Monday, September 26, 2016

"ል ጅ አ ል ባ ው አ ባ ት"


   … የዛሬ ልጆች የሚሸኑበት ዳይፐር በየቀኑ ሲገዛላቸው፣ እኛ የምንሸናበት ድርብና ሶስት መዓዘን የነጠላ ጨርቅ በየቀኑ ይታጠብል ነበር።የዛሬዎቹ ፊደል የሚቆጥሩት ደብተር በሚያክል ተች አስክሪን ስማርት ፎን ሲሆን፣እኛ የፊደል ገበታ የቆጠርነው ደብተር በሚያክል ካርቶን ላይ በተለጠፈች የፊደል መማሪያ ነበር። የዛሬ ልጆች የሚዝናኑት ኤድናሞል፣ እነ ቦራ በሚባሉ ዘመን አፈራሽ አስደሳች መጫወቻዎች ባሉባቸው ስፍራዎች ሲሆን፣ እኛ አንበሳ ግቢ፣ በፍርግርግ ብረት የተከረቸመባቸው አስፈሪ  አንበሶች ሲያዛጉና፣ ሲያገሱ በማየት ነበር። ያም ሆኖ ልጅነቴን ናፍቃለው። ከዘመኑ ልጆች ጋር ልዩነታችን ወሰኑ የሚለያይ ቢሆንም ቅሉ፣ በመጠኑም ቢሆን እነሱን መመልከት ወደ ልጅነቴ የትዝታ ባህር ይሸኘኛል…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  ርዕስና መግቢያውን አንብበህ፣ ልጁ ምን ነካው ? ወፈፍ አደረገው እንዴ? ምን ይዘላብዳል ብለህ ይሆናል?። ግድ የለም አትጨነቅ! እኔ ምንም ወፈፍ አላደረገኝም፣ ወይም በደብተራ መተት ህሊናዬም አልሳትኩም። ግን እመነኝ ልጅ አልባ አባት ሆኛለው። እንዴት ሳትወልድ አባት ሆንክ? ካልከኝ። መልሴ ላልወለድኩት ልጅ የአባትን ፍቅር በሚያስንቅ መልኩ ፍቅር በመስጠቴ ሰበብ፣ የሚለው ይሆናል። ቆይ ግን ሰው ሳይወልድ እንዴት ከወላጁ በላይ ለልጅ ነጋጠባ አንጀቱ ሊንሰፈሰፍ ይችላል? አይገርምህም?  በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠመኝ ትዕንግርት ቢኖር ይኸው ነው።

ሚሩ የሚባል የስድስት አመት ልጅ የህይወት አጋጣሚ አገናኘችን። በቃ ካወኩት ጀምሮ ለሚሩ ከአባት እናቱ በበለጠ መልኩ፣ ስለ ደህንነቱ ማሰብ፣ ስለ ጤንነቱ መጨነቅ፣ ስለ ሳቁ መመኘት፣ ስለ ሀዘኑ መንሰፍሰፍ፣ ጀመርኩ። ይገርምሃል ሚሩ ድንገት ራበኝ ካለኝ ያሳዝነኛል። እይኔ ላይ እንባ ግግር ይሞጀራል፣አንጀቴ ይላወስለታል። ምግብ አስልኬ እስኪመጣለትና እስኪበላ፣ ውስጤ ይንቆራጠጣል። ሳይበላ ቀርቶ አይደለም ከናቱ ጋር ጥብስቅ አድርጎ ቢበላም፣ ልጅ ነውና ሲሮጥ፣ ሲዘል ሲጫወት የበላው ወዲያው ብን ይልበታል። ይህ ሁኔታዬን ተረድቶ ባይርበውም ፍላጎቱን ለማሳካት ራበኝ ይለኛል፣ እንደዋሸ ብነቃበትም እውነት ለማስመሰል የሚያደርገው ጥረት ደግሞ ይበልጥ ያዝናናኛል። ወደ ልጅነቴ ትውስታ ያነጉደኛል። በዚህም የመጣ፣  ልጅ የሌለው አባት ሆኜልሃለው። ገና ሳልወልድ የአባትነት ፍቅርን ማየት ችያለው።

በአንድ እለት አዛው ስራ ቦታ በአንድ ሰው ምሳ ተጋበዝኩ፣ ሚሩን አስከትዬ መሄድ የተጋባዥነት ሞራሌ ይሉኝታ በሚሉት ገመዱ ተብትቦ አሰረኝና ሚሩን ትቼ ለመሄድ ተገደድኩ። ከጋባዤ ጋር ተያይዘን ከሚሩ ራቅን፣ ውስ ጤ ጥዬው ልበላ በመሄዴ፣ የወቀሳአይነት ይደረድርባኛል። ሆዴን ባርባር እያለው ሄድኩ፣ ሚሩ ከአይኑ ስርቅ በስሜ ጠራኝ፣ አቤት ሚሩ ና አልኩት የይሉኝታውን ገመድ የመጣይምጣ በሚል በጣጥሼ።  ሁኔታዬን የተረዳው ጋባዤ " ጃንተስር ማይጠፋው ልጅ ነው? ጥራው ከኛጋር ይበላል ብሎ እሱንም ጋበዘልኝ። ሚሩ ድምፄን ወዳሰማሁበት ቦታ ቱርርር ሲል መጣ። በውስጤ ተፈጥሮ የነበረው የሀዘን ስሜት በደስታ ፀዳል በራ። ምሳውን በሚያስደስት መልኩ ተጋብዤ ወጣው፣ሚሩ አብሮኝ በመጋበዙ ሰበብ። እስከዚህ ድረሰ ሆኗል ለሚሩ ያለኝ ፍቅር። ሚሩ፣ ሲስቅ ነብሴ በደስታ ትፍነከነካለች፣ አዝኖ ሲያለቅስ ውስጤ ያነባል። ስሜቱ ከስሜቴ ጋር ከተቆራኘ ቆይቷል። ከጎረቤት ልጅ ጋር ተጣልቶ፣ በልጅ ፀብ ጣልቃ እየገቡ ለልጆቻቸው እያደሉ  እሱን ሲያስከፉት፣ ከልጆቻቸው ጋር እንዳይጫወት ሲከለክሉት፣ እኔ የሰራሁለትን መጫወቻ፣ ሲወስዱበት፣ የኔ ነው  ቢልም ሰሚ ሳያገኝ ሲቀር፣ እናቱም ተጠግታ ከምትሰራበት ሰዎች ላለመጣላት ስትል፣ አርፈህ ቁጭ በል ስትለው፣ ህፃናት ሲጫወቱ እሱ በእናቱ ትዕዛዝ መሰረት ተቀምጦ አኩርፎ ሲጫወቱ ሲመለከታቸው፣ በመሃል ኩርፊያውን ረስቶ ሲስቅ ሳይ ውስጤ በሀዘን ይርዳል። ያሳዝነኛል። ሰው አይመልከተው እንጂ ውስጤ ይጮኻል እንደ ኢያሪኮ ከተማ። ለሱ ያለኝ ስምት ለምን እንዲህ ሊሆን እንደቻለ ምክኒያቱ ግን ሚስጥር ሆኖብኛል። ለሚሩ ያለኝ ፍቅር ተመልካች፣ ወላጅ አባቱ እየመሰልኳቸው፣ ምን አይነት አባት ነው" ብለው አስኪያሙኝ። ድረስ ደርሷል። ወላጅ አባቱ አለመሆኔን ሲያውቁ ምን እንደሚሉ እንጃ።

  ሚሩ በሞባይልህ ጌም አጫውተኝ ሲለኝ። የምጠብቀው አጣዳፊ ስልክ ቢኖር እንኳ፣ ልከለክለው አቅም ያጥረኛል። ማንኛውም ጥያቄ ቢጠይቀኝ፣ የምችለው ከሆነ ለመስጠት ወይም ለማድረግ ለሱ ያለኝ ፍቅር ያስገድደኛል። ሲዘል ሲጫወት በርቀት ሳየው፣ ካሁን አሁን እንዳይወድቅና፣ ክፉ ነገር እንዳይገጥመው በአይኔ የምከላከለው ይመስላል። እንቅፋት ሲመታው ነብሴን ጥዬ ወደሱ ልንደረደር ይከጅለኛል። ከዚህ ቀደም እንኳን ለባዳ ለወንድም እህቶቼ ልጆች እንዲህ እጅ እግር ጠፍሮ በሚይዝ ስጋት ተከታትያቸው አላውቅም። ለዚህም ነው ለሚሩ እንደዚህ መሆኔ ብህይወቴ አዲስ ገጠመኝ የሆነብኝ። ሰው ላልወለደው ልጅ እንደዚህ የሚሆንበት አንጀት እንዴት ይገጥመዋል?

   ቀን እንደዛ አዛ ሲያደርገኝ ውሎ ማታ እናቱ ይዛው ወደ ቤቱ ሲሄድ ሰላም ቻው እሺ ብሎ፣ ደግሞ በጠዋት ና እሺ" እያለ ለስንብት መጥቶ ያቅፈኛል፣ ይስመኛል። ነገ ማላገኘው ይመስል እኔም ደጋግሜ እስመዋለው፣ ናቱ ጋር ተያይዞ  ወጥቶ ይሄዳል። ድምፄ ይከተለዋል፣ "እጇን እንዳትለቅ እሺ፣ መኪና እንዳይገጭህ፣ እለዋለው እሺ ይለኛል ከቀልቡ ባልሆነ መልስ። ስጋት ይጀምረኛል፣ ቀልቃላና እብድ ነገር ስለሆነ መንገድ ላይ መኪና የሚገጨው ይመስለኛ፣ ይህ ስጋቴ መጠኑን አልፎ አንድ ሁለት ቀን በቅዠት  ሲገጭ አይቼ አባንኖኛል። አቦ አልህ ይጠብቀው እንዴት ያለ መከራ ነው እልና፣ ወደ እንቅልፌ ጠልቄያለው።

  በቀን ውስጥ ህፃናት እስከ  500 የሚደርስ ጥያቄ እንደሚጠይቁ ሳይንሱ ያረጋገጠው የህፃን ወግ ነው። የሚገርመው ሚሩ ከአንድሺህ በላይ እየጠየቀኝ ቢውልም እኔ ለመመለስ አልሰለቸውም። የሚጠይቀኝ ጥያቄዎች ደግሞ ከሚገባው በላይ ያስገርመኛል። ለምሳሌ የመኪና ውድድር ጌም ሰጥቸው በሞባይሌ ሲጫውት፣ በጌሙ ውስጥ የሚገጥሙትን እንቅፋቶች፣ አጥፋልኝ ይለኛል አይቻልም ብለው ለምን እንዴት እያለ እንደፍልስፍና ዘርፍ የማያቆም ጥያቄውን ያንቸለችልብኛል። ደግሞ ሲጫወት ላዬ ላይ፣ለመውጣት ሲንጠራራ፣ ሲዘል ፣ፊቴን እየደባበሰ የጥያቄ መአት ሲያወርድብኝ፣ ሳወራ አፍ አፌን በግርምት ሲያየኝ፣ እቅፌ ውስጥ ሆኖ እያወራውለት በድንገት ሌባ ጣቱን አፍንጫዬ ቀዳዳ ውስጥ ከቶ "ትን ሲያስብለኝና ሲስቅ። በደስታ ከመደሰት በቀር መትቸው ይቅርና ተቆጥቸው አላውቅም። አያት እንኳ እንደዚህ አያቀማጥልም። ሚሩ  ነገረ ስራው ሁሉ ያስቀኛል።

  እንዲህ ልሆን የቻልኩበትን ምክኒያት እስከ ዛሬ እንቆቅልሽ ሆኖብኝ ከርሟል። ወይ ሚሩ፣ እንደው ልጅ አልባው አባት ያደርገኝ? ሳልወልደው፣ ከወለዱት በላይ እንድጨነቅለት ያድርገኝ? ይህን ሁኔታዬን ከምን እንደመነጨ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስወያይ ነው፣ እንቆቅልሹ የተፈታልኝ። ጓደኛዬ ሚሩን አይቶት "ህፃንነቱ፣ ከዘመኑ ልጆች ለየት ያለ ነው፣ ልብ ብለህ ይህን ልጅ ካስተዋልከው ህፃንነቱ፣ጨዋታው፣ ድርጊቱ የዋህነቱ  በፊት በኛ ጊዜ የነበረውን ህፃንነት አይነት ነው።" አዎ ጓዴ እውነቱን ነው።

  የልጅነት ህይወቱን የሚናፍቅ ሰው እንዳለው ሁሉ፣ ባለፈበት መራራ ገጠመኝ የመጣ ለአፍታ ልጅነቱን ማስታወስ የማይፈልግ ሰው አለ። እምደመታደል ሆኖ እኔ የልጅነት ትዝታቸውን ከሚናፍቁ ወስጥ እመደባለው። ልጅነቴን ማስታወስ ለአስደሳች ትውስታዎቼ ስለሚያንደረድረኝ በጣም እወደዋለው። የሚያስታውሰኝንም ሁኔታና ሰው፣ እያየው በውስጡ የልጅነቴን ትዝታ መከለስ ያስደስተኛል። በተለይ ህፃናትን ማየት። እርግጥ ነው የዛሬ ህፃናት፣ እኔ ባለፍኩበት አይነት የህፃንነት ህይወት በንቃተ ህሊናም ሆነ በብዙ ነገር የተለዩ ናቸው። የልዩነት ምሳሌው መግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው።

ሚሩን ልወደው፣ የቻልኩበት ምክኒያት ይህ ነው። አገኘሁት!!   የስድስት አመቱ ሚሩ፣ በኛና በዘመኑ ልጆች ያለውን ልዩነት አጥቦ በመገኘቱ፣ ወደ ልጅነቴ ትውስታ ሸኚ ሳይሆን አድራሼ ስለሆነኝ ነው። እንደ ዘመኑ ልጆች ቆቅ፣ ነገረ ፈጅ፣ ኡላ ነገር አይደለም። ባገኘው ስው ላይ ይንጠላጠላል። የማያውቀውን ሰው ትንሽ ካዋራው ይሄን አድርግልኝ ይላል። የዋህነቱና እንደማውቃቸው እኪዮቹ ሳይሆን ሚሩ የተለየ ነው። አፈር ይበላል፣ ጭቃ እያቦካ ይጫወታል፣ ራቁቱን ሆኖ ሰያብድ፣ሲበጠብጥ ሳየው የራሴ የልጅነት ትውስታዬ በአይኔ ይታየኛል። ልጅነቴን የሚያሳየኝ በዚህ ዘመን ያገኘሁት ሆኖ ተገኝቷል፣ ከሚገባው በላይ እንድወደው፣ ከአባቱ በላይ ለደህንነቱ አሳቢ፣ልጅ አልባ አባት አድርጎኛል። ሚሩ የልጅነቴ መስታወት፣ ሚሩ ሚሪንዳ ግዛ ሲለኝ፣ በልጅነቴ ሚሪንዳ ለመጠጣት የነበረኝ፣በአመት በዓል ቀን የሚሳካው ፍላጎቴ ድቅን ይልብኛል፣ መቆሚያ አልባ ጥያቄዎቹ፣ እኔም በሱ እድሜ እጠይቅ የነበረው ጥያቄና መልስ ትውስ ብሎ ያስቀኛል። እንደውም አንዴ ለአጎቴ ልጅ በልጅነቴ የጠየኩት ጥያቄና የመለሰልኝ መልስ ዛሬም ድረስ ያስቀኛልና መሰነባበቻ ትሆን ዘንድ እነሆ!!
"ኪያር!" አልኩት።
"አቤት"
"አንበሳና ነብር ቢደባደቡ፣ ማን ያሸንፋል?" ብዬ መልሱን በጉጉት ስጠብቅ።
"እኔ አደባድቤያቸው አላውቅም!" ብሎኝ እርፍ።
(ምናለበት አንዱ ያሸንፋል ቢለኝ እስኪ?)።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment