Friday, June 16, 2017

" አ ታ ሳ ዝ ን ም … ወ ይ ?"


====================
#ሳteናw

… በስሙ የምጠራው ወንድ አያቴ ድንኳን በሚያክል ካቦርቱ ወሽቆኝ፣ የወፍቾ ኳስ ሲሰራልኝ ጭላንጭል ትውስታዬን የቀረፅኩባት ስቱዲዬ ነበረች። ፍቅሩን ሳላጣጥም፣ ትውስታው በህሊናዬ ግብዓቱን በደንብ ሳያከማች፣ የቤቱ አንደኛው ምሰሶ ወንድ አያቴ ከሰማይ ቤት ተጠርቶ ሲለየን፣ በእዬዬ የለቅሶ ቀጠና ሆና የተሸኘባት ቤቴ። በብረት ምጣድ፣ ሚናነት ከሳሎን ወደ ሻወር ለውጠናት ገላችንን ታጥበን በእቅፏ የተጠቀለልንባት ፉል ውሃችን።ወይ እሷ ምን ያልሆንባት አለ? አረ ምንም!!

በመጀመሪያ … Granዶቼ የፍቅር ምሰሶ ሆነው ገነቧት፣ የጋተ የናቴን ጡት ያለጊዜው ትቼ፣ የሴቷ አያቴን ደረቅ ጡት እየጠባሁባሁ አደኩባት። እስከ ጉርምስናዬ መጀመሪያ ድረስ ህይወቴ መልህቋን ጥላ የረጋችባት ወደብ፣ ታሪኬን የመዘገብኩባት ድርሳን፣ ሀዘን ደስታዬን የተወንኩባት መድረክ!! ነበረች ቤቴ። ገራዤ በህክምና ይሁን በግብርና መሳሪያ እንደገረዘኝ እንጃለቱ፣ ትንሿ ቆለጤን ሲከረትፍ፣ በፈጠረው ስህተት፣ ፊኛዬ ደህና ቡጢ እንቀመሰ መንጋጭላ አብጣ፣ በዚሁ ሰበብ የሽንት ቧንቧዬ ጠባ፣ ለሶስት ቀን መሽናት ቢያቅተኝ፣አያቴ ጭንቀቷ አላስቆም አላስቀምጥ ብሏት፣ ቢጨንቃት ቢጠባት፣ ዱዓ ለማስደረግ ቆጮና አይብ ተደግሶባት፣(የዚን ሁኔታ መሉውን ማንበብ ከፈለክ የዳዶቃዋ በሚለው ርዕስ ታገኘዋለህ!) በወደጅ ዘመድ እናቶች ዱዓ ለቆለጤ ተለምኖባት፣ በዚሁ ሰበብ ልትፈነዳ የደረሰችው ፊኛዬ፣የፀሎታቸው ጥሪ በፈጣሪ ፈጣን ምላሽ አግኝቶ፣ በመካከላቸው ተበልቅጬ በጀርባዬ እንደተኛው ሽንቴ ወደ ኮርኒሱ ተንፎልፎሎ የተነፈስኩባት፣ የአያቴና የእናቶች ደስታ በእልልታ የደመቀባት፣ ከሷ አልፎ በመርካቶ ያስተጋባባት ነበረች። ይህቺው የዛሬ አሳዛኝ…ቤቴ። ቀይ ፖፖዬን በጳውሎስ ኞኞ ትንግርት መፅሄት ሰበብ፣ የተውኩባት እናት ሀገሬ ነበረች… በአያቴ ልጆች፣ በምላቸው እህቶቼ! ወንድሞቼ። የስጋ ወላጆቼን ከነመፈጠራቸው ሳላስተውል በፍቅር ተከበብቤ ያሳለፍኩባት ዋሻዬ።  ለመጀመሪያ ጊዜ የህፃናት መዋያ ተመዝግቤ፣ ትምህርት የተጀመረ ቀን ስሄድ በአቅሚቲ ዝንጥ ዝንጥንጥ ብዬባት። አሁንም አሁንም ያለ ማቋረጥ፣ እንደ ግሉኮስለሚንጠባጠበው ንፍጤ መቆጣጠሪያ መሃረብ፣ የኮት ደረቴ ላይ በመርፌ ቁልፍ  አንጠልጥዬ፣ እንደ ዘማች በስቄና ትጥቄ ታጅቤ፣ የወጣሁባት፣
በግንቦት 20 ማግስት…
"ደርግ ያሳደገው ሌባ፣
ኢህአዴግ ይቀጣዋል" እያልን ምንነቱ በውል ያልተገለፀልልን፣ ቤት ማይመታ ግጥም፣ እንደ መዝሙር ከአቻ ጓደኞቼ ጋር በህብረት የዘመርንባት፣ የኪነት ክበባችን።

  ደግሞ በዛው ሰሞንበሰፈሬ መርካቶ  ጩሉሌ የወርቅ፣ ይሁን የነሃስ ሰዓቱ የተቀማው የደርግ ወታደር" ሌባውን ውለዱ ሲል"በከባድ መሳሪያው፣ የአናቷን ክፈፍ ድብድቦ ወንፊት ያስመሰላት(የወርቅ ሰዓት ቢሆን እንጂ፣ ለነሃስ ሰዓትማ ይህ ሁሉ ጥይት ያባክናል አልልም)። ሳምታዊዉ የአያቴ የቡና ስርዓት ሲፈፀም፣ የእጣን፣ የአይብና ቆጮ ጠረን ያወዳት፣ በጭሳጭሷ ሳቢያ ሁሌም ሚያድፈው ላንቃዋን(ኮርኒሷን)፣ የረመዳን ፆም በመጣ ቁጥር በቀለም ቀቢ ያስቀባናት፣ አልያም እንደ ቀለም ቀቢ በበርሜልና መሰላል ላይ ተንጠላጥለን ከእህቴ ጋር፣ ኦሞ በራሰ ብጣሽ ጨርቅ የወለወልናት፣ ውሃ እየተረጫጨን ተሳስቀን የፈነደቅንባት የዘመናችን ኤድናሞል የህፃናት መዝናኛ አለም። ከጓደኞቼ በጨዋታ ተጣልተን ተማትቼ ና፣ ሸሽቼ የተደበኩባት ምሽጌ። ሁሌም ግሳፄዋ በኩርኩም የሚጀምር በሆነው፣ ትልቋ እህቴ ኩርኩም በለቅሶ ያላዘንኩባት። ቴቪ ሲገባባት እንደ ሀገር መሪ፣ ደማቅ አቀባበል ያደረግንባት መስክ። አቤት የዛን ለት ቲቪ ብርቅ ሆኖብን፣ ለቲቪው ደህንነት ሲባል በታላላቅ ወንድሞቼ የተቆለፈባት፣ መሽቶ ቲቪ ስናይ ባልጠፋ ቦታ ለአራት አንድ አልጋ ላይ በፍቅር ሰፍቶን የተኛንባት። ወይ አሳዛኝቷ። ቤተሰቡን ብሎ የመጣ ዘመድ፣ ወዳጅ  ያስተናገድንባት፣ እንደራሱ ቤት በነፃነት ያሳለፈባት። ካሏት ክበብ በሶስተኛው፣ በጊዜው ጎረምሳ የነበሩት የታላላቅ ወንድሞቼ ባልንጀሮች ተመሽገው እንደ ፊደል ሀ… ሁ… እያሉ በታላቆቼ የኔታነት የሱስ አይነት ቆጥረው የተማሩባት። እየኮረኮሙ የሚሹትን(የፈረደብኝ እኔን) የላኩባት። በጅምላ ያፈቀሯትን የጎረቤት ቆንጆ፣ ደብዳቤ ያለመታከት የተላላኩባት። (ምናለ ለአንዱ እንኳ እሺ ብትል እስኪ?!)። የቱጃር ቤት ወግ ደርሷት መደበኛ ስልክ የገባባት ዕለት፣ ከት/ቤት ስመለስ፣ አያቴ ሰላት ላይ ብትሆንም፣ ዜናውን እስክትነግረኝ አላስችል ብሏት፣ በጣቷ ጠቁማኝ፣ ስልኩን ወፍራም ትራስ ላይ ተቀምጦ፣ እንደ አመት በዓል ድፎ! ዳንቴል ለብሶ ሳየው በአግራሞት የጮህኩባት፣ቤቴ። ሚስኪን ስታሳዝን።  አመታዊ በዓላት ኢድና አረፋ፣ በመጡ ቁጥር ከትውስታ በማይጠፋ መልኩ በደማቁ ያከበርንባት። ለኢድ የተገዛልኝን ልብስና ጫማ እስኪነጋ አላስችል ብሎኝ ለብሼ የተኛሁባት ድንክ አልጋዬ!!። ለአረፋ በዓል ምክኒያትነት የተገዛውን በሬ ከጓደኞቼ ጋር፣ የኛ ይበልጣል የኛ ይበልጣል ስንል፣ የተፎካከርንባት። የዛን ሰሞን ቁርስ፣ ምሳ እራት፣ ክትፎ በቅቤ፣ የጠጣንባት። በመጨረሻም (ፎላ) ሻኛው ድፍኑን ተቀቅሎ ወዳጅ ዘመድ፣ በተገኘበት በባህላዊ የቡና ስነ ስርዓት፣ በአያቴ እንደ ተቆራጭ ኬክ ተቆራርጦ ና ታድሎን በልተን፣ በሬውን ከብልቱ፣ እስከ ጥፍሩ ደረስ፣ አንድም ሳናስተርፍ ቁርጥምጥም አድርገን በልተን፣ መጨረሳችንን ያወጅንባት። እህቴ ለማንም የማይቀረው ጉዞ ወደ አረቡ አለም በሄደችበት ምሽት፣ እኔና አያቴ መኝታዋ ባዶ ሲኖንብን፣ ገና በአንድ ቀኗ ናፍቆቷን መቋቋም ተስኖን፣ በውድቅት ሌሊት፣ ከእንቅልፍ ባነን ተቃቅፈን ያነባንባት። አቤት አንድነታችን፣ አቤት ፍቅራችን!! ይህን ሁሉ ነገር በእቅፏ ሸሽጋ ያስተወነችን መድረክ!። ታላላቅ ወንድም እህቶቼን ተኩለው ሲዳሩ፣ ፣ጉሮ ወሸባዬ ፈንጥዘን የሰረግንባት። አልቅሰን፣ ሙሾ አውርደን ሬሳ በየተራው የሸኘንባት ነበረች። ደግፋ ይዛት የነበረችው አንድ ምሰሶ(አያቴ) በሞት ተጠልፋ ስትድቅ፣ ፍፁም ተቀየረች የማናውቃት የማታወቀን ሀገር ሆና አረፈች። የታሪክ ድርሳንነቷ ቀርቶ፣ የታሪክ አተላ ሆነች!! በሳቃችን እንዳልሳቀች፣በዳንሳችን እንዳልተውረገረገች፣በለቅሷችን እንዳላነባች፣የሆነውን እንዳልሆነች፣የጠላነውን፣ እንዳልጠላች፣ የወደደነውን፣ እንዳልወደደች። ቤተሰቡን ያለ አንዳች አድሎ በፍቅር አስተሳስራ እንዳላኖረች ሁሉ። ዛሬ ግን ክፉ ቀን መጣና፣ የጋራው ፍቅር በራስ ወዳድነት ተለወጠና። የአንድነት ፍቅር ጠፋና፣ ከሰው ገንዘብ አስበለጠችና እሷም በአቅሟ  እንደዘመኑ ሰው ፍትሃዊነቷ የውሃ ሽታ ሆነና፣ ለባለጊዜ አንድ ወገን አደላችና፣ "ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ" ሲሉ ሰምታ ራሷን ሰማይ ሰቀለች። ገንዘብ ተከትላ ሄደች። ታች ያለ ቤተሰቧን በተነች፣ አይኗን በጨው አጥባ አላውቃችሁም ስትል ካደች። ካደመው አደመች፣ትላንት የኔ ነበረች ብሎ ሚዘክራት፣ ዛሬ በሰማይ ላይ ያለች፣ ወተቷን የማያይ የታሪክ ላም ሆነች። ሁሉም አዘነባት!! ይብላኝላት ለሷ እንጂ!! እኛማ ጊዜ ሳይለውጠን አለን። ከምር ግን! አታሳዝንም ወይ? …
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment