Monday, June 19, 2017

" I N T E R V I E W "


#ሳteናw

   ሀገሪቱ የእህል እጥረት በገጠማት በአንድ ወቅት፣ ሊቀመንበሩ፣ የችግሩን ስረ መሰረት ለማወቅና ቀጣይ የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ በሚል ከእህል ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን አካላት ራሳቸው በቢሯቸው አስጠርተው ማነጋገር ጀመሩ! አሉ። አሉ ነው!! ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም። አሉባልታ። በዚህም መሰረት ሶስት የዶሮ እርባታ ድርጅት ባለቤቶች ለኢንተሪቢ(interview) ከቢሯቸው በሰዓታቸው ተገኙ።

ሊቀመንበሩም፣ ከጀርባቸው፣ በሶሻሊዝም ርዕዮተ አለም፣ አርአያ የሚሏቸውን ሰዎች ፎቶ፣ በትልልቁ ከተሰቀለበት ቢሯቸው፣ በወታደራዊ አለባበሳቸው ፏ! ብለው! ተሰይመዋል።

ዶሮ አርቢዎቹ… በአጃቢ እየተመሩ ከቢሯቸው ገብተው ሲቆሙ፣ሊቀመንበሩ በአንድ እጃቸው የስልኩን እጀታ ይዘው እያወሩ ነበር፣ በግማሽ ልብ ሆነው በሌላኛው እጃቸው ለባለጉዳይ በተዘጋጀው ወንበር ላይ እንዲቀመጡ አመለከቷቸውና፣ ሰዎቹ ተቀመጡ። የስልክ ንግግራቸውን እንደጨረሱ፣ ከነበራቸው የጊዜ ጥበት አንፃር ቀጥታ ወደ ጥያቄያቸው ገቡ…

ለመጀመሪያው አርብቶ አደር… ወደሚቀርባቸው ወንበር እንዲቀመጥ አዘው።

"እሺ!!ለምታረባቸው ዶሮዎችህ መብልነት፣ የምታቀርብላቸው ጥሬ ምንድነው?" ሲሉ ጠየቁት የቢሮ ወንበራቸው ላይ እየተደላደሉና፣ መለዯቸውን እያስተካከከሉ።
"ስንዴ! ሲል በኩራት መለሰ። ወታደራዊ ማዕረግ!! ይሸልሙኛል በሚል።

"ምን!" አሉ ሊቀመንበሩ በድንጋጤ። "ስንዴ?! ክው ብለዋል!።

"ስንዴዴዴ?! እንዴዴ…ዴዴ!። ህዝቡ የሚበላው የለው አንተ ለዶሮ ስንዴ?" ለኢትዮጲያ አንድነት፣ ደሙን እያፈሰሰ፣አጥንቱን እየከሰከሰ ላለ ሰራዊታችን ለምናቀርበውን በሶ የስንዴ እጥረት ገጥሞን! አንተ ለዶሮችህ ስንዴ?! ነው እንዴ?" አሉ ብግን እንዳሉ።

"ና ማነህ?" ከአጃቢዎቻቸው አንዱን ጠሩ። አጃቢው መጣ።

"ይህን፣አናርኪስት፣የእናት ጡት ነካሽ፣ወስደህ የእጁን ስጠው።" ትዕዛዛቸው ውስጥ ከፍተኛ ቁጣ አለ። ትዕዛዙን የተቀበለው አጃቢ ወታደር፣ በወታደራዊ ሰላምታ ወለሉን በከስክሱ "ጓ" አድርጎ መሬቱን ሲደቃ፣ ቢሮዋ ተርገበገበች።
ሊቀመንበሩ ሳያስቡት ስለነበር አስደንግጧቸዋል።
"ምንድነው እንደዚህ አገር የሚያውክ ሰላምታ መስጠት?" አሉ በውስጣቸው በሰጠው ሠላም አደፍራሽ ሠላምታ እንደተሸበሩ።  አጃቢ ሆዬ! ገለል ወዳለ ስፍራ ወስዶ! ዷ …ዷ …ዷ… ድ… ው ሰጠውና … በፈጣን እርምጃ ተመልሶ ከቢሯቸው ከች። ሊቀመንበሩ የተቀበሉት በግልምጫ ነበር…

"ምንድነው ለአንድ ሰው ይሄ ሁሉ ሁካታ? እኔ በስንት ኡኡታና!ለቀሶ! በስንት ጩኽትና ልመና! አይደለም እንዴ የማመጣው? ጥይቱን! አይደለም ወይ? ትንሽ አታስብም? ሀገሪቱ የኔ ብቻ ነች እንዴ?" አሉት አሁንም እንደተቆጡ።

"በአንድ ድምፅ እርምጃውን ልውሰድ? ሲል በትህትና ጠየቀ አጃቢው።
"ለምን በአንድ? ከቻልክ በሰደፍ ገላግለው።"
አሉትና አቀርቅረው ማስታወሻቸው ላይ መፃፍ ጀመሩ። ቀጣዩ አርብቶ አደር በቢሮው ስፋት ተደንቆ ሲመለከት ሊቀመንበሩ ከአጃቢው ጋር የተለዋወጡትን አልሰማም ነበር። ይፅፉት ከነበረ ማስታወሻ ቀና እያሉ። እሺ አንተ! ብለው   ጥያቄውን ደገሙለት።

"የኔ ዶሮች የፈረንጅ ዝርያ ስለሆኑ፣ ስንዴ እንኳ ሊበሉ! ጫጩቶቻቸው እንኳ እንደ ብይ አይጫወቱበትም። ስለዚህ… ብሎ አፉን ለመጠራረግ ንግግሩን ገታ አደረገ።

ሊቀመንበሩ ምን ሊል ነው? በሚል ግርምት አፍ! አፉን! ያዩታል።
ቀጠለ … ስለዚህ … ዶሮዎቹ የአገራቸውን የአመጋገብ ስርዓት፣ ጠብቀንላቸው እንዲመገቡ ማድረግ፣እንግዳ ተቀባይ ኢትዮጲያዊነታችን ያስገድደናልና። ለነዚህ ቅንጡ ዶሮዎች የምንቀልባቸው፣ በትውልድ  አገራቸው እንደሚመገቡ በቅቤ የተለወሰ በቆሎ ነው። ለዚህም ነው የኛ ድርጅት የሚያረባቸው ዶሮዎች! ከየትኛውም የዶሮ አርቢ ድርጅቶች በተለየ፣ ባለ ሁለት ፈረሰኛ ሆነው መገኘታቸው። አለ…  በመመፃደቅ አይነት

ሊቁ፣ በመልሱ ቆሽታቸው አሯል። "በቅቤ የተለወሰ በቆሎ? ህም!! አሉ በምፀት።…አሁን አንተ የዶሮ አርቢ? ወይስ የዶሮ አራስ ተንከባካቢ? የምትባለው።… ከህዝብ ጎሮሮ ነጥቀህ! እያደለብካቸው ለምን? አራት ደንደስ አይኑራቸው? ህእ! ጉድ ነው! ደግሞ ስንዴ አይበሉም! በቆሎ፣ፈረሰኛ ምናምን ይለኛል እንዴ? ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣው" አሉ።  ብስጭት! እብድ! ቅጥል! አሉ። ምርር አላቸው። ይህን ወንበር የወረሱበትን ቀን ረገሙ። "ቆይ! እኛ ከስንቱ ነው የምንዋጋው?"
አጃቢውን ጠሩ። አጃቢው ተጣሩ እቴጌን በሆዱ እየዘፈነ። ከች አለ። "ይህንንም የማይረባ አድሃሪ! የነጭ ቁስ አምላኪ! ከቻልክ ምናምኑን በመቀስ፣ ከልሆነ ቂጡን በሳንጃ በልልኝ።" አሉ። አጃቢው ትዕዛዙን እንደተቀበለ፣ ወታደራዊ ሰላምታውን ሊደግም… ባለበት ቀጥ ብሎ እንደቆመ፣ አንድ እግሩን ሽቅብ ወደላይ… ሰቅሎ… ሰቅሎ… ሰቅሎ…ጉልበቱ ደረቱ ጋር ሲደርስ፣ ለአፍታ አየር ላይ አቆመና፣ ወደታች ቁልቁል አንደርድሮ መሬቱን ሊደቃው ሲል…
"ቆይ …ቆይ… ቆይ … እያሉ ፍንጥር ብለው ከተቀመጡበት ወንበር ተነሱ። እግሩ መሬት ከመድረሷ በፊት ሊያስቆሙት። አጃቢው አየር ላይ የቀረ እግሩን እንዳንጠለጠለና፣ በቆመበት እግሩ ሚዛኑን ለመጠበቅ፣ እየታገለ "ምንድነው?" በሚል ተመለከታቸው።

"ነገርኩህ! ነገርኩህ! ይሄ ግንድ 
እግርህን፣ ድምፅ ሳታሰማ እንደሰቀልክ፣ድምስ ሳታሰማ አውርድ!አሉት። አይናቸውን እንዳፈጠጡበትና በትረ መኮንናቸው በማስጠንቀቂያ መልክ እየቀሰሩበትበት።

አጃቢ ሆዬ! አየር ላይ ተንጠልጥሎ ከቁጥጥሩ ውጪ የሆነበት እግሩን ጥርሱን ነክሶ፣ትንፋሹን ውጦ፣ ሚዛኑን አጥቶ እየተንገዳገደ ቀስ አድርጎ ድምፅ ሳያሰማ መሬት አስነካት፣ ሰውየውን ይዞ መውጣት ጀመረ

"ይሄን ጉልበት በባዶ ሜዳ ከምታመክኑት፣ ልማት ላይ ብታውሉት ምን አለ? " እያሉ ወደ መቀመጫቸው ተመለሱ።

ተግሳፃቸው ከኋላው እየተከተለው። ኮቴውን ሳያሰማ በጥፍሩ እየተራመደ ሄደ። በሰውየው ገለል ካለ ስፍራ ወስዶ እርምጃውን ሲወስድበት ምንም አይነት የተኩስ ድምፅ፣ ሳያሰማ፣ተመልሶ ከቢሮው ገባ። ያለምንም ተኩስ እንደሸኘው የታዘቡት ሊቀመንበር
"በሰደፍ ነው?" አሉት።
"አይ "
"እና… "
"ለሰላምታ አውጥቼው የነበረው ጉልበት መክኖ እንዳይቀር፣ ጓሮ ወስጄ በጀርባው ካስተኛሁት ቡሃላ፣እዚህ እግሬን አንጠልጥዬ ካቆሙኩት፣ ጀመርኩና፣ በከፍተኛ ሀይል ቁልቁል አንደርድሬ፣ልቡ ላይ በማሳረፍ፣ሸኘሁት።"

"በጣም ጥሩ! በጣም ጥሩ!። እንዲህ ንቁና ፈጣን ወታደር ነው የሚያስፈልገን፣ ብለው አመስግነው። ወደ መጨረሻው ዶሮ አርቢ ዞረው ። "እሺ አንተስ?" ሲሉ ጠየቁት ስልችት መንፈስ… ይሄኛው ነቄ ነው። አቻዎቹ ገለል ወዳለ ስፍራ ተወስደው፣ የደስታ ርችት እንዳልተተኮሰላቸው ወይም በድምፅ አልባ ጭብጨባ እንዳላመሰገኗቸው አውቋል። ስለዚህ አንድ ዘዴ ፈጥሮ ማምለጥ አለበት። በመጨረሻም ይህን መልስ ሰጠ "ጌታዬ! እኔ እንኳን፣ ስንዴም፣ በቆሎም አልቀልባቸውም። ገንዘቡን ነው አንድ ሁለት ብዬ ቆጥሬ የምሰጣቸው።ገንዘቡን ወስደው ምን እንደሚበሉት ግን እኔንጃ።" ሲል መለሰአሉ። ልብ አርግ አሉ ነው!! ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም። አሉባልታ።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment