Friday, June 23, 2017

"ሰው > ይበልጣል"

" ሰ ው > ይ በ ል ጣ ል !"
# ሳteናw

"ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ" ልክ ነው። ገንዘብ ካልከፈልክ መች በአውሮኘላን መጓዝ ትችላለህ?  አይደለም መጓዝ። አየርመንገድ ገብተህ ሰው መሸኘትም መቀበልም አትችልም። ዘመኑ የገንዘብ ነው። ይህ ማንም ሊክደው የማችል ሀቅ ነው። ዛሬ ገንዘብ የማይገዛው ነገር የለም። ፍቅር ይገዛል፣ መልካም በማድረግ፣ የሰዎችን ቀልብ በፍቅር ትገዛለህ። "ዉይ! እሱ ቸር እኮ ነው!!" አስብሎ በሰዎች ልብ ቦታ ያሰጥሃል።
ዛሬ ሰው በብሩ፣ እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ባለ ብዙ ሚስት ለመሆን በየቀኑ ሚስት መከራየት ተችሏል።

በገንዘብ ቁንጅናና መልክ ትገዛለህ። በእድሜ ብዛት የተሸበሸበ ቆዳ፣ እንደ ጎማ ታስለጥጣለህ። እድሜ ሰርጀሪ ለሚባል ህክምና። በገንዘብ፣ፆታ ይለወጣል። አዳሞች በብራቸው ሄዋን እየሆኑ ይገኛሉ። ሄዋንያን አዳምን ለመሆን፣ በጭኖቻቸው መሀል ጉጥ ያስተክላሉ። ባል የሌላቸው ባለሀብት ባልቴቶች፣ የወጣት ባል ዝርዝር፣ እንደ ምግብ አይነትበሜኑ ቀርቦላቸው፣ ጠቦቱን፣ ከሙክቱ፣ በላቱ በባቱ እንደበግ አማርጠው ቤታቸው ድረስ ያስመጣሉ። ላስተናገዳቸው ጠቀም ያለ ጉርሻ ይሸጉጣሉ። ወዳጄ በዚህ ዘመን ገንዘብ ከማያደርገው የሚያደርገው ይልቃል። ሀቀኛውን ውሸታም ያሰኛል። ውሸታሙን፣ የእውነት አባት ያስብላል። ዘፋኞች፣
"እያለህ ካልሆነ፣ ከሌለህ የለህም!" በሚል በተወራረሱት ዜማ
የደሃን ሞራል እንክትክቱ አውጥተዋል። ፈጣሪ ይይላቸው!!በቁምህ ሞተሃል ሲሉ ተሳልቀውበታል። የገንዘብ ሰባኪያን እንደ ፈጣሪ " ሁሉን ቻይ ኤልሻዳይ፣ምን ይሳንሃል!"  ምናምን እያሉ አምልከውታል። በውዳሴ ዘምረውለታል።

ዛሬ ላይ የገንዘብ ነገር እዚህ ደረጃ የደረሰ ቢሆንም ቅሉ፣ የገንዘብ አቅም የማይበግራቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ሊያደርጋቸው የማይችሉ ነገሮች የሉም አላልኩም! ወላ አልወጣኝም። እርግጥ ነው ህመምና፣ መድሃኒት ይግዛ እንጂ፣ ጤና አይገዛም። ባልም! ሚስትም! ይግዛ እንጂ በዲኤንኤ ቁርኝት ያለው የአብራክ ክፋይ ልጅ አይገዛም። ልብ በል! ህይወት ያጣፍጣል እንጂ ህይወት አይሆንም።የሰው ዘር በሌለበት፣ ብቻህን ትሪልዮነር ብትሆን፣ እመነኝ ራስክን ታጠፋለህ እንጂ፣ በህይወት ለሶስት ቀን አትዘልቅም። ገንዘብ ስጋን እንጂ መንፈስ አይሸምትም። ቁስ እንጂ ደስታ አያስገኝም። ቅንጡ ቪላ ይገንባ እንጂ፣ የህሊና ምቾት አያስገኝም። ለንብረትህ ኢንሹራንስ ትገባበታለህ እንጂ፣ የወደቀበትን አደጋ አትታደግበትም። ነገርን ነገር ያነሳዋልም አይደል እሚባል። ይህን እውነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ገጠመኝ ልንገርህ። 

… ጊዜው ውድቅት ሌሊት ነው፣ ቦታውም የንግድ ቤቶች ከዳር እስከዳር ተገጥግጠው ባሉበት መርካቶ። ባለሀብት ተብዬ ፣ አገር አማን ብሎ ሱቁን  ቆልፎ፣ ሄዷል። ቆልፎ መሄድ ብቻ ሳይሆን በገንዘቡ የቀጠራቸው ዘቦቹን አስጠብቋል። ድንገተኛ እሳት ከአንዱ ሱቅ ይነሳል። ዘብ ተብዬው እንቅልፉን ዧ ብሎ ተኝቷል። ይህን እሳት ማን ያያል በአቅራቢያው ያለ በረንዳ አዳሪ ወንድሞች። ተጯጩሆ ና ተረባርቦ፣ እሳት የተነሳበትን ሱቅ በር ገንጥለው።  እሳቱን ያጠፉታል። በዚህ የመጣ በግራና በቀኝ የነበሩ ብዙ ሱቆች፣ የእሳት እራት ከመሆን ይተርፋሉ። ልብ በሉ! ሱቆቹ ቢወድሙ ቢድኑ የሚጠቀመው የሚጎዳው ባለ ሀብቱ እንጂ፣ እነዚህ ሰዎች አይደሉም። እንቅልፍ አጥተው ያዳኑት ንብረት ለጌታው እንጂ ለነሱ ምንም እንዳልሆነ እያወቁ ነው። ለባለ ንብረቱ፣ ከገንዘቡ ቀድመው የደረሱ እኚሁ ከሌላችሁ የላችሁም የተባሉ ምስኪን ወንድሞች ናቸው። የመርኬው ባለ ሱቅ፣ ከአደጋው የታደገው ገንዘቡ ሳይሆን ሰው ነው። ምነው "ከሌለህ የለህም" ያሉ ሁሉ! ኖረው ይህን ባዩ! እርግጠኛ ነኝ "ባይኖርህም፣ ትኖራለህ፣ ቢኖርህም፣ ትሞታለህ" በሚለው ቀይረው ነጠላ ዜማ ይለቁ ነበር። ያም ሆነ ይህ የሚቀድመውገንዘብ ሳይሆን ሰው ነው። የነገርኩህ አጋጣሚው ለዚህ ምርጥ ማሳያ ነው። በመሆኑም ከሰው ገንዘብን ያስቀደምክ ወንድሜ ሆይ! ስማኝ!! ያመለከው ሀብት የዘመርክለት ንዋይ፣ በእሳት ጠፍቶ እንዳያጠፋህ፣ ደርሶ እሳቱን ያጠፋልህ፣ሰው ነው። በድሎት ዘመንህ፣ በረንዳ ሲያድር  ዞረህ ያላየከው፣ ወንድምህ ነው። ለዛውም
ከሌለው የለም ስትል የተዘባበትክበት ወንድምህ። ባይኖረውም ኖሮ! ንብረትህን ካለመኖር አደጋ ተረባርቦ እንዲኖር፣ አድርጎ አኑሮ ያሳየህ!
ስማኝ ወንድሜ!! በሀብት ሰበብ የመጣ የስኳርና የደም ግፊት በሽታ በማትታወቅበት ስፍራ ድንገት ጥሎ ጣር ቢያንፈራግጥህ፣ ቀድሞ የሚደርስልህ፣ ሳይፀየፍ አፋፍሶ የሚያነሳህ፣ ሰው እንጂ ገንዘብህ አለመሆኑን እወቅ። አቅም ሲከዳህ፣ የሚደግፍህ ሰው እንጂ ብር አንዳይደለ ተረዳ። ብትሞት፣ ቀድሞ ደርሶ የአሞራ ሲሳይ ከመሆን ታድጎ፣  በወጉ ከፍኖ የሚቀብርህ ሰው ነው። የትራፊክ ህግ ለራስህ ደህንነት ስትል፣ ቅድሚያ ለእግረኛ ስጥ! ይልኻል። እኔም እልሃለው ለራስህ ስትል ቅድሚያ ለሰው ስጥ።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment