Friday, June 16, 2017

" ግ መ ሌ ን ም አ ስ ራ ለ ው… "


#ሳteናw

ሁሌም በተለመደው፣ ጊዜ፣ ቦታና ሰዓት፣ ሁሉም መሿለኪያውያን ከአፍጥር ቡሃላ በመሿለኪያዋ ተሰብስበዋል። ቀን በፆም እንደ ቁርበት ደርቆ የዋለ ሁሉ፣ አሁን ዘና ብሏል። ይጫወታል፣ ይሳሳቃል፣ ይጯጯሃል፣ ይቅማል። አዲሱ የፉአድ መንዙማ "ሰላም ነጃ" እያለ ከብሉቱዝ እስፒከሩ ይሰማል። በጉርዷ በርሜል እሳት ይነዳል! በእሳቷ ዙሪያ ተቀምጠዋል። ትኩስ ነገር የሚሸጡ ልጅ አገረዶች፣ የቡናና ሻይ፣ በማቅረብ ረገድ ገበያቸውን አጧጡፈውታል። የጥንቱ የመርካቶ የረመዳን ምሽት ድባብ፣ ጨርሶ እንዳይጠፋ ይመስል፣ በመሿለኪያ ብቻ ይታያል። በምርቃና ሚናነት የነበረው ጫጫታ ቀስ በቀስ ወደ ፀጥታ ሲለወጥ፣ ሁሌም ፀጥታ ጠብቆ መወያያ ድንገት ርዕስ በመክፈት የመታወቀው ሰያ ነጭ ሽንኩርት ዛሬም በድንገት ፀሎትም ምኞትም የመሰለ ንግግር ያንበለብል ጀመረ…

"… ያረቢ በዚህ ረመዳን ይሁንብህ … የተረጋጋች ህይወት፣ መሽታ በነጋች ቁጥር አዳዲስ የምትሆን ቀን። አለ አይደል አሁን እንዳለው አንድ አይነት ከሆነ አዋዋል ተቃራኒ የሆነች። ደግሞ… ተረጋግታ ምታረጋጋኝ፣ የህይወቴ አጋር። ቀን በተረጋጋ ውሎዬ… ናፍቄ፣ ማታ እስካገኛት የሚጨንቀኝ ሚስት። ገና ስገባ ከበሩ… "ሀቢቢ!እንኳን ደህና መጣህ!"ብላ ከንፈሬን በከንፈሯ ጨብጣ ምትቀበለኝ። ቀን ያበሳጨኝን ጉዳዮች ሁሉ፣ ልብ በሚያጠፋ አሳሳሟ የምታጠፋልኝ። አጠገቧ ስሆን፣ ደስታ የተባለ ሁሉ፣ እንደ ዛር በላዬ ላይ ሰፍሮ፣ የሚያንዘረዝረኝ። መቼም የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኢሳት ማየት እንጂ ምኞት አይከለክል። በመሆኑም እመኛለው!! አርቄ አልማለው። ደሃ በህልሙ ምናምን ብለህ ደግሞ ሙድ ጋማ!።በል አሉህ። ምድረ በርሜል!!። እኔ ከምሬ ነው። የሚያሳካው እሱ ነው። ይሄኔ እኮ በዚህም ያሳከከህ አለህ!! የራስህ ጉዳይ! ብቻ የተረጋጋች…

"አረ!! ቆይ … አረ!! ቆይ… እስኪ ተረጋጋ! አበድክ እኮ!! " ሳተናው እየጮኸ አቋረጠው።

"ይኸው!! ምን አልኩ? ምን ብዬ ነበር? አያችሁ ሲያሳክከው! እንዳንተ አይነት ምቀኛ እያለ በየት በኩል እንመኝ? ስማ አከክም አላከክም፣እኔ እመኛለው። ተረጋግቼ አልማለው። ተስፋ እስንቃለው። ፀሎት ጠዋት ማታ አደርሳለው። በአስተማማኝ ሁኔታ መሰረት ያለው የተረጋጋና በቂ የገቢ ምንጭ ያለው መተዳደሪያ፣ የተግበሰበሰ ብር ባልጠላም የተግበሰበሰ ኑሮ  አልፈልግም! በቃ የተረጋጋ! ብቻ የምፈልገውን ማድረግ ያስችለኝ!!ከዛ ውጪ ወላ ሃንቲ!! ከሚስቴ ጋር ተረጋግተን ……

"አረ ባክህ ተረጋጋ አንተ ሰው!! "ቡፌት ነበር ያቋረጠው። "ምንድነው ብቻህን ምታብደው!? ግልፅ አድርገውና አብረን እንበድ?! 

"ዝም በል! እኔ አላበድኩም ምኞቴን ነው የለመንኩት!!"

"ድንበሩን ያለፈ ምኞት ከእብድ ነው !! ስለዚህ እመነኝ ሰያ አብደሃል፣ ደግሞም እብድ ሁሉ አብጃለው አይልም እኮ! እንደፈረደብን ይህን ልጅ የሆነ መላ ተፈላልጠን  አማኑኤል ሆስፒታል እናስገባው እንጂ!! ዝም ትላላችሁ እንዴ? ጎበዝ? "

"አረ! የአማኑኤል ጂኒ ይፈለጥህ! አን ግባሶ! ሟርተኛ፣ ደግሞ መመኘትም ልትከለክለኝ ነው?" በሰያ ቀልዳዊ ስድብ መሿለኪያን አስገምጋሚ፣ የሳቅ  ወጀብ አናወጣት።

"አይደለማ!ሰ…" ብሎ ጀመረ ሳተናው። "…ስትመኝ ካለህበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሊሆን ይገባል!! ለትልቁ ምኞትህ ቢያንስ ቀድመህ ሁለት እርምጃ መቅረብ አለብህ። ሰው ሚልየነር ሆኖ ቢልየነርነት ቢመኝ አግባብ ነው!! ለቂጡ ጨርቅ የሌለው ትሪልዮነር ያርገኝ ቢል ይሄ ሰው በእርግጥ አብዷል። አንተም ሳስብህ ልክ እንደዚህኛው ሰውዬ እያበድክ ነው … ቅድሚያ የምትመኘውን እወቅ። ሚስት ከመመኘትህ በፊት፣ ራስህን ማስተዳደር መቻልህን አረጋግጥ። ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቀህ ያለማንም ድጋፍና እርዳታ በመቆም ሀላፍትናን ልትለማመድ ይገባል። ይህን ስታረጋግጥ ሃላፍትናዎችን መሸከም እንደማይከብድህ ስታምን፣ ትዳር ምናምን የተባሉ ነገሮችን በርህን ክፍት አድርገህ ትመኛለህ፣ ብሎም ትፀልያለህ።፣ የዛኔ ተግባርህ፣ ከፀሎትህ ጋር ተጋግዞ ወለል ካለው በርህ ይገባልሃል። ይህ ነው አካሄዱ። ዝም ብሎ ተቀምጦ ድንበር የጣሰ ምኞት እብደት እንጂ ሌላ አይደለም።" ሲል ሳተናው ሁሉም በጥሞና  ያደምጠው ነበር።

"የምኞት ድንበር ቸካይ ያደረገህ ማን ነው ባክህ? ደግሞ የሚያሳካው ፈጣሪ ነው" አለው ሰያ በአንድ በኩል የሳተናው ንግግር እውነታነት እየታየው።

"ልክ ነው! አለው የንግግሩን ቅላፄ ወደ ቁም ነገር እየለወጠ። "እንዳልከው የሚያሳካው ፈጣሪ ነው! እኔም ሳጥናኤል ነው አልወጣኝም። ዋናው ነጥቤ ግን ፈጣሪ የሚያሳካልህ፣ አንተ መንቀሳቀስ ስትጀምር፣ ነው። ለስኬትህ መጀመሪያ፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምር ነው። ይሄን ሳታደርግ እጅ እግርህን አጣጥፈህ፣ፈጣሪ ነው የሚመግበኝ ብለህ፣ በርህን ዘግተህ ብትውል፣ ጠኔ ይቀረጥፍሃል እንጂ፣ በአረቢያንስ ናይት ተረት ተረት መፅሀፍ ላይ … እንዳለው ታሪክ፣ አላዲን ፋኖሱን ሲፈትግ እንደሚመጣው ጂኒ፣ ጣፋጭ ምግብ፣ በወርቅ ሳህን አሳብዶ አያቀርብልህም። ገብቶሃል? የምልህ?።  ለመብላት፣ መንቀሳቀስ መስራት ይጠበቅብሃል፣ የዛኔ ፈጣሪም እገዛውን ያደርግልሃል። ስራህን ያገራልሃል፣ ይመግብሃል። የራስህ ጥረትና ጥንቃቄ ሳታደርግ ፈጣሪ አዳኝ ነው፣ ጠባቂ ነው፣ብለህ ብቻ ከምትደረድርበት ኤፍኤስአር ላይ ተወርወር እስኪ? በፓራሹት የሚቀልብህ መሰለህ? የሚያድንህ፣ የሚጠብቅህ፣ መጀመሪያ፣ መጠንቀቅ ስትችል ነው። እራስህን ስትጠብቅ ነው። ግልፅ ነው? ብሎ ቀና አየው ሳተናው።

  የንግግሩ እውነታነት ፍንትው ብሎ የታየው ሰያ ነጭ ሽንኩርት! አሁን ተረጋግቶ በአዎንታ ራሱን ነቀነቀ። ማላገጥ ሟንጓጠጡ ቀርቶ፣ ሁሉም በቁም ነገር እያደመጡ መሆኑ ሲረዳ ሁሉንም የሚያማክል ወቅታዊ ሀሳቡን አከለ…" ባይሆን ሁላችንም ከተግባር ለውጥ ጋር ያለንበት የረመዳን የመጨረሻው አስር ቀን ፈጣሪ የባሮቹን ፀሎት ከየትኛውም ግዜ በበለጠ የሚቀበልበት ጊዜ ነው። ልንጠቀምበት ተገቢ ነው። ይሄ ለሊቱን ሙሉ መቃማችን ቀርቶ በተሃጁድ ሰላት ላይ፣ እንለምነው። ደግሞ ተሃጁድ ሰላት ላይ፣ ይሄን ገለምሶ አፍሰን አፍሰን፣ ለቅሶአችን ከፋቲሃ ጀምሮ፣ የሰጋጁን ጥሞና የሚሰርቅ እንዳይሆን እንጠንቀቅ። ልብ አድርጉ!! አናልቅስ አላልኩም!!ማልቀስ ካለብን በስርዓት ድምፅን ቀንሰን፣ ሌላውን ሳናውክ አልቅሰን እንማፀነው። የተግባር ለውጣችንንም ከዚህ ጊዜ ጀመሮ፣ እንተግብረው… የሚናገረው ከልቡ ነበር። "…ቆይ! ለውጥ አንፈልግም? ለውጥ አትፈልግም ጄጃን? ለውጥ አትፈልግም ቡፌት? አንተስ ጃንደረባው ለውጥ አትፈልግም? ቅድም ሰያ የተመኘውን በህይወታችን እንዲፈፀም ሁላችን አንሻም? እርግጠኛ ነኝ የሁላችንም መልስ "እንፈልጋለን" ነው። ስለዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንጀምር።  አረቦች እንደሚሉት "ግመላችንንም እንሰረው፣ በአላህም እንመካለው"። ምን ለማለት ነው? ከፀሎታችን ጎን ለጎን ለፍላጎታችን መሳካት የተግባር እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው ። እንደውም ዛሬውኑ፣ እላፊ ወጪ ለመቀነስና ለመቆጠብ፣ ፈጣሪም ይረዳን ዘንድ የተሃጁድ ሰላት ብንጀምርስ?። ልክ አይደል እንዴ? ሲል ሁሉንም ጠየቀ። "አዎ"ሲሉ ከልባቸው በህብረት መለሱለት። አላህም ያግዛቸው።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment