Saturday, June 10, 2017

"ጉ ራ = ብ ቻ!"


#ሳteናw

   ምድሪቷ መንጋቷን የሚያበስረው የመስጊዱ የአዛን ጥሪ ሲሰማ፣ በንዴት ተከናንቦ የተኛበትን ብርድልብስ ገልቦ ተነሳና በጨለማው ተቀመጠ። አዛን ብቻ ሳይሆን፣ ተስሃሩ ፣ ተከለሉ፣ የሚለውን የመስጂድ ጥሪም አንድ በአንድ በቅደም ተከተላቸው  ሰምቷል። በኮርኒሱ ውስጥ የሚራኮቱ አይጦችን ኮቴ፣ ልብ ብሎ ከመስማቱ የተነሳ፣ በኮቴያቸው ብቻ፣ ብዛታቸውን፣ ትልቅ ይሁኑ ትንሽ  መጠናቸውን፣ ለይቶ አዉቋቸዋል። ትንሽ ቢቆይ ቋንቋንቸውን ራሱ፣ ሳይለምድ አይቀርም። መኝታው ላይ እንደተቀመጠ በጨለማው ላይ አፍጥጧል።

የሰውነቱ ሙቀት፣ የዳቦ ሊጥ፣ እንደ ባትራ ቢጣድበት እንደሚጋግረው አልተጠራጠረም። በደምስሩ የሚዟዟረው እሳት እንጂ ደም አልመስልህ አልመስልህ ብሎታል። ኡፍፍፍ… ተንቆራጠ፣ ተቀመጠ ፣ተነሳ።  ምን እንደሚያደርግ ግራ ግብት ብሎታል።  "ወይኔ!" ይላል በንዴት ደግሞ ደጋግሞ።

ለዚህ ያበቃው ንዴት በመስጊዱ የአዛን ጥሪ፣ ወይም በአይጦቹ ቀልቃላነት አልነበረም። በምርቃና ለሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በማጣቱ እንጂ። "ይሄ ሰውዬ ምንድን ነው ያስቃመን?" ራሱን ይጠይቃል። ምሽቱን የቃመውን ጫት፣የሸጠለትን ሰው!!። በመላው ደምስሩ የነበልባል ፍጅት ይዟዟራል። ጫቱን ሉሉ አድርጎ የተኛው እኩለሌሊት ቢሆንም፣ ሁለተኛው የሌሊቱ ክፍል እስኪገባደድ እንቅልፍ በአይኑ አልዞረም። "ኡፍፍ በገዛ ገንዘቤ እሳት?"። እንቅልፍ ያጣ አይኑ ይቆጠቁጠዋል፣ እንቅልፍ ግን ወፍ የለችም። ሲተኛ ከራስጌው አስቀምጦት የነበረውን የታሸገ ውሃ፣ በደመነብሳዊ ግምት ፣ እጁን ሰዶ አነሳና በመሃል አናቱ ላይ አንደቀደቀው። ከአናቱ ወርዶ በጀርባው አልፎ፣ የውስጥ ሱሪው ድረስ የውሃው ቅዝቃዜ ሲያረሰርሰው፣ ትንሽ ቀለል፣አለው። የመኝታ ልብሱ፣ ፍራሹ የመበስበሱ ጉዳይ ከገጠመው የምርቃና ጉድ! አንፃር ቁብም አልሰጠውም።

ጫት እንቅልፍ ይከለክላል ሲባል በወሬ ደረጃ ይስማ እንጂ፣ ከእድሜው አንድ ሶስተኛውን በቃመበት ጊዜያት እንደዚህ ጉድ የሰራው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ጫት  የጀመረ ሰሞን ምርቃና ለብሶ የሚተኛው ሌላ ብርድልብስ አለመኖሩን አስረስቶ፣ በውድቅት ሌሊት የሚተኛበት ብርድልብሱን ካዘፈዘፈው በቀር፣ እንደዛሬው ጉድ የሰራውን አያስታውስም።

"አረ! መርዝ ያርግብኝ ሁለተኛ ከቃምኩ" እያለ ሌሊቱን ሙሉ ዝቷል። ዛቻውን ይፈፅም አይፈፅም ግን እርግጠኛ አይደለም። የቃሚ ነገር ይኸው ነው። አልቅምም ብሎ ዝቶ ያድራል፣ በማግስቱ ዛቻው ዛቻ ብቻ ሆኖ ይቀራል። በጠዋት ለስራ መነሳት ግድ ቢለውም፣ የቀጠሮ ሰዓቱን አራዝሞ ቀጠረውና፣ ሰላቱን ሰግዶ ተመልሶ ተከናንቦ ተኛ። አሁን ትንሽ ለውጥ አለ። የውሃ ቅዝቃዜ የፈጠረበት ስሜት እንቅልፉን እንዲያመጣለት እየፀለየ… ለሰላሳ ምናምነኛ ግዜ ለመተኛት ሙከራ አደረገ … ተሳካለት።

… ድንገት ከአንቅልፉ ሲባንን ከመኝታ ቤቱ በር ስንጥቆች የገባው ብርሃን፣ ክፍሏን አጥለቅልቋት ነበር። ተንቀሳቃሽ ስልኩን አንስቶ ሰዓቱን ተመለከተ። ከረፋዱ አምስት ሰዓት ይላል። በድንጋጤ ተነስቶ ልብሶቹን በችኮላ መለባበስ ጀመረ። የቀጠረው የሰዓት ድምፅ፣ በቀጠሮው አለመስማቱ አስገርሞታል። ደግነቱ የግሉን ስራ ስለሚሰራ ለምን አረፈድክ ብሎ የሚገላምጠው፣ ህሊና እንጂ አለቃ የለበትም። በዛ ላይ የፃም ወቅት በመሆኑ የስራ ቦታው መሞቅ የሚጀምረው ከእኩለ ቀን ቡሃላ መሆኑን እያምሰለሰለ ልብሶቹን ለባብሶ በአቅራቢያው ወደ ሚገኘው የስራ ቦታው ወደሆነችው መሻለኪያ ሄደ። እንዳሰበው የገበያ ስፍራው አልሞቀም ነበር። እቃዎቹን ደርድሮ ካስተካከለ ቡሃላ፣ እንቅልፍ  ያልጠገበ ፊቱን ለአላፊ አግዳሚው ክፍት ኢግዚቢሽን አድርጎ ገበያ መጠበቅ ጀመረ።

ሌሊቱን በሙሉ እንቅልፍ ያሳጣው የጫቱ ነገር ግን ከንክኖታል። ችግሩ ከሱ ይሁን ከጫቱ እንቆቅልሽ ሁኖበታል። ይሄ ሰውዬ ጉድ ሰራኝ! ይላል ለራሱ።  የሀረርጌ ጫት አስመጥቶ የሚሸጥ የስራ ጎረቤቱን።"እኔን ብቻ ነው ወይስ እነሱም እንደኔ እንቅልፍ አጥተው ይሆን?" ቆይ እስኪ የእነሱን ሁኔታ ልጠይቅና፣ እውነቱን እደርስበትየለ? አለ። ማታውን አብረውት የቃሙ የመሿለኪያ ጓደኞቹን። ብዙም ሳይቆይ አንዱ ጓደኛው አይኑ ደምመስሎ መጣ። ከሰላምታ በፊት የጠቀው ስለ ጫቱ ነበር። "ማታ ተኛህ ሰያ?" አለው ምን ብሎ እንደሚመልስለት ለማወቅ  እየጓጓ።

"ምን እተኛለው!! መቃብር ላይ የበቀለ ጫት ነው እንዴ የሸጠልን?  መገላበጥ ሲሰለቸኝ ተነስቼ ወጣው። አንተንም ከልክሎህ ነበር እንዴ?" አለው ብስጭት ባለ ድምፅ። የሰያ መልስ ሳቅ አጫረበት። ባንድ በኩል ችግሩ የሱ ሳይሆን የጫቱ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ጓደኛውም ችግሩን በመጋራቱ እያፅናናው። ሁሉም ጓደኞቹ መጥተው ስለጫቱ ጠይቆ የሰጡት መልስ አንድ አይነት ነበር። አልተኛንም። ሌሊቱን እንዴት በስቃይና በእንቅልፍ እጦት እንዳሳለፉት ሁሉም በምሬት ተናገሩ።
ሌላው አባል ሙልጌ ምሬቱን ከገለፀ ቡሃላ ጫት ሻጩን
"የኔ ወንድም!! ያንተ ጫት የቃመ ሰው እኮ ለመተኛት፣ አማኑኤል ሄዶ የእብድ መርፌ መወጋት አለበት!" ሲለው ሁሉም ቢስቁም፣ ማማረራቸው ግን አልቀረም። አስገድዶ ያስቅማቸው ይመስል። በመጨረሻም አንድ ድምዳሜ ላይ ደረሱ። "ጫት አንቅምም!!" ወይ የቃሚ ዛቻ አስኪ እናያለን!!

የአፍጥር ሰዓት ደረሰ። በአራራ ሲንገበገ የዋለ ሁሉ! ለሱሱ ምላሽ ሰጠ። በልቶ ጠጥቶ ጠገበ። ጥጋብ ያሳለፈውን፣ የመከራ ሌሊት አስረሳው። ሰውዬው ጫቱን ይዞ ሲመጣ፣ የመሿለኪያዊያን የአንቅምም ዛቻ፣ እንደ ጠዋት ጤዛ በነነ። የጫቱን ቀንበጥ ሲያዩ ጥርሳቸው ሻፈደ። በጥጋብ ሆነው የትላንት መከራቸውን ረሱ!! ጫቱን ተሻምቶ ለመግዛት፣ የሚቀድማቸው ጠፋ። ሁሉም የሰውዬውን ጫት መቃም ጀመሩ። የተማረሩበትን ትራጄዲ ሌሊት፣ በኮሜዲ ቀይረው ምሽቱን ይዝናኑበት ገቡ። ጥጋቡ ጋብ ብሎ የማታው መከራ ተደግሞ እስኪያማርሩ!! ትዝብት ነው ብቻ።

"ላያድን ቃል ብቻ!!
ምን ያደረጋል ዛቻ!ጉራ ብቻ!!"
አለ ቴዲ ምርጥ ሰው! ።
እውነቱን ነው።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment