Tuesday, January 15, 2019

ፍ ቅ ር … የ መ ኖ ር ተ ስ ፋ

ፍቅር … የመኖር ተስፋ
#ሳteናw
ቴዲ ያቀነቅናል…
አይኖቼ አያዩ ብርሃን የላቸው፣በልጅነቴ ድሮ አጥቻቸው፣
ልቤን ተሰማው እንግዳ ነገር፣ምርኩዝ ይዤ ነው የሚውቀው ሀገር።
አለም ታየችኝ ባንቺ ውስጥ ሆና፣ በፍቅር ኩራዝ በላንባዲና።

ቴዲ ልክ ነው፣ ፍቅርን ብርሃን ፈንጣቂ ላንባዲና አድርጎ ማቀንቀኑ ስሜት የሚሰጥ ነው። በተለይ ከኔ ህይወት ጋር… በሚገባ ይጣጣማል የቴዲ ላንባዲና። ይኸው ሙዚቃ  በህይወቴ ሲተነተን ተከታዩን ምስል ይሰጣል።

እርግጥ ነው፣ በልጅነቴም ሆነ አሁን አይኖች የሌሉኝ አይነስውር አይደለሁም። በአይን የገለፅኳት አሳዳጊ አያቴን ነው። አስተዳደጌ በአያቴ እጅ ነበር። እና አአያቴ አይኖቼ ነበረች ብል ዝያጋነንኩ እንዳይመስልህ፣ (ከመሰለህም ሂድበት)። በመሆኑም በአያቴ እጅ ማደጌ፣ ወሰኑን ያለፈ እንክብካቤ እና ፣ ፍቅር እንደ አይን ሆኖኛል። እኔ ልብ ያላልኩትን እንቅፋት፣ ችግር አደጋ…  በአያቴ ተንከባካቢ አይን ይገባና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከአያቴ ይሰጠኛል። እንቅፋቴን ይጠረግልኛል።ችግሮቼን በአያቴ የፍቅር አይን ይወገድልኛል። ካንዣበብኝ አደጋ ይጠብቀኛል። አይን የሆነኝ የአያቴ ፍቅር ብዙ መልካም ነገሮች እዲገጥሙኝ ሆኗል። አያቴ ይህን በነበረን አጭር የህይወት ቆይታ በሚገባ  አለማምዳኛለች። ነገር ግን ላታዛልቀኝ በልጅነቴ ጥላኝ ወደሌላው አለም ነክታዋለች። በልጅነቴ ፍቅሬን አይኔን አጣሁት። አያቴን።

ቴዲ ይቀጥላል …

የአያቴን የፍቅር አይኖቼን በልጅነቴ ማጣቴ ያልተረጋጋ ህይወት እንድመራ ሆንኩ።  ከሌላው ቤተሰብ ጋር ህይወቴ ቢቀጥልም እንደ አያቴ አይኔ መሆን አልቻሉም።  የአያቴን እንክብካቤ ከሌሎቹ ቤተሰቦቼ ማግኘት አልቻልኩም። አያቴ አይታ ትሸፍንልኝ የነበረውን ክፍተት የሚያከናንበው ጠፋ። ይህ ክፉ ልማድ ዘያቴን ካጣሁ ቡሃላ ለማህበራዊ ህይወቴ እንደግርዶሽ ሆኖ በአቅራቢያዬ የሚገኙ መልካም ነገሮችን ጋረደኝ። የባይተዋር፣ የግድ የለሽ፣ ቀቢፀ ተስፋ የህይወቴ እርምጃ ምርኩዜ ሆነ። ይህም ለብዙ ታዛቢ የሚያስታውቅ ምልክት አሳየ ፣ ምክኒያቱም ከአይኖቼ መጥፋት ቡሃላ(ከአያቴ ሞት) ምርኩዜ የሆኑት፣ባይተዋርነትና፣ ቀቢፀ ተስፋዎቼ በግልፅ ያስታውቁብኝ ነበሩ። ልቤን ደስታ ተሰማው። ከመሬት ተነስቶ አልነበረም። በህይወት አጋጣሚ፣  ተላመድኩ። ተዋደድኩ። ተፋቀርኩ። ብቸኝነቴን፣ ባይተዋርነቴን በርሷ ፍቅር አሸነፍኩ፣ ተስፋ አልባነቴን ከሷ ጋር ወደፊት በሚኖረኝ ተስፋ ሞላው። ለተመልካች አስገራሚ ለውጥ አሳየው።

የመኖር ትርጉሞቼ በፍቅር ሰበብ ታዩኝ፣ አላማና ስኬቴ
ይገለፁልኝ ጀመር። ከዚህ ቀደም ባህሪዬ የነበረው ግድ የለሽነት፣ ደብዛው ጠፍቶ ለህይወቴ ግድ መስጠት ግድ አለኝ። በስራዬ ቀልጣፋና፣ በሀይማኖቶ ደህና፣ በማህበራዊ ህይወቴ ንቁ እሆን ገባው፣ የከበበኝ ፅልመት በፍቅር ብርሃን ተገፈፈ። ይህን ለውጤን ያየ የሚያወወቀኝ ሁሉ በግርምት ለፈለፈ። ፍቅር ለምባዲና ሆኖ አለምን አሳየኝ። የፆታ ፍቀር ብቻ አይደለም። ከዚህ ቀደም በፅልመቴ ሳቢያ ትኩረት የነፈኳቸውን  ዘሪያ ገቤ ያሉ መልካም ነገሮች አይቼ አንዳፈቅር ሆንኩ ፣ ለሀገሬ፣ለቤተሰቤ፣ አፀፋዊ ፍቅር ባገኝም ባላገኝም ፍቀር መስጠት እንዳለብኝ ተረዳው፣ እውነተኛ አፍቃሪ ምላሽም ሆነ ምስጋና አይከጅልም። አሁን አየ አይኔ፣ አሁን አየ አይኔ፣ የሚለው የቴዲ ስንኝ በህይወቴ ትርጉም አገኘ።

……
እንደትኮራበት አህንህን ፍቅር ያልነካው ልብህን።
በማየትበ ስለማትበልጠኝ ና መነፅሬን ለውጠኝ።
ፍቅር የለሌለው አይናማ ውጦታልና ጨለማ፣
ሰው ወዶ ሰው ያልወደደው ምርኩዜን መጥቶ ይውሰደው።

ፍቅር መስጠት የማይችል ፍቅር ሊያገኝ አይችልም። ፍቀር ከሌሌ ህይወት ጨለማ ነች የግዞት እስር ቤት ነች። የፍቅርን ሀይል ማወቅ የሚሻ ልቡን ለፍቅር ይክፈት ፣ አለ አይደል ወለለለለል ፣ ነገር።
ፍቅር ብሌን ነው። ፍቅር አይን ነው። ዙሪያ ገብህን የራቀህን ተስፋ የምታይበት መመልከቻ መነፅር ነው።  ፍቅር አጥተህ የታወርክ ካለህ…  የተመልካችነት ስሜት ተሰምቶህ እንዳትኮፈስ፣ ፍቅር አልባ ከሆንክ አምነኝ ታውረሃል፣ ለሀይማኖትህ ፍቅር ከሌለህ፣ በተግባር ያላሳየህ ከሆነ። ሀይማኖተኛ ነኝ የሚል ቃል ትንፍሽ አንዳትል!! በጭራሽ እንዳይዋጣህ!!  ለሀገርህ ያለህ ስሜት፣ የሟሸሸ ከሆነ፣ የተስፋ አይታይህም። ተስፋህ አየር  ላይ አልያም  በፍቀር የመጣ ህይወቴ ተቀይራለችና፣ በተስፋ ሙላት ተሞልታለችና፣ ለሀይማኖት፣ ለቤተሰብ፣ ለህዝቤ፣ ለሀገሬ ፍቅ ር እንዲኖረኝ ገርቶኛልና፣ ልምዴን ተቀበል፣ እንካ መነፅሬን ውሰድና፣ ፍቅር ልበስበት። በጎ በጎውን ተመልከትበት። ሰበብ ሊሆንህ ይችላል። የሀገር ፍቅር ከመሬት ተነስቶ አይገኝምና የኔ ምክር መንገዱን ያሰፋልህ ይሆናል። በፖለቲካና በአስተዳደር የመጣ ያጣኸውን የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ዞር ብለህ በፍቅር መነፅር ሚስኪንወገንህን ተመልከት። የዛኔ በሀገር ፍቅር መንፈስ ትሞላለህ። አንድነትን ታጠናክራራልህ። ለመጥላት ሰበብ የሆነህን ሁኔታ በአንድነት ፍቅር ትደመስሳለህ። የዛኔ ልክ እንደኔው አሁን አየ አይኔን በስሜት ታቀነቅነቀለህ።
ወገሬት!!

Monday, September 24, 2018

የማንነት ጥያቄ

"የማንነት ጥያቄ"
#ሳteናw
ዛሬ የተፈጠረው ነገር ጄጃን
በቤተሰቡ  ላይ የነበረውን እምነት፣ 
የጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶታል።
እናቱን በአንድ አባት የሚጠሩ
እህት ወንድሞቹን፣ እውን የስጋ
ወንድሞቹ መሆናቸውን
ተጠራጥሯል። 

… ገና ጨቅላ ሳለ ሞቶ እንደተቀበረ
የሚያውቀውና በስሙ የሚጠራበት
አባቱን፣ ዛሬ እንደ አዲስ
ሞተ ተብሎ ከአሳዳጊ ሴት አያቱ
ጋር ለቅሶውን ደርሶ ከመጣ
ቅፅበት ጀምሮ አይምሮው የጥያቄ
ጋጋታዎች የሚተራመሱበት፣ መድረክ ሆኗል።
ይበልጥ  የገረመው ደግሞ የአባቱን ሀዘን
በራሱ ቤት የሚደረሰው ሳይሆን፣
ራሱ በሰው ቤት ሄዶ መድረሱ? 
" ቆይ እሺ ዛሬ የሞተው አባቴ ከሆነ!!
የወንድም እህቶቼስ አባት አይደለም? እና
አያቴ ምን ሆና ነው?  እኔን ብቻ ይዛኝ
ምትሄደው?" ይላል ደጋግሞ ለራሱ።
ለጊዜው ማንነቱ ላይ ፍቺውን ያላወቀው
እንቆቅልሽ እንዳለ ገብቶታል!!
"ኡፍፍፍፍ" አለ ከተጋደመበት ሶፋ ወንበር
ላይ ቀና ብሎ እየተንጠራራ።

ተመልሶ ወደ … ሀሳቡ ገባ።
ለዚህ ሁሉ ውዝግብ ያበቃውን የዛሬውን
ገጠመኝ ውሎ አንድ በአንድ በህሊናው
ይከልሰው ጀመር …

… የአስራሁለት አመቱ ጄጃን፣
ከትምህርት ቤት ለምሳ እደተለቀቀ፣
የቀትሩ ፀሀይ መሀል አናቱን እንደድሪል
ቦርቡሮ ሳይበሳው ከሰፈሩ ደረሰ።
ወደ ቤት ዘው ብሎ ሲገባ፣ ከእናቱ በላይ
የሚያፈቅራቸው አሳዳጊ ሴት አያቱ ያለ
ወትሮው ገፅታቸው ላይ የሀዘን ስሜት
አነበበና።

"እማ ምን ሆነሽ ነው? ሲል ጠየቃቸው?"
ገና ደብተሩን ሳያስቀምጥ፣ በፍጥነት
ከጎናቸው መደቡ ላይ እየተቀመጠ።

ጄጃን የእናቱን እናት አያቱን ከወላጅ
እናቱ በላይ ያፈቅራቸዋል! ምክንያቱም
ነብስ ሳያውቅ ጀምሮ በእናትነት ፍቅር
አሳድገውታል። የአያቱን ልጆች ማለትም
አጎት አክስቶቹንም ወንድሜ እህቴ እያለ
ከማደጉም በላይ፣ የሚጠራውም በወንድ
አያቱ ስም ነበር።

  ጄጃን ብዙ ሚስቶች ያለው ወላጅ አባቱን
አይቶት አያውቅም። ስለሱ ሲወራም
አልሰማም። እናቱ አንዳንዴ እናቷ ዘንድ
ስትመጣ ቢያያትም አብሯት ስላላደገ፣እሷ
የእናትነት ፍቅር ልትሰጠው ብትሞክርም
ወላጅ እናቱ እንደሆነች ብትገልፅለትም፣
እሱ ግን የእናትነት ፍቅር ሊሰጣት
አልተቻለውም። ጄጃን የእናትነት ፍቅር
መስጠት የቻለውለአሳዳጊ አያቱ ብቻ
ነው።

"ምንም አልሆንኩም? ዛሬ ከሰዓት
ትምህርት ቤት እንዳትሄድ የምንሄድበት
ቦታ አለ" አሉት አያትየው ፣ አጠገባቸው
የተቀመጠው የልጅ ልጃቸውን ፀጉሩን
እየዳበሱ …
ጥያቄም ልመናም በመሰለ ቃና።

"የት ነው የምንሄደው  እማ?" አለ።
"አንድ የምንደርሰው ለቅሶ አለ" አሉት።
ሌላ ጥያቄ እንዳያስከትልባቸው እየሰጉ።
በአያት ተቀማጥሎ በነፃነት ያደገው ጄጃን።
ሌላ ጥያቄውን በግርምት አስከተለ።

"እንዴ እማ ከኔ ጋር ለቅሶ ሄደን እኮ
አናውቅም። ዛሬ ምን ተፈጠረ?
ደግሞ ማን ነው የሞተው"ጥያቄ ላይ፣
ጥያቄ እደራረበ።

"በቃ እንሄዳለን አልኩህ!" አሉት ትንታኔ
ውስጥ ላለመግባት ጫን ባለ ቃላቸው።

"ጄጃን ከአያቱ አጥጋቢ ምላሽ ባያገኝም፣
ማብራሪያውን ለጊዜው ሊነግሩት
እንዳልፈለጉ ገባውና ዝምታውን መረጠ።
አንደበቱ ዝም ይበል እንጂ፣ አይምሮው
ብዙ ነገር ያወጣል ያወርዳል። የቀረበለትን
ምሳ ከአወዛጋቢ ሀሳቡ ጋር እያላመጠ
አበቃ።

    በአያቱና በጎረቤት እናቶች ታጅቦ ወደ
አላወቀው ለቅሶ ቤት መሄድ ጀመሩ።
በተሳፈሩበት ውይይት ታክሲ ውስጥ፣
የጎረቤት ሴቶች ከዚህቀደሙ ለየት ባለ
የሀዘኔታ አስተያየት ሲያዩት… የበለጠ
ድንግርግር አለው። ከታክሲ መውረጃው
ደረሱ። በአያቱ መሪነት ጥቂት የኮሮኮንች
መንገድ እንደተጓዙ በቆርቆሮ አጥር
የታጠረና በሩ ገርበብ ካለ ጊቢ ደረሱ።

ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሁሉም ሴቶች
የተመካከሩ ይመስል ለቅሷቸውን
በጅምላ  እየለቀቁት ገቡ …
(በሀዘን ቤቱ፣ብዙ ሰው አለመኖርና፣
ጭርታው፣  አንድ ሁለት ቀን ያለፈው
ለቅሶ  ይመስላል።)
አያቱን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች ለሀዘንተኛ
በተደረደው ወንበር ላይ ተደርድረው
ሲቀመጡ ፣እሱም ተከትሎ ከአያቱ
አጠገብ ባለ ክፍት ወንበር ላይ ተቀምጦ
የሚያለቅሰውን ሰው አንድ በአንድ
ይመለከት ጀመር። አጠገቡ ያሉት አያቱ
አልቅስ እንጂ በሚል ይጎሽሙታል።

  ጄጃን የሞተው ማን ይሁን ምን
በማያውቅበት ሁኔታ ማልቀስ አልቻለምና
የአያቱንን ፍላጎት ማሟላት አልሆነለትም።
ዘለግ ካለ ለቅሶ ሁሉም ጋብ ሲል፣
የሀዘንተኛው ሁሉ አይን እሱ ነው።
ነገሩ ከአይምሮው በላይ ሆኖበት ቢጮህና
እውነቱ ቢነገረው በወደደ …  ከአያቱ ጋር
ባደገበት ሰፈር፣ አይነ ደረቅ የሚባልለት
ጄጃን  ያ ሁሉ አይን ሲያርፍበት ሳይፈልግ
በግዱ አይንአፋር ሆነ።

በለቅሶና በሀዘን እጅግ የተጎሳቆሉና፣ ከዚህ
ቀደም አይቷቸው የማያውቅ ሁለት ወጣቶች
(የሟች ልጆች) ከተቀመጡበት ተስፈንጥረው
መጡና… "ቁጭ እራሱን እኮ ነው የሚመስለው"
እያሉ በፍፁም ፍቅር አገላብጠው ይስሙት
ገቡ።"

ጄጃን ከሟች ጋር የሚያገናኘው አንዳች
ነገር  እንዳለ ጠረጠረ። ቆይ ሟቹ ማን
ነው?  ከኔስ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ
ምንድነው? የልጅ አይምሮው ሊፈነዳ ደረሰ።
ቢጨንቀው ወደ አያቱ ዞረና አያቸው።
አያቱም በጭንቀት አዩትና ከሳሙት
ወጣቶች ጋር ለሁሉም የሚሰማ
ወግ ጀመሩ…

"በመጨረሻው ሰዓት ልጆቼን አደራ እያለ፣
ነበር!" ከሳሙት ወጣቶች አንዱ።
… በተለይ የአባት ፍቅር ሳልሰጠው
ከእናቱ እናት ጋር ያደገውን ጄጃንን
አደራ እኔ የነፈኩትን ፍቅር
እናንተ ስጡት፣ እኔን አያውቀኝም፣
እናቱንም እንደዛው፣ ገና ጡት
ሳይጥል ነው ሴት አያቱ ጋር   ማደግ
የጀመረው… እያለ ነው ያረፈው።"
አለ ሳግ በተናነቀው ድምፅ።

ጄጃን  አንድ ነገር መነገንዘብ ቻለ።
ሟቹ ወላጅ አባቱ መሆኑን።
ነገር ግን በአያቱ ቤት እየሰማና
እያመነበት ከኖረው እውነታ ጋር ነገሩ
ተጋጨበት።

  ከዛ ቡሃላ ምን እንደተወራ፣ ከለቅሶው መች
ወጥተው ቤቱ እንደደረሱ ሳያውቀው ራሱን
ካደገበት ቤት አገኘው።

   … የአያቱ ወንድ ልጅ ታላቅ ወንድሙ
ነስሪ ወደቤት መጣ። ቀን የተፈጠረውን
ነገር ሰምቶ በጣም ተቆጣ። በሌላ
ክፍል ውስጥ ከአያቱ ጋር ለምን
ተነገረው? ትልቅ ሲሆን አይደርስም
ነበር ወይ?  በሚል ሲጨቃጨቁ
ይሰማዋል።

አያቱና ነስሪ ጄጀን ካለበት ክፍል መጡ።

ሌላ ጊዜ ቤቱን በአንድ እግር የሚያቆመው
ጄጃን ዛሬ ሶፋው ላይ ትክዝ ጥቅልል
ብሎ ሲያየው ነስሪ ሆዱ ብርዝ አለበት…
እንደምንም ስሜቱን ተቆጣጥሮ …

"ጄጃን" ብሎ ጠራው ። በጥልቅ
ሀሳብ ተክዞ የተቀመጠውን ጄጃን።
"አቤት" አለው በሰጠመበት ዝምታ
እየነቃ።
"አባታችን ማን ነው?" ሲል ጠየቀው።
"እንዴዴዴ!! ያሲን ነዋ አለ" የሚጠራበት
የወንድ አያቱን ስም። በቃ ዛሬም ነገም
ሁሌም አባትህ ያሲን ነው አለው።
ጄጃን በነስሪ ንግግር ትንሽ ቢሆንም
ውስጡ ተረጋጋ።

ቀናቶች ሲፈራረቁ…
ሳምንታት፣ ወር ሲወልዱ… ዕድሜው
እየጨመረና እየበሰለ ሲሄድ ጄጃን
አንድ እውነት ግን መገንዘቡ አልቀረም።
በስሙ የሚጠራበት ያሲን ወላጅ አባቱ
ሳይሆን አያቱ፣ እነነስሪ ወንድሞቹ
ሳይሆኑ አጎት አክስቶቹ መሆናችውን።
(አቦ!! ግን ይሄ ነስሪ ዛሬ የት ሄደ?)

ወገሬት!!

Sunday, August 26, 2018

አ ሰ ብ ት መ ለ ስ ል ን

"አሰብ ትመለስልን "
#ሳteናw

… እኛ ኢትዮጲያዊያን ከሶስት አስርት አመታት በፊት ከ1500 ኪሜ በላይ የሚረዝም የባህር በር እንዳልነበረን ሁሉ፣ ዛሬ ላይ በታሪካዊ ስህተት የባህር በር የማጣታችን ነገር ፣ እንደ አንዳች ነገር ይከነክነኛል፣ ይቆጨኛል፣…  በተለይ በተለይ ለወደብ ሲሉ ደማቸውን የገበሩ ጀግና አባቶቻችንን ሳስብ… ሲያልፍም ሀገሬ በየቀኑ ለወደብ ኪራይ  የምታወጣው ሚሊዮን ዶላሮች፣ እንደቀልድ ያጣነው የባህር በር ኖሮ ቢሆንና ፣ ይህ ለሀገር ውስጥ ልማት ቢውሉ ኖሮ ብዬ ሳስብ። ያሰላም እርርርር ጭስስስስ!!

ይህንን ስሜት አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ወገኔ የሚጋራኝ ይመስለኛል። ለዛሬው የባህር በር ማጣታችን ብዙ ምክኒያቶች መደርደር ቢቻልም፣ በዋናነት ግን በመጨረሻው ዘመን የተደረገው የአልጀርሱ  ስምምነት ይመስለኛል። አዎ በዛ ስምምነት ላይ ኢትዮጲያን "የወከሉት ልኡካን፣ ምን ልኡካን ባንዳ እርግማን ልበላቸው እንጂ!!  በድርድሩ ላይ  ለኢትዮጲያ የባህር በር ማግኘት  ለዘብተኛ አቋም ባይኖራቸው ኖሮ በጊዜው  ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጲያ የባህር በር የማግኘቷ ዕድል ሰፊ እንደነበር በዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም የተፃፈው አሰብ የማን ናት በሚለው መፅሃፍ በዝርዝር ተቀምጣል።

በመሰረቱ  ወደብ አልባ ያደረገን የአልጀርሱ ስምምነት፣ አፄ ሚኒሊክ በጣልያን ተፅዕኖ እጃቸውን ተጠምዝዘው ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ በተዋዋሉት ውል ተንተርሶ የተደረገ ነው። በመሆኑም የኢትዮጲያን ጥቅም ያስጠበቀ አልነበረም። ይህን ያወቁ የኢትዮጲያ ተዋዋዮች ጠበቆች፣ ምን አይነት የኢትዮጲያዊነት ስሜት እንዳላቸው ግልፅ ባይሆንም ሙሉ በሙሉ ኢትዮጲያን የባህር በር ያለምንም ክርክርና  ይግባኝ አስረክበው እጃቸውን እያጨበጨቡ በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ ዘመን አይሽሬ  የበደል በደል የግፍ ግፍ ፈፅመው መጥተዋል።

እርግጥ ነው ከ1500 ኪሎ ሜትር በላይ የነበረው የቀድሞ የኢትዮጲያ የባህር በር ና ቀይ ባህር፣ስትራቴጂክ የሆነ ስፍራ በመሆኑ  በተለያዩ ዘመናትት የውጭ ወራሪዎች በማፈራረቅ ለማስተናገድ ተገዷል። ከወራሪዎቹም  ውስጥ ግብፅ፣ ቱርክ እንግሊዝና ጣልያን በዋናነት ይጠቀሳሉ። ከቅርብ ጊዜ ታሪክ ብንጀምር እንኳ ጣልያን ለ50 አመት፣ እንግሊዝ ለ10 አመት ገዝተዋታል የጥንቷን ሀማሴን የዛሬዋን ኤርትራ!!
ይህም የባንዳ መፈራረቅ በስፍራው ይኖሩ በነበሩ ኢትዮጲያዊያን ላይ የኢትዮጲያዊነት ስሜታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረምና የመገንጠል ፅንሰ ሀሳብ ተፀንሶና ተወልዶ እውን መሆኑ አልቀረም።

ሌላው የባህር በር ለማጣታችን ምክንያት አንዱ የአድዋ ጦርነት ነው።

እምዬ ምኒሊክ በአድዋው ድል  ፣ መረብን አለመሻገራች ለተባራሪው ፋሺሽት ጦር ቀይ ባህር ከመስጠም አዳነው። ሃምሳ አመት ከመረብ ማዶ ባለችው የጥንቷ ሐማሴንና፣  ከአንድ አፋራዊ ግለሰብ የተከራያትን አሰብን  ሰፍቶ ኤርትራ የሚል የሚል ስያሜ አውጥቶ፣ ለሃምሳ አመት ቅኝ ገዛ፣ በሃምሳ አመት ውስጥ በራሱ ስዕብና የተገነባ ትውልድ ተፈጠረ። በዚህ ረጅም ዘመን  ያለፈው የአርትራ  የቀድሞው  ትውልድ በኢትዮጲያዊነት ላይ ምንም ጥያቄ ባይኖረውም በአዲሱ ትውልድ ዘንድ ኢትዮጲያዊነቱ መሸርሸሩ አልቀረም። 
አይ እምዬ ሚኒሊክ ምን ነበር  መረብን ተሻገረው ነጫጭባውን መንጋ ቀይ ባህር ባሰመጡልን ኖሮ።

ሌላኛው አመክኒዮ የፌዴሬሽኑ መፍረስ ነው። በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን ኤርትራ ከኢትዮጲያ ጋር በፌዴሬሽን እንድተዳደር በአለም መንግስታት ተፈርዶ ፌዴሬሽኑ ተግባር ላይ ቢውልም። የኢትዮጲያዊነት ስሜቱ የሚያይልበት የኤርትራ ህዝብ ግን " ለምን በፌዴሬሽን?  ኤርትራ እንደ አንድ የኢትዮጲያ ክልል ትተዳደር " የሚሉ ጥያቄዎች ማንሳታቸው አልቀረም። በኤርትራ ፓርላማ ኤትዮጲያዊ አንድነት አቋም ባላቸው አባላት የድምፅ ብልጫ፣ ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ ተደረገ።

በዚህ የተቃወሙ ሃይላት፣ በኢትዮጲያ ታሪካዊ ጠላቶች ትብብር ጀብሃ የሚባል ታጣቂ ተፈጠረ። አላማውም ኤርትራን ነፃ አውጥቶ በራሳ የምትተዳደር ሃገር ለመመስረት ነበር። ይህ ድርጅት በሃይለስላሴ መንግስት ላይ የራስ ምታት ሆነ። ጀብሃአብዛኛውንና ቆላ የሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚወክል በመሆኑ በደጋውና በክርስትያኑ ህዝብ መካከል ክፍተት ተፈጠረ። ይህንን ክፍተት በመጠቀም የሃይለስላሴ መንግስት ከራሱ ከጀብሃ አባሎች ተገንጥሎ ሻዕቢያ የሚባ ለውን ድርጅት፣ ጀብሃን እንዲያዳክመለት በሚል፣ እንቋቋም ያላሰለሰ ጥረት አደረገ። የአፄው መንግስት ተምኔቱ ሳይሰምር  ቀረ።  ጀብሃን ይሸረሽርልኛል፣ የኢትዮጲያንና የኤርትራን አንድነት  ያስጠብቅልኛል የተባለው ድርጅት ሻዕቢያ፣ ነገሩ ተገላቢጦሽ ሆነና  ለረጅም ዘመናት ለኢትዮጲያ የእሳት አሎሎ ከሆነ ቡሃላ ኤርትራን ከኢትዮጲያ ለመገንጠል፣ በቃ። "አይዋስ ቢዋሰኝ ከባለዕዳ ባሰኝ " ይሉሃለ ይሄ ነው። እነዚህ አመክኒዮዎች እንዳሉ ቢሆንም መግቢያ ላይ በጨረፍታ የተገለጠው  የአልጀርሱ ኢፍትሃዊ ስምምነት ሀገሬን የባህር በር በማሳጣት ረገድ የአንበሳውን ድረሻ ይወስዳል። እንግዲህ የባህር በር ጉዳይ በወፍ በረር ሲቃኝ  ከላይ ያለፈውን ይመስላል።

ያለፈው አልፏል። የአሁኑ ትውልድ ግን በዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ መንገድ ኢትዮጲያን የባህር በር እንድታገኝ ያላሰለሰ ጥረት ሊያደርግ ይገባናል፣ አለበለዚያ የባህር በር ላለማጣት የወደቁ የአባቶቹ አጥንት ይፋረደናል!!

ወገሬት!!

" ስ ጋ ት "


#ሳteናw

  በመንደራች ነዋሪዎች ዘንድ እንደ እናት በምትታየው አያቴ ጋር፣ የህልሞችን ፍቺ እየሰማው በማደጌ ነው መሰለኝ ለህልም ያለኝ አመለካከት አዎንታዊ ነው። ለምሳሌ :- አዲስ ጫማ አድርጎ በህልሙ ያየ፣ ሚስት የማግባት መልዕክት። ጥርስ መውለቅ፣ የሚሞት ሰው መኖሩን።… ወርቅ ማድረግ፣ልጅን የማግኘትን። ወዘተ… ከአያቴ  እና ከማህበረሰቤ በተለያዩ ወቅቶች የሰማዋቸው የህልም ፍቺዎች ነበሩ።

  ትልቅ ከሆንኩም ቡሃላ ከሰውም ከራሴም ህልም እንደተረዳሁት ህልም ለሰው ልጅ ቀድሞ የሚተላለፍ መልዕክት ሁላ ይመስለኛል። አንድ ቀን ታላቋ እህቴ የታችኛው ጥርሷ ወልቆ በህልሟ ማየቷን ስትነግረኝ፣ ስለ ህልም ከነበረችኝ ትንሿ ግንዛቤዬ ማንነቷን ያላወኳት ሴት እንደምትሞት ነገርኳት። እንዳልኩትም በሳምነቱ በጣም የምትወዳት ጓደኛዋ ሞተች።
እንደውም የሆነ ጊዜ እኔ እራሴ በህልሜ የታችኛው ጥርስ ሲነቃነቅ በማየቴ፣ ወይ እናቴ ወይ ከእህቶቼ አንዷ ባትሞትም ጤናዋ ላይ እክል እንደሚገጥማት ፍቺውን ለራሴ ሰጥቼ፣ በስጋት አየጠበኩ ነበር። ፍቺውን ልክ ነበርኩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ውጪ የነበረችው አንዷ እህቴ ለከፋ አደጋ ያላጋለጣት የመኪና ግጭት ደርሶባት ሆስፒታል ውስጥ እንደሆነች አወኩ። እነዚህና የአያቴ የህልም ፍቺዎች ተደራርበው የህልምን  እውነትነት አረጋግጠውልኛል። ነገርን ነገር ያሳዋል አይደለም ነገሩ፣ ህልም ስል አንድ ድሮ በኢቲቪ  ያየሁት ቀልድ ትዝ አለኝ። ቀልዱ እንዲህ ነው…

ብርቱካን የምትባል ልጃቸውን ያፈቀረው ወጣት  የአይን ፍቅሩን ለማስታገስ ህልም በማስፈታት ሰበብ፣ አርጩሜ ይዘው በር ላይ ከተቀመጡት አባቷ ዘንድ ይቀርብና ህልሙን ይተርክላቸው ጀመር። "ተራራማ ቦታ ይመስለኛል … ወንዝም አለ … ከሱ ለጥቆ የዝሆኖች መንጋ ይታየኛል … ከዝሆኖቹ ማዶ ደግሞ የቆመ ትልቅ ጥቁር ሰውዬ አርጩሜ ይዞ  የብርቱካን ተክል  ሲጠብቅ አየው ሲል … (ብርቱካን የምትለዋን ቃል ጠበቅ አድርጎ) እየተፍለቀለቀ ይነግራቸዋል።
… ግሩም ነው ሲሉ ጀመሩ አዛውንቱ። ግሩም ህልም ነው… እንግዲህ ፍቺው… ብለው አቋረጡና  በመጀመሪያ የደንቧን እስር ብር ብለው እጃቸውን ይዘረጉለታል። አውጥቶ ይሰጣቸዋል። ቀጠሉ አዛውንቱ ያው እንግዲህ ተራራው ተራራ ነው፣ እእእ ወንዙም ወንዝ ነው ብለው ፍቺውን ያበቃሉ። እሺሺሺ አለ፣ ህልሙን እንዲጨርሱለት የጠበቀው ወጣት።  ለቀሪው ህልም ተጨማሪ አስር ብር መክፈል እንዳለበት ያረዱታል። አሱም እያጉረመረመ አስር ብር አውጥቶ ይጨምርላቸዋል።
ከወንዙ ማዶ ያየኸው ዝሆንም አይደል? ዝሆኑም ያው ዝሆን ነው ብለው … ያበቃሉ።  ሌላ ፍቹ ቢጠብቅ፣ አይን አይናቸውን እያየ ቢቁለጨለጭ፣ ጭጭ!!
"እንዴ ምንድነው?" ወጣቱ ብስጭት ይላል በፍቺው።
"ምነው ምን ሆንክ?" አሉት።
"ተራራውም ተራራ ነው! ዝሆኑም ዝሆን ነው! ወንዙም ወንዝ ነው! ምን አይነት የህልም አፈታት ነው?" አሁንንም ንድድ እንዳለው ጠየቃቸው።
"እና እንዴት እንድፈታልህ ነው? የፈለከው? ተራራውን ፣ ሜዳ ነው ልበልህ?  ዝሆኑን ጦጣ ነው ልበልህ? ወንዙን ቀይ ባ ህር ነው ልበልህ?  ሲሉ አፈጠጡበት ከሱ ይበልጥ ግለው። ይሄኔ ዋናውና የመጨረሻው ፍቺ እንዳያመልጠው ሰግቶ በረድ ብሎ ቀጣዩን እንዲፈቱልት በመማፀን ገፅታ ጠየቀ። ሌላ አስርብር ተጠየቀ። ከፈለ። ፍቺው ቀጠለ…
"እንግዲህ የህልሙ አስኳል፣ ጥቁሩ ደውዬና ፣የብርትኳኑ ተክል ነው። ብርቱካኑ የኔ ልጅ ብርቱካን ነች። ጥቁሩ ሰውዬ ደግሞ እኔ ነኝ።
ወጣቱ ያፈቀራት ልጅ ስም በመነሳቱ ሲፍለቀለቅ  … ሽማግሌው ቀጠሉ። ወጣት ህልሙ ተፈታልህ አይደል?  በል ሂድ ብርቱካንን መንካት የለም!! እኔ እዚህ የምጠብቀው እሷኑ መስሎኝ! ብለው በያዙት አርጩሜ ጀርባውን ላጥ፣ ሲያደርጉት ተነስቶ ቅድድ።

  ወደ ዋናው ሀሳቤ ስመለስ፣ ለህልም ካለኝ ጥቂት ልምድና አመለካከት ተጨማምሮ ፣ እጅግ በጣም የምወዳት ጓደኛዬ፣ የጥርስ መውለቋን ህልም አናቱ አንዳየች በጨዋታችን መሃል ነግራኝ ስጋት ገብቶኛል  "የእናቷ ፍቺ የችግር መነቀል ነው" መሆኑን ገልፃልኛለች ። በኔ ፍቺ ደግሞ ማን ሊሞት ነው የሚል ጥያቄ ህሊናዬን ወጥሮ እረፍት ነስቶኛል፣ እሷን ነው እህቷን ? አክስቷን ወይስ ማን? በሚለው የጥያቄ ናዳ ህልም ፣ የእውን አለም ስጋት ሆኖብኛል ምን ይሻለኛል? ለነገሩ ተውት "አበው ናቸው እመው? ህልም እንደፈቺው ነው! " ብለው የለ?! በእናቷ ፍቺ ያድርገው በሚለው ፀሎት እስክ እገዙኝ!!

ወገሬት!!

Friday, June 23, 2017

"ሰው > ይበልጣል"

" ሰ ው > ይ በ ል ጣ ል !"
# ሳteናw

"ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ" ልክ ነው። ገንዘብ ካልከፈልክ መች በአውሮኘላን መጓዝ ትችላለህ?  አይደለም መጓዝ። አየርመንገድ ገብተህ ሰው መሸኘትም መቀበልም አትችልም። ዘመኑ የገንዘብ ነው። ይህ ማንም ሊክደው የማችል ሀቅ ነው። ዛሬ ገንዘብ የማይገዛው ነገር የለም። ፍቅር ይገዛል፣ መልካም በማድረግ፣ የሰዎችን ቀልብ በፍቅር ትገዛለህ። "ዉይ! እሱ ቸር እኮ ነው!!" አስብሎ በሰዎች ልብ ቦታ ያሰጥሃል።
ዛሬ ሰው በብሩ፣ እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ባለ ብዙ ሚስት ለመሆን በየቀኑ ሚስት መከራየት ተችሏል።

በገንዘብ ቁንጅናና መልክ ትገዛለህ። በእድሜ ብዛት የተሸበሸበ ቆዳ፣ እንደ ጎማ ታስለጥጣለህ። እድሜ ሰርጀሪ ለሚባል ህክምና። በገንዘብ፣ፆታ ይለወጣል። አዳሞች በብራቸው ሄዋን እየሆኑ ይገኛሉ። ሄዋንያን አዳምን ለመሆን፣ በጭኖቻቸው መሀል ጉጥ ያስተክላሉ። ባል የሌላቸው ባለሀብት ባልቴቶች፣ የወጣት ባል ዝርዝር፣ እንደ ምግብ አይነትበሜኑ ቀርቦላቸው፣ ጠቦቱን፣ ከሙክቱ፣ በላቱ በባቱ እንደበግ አማርጠው ቤታቸው ድረስ ያስመጣሉ። ላስተናገዳቸው ጠቀም ያለ ጉርሻ ይሸጉጣሉ። ወዳጄ በዚህ ዘመን ገንዘብ ከማያደርገው የሚያደርገው ይልቃል። ሀቀኛውን ውሸታም ያሰኛል። ውሸታሙን፣ የእውነት አባት ያስብላል። ዘፋኞች፣
"እያለህ ካልሆነ፣ ከሌለህ የለህም!" በሚል በተወራረሱት ዜማ
የደሃን ሞራል እንክትክቱ አውጥተዋል። ፈጣሪ ይይላቸው!!በቁምህ ሞተሃል ሲሉ ተሳልቀውበታል። የገንዘብ ሰባኪያን እንደ ፈጣሪ " ሁሉን ቻይ ኤልሻዳይ፣ምን ይሳንሃል!"  ምናምን እያሉ አምልከውታል። በውዳሴ ዘምረውለታል።

ዛሬ ላይ የገንዘብ ነገር እዚህ ደረጃ የደረሰ ቢሆንም ቅሉ፣ የገንዘብ አቅም የማይበግራቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ሊያደርጋቸው የማይችሉ ነገሮች የሉም አላልኩም! ወላ አልወጣኝም። እርግጥ ነው ህመምና፣ መድሃኒት ይግዛ እንጂ፣ ጤና አይገዛም። ባልም! ሚስትም! ይግዛ እንጂ በዲኤንኤ ቁርኝት ያለው የአብራክ ክፋይ ልጅ አይገዛም። ልብ በል! ህይወት ያጣፍጣል እንጂ ህይወት አይሆንም።የሰው ዘር በሌለበት፣ ብቻህን ትሪልዮነር ብትሆን፣ እመነኝ ራስክን ታጠፋለህ እንጂ፣ በህይወት ለሶስት ቀን አትዘልቅም። ገንዘብ ስጋን እንጂ መንፈስ አይሸምትም። ቁስ እንጂ ደስታ አያስገኝም። ቅንጡ ቪላ ይገንባ እንጂ፣ የህሊና ምቾት አያስገኝም። ለንብረትህ ኢንሹራንስ ትገባበታለህ እንጂ፣ የወደቀበትን አደጋ አትታደግበትም። ነገርን ነገር ያነሳዋልም አይደል እሚባል። ይህን እውነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ገጠመኝ ልንገርህ። 

… ጊዜው ውድቅት ሌሊት ነው፣ ቦታውም የንግድ ቤቶች ከዳር እስከዳር ተገጥግጠው ባሉበት መርካቶ። ባለሀብት ተብዬ ፣ አገር አማን ብሎ ሱቁን  ቆልፎ፣ ሄዷል። ቆልፎ መሄድ ብቻ ሳይሆን በገንዘቡ የቀጠራቸው ዘቦቹን አስጠብቋል። ድንገተኛ እሳት ከአንዱ ሱቅ ይነሳል። ዘብ ተብዬው እንቅልፉን ዧ ብሎ ተኝቷል። ይህን እሳት ማን ያያል በአቅራቢያው ያለ በረንዳ አዳሪ ወንድሞች። ተጯጩሆ ና ተረባርቦ፣ እሳት የተነሳበትን ሱቅ በር ገንጥለው።  እሳቱን ያጠፉታል። በዚህ የመጣ በግራና በቀኝ የነበሩ ብዙ ሱቆች፣ የእሳት እራት ከመሆን ይተርፋሉ። ልብ በሉ! ሱቆቹ ቢወድሙ ቢድኑ የሚጠቀመው የሚጎዳው ባለ ሀብቱ እንጂ፣ እነዚህ ሰዎች አይደሉም። እንቅልፍ አጥተው ያዳኑት ንብረት ለጌታው እንጂ ለነሱ ምንም እንዳልሆነ እያወቁ ነው። ለባለ ንብረቱ፣ ከገንዘቡ ቀድመው የደረሱ እኚሁ ከሌላችሁ የላችሁም የተባሉ ምስኪን ወንድሞች ናቸው። የመርኬው ባለ ሱቅ፣ ከአደጋው የታደገው ገንዘቡ ሳይሆን ሰው ነው። ምነው "ከሌለህ የለህም" ያሉ ሁሉ! ኖረው ይህን ባዩ! እርግጠኛ ነኝ "ባይኖርህም፣ ትኖራለህ፣ ቢኖርህም፣ ትሞታለህ" በሚለው ቀይረው ነጠላ ዜማ ይለቁ ነበር። ያም ሆነ ይህ የሚቀድመውገንዘብ ሳይሆን ሰው ነው። የነገርኩህ አጋጣሚው ለዚህ ምርጥ ማሳያ ነው። በመሆኑም ከሰው ገንዘብን ያስቀደምክ ወንድሜ ሆይ! ስማኝ!! ያመለከው ሀብት የዘመርክለት ንዋይ፣ በእሳት ጠፍቶ እንዳያጠፋህ፣ ደርሶ እሳቱን ያጠፋልህ፣ሰው ነው። በድሎት ዘመንህ፣ በረንዳ ሲያድር  ዞረህ ያላየከው፣ ወንድምህ ነው። ለዛውም
ከሌለው የለም ስትል የተዘባበትክበት ወንድምህ። ባይኖረውም ኖሮ! ንብረትህን ካለመኖር አደጋ ተረባርቦ እንዲኖር፣ አድርጎ አኑሮ ያሳየህ!
ስማኝ ወንድሜ!! በሀብት ሰበብ የመጣ የስኳርና የደም ግፊት በሽታ በማትታወቅበት ስፍራ ድንገት ጥሎ ጣር ቢያንፈራግጥህ፣ ቀድሞ የሚደርስልህ፣ ሳይፀየፍ አፋፍሶ የሚያነሳህ፣ ሰው እንጂ ገንዘብህ አለመሆኑን እወቅ። አቅም ሲከዳህ፣ የሚደግፍህ ሰው እንጂ ብር አንዳይደለ ተረዳ። ብትሞት፣ ቀድሞ ደርሶ የአሞራ ሲሳይ ከመሆን ታድጎ፣  በወጉ ከፍኖ የሚቀብርህ ሰው ነው። የትራፊክ ህግ ለራስህ ደህንነት ስትል፣ ቅድሚያ ለእግረኛ ስጥ! ይልኻል። እኔም እልሃለው ለራስህ ስትል ቅድሚያ ለሰው ስጥ።
ወገሬት!!

Tuesday, June 20, 2017

" እ ወ ዳ ታ ለ ው "

" እ ወ ዳ ታ ለ ው "
#ሳteናw

… አቤት ስወዳት!! እንደሷ የምወደው ሴት ምድር ላይ አለ እንዴ? እኔንጃ ያለ አይመስለኝም!! በጣም ውድድድድ በቃ!! እስኪገርምህ ድረስ። ብወድሽ ብወድሽ አለሰለችህ አለኝ! ሲል ቴዲ ለፍቅረኛው ቢዘፍንም እኔ ግን ይህን ዘፈን የምዘፍነው ማህፀን ለምትጋራኝ እህቴ ነው። ይገርምሃል!! ነብሱን ይማረውና አባቴ በስነ ተዋልዶ ዙሪያ ታታሪ ተራቢ ነበርና ብዙ እህቶች አሉኝ። የእህት ሀብታም ነኝ። እንደሷ ልወዳቸው ብሞክር እንኳ አልተሳካልኝም። መውደድን ስለፈለከው ሳይሆን፣ የውስጥ ስሜትህ የሚሰጥህ መሆኑን እዚህች ጋር በቀይ እስክሪብቶ አስምርበት። እስክሪፕቶ አልያዝክም? በቃ የሃሳብ መስመር አስምርበት። ልትወደው ብትሞክር እንኳ የማይሳካልህ ነገር ገጥሞህ አያውቅም? ሌሎቹ እህቶቼ በህፃንነቴ ቢንከባከቡኝ፣ ሀቢቢ፣ገልቢ፣ ሩሂ፣ ምናምን እያሉ ከመካከለኛው ምስራቅ በተዋሱት  ቋንቋ ቢያቆላምጡኝ!! በሰቅሉኝ፣ቢክቡኝ፣ ቢቆልሉኝ ወላ ሃንቲ!! እሷግን እየተጣላንም፣ እየኮረኮመችኝም፣እየሰደበችኝም ከጓደኞቿ ጋር ስታወራ "ምንድነው?" ብዬ አፌን ከፍቼ ልሰማ ፈልጌ፣ ሂድ ውጣ ሴታ ሴት ብላ፣ ነጠላ ጫማ ወርውራ ብታባርረኝም! እወዳታለው። ወረኛ እንድሆንባት አትፈልግማ!!

አቤት!! የውዴታዬ ብዛት! ስህተተኛ ብትሆን እንኳ ለሷ ወግኜ ከእህቶቼ ጋር ተጣልቻለው። ለምን ቅር አሰኟቿት ስል ለረጅም ግዜ አኩርፌያቸዋለው። ስህተቷን የሚጋርድብኝ ኢፍትሃዊ ሆኜ አይደለም። ወይም ከሷ የተለየ ነገር ስለምጠቀም አይደለም። በቃ ለረጅም ግዜ ከሌሎቹ በተለየ አብሮ ማደጋችን የቸረኝ ፍቅር። የሚገርመው የፍቅር ልውውጣችን ለሁለታችን እንጂ ለማንም አያስታውቅም። አጠገብ ላጠገብ፣ ስንከራከር ስንጨቃጨቅ ብታየን። "ድንቄም መዋደድ ብለ ልታሽሟጥጥ ትችላለህ" (ያው ማሽሟጠጥ ስራህም አይደል!!)። አይገባህማ!! ፍቅራችን ለራሳችን እንጂ ላንተ አይታይህማ። እንዲታይህ የኔን አይን ተከራይተህ እሷን፣ አልያም የሷን ማያ ተውሰህ እኔን ማየት አለብህ።  የዛኔ ትረዳዋለህ።

  የዝንጀሮ ባል፣ ሲላፋት ሲያጫውታት፣ አይተህ አቤት ፍቅራቸው ሮሚዮና ጁሊየት ምናምን ትል ይሆናል።  እውነት አይምሰልህ። አንድ ቀበሮ ቢመጣ ፈሱን እያንጣጣ ነው ጥሏት የሚነካው። ኮስተር ጀንተል ብሎ ከሚስቱ አጠገብ የተቀመጠ አንበሳ አይተህ ደግሞ "ምን እንደባላባት ይጀነናል!" ትልም ይሆናል  አንድ አደጋ ቢከሰት ቀድሞ ይሞታታል እንጂ፣ እንደ ዝንጀሮው ጥሏት አይነካውም። አየህ የተግባር ፍቅር ይሉሃል ምሳሌው ይሄ ነው። ለሰው የማይታይ በልብ ያለ ፍቅር!! በለው። የኛንም ፍቅር በዚህ መስለው። "ካላየው አላምንም ብለህ ከገተርክ ተወው"። ነገር ግን ሳያዩ ያመኑ ብፁአን ናቸው። የሚለውን የመፅሀፍ ቅዱስ አንቀፅ አስታውስሃለው። እኔ ለሷ የማልሆነው ነገር ቢኖርም፣ እሷ ለኔ ማትሆነው የለም!! ለኔ ካሏት ህይወቷን እስከመስጠት ትደርሳለች። ይሄን ዝም ብዬ የምተረተረው ሳይሆን በተደጋጋሚ በእውነታ ያረጋገጥኩት ሀቅ ነው። ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደልም እሚባል። ከነሱም ውስጥ አንዱን ገጠመኝ ልንገርህ።

…  ከአስር አመት የአረብ አገር ቆይታ ብኋላ ይሕቺው ውዷ እህቴ ለአገሯ በቃች። በዚህም ደስታችን ወደር አጣ። በሀሴት ሰከርን። በዛው ሰሞን የቀድሞ ህይወቷ በገጠር የነበረውን እናታችንን ለመጠየቅ፣ በሷ እስፖንሰርነት ወደ አገርቤት፣ ሁለት ዘመዶቻችንን አስከትለን ሄድን።

በአገር ቤት የነበረን ቆይታ ከትውስታ የማይጠፋ አስደሳች ነበር። እንደቱሪስት ተዝናናን።በመጨረሻም መዝናናታችን፣ ሮንግ ተርን እንደሚለው ፊልም ጫካ ለጫካ በጨለማ በመረራሯጥ ተፈፀመ እንጂ። በገጠር የነበረን አስደሳች ቆይታ፣ የመጨረሻው ምሽት ተከታዩ ነበር።
በምሽቱ በእናታችን ጎጆ ቤት ውስጥ የነበረው ድባብ ደማቅ ነበር። ወዳጅ ዘመድ በቤቱ ተኮልኩሏል። ከምድጃው አጠገብ ባለው ቋሚ ምድጃ ላይ የሚነደው ፍልጥ ከሙቀት አልፎ የቤቱ ብርሃን ሆኗል። እስከዛሬ ድረስ ቃናው የማይረሳኝን የቡና ቁርስ ቆጮ በአይብ በልተን አብቅተናል። ጨዋታው ደርቷል። በአንድ በኩል እናቴ ቡናዋን እንደያዘች ከጎረቤት ሴቶች ጋር ወግ ይዛለች።  እኔ ከታላቅ እህቴ እግር ላይ ተንተርሼ፣በጀርባዬ ተኝቼ፣ ፀጎሬንእንደማከክ ስትደባበሰኝ፣ በልጅነቴ የአያቴን ድርጊት አስታውሶኝ በሃሳብ ነጉጃለው። እሷ አብረውን ገጠር ከሄዱት የወንድሜ ሚስትና፣ የታላቅ እህታችን የባል ወንድም ጋር የጋራ ወይይት ይዘዋል። ከጎጆ ቤቷ ክበብ የሩብ ጨረቃ ቅርፅ ባለው በአንዱ ጥግ ላይ ባለው በረት ውስጥ ያሉ ከብቶች፣ በየመሃሉ ድምፃቸውን ሲያጓሩ፣ የገጠር ህይወን ከማጉሏታቸው ባሻገር፣ በቤቱ ድባብ የተደሰቱ ይመስላሉ። ከበረታቸው በላይ ያለው የማገዶ እንጨት ማከማቻ ቆጥ ነገር ላይ ባለው የዶሮ ቅርጫት ውስጥ ያሉ ዶሮዎች እንደ አላርም ሰዓት እየጠበቁ ይጮሃሉ። በሌላ ጥግ የታላቅ ወንድማችን ልጆች " በየመሃሉ የእናታቸውን እናንተ ልጆች አድቡ" የሚለውን ግሳፄ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ይላፋሉ፣ይስቃሉ፣ ይጣላሉ፣ ያለቅሳሉ። መልስው ይጫወታሉ።(አይ የልጅ ነገር።  ሁሉም በየራሱ ሙድ ፍንትው ብሏል።






ታላቅ ወንድሜ(ጉዳዩ) ብቻ ከበሩ አጠገብ ባለ በርጩማ ወንበር ላይ ገፅታውን አኮስሶ ተቀምጧል። ይህ ሁኔታው አላማረኝም። ይህን ሀሳቤን ለእህቴ በሹክሹክታ አካፈልኳት። "እሷም፣ ስጋቴ ገብቷት ኖሮ ህመሙ ሊነሳ ሲል እንዲህ ያደርገዋል" ብላ የማውቀውን የበሽታ አጀማመሩን አስታወሰችኝና። ወደ ጨዋታዋ ተመለሰች። አንድ የአጎቴ ልጅ ሰላምታ አስቀድማ ገባችና፣ ከነ እናቴ ስብስብ ተቀላቀለች።

ይህ መልካም ምሽት በንደዚህ ሁኔታ አልፎ ፣ግማሹ ወዳጅ ዘመድ ጠብጠብ፣ ደህና እደሩ እያለ ቀስ በቀስ ጭር ማለት ጀመረ።

ጉዳዩ ከተቀመጠበት በርጩማ ድንገት ፍንጥር ብሎ ተነሳና እንደጦጣ እየተንጠላጠለ፣ ከበረቱ በላይ ካለው እንጨት ማከማቻ ወጥቶ አንዳች እቃ እያተረማመሰ ይፈልግ ጀመር። በቤቱ ያለነው በሙሉ ትኩረታችን እሱ ላይ ሆኖ፣ በመድረክ ላይ ሰርከስ እንደሚያይ ተመልካች እናየዋለን።

ፍልጦቹን አተራምሶ አተራምሶ፣ የፈለገውን ነገር ሲያጣ፣ አንድ ትልቅ ፍልጥ አንደ ቀስት ወርዋሪ ፍልጡን ይዞ ቆመ። ሁኔታውን ስናይ ወደኛ ለመወርወር የተዘጋጀ ይመስላል።
"ተነሽ አንቺ ብሎ" ምቾቴ ሆና በተተንተራስኳት እህቴ ላይ ጮኸ። ጉዳዩ ከኔ ጋር መሆኑን ነጋሪ አላሻኝም። ብድግ ብዬ ቆምኩና "ወርደህ አነጋግረኝ?" ብዬ መፎከር ጀመርኩ።።ሁሉም ካለበት በድንጋጤ ቆሞ ይለምነው ገባ። ፍልጡን ወደኔ ለመወርወር ኢላማውን ለማስገባት ወደኔ አቅጣጫ አንድ ሁለት አያለ እንደመወርወር አደረገና በሶስተኛው ፍልጡን ወረወረው፣ በዚሁ ቅፅበት እህቴ ለተወረወረብኝ ፍልጥ እንደጋሻ በራሷ ልትመክት መጥታ ተለጠፈችብኝ። በትልልቅ አይኖቿ በሚሰረስር አስተያየት አፍጥጣበታለች። እንደሌሎቹ ሳትጮህ ሳትንጫጫ ጋሻዬ ሆናለች። የተግባር ፍቅር ተመልከት።

የተወረወረው ፍልጥ ማናችንንም ሳያገኝ ተመዘግዝጎ እግራችን ስር ወደቀ። እኔ እህቴን ከራሴ ለማላቀቅ እየታገልኩ እጮኻለው "ወንድ ከሆንክ ወረድና አናግረኝ" እሱ ሌላ ፍልጥ አነሳ ኢላማውን አስተካክሎ ድጋሚ  ወረወረ። የጎጆ ቤቱ ምሰሶ ጨርፎ አቅጣጫውን አስቶት በሚነደው ምድጃ ላይ ወደቀ። የእሳትና የአመድ ብና ጎጆዋን የዘመን መለወጫ ርችት የተተኮሰባት ሰማይ በጭስ፣ አመድና የእሳት ፍንጣሪ! ተሞልታ፣ በጨለማ ተዋጠች። ማንም ከማንም መተያየት አልቻለም ጫጫታና ጩኸት ብቻ።

እህቴን እንዳቀፍኩ የሆነ ሰው እጄን ይዞ እንድከተለው ጎተተኝ። እሷን ይዤ የሚገትተኝን እጅ ተከትለን ከቤቱ ወጥተን መሮጥ ጀመርን። ውጪውም እልም ያለ ጨረቃ የሌለበት ጨለማ ነበር። ወዴት እንደምንሄድ ሳናውቅ እየጎተተኝ የሚሮጠውን እጅ፣ እየተከተልን፣ በባዶ እግር መሄድ ያለመደው እግራችን እንደልብ እንዳንሮጥ ቢያግደንም፣ ጭቃው ቢያዳልጠንም፣ በማይታየው ጨለማ ሮጥን። መሪያችን እንዴት ታይቶት እንደሚመራን አላውቅም። አይኔ ጨለማውን እየለመደ እየለመደ መጥቶ በመጠኑም ቢሆን ይታየኝ ጀመር። የግቢ አጥራችንን ለቀን በአውራ ጎዳናው ቁልቁል ወረድን። የምትመራን ሴት ትሁን እንጂ ማን ትሁን ወዴት ትወሰደን የማውቀው ነገር አልነበረም። ወደ አንፍ ጎጆ አጥሩን አልፈን ወደ በሩ ተጠጋን። መሪያችን በሩን አንኳኳች። ""ማነው?" መሪያችን "እኔ ነኝ" ስትል በድምፇ አወኳት። የአጎቴ ልጅ ነበረች። በሩ ተከፈተ። ውጪ ከነበረው ጭለማ አንፃር፣ ጎጆ ውስጥ የምትንጨላጨለው ብርሃን በቂ ነበረች።  የከፈተችውም የአጎታችን ልጅ መሆኑን አወኩ። በድንጋጤ ክው ብላ ደርቃ ቀረች። ከሁኔታችን አንዳች ነገር ሸሽተን እንደመጣን ታውቋታል። መርታ ያደረሰችን የአጎቴ ልጅ በሩን ከውስጥ ቀርቅራ፣ ወደ መቀመጫው እያመላከተችን፣ የተከተለን ሰው ይኑር አይኑር በሩ ተለጥፈፋ አጣራችና መጥታ ከጎኔ ተቀመጠች። "ተረፋቹ? ፍልጡ አገኘኛቹ እንዴ?" አለችኝ። እህቴ ድንጋጤ አልለቀቃትም እንደተለጠፈችብኝ እየተንቀጠቀጠች ታለቅሳለች። "አይ አልነካንም" አልኳት። በድንጋጤ ደርቃ ቀርታ የነበረችው የአጎቴ ልጅ ፣ መሪያችን የሆነውን ሁሉ ስትነግራት። ድንጋጤዋ በረታ። "አዎ ቀን ሀያት(የወንድሜን ሚስት ማለቷ ነው) ሲነሳበት የሚይዘውን ጦር ከቆጥ አውርዳ፣ ስትደብቅ፣ አይቻት። ምን ሆነሽ ነው? ስላት። "ዛሬ ሁኔታው አላማረኝም" ብላኝ ነበር። እንደገመተችው ተነሳበት ማለት ነው?" አለች። አንዳች ነገር ከእግር እስከጥፍሬ አንጨረጨረኝ። አላገኘውም እንጂ ሊወረውርብኝ ሲፈልግ የነበረው ጦር ነበር ማለት ነው? ። ንዴት ይሁን ድንጋጤ ወረረኝ። "እሺ እንግዶቹን አዛው ጥዬ ነው የመጣሁት ይዣቸው ልምጣ አልኩ። የአጎቶቼ ልጆች አልፈቀዱልኝም። ቢፈቅዱልኝም በትክክል በጨለማው መሄድ መቻሌ እ ራጠራለው። "እኔ ሄጄ አመጣቸዋለው! ብላ መሪያችን በሩን ከውስጥ እንድትቀረቅር ለሌላኛው የአጎቴ ልጅ ነግራት ወጥታ ሄደች። እኔም እህቴም የሆነው ነገር ሁሉ እውነት እውነት አልመስል ብሎናል። ከአፍታ የነበርንበት ጎጆ በር ተንኳኳ። ድምፃችን አጠፋን።ልጅቷ ወደ በሩ ተጠግታ በማንሾካሾክ "ማን ነው አለች። መሪያችን ነበረች። እንግዶቹን ይዛ መጣች። እነሱም ድንጋጤ አርበትብቷቸዋል። ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰው ባዳ በመሆናቸው ድንጋጤያቸው ከኛ ቢበዛ እንጂ አያንስም ነበር። ቀስ በቀስ ተረጋጋን። እኔቴና በቤቱ የነበሩ ሁሉ ጓዛችንን እንደያዙ ያለንበት ጎጆ መጡ። ተረፋችሁ ብለው ከጠየቁን ቡሃላ።  እኛ ከቤት ከወጣን ቡሃላ ስለተፈጠረው ነገር ነገሩን። ወንድሜ ይህን ከፈፀመ ቡሃላ የተፈጠረውን ነገር ማወቅ አልቻለም። ነብሱ በደንብ ከተመለሰች ቡሃላ እኛን"የት ሄደው ነው? " ብሎ  መጠየቁን። እራቱን በልቶ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ እንደወሰደው ነገሩን። ያደረገውን ነገር አለማወቁ፣ በሱ እንዳንፈርድ አደረገን። ወደ አይደለም አልን።  እናቴ ግን ነገውኑ ወደ ከተማ እንድንመለስ አስጠነቀቀችን። ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም ለማንኛውም እናንተ ሂዱ። እኛ እንደሚሆን እናደርጋለን ብላን። አስደሳቹን ጊዜ በአሳዛኝ ሁኔታ አጠናቀን፣ በማግስቱ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ። ይህን ሁሉ ልዘበዝብልህ፣ የቻልኩት ለኔ ካሏት መስዋዕት ትከፍላለች ባልኩህ እህቴ ሰበብም አደል። አዎ!! ዛሬም ነገም! እወዳታለው!!

ወገሬት!!