Friday, July 1, 2016

" የስራ… ሀ ሁ"

"የ ስ ራ ……  ሀ ሁ"
#ሳteናw

…  እነ ዲኬቲ ኢትዮጲያ በየጎዳናው በሚቆሙ ቢልቦርድ ምርታቸውን ለሚያስተዋውቁላቸው ሞዴሎች በሚልዮን የሚቆጠር ብር በሚከፍሉበት ምድር፣ አሰሪዬ ቶፊቅ ቆንጆዎችን ያለክፍያ በዘዴ እንደ ተንቀሳቃሽ ቢል ቦርድ የመጠቀም ሃሳቡን አድንቄለት!!) ወዳዘዘኝ ተግባር ወዲያው ተሰማራው…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

    ሃያኛው ክ/ዘ ተጠናቆ ሃያ አንደኛው ክ/ዘ 2ሺ ሚሊኒየም ገባ። 99 ላይ የወሰድኩትን የማትሪክ ፈተና ውጤት … ቤተሰብ የፕሪፕ ነጥብ ካላመጣህ በዛው ንካው ከሚል ማስጠንቂያ ጋር  በፆም በፀሎት ብጠብቅም አልተሳካም። …  ፈተና በማጥናት እንጂ በጠሎት ብቻ እንዳልሆነ የሚያስገነዝበኝን ሆኖ ውጤቱ ወጣ። ውጤቱ ለፕሪፕም ሆነ ለቤት መግቢያነት ስላላበቃኝ። መጀመሪያ መቀመጫዬን… በሚለው ብሂል መሰረት ፕሪፑን ትቼ ቤት በሽማግሌ ገባው።(ምናለ የመሰናዶ ትምህርትም በሽምግልና ቢገባ?)። የመጣልኝ ነጥብ ለአንድ አመት በሰርተክፌት መርሃ ግብር በሙያ ኮሌጅ ያስቀጥለኝ ነበርና ይህን ብዬ የሙያ ኮሌጅ መግቢያ ፎርም ሞላው። አስገባው። በየተመደባችሁበት ኮሌጅ ስማችሁ ይለጠፋል ጠብቁ ተባልን።… በዛን ሰሞን በምድሪቷ የሞላው ወሬ ስለ ሚሊኒየም ነበር። 99 ዓ/ም አመቱ ሙሉ የተወራለት፣ ሚሊኒየም በአንድ ቀን ጀንበር አልቆ ተገባደደ። ከዛ ቡሃላ በአንድ ሰሞን ወረት የነበረው ሚሊኒየም ቀስ በቀስ  እየደበዘዘ እየደበዘዘ "ምንምየለም" ሆኖ አረፈው። ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስተውለው ከሚሊኒየም ያተረፍነው ነገር ቢኖር፣ የመንገድ መስፋትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ የስራ ማጣትንና፣ ከተኖረበት ቀዬ በልማት ሰበብ መፈናቀልን ሆነ። እርግጥ ነው መልሶ ማልማት ከሀገር እድገት ቢመደብም፣ ህዝቤ በኑሮ ውድነት ቀን በቀን ኪሎው እየቀነሰና በቁም እየፈረሰ የድንጋይ ድርዳሮ ማቆምምና ማንጠፍ ብቻውን የሀገር ዕድገት መሆኑ ያጠራጥራል። ምክኒያቱም ሀገር ማለት ህዝም ጭምር እንጂ ምድርና ሰማዩ ብቻ አይደለም። እድገት የሚባለውም ህዝቡም ልማቱም ተያይዘው እኩል በእድገት ጎዳና ሲጓዙ እንጂ፣ ልማቱ ብቻውን እየኮበለለ ህዝቡ በጠኔ እየተንጓለለ እለመሆኑን ለማወቅ ሊቅ መሆን አያሻም። የሆነው ሆኖ ሚሊኒየም ገብቶ ምንም የለም ኑሮ ተጀመረ።

   የኮሌጁ ደልድድ ተለጥፏል የተባለ ቀን በመረጡልኝ ኮሌጅ በር ሄጄ ከተለጠፈው ስምና የትምህርት ዘርፍ ላይ ስሜን መፈለግ ጀመርኩ። የስሙ መብዛት የኢትዮጲያ ተማሪ በሙሉ ወደዚህ ኮሌጅ የተመደበ ያስመስለው ነበር። ቆይ ይህን ሁሉ ተማሪ ሊያስተምሩት ነው ወይስ የምርጫ ካርድ ሊሰጡት?። (ከብዛት ጥራት የሚለው የመርካቶ ሰፈሬ ቋንቋ እዚህ ኮሌጅ አይሰራም።) ስሜን ፈለኩ… ፈለኩ… ስሜን አጣሁት። ረስተውኝ ይሆን እንዴ? መፈለጉ ታክተኝ… ድሮም ትዕግስት የሚባል ነገር አልፈጠረብኝም!! እዚህ ስሜን ስፈልግ ከምውል … ለምን መርካቶ ገብቼ ዕጣ ፈንታዬን አልፈልግም አልኩና ኮሌጁን ትቸው መርካቶ ከሚገኘው ቤት መጣው። የያዝኩትን የማትሪክ ሰርተክፌት የሰው መሳቂያ እንዳያደርገኝ ብዬ የሰው ዘር ከማይደርስበት ስፍራ አስቀመጥኩት። የግል ኮሌጅ ወይም የርቀት ትምህርት እንድቀጥል ከቤተሰብ ሀሳብ ቀረበ። አልተስማማሁም። የትምህርት ሀፒታይቴን ስለማውቅ ሰበብ አስባብ ፈጥሬ ሀሳቡን ውድቅ አደረኩት። ከትምህርት ጋር እንኳን ርቄው በክፍል ውስጥ የመጀመሪያ ወንበር ላይ ተቀምጬም አልተስማማንም። ካደኩባት መርካቶ… ከዙሪያዋ ካለው የንግዱ ማህበረሰብ ለመቀላቀል ጊቢ በር ላይ የስራ ያለህ በሚመስል ሁኔታ ቆሜ መዋል ጀምርኩ። ከሚሊኒየም ቡሃላ አመቱ ከ365 ቀናት ወደ 36.5 ቀናት የተቀየረ እስኪመስለኝ ድረስ ፈጠነበኝ። በመቆም ብቻ ከእድሜዬ አንዷን አመት እንደ ቀልድ ቁርጥምጥም አድርጌ በላኋት። አንድ አመት ተምሬ የሙያ ኮሌጅ ሰርተክፌት ባይሰጠኝም፣ አንድ አመት በመቆም ቋሚው የሚል የማይታይ የማይዳሰስ ሰርተክፌት ከማህበረሰቤ ተሰጠኝ። (እንዴት መርካቶ እየዋልክ አመት ሙሉ ስራ አጣህ? የሚል ጥያቄ ካነሳህ… መርካቶ የጓዳ ሚስጥሯን አውቆና ንቆ ላደገባት ሳይሆን፣ ስራ ሳይንቅ ለሰራባት መጤ የምትቤዥ ስለሆነች ነው የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው፣ የሚባለው ተረት በተግባር እንድተውን ተመርጬም ሊሆንም ይችላል። አባይንስ ስለናቅነው አልነበር ልጁን በጥም ቆልቶ፣ የባዳውን ጥም ያረካው?)

    አንድ አመት ያለ ስራ መቆሜን የታዘበው እንድ ሰው በቆምኩበት መጣና…" አንተ ሰው እዚህ ቆመህ ከምትውል እኔ ጋር በክፍያ ቆመህ የምትሰራውን ስራ ብሰጥህ አይሻልም?" ሲለኝ ተስማማሁና በሚሰራው የባዛር ስራ ላይ እቃ ሻጭ አድርጎ ቀጠረኝ። በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ኢግዝቢሽን ሟ ማዕከል በተዘጋጀው የገና ባዛር ዝግጅት ላይ አሰሪዬ በግሉ ተሳትፎ በካሬ 70 ብር የተከራያትን ጊዚያዊ የድንኳን ሱቅ ውስጥ በመቆም የስራ… ሀሁ  ጀመርሁ…

   ለ10 ቀን በኢግዚቢሽን ማዕከል ባሳለፍኩት ጊዜ ከስራ ልምድ ባሻገር ብዙ ነገር ታዘብኩ … ሐበሾች ምን ያህል ከሌላው አለም የተለየን ቆንጆዎች መሆናችንን ለመረዳት ዕድሉ ፈጠረልኝ። (ቆይ ግን ሐበሾች እንዲህ ቆንጆ ነን እንዴ? ቆንጆዎች በበዙበት ቦታ ነው ቁንጅናችን ጎልቶ የሚታየው? ወይስ ባዛር ሲመጣ ችግር መከራውን ሸፍኖ ያለ የሌለ የክት ልብሱን ተጎናፅፎ እንደደላው ሆኖ ስለሚታይ ነው?)። የባዛሩ አዘጋጅ ኮሚት በግል ሆነ በድርጅት ለተሳተፉ መግቢያ መውጫ ባጅ አዘጋጅቶ ነበር። ታዲያ ከባዛሩ ጊቢ ለአንድ ነገር ወጥተህ ስትመለስ ወደ ባዛሩ ጊቢ ለመግባት በተሰለፉ የአዲስ አበባ ቆንጆዎች መሃል "ምነው እሱን ባረገኝ" ብለው እስኪመኙ ድረስ በሙሉ ነፃነት ባጅን አሳይተህ በልዩ በር ደረትህን ነፍተህ መግባት መውጣቱ እራሱ ለንደኔ አይነቱ የመርካቶ ጉረኛ መልካም አጋጣሚ ነበር። የባዛር ስራ ቆንጆ መዝናኛ ነው። ስራህን እየሰራህ ሀገርህ ያበቀላቸውን ኮረዶች እየሾፍክ… በቴቪ መስኮት የምታውቃቸው አርቲስቶች … በአካል እየተፈራረቁ ሲያዝናኑ ማየት በራሱ የሚደላህ መዝናኛ አይደለም? ትላለህ! አረ ይደላል። ለምሳሌ ይሄ በመርካቶ የለም። በመርካቶ ምድር በስራህ መሀል የሚመጣው የሚያዝናና አቀንቃኝ ሳይሆን በሚያሳዝን ድምፅ እያቀነቀነ ምፅዋት የሚጠይቅ የኔ ቢጤ ነው። በባዛር ውሎ ስራ ሳትሰራ ብትውም የአዲስ አበባ ቆንጆዎች በጉብኝታቸው ሂደት አንተን ባያዩህም በሽያጭ ሱቅህ ተቀምጠህ በተጨናነቀው ቀጭን መተላለፊያ ሲተላለፉ ማየት በራሱ ደስ የሚል የትዕይንት ትርፍ ይፈጥርልሃል። በተለይ አንደኔ ላለው መርካቶ ውስጥ ሰውና አህያ ተጋፍተው ሲተራመሱ እያየ ላደገ ሰው። በባዛሩ ጊዜያዊ ሱቃችን እኛ እንሸጥ የነበረው እቃዎች ፈሳሽ ሳሙና፣ሬዲዮ፣ ጫማ፣ ቺብስ፣ የኘላስቲክ ለስላሳ መጠጦች ወዘተ እንደ ሱፐር ማርኬት የተቀላቀለ አይነት ዕቃ ነበር። (በነገራችን ላይ በተለምዶ የምናውቀው የኢግዝቢሽን ገበያ ከመደበኛው ገበያ የዋጋ ቅናሽ እንደሚኖረው ነው አይደል? ነገር ግን እኔ በአስር ቀን የኢግዝቢሽን ልምዴ የተረዳውት የዚህን ተቃራኒ ነው። የመርካቶ እቃ በኢግዝቢሽን ማዕከል እንደውም በጭማሪ ለትርፍ ይሸጣል። ሰው ቅናሽ ነው የሚለው እሳቤ ይዞ መጥቶ ኡሞ ገብቶለት ይሄዳል። መርካቶ አልሸጥ ያሉና ኤክፓየር ዴታቸው የደረሰ እሽግ ምግቦ በባዛር በደንብ ይሸጣሉ። የዋጋ ጭማሪ የሚታየው እንደኛ ላሉ በግል የተሳተፉ ሻጮች እንጂ ድርጅቶችን እንዳልሆነ ልታሰምርልኝ ይገባል።)   በአንዱ ቀን አሰሪዬ ቶፊቅ ለኔና አንድ አብሮኝ ለሚሰራው ልጅ። አልሸጥ ያለለንን ቺብስ ለማስተዋወቅ አልፎ አልፎ አንድ አንድ በነፃ አድሉ! በተለይ የማንም አይን ለሚስቡ ለቆንጆ ሴቶች! እነሱ ለመታየት ቅርብ ስለሆኑ በዛውም ቺብሱን ያስተዋውቁልናል አለን። በጣም ደነቀኝ!! " እነ ዲኬቲ ኢትዮጲያ በየጎዳናው በሚቆሙ ቢልቦርድ ምርታቸውን ለሚያስተዋውቁላቸው ሞዴሎች በሚልዮን የሚቆጠር ብር በሚከፍሉበት ምድር፣ አሰሪዬ ቶፊቅ ቆንጆዎችን ያለክፍያ በዘዴ እንደ ተንቀሳቃሽ ቢል ቦርድ የመጠቀም ሃሳቡን አድንቄለት!!) ወዳዘዘኝ ተግባር ወዲያው ተሰማራው። ሽያጩን ለስራ ባልደረባዬ ዳይቨርት አድርጌ ትቼ በፊቴ ከሚያልፈው የቆንጆ ጅረት የሳበችን በአይኔ እየተጠራው ተጋበዙልኝ እያልኩ እንደደጋሽ ቺብሱ ሳድል ዋልኩ (በወቅቱ እድሜዬ የጉረርምስና መጀመሪዬ ስለነበር ያየኋት ሴት ሁሉ ትስበኛለች፣ታምረኛለች፣ ታሻፍ… ለች። እንኳን የሄዋን ዘር ፍየል እራሱ ቀሚስ ለብሳ ብታልፈኝ ችብሱን መጋበዜ አይቀርም ነበር። የሆነው ሆኖ ቺብሱን እንደ በራሪ ወረቀት ሳድል ዋልኩ። አመሻሽ ላይ አሰሪዬ ቶፊቅ መጥቶ ሂሳብ ስንሰራ ቺብሱ የሁለት ካርቶን ጉድለት አሳየ።

"እንዴ ምንድነው?" አለ።

"ለቆንጆ ሴቶች አድል ያልከኝ ነው ጉድለቱ?" አልኩት ፈርጠም ብዬ።

"አልፎ አልፎ ማለት ታዲያ ሁለት ካርቶን ሙሉ እስኪያልቅ ነው እንዴ?"

"እሱማ አልፎ አልፎ ነበር ያልከኝ… "

"እና! … "

"እናማ … እየተንተባተብኩ… ነገር ግን እዚህ የሚያልፉት ሁሉ ቆነጁብኝ ምን ላድርግ? ሁሉም ቢቆነጁብኝ ጊዜ ቢለዩ ቢለዩ ብዬ …ለሁሉም  አደልኳቸው… ዛሬ ደግሞ እንዳለ ቆንጆ ብቻ፣ነበር…  አደለ እንዴ ብዬ ወደ ስራ ባለደረባዬ ዞርኩ…

"አዎ በሚል ጭንቅላቱን ነቀነቀ።"

"ዝጋ! ቆይ ችግር የለም! በደሞዝህ እንነጋገራለን። ብሎ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ሄደ። ምስኪን ቶፊቅ አሁን የተናገረውን ቡሃላ ይረሳዋል። በሆዱ ማቄም የሚባል ነገር አያስተናግድም። በደሞዜ ይዛት እንጂ አልቆረጠብኝም ነበር…የአዲስ አበባው ባዛር አልቆ ቀጣይ በተዘጋጀው የአዋሳ ባዛር ተሳትፈን … ወደ አዋሳው ባዛር የስራ አቡጊዳዬን ለመቀጠል አቀናው… በአዋሳ በጣም ደስ የሚል አስቂኝ፣ ገጠመኝ… በማስተናገድ ለ15 ቀን አሳለፍን…
ወገሬት!! 

No comments:

Post a Comment