በመጨረሻው አንድ ተሳፋሪ ገብቶ  ጭንቅንቁ ቢጨንቀው ወዲያው ወረደ።

"ለመመዘን ነው እንዴ የወጣሀው?" አለው ረዳቱ።

"በቃ ሞላ እኮ ለምን አንሄድም?" ደፈር ያለ ተሳፋሪ ረዳቱ ላይ ሲያንባርቅበት ረዳቱ ሹፌሩ ለመጥራት ፀጉሩን እየቋጨ ሄደ። ረዳቱ አሳዘነኝ ተሳፋሪም ሹፌርም ጠርቶ እንዴት ይችለዋል።

የሀይገር ሾፌርና ረዳቶች በአብዛኛው አጠቃ ሱሴ ናቸው። አጠቃ ሁሉንም ሱስ ለሚተገብሩ ለካምፓስ ተማሪዎች የወጣ ስያሜ ነው። አጫሽ፣ጠጪ፣ቃሚን ይወክላል። የሀይገር ሾፌርና ረዳቶችን ግን (አጠቃ + በ) ብያቸዋለው (በ) በምትፈልጉት ቃል ስሩባት። ሌላው አጠቃበ ዎች ለሱሳቸው ገንዘብ ይሙላላቸው እንጂ ለተሳፋሪ ምቾት ደንታም የላቸው። ተጨናንቆ የቆመን ተሳፋሪ እንኳ እነሱ በሚፈልጉት መልኩ እንዲቆምላቸው ለገፀ ባህሪይ ተዋናይ በእንቅስቃሴው ድርጊቱን  እንደሚያሳይ ዳይሬክተር እንዴት መቆም እንዳለበት በስእላዊ መግለጫ ያሳዩታል።የሀይገር ውስጥ ዳይሬክሮች ብያቸዋለው። ለሲኒማው እድገት ሳይሆን ለሱሳቸው እድገት የሚታትሩ ዳይሬክተሮች። እንደዚህ ቁም ፣ይሄን ዘንግ በቀኝ እጅህ ያዝ። አንዳንዴማ ድርጊታቸው የሰርከስ አሰልጣኝ ሁላ ያስመስላቸዋል። ተሳፋሪው የተቃወመ እንደሆነ

"ካልተመቸህ መውረድ ትችላለህ!" ሲሉ አማራጭ ያቀርብለታል አልወርድም ካለ፣ ሹፌር ሆዬ ሞተሩን አጥፍቶ ቁልፉን ነቅሎ ይወርዳል። የሚገርመው እኮ እንደዚህ ሰውን እንደ እህል ጭነው እየሰሩ የቲሸርት ለውጥ እንኳ ሲያሳዩ አለመታየቱ ነው። ወንዱ ተሳፈሰሪ ፍሬው እስኪሟሟ ሴቷ ተሳፋሪ ጭኗ እስኪላላ አጣብቀው ጭነው ቢለወጡ አንድ ነገር ነበር። አረ ምን ቢለወጡ! እንደንቀሳት የማይለቅ ቲሸርታቸውን በለወጡ። በሀይገር በሹፌሩና በረዳቱ መካከል የሚለወጥ ነገር ቢኖር የመኪናው ጎማ ብቻ ነው። ይህ ተሽከርከሰሪ ከቻይና እንደመጣ አይረባም የሚል ትችት ገጥሞት ነበር። ትችቱ ስህተት እንደነበር ለማረጋገጥ ቺፍ ሜካኒክ መሆን አላሻም። ለስምንት አመት እንዳ አንበሳ አውቶብስ ሰው አጭቀው እየጫኑ ቀጥቅጠው ሰርተውበታል፣ጎማ ቀይረውበታል፣ ሱሳቸውን አስፋፍተውበታል። ሀይገር ባስ ተሳፋሪን አሰቃይቶ ከማጓጓዙ በተጨማሪ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ በጎማ መለወጥ ብቻ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

ሾፌሩን ሊጠራ የሄደው ረዳት ቀረ። የሀይገሩን መሙላት በናፍቆት መጠበቄ ሲያበቃ ሾፌርና ረዳትን በናፍቆት ወደ መጠበቅ ተዛወረ።

"ይሄኔ ሺሻውን ሊያፈነዳ ሄዶ ነው" አለ ሌላው ተሳፋሪ እየተበሳጨ።

"አረ አንዳች ያፈንዳው!እቴ" አሉ መቀመጫዋ የሚያምር ወጣት መቀመጫዋን የለቀቀችላቸው እናት። ሾፌሩና ረዳቱ እየተጣደፉ በየበራቸው ገቡ። የተሳፋሪውን ቅሬት ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ጉዞ ጀመርን…

  አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ተሳፋሪ በፌስቡክ ሜሴጅ ይፃፃፋል። አያያዙ በፌስቡክ ሱስ እንደያዘው ያሳብቃል። ከጣቱ እስከ ትኩረቱ በሞባይሉ ስክሪን ተጠዷል። ይሄኔ አንዷን እየጀነጀነ ነው። አንድ ሰሞን አኔም በፌስ ቡክ ሱስ ተጠምጄ ነበር። የኔውማ አይጣል ነበር። ሳልዝበርግ ኦስትሪያ እና ሪያድ ሳውድ አረቢያ ከነበሩ ሁለት ቺኮች ጋር በመቸካቸክ የተጀመረው የሶሻል ኔትዎርክ ፎንቃ ረጅም ጊዜ አጃጃለኝ። ስንትና ስንት ሌሊት ነጋብኝ። የዛኔ ሞባይሌ ኖኪያ ነበረች። ስፃፃፍ ስፃፃፍ የጣቶቼን የጠቅጠቅ ውርጂብኝ መቋቋም ያቃተው በተንቦርድ ሁለት ጊዜ እንደ አንበሳ ጫማ ሶል ማስቀየር ግድ አለኝ። አውራ ጣቴም ባንድ በኩሉ ተዛነፍብኝ። አላህ ይስጣት ውጪ የነበረች እህቴ አውራ ጣቴ ሳትቆመጥ ተች ስክሪን ስማርት ፎን ልካ ገላገለችኝ። አሁን እንዲህ ሊያስጠላኝ!!።

  አይኔን ከባለ ፌስቡኩ ልጅ  ነቅዬ ወደ ሌላው ትዕይንት ወረወርኩ። ለሴትየዋ መቀመጫዋን የለቀቀችው ባለ ቆንጆ መቀመጫማዋ ኮረዳ በሰው ጫካ ውስጥ ገብታ ተሰንጋለች። በዙሪያዋ የነበሩ የአዳም ዝርዮች ፊታቸው ወደሷ አዙረው ቆመዋል። ዙሪያዋን በፍትወት ንዳድ ባኮቦኮቡ ሙርጥ የተከበበችው ባለ ቆንጆ … መቀመጫዋን ከጎኑ ሙርጦች መሸሸግ የምትችል ይመስል ትቁነጠነጣለች። በዚህ ስትሸሽ በዚህ በዚያ ብትል በወዲህ … የጭንቀቷ ብዛት ፊቷ ድልህ መሰለ። ሙርጣሞቹም እንዳልተመቸው በመሆን ይቁነጠነጣሉ። ሆን ብለው ተለጥፈዋት ልብ እንዳላለ ሰው አይናቸውን ሌላ ቦታ ተክለዋል። እንዳይጣሉ ሰጋው። በሴት የመጣ ፀብ መቆሚያ የለው። ለዛውም መቀመጫዋ በሚያምር፣ መቀመጫዋን ለታላቅ አክብራ በለቀቀች ሴት። የነዚህ አዳሞች ተግባርም ሱስ እንሚሆን በመሀመድ ሰልማን መፅሀፍ አንብቤዋለው። አቦ ሀገራችንን የሱስ አብዮት ገደላት እኮ!!

ባለ ቆንጆ መቀመጫዋ ልጅ አስኮ ሲደርስ የአዳምን ዘር በሚያሳፍር መልኩ…ባለ ሙርጦቹን አጥረግርጋቸው ወረደች።
"ስሙ የትራንስፖርት ችግር እንጂ የቁ* ችግር አይደለም በዚህ ያሳፈረኝ! በረት መሰላችሁ ምድረ ከብት!… በሩ ላይ ቆማ ስድቧን …ቀጥላለች… ረፍዶብኝ ስለነበር ስድቧን ሳትጨርስ ወደ ቤት ሄድኩ።

No comments:

Post a Comment