Thursday, June 8, 2017

"የ ዳ ዶ = ቃዋ! "


#ሳteናw

  ከቤቱ የሚወጣው የቡና፣ የእጣን፣ የቆጮናአይብ፣ ጠረን ከራሱ አልፎ ጊቢውን አውዶታል። ይኸው መዓዛ ለጎረቤቱና ለመንደሩ ሁሉ በተለምዶ ለሚያውቁት (የዳዶ፣ቡና) በዋሽቶ ቤት መድረሱን ያውጃል። በዚሁ ሰፊ ቤት ውስጥ፣ ከዳር እስከዳር ኬሻ በተነጠፈበት ሜዳ ላይ ትራስ እንደ ውሃልክ ጠርዙን ተከትሎ በተደረደረና፣ ነጭ በነጭ በለበሱ በጎረቤት፣ በወዳጅዘመድ እናቶች ከጥግ እስከጥግ ተሞልቷል። የሰፈነው ፀጥታ፣ እንኳ ሃያ ሰላሳ የሚሆኑ እናቶች፣ አንድ ሰው ያለበት አይመስልም ነበር። ሁሉም ፀጥ ብሏል። ከቤቱ ጥግ በመጋረጃ ለተጋረደው አልጋቸው፣ ጀርባቸውን ሰጥተው፣ እንደታደሙት እናቶች በነጭ ልብሳቸው ደምቀው፣ ከደርባባ ሰውነታቸው ጋር የተለየ ግርሟ ተላብሰው፣ ከፍ ባደረጋቸው ፍራሽ ላይ ወይዘሮ ሸምሲያ (ዋሽቶ) ተሰይመዋል። ከፊት ለፊታቸው እንስራ በሚያክለው ጀበና የፈላው ቡና በመንተክተክ የጀበናውን ክዳን እያስዘለለው በሸፎው ላይ ተቀምጧል። አጠገቡ በስኒ የተገጠገጠው ረከቦት፣ የቡና ቁርሶቹ ዳንቴል እንደለበሱ ቦታ ቦታውን ይዘዋል። ዋሽቶ ከጎናቸው በተደጋገመ ግርዛት ሳቢያ፣ በሽንቱ ቧንቧ ላይ በተፈጠረው ኢንፌክሽን ምክኒያት፣ ከሸና ሶስት ቀን የሆነውን፣ የሁለት አመቱን የልጅ ልጃቸውን ከወገቡ በታች እርቃኑን እንደሆነ በሀኪም የተለጣጠፈች ወሸላው በግልፅ እየታየች እና ትንንሽ እግሮቹን እያንፈራጠቀ ተኝቷል። አሁንም አሁንም አንድ ነገር ይሆንብኛል በሚል ስጋት ይመለከቱታል።
ከምድጃው የሚተነው የእጣን ጭስ፣ ቤቱን ከማወዱ ባሻገር፣ ድባቡን በማሞቅ ረገድ ሰፊውን ድርሻ ወስዷል። ሁለቱም የቤቱ ልጅ አገረዶች፣ እቃ በማቀራረብ እንቅስቃሴ ተጠምደዋል።

ዋሽቶ ዱዓውን ለመጀመር፣ የቀረውን ነገር ካለ በሚል ማዕዱን መረመሩ። የቀረ አለመኖሩን ሲያረጋግጡ። ወደ ታዳሚ እናቶች ቀና ብለው የጭሱን ጭጋግ በአይናቸው ትኩረት እየሰነጠቁ የእናቶችን ስብስብ ከቃኙ ቡሃላ…
ዝግ ባለ ድምፅ
"ልጄ! ለዘምዘም መልዕከቱን አላደረሳችሁላትም እንዴ?" ሲሉ ጠየቁ።
"አረ! ጠርቻቸዋለው እማዬ" ስትል መልሰች ከጀበናው ፊት የተሰየመች የልጅ ልጃቸው፣ ማለትም የታመመው ህፃን ልጃቸው ታላቅ እህት።
"ታዲያ ለምን ዘገየች? ለልጄ ዱዓ ልናደርግ ነው ብለሽ አስጠንቅቀሽ አልነገርሻትም እንዴ?"
"አረ!! ነግሬያለው!" አለች።
"እሺ"ብለው
ቅቤውን እሳቱ ላይ ጣጂው በሚል ምልክት እያዘዟት ወይዘሮ ዘምዘም
"አሰላሙ አለይኩም" ሲሉ ገቡ።
"ዋአለይኩም ሰላም" የእናቶች የጅምላ ድምፅ ምላሽ ሰጣቸው።

  ወይዘሮ ዘምዘም በረጅሙ በኮባ የተጠቀለለ ጫታቸውን እንደያዙ ከዋሽቶ አጠገብ ተቀመጡ። በአይናቸው የታመመውን ህፃን በሀዘኔታ ተመልክተው ቀና ሲሉ፣ ለምን ዘገየሽ በሚል እይታ ዋሽቶ ሲገረምሟቸው አይን ለአይን ተገጣጠሙ።

ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአይናቸው የቀረውን ነገር አጣሩና ማዳውን(የቡናቁርሱን) ማሰነዳዳት ጀመሩ።  የረጋውን ቅቤ በሻይ ማንኪያ ሞዥቀው፣ ፈልቶ ዘራፍ ይል በነበረው ቡና ላይ፣በሌላ እጃቸው የጀበናውን ክዳን አንስተው፣ በቀዳዳው በላይ በላይ ቅቤውን ሲያጎርሱት፣ በግለቱ ቅቤውን አቅልጦ በማንሸራተት ወደ ሰፊው ሆድቃው ሰለቀጠው። ክዳኑን መልሰው ከደኑት። በሰፊ ጎድጓዳ ሳህን ተሞልቶ የቀረበው አይቤናጎመን የተሸፈነበትን ዳንቴል አንስተው፣ ምድጃው ላይ በእጀታ ኒኬል የቀለጠውን ቅቤ ገልብጠውበት ሲያበቁ፣ በላዩ ላይ የሚጥሚጣ ዱቄት ነሰነሱበት። አይብና ጎመኑ የተንሳፈፈበትን ቅቤና ሚጥሚጣ እስኪያሰርገው ድረስ፣ በሌላ ትሪ ዳንቴን ለብሶ ተነባብሮ የተቀመጠውን ቆጮ ገልጠው፣ በዳቦ ቢላ በአፋቸው ለማንም የማይሰማ ፀሎት እያነበነቡ፣ እንደ አነባበሮ እያሰመሩ ይጠርዙት ያዙ። የእንቅስቃሴቸው ዝግታነትና መመሰጥ፣ የመሬት ስበት በሌለበት ህዋ ላይ እንዳለ ተመራማሪ እተንሳፈፉ የሚያከናውኑ እንጂ፣ በቤታቸው ተቀምጠው የዳዶ ቡና የሚያሰናዱ አይመስልም ነበር…
በመሆኑ የሁሉንም ታዳሚ ቀልብ ስቧል። የቅመማ ቅመሙ መልካም ጠረን የታዳሚውን አንጀት  ያንቋርረዋል። ይህን አከናውነው እንዳበቁ ለሁሉም በሚሰማ መልኩ የመክፈቻ ዱዓቸውን (ጀባታ) ማድረግ ጀመሩ፣ አሚን አሚን አሚን በማለት ዱዓውን ተቀብለው አበቁ።
ጀባታው እንዳበቃ፣ ከፊት ለፊታቸው ተቀምጣ የነበረችው የልጅ ልጃቸው ጀበናውን አንስታ በቅቤ የወዛውን ቡና፣ አያቷ ባስተማሯት የተረጋጋ ስልት በሲኒዎቹ ትቀዳ ጀመር፣ በአንፃሩ እሳቸውም፣ አይቤበጎመኑን፣ በቅቤና በሚጥሚጣው ማላወስ ሲጀምሩ፣ ወይዘሮ ዘምዘም ደግሞ የተቆራረጠውን ቆጮ እየነጣጠሉና በትንንሽ ሰሐን አስተካክለው አቀረቡ፣ ዋሽቶ ያላወሱትን አይብበጎመን  በእፍኛቸው ዘግነው የተቆራረጠ ቆጮ ላይ በማድረግ ለታዳሚው ለምታደርሰው ሌላ ልጃቸው እያቀበሉ ማከፋፈል ጀመሩ። የሚግባቡትም በሹክሹክታ ስለነበር ቡናና ቁርሱም ለሁሉም እናቶች ደርሶ ሲመገቡም ሆነ ሲጠጡ በፍፁም ፀጥታ ነበር። በዚህ መካከል ለሚደርሰውም  ታዳሚም ሆነ ከቤቱ ውጪ ላሉ የጎረቤት ልጆች፣ ድንገት ጠረኑ ጠርቶት የደረሰ የኔቢጤውም የቡና ቁርሱ ታድሎት ተበልቶ ተጠጥቶ አበቃ። ዋሽቶ ላልነበሩ ልጆቻቸውና ለጎረቤቶች ድረሻቸውን በመጡበት ሰዓት እንዲበሉ ለይተው ከአልጋቸው ስር አስቀመጡላቸው።

ይህ ከሆነ ከተበላ ከተጠጣ ቡሃላ ሁሉም እናቶች ያመጡትን ጫት በአንድነት ከዋሽቶ ፊት ለፊት በመቆለል በሰፊው የእናቶች ዱዓ መረደግ ጀመረ። ዋናው የዱዓው አጀንዳ ለልጅ ልጃቸው ቢሆንም ቅሉ፣ ስለ ሁሉም ነገር ፈጣሪያቸውን ተለማመኑ። አሚን …አሚን …አሚን የሚለው የህብረት ድምፃቸው እንኳን  ቤት ውስጥ ላለው ለውጪውም ሰው ትኩረት ይስባል።
በሁሉም እናቶች የሚደረገው ዱዓ ደራ፣ የእናትነት ገራገር ባህሪያቸው ሆኖ፣ ስለ ግል ጥቅማቸው ሳይሆን፣ ስለልጆቻቸው፣ በወቅቱ ሰላም ስላጣችው ስለ ሀገራቸው ጭምር ፣ነበር። ረጅም ሰዓት የፈጀው የዱዓ ስነስርዓት ካበቃ ቡሃላ! ሁሉም እናቶች የታደላቸውን ጫት እየቃሙ ጥንድ ጥንድ ሆነው ወግ ጀመሩ። ይህን የተመለከቱት ዋሽቶ በመንዙማና በዚክር፣ ትክረታቸውን ለመሰብሰብ ከጅርባቸው ያለውን መጋረጃ ገለጥ አደርገው ከአልጋው ስር እድሜ ያወዛውን ድቤያቸውን አውጥተው አንዴ ሲመቱት አስገምጋሚ ድምፁ እንዳሰቡት የሁሉንም እናቶች ቀልብ ሳበላቸው። በመቀጠል ፈጣሪያቸውን፣ ነቢዩ ሙሀመድን(ሰዐወ) ደጋግ የፈጣሪ ባሮችን ታሪክ የሚያወሳ፣ ገድላቸውን የሚዘክር መንዙማ ይባል ጀመር። ቤቷ በድቤው ድው ድው ደው  ድው በሚለው ድምፁ፣ ሪትሙን በጠበቀው ጭብጨባ፣ በሚያወጡት ዜማና ግጥም፣ ልዩ ድምቀት ፈጠረች። ነሻጣ፣ ጨመረ፣ የነቢዩ(ሰዐወ) ስም ሲወሳ በሚያነቡ እናቶች እንባ ሰከረች።ከቀትር የጀመረው የዱዓው ስነ ስርዓት ፀሀይ ማዘቅዘቅ ስትጀምር የእናቶች ስብስብ ከመበተኑ በፊት የሚደረገው  የማሳረጊያው ፀሎት የሚጀመርበት ሰዓት ደረሰ። ይህን የተገነዘቡት ዋሽቶ ከወገብ በላይ እርቃኑን የተኛ የልጅ ልጃቸውን፣ ከነ ፍራሹ ተሸክመው ወደ እናቶች መሃል ሲያስገቡት። የቅድሙ ፀጥታ ሰፈነ። የማሳረጊያው ፀሎት ይደረግ ጀመር፣ ሁሉም እናቶች እንትፍ እንትፍ እያሉ ለዋሽቶ የልጅ ልጅ ዱዓ አደረጉ። ድዓቸው ከአርሽ በላይ ካለው ፈጣሪ ዘንድ ደረሰ፣ምላሹ ከሰባተኛ ሰማይ ወደ እናቶች ወረደ። ዋሽቶ የማሳረጊያው ፀሎቱ እንዳበቃ። የልጅ ልጃቸውን አንስተው ወደቦታቸ ሲመለሱ፣ የፈጣሪን ተዓምር አዩ። ክንዳቸው ላይ የተኛው ልጃቸው ድንገት ሽንቱን ፍንጥቅ፣ ብላ ውልብ ስትል፣ ዋሽቶ ባለማመን ቆይ ብለው ባሉበት ቀጥ አሉ። ቀስ ብለው ከእጃቸው ላይ ወደ መሬት ተነበርክከው ልጁን ከነፍራሹ  አጋድመው
"ሲሸና ያየው መሰለኝ" አሉ። ለማረጋገጥ የተኛበትን ትንሽዬ ፍራሽ እርጥበት እየደባበሱ። ለመሄድ ይዘገጃጁ የነበሩ እናቶች ዋሽቶንና ልጃቸውን ከበው ቆሙና እንደ ዋሽቶ ወደ እንትኑ፣ ሽንቱን በአይናቸው ጎትተው ያወጡ ይመስል አፈጠጡበት። በመካከላቸው ፍፁም ፀጥታ ሰፈነ። ትኩረታቸውን ከኋላ ለተመለከተ ሰው በቀብር ዙሮያ ቆሞ አንዱ በአንዱ ተደጋግፎ ወደ ጉድጓዱ የሚመለከት የቀባሪ ስብስብ ይመስሉ ነበር። ፀጥታው ደግሞ የሁሉም የልብ ትርታ እስከሚሰማ ድረስ አስመስሎታል።
ድድው… ድድው… ድድው…
ከአፍታ ትኩረት ቡሃላ የሽንቱ ፍንጣቂ ፍንጥር ፍንጥር ብሎ በመጨረሻም ያለ ማቋረጥ በረጅሙ መንፎልፎል ጀመረ። ለሶስት ቀን የተገደበው ሽንቱ ለረጅም ደቂቃ ሽንቱ ሽቅብ ተንቧቧ። ይህን የተመለከቱ እናቶችሁሉ፣ የፈጣሪን ምላሽ፣ በእልልታ አመሰገኑ።
እልልልልልልልል!
እልልልልልልልል!
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment