Sunday, January 8, 2017

ሚንጊ ነኝ

#ሳteናw

በሐመር ብሄረሰብ ላም፣ በግ ወዘተ … ጥርስ ማብቀል የሚጀምሩት በታችኛው ድዳቸው ስለሆነ ቅዱስ ይባላሉ። አህያ ፈረስ፣ ጅብ በላይኛው ድዳቸው ስለሚያበቅሉ ርኩስ ይባላሉ። የሰው ልጅም የወተት ጥርሱን በታችኛው ማብቀል ሲገባው እንደ እርኩሳኑ በላይኛው ያበቀለ እንደሆነ ለማህበረሰቡ አይበጅም፣ ቢያድግም አባቱን የሚጋፋ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህም ገፊ(በአካባቢው አጠራር ሚንጊ ተብሎ) ይጣላል። ከዚህም በተጨማሪ ጥርስ እንደማብቀሉ ሁሉ መውለቁም ካይ ችግር አለበት። በላይኛው የበቀለው ድዱ አሁንም ቀድሞ ከወለቀ ሚንጊ ተብሎ ይጣላል። የዚህ እምነት ሰለባ ከሆኑ የሐመር ተወላጆች አንዱ እኔ ነኝ።

ከሎ ሆራ እባላለው። የተወለድኩት ሐመሮች በብዛት ከሚገኙበት ቡስካ ተራራ ስር ነው። በሕፃንነቴ እናቴ በምትለብሰው ቆዳ ሸፈን አድርጋኝ ከሰውነቷ ጋር ለጥፋኝ ስቅስቅ ብላ ታለቅስና በሻካራ ቅጠል የታችኛው ጥርሴን ትሞርድልኝ ነበር።

ጥርሴ የበቀለው መጀመሪያ በታችኛው ቀጥሎ በላይኛው ድዴ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ጥጃ ለመመለስ ስሮጥ ወድቄ የላይኛው አንድ ጥርሴ ወለቀ፣ ሌላኛው ደግሞ ተሸረፈ። እንዳበቃቀሉ ሁሉ በታችኛው ድዴ የበቀለው ጥርሴ መውለቅ ሲገባው፣ የላይኛው ቀድሞ በመውለቁ ለአደጋ ተጋለጥኩ። እናቴ ጥርሴን ትሞርድልኝ የነበረው የታችኛው ቀድሞ የወለቀ ለማስመሰል ነበር።

ጥረቷ ሁሉ ከንቱ ነበር። ወድቄ ሳለቅስ ያዩኝ ሰዎች ቀድመው ለሽማግሌዎች ነግረው ስለነበር፣ አንድ ቀን አባቴ! በሌለበት "ሚንጊ" የተባሉ ልጆችን የሚጥሉ ሽማግሌዎች ወደኛ ጎጆ መጡ። እናቴ በርቀት እንዳየቻቸው ተንቀጠቀጠች፣ እንቦሳዋን እንደምትልስ ላም ሰውነቴን ደጋግማ እየሳመች ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ሽማግሌዎች "ጥርሱን አስነቅለነው እንምጣው" ብለው ከእቅፏ መነጨቁኝ። ብትቃወም ባህል ገርሳሽ ተብላ የከፋ መከራ ስለሚደርስባት አልተከላከለችም። እንደዘበት ገፋ አድርጋ አስረከበችኝ። እሪታዬን አቀለጥኩት የደረሰልኝ ግን ማንም አልነበረም።

ሽማግሌዎቹ ራቅ ወዳለ ስፍራ ወሰዱኝ። ቁጥቋጦ የበዛበት የተራራ ጫፍ ስንደርስ ወደነሱ ሳልዞር ከፊት ለፊታቸው የተራራው ጫፍ ለይ እንድቆም አዘዙኝ። አላስችል ብሎኝ ድንገት ዞር ስል፣ አንደኛው ሽማግሌ የወረወረው ጦር ትከሻዬ ላይ ተቀበቀበ። ወዲያው ገፈታትረው ወደ ገደሉ ጨመሩኝ። ከተራራው አናት የወረወሯቸው ትንንሽ ናዳዎች ፈነካከቱኝ። የደም አበላ ዋጠኝ። እነሱም ሞቷል ብለው ትተውኝ ሄዱ። እዛ ስጓጉር አድሬ በነጋታው ረፋድ ላይ ድምፄን የሰሙ መንገደኞች አግኝተው ወደ ቤታቸው ወስደው ከሞት አተረፉኝ። ለትንሽ ጊዜ ከነሱ ጋር ከሰነባበትኩ ቡኋላ፣የመንግስት ሰራተኞች ስለነበሩ ወደ ጂንካ ከተማ ሲዘዋወሩ አብሬ ሄድኩ። እዚያም ትምህርት ቤት አስገቡኝና ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። ከወላጆቼና ከአካባቢዬ በተለየው በአስራ ሶስት አመቴ የመሰረተ ትምህርት ዘማች ሆኜ ወደ ቀዬዬ ዘመትኩ። እዚያ እንደደረስኩ አንጋፋዎቹ አወቁኝ። አባቴ ቢሞትም እናቴንና ሌሎች ዘመዶቼን በሰላም አገኘኋቸው። ገፈታትረው ገደል የከተቱኝን ሽማግሌዎች ሳያቸው ቂም ያረገዘው ልቤ ሊበቀላቸው ቋመጠ። ዳሩ ግን ባሀረሉ እንጂ ሰዎቹ ተፈጥሮአዊ ጭካኔ እንደሌላቸው በትምህርት የተገራው በሳሉ አእምሮዬ ሹክ አለኝ። እኔም ፊደል ከማስቆጠር ጎን ለጎን ይህንንና ሌሎች ጎጂ ልማዶችን ማህበረሰቡ እንዲዋጉ ለማድረግ ቆርጨ ተነሳው።
☞ ከቡስካው በስተጀርባ የተቀነጨበ = በፍቅረማርቆስ ደስታ፣ 1987
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment