Sunday, September 4, 2016

ጥቁር ሳምንት

"ጥቁር ሳምንት"
#ሳteናw

  በመሀል መርካቶ ልዩ ስሙ ስጋተራ ከቀኑ 8:30 ላይ ከፍተኛ የከባድ መኪና ግጭት ካለንበት የድብርት ሁኔታ አነቃን። ወዲያው የሰዎች የኡኡታ ድምፅ ተከተለ። በፍጥነት ወደ ጩኸቱና ግጭቱ ስፍራ ሮጠን ሄድን። አንድ fsr isuzu  ከአንድ ሱቅ ግንብ ጋር ተላትሞ ደረስን። በግንቡና በመኪናው መካከል ባለው ሰው በማያቆም ክፍተት ቅርፁን የቀየረ የራስ ቅል ተመለከትኩ። የመኪናው ስኮርት ሹፌር በግርግሩ አምልጦ ስለነበር ተጯጩኸን መኪናውን በሌላ ሹፌር ከተጣበቀበት ግንብ  ወደኋላ ተመለሰ። የተገጨው ሰው በደም ተጨማልቆ ግንቡ  እምደተጣበቀ ተንሸራቶ መሬት ላይ ወደቀ። ግራ አይኑ ጉድጓዷን ለቃ በያዛት ጅማት ጉንጩ ላይ ተንጠለጠለች። የቀኝ እጁ ሌባ ጣት እንደተቀሰረች ቀርታለች(የአምላክን አንድነት መስክሮ) ሸሃዳ ይዞ። እንደዚህ አይነት ዘግናኝ ግጭት ስመለከት የመጀመሪያዬ ስለነበር በድንጋጤ ደርቄ ቀረው። በግጭቱ ሳቢያ የፊቱ ቅርፅ በመበላሸቱ ማንነቱን  ለመለየት ደቂቃዎች ወሰዱብን። ከመኪናው ግጭት በተአምር ማን ገፍትሮ እናዳወጣት ለራሷ አጃዒብ የሆነባት ሻይ አፍልታ የምትሸጥ ልጅ በእጇ አረንጓዴ ጆግ ይዛ… በድንጋጤ አይኗ ፈጦ  ቆማለች… የተገጨው ሰው ማን እንደሆነ ብንጠይቃት ለመመለስ አንደበቷ ተሳስሮ ቃላት ከዷት…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
   ከቀኑ 7:00 ሰዓት እንደሁሌውም መርካቶ ስጋ ተራ ወደ ክፍለ ሀገር ሸቀጥ በሚጭኑ ከባድ መኪናዎች ተሞልታለች። ተራ አስካባሪዎቹ መኪናዎቹን እያሸጋሸጉ ለማብቃቃት በመዋከብ ላይ ናቸው። ከመኪናው መብዛት በተቃራኒ በሰፈሩ እንደ ወደብ መጫንና ማውረድ እንጂ ግብይቱ ከጎረቤት ተራዎች በመሆኑ የስጋተራ ልጆች የበይ ተመልካች ሆነናል። እኔም በበኩሌ የስራው አለመኖር እያበሳጨኝ እያማረርኩ ስብስብ ብለን ተቀምጠናል። በመርካቶ ምድር ስራ ፈትተን ለመቀመጥ ያበቃን የስራው አለመኖር መሆኑን ሳልነግርህ የምትረዳው ሀቅ ነው። በዛ ላይ ቀኑ ከወትሮው በተለየ ድብት ይላል። የመርካቶ ማህበረሰብ አባላችን ሙሂዲን ከስብስባችን መጥቶ፣ የኛም ስሜት የሆነውን የቀነኑ መክበድ ገልፆልንና አብሽሩ ብሎን ሄደ። ሙሂዲን በባህሪው የምትወደው አይነት ፀባይ ያለው ልጅ ነው። ሰላምታውና ለሰው ያለው መተናነስ በማህበረሰቡ የሚወደስበት ባህሪ የተላበሰ በሀይማኖቱ የጠነከረ እድሜው አርባ የሚጠጋ ጅመር ጎልማሳ ነው። ባለትዳርና የልጆች አባት ነው ሙሂዲን። ከኔ ጋር አንድ አይነት የስራ ፊልድ የምንሰራ ሲሆን በስራ አጋጣሚ የረጅም ጊዜ ደንበኛውን አስኮብልዬበት ነበር። የሚገርመው ሙሂዲን ይህን ባደርግም ሰላምታውን አላቆመም። እኔ ወይ ይወቅሰኛል ወይ ያኮርፈኛል ብዬ ብጠብቅም የሱ ተቃራኒ ሆነ። በፍቅር አሸነፈኝ። ድርጊቱ የህሊና ጫና አሳደረብኝና ያን ነጋዴውን በዘዴ ወደሱ እንዲመለስ አደረኩ። … ሙሂዲን ከተለየን ቡሃላ ስብስቡ ስለሱ ያለውን እውነታ ያወራ ጀመር። ወደ ጆሮዬ ከደረሱ መረጃዎች ውስጥ የሚከተሉት ነበሩ።
"እኔ ሀያ አመት ይሆነኛል እሱን ሳውቅ አንድ ቀን ክፉ ሲናገር ሰምቼው የማላውቅ ሰው ቢኖር ሙሄ ነው።"
"ለነኸይሬ ዘመድ ነው አይደል? "
"አረ አይደለም፣ እሱ እንደውም ድሮ ክርስቲያን ነበር ሰልሞ ነው እንደውም ስሙ ጌቾ ነበር።"
"ሰልሞ ነው እንደዛ ከከመስጊድ ሰላት የማይታጣው? ይገርማል!!
"አዎ ሰሞኑን እናቱን ዘይሮ እንደመጣ ነግሮኛል! ሚስቱም ከረጅም አመት የውጪ ሀገር ቆይታ ቡሃላ ነው የመጣችው አሁን እንደውም አራስ ነች አሉ"።
ሙሂዲንን አሰሪዎቹ በጣም ያቀርቡታ ይወዱታል። እንኳን እነሱ በሩቁ የምናውቀው እና እንኳ በትህትናው በፀባዩ እናከብረዋለን እንወደዋለን።

ሙሂዲን ከምሳ በፊት አንድ የክፍለ ሃገር ነጋዴ በአደራ  መልክ ለነጋዴዎች እንዲከፍልለት የላከለትን ብር በአደራው መሰረት አከፋፍሎ ከጨረሰ ቡሃላ ከአሰሪዎቹ ጋር ምሳውንእየበላ "የማን እንደሆነ ያል ተገለፀለት  ትርፍ መቶ ሃያ ብር ኪሱ ውስጥ ማግኘቱን ለአሰሪዎቹ ተናገረ። ለማንኛውም ለብቻው ይቀመጥ ብሎ ከደረት ኪሱ እያዩት አስቀመጠውና "ዘንድሮ እኔንጃ መርሳት አብዝቻለው" የሚል ቃል ከአንደበቱ ወጣ። በጊዜው ይህቺ ቃሉን ማንም ልብ አላለውም። ሙሂዲን ምሳውን በልቶ ከጨረሰ ቡሃላ እጁን ሊታጠብ ከሱቁ ግንብ ስር ሻይ አፍታ ከምትሸጠው ልጅ ጋር ሄደ። ስላልነበረች እቃዋን ላላመንካት ቆሞ ይጠብቃታል። ከቆመበት ትይዩ ከግንቡ ፊትለፊት የቆመውን fsr isuzu መኪና ተራ አስከባሪው ቦታ ለማሸጋሸግ ሾፌሩን ፈልጎ አጣውና ስኮርት ሾፌሩን እንዲያስጠጋው አዘዘው። ሙሂዲን ሻይ አፍይዋ ስትመጣ የእጅ ውሃ እንድትሰጠው ጠይቋት እሱ አንዳጎነበሰ በያዘችው አረንጓዴ ጆግ እጁን ታስታጥበው ጀመር… በተራ አስከባሪው ትዕዛዝ ተዋክቦ ስኮሩት ሾፌሩ ልብ ሳይል አንደኛ ማርሽ ላይ እንዳለ ሞተሩን አስነሳው። መኪናው ዘሎ ከፊት ለፊቱ ካለው የሱቅ ግንብ ጋር ተላተመ …ጓ!  የሙሂዲን እስትንፋስ ከዚህች ቅፅበት ቡሃላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆመች። ኢናሊላሂ ወኢና አለይሂ ራጂዑን።

በቃ የኛው ነገር ይሄው ነው። እንደ እንቁላል መች ፍርጥ እንደምንል አናውቅ፣  መች እንደምለያት ለማናውቃት ምድር መንገብገብ፣ መበላላትት፣በበነነ ተነነው ማማረራችን፣ በቃ ለዚሁ ነው። እስኪ እውነቱን እናውራ አሁን ባለንበት ባህሪያችን ሁኔታ ብንሞት እንወዳለን?  በጭራሽ!! ይኸው 7:00 ሰአት ላይ ጥሩነቱን ያወራንለት ሙሂዲን 8:300 ላይ ከምድርን ተለየ። ለመሆኑ  እኛ እንደሱ በመልካም የሚመሰከርልን ስራ ሰርተናልን? መች እንደምንሞት አናውቅምና … የምንለወጥበትን መንገድ እሱው ያግራልን። መጨረሻችንን ያሳምርልን፣በመካከላችን ፍቅርንም ይስጠን ለሟቹም ጀነተል ፍርደውስ ይወፍቀው። አሚን!! በሚል ፀሎት ያሳለፍነውን ጥቁር ሳምንት እንማርበት ዘንድ መልዕክቴን አስተላልፋለው።
ወገሬት!! 

No comments:

Post a Comment