Tuesday, March 28, 2017

"ተ ሰ ው  አ ለ ው  ብ ዬ … ተ ጅ ብ  ተ ዳ ብ ዬ "


#ሳteናw

  የዛሬው የመሿለኪያ ቆይታ በክርክር ተጀመረ። … በአዘቦት ቀን በተለመደው ስፍራ፣ ቦታና፣ ጊዜ ሁሉም ከየአቅጣጫው ወደ መሿለኪያዋ መቆያውን ይዞ ሲተም… መተዳደሪያቸው ሸቀጥ በመኪና ላይ መደርደር የሆነው ጃንደረባዉና ሙልጌ ደግሞ ቀን በስራ ሳቢያ ያጨቃጨቃቸውን ጭቅጭቅ ይዘው፣ ገና ከበሩ እየተጨቃጨቁ ተመሙ። ወጣቶቹ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቢቀመጡም፣ የሁለቱ አባላት ጭቅጭቅ ትኩረታቸውን ሳበው።
"ምንድነው ያጨቃጨቃችሁ?" ቡፌት ጠየቀ…
"ይኼ ነዋ!! እኔ ቢዝነስ ጠርሮብኝ፣ እሱ እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ ከአንዱ መኪና ወደ አንዱ እየዘለል ሲሰራ ትንሽ ማይሰቀጥጠው፣ አንዱን ስራ ምናለ ቢለቅ እስኪ!!" ብስጭት እያለና፣ ለቅሶ በመሰለ ድምፅ ስሞታውን አቀረበ ግድ የለሹ መልጌ።
"እሺ ጃንደረባው ለምን አንዱን ስራ አልተውክለትም?" ሰያ ነጭ ሽንኩርት ጥያቄ አስከተለ…
" ልተውለት ብፈልግም፣ አልቻልኩም!!"
"ለምን አልቻልክም?"
" ሁለቱም ደንበኞቼ ካንተ ውጪ ማንም አይደረድርልም፣ ከፈለክ ዕቃ ሲመጣ በተራ በተራ ደርድርልን መኪናውን አጠገብ ለአጠገብ እናቆምልሃለን አሉኝ!! እኔ ምን ማድረግ እችላለው።"
"ቢሆንስ አንተ ብታሳምናቸው እንቢ አይሉም ነበር፣ ትንሽ ሰበብ ማግኘትህና መስገብገብህ እንጂ!!"  ብሎ ጣልቃ ገባ።

ጃንደረባው አንዳች ነገር ለመግዛት፣ ክርክሩን አቋርጦ "ቆይ አንዴ መጣው!" ብሎ ከመሿለኪያ ወጣ…

  ዝምተኛው ጄጃን፣ እንደሁሌው ዝም፣ ብሎ ሲያዳምጥ ቆይቶ፣ በንግግራቸው መሃል "መስገብገብህ እንጂ…"  የምትለዋን ሀረግ ይዞ በስግብግብት ዙሪያ የራሱን ግንዛቤ በማስታወሻው ላይ ማስፈር ጀመረ …

  ስግብግብነት መቼ ተጀመረ ለሚለው ጥያቄ እንደኔ እንደኔ መልሱ፣ ህይወት ያለው ነገር ምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሚል ይሆናል። የጅማሬውም ባለቤት የአዳም ልጅ ቃየል ነው። ለወንድሙ አቤል ሚስትነት ትገባው የነበረችውን የራሱን መንትያ ስሟ ማን እንደ ነበር እኔንጃ! ብቻ ለኔ ካልሆነለች በሚል ቀወጠው አሉ። እነ አዳም አረ መስሚያችን ጥጥ ነው፣ ላሽ በል ሲገጩት። መንትያ ወንድሙን በራስ ወዳድነት፣ በስግብግብነት ስሜት አቤልን በሳንጃ ይሁን በአጃራ አስጫረው። በቃ አዚህ ጋር ስግብግብነት "ሀ" ብሎ ቢጀመምርም "ፖ"  ብሎ የቋጨው አልተገኘም። ሁሌም ይቀጥላል። ህይወት እስካለች ዑደቷን እስካላቆመች ድረስ። ሰግብግብነት ራስን ብቻ የመውደድና ስለሌላው ምንም አለመጨነቅን ያመለክታል። በሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን በእንስሳዎችም ላይ ይስተዋላል… …  በእርግጥ እንስሳት ቢስገበገቡም ባይስገበገቡም አይገርምም። ምክኒያቱም እንደስው ክፉ ደጉን የሚለዩበት የሚያመዛዝኑበት አይምሮ ስላልተፈጠረላቸው። ሊግርመን የሚገባው  አሳቢ ተብየው የሰው መስገብገብ ነው። ሰግብግብነት የእድገት እንቅፋት፣ የሰላም ጠንቅ፣  የልማት ፀር ነው!!"  እንዲሉ  እነ እንትና።

…"ብስገበገብማ መች እሱ ይስራ ብዬ እጠይቃቸው ነበር፣ ችግር አለብህ የራስህን እንጂ የሰውን አትረዳም!!"   እያለ ጃንደረባው ወደ መሻለኪያዋ ተመልሶ ሲመጣ

ጄጃን ፅሁፉን ገታ አድርጎ ወደነ ጃንደረባው ክርክር ቀልቡን መለሰ…

"እሺ እንደረዳቴ አድርጌ ላሰራው ብለሃቸዋል?" ሳተናው በመስቀለኛ ጥያቄ …
"አላልኩም…"
"ለምን?"
"እኔንጃ በሰዓቱ ሀሳቡ ስላልመጣልኝ ይሆናል…

ይህን እየተባባሉ ጄጃን … ከቀናቶች በአንዱ በታክሲ ውስጥ አንድ በመጠጥ ስካር አቅሉን የሳተ ተሳፋሪ፣ የታክሲው ራዲዮ ስለብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ በውጪ ዜናው ስለ ፅንፈኛው ቡድን አይሲስ፣ ተናግሮ  ሲያበቃ ሰካራሙ ዜናዎቹን ተከትሎ የተናገረውን አስታወሰ…
"ምድረ ሴረኛ!!" ሲል ጀመረ ሰካራሙ ተሳፋሪ መጠጥ ባኮላተፈው አንደበቱ እየተንተፋተፈ…"ምድረ ሴረኛ … ማንን ለማታለል ነው? አይሲስ ቅብርጥሶ የሚሉት… አይሲስም በለው ኢቦላ፣ በአለማችን የሚከሰቱ  እልቂቶች ምንጫቸው እንደ ሎተሪ ተፍቆ ቢታይ በእርግጠኝነት የኋያላን ሀገራት ሴራ ሆኖ እንደሚገኝ አትጠራጠር …ህቅ!! አዎ! ለራሳቸው ምቾት ሲሉ በሴራቸው ለምቾታችን ስጋት ይሆናል ያሉትን ሀገርም ሆነ ግለሰብ ላይ አደጋ ከማድረስ ወደኋላ ያሉበት ጊዜ የለም። እንቅልፍ አጥተው ሌት ተቀን ምድር ቆፍረው ሰማይ ቧጠው አላማቸውን በማሳካት ላይ ናቸው፣ እንደኔና እንዳንተ አይነቱ በደሃና በመካከለኛ ደረጃ በሚገኙ  አገራት የምንኖር ምስኪኖች የነሱ የሴራቸው ሰለባ ነን፣ ህቅ!!…

ታክሲዋ፣የሰካራሙ ንግግር ነገሰባት።

  …በስልጣኔያቸው የበከሉት የአየርን ንብረት፣ ቀሪዋን እየተነፈሱ ይቀራመቱናል በሚል ይሁን በሌላ የሚስኪኑን እስትንፋስ ለመቁረጥ ወደ ኋላ ያሉበት ጊዜ እርሳው…፣ አይሲስም  የእርስ በእርስ ፍጅት፣ ምንጩን ለማግኘት እንደ ቱባክር ተርትረህ ጫፉ ስትደርስ እነሱን ታገኛለህ። የሚስኪኑ መስዋዕትነት በዚህ አይቋጭም። የራሳችን ዜጎች የምንላቸው መሪዎችም ለራሳቸው፣ ወይም ለፖለቲካ ድርጅታቸው ሲሉ እኛን ለመስዋዕትነት የቀረበ ሙክት ያድርጉናል። አይሄሄሄ ብዙ አታናግሩኝ እስኪ … ህቅ!!"(ማን ተናገር አለው እስኪ?)… ተሰው አለው ብዬ ተጅብ ተዳብዬ" ነው ነገሩ…ህቅ!! ህቅታው አይሎ!! ሊያስመልሰው ሲዳዳው፣ አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ ሻንፓይኑን አርከፈከፈብኝ በሚል ወደ መስታወቱ በሽሽት ተለጠፈ። (ሊዘል ነው እንዴ?) "ይገርምሃል!! … ለስጣናቸው እድሜ አዎንታዊ ያሉትን  አስተሳሰብ፣ ወደድክም ጠላህም አስረድቶ ከማሳመን ይልቅ በሃይል ይጭኑብሃል። አስተሳሰባችን እኛነታዊነት ያለው በምንፈልገው መልኩ ሳይሆን እነሱ እንደሚፈልጉት መልኩ እንዲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስገድዱሃል። ይህም የመነጨው ከስልጣን ፍቅር የተነሳ ነው። ስግብግብነት በለው። ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ!! ይህን ትውልድ ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድእንኳ በሚፈልጉት በመልኩ ለመግዛት ያላቸው ፍላጎት… ዛሬ የሚሰሩት በመልካም ስም የሸፈኑት ሴራቸው ይናገራል። ለምሳሌ በብሄር ብሄረቦች ቀን ስም ህዝብን ለመለያየት፣ ሌላው ቀርቶ በሚዲያ የሚሰጠው ሰፊ የአየር ሰዓት ምን ያህል ስለ ልዩነት ሰበካ እየለፉ እየደከሙ እያለ የምናውቀው ሀቅ ነው… ህቅ!! ድርጊቱ ምነው ስለ አንድነት እንዲህ ትኩረት በተሰጠ ያስብላል። … እውነት ያንተ ባህላዊ አመጋገብ፣ ያንተ ባህላዊ ጭፈራ፣ ስቧቸው በመልካም መንገድ ወስደውት እንዳይመስልህ…ጉዳዩ ሌላ ነው። ህዝብን ለያይቶ ለመግዛት ካላቸው ፅኑ ፍላጎት እንጂ!! እውን የኢትዮጲያን ጉራማይሌ ውበት ሲተነትኑ እነደሰይመስልህ። የልዩነት እርከኑ ሰፍቶ የክፋት አረም እንዲያፈራ …ነው። አዎ ዛሬ ደግሞ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሚል የበግ ለምድ እንደለበሰ ቀበሮ ላዩን ሸፍነውት ውስጡ መርዝ የሆነውን ሴራ የሚያርከፈክፉብህ…
የመጨረሻ የሚያሳፍረው ድርጊት  ደግም በዚህ ትውልድ ብቻ ሊቆሙ አለመቻላቸው… ህቅ!!  ገና ክፉ ደጉን ለይተው የማያውቁ ህፃናትን በየትምህርት ቤታቸው የትምህርት ገበታ ጊዜያቸውን፣ ለዚህ እኩይ አላማ ማባከናቸው። አንተ የሀደሬ ኮፍያ ለብሰህ ና፣ አንተ የአፋርን ሽርጥ አሸርጠህ አንደትመጣ እያሉ፣ ጨቅላ ህፃናቱን የተለያየን ነን የሚል እሳቤ ይዘው አድገው፣ ለነገ አገዛዛቸው…"

ሰካራሚ ድንገት ንግገሩን ገታ አድርጎ "ሾፌር!! … ምነው ከወትሮው መንገዱ ረዘመብኝሳ፣ መንገዱ ማታ ማታ  ይለጠጣል እንዴ…?"

የተሳፋሪው ሳቅ አጀበው። ካካካካ… ቂቂቂቂ

… ለዛ ይሆን ሲመሽ ታሪፍ የምትጨምሩብን? ካካካካ… ቂቂቂቂ

ሰካራሙ ወሬውን ሳይጨርስ ከመድረሻው አልፎ መሄዱን ሲረዳ…
"አረ አሳለፍከኝ!!  ወራጅ አለ!!" ብሎ እንደ አንደበቱ እየተንተፋተፈ ወረደ።

ጄጃን ከትውስታው ሲመለስ ጃንደረባውና ሙልጌ ተስማምተው፣ ሲሳሳቁ፣ አፍ ለአፍ ገጥመው ሲያወጉ ተመለከተ።

"ከምኔው ፍቅር በፍቅር ሆኑ?"

"አንተ ባገሩ የለህም!! ማለት ነው!! ቆይ ምንድነው ዝም ብለህ ምትቸከችከው፣ ምታሰላስለው? ያው ታቀው የለ!! በኛ ውስጥ ረዥም እድሜ ያለው ፀብ አለመኖሩን። ጃንዴ! ከሰራው ገንዘብ የተወሰነ ቦጨቀለታ።"
የመሻለኪያዊያንን የተካፍሎ መብላት ባህል ጠንቅቆ የሚያውቀው ጄጃን፣ በነገሩ ሳይገረም፣ በስንት ጊዜ አንዴ የሚያፈነጥቀውን ፈገግታ ብልጭ፣ አድርጎ ወደ ዝምተኛነቱ  ባህሪው ተመለሰ።

ወገሬት!!

Sunday, March 19, 2017

" የ ም ሞ ተ ው  ዛ ሬ  ማ ታ … "


#ሳteናw

… አንተ አኔን ልትውሸደኝ? አለው ቡፌት በስራ የመጣ አለመግባባት ከተፈጠረበት ሌላኛውን የመሿለኪያ አባል ሙልጌን፣ ሊሸውደው ያደረገው ጥረት አማሮት…

… አታውቀኝማ ምን ታደርግ? መርካቶን ከፀጉር እስከ ጥፍሯ፣ ሸገርርን ከአፍ እስከ ቂጧ እንደ ማውቃት? ብሽቅ "ከች" ነትን (መጤነትህን) ረስተህ ለዚህም በቃህ? ጉድ ነው "ጋኖች አለቁና፣ ምንቸቶች ጋን ሆኑ" አሉ የሆንክ ጋን ነገር።

ሙልጌ እንደ ላውንቸር ያለ ማቋረጥ የሚንካካውን ሳቁን አጅቦ ለሌላ ሳቅ የሚጋብዝ ጥያቄውን ጣል አደረገ።
"ካካካካ የሸገር አፏ የት ነው? ቂጧስ?"

"እንደሱ ነዋ ሚባለው! አለማወቅህን አውቀህ፣ ለማወቅ መጠየቅህ በራሱ አዋቂነት ነው…
"ለቀማንድህን ትተህ አስኪ… ?" በመልሱ ለመሳቅ ጓግቶ … ሙልጌ

"አፏ ያው ልክ እንዳንተ አፍ ከጧት እስከማታ ጫት ስለማያጣው ጫት ተራ ነው። ቂጧ ደግሞ ቆሼ!።

በምልልሳቸው እንደ ጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታ ተመልካች አንገቱን ከቡፌት ወደ ሙልጌ፣ ከ ሙልጌ ወደ ቡፌት  ያመላልሱ የነበረው የመሿለኪያዋ ወጣቶች። በቡፌት መልስ ሳቃቸውን አፈነዱት… ካካካካከካካ…

   የመሿለኪያን ወጣት አባላት ለየት የሚያደርጋቸው ይህ ነው። ምን አለመግባባት በመካከላቸው ቢፈጠር ይተላለፋሉ። በቀልድ አጅበው መሳቂያ ያደርጋሉ እንጂ ለፀብ ብሎም ለቂም አይገባበዙም። ዛሬም በቡፌትና በሙልጌ መካከል የተፈጠረችው አለመግባባት በቀልድ ተዋዝታ ተደመደመች።

"አረ ባካችሁ ሳቅ ቀንሱ ሼም ነው! ቆሼ ተብሎ ሚታወቀው አካባቢ የቆሻሻው ክምር እንደ በረዶ ግግር ተንሸራቶ ላለቁ ሰዎች የሀዘን ቀን መታወጁን ዘነጋችሁት እንዴ? ቀዥቃዣው ሳተናው ነበር ከልቡ በሆነ ስሜት ጓደኞቹን የገሰፀው።

" በጣም ያሳዝናል? እኔ መጀመሪያውኑ እዛ አካባቢ መኖሪያ ቤት መገንባቱ እራሱ ገራሚ ነው። ለመሆኑ በመንግስት የተመራ፣ ለኑሮ ምቹነት በመሀንዲንስ ቦታው የተጠናና  ይሁንታ የተሰጠው ስፍራ ነው?  እኔ ይህን ለማመን ይቸግረኛል!" አለ አንዱ አባል።

"አዎ ልክ ነህ አደጋው የደረሰባቸው ቤቶች በመንግስት እውቅና ያላቸው ባይሆኑም በዛው አቅራቢያ ህጋዊ ቤቶች አሉ ሲባል የሰማው መሰለኝ፣ ቦታው እኮ እንኳን ለዚህ ዘመን ሰው፣ ከግዝፈታቸው የተነሳ ዛፍ ባአንድ እጃቸው ከስሩ መንግለው መንቀል ይችሉ ለነበሩት ለነቢዩ ሁድ ህዝቦች እራሱ አስጊ፣ ነው … ሳተናው ነበር።

"ከአደጋው ቡሃላ ከንቲባው ከስፋራው ተገኝተው የሀዘን ተካፋይ መሆናቸውና፣ በመግለጫቸውም አደጋው ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ሀዘናቸውን መግለፃቸውን አልሰማህም?"

"ያሳዝናል!! ነዋሪውም ቢሆን በዛ ለጤና ጠንቅ  ለህይወት አስጊ እንደሆነ ባወቀው ስፈራ ላይ፣ "ናዳ መጣብህ ቢሉት፣ ተከናንቤያለው" እንዳለው ሞኝ ሰውዬ አይነት ነገር ቤት መገንባታቸው…"

"… በነሱ አይፈረድም በከተማዋ ያለው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፣ "መጀመሪያ መቀመጫዬን" በሚለው ብሂል ሄደው ነው በዚህ አደገኛ ቦታ ለመኖር ያስገደዳቸውና ህይወት ዋጋ ያስከፈላቸው።" አለሰያ ነጭ ሽንኩርት የዘወትር ልማዱን የኤር ፎን ገመድ ለመቀጠል እየቋጨ።

"ይሄ የከተማችንን የመኖሪያ ቤት ችግር ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ነው…

የከንቲባው ከቦታው መገኘት፣ ከዛ ቡሃላ ከተለያዩ አካላት ከአደጋው የተረፉትን መልሶ ለማቋቋም የተደረገው ርብርብ ይበል የሚያሰኝ ነው… ከንቲባው የተረፉትንና፣ እዛው አካባቢ ላሉ ነዋሪዎች፣ ቦታው ለመኖሪያነት የማይመችና፣ ለአደጋ የተጋለጠ በመሆኑ ሌላ ስፍራ እናዘዋውሯቿለን አሉ! አሉ።

ዘ ይግረም! ነው! እኔ እኮ የሚገርመኝ ይሄ ባህላችን እኮ ነው። አደጋ ከደረሰ ቡሃላ የምንረባረበው ነገር…  አለ በብስጭት …

"እንዴ ሌላው የራሱ ችግር ቋቅ ያለው ህዝብ የነሱን ችግር፣ ቀድሞ በምን ያውቃል?"

… ህዝቡን አላልኩም፣ አስተዳደሩን ነው። ነዋሪዎቹ ከአደጋው በፊት ስጋታቸውን ለሚመለከተው አካል አመልክተው ነበር! አሉ ግን ምላሽ አልነበረም።
በእውነቱ ከሆነ ነዋሪው ከማመልከቱ በፊት ቅድሚያ ሊገነዘቡ የተገባ ነበር። ግን ምን ታደርገዋለህ… ሁሌ እንደሞኝ ከስህተት እንጂ ከመጀሪያው ሊሆን ይችላል በሚል እንደ በሳል አዕምሮ  አይገመትም እኮ። … ትላንት የነዋሪው ስሞታ ላሽ ተብሎ፣ የሀዘን ቀን ማወጅ… ቀድሞው ነው እንጂ አልሞ መዶቀስ…አሉ።

አሁን በማን ሞት ከሚመለከተው አካል ውጪ ለዚህ አደጋ ሀላፍትናውን የሚወስደውስ ማን ነው?  አይ ሲስ ወይም ቦኮሀራም? እንዳልሆኑ መቼም ግልፅ ነው… ችግሩ ከሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ   አለማግኘት ይመስለኛል። ግን እውነት እናውራ ካልን ጉዳዮቹ ቀድመው የሚደፍኑት ቀዳዳ አላቸው !"  አለ አንዱ

"ምንድነው ደግሞ?" አሉ ሁሉም የተመካከሩ ይመስል በአንድ ድምፅ፣ በተሰላቸ ሌላ መርዶ ለመስማት በተዘጋጀ መንፈስ።

"… የፑተለካው ጉዳይነዋ ። በዛ በኩል ፈጣን ናቸው። ከትራንስፎርሜሽኑ እቅድ በእጥፍ እጥፍ እጥፍ  ይቀድማሉ። እንቅፋት ነው ብለው ያገኙትን፣ ምን ያገኙትን የተጠራጠሩት ቀዳዳ በፈጥነት ይደፍኑታል፣ ያዳፉታል ወህኒ ወስደው በሩን ያዳፍኑበታል። አንቀፅ እየደረደሩ የክስ መዝገቡን በአንድ ሺህ ገፅ ይጠርዙለታል። በዶክመንተሪ ፊልም ጥላሸት የመቀባት ስም ማጥፋት ዘመቻ ያፋፍሙበታል። እድሜ እንደ ዳትሰን ሰፈር ደላሎች ጤፍ የሚቆላ ምላስ ላላቸው ልማታዊ ጋዜጠኞች፣ ሆሆሆ።  ከዚህ ውጪ ያሉ ጉዳዮች ቀድሞ ምላሽ የመሰጠት ዕድል የላቸውም። ብቻ ያሳዝናል በስንቱ ኡኡኡ እንደሚባል!   ምንጠይቀው የዛሬ ችግር፣ የእነ ጀለሴ የመልስ ለትናንት። ከህዝብ ጋር እኩል እየተራመዱ አይደለም!!  የትላንቱ አይደፈን ማለት አይደለም ይደፈን፣ ጎን ለጎን የዛሬውም ቢደፈን። እንደ ወጉማ ቢሆን መሪነት በራሱ ከህዝብ ፊት ሆኖ መምራት ነበር!! ጉዳዩ ግን ተገላቢጦሽ ሆኖ ተመሪው በብዙ እርምጃ ከፊት ዛሬ ላይ ቆሞ።፣ እንደ መጥምቁ ዮሃንስ በምድረ በዳ ሰሚ የሌለው ጩኸት ያሰማል። ዛሬ ሰሚ ቢኖር በስንት ጠዓሙ።

ባካቹ ተውት "የምሞተው ዛሬ ማታ፣ ገብስ የሚደርሰው ለፍልሰታ" አይነት ነገር ነው። የኛ ጉዳይ!!  እንደው እኩል ያራምደን ብሎ ከመፀለይ ውጪ ሌላ ምን ይባላል?"
"ምንም" ሲሉ በህብረት መለሱ።
ወገሬት!!!