Wednesday, July 13, 2016

"ቀ ለ ማ ተ … አ ዳ ም"

" ቀለማተ አዳም  "
#ሳteናw

   አንዳንዴ ሳስበው ያለው የእውቀት መጠን በ30 ሚሊዮን መፅሀፍት፣ በአንደኝነት የሚመራው የኮንግረስ ላይብሪ ወይም በ22 ሚሊዮን መፅሀፍት የሚከተለው የቻይናው ላይብረሪ…  ይመስለኛል…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

     ከፈለገ የአይምሮ ዶክተር፣ ከፈለገ ፖለቲከኛ፣ ከፈለገ ታሪክ አዋቂ፣ከፈለገ ሰዓሊ፣ ከፈለገ አንጥረኛ፣ ከፈለገ ፈላስፋ … የፈለገውን እየሆነ መፃፍ እንዲችል… አስችሎታል። አንዳንዴ ሳስበው በ 30 ሚሊዮን መፅሀፍት፣ በአንደኝነት የሚመራው የኮንግረስ ላይብሪ ወይም በ22 ሚሊዮን መፅሀፍት የሚከተለው የቻይናው ላይብሪ…  ይመስለኛል… ያለው ጥልቅ እውቀት…

በ1950 በአዲስ አበባ ተወልዶ … በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪውን… ማስተርሱን በውጪ ባለ የትምህርት ተቋም አግኝቷል። ደራሲ አዳም ረታ።

  አዳም ረታ፣ የራሱ በሆነ የአፃፃፍ ስልቱ ይታወቃል። የፅሁፍ ስልቱ አወራረድ እስክትግባባው እያወዛገበ ቢያደክምህም… ከተግባባከው ቡሃላ እንዴ እያሳቀ፣ እያስገረመህ፣ እያመራመረህ፣… በመሀል ራሱን እያደነቅከው በሚቀያየር ስሜት ከድረሰቶቹ ጋር ትንሳፈፋለህ። ድንቅ በሆነ የአተራረክ ስልቱ… ልብ የማትላቸው ሁኔታዎችን በሚያስደምም አገላለፅ እየፈለፈለና እየለቀመ ከራሱ ጥልቅ አመለካከት ጋር አሟሽቶ፣አዋዝቶ በመተረክ  ለስነ ፅሁፍ የተፈጠረ መሆኑን አስመስክሯል።

የቃላት ሀብቱን መጠን በመፅሀፎቹ ደልዳላነትና አዲስ በሚሆኑ …  ቃላት ብዛት ያስመሰከረው አዳም ረታ ከአንባቢ ጋር የተዋወቀባቸው ቀደምት ስራዎቹ :-በጋዜጦች ላይ ከሚሳተፍባቸው ግጥሞችና ፅሁፎች ሌላ  "አባ ደፋርና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች" 1977። "ጭጋግና ጠል" 1980" (ከሌሎች ደራሲዎች ጋር የታተሙለት ስለነበር እንደ ወጥ ጥራዝ አብዛኛዎቻችን አናውቀውም) ማህሌት/1981/፣ ግራጫ ቃጭሎች/1997/፣አለንጋና ምስር፣እቴሜቴ ሎሚ ሽታ፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር(2004)፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ(2004)፣ ህማማትና በገና(2005)፣ እና መረቅ /2007/ናቸው። አልዋሽህም ሁሉንም ስራዎች ባላነባቸውም ግማሽ ያህሉን አንብቤያቸዋለው፣(እድሜ ለጀለሱካዬ ሱሌ)

(…ዳኛቸው ወርቁ በ“አደፍርስ” የኢፒሶዲክ ሕግጋትን አጋምሶ ለማስተዋወቅ ከሞከረ ወዲህ በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በኢፒሶዲክ ተሟልቶ የተገኘ ድርሰት “ግራጫ ቃጭሎች” ነው። ይህቺ የአለማየው ገላጋይ ገለፃ ነች)።

በተለይ የግራጫ ቃጭሉን ገፀ ባህሪይ ዝምተኛው፣ ብቸኛው፣ ፈላስፋው፣  ከጎልሏቷ የሚቀመጠው መዝገቡን እንዴት ስተዋለው? የመረቁ አልአዛርም አይጠፋኝም…

   አዳም፣ በዚሁ፣አመትና ባሳለፍነው ወር ለአንባቢዎቹ… በቅርፅና ይዘቱ፣ የተለየ በገፅ ብዛቱ በኢትዮጲያ የረጅም… ልብወለድ ታሪክ፣ ክብረ ወሰን የነቀነቀቀ አዲስ መፅሀፍ ጀባ ብሏል። የስንብት ቀለማት በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው ይሔው አዲስ መፅሀፍ በንፋስ ስልክ ዙሪያ ያሉ ማህበረሰቦች… ውስጥ የመረጣቸውን ገፀ ባህሪያት… ሁሉንም ወክሎ… የመጡበትን የታሪክ ዳራ እየመዘዘ… ከነ ተለያየ አመለካከታቸው ጋር፣ በውብና ጥልቅ የስነ ፅሁፍ ችሎታው በራሳቸው አፍ ይተርከዋል። የስንብት ቀለማት በ960።ገፆች ፣ በ46 ንዑስ ምዕራፎች፣ በ8 አቢይ ምዕራፎች፣ በ350 ብር፣ ለገበያ በቅቷል።ምርጥ መፅሀፍ ነው አንብበው ግብዣዬ ነው…

የታመቀ የስነፅሁፍ ዛር የሰፈረብህ ከሆን ደግሞ…የአዳምን መፅሀፎች በደንብ እንድታነብ እመክርሃለው… ምክሬን ስትተገብር… የታመቀ  ዛርህን እንደ ድኝና ቀበርቾ ጢስ ዛርህ አስነስቶ… እንድትፅፍ እንድትቸከችክ… ስታዲያም ካጨናነቀ ደጋፊ ባልተናነሰ… ሞራል… ይሰጥሃል፣ አዳፍነህ ካፈንከው የስነፅሁፍ ተሰጦ ያነቃቃሃል… ቸክችክ ቸክችክ ይልሃል።
ወገሬት!!

Tuesday, July 12, 2016

"የማዕረጎች ሁሉ ማዕረግ"

"የማዕረጎች ሁሉ ማዕረግ"
#ሳteናw

…  አንድ ጉርሻ ጠቅልዬ ስጎርስ … አታምንም…(ትን ብሎኝ ፣ ፍንግል፣ድፍት የምል ይመስላታል… ካሁን አሁን… አንቆት ውሃ ሊጠይቀኝ ይችላል በሚል… … ልትጎርስ…  የጠቀለለችውን ጉርሻ… አየር  ላይ እንዳንጠለጠለች… ጉርሻዬ በጎሮሮዬ ተንሸራቶ እስኪወርድ… በተጠንቀቅ… ትከታተላለኛለች… መዋጤን ስታረጋግጥ… አየር ላይ ያስቀረቻትን ጉርሻ… (ትጎርሳታለች) !!የምልህ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል!! … አትጎርሳትም…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

   በእንግሊዝ ትልቅ ስኬት ከሚሰኘው ሰርነት(ser) ማዕረግ ይበልጣል። ማርስ ላይ ስም ከሚያስፅፈው ሎሬትነት ይልቃል። አለማዊ ዕውቀት ከሚያስጎናፅፈው ፕሮፌሰርነት ይበዛል።  ከማዕረጎች ሁሉ ይጠጥራል። ይህ ፆታ ለይ ማዕረግ ለራስ በራስ በሆነ ጥረት እንደ ሚገኙት ኘሮፌሰርነት፣ዶክተርነት፣ ወይም ሎሬትነት ማዕረጎች ከትልልቅ ትምህርት ተቋም… አልያም መሰል ድርጅቶች አይገኝም።

…  ያለምንም፣ የቀለም እውቀትና የሀብት ስኬት ለወላድ ሔዋንያን ተፈጥሮ የምትቸረው ማዕረግ ነው !እናትነትን! ለራሷ ሳይሆን ለአብራኳ ክፋይ የራሷን ህይወት፣ ደስታ፣ምቾት፣ጥጋብ፣ አሳልፋ በመስጠቷ  የምትጎናፀፈው ማዕረግ ነው!! እናትነት…!!የማዕረጎች ሁሉ ማዕረግ።

  እናት ለልጇ መኖር፣ በልጇ የእውነት ደስታ ሚሰማት፣ ስትወልደው አይደለም። ዶክተር የሁለት ወር ቅሪት ነሽ (ዘመናዊ እናት ከሆነች)ካላት፣ ወይም ነብሰ ጡር መሆኗን ካወቀችበት፣ ቅጽበት ይጀምራል።
ከዛስ… ሆዷ ውስጥ ያለው ፅንስ ተንፈራግጦ ሲረግጣት  በደስታ ትፈድቃለች። እስክትወልደው ድረስ እርግዝናዋን ትጠነቀቅለታለች። ህመሟን ውጣ ምቾቱን ትጠብቃለች።
መውለጃዋ ሲደርስ ልቧ ከበፊቱ እጥፍ የደስታ ድቤዋን ትደቃለች። በወሊድ ወቅት፣ ያስጮሃት፣ ያስጨነቃት፣ ምጥ ስትገላገል… ይህን…  ረስታ ከነደሙ በፈገግታ ከአዋላጅ እጅ ትቀበላለች። ስታጠባው…ወተት የሞላው ግቷ…  አፍኖ ይገለው ይሆን?… በሚል ስጋት የምታደርገው ጥንቃቄ ቦምብ አምካኝን ታስንቃለች። የራሷ ጉንጭ ደርቆ፣ ስለልጇ ድንቡሽቡሽነት ትተክዛለች። ህፃኑ ድክ ድክ እያለ ሲንቸፋቸፍ… ካሁን አሁን ወደቀ! ምን ነካው? ስትል ቀልቧን…ትስታለች። ነጋ ጠባ ከአፉ እየተንዠረገገ የሚወርደውን ለሀጭ በአፏ ትቀበለዋለች፣ መጠየፍ አይነካካትም፣…  ይህ ለልጇ የምከፍለው መስዋዕትነት… ሁለቱም እስካሉ ድረስ ይቀጥላል…  እናትነት… በምንም ብህር እስከ ፅንፍ አይገለጥም… በምንም ውለታ አይመለስም፣ … ።

ስለ እናት ማንሳቴ ከእናቴ ጋር ያደረግነው፣  የሁሌና የማታውን ሁኔታ …ለርዕሴ ማጠናከሪያነት እንዳክለው ገፋፋኝ…

… ክፍት ሆኖ የሚጠብቀኝን…  የግቢውን በር አልፌ … ገብቼ፣ ከውስጥ ቀርቅሬ። … የዋና ቤቱን በር ከፍቼ ስገባ ነው… ፍራሼ ላይ ጥቅልል ብላ ብርድልብሴን ለብሳው… ትኩረቷ እኔን በመጠበቅ… አይኗ በሩ ላይ እንደተተከለ… አይኔና አይኗ ሲጋጭ… ማውቀው!! ከሰላምታና፣ ከስራ ሁኔታ ጥየቃ ቡሃላ… ልብሴን ቀይሬና… አጠገቧ… ተቀምጬ ሞባይሌን መነካካት ስጀምር… እራት ለማቅረብ ጉድ ጉድ ማለቷን ትጀምራለች።
የራሴን ምቾት የጠበቁ ጥያቄዎች አነሳለው…!!
"ውሃ መጣ እንዴ ዳዳ ?"
"አዎ"… ስራዋን እያከናወነች።
"ልብሶቼስ ታጠቡ…?"
"አዎ"።
ዝምታ ሲነግስ ቤቱ ጭር ሲልብኝ…
"ይሄ ቲቪና ሪሲቨር በቃ ተቃጥሎ ቀረ?"
"ማን ያሰራው ታዲያ…?" … ሀላፍትናው አንተን ነው የሚመለከተው በሚመስል ሁኔታ።(ግን ደፍራ አሰራው አትልም፣አስጨንቀዋለው በሚል)
"እንዴ! አሰራዋለው አላለችም እንዴ?"
"ማን?"… ስራዋን አቁማ እያየችኝ።
"ሶፊ ነቻ!!"(እህቴን)
"ምፅ!!የኔ እናት ስራው አልተመቻትም መሰለኝ… ለዛ ነው?!"ስራዋን ካቆመችበት ትቀጥላለች።
"የራሷ ጉዳይ!! ብዬ ተወዋለው ድሮም ስለማንስማማ ትንሽ ነገር ነው /ልገላምጣት፣ልታመናጭቀኝ/የሚበቃን። ሁለታችንም ሀይለኞች ነን። ትንሽ መጨቃጨቅ ስንጀምር፣ የጭንቀት፣ ፈገግታ ታሳየናለች። ለሁለታችንም የማያዳላ ሽምግልና ትቆማለች።

እናቴ እራቱ አቀረበች።

… አብረን ስንበላ… አንድ ጉርሻ ስጎርስ … አታምንም…ትን፣ ፍንግል፣ድፍት የምል ይመስላታል… ካሁን አሁን አንቆት ውሃ ሊጠይቀኝ ይችላል በሚል…ልትጎርስ…  የጠቀለለችውን ጉርሻ… አየር  ላይ እንዳንጠለጠለች… ጉርሻዬ በጎሮሮዬ ተንሸራቶ እስኪወርድ… በተጠንቀቅ… ትከታተላለኛለች…(ብዩ እንጂ)   መዋጤን ስታረጋግጥ… አየር ላይ ያስቀረቻትን ጉርሻ… (ትጎርሳታለች) !!የምልህ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል… ካላጎረስኩህ ትለኛለች… አልሰማትም… አንቺ አልበላሽም ጉረሺው ብዬ በግድ እንድትጎርስ አደርጋታለው… ብዪ…  ብላ!  በሚል ስንጨቃጨቅ… እሷ በቅጡ ሳትበላ እኔ እጠግባለው!!

  በቃኝ ብዬ ስነሳ የሚገጥመኝን ንትርክ አስባለው…!!  ከመነሳቴ በፊት… በአይኔ በቅቶኛል በሚል እለማመጣታለው… "ጀመረህ ደግሞ!" ብላ እንደመገላመጥ ታየኛለች… ቀልቧን ማስከፋት ስለማልፈልግ…  ልምምጤን በአንደበቴ ጀምራለው…!!

"ወላሂ ዳዳ በጣም ነው የጠገብኩት… እየው ካላመንሽ ሆዴን እዪውማ?" ብዬ ቲሸርቴን ገልጬ ሆዴን ነፍቼ አሳያታለው…! 
"አቤት?!ተበርቼ ሰላም…!!  ብላ ትስቃለች…ካካካካ… ። ሳቋን እንደ ሽፋን ተጠቅሜ… ላጥ ብዬ አጄን ልታጠብ  እነሳለው…  ማስታጠቢያው ጋር ሳልደርስ
"እሺ ይሄን ምን ላድርገው…!? " ስትለኝ…  እቆማለው። ድጋሚ ዞሬ… የማለቅስ በሚመስል ድምፅ…!!
"በናትሽ! የአንድ ጉርሻ  ቦታ የለም!!" እላታለው…
የውሸት በሆነ ኩርፊያ ወደ ማዕዱ ትዞራለች። እናትነት ይህ ነው። ምንም ብትበላ የምጠግብ አይመስላትም፣ ጠራርገህ ስትበላ… ካልጨመርኩ… ሌላ ግብግብ… አንድ ስኒ ቡና ከጠጣህ… ካልደገምኩልህ!።

በቃ ሁሌም ብቻዋን አይበላላትም… እንደተነሳው… በቃኝ® ትልና  ታነሳዋለች።

እኔ ሳሎን ቤት ስተኛ አስር አይነት ልብስ ሳትደራርብልኝና… "አረ በቃ አፍነሽ ልትገዪኝ ነው እንዴ?" ብዬ ካላስቆምኳት በስተቀር ብርድ ይነካሃል በሚል ስጋት መደራረብ አታቆምም!! 
እሷ መኝታ ቤት አልጋዋ ላይ ብትተኛም… ልቧ ከኔ ጋር ነው…የኔ ልብ ኢንተርኔት ላይ ተጥዳል…
"አንተ ልጅ በረደህ?" ከመኝታ ክፍሏ ድምፇ ሳስቶ ይመጣል።
"አይይይ" እላታለው… ትኩረቴን ከሞባይሌ ስክሪኔ ላይ ሳልነቅል… ትቆይና… በተመሰጥኩበት…
"ለሽንት ከተነሳህ ልብስ መደረብህን እንዳትረሳ?"…ዝም እላታው… ትኩረቴን በሳበው… ኢንተርኔት… ተውጬ…!
ድሜፄ ሲጠፋባት…!! ሰማከኝ!ሰሉ… ተኛህ እንዴ…??
"አዎ! ዳዳ…፣ ተኚ በቃ!!" እላትና!! ወደ ትኩረት ሰራቂዬ እመለሳለው… አንድ ሶስት ደቂቃ ዝም ካለች ቡሃላ አያስችላትም…
"ወይ ካልሆነ አልጋ ላይ ትተኛለህ…እንዴ?" ይሄኔ… ነቅላለው…
"ጥ!! አረ በአላህ ዳዳ! ምንም አልሆንም በቃ!" በነጭናጫና በጎላ ድምፅ ብዬ ጥያቄዋን ስጋቷን፣ እንድታቆም፣ ፈልጋለው። እንቅልፍ እስኪወስደኝ… ምቾቴን ለመጠበቅ በምታነሳው የጥያቄ ጋጋታ ማስተናገድ ግድ ይለኛል… ስለራሷ ደህንነት ተጨንቃ አትጠይቀኝም! ወይም እንድቸገር አትፈልግም!! ሁሌም ለራሴው!! ሁሌም ለወንድም እህቶቼ ነው ጭንቀቷ። ምን ታድርግ ተፈጥሮ ያደላት ማዕረጓ፣ነው!!  እናትነቷ!!
ረጅም እድሜና፣ጤና፣ጀነት ለማዙካዎቻችን!
ወገሬት!!
 

Sunday, July 10, 2016

"አስመራ ናፈቀችኝ"

"አ  ስ  መ  ራ…  ና  ፈ  ቀ  ች  ኝ!! "
#ሳteናw

… በቀይ ባህር ዳርቻ አሸዋው ላይ ባዶ እግሬን ወክ እያደረኩ የንፋሱ ሽውታ፣ በከፊል ቁልፉን  የከፈትኩት ሸሚዜንና ቁምጣዬን…  እያርገበገበው…  የተፈጥሮን ውበት ሳጣጥም… ከማዶ ደግሞ… ፀጋዬ ሀይለማርይምና የአስመራዋ ቆንጆ! ፊያሜታ ጊላይ  ሲያወጉ፣ ሲሳሳቁ፣ በሰበብ አስባቡ ሲነካኩ … ሲሸፋ*ዱ… እሷ  አየሳቀች "ዋእ! አባቴ ይሙት ደደብ ነህ" ስትለው…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም እንዴ? እርግጠኛ ነኝ መልስህ አዎ ነው። እኔ ግን አልሃለው።  አይቻት የማላውቀውን ሀገር በስዕላዊ ብዕር እንድናፍቅ ሆኛለው። የቷ ሀገር ነች ሳታያት የናፈቀችህ ካልከኝ? መልሴ አስመራ ይሆናል። የቀድሞ ክፍለ ሀገራችን፣የዛሬ ጎረቤት አገራችን አስመራን… ።

አዎ! ተዓምረኛው ብዕረኛ ለናፍቆት የሚያደርሰው ያዩት ሀገር ብቻ ሳይሆን፣ በአይን በብረቱ ያላዩትንም ሀገር፣ በስዕላዊ ብዕር አሳይቶ ማስናፈቅ እንደሚቻል አስመስክሯል!! ይገርምሃል ብዕሩን ከሁሉም አቅጣጫ እንደሚቀርፅ ዲጂታል ካሜራ ተጠቅሞ፣ 3D መነፅር አድርጌ ስክሪን ላይ የምሾፋት እስኪመስለኝ ድረስ አስመራን አሳይቶኛል።

ማን ነው እሱ? ማንነቱን ከመግለፄ በፊት ያስደነቀኝ ስዕላዊ ብዕሩን በስሱ እንየው…

  … እንደ ምላስ ንፁህ የሆኑ አውራ ጎዳናዎቿ ላይ በወታደራዊ ሰልፍ ቀጥ ብለው የቆሙ የሚመስሉ አሸብሻቢ ዘንባባዎቿን፣ የገበያዋን ትርምስ፣ዮሃንስ አራተኛ አየር ማረፊያን፣ አይሮፕላኖቹ ሽቅብ ሲያኮበኩቡ፣ ቁልቁል አፍንጫቸውን አዘቅዝቀው መሬት ሲስሙ፣ የሀዝሀዝን የሴቶች እስርቤት ውጪያዊ ገፅታ፣

   የአስመራን ቆንጆዎች ከሹሩባቸው ጋር ውበት ፈሶባቸው፣ የደሀ ቦርጭ በሚያካክሉ በወርቅ ጌጦቻቸው ተጊጠው በፅዱ ጎዳናዎች ሲተላለፉ፣… በነጭ ወረቀት ላይ የሰካካቸው ስዕላዊ ቃላት… ንባብ ላይ መሆኔን አስዘንግቶ… እነዚህ የአስመራ ቆንጆዎች መርካቶ ውስጥ በአጠገቤ የሚያልፉ መስሎኝ "ናይ አስመሪና ፅብቅቲ" ብዬ… ላደንቃቸው በዘመኑ ቋንቋ (ልለክፋቸው) እስኪቃጣኝ… ድረስ ነው ትረካው መስጦ  የሸወደኝ። (ሳፈላ ነው)።

3ዲው ብዕር… በአስመራ ቤተመንግስት፣ መሰብሰቢያ፣ አዳራሽ ውስጥ፣ በመንግስቱ ሀይለማሪያም የተመራውን የቀይ ኮከብ ዘመቻ ስብሰባ ላይ፣ የተገኙ የደርግ ጄነራሎች፣ ኘሮቶኮል ከጠበቀው አለባበሳቸው፣ አንስቶ እስከ አድርባይነት መሽቆጥቆጣቸው ድረስ ያሳዩትን እንቅስቃሴ … በራሱ እይታና ትዝብት የተወከልኩ የስብሰባው ታዳሚ አድርጎ አስሹፎኛል

   ደግሞ በመሃል አስመራ ታዋቂውን በፓራዲዞን ቡና ቤት ውስጡ፣ ቆሜ… የብርጭቅቆች ግጭጭት፣ ቢራ ሲከፈት (ፕስስስ) ሲል ፣የተስተናጋጆች ጫጫታ፣ ሳቅ፣ትዕዛዝ ቡና ቤቷን ሲያዋክባት… ደግሞ  አንዱ ወንበር ላይ የሻዕቢያ ሰላይ የነበረውን ስዕላይ በራኺ ከነ ሸረኛ መልኩ ተቀምጦ በተመስጦ ሲጋራዉን እየመጠጠ ጀሌዎቹን ሲጠብቅ… በቡና ቤቱ ምድር ውስጥ ለውስጥ እንደ ሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ተፈልፍሎ የተሰራውን የሻዕቢያ ህዋስ ሚስጥራዊ ፅህፈት ቤትን፣ … በሻወር ቤት ውስጥ በማያስነቃ መልኩ የተገነባውና፣ መታጠቢያው ገንዳ ተንሸራቶ ሲከፈት ወደ ፅ/ቤቱ የሚያስገባ በጨለማ የተዋጠ ደረጃዎች የሆነውን… ሚስጥራዊን መግቢያ በር እየመራና… እያስደነቀኝ…  በዚህ ዋሻ ውስጥ ይኖራል ተብሎ የማይገመት እጅግ ዘመናዊነት የተላበሱ፣ ከዳር እስከዳር በተነጠፉ ቀይ ንፁህ ምንጣፎች የተንጣለሉባቸውን፣ ምቹ ወንበር የተሞሉባቸውን ቢሮዎች… ከነ ገለፃው…  ደግሞ
… በቀይ ባህር ዳርቻ አሸዋው ላይ ባዶ እግሬን ወክ እያደረኩ የንፋሱ ሽውታ፣ በከፊል ቁልፉን  የከፈትኩት ሸሚዜንና ቁምጣዬን…  እያርገበገበው…  የተፈጥሮን ውበት ሳጣጥም… ከማዶ ደግሞ… ገፀ ባህሪያቱ ፀጋዬ ሀይለማርይምና የአስመራዋ ቆንጆ! ፊያሜታ ጊላይ  ሲያወጉ፣ ሲሳሳቁ፣ በሰበብ አስባቡ ሲነካኩ … ሲሸፋ*ዱ… እሷ  አየሳቀች "ዋእ! አባቴ ይሙት ደደብ ነህ" ስትለው… የአንደበቷን ለዛ ሳይቀር … ከመሀከላቸው ተገኝቼ በአካል ድባቡን በእውን የምታዘብ… እጄን የኋሊት አጣምሬ በጭንቅላቴ ንቅናቄ አዎንንታዊ ምላሽ እየሰጠሁት የሚያስጎበኘኝ አስጎብኚ እስኪመስለኝ ድረስ ነው በስዕላዊ ብዕሩ እየመራ በምናብ፣ አስመራን ያስከለመኝ… ታዲያ ብናፍቅ ትፈርድብኛለህ?
መፅሀፉ አስመራን በአካል ሄጄ ባላያትም በአይነ ህሊና አሳይቶ … አስናፈቀኝ። እንዲህም ስል…  አስመኘኝ…
ምን ነበር? የኤልሞሌ ወላጆች ድንበሩን ከመስበራቸው በፊት ሰላም ወርዶ ቢሆን ኖሮ? ምነው ይህቺ አስመሪና ከኢትዮጲያ ባለተገነጠለች ኖሮ ?…  ግን ማን ያውቃል? አንድ ቀን… ስንሰለጥንና የአንድነት ሀይል ሲገለጥልን እንደ አውሮፓ በአንድ ፓስፖርት የምንጠቀም ሀገሮች እንሆን ይሆናል!!

እመነኝ ኦሮማይን ሳነብ የንባቡ ሂደት የፈጠረብኝ ምስል… ልክ አንደዚህ ነው… ብዕሩ፣ እንደ ተንቀሳቃሽ ምስል ሆኖ፣ የማላውቃትን ሀገር አስመራን እንድናፍቅ ያደረገኝ…ግን ማነው ደራሲው? በዚሁ መፅሀፍ የመጣ ህይወቱን የከፈለና እስከዛሬ አሟሟቱ በግልፅ ያልታወቀው ድንቁ ብዕረኛ በአሉ ግርማ ነው(ነብስይማር)። ኦሮማይን ካላነበብከው አንብበው እልሃለው!!)
ወገሬት!!

Saturday, July 9, 2016

"ስምና … አመል "

"ስምና… አመል"
#ሳteናw

…  ዘንድሮ ግን ትውልዱ ስንቁ አንሶ አመሉ በዝቷል። ምን ያድርግ? ስንቁ ያነሰው አንደዛ ዘመን በግ በአምስት ብር ገዝቶ ቆዳውን በሶስት ብር እንዳይሸጥ ያደረገው ዘመን አመጣሹ የኑሮ ውድነት ነው። አመሉን ያበዛው ብሶት ሆነ። ሳይወድ በግዱ በጉያው የሚይዘው ስንቅ ጫት፣ በአህያ የሚጭነው ሸክም አመሉ፣ ሆነበት።

ታዲያ አፄ ሚኒሊክ በኛ ትውልድ ቢገኙ ኖሮ መልዕክታቸው … "አመልህን በአህያ፣በርጫህን በጉያህ"… አይሆንም ነበር ትላላችሁ?…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

    ከቤተሰባችንና ከማህበረሰባችን ከወረስናቸው ብዙ ነገሮች ውስጥ፣ ሁለቱ ስምና አመል ናቸው። ስም :-መልክን፣ እምነትን፣ ምኞትን፣ ነባራዊ ሁኔታን … መሰረት ተደርጎ ቤተሰብ ያወጣልናል። ለልጁ ምንም ሀብት ማውረስ እንደማይችል የተረዳ ደሃ ቤተሰብ፣ ለልጁ ሀብታሙ፣ ሚሊዮን፣ ወዘተ የሚል  የሀብት ምኞት አዘል ስም ሲያወርስ ፣ የሀብታም ልጅ ከቤተሰቡ ስምም ሀብት ይወርሳል።

  በአንፃሩ አመል በአስተዳደግ ፣ በስነ ልቦናዊ ጫና ፣ባመዘንበት ፍላጎታችን በመሳሰሉት አብሮን ያድጋል። በዚህም የመጣ አመል መለያ ይሆናል። ልክ እንደ ስም። "ሌባው" ይባላል የእጅ አመል ያለበት ሰው።" አልያም አንባቢው የሚል መለያ ይሰጠዋል። ጠጪው፣ አጫሹ፣ቃሚው፣በ*ው፣ ታታሪው፣ ምላሰኛው፣ ቋጣሪው፣ ለጋሹ ወዘተ እየተባለ ፣አመልህን ያማከለ መለያ ስም ከማህረሰብህ ይሰጥሃል። ስምን ለራሱ ያወጣ እንደሌለ ሁሉ፣ አመልም ከማህበረሰብ ይወጣል።

  አንዳንዴ ቤተሰብ በተምኔት ያወረሰን ስምና፣ ከማህበረሰብ  የምንወርሰው ባህሪይ አይገጥሙም። በምሳሌ እንይ…

ሰውየው በጣም ታዋቂ ሌባ ነው አሉ። የሚኖርበት  አካባቢም በሌቦች ብዛት ይታማል። ይህ ሌባ ወንድ ልጅ ሲወልድ… የራሱ አይነት ሌባ እንዳይሆንና መልካም ልጅ እንዲሆንለት በመመኘት ስሙን መልካሙ ሲል ሰየመው። መልካም እንዲሆን የተመኘው ሌባ አባት እለት ከለት ዘርፎ የሚያመጣውን ነገር ህፃኑ መልካሙ እያየ አባቱን የማህበረሰቡን የስርቆት እንቅስቃሴ እያስተዋለ ያድጋል። ።ይህን እያየ ያደገው ህፃኑ መልካሙ፣ አባቱ መልካም  ወደ ሌብነት ለመግባት የማንምም ምክር ሳይሻ ከአባቱ የባሰ ሌባ ሆኖ ተገኘ። ይህን የተመለከተው አባት ለልጁ የሰጠው ስያሜ ወዲያው ቀየረው። ይባስ ብሎ እንደ አዲስ ሰየመው አሉ። ምን ያድርግ!! ስያሜውና አመሉ አልገጥም ቢለው ነው።

  እኔ በአያቴ የወጣልኝ ስም peace ነው (ወደ አማርኛ ከርብተው)። አያቴ ይህን ስያሜ ያወጣችልኝ እኔም በወቅቱ ሰላም ያልነበረበችው ሀገራችን ሰላማዊ እንድትሆንላት በመመኘቷ ነበረ። ምኞቷ በሀገሪቷ ሰላምነት ሲሰምር፣ በእኔ አዛ ባህሪ መከነ። ከስሜ ተቃራኒ ሆኜ ተገኘው። ይህን የታዘበች አንድ የመንደሬ ሴት፣ አንድ ለት በአንዳች ነገር ብጦልባት፣

"አንተን ሰላም ብሎ ስም ያወጣልህ ሰላም አይቶ የማያውቅ ነው!!" ብላ ከትውስታ ማይፋቅ ምሬቷን ጣለችብኝ።

"አዎ ስሜ ሲወጣ በሀገሪቱ ሰላም አልታየም" ልላት አልኩና ተውኩት… 

እኔና ይባስ ብቻ አይደለንም። የስያሜ ምኞቱ ሳይሰምር፣ በድህነቱ የዘለቀ ሀብታሙ፣ ደሀ ሆኖ ቀርቷል። አልያም ጤንንት የተመኙሉት ጤናው… በሽተኛ ሆኖ የሚቀርበት አጋጣሚ በበሽ አለ… አስበው ስሙ ቸሩ ተብሎ፣ እልም ያለ ቋጣሪ፣ገብጋባ፣ መንጠቆ፣ ጌታሁን ተብሎ የሀብታም ዘበኛ፣ ሰላም ተብሎ አገር ያቃጠለ አዛ ሆኖ ሲገኝ። ማሙሽ ተብሎ ተሰይሞ እድሜ ሰጥቶት ሲያረጅ ጋሽ ማሙሽ ብለህ ስትጠራው!! " ስምን መልዓክ ያወጣዋል እዚህ ጋር… አይነፋም። እንደ ስም አመልም ከቤተሰብና ከማህበረሰብ ተጀብቶናል። ልክ እንደኔ ና እንደ ህፃኑ ይባስ።

ሀገር በቀል የሆነ አባባል አለ፣

ግመል ምን ጭነሃል? ሽመል፣ ምን ያወዛውዝሃል? አመል!!።
እርግጥ ነው ግመል ያወዛወዘው ሸክሙ ከብዶት፣ ሳይሆን ልማድ አመሉ ነው።

የሰው ልጅ እንደ ስም ፣መልክና አሻራው ከሚለያይባቸው ነገሮች ሌላው አመሉ ነው።

አንድ ሰው የተለያዩ አመሎችን ቢያንፀባርቅም ከሁሉም የሚያመዝንበት አንድ አመል አለው። አመል ሁለት አይነት ነው። መልካምና መጥፎ በለው። ከሁለቱም ወገን ያልሆነ ሊኖርም ይችላል።

አመል ስል ይሄም ትዝ አለኝ

… አፄ ምኒሊክ በፋሺሽት ኢጣሊያ ሲወረሩ ክተት ባወጁ ጊዜ፣ ለዘማቹ አፅንኦት ሰጥተው ያስተላለፉትን መልዕክት ተከታዩ ነበር…

"አመልህን፣በጉያህ፣ ስንቅህን፣በአህያ"።

  ዘንድሮ ግን ትውልዱ ስንቁ አንሶ አመሉ በዝቷል። ምን ያድርግ? ስንቁ ያነሰው አንደዛ ዘመን በግ በአምስት ብር ገዝቶ ቆዳውን በሶስት ብር እንዳይሸጥ ያደረገው ዘመን አመጣሹ የኑሮ ውድነት ነው። አመሉን ያበዛው ብሶት ሆነ። ሳይወድ በግዱ በጉያው የሚይዘው ስንቅ ጫት፣ በአህያ የሚጭነው ሸክም አመሉ፣ ሆነበት።

ታዲያ አፄ ሚኒሊክ በኛ ትውልድ ቢገኙ ኖሮ መልዕክታቸው … "አመልህን በአህያ፣በርጫህን በጉያህ"… አይሆንም ነበር ትላላችሁ?…

ስለሰውና ባህሪው ብዙማለት ይቻላል … ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራልና ይብራ…

ስምን ለራሱ ያወጣ እንደሌለ ሁሉ፣ አመልም ከማህበረሰብ ይወረሳል። ልክ እንደ ህፃኑ ይባስ። ይህን ውርሳችንን መልካም ከሆነ መልካም፣ መልካም ካልሆነ ልንተራረም እንጂ ልንቃረንበት፣ በጅምላ ልንሰዳደብበት አይገባም። በተለይ በብሄርና፣ በሀይማኖት።

  እስካሁን… የተንዛዛውብህ፣ እንደ ፈላስፋ ያወዛገብኩህ፣ ለሌላ አይደለም…! እንደ ስምና መልካችን የተለያየውን አመላችንን፣ አስማምቶ  ያቻችለን፣ አጣጥሞ ያፋቅረን አንድነት ይስጠን ለማለት!!
ወገሬት!!

Friday, July 1, 2016

" የስራ… ሀ ሁ"

"የ ስ ራ ……  ሀ ሁ"
#ሳteናw

…  እነ ዲኬቲ ኢትዮጲያ በየጎዳናው በሚቆሙ ቢልቦርድ ምርታቸውን ለሚያስተዋውቁላቸው ሞዴሎች በሚልዮን የሚቆጠር ብር በሚከፍሉበት ምድር፣ አሰሪዬ ቶፊቅ ቆንጆዎችን ያለክፍያ በዘዴ እንደ ተንቀሳቃሽ ቢል ቦርድ የመጠቀም ሃሳቡን አድንቄለት!!) ወዳዘዘኝ ተግባር ወዲያው ተሰማራው…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

    ሃያኛው ክ/ዘ ተጠናቆ ሃያ አንደኛው ክ/ዘ 2ሺ ሚሊኒየም ገባ። 99 ላይ የወሰድኩትን የማትሪክ ፈተና ውጤት … ቤተሰብ የፕሪፕ ነጥብ ካላመጣህ በዛው ንካው ከሚል ማስጠንቂያ ጋር  በፆም በፀሎት ብጠብቅም አልተሳካም። …  ፈተና በማጥናት እንጂ በጠሎት ብቻ እንዳልሆነ የሚያስገነዝበኝን ሆኖ ውጤቱ ወጣ። ውጤቱ ለፕሪፕም ሆነ ለቤት መግቢያነት ስላላበቃኝ። መጀመሪያ መቀመጫዬን… በሚለው ብሂል መሰረት ፕሪፑን ትቼ ቤት በሽማግሌ ገባው።(ምናለ የመሰናዶ ትምህርትም በሽምግልና ቢገባ?)። የመጣልኝ ነጥብ ለአንድ አመት በሰርተክፌት መርሃ ግብር በሙያ ኮሌጅ ያስቀጥለኝ ነበርና ይህን ብዬ የሙያ ኮሌጅ መግቢያ ፎርም ሞላው። አስገባው። በየተመደባችሁበት ኮሌጅ ስማችሁ ይለጠፋል ጠብቁ ተባልን።… በዛን ሰሞን በምድሪቷ የሞላው ወሬ ስለ ሚሊኒየም ነበር። 99 ዓ/ም አመቱ ሙሉ የተወራለት፣ ሚሊኒየም በአንድ ቀን ጀንበር አልቆ ተገባደደ። ከዛ ቡሃላ በአንድ ሰሞን ወረት የነበረው ሚሊኒየም ቀስ በቀስ  እየደበዘዘ እየደበዘዘ "ምንምየለም" ሆኖ አረፈው። ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስተውለው ከሚሊኒየም ያተረፍነው ነገር ቢኖር፣ የመንገድ መስፋትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ የስራ ማጣትንና፣ ከተኖረበት ቀዬ በልማት ሰበብ መፈናቀልን ሆነ። እርግጥ ነው መልሶ ማልማት ከሀገር እድገት ቢመደብም፣ ህዝቤ በኑሮ ውድነት ቀን በቀን ኪሎው እየቀነሰና በቁም እየፈረሰ የድንጋይ ድርዳሮ ማቆምምና ማንጠፍ ብቻውን የሀገር ዕድገት መሆኑ ያጠራጥራል። ምክኒያቱም ሀገር ማለት ህዝም ጭምር እንጂ ምድርና ሰማዩ ብቻ አይደለም። እድገት የሚባለውም ህዝቡም ልማቱም ተያይዘው እኩል በእድገት ጎዳና ሲጓዙ እንጂ፣ ልማቱ ብቻውን እየኮበለለ ህዝቡ በጠኔ እየተንጓለለ እለመሆኑን ለማወቅ ሊቅ መሆን አያሻም። የሆነው ሆኖ ሚሊኒየም ገብቶ ምንም የለም ኑሮ ተጀመረ።

   የኮሌጁ ደልድድ ተለጥፏል የተባለ ቀን በመረጡልኝ ኮሌጅ በር ሄጄ ከተለጠፈው ስምና የትምህርት ዘርፍ ላይ ስሜን መፈለግ ጀመርኩ። የስሙ መብዛት የኢትዮጲያ ተማሪ በሙሉ ወደዚህ ኮሌጅ የተመደበ ያስመስለው ነበር። ቆይ ይህን ሁሉ ተማሪ ሊያስተምሩት ነው ወይስ የምርጫ ካርድ ሊሰጡት?። (ከብዛት ጥራት የሚለው የመርካቶ ሰፈሬ ቋንቋ እዚህ ኮሌጅ አይሰራም።) ስሜን ፈለኩ… ፈለኩ… ስሜን አጣሁት። ረስተውኝ ይሆን እንዴ? መፈለጉ ታክተኝ… ድሮም ትዕግስት የሚባል ነገር አልፈጠረብኝም!! እዚህ ስሜን ስፈልግ ከምውል … ለምን መርካቶ ገብቼ ዕጣ ፈንታዬን አልፈልግም አልኩና ኮሌጁን ትቸው መርካቶ ከሚገኘው ቤት መጣው። የያዝኩትን የማትሪክ ሰርተክፌት የሰው መሳቂያ እንዳያደርገኝ ብዬ የሰው ዘር ከማይደርስበት ስፍራ አስቀመጥኩት። የግል ኮሌጅ ወይም የርቀት ትምህርት እንድቀጥል ከቤተሰብ ሀሳብ ቀረበ። አልተስማማሁም። የትምህርት ሀፒታይቴን ስለማውቅ ሰበብ አስባብ ፈጥሬ ሀሳቡን ውድቅ አደረኩት። ከትምህርት ጋር እንኳን ርቄው በክፍል ውስጥ የመጀመሪያ ወንበር ላይ ተቀምጬም አልተስማማንም። ካደኩባት መርካቶ… ከዙሪያዋ ካለው የንግዱ ማህበረሰብ ለመቀላቀል ጊቢ በር ላይ የስራ ያለህ በሚመስል ሁኔታ ቆሜ መዋል ጀምርኩ። ከሚሊኒየም ቡሃላ አመቱ ከ365 ቀናት ወደ 36.5 ቀናት የተቀየረ እስኪመስለኝ ድረስ ፈጠነበኝ። በመቆም ብቻ ከእድሜዬ አንዷን አመት እንደ ቀልድ ቁርጥምጥም አድርጌ በላኋት። አንድ አመት ተምሬ የሙያ ኮሌጅ ሰርተክፌት ባይሰጠኝም፣ አንድ አመት በመቆም ቋሚው የሚል የማይታይ የማይዳሰስ ሰርተክፌት ከማህበረሰቤ ተሰጠኝ። (እንዴት መርካቶ እየዋልክ አመት ሙሉ ስራ አጣህ? የሚል ጥያቄ ካነሳህ… መርካቶ የጓዳ ሚስጥሯን አውቆና ንቆ ላደገባት ሳይሆን፣ ስራ ሳይንቅ ለሰራባት መጤ የምትቤዥ ስለሆነች ነው የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው፣ የሚባለው ተረት በተግባር እንድተውን ተመርጬም ሊሆንም ይችላል። አባይንስ ስለናቅነው አልነበር ልጁን በጥም ቆልቶ፣ የባዳውን ጥም ያረካው?)

    አንድ አመት ያለ ስራ መቆሜን የታዘበው እንድ ሰው በቆምኩበት መጣና…" አንተ ሰው እዚህ ቆመህ ከምትውል እኔ ጋር በክፍያ ቆመህ የምትሰራውን ስራ ብሰጥህ አይሻልም?" ሲለኝ ተስማማሁና በሚሰራው የባዛር ስራ ላይ እቃ ሻጭ አድርጎ ቀጠረኝ። በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ኢግዝቢሽን ሟ ማዕከል በተዘጋጀው የገና ባዛር ዝግጅት ላይ አሰሪዬ በግሉ ተሳትፎ በካሬ 70 ብር የተከራያትን ጊዚያዊ የድንኳን ሱቅ ውስጥ በመቆም የስራ… ሀሁ  ጀመርሁ…

   ለ10 ቀን በኢግዚቢሽን ማዕከል ባሳለፍኩት ጊዜ ከስራ ልምድ ባሻገር ብዙ ነገር ታዘብኩ … ሐበሾች ምን ያህል ከሌላው አለም የተለየን ቆንጆዎች መሆናችንን ለመረዳት ዕድሉ ፈጠረልኝ። (ቆይ ግን ሐበሾች እንዲህ ቆንጆ ነን እንዴ? ቆንጆዎች በበዙበት ቦታ ነው ቁንጅናችን ጎልቶ የሚታየው? ወይስ ባዛር ሲመጣ ችግር መከራውን ሸፍኖ ያለ የሌለ የክት ልብሱን ተጎናፅፎ እንደደላው ሆኖ ስለሚታይ ነው?)። የባዛሩ አዘጋጅ ኮሚት በግል ሆነ በድርጅት ለተሳተፉ መግቢያ መውጫ ባጅ አዘጋጅቶ ነበር። ታዲያ ከባዛሩ ጊቢ ለአንድ ነገር ወጥተህ ስትመለስ ወደ ባዛሩ ጊቢ ለመግባት በተሰለፉ የአዲስ አበባ ቆንጆዎች መሃል "ምነው እሱን ባረገኝ" ብለው እስኪመኙ ድረስ በሙሉ ነፃነት ባጅን አሳይተህ በልዩ በር ደረትህን ነፍተህ መግባት መውጣቱ እራሱ ለንደኔ አይነቱ የመርካቶ ጉረኛ መልካም አጋጣሚ ነበር። የባዛር ስራ ቆንጆ መዝናኛ ነው። ስራህን እየሰራህ ሀገርህ ያበቀላቸውን ኮረዶች እየሾፍክ… በቴቪ መስኮት የምታውቃቸው አርቲስቶች … በአካል እየተፈራረቁ ሲያዝናኑ ማየት በራሱ የሚደላህ መዝናኛ አይደለም? ትላለህ! አረ ይደላል። ለምሳሌ ይሄ በመርካቶ የለም። በመርካቶ ምድር በስራህ መሀል የሚመጣው የሚያዝናና አቀንቃኝ ሳይሆን በሚያሳዝን ድምፅ እያቀነቀነ ምፅዋት የሚጠይቅ የኔ ቢጤ ነው። በባዛር ውሎ ስራ ሳትሰራ ብትውም የአዲስ አበባ ቆንጆዎች በጉብኝታቸው ሂደት አንተን ባያዩህም በሽያጭ ሱቅህ ተቀምጠህ በተጨናነቀው ቀጭን መተላለፊያ ሲተላለፉ ማየት በራሱ ደስ የሚል የትዕይንት ትርፍ ይፈጥርልሃል። በተለይ አንደኔ ላለው መርካቶ ውስጥ ሰውና አህያ ተጋፍተው ሲተራመሱ እያየ ላደገ ሰው። በባዛሩ ጊዜያዊ ሱቃችን እኛ እንሸጥ የነበረው እቃዎች ፈሳሽ ሳሙና፣ሬዲዮ፣ ጫማ፣ ቺብስ፣ የኘላስቲክ ለስላሳ መጠጦች ወዘተ እንደ ሱፐር ማርኬት የተቀላቀለ አይነት ዕቃ ነበር። (በነገራችን ላይ በተለምዶ የምናውቀው የኢግዝቢሽን ገበያ ከመደበኛው ገበያ የዋጋ ቅናሽ እንደሚኖረው ነው አይደል? ነገር ግን እኔ በአስር ቀን የኢግዝቢሽን ልምዴ የተረዳውት የዚህን ተቃራኒ ነው። የመርካቶ እቃ በኢግዝቢሽን ማዕከል እንደውም በጭማሪ ለትርፍ ይሸጣል። ሰው ቅናሽ ነው የሚለው እሳቤ ይዞ መጥቶ ኡሞ ገብቶለት ይሄዳል። መርካቶ አልሸጥ ያሉና ኤክፓየር ዴታቸው የደረሰ እሽግ ምግቦ በባዛር በደንብ ይሸጣሉ። የዋጋ ጭማሪ የሚታየው እንደኛ ላሉ በግል የተሳተፉ ሻጮች እንጂ ድርጅቶችን እንዳልሆነ ልታሰምርልኝ ይገባል።)   በአንዱ ቀን አሰሪዬ ቶፊቅ ለኔና አንድ አብሮኝ ለሚሰራው ልጅ። አልሸጥ ያለለንን ቺብስ ለማስተዋወቅ አልፎ አልፎ አንድ አንድ በነፃ አድሉ! በተለይ የማንም አይን ለሚስቡ ለቆንጆ ሴቶች! እነሱ ለመታየት ቅርብ ስለሆኑ በዛውም ቺብሱን ያስተዋውቁልናል አለን። በጣም ደነቀኝ!! " እነ ዲኬቲ ኢትዮጲያ በየጎዳናው በሚቆሙ ቢልቦርድ ምርታቸውን ለሚያስተዋውቁላቸው ሞዴሎች በሚልዮን የሚቆጠር ብር በሚከፍሉበት ምድር፣ አሰሪዬ ቶፊቅ ቆንጆዎችን ያለክፍያ በዘዴ እንደ ተንቀሳቃሽ ቢል ቦርድ የመጠቀም ሃሳቡን አድንቄለት!!) ወዳዘዘኝ ተግባር ወዲያው ተሰማራው። ሽያጩን ለስራ ባልደረባዬ ዳይቨርት አድርጌ ትቼ በፊቴ ከሚያልፈው የቆንጆ ጅረት የሳበችን በአይኔ እየተጠራው ተጋበዙልኝ እያልኩ እንደደጋሽ ቺብሱ ሳድል ዋልኩ (በወቅቱ እድሜዬ የጉረርምስና መጀመሪዬ ስለነበር ያየኋት ሴት ሁሉ ትስበኛለች፣ታምረኛለች፣ ታሻፍ… ለች። እንኳን የሄዋን ዘር ፍየል እራሱ ቀሚስ ለብሳ ብታልፈኝ ችብሱን መጋበዜ አይቀርም ነበር። የሆነው ሆኖ ቺብሱን እንደ በራሪ ወረቀት ሳድል ዋልኩ። አመሻሽ ላይ አሰሪዬ ቶፊቅ መጥቶ ሂሳብ ስንሰራ ቺብሱ የሁለት ካርቶን ጉድለት አሳየ።

"እንዴ ምንድነው?" አለ።

"ለቆንጆ ሴቶች አድል ያልከኝ ነው ጉድለቱ?" አልኩት ፈርጠም ብዬ።

"አልፎ አልፎ ማለት ታዲያ ሁለት ካርቶን ሙሉ እስኪያልቅ ነው እንዴ?"

"እሱማ አልፎ አልፎ ነበር ያልከኝ… "

"እና! … "

"እናማ … እየተንተባተብኩ… ነገር ግን እዚህ የሚያልፉት ሁሉ ቆነጁብኝ ምን ላድርግ? ሁሉም ቢቆነጁብኝ ጊዜ ቢለዩ ቢለዩ ብዬ …ለሁሉም  አደልኳቸው… ዛሬ ደግሞ እንዳለ ቆንጆ ብቻ፣ነበር…  አደለ እንዴ ብዬ ወደ ስራ ባለደረባዬ ዞርኩ…

"አዎ በሚል ጭንቅላቱን ነቀነቀ።"

"ዝጋ! ቆይ ችግር የለም! በደሞዝህ እንነጋገራለን። ብሎ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ሄደ። ምስኪን ቶፊቅ አሁን የተናገረውን ቡሃላ ይረሳዋል። በሆዱ ማቄም የሚባል ነገር አያስተናግድም። በደሞዜ ይዛት እንጂ አልቆረጠብኝም ነበር…የአዲስ አበባው ባዛር አልቆ ቀጣይ በተዘጋጀው የአዋሳ ባዛር ተሳትፈን … ወደ አዋሳው ባዛር የስራ አቡጊዳዬን ለመቀጠል አቀናው… በአዋሳ በጣም ደስ የሚል አስቂኝ፣ ገጠመኝ… በማስተናገድ ለ15 ቀን አሳለፍን…
ወገሬት!!