Thursday, January 12, 2017

"ም ር መ ራ"

"ምርመራ"
#ሳteናw

…የተናፈሰውን አሉባልታ በሰማ ቅፅበት ሙዱ ተቦክሞበታል። የወደፊት ምኞትና ተስፋው፣ በአንዴ ጨለማ ሲለብስ ይታየዋል። ወይኔ ጉዴ!! ይላል አስሬ በሆዱ። ይኼን እንዴት እስከዛሬ ሳልገምት ቀረው? ለነገሩ ቀድሜ ባውቅስ ምን አዲስ ነገር ይኖራል? የስቃይ ዘመን ከማራዘም በቀር? እያለ ያሰላስላል። ወሬውን ውጪ ቢሰማውም፣ አሁን መሿለኪያ ውስጥ ተቀምጧል። መሿለኪያዎች የሚያወሩትን የወሬ ግንጣዮች ይሰማል እንጂ አያዳምጥም። አካሉ መሿለኪያ፣ ልቡ ሌላ ቦታ።

እንደዛሬ ሳይለያዩ፣ የረገጥከውን፣ የረገጥሺውን፣ አልረግጥም ሳይባባሉ በፊት ያሳለፉትን  ጊዜያቶች አንድ በአንድ ያወጣ ያወርድ ጀመር። "መንስኤው እኔ ነኝ ወይስ እሷ?"፣ ደውሎ አሉ ባልታውን እንዳይጠይቃት፣ አይንህ ላፈር፣ አይንሽ ላፈር፣ ተባብለዋልና ምን ያድርግ ። ከሷ ውጪ አያውቅም። ጨንቆታል፣ ጠቦታል። በፍርሃት ብዛት ሆዱ ተንቦጫቦጨ። ደህና የነበረው ልጅ አስሬ አተት እንደያዘው ሰው ሽንት ቤት አበዛ። ቆመ፣ ተቀመጠ፣ ተንቆራጠጠ። ይህ ለራሱ ባይታቀውም፣ ለመሿለኪያዊያን ግልፅ ነበር። ሁኔታው አዲስ የሆነበት ሰያ ነጭ ሽንኩር "ጓድ!ምን ሆነሃል?" ሲል ጠየቀው።
እውነቱን ነግሯቸው ስጋቱ ስጋታቸው እንዲሆን፣ አልፈለገም። ሳያረጋግጥ፣ ማውራቱን አልወደደም። ቢነግራቸው አሁኑኑ ማወቅ አለብህ በሚል በመሿለኪያዊያን ውሳኔያቸው አንጠልጥለው፣…  እንደሚወስዱት፣ አላጣውም።

"ምንም ብዙ ውሃ ስለጠጣው ነው መሰለኝ ውሃ ሽንት ቶሎ ቶሎ ይመጣብኛል" አለ ሌላ ጥያቄ እንዳያስከትሉበት… በመስጋት።

። ቤቱ ከመግባቱ በፊት፣ አሉ ባልታው እውነት ይሁን ውሸት ማረጋገጥ መቻል እንዳለበት ያውጠነጥናል ፣…  አለበለዚያማ ልተኛ አይደለም። በሀሳብ ስንገላታ እንዲሁ ማደሬ ነው" ሲል ዛሬውኑ ማወቅ እንዳለበት ወስኗል። ሌላ ቀን ያጥርበት የነበረው  የመሿለኪያ የቆይታ ሰዓት፣ ዛሬ አልሄድልህ ብሎታል ወይ አምላኬ! ግን እንዴት? ባለፈው ታዲያ ስጠይቃት፣ ምላሿ እንደዛሬው አሉባልታ ለምን አልሆነም? እያታለለችኝ ነበር ማለት ነው?  ወይስ እየተበቀለችኝ?" ይላል ለራሱ።
ለወትሮው በቃንቄ ምላሱ መሿለኪያን ይቆጣጠር የነበረ ልጅ ዛሬ በጥልቅ ዝምታ ውስጥ መሆኑ ለመሿለኪያዊያን አዲስ ነገር ሆኖባቸዋል።

"አረ!!…ፍሬንዴ ዛሬ ምላስህ ላይ ነው እንዴ የተቀመጥከው??" ከቡፌት ነቆራ አላመለጠም። ምላሹ ከልቡ ያልሆነ ፈገግታ ማሳየት ነበር።

ከዚህ ሁሉ ለምን ቶሎ ሄጄ፣ እውነቱን አላረጋግጥም? ያበጠው ይፈንዳ!!" ብሎ ያለ ሰዓቱ መሿለኪያን ለቆ ወጣ። በመንገድ ላይና፣በታክሲ ውስጥ ያሳለፈውን ጊዜ ሳያስተውል ከሰፈሩ ደረሰ። በአቅራቢያው ካለ መካከለኛ ክሊኒክ ገባ።

ወጣት የጤና ባለሙያ በፈገግታ ተቀበለው።
"ምን ነበር?"
"… ምርመራ ለማድረግ ነበር። አለ ድንጋጤ ባርገበገበው ድምፅ።
"ሰባ ብር ነው"።
"ችግር  የለም!! ስንት ደቂቃ ይፈጃል ግን?" ያሰጋው ዋጋው ሳይሆን፣ ጊዜው ነበር።
"ከአስራ አምስት አስከ ሃያ ደቂቃ ቢወስድ ነው!! ሲለው በጭንቅላቱ ንቅናቄ መስማማቱን፣ ሲገልፅለት… እሺ አንዴ ጠብቀኝ ብሎት ወደ ሌላ ክፍል ሄደ ። እሱም ወደ እንግዳ ማረፊያው፣ ገባና ተቀመጦ ጠብቀው። ወጣቱ መርማሪ …ጓንት፣ መርፌ፣ የአልኮል ብልቃጥ፣ ጥጥ እና የደም ናሙና መመርመሪያ (ኪት) በእጁ አንጠልጥሎ፣ ተከተለኝ በማለት ወደምርመራ ክፍል ይዞት ገባ።  እውነቱን ለማወቅ በቀረበ ቁጥር የልብ ምቱ እጥፍ ሆኗል።

ከምርመራው ክፍል ገብቶ እንደተቀመጠ  የሸሚዙን እጅጌ ክርኑ ድረስ ሰብስቦ ተዘጋጀ። ካሁን አሁን መጅ የሚያክል መርፌ ሲጠብቅ… መርማሪው… ጓንት፣  አልኮል በራሰ ጥጥ፣ የቀለበት ጣቱን፣ አሽቶ አፀዳለትና፣ በትንሽዬ ስለታማ ነገር ጠቅ፣ አደረገው ወገው ፣ደም ከየት ይምጣ? … ይቅርታ በአይኑ ጠይቆት ጠቅ ደገመው፣ ጣቱንን አልመዝምዞ አልመዝምዞ፣ በስንት ምጥ የደም ጠብታ፣መመርመሪያዋ ላይ አደረገው። እሱ ደግሞ የተበሳችው ጣቱን በጥጡ ይዞ… ባለሙያውን በአይኑ ይከታተል፣ ጀመር…

በብልቃጥ ያለ ፈሳሽ  የደም ጠብታው ላይ ጠብ አድርጎ፣ ውጪ እንዲጠብቀው ነገረው። ወጣ። ወና የሆነው እንግዳ ማረፊያ፣ ቴሌቪዥኑ ብቻ ይጮህበታል። ተቀመጦ ውጤቱን ይጠባበቅ ጀመር።
የምርመራ ክፍል ውስጥ የተመለከታት የመመርመሪያ መሳሪያ ትንሽነትና፣ ቅለት፣ በትክክል መስራቷ አጠራጥሮታል። ይሁን እንጂ መሳሪያዋ፣ ዓለም አቀፉን ዝቅተኛ መስፈርት አያሟላም ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የኤች.አይ.ቪ /ኤድስ/ መመርመሪያ ኪት በብቃት አገልግሎት መስጠት እንደሚችል በተደረገለት የጥራት ፍተሻ ተረጋግጧል።

ባሙያውም ውጤቱን ለማወቅ ጥቂት ደቂቃ  መጠበቅ ስለነበረበት፣ እንግዳ ማረፊያው መጥቶ አብሮት ተቀመጠ።
… ምክር ምናምን የሚጀነጅነው መስሎት፣ ፊቱን ዘፈዘፈው ፣እትት ሳይባል ውጤቱን ተነግሮት ብቻ ነው፣ መሄድ የፈለገው። ፍላጎቱ ተሳካለት። ባለሙያው ምንም አላለውም።(መርቅኖ ይሆን?)… አይኑን አንዴ ቲቪ ላይ፣ አንድ ጊዜ ግድግዳው ላይ የተለጠፉ ምስሎች ላይ ማንከራተቱ ሲሰለቸው፣ ተንቀሳቃሽ ስልኩን አውጥቶ መነካካት ያዘ። ማህበራዊ ድህረገፅ ከፍቶ ማየቱ  ሃሳቡን በደንብ ሰበሰበለት። የጭንቀት ሰዓቱንም አሳጠረለት። ስንት ደቂቃ እንደሆነ ሳያስተውል፣ አጠገቡ የነበረው ባለሙያም ወደ ምርመራ ክፍል መግባቱንም ልብ አላለም። ከነበረበት ተመስጦ፣ ድምፅ አባነነው። ከሞባይል ስክሪኑ ላይ ቀና አለ። ወጣቱ መርማሪ የምርመራው ክፍል በር ላይ ቆሞ …  ውጤቱን እየነገረው ነበር።
" ምን አልኸኝኝ?"
" ነፃ ነህ!"
እንዴት በደስታ ተስፈንጥሮ እንደተሳና፣… እንደረሰ ሳያውቅ፣ ራሱን ከቤቱ ውስጥ አገኘው።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment