Thursday, January 12, 2017

"ም ር መ ራ"

"ምርመራ"
#ሳteናw

…የተናፈሰውን አሉባልታ በሰማ ቅፅበት ሙዱ ተቦክሞበታል። የወደፊት ምኞትና ተስፋው፣ በአንዴ ጨለማ ሲለብስ ይታየዋል። ወይኔ ጉዴ!! ይላል አስሬ በሆዱ። ይኼን እንዴት እስከዛሬ ሳልገምት ቀረው? ለነገሩ ቀድሜ ባውቅስ ምን አዲስ ነገር ይኖራል? የስቃይ ዘመን ከማራዘም በቀር? እያለ ያሰላስላል። ወሬውን ውጪ ቢሰማውም፣ አሁን መሿለኪያ ውስጥ ተቀምጧል። መሿለኪያዎች የሚያወሩትን የወሬ ግንጣዮች ይሰማል እንጂ አያዳምጥም። አካሉ መሿለኪያ፣ ልቡ ሌላ ቦታ።

እንደዛሬ ሳይለያዩ፣ የረገጥከውን፣ የረገጥሺውን፣ አልረግጥም ሳይባባሉ በፊት ያሳለፉትን  ጊዜያቶች አንድ በአንድ ያወጣ ያወርድ ጀመር። "መንስኤው እኔ ነኝ ወይስ እሷ?"፣ ደውሎ አሉ ባልታውን እንዳይጠይቃት፣ አይንህ ላፈር፣ አይንሽ ላፈር፣ ተባብለዋልና ምን ያድርግ ። ከሷ ውጪ አያውቅም። ጨንቆታል፣ ጠቦታል። በፍርሃት ብዛት ሆዱ ተንቦጫቦጨ። ደህና የነበረው ልጅ አስሬ አተት እንደያዘው ሰው ሽንት ቤት አበዛ። ቆመ፣ ተቀመጠ፣ ተንቆራጠጠ። ይህ ለራሱ ባይታቀውም፣ ለመሿለኪያዊያን ግልፅ ነበር። ሁኔታው አዲስ የሆነበት ሰያ ነጭ ሽንኩር "ጓድ!ምን ሆነሃል?" ሲል ጠየቀው።
እውነቱን ነግሯቸው ስጋቱ ስጋታቸው እንዲሆን፣ አልፈለገም። ሳያረጋግጥ፣ ማውራቱን አልወደደም። ቢነግራቸው አሁኑኑ ማወቅ አለብህ በሚል በመሿለኪያዊያን ውሳኔያቸው አንጠልጥለው፣…  እንደሚወስዱት፣ አላጣውም።

"ምንም ብዙ ውሃ ስለጠጣው ነው መሰለኝ ውሃ ሽንት ቶሎ ቶሎ ይመጣብኛል" አለ ሌላ ጥያቄ እንዳያስከትሉበት… በመስጋት።

። ቤቱ ከመግባቱ በፊት፣ አሉ ባልታው እውነት ይሁን ውሸት ማረጋገጥ መቻል እንዳለበት ያውጠነጥናል ፣…  አለበለዚያማ ልተኛ አይደለም። በሀሳብ ስንገላታ እንዲሁ ማደሬ ነው" ሲል ዛሬውኑ ማወቅ እንዳለበት ወስኗል። ሌላ ቀን ያጥርበት የነበረው  የመሿለኪያ የቆይታ ሰዓት፣ ዛሬ አልሄድልህ ብሎታል ወይ አምላኬ! ግን እንዴት? ባለፈው ታዲያ ስጠይቃት፣ ምላሿ እንደዛሬው አሉባልታ ለምን አልሆነም? እያታለለችኝ ነበር ማለት ነው?  ወይስ እየተበቀለችኝ?" ይላል ለራሱ።
ለወትሮው በቃንቄ ምላሱ መሿለኪያን ይቆጣጠር የነበረ ልጅ ዛሬ በጥልቅ ዝምታ ውስጥ መሆኑ ለመሿለኪያዊያን አዲስ ነገር ሆኖባቸዋል።

"አረ!!…ፍሬንዴ ዛሬ ምላስህ ላይ ነው እንዴ የተቀመጥከው??" ከቡፌት ነቆራ አላመለጠም። ምላሹ ከልቡ ያልሆነ ፈገግታ ማሳየት ነበር።

ከዚህ ሁሉ ለምን ቶሎ ሄጄ፣ እውነቱን አላረጋግጥም? ያበጠው ይፈንዳ!!" ብሎ ያለ ሰዓቱ መሿለኪያን ለቆ ወጣ። በመንገድ ላይና፣በታክሲ ውስጥ ያሳለፈውን ጊዜ ሳያስተውል ከሰፈሩ ደረሰ። በአቅራቢያው ካለ መካከለኛ ክሊኒክ ገባ።

ወጣት የጤና ባለሙያ በፈገግታ ተቀበለው።
"ምን ነበር?"
"… ምርመራ ለማድረግ ነበር። አለ ድንጋጤ ባርገበገበው ድምፅ።
"ሰባ ብር ነው"።
"ችግር  የለም!! ስንት ደቂቃ ይፈጃል ግን?" ያሰጋው ዋጋው ሳይሆን፣ ጊዜው ነበር።
"ከአስራ አምስት አስከ ሃያ ደቂቃ ቢወስድ ነው!! ሲለው በጭንቅላቱ ንቅናቄ መስማማቱን፣ ሲገልፅለት… እሺ አንዴ ጠብቀኝ ብሎት ወደ ሌላ ክፍል ሄደ ። እሱም ወደ እንግዳ ማረፊያው፣ ገባና ተቀመጦ ጠብቀው። ወጣቱ መርማሪ …ጓንት፣ መርፌ፣ የአልኮል ብልቃጥ፣ ጥጥ እና የደም ናሙና መመርመሪያ (ኪት) በእጁ አንጠልጥሎ፣ ተከተለኝ በማለት ወደምርመራ ክፍል ይዞት ገባ።  እውነቱን ለማወቅ በቀረበ ቁጥር የልብ ምቱ እጥፍ ሆኗል።

ከምርመራው ክፍል ገብቶ እንደተቀመጠ  የሸሚዙን እጅጌ ክርኑ ድረስ ሰብስቦ ተዘጋጀ። ካሁን አሁን መጅ የሚያክል መርፌ ሲጠብቅ… መርማሪው… ጓንት፣  አልኮል በራሰ ጥጥ፣ የቀለበት ጣቱን፣ አሽቶ አፀዳለትና፣ በትንሽዬ ስለታማ ነገር ጠቅ፣ አደረገው ወገው ፣ደም ከየት ይምጣ? … ይቅርታ በአይኑ ጠይቆት ጠቅ ደገመው፣ ጣቱንን አልመዝምዞ አልመዝምዞ፣ በስንት ምጥ የደም ጠብታ፣መመርመሪያዋ ላይ አደረገው። እሱ ደግሞ የተበሳችው ጣቱን በጥጡ ይዞ… ባለሙያውን በአይኑ ይከታተል፣ ጀመር…

በብልቃጥ ያለ ፈሳሽ  የደም ጠብታው ላይ ጠብ አድርጎ፣ ውጪ እንዲጠብቀው ነገረው። ወጣ። ወና የሆነው እንግዳ ማረፊያ፣ ቴሌቪዥኑ ብቻ ይጮህበታል። ተቀመጦ ውጤቱን ይጠባበቅ ጀመር።
የምርመራ ክፍል ውስጥ የተመለከታት የመመርመሪያ መሳሪያ ትንሽነትና፣ ቅለት፣ በትክክል መስራቷ አጠራጥሮታል። ይሁን እንጂ መሳሪያዋ፣ ዓለም አቀፉን ዝቅተኛ መስፈርት አያሟላም ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የኤች.አይ.ቪ /ኤድስ/ መመርመሪያ ኪት በብቃት አገልግሎት መስጠት እንደሚችል በተደረገለት የጥራት ፍተሻ ተረጋግጧል።

ባሙያውም ውጤቱን ለማወቅ ጥቂት ደቂቃ  መጠበቅ ስለነበረበት፣ እንግዳ ማረፊያው መጥቶ አብሮት ተቀመጠ።
… ምክር ምናምን የሚጀነጅነው መስሎት፣ ፊቱን ዘፈዘፈው ፣እትት ሳይባል ውጤቱን ተነግሮት ብቻ ነው፣ መሄድ የፈለገው። ፍላጎቱ ተሳካለት። ባለሙያው ምንም አላለውም።(መርቅኖ ይሆን?)… አይኑን አንዴ ቲቪ ላይ፣ አንድ ጊዜ ግድግዳው ላይ የተለጠፉ ምስሎች ላይ ማንከራተቱ ሲሰለቸው፣ ተንቀሳቃሽ ስልኩን አውጥቶ መነካካት ያዘ። ማህበራዊ ድህረገፅ ከፍቶ ማየቱ  ሃሳቡን በደንብ ሰበሰበለት። የጭንቀት ሰዓቱንም አሳጠረለት። ስንት ደቂቃ እንደሆነ ሳያስተውል፣ አጠገቡ የነበረው ባለሙያም ወደ ምርመራ ክፍል መግባቱንም ልብ አላለም። ከነበረበት ተመስጦ፣ ድምፅ አባነነው። ከሞባይል ስክሪኑ ላይ ቀና አለ። ወጣቱ መርማሪ የምርመራው ክፍል በር ላይ ቆሞ …  ውጤቱን እየነገረው ነበር።
" ምን አልኸኝኝ?"
" ነፃ ነህ!"
እንዴት በደስታ ተስፈንጥሮ እንደተሳና፣… እንደረሰ ሳያውቅ፣ ራሱን ከቤቱ ውስጥ አገኘው።
ወገሬት!!

Wednesday, January 11, 2017

"ቅንነትም እርዳታ ነው"


#ሳteናw

… ቅን መሆን በራሱ እርዳታ ነው። ለዛውም የረጂውን ጥቅም ሳይነካ ተረጂውን የሚጠቅም ብሎም ህይወቱን የሚቀይር ሀይል ያለው። ለዚህ ምርጥ ምሳሌ የሚሆነው የአባላችን ጄጃንና የእንጀራ ወንድሙ ነስሪ፣የህይወት ታሪክ ነው…
⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂

  እንደተለመደው የመሿለኪያዋ ወጣቶች ከስራ ውሏቸው ቡሃላ ምሽቱን በመሿለኪያቸው ተሰባስበዋል። የሰሞኑ ውርጭ የፈጠረው ቅዝቃዜ በጉርድ በርሜል እንጨት ለማንደድ አስገድዷቸዋል። ይህ የአየር ንብረት( ምን የአየር ንብረት! የአየር ክስረት ነው እንጂ) … መሿለኪያን ወደ ፍሪጅነት ለውጦት፣ አባላቱን  በሞላ  ከቤቱ  ጋቢና ክንብንብ አምጥቶ ለማስለበስ ምንም አልቀረውም።  … ሙቀቱን ፍለጋ በበርሜሏ ዙሪያ … መሸጋሸጋቸው፣ አፍ ለአፍ ገጥመው ሚንሾካሸኩ የከንፈር ወዳጆች አስመስሏቸዋል። የሚንቦገቦገውን እሳት ከበው ሁሉም በርጫ እየበረጩ ነው፣ አጫሹም ፋታ እየሰጠ ያጨሳል። አንድ የጋራ መወያያ ርዕስ ካልተነሳ … አንዱ ከአንዱ ጋር መወያየት የተለመደ ነው። ቡፌት ስለ ሰሞኑ የአየር ፀባይ፣ ሳተናው: ከጄጃን ጋር፣ ሌላው ስለሌላ የተለያዩ አጀንዳዎች ወሬው ጥንድ ጥንድ ሆኖ አፍክቶቷል።

  እኔ ምለው ሲል ጀመረ ቡፌት" እኔ ምለው የሰሞኑ አየር ፀባይ!!…  ቆይ ምንሼነው? አለ አይደል፣ መላ ቅጡ እንደጠፋ፣ ይህ ነው ለማለት የቸገረ አይነት ሆነ እኮ። ፀሀዩ እንደ ክፉ ሰው ምላስ አቃጠለኝ ብለህ ጥላህን ስትይዝ…  ቀዝቃዛነት ያዘለ ንፋስ… ወላ ውርጭ በለው!! ወዛም የነበርከውን ሰው በአንዴ እንደ ሽሮ እቃ  አመዳም አድርጎ ቁጭ ይላል። በተለይ በሌሊት ምትነሳ ከሆነ…  አይጣል ነው። እንደውም መቼ ለት እንደ ልማዴ በሌሊት ስነሳ፣ ለወትሮው የሚቀበለኝ የወፎች ድምፅ ደብዛው ጠፍቶ ሳይለንት ላይ አክቲቬት ሆኗል። እንዴት ነው ነገሩ ብዬ የመኝታ ክፍሌን መስኮት ገልጬ አዕዋፋቱን ስሾፈትርልህ፣ አዕዋፋቱ ብርዱ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ መንቁራቸውን እያንቀጫቀጩ …  ቫይብሬት ላይ ሆነዋል።" የአባላት ሳቅ አጀበው። ሳተናው ሀሳቡን ከሳበው የቡፌት ቀልድ፣ ከጄጃን  ጋር ወደ ጀመረው ጨዋታ ዞረ።

"ቆይ ይኸውልህ ጄጃን! ስለ አንተና ወንድምህ ነስሪ ከስር መሰረቱ አስረዳኝ እስኪ?"

"አለ አይደል እንዴት ላስረዳህ! አለ በዝምተኛነቱ የሚታወቀው ጄጃን።
የቤተሰባችንን ሁኔታ በቀላሉ ለማስረዳት ከባድና፣ ውስብስብ በመሆኑ ያስቸግራል። አለ አይደል ጊዜና ጆሮ ሰጥተህ ካደመጥከኝ ልነግርህ ፍቃደኛ ነኝ አለ።"

"እባክህ ዝም ብለህ ንገረኝ!"ሲል ሳተናው ፣ ሁሉም አባል ጆሮውን ለጄጃን ሰጠ።

" የእናቴ እናት፣ ከእናቴ አባት ጋር ባለመስማማት ከተፋታች ቡሃላ፣ እንደሷ አግብቶ የፈታ ሰው አገኘችና ከተማ ውስጥ ትዳር መሰረቱ። ይህ ባሏ ከቀድሞ ሚስቱ የወለዳቸው ልጆች ነበሩትና፣ እነሱን በእንክብካቤ ታሳድግ ጀመር። ልጇ ማለትም እናቴ ኑሮዋ ገጠር ነበር። አያቴ ና ባለቤቷ ፍቅር ነበራቸው። አያቴ የባሏን ልጆች በእንክብካቤ ስታሳድግ፣ የአብራኳን ክፋይ እናቴ  ግን ገጠር ኖረች። አያቴና ባሏ በዚህ ትዳራቸው ንብረት አፈሩ። በአንፃሩ እናቴም ተድራ ልጆች ወለደች። ከእነሱም ውስጥ እኔ በከተማው አያቴ ቤት ማደግ ጀመርኩ። ከአያቴ ባለቤት ልጆች ጋር እንደ ወንድምና እህት በሆነ ስሜት። ሞት የተባለው የተፈጥሮ ህግ ከአያቴ ባለቤት፣ ጀመረ፣ ቀጠለ የሱን ልጆች አንዱ ነስሪ እስኪቀር ወደ ማይቀረው አለም ሄዱ(መቼም መልካም ሰዎች አይበረክቱም)፣ በመጨረሻም፣አያቴን ወሰደ።  በወቅቱ እኔ የአሰራሥድስት አመት ልጅ ነበርሁ። የአያቴ የእንጀራ ልጅ ነስሪ ደግሞ ትዳር መስርቶ ኑሮው በሌላ ስፍራ ነበር። አያቴ ስትሞት በጊዜው በቤቱ እኔ ብቻ ቀረው። የህይወቴ ሁለተኛም ምዕራፍ ከዚህ ጀመረ። አያቴ ከሞተች ቡሃላ በመርካቶው ቤት እኔ ብቻ መኖሬን የታዘበ ጎረቤት ቀበሌ ሄዶ<<ለጄጃን ተመጣጣኝ ቤት ይሰጠው ይሄን ለኔ ስጡኝ>> ሲል አመለከተ። ቀበሌ ከሚሰራ ሰው ጥቆማው የደረሰው ነስሪ ጓዙን ጠቅልሎ መርካቶ ቤት ገብቶ አብረን መኖር ጀመርን። ከዛ ቡሃላ ወንድሜ ነስሪ ለኔ ሁለት አይነት ሰው ሆነ። ከህፃንነት እስከ ጉርምስናዬ ያለው ነስሪና ከዛ ቡሃላ ያለው ነስሪ ። በጨቅላነት ዘመኔ ማንም ታላቅ ለታናሹ እንደሚሳሳው የሚሳሳልኝ የሚያዝንልኝ የሚንከባከበኝ ሲሆን። ከአያቴ ህልፈት ቡሓላ ማለትም ከሱ ጋር መኖር ከጀመርኩበት ማግስት ሌላ የማላውቀው ነስሪ ሆነብኝ። እንደ ልጅነቴ የነስሪን ፍቅር አጣው። በፊት የሚጫወት የሚያቃልደኝ የሚመክረኝ ነስሪ ባላወኩት ምክኒያት መሰረታዊ ፍላጎቶቼ በርሱ እጅ በሆነ በጥቂት ጊዜ  ውስጥ በበነነ ተነነው የሚቆጣ ቁጥጥር የሚያበዛ … የሚነጫነጭ ሆነ።

  ነስሪ በልጅነቴ አይቆጣኝም ነበር ማለቴ አይደለም። ይቆጣኛል። በልጅነቴ  ቁጣው ውስጥ የወንድማዊነት፣ የአዘኔታ፣ እና ለራሴው ጥቅም የሆነ መንፈስ ይታየኝ ነበረ። ከአያቴ ሞትና ከጉርምስናዬ ቡሃላ ግን ነስሪ ሳጠፋ የሚቆጣኝ ቁጣ አስጠንቃቂና አስፈራሪ፣ አስበርጋጊ እየሆኑ መጡ። <<የምትኖር ከሆነ ስርዓትህን ይዘህ ኑር!>> የሚል።  ሰሞኑን ከፍቶት ነው ብዬ ምክኒያት በራሴ ሰጠሁት። አስፈራሪና አስጠንቃቂው ቁጣ ተደጋገመ ነገሩ ባሳለፍነው ህይወት ተከስቶ የማያውቅ ስለነበር በጣም ግር አለኝ። ለሱ ግን የታወቀው አይመስለኝም። የዛን ሰሞን የቀበሌ መታወቂያ ፈርመህ አውጣልኝ አልኩት።"ምን ሊያደርግልህ ነው?" ብሎ ከጠበኩት በላይ ተቆጣ ግራ ገባኝ! ቁጣው የቤቱን ስም በኔ አዙርልኝ ያልኩት እስኪመስለኝ ድረስ በረታ። መታወቂያ ካርድ ምን ሊያደርግልህ ነው ይባላል እንዴ? ወቅቱ የ97 ምርጫ ካርድ የሚታደልበት ስለነበር ካርድ ለማውጣት ስል ብቻ ቁጣውን ተቋቋምኩት። በዚሁ ስሜት ቀበሌ ሄዶ ፈረመልኝና የመታወቂያ ካርድ ተቀበልኩ። ምን ሊያደርግልህ ነው ብሎ የተቆጣኝ ግን ብዙ ነገር እንድፈላፈል አደረገኝ። የድሮው ነስሪ ናፈቀኝ። ጭራሽ ግራ ቢገባኝ ነስሪ እንዲህ የተለወጠብኝ በምን ይሆን? ስል ግልፅ መልስ ያጣሁበት መብሰልሰል ላይ ጣለኝ።

  ከዛም ቡሃላ አንድ ነገር ሳጠፋ የነስሪ ቁጣ <<የምትኖር ከሆነ ስርዓትህን ይዘህ ኑር!>> የሚል ቃላት የበዛበት ሆነ። በዚህ ቁጣ ውስጥ አርፈህ መኖር ማትችል ከሆነ ቤቱን ለቀህ ውጣ የሚል ትርጉም እንደሚሰጠኝ ማስታወስ አይጠበቅብኝም። በወቅቱ ተማሪ ነኝ… ከነስሪ ጋር በመኖር ሂደት ውስጥ ስንኖር ከዛሬ ነገ ያባርረኛል የሚል ስጋት ያድርብኝ ጀመር። ይህ የስነልቦና ጫና እየቦረቅኩ እየዘለልኩ ባደኩበት ቤት ውስጥ  በነፃነት የመንቀሳቀስ ሞራሌን አጠፋው። እራሴን እንደባዳና ነገ እንደራሴ ቤት ያለ ስጋት አብረን ስለመኖራችን ዋስትና የሌለኝ አድርጌ ወሰድኩ። ምሽት ላይ ድሮ ሶፋው ላይ እየተንከባለልኩ ቪዲዮ ሙዚቃ እየመረጥኩ የማሳልፍ ልጅ ሳሎን በር ላይ ባለ ነጭ የኘላስቲክ ወንበር ላይ እስክንተኛ መቀመጥ አዘወተርኩ። ቤቴ ነው የሚለው እምነት ከህሊናዬ ደበዘዘ። ከዛሬ ነገ ይለወጣል ያልኩት ይህ የነስሪ የባህሪ ለውጥ መሻሻል ሳያሳይ ቀረ። በዚህ ሁኔታ አብሮ ማሳለፋችን ለተለያዩ ጭቅጭቆችና ንዝንዞች ሲያጋልጠኝ በተቻለኝ መጠን ከቤት መራቅ ጀመርኩ። ውጪ ውጪ አልኩ። አያቴ በህይወት እያለች የነበረን ፍቅር ናፈቀኝ። ትዝ ሲለኝ ያስለቅሰኝ ያስተክዘኝ ጀመር። ነስሪ በተደጋጋሚ የሚቆጣኝ አስጠንቃቂ ቁጣ እራሴን ከቤት እንዳገል አስገደደኝ። የቤተሰብ አባል አይደለህም የሚል መልዕክት አስተላለፈልኝ። እንደዛ ሳደርግ ነስሪም ለምን ብሎ ሳይጠይቀኝ ቀረ። በቃ ይህንን ነው የፈለገው ብዬ ውጪ ውጪ ማለቴን አበዛው… ከአይሆኑ ጓደኞች ገጥሜ ለተለያዩ ሱሶች ተጋለጥኩ። ከምቹ ሶፋ ወደ ደረቅ ወንበር ስሸጋገር ለምን ብሎ ያልጠየቀኝ ነስሪ በዚህ ድርጊቴ ተቆጣኝ። ቢቆጣኝም የቁጣው መንፈስ እንደ ልጅነቴው ዘመን በወንድማዊነት በአዘኔታዊ መንፈስ ስላልነበር ቁጣው ከልቤ ጠልቆ መዝለቅ አልቻለም። በዚህ ሂደት ነስሪ ስራ ለመጀመር የተወሰነ ብር ሰጥቶኝ ነበር። ዛሬ እንድሰራበት ከሰጠኝ ብር ግን በልጅነት ዘመኔ በወንድማዊ ስሜት የገዛልኝ መፅሀፍት ይበልጡብኛል። የባዳነት ፊት አሳይቶ ከሚሰጥ ሺህ ብር በወንድማዊነት መንፈስ የተሰጠ አስር ብር በስንት ጠአሙ። ያ እንድሰራበት የተሰጠኝ ብር ከዚህ ቀደም ከቤት ስሸሽ ባዳበርኩት ሱስ ምክኒያት ወደመ። በተደጋጋሚ የስራ መስኮችን ብሳተፍም እድገት ማምጣት አልቻልኩም። ከነስሪ ጋር ብንኖርም በልጅነት ዘመኔ የነበረው በወንድማዊ መንፈስ የመተያየትና የመተሳሰብ ስሜት ከአያቴ ጋር ላይመለስ ሄደ። ነስሪ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ያሳደረብኝ ተፅእኖ ለዛሬው ለሞራል አልባው ስብዕናዬ መሰረት ሆኗል። ዛሬ ልወቅሰው አልፈልግም ነገር ግን ምክኒይቱ ይህ ነው። ዛሬ ዛሬ ሳስበው የወንድማዊነት ስሜታችንን ያላላው መኖሪያ ቤታችን በመርካቶ ዙሪያ በመሆኑና ለወደፊት ህይወት ጠቃሚ ይዞታ ስለሆነ ይመስለኛል። ታዲያ ይሁና! ከኔ ጋር ምን ያገናኘዋል። የወራሽነት መብቱ ቢኖረኝምኝ! ፍላጎቱም የለኝ! ታዲያ የሚያገለኝንና ለህሊናዬ የማይፋቅ በቁጣ የተሸፈነ የምላስ ቢላ ለምን ተሳለብኝ እኮ ለምን? መልስ ያጣሁለት ነገር ነበር።

ነስሪ ቤት ውስጥ የራሴ አንድ ክፍል ነበረኝ። ማታ ገባለው  ጠዋት እወጣለው። ብቸኝነቱ ሲበዛብኝ አንዳንዴ ዘመድ ቤት አድራለው።  በመልሶ ግንባታ ምክኒያት ክፍሌ ፈረሰች። ግንባታው እሲኪያልቅ በመርካቶው ንግድ ቤት ለመሆን ሀሳብ ለነስሪ አቅርቤ ነበር። ነስሪ እንደማይሆንና እዛው አንድ ክፍል ውስጥ አንድ ላይ ማደር እንዳለብን አሳወቀኝ… ክፉ ጎኔን ብቻ እያነሳ ኮነነኝ።

…ይህ አባባሉ ውስጥም የታየኝ…  ሸር ያሰብኩበት መስሎት እንደከለከለኝ … ነው። ደግሞ በባልና በሚስት ክፍል አንድ ላይ እንደር ማለት ውጣ ከማለት በምን ይተናነሳል?። የነስሪ የልቡን አላህ ነው የሚያውቀው። ለኔ ደህንነት ቢሆን ይሄን ጥያቄ ሳላነሳ በፊት ወንድማዊ ምክሩን በቸረኝ ነበር። ከነነስሪ ጋር በአንድ ክፍል ማደሩ ከበደኝ… ምክኒያቱስ …  ይሄ ስሜት ከአሳዳጊ አያቴ ሞት ቡሃላ ለረጅም አመት በህይወቴ ያለተከሰተ ጉዳይ ነው። ከአያቴ ሞት ቡሃላ የነስሪ አውቆም ይሁን ሳያውቀው ያሳየኝ የባህሪ ለውጥ ነው። ከአያቴ ሞት ቡሃላ በቤቱ ውስጥ አራሴን ሳገል ዝም መባሌ ነው። ከአያቴ ሞት ቡሃላ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ… አይነት አስጠንቃቂ ቀጣ ነው። ምን ላድርግ ወድጄ አይደለም!  ነስሪ ይቆጣኝ የነበረው አሰጠንቃቂ ቁጣ ህሊናዬ ላይ ከባድ ህመምና ጠባሳ አትሞብኛል። ነስሪ አውቆም ይሁን ሳያው የሚያደርጋቸው ነገሮች፣ እኔን የባዳነት ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርጉ ነበሩ። በአንፃሩ እናቴም ከገጠር ወደ ከተማ ጠቅልላ ኑሮዋ በከተማ ሆኖ ነበር።  እኔና ነስሪ የምንኖርበት ቤት በግንባታ ሰበብ ስለጠበበ እኔ ከእናቴ ጋር ለመኖር ተገደድኩ። ገና አያቴ እንደሞተች እናቴ መርካቶ ያለው የንግድ ቤት የእናቴ ድርሻ ሊሰጠኝ ይገባል የሚል ጥያቄ ለማንሳት ስትሞክር እኔ ነኝ፣ እባክሽን ቤተሰባዊነቱ ይሻለናል፣ ለአለማዊ ጥቅም ስንል፣ አንቆራረጥ ብዬ ያስቆምኳት። ዛሬ ይኸው በቤተሰቦቻችን ንብረት የሚጠቀምበት ነስሪና ሌላ ሶስተኛ ወገን ሆነ፣ እኔና እናቴም በነስሪ ወደ ጎን ተደርገን የችግር ኑሮ እንመራለን " አለና ጄጃን ንግግሩን ቋጭቶ ወደ ዝምተኛነቱ ባህሪው  ተመለሰ። በታሪኩ ሁሉም የመሿለኪያ አባላት ተመስጠው፣ በጥሞና ነበር ያዳምጡ የነበረው። በዛ ላይ ጄጃንንም ነስሪንም በቅርበት ያውቋቸዋል።

"ጄጃን ልክ አላደረክም፣ እናትህ ድርሿዋን ልታስከብር ይገባ ነበር።" አለው ቡፊት ዛሬ ጄጃንና እናቱ የኑሮዋቸውን ሁኔታ እያሰላሰለ።"

"እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጄጃንም ሆነ እናቱ ይህን ከማሰባቸው በፊት፣ ነስሪ ፍትሃዊ ክፍፍል ማድረግ ይገባው ነበር። ልብ በሉ!! ቤቱ በጣም ሰፊ እንደሆነ ታውቃላችሁ። ነስሪ ቅን ቢሆን ኖሮ የራሱ ጥቅም ሳይነካ እነሱንም መጥቀም ይችል ነበር። ግን ቅንነት ይጎድለዋል። አስቡት ቅን ቢሆን ኖሮ እኮ ወደፊት ለሚደረገው የመልሶ ማልማት ግንባታ እራሱ፣ ነስሪም የጄጃን እናትም የአክሲዮን ባለቤት መሆን ይችሉ ነበር። ሁለቱም ስለ ገንዘብ ሳያስቡ መኖር ሲችሉ፣ ምን እነሱ ብቻ። ሌላም ባለድርሻ ቤተሰብ ቢኖር በቂ ነበር። ምን ያደርጋል በነስሪ ቅንነት መጉደል ምክኒያት ይህ ሁሉ ሊበላሽ ችሏል።" አለ ሰያ ነጭ ሽንኩርት በቁጭት ስሜት።

ግድ የለሹ ሙልጌ ቀጠለ… "ምንም! የተበላሸ ነገር የለም። አሁንም ቢሆን የተበላሸውን ማስተካከል ይቻላል። በገዛ ንብረታችሁ የበይ ተመልካች ልትሆኑ አይገባም። ትሰማለህ ጄጃን የወንድማዊነት ይሉኝታ ምናምን ምትለውን ቡቱቶ አውልቅና ጣል። እሱ ይህ ስሜት ቢኖረው ዛሬ ስትቸገሩ እያየ ዝም አይልም ነበር። አሁንም ቢሆን ቤቱ ሰፊ ነው፣ ለሁላችሁም ይበቃል። ፍትህ ልታገኙ ይገባል። መጀመሪያ በሽምግልና ካልሆነ በህግም ቢሆን ሄደህ፣ መብታችሁን ማስከበር አለብህ።  ፍትሃዊ ክፍፍል እስኪደረግ ድረስ፣ መራመድ ይጠበቅብሃል። ለዚህ ደግሞ እኛ የመሿለኪያ አባላት ከጎንህ ነን አይደል እንዴ? ሲል የስብስቡን አባላት እየዞረ ቃኘ። ሁሉም ልክ ነው!! በሚል ራሳቸውን በአዎንታ ነቀነቁ።

"ይገርማል!!ብሎ ጀመረ … ሳተናው፣ የሚነድ እንጨት ወደ ጉርዷ በርሜል እየጨመረ። … ይገርማል!!
ቅን መሆን በራሱ እርዳታ ነው። ለዛውም የረጂውን ጥቅም ሳይነካ ተረጂውን የሚጠቅም ብሎም ህይወቱን የሚቀይር ሀይል ያለው። ለዚህ ምርጥ ምሳሌ የሚሆነው የአባላችን ጄጃንና የእንጀራ ወንድሙ ነስሪ፣የህይወት ታሪክ ነው። ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚለው አባባል እውነትነቱ የጎላብኝ አሁን ነው። ለምን ቢባል ሰው መርዳት በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሃሳብም በቅናዊነትም። ስለዚህ ሰውን መርዳት ቀላልና፣ የሚያፀድቅ በጎ ተግባር ነው። ረጂ ለመሆን ከገንዘብና ሀሳብ በተጨማሪ ቅንነትም ያስችላል። ይህ ቅንነት በሀገራችን ቢስፋፋ፣ ፍትሃዊ ክፍፍል ቢነግስ ዛሬ የሚኖረንን ለውጥ፣ እስኪ በጄጃን ታሪክ መስላችሁ አስቡት እስኪ" ብሎ ፍልስፍናውን ቋጨ።

ጄጃን ለሙልጌ ሀሳብ እሺም እምቢም፣ የሚል ምላሽ አልሰጠም። የመሿለኪያ አባላት ወንድሞቹ የሚሰጡትን አስተያየት፣ በጥሞና አዳምጧል፣ የተናገሩትንም አንደሚተገብሩት ጠንቅቆ ያውቃል። ግን ምንም ሳይል ወደ ዝምተኛነቱ ባህር ጠለቀ።
ወገሬት!!

Sunday, January 8, 2017

"ምን አገባኝ እስኪ…!!"

#ሳteናw

… ሴት ልጅ በተፈጥሮዋ መደመጥ ትፈልጋለች፣ ለሚያዳምጣት ወንድ የትለየ ክብርና ፍቅር ትቸራለች። ራሷንና  ጓደኞቿን የሚያከብርላትን፣ የሚያምናትን ወንድ ቅድሚያ ትሰጠዋለች፣ ፍቅር ትሰጠዋለች ቪዋን ትጀብተዋለች፣ ይህንን ለማወቅ ሳይካትሪስት መሆን አይጠበቅብህም!! በርካታ የፍቅር ሰይኮሎጂ …
⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂

   ሁልጊዜ አንድ አይነት ከሆነው ውሎዬ ቡሃላ ወደቤት ለመሄድ፣ ታክሲ ውስጥ ተቀምጫለው። በመስኮቱ አሻግሬ አላፊ አግዳሚውን ቃኛለው። የጎዳላው ላይ ውክቢያ፣ ጩኸት የተለያዩ ነገሮች ትርምስ ህብረ ወከባ ይታይበታል። ወያላው ይጮሃል፣ የመኪና ው ሞተር፣ ይጮኻል፣ ውሻ ይጮሓል፣ ከየኤሌክትሮኒክስ ሱቆች የሚለቀቀው ሙዚቃ ይጮኻል። ህብረ ጫጫታው … አለ አይደል… የድምፆች አብስትራክት ሆኖ አንዱን ከሌላው ለመለየት የተለየ ትኩረት የሚጠይቅ አይነት ነገር…  የአካባቢው ምሽቱ ድባብ። ከዚህ ሁሉ ውክቢያ መሃል፣ የትኛውንም ወንድ የሚያማልል፣ … እንደ አሎሎ ማጅራቴ ላይ ለጥፌ በተሽከረከርኩ፣ የሚያሰኝ… አለ አይደል! በዘመኑ ቋንቋ የሚያሻ*ድ ግት ያሏት ቀበሮ (ልጅ) ድንገት አየው። በአይኔ ተከተልኳት።  የግቷን ባለቤት ቀናም ብዬ ፊቷን አየው ፣ እንደ ግቷ ባይሆንም ለክፋ የሚሰጥ አልነበረም። የጠይም ቆንጆ በዛ ላይ ልጅ እግር፣ የልጅነት ወዘናዋ በተክለ ቁመናዋ ላይ፣ የበለጠ ሳቢ እንድትሆን የራሱን ሚና ተጫውታል። አይኔ መላ ገፅታዋን ሲቀርፅ አይምሮዬ ውበታቷን አንድ በአንድ እየበታተነ በሰንጠረዥ ይሄ ከዚህ ፣ ያ ከዛ ይበልጣል እያለ የራሱን የንፅፅር መስመር ይሰራል። ልጅት ከአንድ ጎረምሳ ጋር ተገናኘች። ቆማ  ታወራው ጀመር። ቀርቤ የሚያወሩትን ባልሰማም፣ ሰላማዊ ያልሆነ ንግግር እንደያዙ ከእንቅስቃሴያቸው ተረዳው። እጁን እያወናጨፈ ያወራል። ምን ይሆን የሚያጨቃጭቃቸው? ቀርቤ ብሰማቸው በወደድኩ። እሱ ያወራል። መልስ ስትሰጠው ድምፁን እያጎላ ፍጥነቱን እየጨመረ እሱን ብቻ እንድትሰማው ያደርጋል።  ምላሿን አልሰማ ሲል… ዝም ብላ ሁለት እጆቻቿን የሚያማምሩ ግቶቿን አቅፋ (በመምህራን ቋንቋ እጇን በደረት አድርጋው) ግድ የለሽ በሆነ ልብ ትሰማው ጀመር። ጀለሴ ዝም ስትለው፣  ከልቧ የምታዳምጠው መስሎት… በሌላ ሞራል  እትትትትትትውን አቀለጠው፣ ደጋግማ ሰዓቷን አየች። አልገባውም እንጂ አረ ተፋታኝ በቃ!! እያለችው ነበር።  መጨረሻቸውን ለማወቅ ጓጓው።
ተሰናብታው እኔ ያለሁበት ታክሲ በር ላይ ልግባ አልግባ ስትል አመንትታ በመጨረሻም ገባችና ከፊቴ ካለው ወንበር ዘፍ ብላ ተቀመጠች። ስትቀመጥ ወንበሩን የኋሊት አንገራገጨችው፣ እንደ ግቷ ፍዴዋም ግብዳ ይሆን እንዴ? …ከመቀመጧ በረጅሙ ተነፈሰች። ምን ያህል ቢያቃጥላት ነው? እዛው ቆሟል እንድታየው ያያታል። … አለ አይደል እንደ መሳጭ ፍቅረኛ፣ እጇን እያውለበለበች… መዳፏን ስማ በሃሳባዊ ትዕይንት የከንፈሯን ቅርፅ እንደ ቢራቢሮ በትንፋሿ ገፍታ እንድትልክለት!! ምናምን ጠብቋል…

…  እሷ፣ ለአፍታ እንኳ ዞራ አላየችውም። ታክሲው እስኪንቀሳቀስ ልጁ በተስፋ እየጠበቀ አልተንቀሳቀሰም ነበር። እንደጨከነችበት ሲያውቅ ፊቱ ላይ የእልክ ስሜት ይነበብ ጀመር። ታክሲው ተንቀሳቀሰ። እኔንም እሷንም፣ ወያላውን፣ ሹፌሩን ተሳፋሪዎችን ጠቅልሎ የዋጠውን የታክሲዋ ሆድ፣ ከመንገድ መብራቱ ብርሃን… ተንቀሳቅሶ ለአፍታ ጨለማ ሲውጠው፣ እንዳየችው እንዳያያት ዞራ አየችው። አብሬያት ዞርኩ። ጀለስካ መሄድ ጀምሯል። ታክሲው ከቆመበት ጠርዝ ወደ ዋናው መንገድ ገብቶ ፍጥነት ሲጨምር … ተደላድላ ተቀመጠች። ከልጁ ስትርቅ ምቾቷ ይሰማታል ማለት ነው?። አንዳች ነገር አልጎመጎመችና፣ ሞባይሏን አውጥታ የተደዋወለችውን ቁጥሮች መሰረዝ ጀመረች። ይህ ድርጊቷ የልጁን የቁጥጥር ወሰን… ፣ ወይም አንድ ያለ ፍቃዷ ስልኳን የሚጎረጉርና ጫና የሚፈጥርባት ሰው መኖሩን አመላካች ይመስላል። ስልኳ እየነካካችው ሳለ ድንገት ጠራ። በንዴት ልትወረውረው ቃጣት። ልጁ መሆኑ ገባኝ። አነሳችው…  ሀሎ… ያልጨረሰውን ሃሳብ በስልኩ ይተገትግባት ገባ። እሺ እሺ እያለች መልስ ትሰጣለች። በመሃል "እንዴት የራሷ ጉዳይ ሴት ልጅ እኮ ነች!" የሚል ምላሽ ሰጠችው።" መጥፎ መልስ ሰጣት መሰለኝ፣ ምላሽ ነስታው ዝም ብላ መስማት ቀጠለች። "እየሰማውህ ነው ቀጥል።  ይሄ ከንቱ፣ ዝም ብሎ መለፍለፍ አይሰለቸውም እንዴ?  ለሷ እኔ ጨነቀኝ። አሳዘነችኝ። መውረጃዋ ደርሶ ከታክሲው  ስትወርድ፣ እንደቅድሙ በፍትወታዊ ሽ*ደት፣ ሳይሆን በወንድማዊ እዝነት፣ እያየው ሸኘኋት።

  … ሁኔታዋ ግን እኔው ጋር ቀረ። ጠቅለል ባለ መልኩ ስረዳት። ልጅት ልጁን ትወደዋለች፣ ታምነዋለች። በተቃራኒው እሱ ይወዳታል፣ ነገር ግን አያምናትም፣ ከአይኑ በራቀች ቁጥር፣ ወደ ሌላ የምትሄድበት ይመስለዋል። ከሚያውቀውና ከሚጠረጥረው ሰው ጋር እንደመጠርጠር…  አለ አይደል፣ ክላስ ይዘው ከንፈር ለከንፈር ስትሳሳም፣ መርፌና ክር ስትሆን፣ ያ ፋራ እያለች፣ ስታማው፣ስትሳሳቅ ምናምን አይነ ህሊናው የራሱን ጥርጣሬውንና በገሃድ ያያቸውን ትዕይንቶች እንደ አኬልዳማ፣ ጂሃዳዊ… ምናምን …  አቀናብሮ የሚያስከልመው ይመስለኛል። በዚህም ይመስላል እልክ ተያይዟታል፣ እንድን ነገር የሚያሳምናትውይይት ሳይሆን በጩኸት እንደሆነ፣ በአይኔ በብረቱ ያረጋገጥኩትነገር ነው። በዛ ላይ የራሱን ጎን እንጂ የሳን ጎን የመስማት አባዜ አይታይበትም።

  ሴት ልጅ በተፈጥሮዋ መደመጥ ትፈልጋለች፣ ለሚያዳምጣት ወንድ የትለየ ክብርና ፍቅር ትቸራለች። ራሷንና  ጓደኞቿን የሚያከብርላትን፣ የሚያምናትን ወንድ ቅድሚያ ትሰጠዋለች፣ ፍቅር ትሰጠዋለች ቪዋን ትጀብተዋለች፣ ይህንን ለማወቅ ሳይካትሪስት መሆን አይጠበቅብህም!! የፍቅር ሰይኮሎጂ መፅሀፍትን ገለጥ ገለጥለጥ ማድረግ በቂ ነው… እናም ሄዋኖች ከአዳሞች የሚሹትን ነገር፣ ይህ ልጅ አልተገበረም። አያምናትም፣ አያዳምጣትም፣ለጓደኞቿም ሆነ ለሷ አክብሮት የለውም። እነዚህ ሁኔታዎችን ካላስተካከለ በአጭር ግዜ ውስጥ ፍቅራቸው አደጋ ላይ …

እንዴዴዴዴ …ቆይ… ቆይ… ቆይ… የኔ ጥብቅናና በማያገባኝ መፈተል አልገረመህም?ምን አገባኝ እስኪ?
ወገሬት!!

" የ ሀ ገ ር ፍ ቅ ር "

#ሳteናw

    ሁሉም ወጣት እንደተለመደው በመሿለኪያዋ ተሰብስቧል። ከሬዲዮኑ … የቴዲ አፍሮ ላምባዲና እየተስረቀረቀ የመሿለኪያን ድባብ ተቆጣጥሯል። አባላት በሞላየቴዲን ዜማ በሃሳብ ተውጦ ይሰማል። በተለይ … አንዱ!! በየስንኙ መሃል በአይነ ህሊናው ግጥሙን ከህይወቱ ጋር  የሚገናኘውን ነጥብ  ያምሰለስላል።

አይኖቼ አያዩ ብርሃን የላቸው፣
በልጅነቴ ድሮ አጥቻቸው።

… በልጅነቱ ያጣቸው አሳዳጊ አያቱ: አይኑ ላይ ድቅን አሉበት። አያቱ አይኖቹ ነበሩ።  እንዴት በፍቅር እንዳሳደጉት ርህራሄ እንክብክባያቸው አንድ በአንድ ታወሰው። እንዳይኑ ብሌን የሚያያቸው አያቱን ካጣ ቡሃላ ያሳለፈው ፍቅር አልባ ህይወት፣ ያጣቸው ነገሮች፣ በብቸኝነት ከሰው ሳይስማማ ያሳለፈው ፣ የመኖር ትርጉሙ ከህይወቱ  ውስጥ ሊያገኝበት ያልቻለበት ጊዤ፣ በአንድ በአንድ ድቅን… ሲልበት… ግድ የለሽ ህይወቱ በአንድ ሰው ሳቢያ መስተካከሉ። ከአያቱ ያጣው የፍቅር ክፍተት መሙላቱ የሚኖርለት የሚሞትለት ሰው ማግኘቱ፣ የመኖር ጉጉቱን እንደጨመረው። ለካ ሰው  ፍቅርን ካጣ ኖረ ሞተ ጉዳዩ አይደለም? የሰውን ልጅ ለመኖር ተስፋና ገጉት የሚፈጥርለት ፍቅርና ተስፋ ሆኗል። እያለ ሲያውጠነጥን።

… ሰያ ነጭ ሽንኩርት
"ሀገር ማለት ህዝብም ጭምር ነው።" ሲል ድንገት የተናገረው ቃል ከአሳቡ አባነነው።

"ማለት?" አንድ አባል ጠየቀ።

ሰያ ቀጠለ "ዛሬ እያንዳንዳችን  ለሀገራችን ያለን የፍቅር ወይም የግድየለሽ ስሜት ዝም ብሎ በድንገት የተፈጠረ አይደለም አንድ አመክኒዮ አለ።"

… ልክ ነህ በሚል ጭንቅላቱን  ነቀነቀ ሳተናው። በአንድ በኩል በውስጡ የሚያምሰለስለው ነገር በመነሳቱ በግጥምጥሞሹ እየተገረመ።

" እንዴት?" ሲል ሀሳቡን እንዲያብራራ  ቡፌት ሌላው አባል ጥያቄውን ሰነዘረ።

ሰያ ጎሮሮውን ጠረገና።
"…  ዛሬ ሃገራችን የመውደድ ወይም የመጥላት ስሜት ጀርባ፣ እያንዳንድሽ በህይወትሽ ላይ የተፈጠረ እውነታ አለ…
"ጀለሴ በትርፍ ሰዓትህ መፈላሰፍ ጀመርክ እንዴ? " ብሉ ሃሳቡን አቋረጠበት ጃንደረባው (ፂም አልባ ፊቱ ሁሌም ህፃን ያስመስለዋል)።

"ቆይ ዝም በል እስኪ!" አለው ቡፌት የሰያ ማብራሪያ እንዲቋረጥ ስላልፈለገ።
… ሰያ ጃንደረባው ያቋረጠበትን ሀሳብ ቀጠለ…

"… አዎ ለዛሬው ለሀገር ፍቅር ያለን ስሜት ከየትም የመነጨ አይደለም። ከህይወታችን እንጂ። እንደውም በራሴ ህይወት ምሳሌ ልስጣችሁ … እኔ ለሃገር ፍቅር በልቤ ውስጥ ያለው ቦታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምንም ነበር ማለት ይቻላል።

"እንዴት?"

"እንዴት ማለት ጥሩ! ይህ ለሃገሬ የሞተ ስሜት ለምን ሊፈጠር እንደቻለ የአስተዳደግ ሁኔታዬ ይመልሰዋል።

… እናቴ እኔን ስትወልድ ነበር የሞተችው። በማህበረሰቤ ዘንድ እናቱን ያጣ አሳዛኝ ሚስኪን ሳይሆን ገደቢስ፣ ገፊ እባል ነበር። ከዚህ ማህበረሰቤ ያተረፍኩት እናቱን እንዳጣ ህፃን እዝነት፣እንክብካቤን  ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን ሆነ። ታዲያ ፍቅር ላልሰጠኝ ማህበረሰብ ከየት አምጥቼ ነው ፍቅር ልሰጠው የምችለው።ቤታችን የሚቀጠሩ ሴቶች፣ ልብሴ ላይ አምልጦኝ ሽንቴን በሸናው ቁጥር እየቆነጠጡኝ እየደበደቡኝ አድጌ፣ እንዴት ነው ለሴት ልጅ ክብርና ፍቅር የሚኖረኝ። በሙያው ለማህበረሰቡ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው ወላጅ አባቴ ፣ለኔ ቁብ ሰጥቶት አላሳደገኝም። ሌላው ይቅር አቅፎ ስሞኝ አያውቅም። ፍቅር ሰጥቶ ላላሳደገ አባት ፍቅር መስጠት መቻል ዘበት ነው… አያችሁ ለዚህ ነው። ለሃገራችን ያለን የፍቅር ስሜት ያለምክኒያት አይፈጠርም ያልኩት።

"ታዲያ የግለሰቦች ጥላቻ እንዴ ሀገርን ለመጥላት መንስኤ ይሆናል?"

በጣም ጥሩ!! አለ ሰያ…  ሀገር ማለት ህዝብ ነው ብለናል። ያለ ህዝብ ሜዳው ጋራው፣ ሸንተሩሩ ወንዙ፣ ቁልቁለት ዳገቱ ደን እንጂ ሌላ አይደለም። ስለዚህ ሀገር ማለት ህዝብም ጭምር ነው። ህዝብ ደግሞ የግለሰብ፣ የቤተሰብ፣ የማህበረሰብ ስብጥር ነው። አለቀ፣ ከቤተሰብ ከማህበረሰብህ ጥላቻን ከተቀበልክ፣ ምላሽህ ጥላቻ ነው። ሀገርን ለመጥላት ከዚህ የበለጠ ምክኒያት ያስፈልጋል?" ሲል ወደ ሁሉም ተገላመጠ። በስሜት ያወራ ስለነበር መርፌ ቢወድቅ እንኳ በሚሰማ ሁኔታ ነበር በመሻለኪያ ፀጥታ የሰፈነው። ከሰመጠበት የስሜት ንግግር፣ ወጥቶ የፈገግታ ብልጭታ እያሳየ ቀጠለ…

"…  በህይወት ዑደት ካልጠበከው አካል የምታገኘው ፍቅር፣ ለሃገር ፍቅር እንዲኖር ያደርጋል። ለኔም ይህቺ መሿለኪያ ውስጥ ከእናንተ ዘር፣ ጎሳ፣ ብሄር፣ እምነት የማይለየው ፍቅር ፣ ለሃገሬ ፍቅር እንዲያድርብኝ አድርጎኛል። በህይወት ለመኖር ብሎም ለሃገሬ አንድ ነገር ለመስራት ከፍተኛ ጉጉት ፈጥሮብኛል። አየህ ለሃገርህ ፍቅር እንዲኖርህ ከቤተሰብ፣ ከማህበረሰብ ልዩነት አልባ ፍቅር መተሳሰብና መዋደድ መሰረት ይሆናል። ዛሬ የወጣቱን የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ለመመለስ ለሀገር ለወገኑ በዘርፉ አንዳች ነገር እንዲፈጥር ጉጉት እንዲያድርበት፣ ፍቅር ማስተማር ያስፈልጋል።

ሰያ ይህን ከህይወቱ ጋር የተቆራኘውን እውነታ ሲተነትን። የመሿለኪያ የወጣት ስብስብ አባላት ደስታቸው ወሰን አጣ። የባለታሪኩን አባል ለሃገር ያለው አመለካከት አቅጣጫውን በፍቅር ለመቀየር ሰበብ መሆናቸው ስብስባቸውን ለማዝለቅ አስተሳሰባቸውንም ከመሿለኪያ ውጪ ለማስፋት ምኞት አደረባቸው። ሁሉም እየተነሱ ሰያን በስሜት አቀፉት።…

ወገሬት!

ሚንጊ ነኝ

#ሳteናw

በሐመር ብሄረሰብ ላም፣ በግ ወዘተ … ጥርስ ማብቀል የሚጀምሩት በታችኛው ድዳቸው ስለሆነ ቅዱስ ይባላሉ። አህያ ፈረስ፣ ጅብ በላይኛው ድዳቸው ስለሚያበቅሉ ርኩስ ይባላሉ። የሰው ልጅም የወተት ጥርሱን በታችኛው ማብቀል ሲገባው እንደ እርኩሳኑ በላይኛው ያበቀለ እንደሆነ ለማህበረሰቡ አይበጅም፣ ቢያድግም አባቱን የሚጋፋ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህም ገፊ(በአካባቢው አጠራር ሚንጊ ተብሎ) ይጣላል። ከዚህም በተጨማሪ ጥርስ እንደማብቀሉ ሁሉ መውለቁም ካይ ችግር አለበት። በላይኛው የበቀለው ድዱ አሁንም ቀድሞ ከወለቀ ሚንጊ ተብሎ ይጣላል። የዚህ እምነት ሰለባ ከሆኑ የሐመር ተወላጆች አንዱ እኔ ነኝ።

ከሎ ሆራ እባላለው። የተወለድኩት ሐመሮች በብዛት ከሚገኙበት ቡስካ ተራራ ስር ነው። በሕፃንነቴ እናቴ በምትለብሰው ቆዳ ሸፈን አድርጋኝ ከሰውነቷ ጋር ለጥፋኝ ስቅስቅ ብላ ታለቅስና በሻካራ ቅጠል የታችኛው ጥርሴን ትሞርድልኝ ነበር።

ጥርሴ የበቀለው መጀመሪያ በታችኛው ቀጥሎ በላይኛው ድዴ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ጥጃ ለመመለስ ስሮጥ ወድቄ የላይኛው አንድ ጥርሴ ወለቀ፣ ሌላኛው ደግሞ ተሸረፈ። እንዳበቃቀሉ ሁሉ በታችኛው ድዴ የበቀለው ጥርሴ መውለቅ ሲገባው፣ የላይኛው ቀድሞ በመውለቁ ለአደጋ ተጋለጥኩ። እናቴ ጥርሴን ትሞርድልኝ የነበረው የታችኛው ቀድሞ የወለቀ ለማስመሰል ነበር።

ጥረቷ ሁሉ ከንቱ ነበር። ወድቄ ሳለቅስ ያዩኝ ሰዎች ቀድመው ለሽማግሌዎች ነግረው ስለነበር፣ አንድ ቀን አባቴ! በሌለበት "ሚንጊ" የተባሉ ልጆችን የሚጥሉ ሽማግሌዎች ወደኛ ጎጆ መጡ። እናቴ በርቀት እንዳየቻቸው ተንቀጠቀጠች፣ እንቦሳዋን እንደምትልስ ላም ሰውነቴን ደጋግማ እየሳመች ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ሽማግሌዎች "ጥርሱን አስነቅለነው እንምጣው" ብለው ከእቅፏ መነጨቁኝ። ብትቃወም ባህል ገርሳሽ ተብላ የከፋ መከራ ስለሚደርስባት አልተከላከለችም። እንደዘበት ገፋ አድርጋ አስረከበችኝ። እሪታዬን አቀለጥኩት የደረሰልኝ ግን ማንም አልነበረም።

ሽማግሌዎቹ ራቅ ወዳለ ስፍራ ወሰዱኝ። ቁጥቋጦ የበዛበት የተራራ ጫፍ ስንደርስ ወደነሱ ሳልዞር ከፊት ለፊታቸው የተራራው ጫፍ ለይ እንድቆም አዘዙኝ። አላስችል ብሎኝ ድንገት ዞር ስል፣ አንደኛው ሽማግሌ የወረወረው ጦር ትከሻዬ ላይ ተቀበቀበ። ወዲያው ገፈታትረው ወደ ገደሉ ጨመሩኝ። ከተራራው አናት የወረወሯቸው ትንንሽ ናዳዎች ፈነካከቱኝ። የደም አበላ ዋጠኝ። እነሱም ሞቷል ብለው ትተውኝ ሄዱ። እዛ ስጓጉር አድሬ በነጋታው ረፋድ ላይ ድምፄን የሰሙ መንገደኞች አግኝተው ወደ ቤታቸው ወስደው ከሞት አተረፉኝ። ለትንሽ ጊዜ ከነሱ ጋር ከሰነባበትኩ ቡኋላ፣የመንግስት ሰራተኞች ስለነበሩ ወደ ጂንካ ከተማ ሲዘዋወሩ አብሬ ሄድኩ። እዚያም ትምህርት ቤት አስገቡኝና ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። ከወላጆቼና ከአካባቢዬ በተለየው በአስራ ሶስት አመቴ የመሰረተ ትምህርት ዘማች ሆኜ ወደ ቀዬዬ ዘመትኩ። እዚያ እንደደረስኩ አንጋፋዎቹ አወቁኝ። አባቴ ቢሞትም እናቴንና ሌሎች ዘመዶቼን በሰላም አገኘኋቸው። ገፈታትረው ገደል የከተቱኝን ሽማግሌዎች ሳያቸው ቂም ያረገዘው ልቤ ሊበቀላቸው ቋመጠ። ዳሩ ግን ባሀረሉ እንጂ ሰዎቹ ተፈጥሮአዊ ጭካኔ እንደሌላቸው በትምህርት የተገራው በሳሉ አእምሮዬ ሹክ አለኝ። እኔም ፊደል ከማስቆጠር ጎን ለጎን ይህንንና ሌሎች ጎጂ ልማዶችን ማህበረሰቡ እንዲዋጉ ለማድረግ ቆርጨ ተነሳው።
☞ ከቡስካው በስተጀርባ የተቀነጨበ = በፍቅረማርቆስ ደስታ፣ 1987
ወገሬት!!