Wednesday, January 11, 2017

"ቅንነትም እርዳታ ነው"


#ሳteናw

… ቅን መሆን በራሱ እርዳታ ነው። ለዛውም የረጂውን ጥቅም ሳይነካ ተረጂውን የሚጠቅም ብሎም ህይወቱን የሚቀይር ሀይል ያለው። ለዚህ ምርጥ ምሳሌ የሚሆነው የአባላችን ጄጃንና የእንጀራ ወንድሙ ነስሪ፣የህይወት ታሪክ ነው…
⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂⚂

  እንደተለመደው የመሿለኪያዋ ወጣቶች ከስራ ውሏቸው ቡሃላ ምሽቱን በመሿለኪያቸው ተሰባስበዋል። የሰሞኑ ውርጭ የፈጠረው ቅዝቃዜ በጉርድ በርሜል እንጨት ለማንደድ አስገድዷቸዋል። ይህ የአየር ንብረት( ምን የአየር ንብረት! የአየር ክስረት ነው እንጂ) … መሿለኪያን ወደ ፍሪጅነት ለውጦት፣ አባላቱን  በሞላ  ከቤቱ  ጋቢና ክንብንብ አምጥቶ ለማስለበስ ምንም አልቀረውም።  … ሙቀቱን ፍለጋ በበርሜሏ ዙሪያ … መሸጋሸጋቸው፣ አፍ ለአፍ ገጥመው ሚንሾካሸኩ የከንፈር ወዳጆች አስመስሏቸዋል። የሚንቦገቦገውን እሳት ከበው ሁሉም በርጫ እየበረጩ ነው፣ አጫሹም ፋታ እየሰጠ ያጨሳል። አንድ የጋራ መወያያ ርዕስ ካልተነሳ … አንዱ ከአንዱ ጋር መወያየት የተለመደ ነው። ቡፌት ስለ ሰሞኑ የአየር ፀባይ፣ ሳተናው: ከጄጃን ጋር፣ ሌላው ስለሌላ የተለያዩ አጀንዳዎች ወሬው ጥንድ ጥንድ ሆኖ አፍክቶቷል።

  እኔ ምለው ሲል ጀመረ ቡፌት" እኔ ምለው የሰሞኑ አየር ፀባይ!!…  ቆይ ምንሼነው? አለ አይደል፣ መላ ቅጡ እንደጠፋ፣ ይህ ነው ለማለት የቸገረ አይነት ሆነ እኮ። ፀሀዩ እንደ ክፉ ሰው ምላስ አቃጠለኝ ብለህ ጥላህን ስትይዝ…  ቀዝቃዛነት ያዘለ ንፋስ… ወላ ውርጭ በለው!! ወዛም የነበርከውን ሰው በአንዴ እንደ ሽሮ እቃ  አመዳም አድርጎ ቁጭ ይላል። በተለይ በሌሊት ምትነሳ ከሆነ…  አይጣል ነው። እንደውም መቼ ለት እንደ ልማዴ በሌሊት ስነሳ፣ ለወትሮው የሚቀበለኝ የወፎች ድምፅ ደብዛው ጠፍቶ ሳይለንት ላይ አክቲቬት ሆኗል። እንዴት ነው ነገሩ ብዬ የመኝታ ክፍሌን መስኮት ገልጬ አዕዋፋቱን ስሾፈትርልህ፣ አዕዋፋቱ ብርዱ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ መንቁራቸውን እያንቀጫቀጩ …  ቫይብሬት ላይ ሆነዋል።" የአባላት ሳቅ አጀበው። ሳተናው ሀሳቡን ከሳበው የቡፌት ቀልድ፣ ከጄጃን  ጋር ወደ ጀመረው ጨዋታ ዞረ።

"ቆይ ይኸውልህ ጄጃን! ስለ አንተና ወንድምህ ነስሪ ከስር መሰረቱ አስረዳኝ እስኪ?"

"አለ አይደል እንዴት ላስረዳህ! አለ በዝምተኛነቱ የሚታወቀው ጄጃን።
የቤተሰባችንን ሁኔታ በቀላሉ ለማስረዳት ከባድና፣ ውስብስብ በመሆኑ ያስቸግራል። አለ አይደል ጊዜና ጆሮ ሰጥተህ ካደመጥከኝ ልነግርህ ፍቃደኛ ነኝ አለ።"

"እባክህ ዝም ብለህ ንገረኝ!"ሲል ሳተናው ፣ ሁሉም አባል ጆሮውን ለጄጃን ሰጠ።

" የእናቴ እናት፣ ከእናቴ አባት ጋር ባለመስማማት ከተፋታች ቡሃላ፣ እንደሷ አግብቶ የፈታ ሰው አገኘችና ከተማ ውስጥ ትዳር መሰረቱ። ይህ ባሏ ከቀድሞ ሚስቱ የወለዳቸው ልጆች ነበሩትና፣ እነሱን በእንክብካቤ ታሳድግ ጀመር። ልጇ ማለትም እናቴ ኑሮዋ ገጠር ነበር። አያቴ ና ባለቤቷ ፍቅር ነበራቸው። አያቴ የባሏን ልጆች በእንክብካቤ ስታሳድግ፣ የአብራኳን ክፋይ እናቴ  ግን ገጠር ኖረች። አያቴና ባሏ በዚህ ትዳራቸው ንብረት አፈሩ። በአንፃሩ እናቴም ተድራ ልጆች ወለደች። ከእነሱም ውስጥ እኔ በከተማው አያቴ ቤት ማደግ ጀመርኩ። ከአያቴ ባለቤት ልጆች ጋር እንደ ወንድምና እህት በሆነ ስሜት። ሞት የተባለው የተፈጥሮ ህግ ከአያቴ ባለቤት፣ ጀመረ፣ ቀጠለ የሱን ልጆች አንዱ ነስሪ እስኪቀር ወደ ማይቀረው አለም ሄዱ(መቼም መልካም ሰዎች አይበረክቱም)፣ በመጨረሻም፣አያቴን ወሰደ።  በወቅቱ እኔ የአሰራሥድስት አመት ልጅ ነበርሁ። የአያቴ የእንጀራ ልጅ ነስሪ ደግሞ ትዳር መስርቶ ኑሮው በሌላ ስፍራ ነበር። አያቴ ስትሞት በጊዜው በቤቱ እኔ ብቻ ቀረው። የህይወቴ ሁለተኛም ምዕራፍ ከዚህ ጀመረ። አያቴ ከሞተች ቡሃላ በመርካቶው ቤት እኔ ብቻ መኖሬን የታዘበ ጎረቤት ቀበሌ ሄዶ<<ለጄጃን ተመጣጣኝ ቤት ይሰጠው ይሄን ለኔ ስጡኝ>> ሲል አመለከተ። ቀበሌ ከሚሰራ ሰው ጥቆማው የደረሰው ነስሪ ጓዙን ጠቅልሎ መርካቶ ቤት ገብቶ አብረን መኖር ጀመርን። ከዛ ቡሃላ ወንድሜ ነስሪ ለኔ ሁለት አይነት ሰው ሆነ። ከህፃንነት እስከ ጉርምስናዬ ያለው ነስሪና ከዛ ቡሃላ ያለው ነስሪ ። በጨቅላነት ዘመኔ ማንም ታላቅ ለታናሹ እንደሚሳሳው የሚሳሳልኝ የሚያዝንልኝ የሚንከባከበኝ ሲሆን። ከአያቴ ህልፈት ቡሓላ ማለትም ከሱ ጋር መኖር ከጀመርኩበት ማግስት ሌላ የማላውቀው ነስሪ ሆነብኝ። እንደ ልጅነቴ የነስሪን ፍቅር አጣው። በፊት የሚጫወት የሚያቃልደኝ የሚመክረኝ ነስሪ ባላወኩት ምክኒያት መሰረታዊ ፍላጎቶቼ በርሱ እጅ በሆነ በጥቂት ጊዜ  ውስጥ በበነነ ተነነው የሚቆጣ ቁጥጥር የሚያበዛ … የሚነጫነጭ ሆነ።

  ነስሪ በልጅነቴ አይቆጣኝም ነበር ማለቴ አይደለም። ይቆጣኛል። በልጅነቴ  ቁጣው ውስጥ የወንድማዊነት፣ የአዘኔታ፣ እና ለራሴው ጥቅም የሆነ መንፈስ ይታየኝ ነበረ። ከአያቴ ሞትና ከጉርምስናዬ ቡሃላ ግን ነስሪ ሳጠፋ የሚቆጣኝ ቁጣ አስጠንቃቂና አስፈራሪ፣ አስበርጋጊ እየሆኑ መጡ። <<የምትኖር ከሆነ ስርዓትህን ይዘህ ኑር!>> የሚል።  ሰሞኑን ከፍቶት ነው ብዬ ምክኒያት በራሴ ሰጠሁት። አስፈራሪና አስጠንቃቂው ቁጣ ተደጋገመ ነገሩ ባሳለፍነው ህይወት ተከስቶ የማያውቅ ስለነበር በጣም ግር አለኝ። ለሱ ግን የታወቀው አይመስለኝም። የዛን ሰሞን የቀበሌ መታወቂያ ፈርመህ አውጣልኝ አልኩት።"ምን ሊያደርግልህ ነው?" ብሎ ከጠበኩት በላይ ተቆጣ ግራ ገባኝ! ቁጣው የቤቱን ስም በኔ አዙርልኝ ያልኩት እስኪመስለኝ ድረስ በረታ። መታወቂያ ካርድ ምን ሊያደርግልህ ነው ይባላል እንዴ? ወቅቱ የ97 ምርጫ ካርድ የሚታደልበት ስለነበር ካርድ ለማውጣት ስል ብቻ ቁጣውን ተቋቋምኩት። በዚሁ ስሜት ቀበሌ ሄዶ ፈረመልኝና የመታወቂያ ካርድ ተቀበልኩ። ምን ሊያደርግልህ ነው ብሎ የተቆጣኝ ግን ብዙ ነገር እንድፈላፈል አደረገኝ። የድሮው ነስሪ ናፈቀኝ። ጭራሽ ግራ ቢገባኝ ነስሪ እንዲህ የተለወጠብኝ በምን ይሆን? ስል ግልፅ መልስ ያጣሁበት መብሰልሰል ላይ ጣለኝ።

  ከዛም ቡሃላ አንድ ነገር ሳጠፋ የነስሪ ቁጣ <<የምትኖር ከሆነ ስርዓትህን ይዘህ ኑር!>> የሚል ቃላት የበዛበት ሆነ። በዚህ ቁጣ ውስጥ አርፈህ መኖር ማትችል ከሆነ ቤቱን ለቀህ ውጣ የሚል ትርጉም እንደሚሰጠኝ ማስታወስ አይጠበቅብኝም። በወቅቱ ተማሪ ነኝ… ከነስሪ ጋር በመኖር ሂደት ውስጥ ስንኖር ከዛሬ ነገ ያባርረኛል የሚል ስጋት ያድርብኝ ጀመር። ይህ የስነልቦና ጫና እየቦረቅኩ እየዘለልኩ ባደኩበት ቤት ውስጥ  በነፃነት የመንቀሳቀስ ሞራሌን አጠፋው። እራሴን እንደባዳና ነገ እንደራሴ ቤት ያለ ስጋት አብረን ስለመኖራችን ዋስትና የሌለኝ አድርጌ ወሰድኩ። ምሽት ላይ ድሮ ሶፋው ላይ እየተንከባለልኩ ቪዲዮ ሙዚቃ እየመረጥኩ የማሳልፍ ልጅ ሳሎን በር ላይ ባለ ነጭ የኘላስቲክ ወንበር ላይ እስክንተኛ መቀመጥ አዘወተርኩ። ቤቴ ነው የሚለው እምነት ከህሊናዬ ደበዘዘ። ከዛሬ ነገ ይለወጣል ያልኩት ይህ የነስሪ የባህሪ ለውጥ መሻሻል ሳያሳይ ቀረ። በዚህ ሁኔታ አብሮ ማሳለፋችን ለተለያዩ ጭቅጭቆችና ንዝንዞች ሲያጋልጠኝ በተቻለኝ መጠን ከቤት መራቅ ጀመርኩ። ውጪ ውጪ አልኩ። አያቴ በህይወት እያለች የነበረን ፍቅር ናፈቀኝ። ትዝ ሲለኝ ያስለቅሰኝ ያስተክዘኝ ጀመር። ነስሪ በተደጋጋሚ የሚቆጣኝ አስጠንቃቂ ቁጣ እራሴን ከቤት እንዳገል አስገደደኝ። የቤተሰብ አባል አይደለህም የሚል መልዕክት አስተላለፈልኝ። እንደዛ ሳደርግ ነስሪም ለምን ብሎ ሳይጠይቀኝ ቀረ። በቃ ይህንን ነው የፈለገው ብዬ ውጪ ውጪ ማለቴን አበዛው… ከአይሆኑ ጓደኞች ገጥሜ ለተለያዩ ሱሶች ተጋለጥኩ። ከምቹ ሶፋ ወደ ደረቅ ወንበር ስሸጋገር ለምን ብሎ ያልጠየቀኝ ነስሪ በዚህ ድርጊቴ ተቆጣኝ። ቢቆጣኝም የቁጣው መንፈስ እንደ ልጅነቴው ዘመን በወንድማዊነት በአዘኔታዊ መንፈስ ስላልነበር ቁጣው ከልቤ ጠልቆ መዝለቅ አልቻለም። በዚህ ሂደት ነስሪ ስራ ለመጀመር የተወሰነ ብር ሰጥቶኝ ነበር። ዛሬ እንድሰራበት ከሰጠኝ ብር ግን በልጅነት ዘመኔ በወንድማዊ ስሜት የገዛልኝ መፅሀፍት ይበልጡብኛል። የባዳነት ፊት አሳይቶ ከሚሰጥ ሺህ ብር በወንድማዊነት መንፈስ የተሰጠ አስር ብር በስንት ጠአሙ። ያ እንድሰራበት የተሰጠኝ ብር ከዚህ ቀደም ከቤት ስሸሽ ባዳበርኩት ሱስ ምክኒያት ወደመ። በተደጋጋሚ የስራ መስኮችን ብሳተፍም እድገት ማምጣት አልቻልኩም። ከነስሪ ጋር ብንኖርም በልጅነት ዘመኔ የነበረው በወንድማዊ መንፈስ የመተያየትና የመተሳሰብ ስሜት ከአያቴ ጋር ላይመለስ ሄደ። ነስሪ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ያሳደረብኝ ተፅእኖ ለዛሬው ለሞራል አልባው ስብዕናዬ መሰረት ሆኗል። ዛሬ ልወቅሰው አልፈልግም ነገር ግን ምክኒይቱ ይህ ነው። ዛሬ ዛሬ ሳስበው የወንድማዊነት ስሜታችንን ያላላው መኖሪያ ቤታችን በመርካቶ ዙሪያ በመሆኑና ለወደፊት ህይወት ጠቃሚ ይዞታ ስለሆነ ይመስለኛል። ታዲያ ይሁና! ከኔ ጋር ምን ያገናኘዋል። የወራሽነት መብቱ ቢኖረኝምኝ! ፍላጎቱም የለኝ! ታዲያ የሚያገለኝንና ለህሊናዬ የማይፋቅ በቁጣ የተሸፈነ የምላስ ቢላ ለምን ተሳለብኝ እኮ ለምን? መልስ ያጣሁለት ነገር ነበር።

ነስሪ ቤት ውስጥ የራሴ አንድ ክፍል ነበረኝ። ማታ ገባለው  ጠዋት እወጣለው። ብቸኝነቱ ሲበዛብኝ አንዳንዴ ዘመድ ቤት አድራለው።  በመልሶ ግንባታ ምክኒያት ክፍሌ ፈረሰች። ግንባታው እሲኪያልቅ በመርካቶው ንግድ ቤት ለመሆን ሀሳብ ለነስሪ አቅርቤ ነበር። ነስሪ እንደማይሆንና እዛው አንድ ክፍል ውስጥ አንድ ላይ ማደር እንዳለብን አሳወቀኝ… ክፉ ጎኔን ብቻ እያነሳ ኮነነኝ።

…ይህ አባባሉ ውስጥም የታየኝ…  ሸር ያሰብኩበት መስሎት እንደከለከለኝ … ነው። ደግሞ በባልና በሚስት ክፍል አንድ ላይ እንደር ማለት ውጣ ከማለት በምን ይተናነሳል?። የነስሪ የልቡን አላህ ነው የሚያውቀው። ለኔ ደህንነት ቢሆን ይሄን ጥያቄ ሳላነሳ በፊት ወንድማዊ ምክሩን በቸረኝ ነበር። ከነነስሪ ጋር በአንድ ክፍል ማደሩ ከበደኝ… ምክኒያቱስ …  ይሄ ስሜት ከአሳዳጊ አያቴ ሞት ቡሃላ ለረጅም አመት በህይወቴ ያለተከሰተ ጉዳይ ነው። ከአያቴ ሞት ቡሃላ የነስሪ አውቆም ይሁን ሳያውቀው ያሳየኝ የባህሪ ለውጥ ነው። ከአያቴ ሞት ቡሃላ በቤቱ ውስጥ አራሴን ሳገል ዝም መባሌ ነው። ከአያቴ ሞት ቡሃላ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ… አይነት አስጠንቃቂ ቀጣ ነው። ምን ላድርግ ወድጄ አይደለም!  ነስሪ ይቆጣኝ የነበረው አሰጠንቃቂ ቁጣ ህሊናዬ ላይ ከባድ ህመምና ጠባሳ አትሞብኛል። ነስሪ አውቆም ይሁን ሳያው የሚያደርጋቸው ነገሮች፣ እኔን የባዳነት ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርጉ ነበሩ። በአንፃሩ እናቴም ከገጠር ወደ ከተማ ጠቅልላ ኑሮዋ በከተማ ሆኖ ነበር።  እኔና ነስሪ የምንኖርበት ቤት በግንባታ ሰበብ ስለጠበበ እኔ ከእናቴ ጋር ለመኖር ተገደድኩ። ገና አያቴ እንደሞተች እናቴ መርካቶ ያለው የንግድ ቤት የእናቴ ድርሻ ሊሰጠኝ ይገባል የሚል ጥያቄ ለማንሳት ስትሞክር እኔ ነኝ፣ እባክሽን ቤተሰባዊነቱ ይሻለናል፣ ለአለማዊ ጥቅም ስንል፣ አንቆራረጥ ብዬ ያስቆምኳት። ዛሬ ይኸው በቤተሰቦቻችን ንብረት የሚጠቀምበት ነስሪና ሌላ ሶስተኛ ወገን ሆነ፣ እኔና እናቴም በነስሪ ወደ ጎን ተደርገን የችግር ኑሮ እንመራለን " አለና ጄጃን ንግግሩን ቋጭቶ ወደ ዝምተኛነቱ ባህሪው  ተመለሰ። በታሪኩ ሁሉም የመሿለኪያ አባላት ተመስጠው፣ በጥሞና ነበር ያዳምጡ የነበረው። በዛ ላይ ጄጃንንም ነስሪንም በቅርበት ያውቋቸዋል።

"ጄጃን ልክ አላደረክም፣ እናትህ ድርሿዋን ልታስከብር ይገባ ነበር።" አለው ቡፊት ዛሬ ጄጃንና እናቱ የኑሮዋቸውን ሁኔታ እያሰላሰለ።"

"እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጄጃንም ሆነ እናቱ ይህን ከማሰባቸው በፊት፣ ነስሪ ፍትሃዊ ክፍፍል ማድረግ ይገባው ነበር። ልብ በሉ!! ቤቱ በጣም ሰፊ እንደሆነ ታውቃላችሁ። ነስሪ ቅን ቢሆን ኖሮ የራሱ ጥቅም ሳይነካ እነሱንም መጥቀም ይችል ነበር። ግን ቅንነት ይጎድለዋል። አስቡት ቅን ቢሆን ኖሮ እኮ ወደፊት ለሚደረገው የመልሶ ማልማት ግንባታ እራሱ፣ ነስሪም የጄጃን እናትም የአክሲዮን ባለቤት መሆን ይችሉ ነበር። ሁለቱም ስለ ገንዘብ ሳያስቡ መኖር ሲችሉ፣ ምን እነሱ ብቻ። ሌላም ባለድርሻ ቤተሰብ ቢኖር በቂ ነበር። ምን ያደርጋል በነስሪ ቅንነት መጉደል ምክኒያት ይህ ሁሉ ሊበላሽ ችሏል።" አለ ሰያ ነጭ ሽንኩርት በቁጭት ስሜት።

ግድ የለሹ ሙልጌ ቀጠለ… "ምንም! የተበላሸ ነገር የለም። አሁንም ቢሆን የተበላሸውን ማስተካከል ይቻላል። በገዛ ንብረታችሁ የበይ ተመልካች ልትሆኑ አይገባም። ትሰማለህ ጄጃን የወንድማዊነት ይሉኝታ ምናምን ምትለውን ቡቱቶ አውልቅና ጣል። እሱ ይህ ስሜት ቢኖረው ዛሬ ስትቸገሩ እያየ ዝም አይልም ነበር። አሁንም ቢሆን ቤቱ ሰፊ ነው፣ ለሁላችሁም ይበቃል። ፍትህ ልታገኙ ይገባል። መጀመሪያ በሽምግልና ካልሆነ በህግም ቢሆን ሄደህ፣ መብታችሁን ማስከበር አለብህ።  ፍትሃዊ ክፍፍል እስኪደረግ ድረስ፣ መራመድ ይጠበቅብሃል። ለዚህ ደግሞ እኛ የመሿለኪያ አባላት ከጎንህ ነን አይደል እንዴ? ሲል የስብስቡን አባላት እየዞረ ቃኘ። ሁሉም ልክ ነው!! በሚል ራሳቸውን በአዎንታ ነቀነቁ።

"ይገርማል!!ብሎ ጀመረ … ሳተናው፣ የሚነድ እንጨት ወደ ጉርዷ በርሜል እየጨመረ። … ይገርማል!!
ቅን መሆን በራሱ እርዳታ ነው። ለዛውም የረጂውን ጥቅም ሳይነካ ተረጂውን የሚጠቅም ብሎም ህይወቱን የሚቀይር ሀይል ያለው። ለዚህ ምርጥ ምሳሌ የሚሆነው የአባላችን ጄጃንና የእንጀራ ወንድሙ ነስሪ፣የህይወት ታሪክ ነው። ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚለው አባባል እውነትነቱ የጎላብኝ አሁን ነው። ለምን ቢባል ሰው መርዳት በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሃሳብም በቅናዊነትም። ስለዚህ ሰውን መርዳት ቀላልና፣ የሚያፀድቅ በጎ ተግባር ነው። ረጂ ለመሆን ከገንዘብና ሀሳብ በተጨማሪ ቅንነትም ያስችላል። ይህ ቅንነት በሀገራችን ቢስፋፋ፣ ፍትሃዊ ክፍፍል ቢነግስ ዛሬ የሚኖረንን ለውጥ፣ እስኪ በጄጃን ታሪክ መስላችሁ አስቡት እስኪ" ብሎ ፍልስፍናውን ቋጨ።

ጄጃን ለሙልጌ ሀሳብ እሺም እምቢም፣ የሚል ምላሽ አልሰጠም። የመሿለኪያ አባላት ወንድሞቹ የሚሰጡትን አስተያየት፣ በጥሞና አዳምጧል፣ የተናገሩትንም አንደሚተገብሩት ጠንቅቆ ያውቃል። ግን ምንም ሳይል ወደ ዝምተኛነቱ ባህር ጠለቀ።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment