Tuesday, June 20, 2017

" እ ወ ዳ ታ ለ ው "

" እ ወ ዳ ታ ለ ው "
#ሳteናw

… አቤት ስወዳት!! እንደሷ የምወደው ሴት ምድር ላይ አለ እንዴ? እኔንጃ ያለ አይመስለኝም!! በጣም ውድድድድ በቃ!! እስኪገርምህ ድረስ። ብወድሽ ብወድሽ አለሰለችህ አለኝ! ሲል ቴዲ ለፍቅረኛው ቢዘፍንም እኔ ግን ይህን ዘፈን የምዘፍነው ማህፀን ለምትጋራኝ እህቴ ነው። ይገርምሃል!! ነብሱን ይማረውና አባቴ በስነ ተዋልዶ ዙሪያ ታታሪ ተራቢ ነበርና ብዙ እህቶች አሉኝ። የእህት ሀብታም ነኝ። እንደሷ ልወዳቸው ብሞክር እንኳ አልተሳካልኝም። መውደድን ስለፈለከው ሳይሆን፣ የውስጥ ስሜትህ የሚሰጥህ መሆኑን እዚህች ጋር በቀይ እስክሪብቶ አስምርበት። እስክሪፕቶ አልያዝክም? በቃ የሃሳብ መስመር አስምርበት። ልትወደው ብትሞክር እንኳ የማይሳካልህ ነገር ገጥሞህ አያውቅም? ሌሎቹ እህቶቼ በህፃንነቴ ቢንከባከቡኝ፣ ሀቢቢ፣ገልቢ፣ ሩሂ፣ ምናምን እያሉ ከመካከለኛው ምስራቅ በተዋሱት  ቋንቋ ቢያቆላምጡኝ!! በሰቅሉኝ፣ቢክቡኝ፣ ቢቆልሉኝ ወላ ሃንቲ!! እሷግን እየተጣላንም፣ እየኮረኮመችኝም፣እየሰደበችኝም ከጓደኞቿ ጋር ስታወራ "ምንድነው?" ብዬ አፌን ከፍቼ ልሰማ ፈልጌ፣ ሂድ ውጣ ሴታ ሴት ብላ፣ ነጠላ ጫማ ወርውራ ብታባርረኝም! እወዳታለው። ወረኛ እንድሆንባት አትፈልግማ!!

አቤት!! የውዴታዬ ብዛት! ስህተተኛ ብትሆን እንኳ ለሷ ወግኜ ከእህቶቼ ጋር ተጣልቻለው። ለምን ቅር አሰኟቿት ስል ለረጅም ግዜ አኩርፌያቸዋለው። ስህተቷን የሚጋርድብኝ ኢፍትሃዊ ሆኜ አይደለም። ወይም ከሷ የተለየ ነገር ስለምጠቀም አይደለም። በቃ ለረጅም ግዜ ከሌሎቹ በተለየ አብሮ ማደጋችን የቸረኝ ፍቅር። የሚገርመው የፍቅር ልውውጣችን ለሁለታችን እንጂ ለማንም አያስታውቅም። አጠገብ ላጠገብ፣ ስንከራከር ስንጨቃጨቅ ብታየን። "ድንቄም መዋደድ ብለ ልታሽሟጥጥ ትችላለህ" (ያው ማሽሟጠጥ ስራህም አይደል!!)። አይገባህማ!! ፍቅራችን ለራሳችን እንጂ ላንተ አይታይህማ። እንዲታይህ የኔን አይን ተከራይተህ እሷን፣ አልያም የሷን ማያ ተውሰህ እኔን ማየት አለብህ።  የዛኔ ትረዳዋለህ።

  የዝንጀሮ ባል፣ ሲላፋት ሲያጫውታት፣ አይተህ አቤት ፍቅራቸው ሮሚዮና ጁሊየት ምናምን ትል ይሆናል።  እውነት አይምሰልህ። አንድ ቀበሮ ቢመጣ ፈሱን እያንጣጣ ነው ጥሏት የሚነካው። ኮስተር ጀንተል ብሎ ከሚስቱ አጠገብ የተቀመጠ አንበሳ አይተህ ደግሞ "ምን እንደባላባት ይጀነናል!" ትልም ይሆናል  አንድ አደጋ ቢከሰት ቀድሞ ይሞታታል እንጂ፣ እንደ ዝንጀሮው ጥሏት አይነካውም። አየህ የተግባር ፍቅር ይሉሃል ምሳሌው ይሄ ነው። ለሰው የማይታይ በልብ ያለ ፍቅር!! በለው። የኛንም ፍቅር በዚህ መስለው። "ካላየው አላምንም ብለህ ከገተርክ ተወው"። ነገር ግን ሳያዩ ያመኑ ብፁአን ናቸው። የሚለውን የመፅሀፍ ቅዱስ አንቀፅ አስታውስሃለው። እኔ ለሷ የማልሆነው ነገር ቢኖርም፣ እሷ ለኔ ማትሆነው የለም!! ለኔ ካሏት ህይወቷን እስከመስጠት ትደርሳለች። ይሄን ዝም ብዬ የምተረተረው ሳይሆን በተደጋጋሚ በእውነታ ያረጋገጥኩት ሀቅ ነው። ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደልም እሚባል። ከነሱም ውስጥ አንዱን ገጠመኝ ልንገርህ።

…  ከአስር አመት የአረብ አገር ቆይታ ብኋላ ይሕቺው ውዷ እህቴ ለአገሯ በቃች። በዚህም ደስታችን ወደር አጣ። በሀሴት ሰከርን። በዛው ሰሞን የቀድሞ ህይወቷ በገጠር የነበረውን እናታችንን ለመጠየቅ፣ በሷ እስፖንሰርነት ወደ አገርቤት፣ ሁለት ዘመዶቻችንን አስከትለን ሄድን።

በአገር ቤት የነበረን ቆይታ ከትውስታ የማይጠፋ አስደሳች ነበር። እንደቱሪስት ተዝናናን።በመጨረሻም መዝናናታችን፣ ሮንግ ተርን እንደሚለው ፊልም ጫካ ለጫካ በጨለማ በመረራሯጥ ተፈፀመ እንጂ። በገጠር የነበረን አስደሳች ቆይታ፣ የመጨረሻው ምሽት ተከታዩ ነበር።
በምሽቱ በእናታችን ጎጆ ቤት ውስጥ የነበረው ድባብ ደማቅ ነበር። ወዳጅ ዘመድ በቤቱ ተኮልኩሏል። ከምድጃው አጠገብ ባለው ቋሚ ምድጃ ላይ የሚነደው ፍልጥ ከሙቀት አልፎ የቤቱ ብርሃን ሆኗል። እስከዛሬ ድረስ ቃናው የማይረሳኝን የቡና ቁርስ ቆጮ በአይብ በልተን አብቅተናል። ጨዋታው ደርቷል። በአንድ በኩል እናቴ ቡናዋን እንደያዘች ከጎረቤት ሴቶች ጋር ወግ ይዛለች።  እኔ ከታላቅ እህቴ እግር ላይ ተንተርሼ፣በጀርባዬ ተኝቼ፣ ፀጎሬንእንደማከክ ስትደባበሰኝ፣ በልጅነቴ የአያቴን ድርጊት አስታውሶኝ በሃሳብ ነጉጃለው። እሷ አብረውን ገጠር ከሄዱት የወንድሜ ሚስትና፣ የታላቅ እህታችን የባል ወንድም ጋር የጋራ ወይይት ይዘዋል። ከጎጆ ቤቷ ክበብ የሩብ ጨረቃ ቅርፅ ባለው በአንዱ ጥግ ላይ ባለው በረት ውስጥ ያሉ ከብቶች፣ በየመሃሉ ድምፃቸውን ሲያጓሩ፣ የገጠር ህይወን ከማጉሏታቸው ባሻገር፣ በቤቱ ድባብ የተደሰቱ ይመስላሉ። ከበረታቸው በላይ ያለው የማገዶ እንጨት ማከማቻ ቆጥ ነገር ላይ ባለው የዶሮ ቅርጫት ውስጥ ያሉ ዶሮዎች እንደ አላርም ሰዓት እየጠበቁ ይጮሃሉ። በሌላ ጥግ የታላቅ ወንድማችን ልጆች " በየመሃሉ የእናታቸውን እናንተ ልጆች አድቡ" የሚለውን ግሳፄ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ይላፋሉ፣ይስቃሉ፣ ይጣላሉ፣ ያለቅሳሉ። መልስው ይጫወታሉ።(አይ የልጅ ነገር።  ሁሉም በየራሱ ሙድ ፍንትው ብሏል።






ታላቅ ወንድሜ(ጉዳዩ) ብቻ ከበሩ አጠገብ ባለ በርጩማ ወንበር ላይ ገፅታውን አኮስሶ ተቀምጧል። ይህ ሁኔታው አላማረኝም። ይህን ሀሳቤን ለእህቴ በሹክሹክታ አካፈልኳት። "እሷም፣ ስጋቴ ገብቷት ኖሮ ህመሙ ሊነሳ ሲል እንዲህ ያደርገዋል" ብላ የማውቀውን የበሽታ አጀማመሩን አስታወሰችኝና። ወደ ጨዋታዋ ተመለሰች። አንድ የአጎቴ ልጅ ሰላምታ አስቀድማ ገባችና፣ ከነ እናቴ ስብስብ ተቀላቀለች።

ይህ መልካም ምሽት በንደዚህ ሁኔታ አልፎ ፣ግማሹ ወዳጅ ዘመድ ጠብጠብ፣ ደህና እደሩ እያለ ቀስ በቀስ ጭር ማለት ጀመረ።

ጉዳዩ ከተቀመጠበት በርጩማ ድንገት ፍንጥር ብሎ ተነሳና እንደጦጣ እየተንጠላጠለ፣ ከበረቱ በላይ ካለው እንጨት ማከማቻ ወጥቶ አንዳች እቃ እያተረማመሰ ይፈልግ ጀመር። በቤቱ ያለነው በሙሉ ትኩረታችን እሱ ላይ ሆኖ፣ በመድረክ ላይ ሰርከስ እንደሚያይ ተመልካች እናየዋለን።

ፍልጦቹን አተራምሶ አተራምሶ፣ የፈለገውን ነገር ሲያጣ፣ አንድ ትልቅ ፍልጥ አንደ ቀስት ወርዋሪ ፍልጡን ይዞ ቆመ። ሁኔታውን ስናይ ወደኛ ለመወርወር የተዘጋጀ ይመስላል።
"ተነሽ አንቺ ብሎ" ምቾቴ ሆና በተተንተራስኳት እህቴ ላይ ጮኸ። ጉዳዩ ከኔ ጋር መሆኑን ነጋሪ አላሻኝም። ብድግ ብዬ ቆምኩና "ወርደህ አነጋግረኝ?" ብዬ መፎከር ጀመርኩ።።ሁሉም ካለበት በድንጋጤ ቆሞ ይለምነው ገባ። ፍልጡን ወደኔ ለመወርወር ኢላማውን ለማስገባት ወደኔ አቅጣጫ አንድ ሁለት አያለ እንደመወርወር አደረገና በሶስተኛው ፍልጡን ወረወረው፣ በዚሁ ቅፅበት እህቴ ለተወረወረብኝ ፍልጥ እንደጋሻ በራሷ ልትመክት መጥታ ተለጠፈችብኝ። በትልልቅ አይኖቿ በሚሰረስር አስተያየት አፍጥጣበታለች። እንደሌሎቹ ሳትጮህ ሳትንጫጫ ጋሻዬ ሆናለች። የተግባር ፍቅር ተመልከት።

የተወረወረው ፍልጥ ማናችንንም ሳያገኝ ተመዘግዝጎ እግራችን ስር ወደቀ። እኔ እህቴን ከራሴ ለማላቀቅ እየታገልኩ እጮኻለው "ወንድ ከሆንክ ወረድና አናግረኝ" እሱ ሌላ ፍልጥ አነሳ ኢላማውን አስተካክሎ ድጋሚ  ወረወረ። የጎጆ ቤቱ ምሰሶ ጨርፎ አቅጣጫውን አስቶት በሚነደው ምድጃ ላይ ወደቀ። የእሳትና የአመድ ብና ጎጆዋን የዘመን መለወጫ ርችት የተተኮሰባት ሰማይ በጭስ፣ አመድና የእሳት ፍንጣሪ! ተሞልታ፣ በጨለማ ተዋጠች። ማንም ከማንም መተያየት አልቻለም ጫጫታና ጩኸት ብቻ።

እህቴን እንዳቀፍኩ የሆነ ሰው እጄን ይዞ እንድከተለው ጎተተኝ። እሷን ይዤ የሚገትተኝን እጅ ተከትለን ከቤቱ ወጥተን መሮጥ ጀመርን። ውጪውም እልም ያለ ጨረቃ የሌለበት ጨለማ ነበር። ወዴት እንደምንሄድ ሳናውቅ እየጎተተኝ የሚሮጠውን እጅ፣ እየተከተልን፣ በባዶ እግር መሄድ ያለመደው እግራችን እንደልብ እንዳንሮጥ ቢያግደንም፣ ጭቃው ቢያዳልጠንም፣ በማይታየው ጨለማ ሮጥን። መሪያችን እንዴት ታይቶት እንደሚመራን አላውቅም። አይኔ ጨለማውን እየለመደ እየለመደ መጥቶ በመጠኑም ቢሆን ይታየኝ ጀመር። የግቢ አጥራችንን ለቀን በአውራ ጎዳናው ቁልቁል ወረድን። የምትመራን ሴት ትሁን እንጂ ማን ትሁን ወዴት ትወሰደን የማውቀው ነገር አልነበረም። ወደ አንፍ ጎጆ አጥሩን አልፈን ወደ በሩ ተጠጋን። መሪያችን በሩን አንኳኳች። ""ማነው?" መሪያችን "እኔ ነኝ" ስትል በድምፇ አወኳት። የአጎቴ ልጅ ነበረች። በሩ ተከፈተ። ውጪ ከነበረው ጭለማ አንፃር፣ ጎጆ ውስጥ የምትንጨላጨለው ብርሃን በቂ ነበረች።  የከፈተችውም የአጎታችን ልጅ መሆኑን አወኩ። በድንጋጤ ክው ብላ ደርቃ ቀረች። ከሁኔታችን አንዳች ነገር ሸሽተን እንደመጣን ታውቋታል። መርታ ያደረሰችን የአጎቴ ልጅ በሩን ከውስጥ ቀርቅራ፣ ወደ መቀመጫው እያመላከተችን፣ የተከተለን ሰው ይኑር አይኑር በሩ ተለጥፈፋ አጣራችና መጥታ ከጎኔ ተቀመጠች። "ተረፋቹ? ፍልጡ አገኘኛቹ እንዴ?" አለችኝ። እህቴ ድንጋጤ አልለቀቃትም እንደተለጠፈችብኝ እየተንቀጠቀጠች ታለቅሳለች። "አይ አልነካንም" አልኳት። በድንጋጤ ደርቃ ቀርታ የነበረችው የአጎቴ ልጅ ፣ መሪያችን የሆነውን ሁሉ ስትነግራት። ድንጋጤዋ በረታ። "አዎ ቀን ሀያት(የወንድሜን ሚስት ማለቷ ነው) ሲነሳበት የሚይዘውን ጦር ከቆጥ አውርዳ፣ ስትደብቅ፣ አይቻት። ምን ሆነሽ ነው? ስላት። "ዛሬ ሁኔታው አላማረኝም" ብላኝ ነበር። እንደገመተችው ተነሳበት ማለት ነው?" አለች። አንዳች ነገር ከእግር እስከጥፍሬ አንጨረጨረኝ። አላገኘውም እንጂ ሊወረውርብኝ ሲፈልግ የነበረው ጦር ነበር ማለት ነው? ። ንዴት ይሁን ድንጋጤ ወረረኝ። "እሺ እንግዶቹን አዛው ጥዬ ነው የመጣሁት ይዣቸው ልምጣ አልኩ። የአጎቶቼ ልጆች አልፈቀዱልኝም። ቢፈቅዱልኝም በትክክል በጨለማው መሄድ መቻሌ እ ራጠራለው። "እኔ ሄጄ አመጣቸዋለው! ብላ መሪያችን በሩን ከውስጥ እንድትቀረቅር ለሌላኛው የአጎቴ ልጅ ነግራት ወጥታ ሄደች። እኔም እህቴም የሆነው ነገር ሁሉ እውነት እውነት አልመስል ብሎናል። ከአፍታ የነበርንበት ጎጆ በር ተንኳኳ። ድምፃችን አጠፋን።ልጅቷ ወደ በሩ ተጠግታ በማንሾካሾክ "ማን ነው አለች። መሪያችን ነበረች። እንግዶቹን ይዛ መጣች። እነሱም ድንጋጤ አርበትብቷቸዋል። ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰው ባዳ በመሆናቸው ድንጋጤያቸው ከኛ ቢበዛ እንጂ አያንስም ነበር። ቀስ በቀስ ተረጋጋን። እኔቴና በቤቱ የነበሩ ሁሉ ጓዛችንን እንደያዙ ያለንበት ጎጆ መጡ። ተረፋችሁ ብለው ከጠየቁን ቡሃላ።  እኛ ከቤት ከወጣን ቡሃላ ስለተፈጠረው ነገር ነገሩን። ወንድሜ ይህን ከፈፀመ ቡሃላ የተፈጠረውን ነገር ማወቅ አልቻለም። ነብሱ በደንብ ከተመለሰች ቡሃላ እኛን"የት ሄደው ነው? " ብሎ  መጠየቁን። እራቱን በልቶ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ እንደወሰደው ነገሩን። ያደረገውን ነገር አለማወቁ፣ በሱ እንዳንፈርድ አደረገን። ወደ አይደለም አልን።  እናቴ ግን ነገውኑ ወደ ከተማ እንድንመለስ አስጠነቀቀችን። ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም ለማንኛውም እናንተ ሂዱ። እኛ እንደሚሆን እናደርጋለን ብላን። አስደሳቹን ጊዜ በአሳዛኝ ሁኔታ አጠናቀን፣ በማግስቱ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ። ይህን ሁሉ ልዘበዝብልህ፣ የቻልኩት ለኔ ካሏት መስዋዕት ትከፍላለች ባልኩህ እህቴ ሰበብም አደል። አዎ!! ዛሬም ነገም! እወዳታለው!!

ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment