Thursday, September 8, 2016

"የእሳት ልጅ… "

"የእሳት ልጅ አመድ"
ሳተናው

… ከረጅም አድካሚ የመኪና ጉዞ ቡኋላ ከአቧቷ ቀዬ የሚያደርሰውን ረጅም አውሯ ጎዳና በእግሯ ተያያዘችው። ሸምስ ጉልበቷ ሳይከዳት፣ የልጅነት ዘመኗን የቦረቀችበት፣ ከአቻዎቿ አፈር ቅማ የተጫወተችበት፣ ወጣነት ዘመኗን ያጣጣመችበት፣ በሀይለኝነቷ የተነሳ በአቻ ጓደኞቿ የምትፈራበት፣ በየሰርግ ቤቱ ኮከብ ጨፋሪ ሆና ያሳለፈችበትን ትውስታ ጎዳናውን ስታይ አንድ በአንድ በአይነ ህሊናዋ ተገጠገጠ። አድካሚው ጉዞ ተጠናቆ ከአባቷ ጎጆ ደረሰች። ከረጅም አመታት ቆይታ ቡኋላ ለቀዬዋ በመብቃቷ ደስታውን ለመግለፅ ጎረቤት፣ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ተቀበላት። ደስታውን ገለፀላት… አጅቧት ወደ ቤት ይዟት ገባ። የአባቷ ጎጆ ለሷ በሚደረገው ዝግጅትና፣ ሽር ጉድ ልዩ ነበር። ተበልቶ፣ተጠጥቶ፣ ቡና እየጠጣ፣ በደስታ እየተጨዋወተ ነበር። የቤቱ ድባብና ጨዋታ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ቢሆንም። የሸምስን ትኩረት ግን…  ሰዉ እየተሻማ ሲስማት በግርግሩ ከሳመቻት በአንዲት አይነ ትላልቅ ልጅአገረድ ላይ ነበር። የልጅቷም ትኩረት ሸምስ ላይ። በተደጋጋሚ አይን ለአይን እየተጋጫጩ ቆዩ። ሸምስ… የልጅቷን ትላልቅ አይን ባየች ቁጥር ልቧ ድንግጥ ይልባታል። እንደበደለ ሰው በሙሉ አይኗ ማየት ተስኗታል። አይኗን ከልጅቷ ፍፁም መንቀልም አቅቷታል። ቢጨንቃት ቢጠባት…
"ያቺ አይነ ትልልቋ የማን ልጅ ነች?" ስትል አጠገቧ የነበረችውን ሴት ጠየቀች። ሴትየዋም ሁሉን ነገር ስለምታውቅ ሳቀችና "እስኪ በደንብ እያት!"።ሸምስ አንዳች ነገር ግልፅ ባይሆንላትም ጠርጥራለች። ግን እርግጠኛ አልሆነችም።
"እባክሽን አታስጨንቂኝ ማነች?" ገና ሳያት ነው ልቤ ድንግጥ ማለት የጀመረው"። ብላ ለአፍታ ወደ ልጅ አገረዷ ዞረች። የልጅቷ አይኖች አሁንም እሷው ላይ እንደተተከሉ ነበር።
"እንግዲየውስ እርምሽን አውጪ ያንቺው ልጅ ነች"ብላ እንቅጩን ነገረቻት። ሸምስ ይህን ቃል ስትሰማ፣ ሰውነቷ ራደ፣ ቁጭት፣ፀፀት፣ጥፋተኝነት ተረባርበው የልብ ምቷን ያቆሙት መሰላት። ትንፋሽ አጠራት፣ የምታየው ሁሉ ጭልም አለባት። ወደ ነብሷ ስትመለስ አስታወሰች፣አዎ ያቺ! ምስኪን ልጇ፣ የአራስ ቤት ጨቅላ እያለች በእልህ ለአባቷ ጥላት የሄደችዋ፣ የአብራኳ ክፋይ…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
 
  ከዚህ ቀደም ከሰማዋቸው የእናቶች ታሪክ የአብራኳን ክፋይ በእልህ ጥላ የእንጀራ ልጆቿን በእንክብካቤ ያሳደገች እናት ብትኖር ሸምስ ነች። ሸምሲያ ቡሴር፣ ሳቆላምጠው(ሸምስ)። ለመሆኑ ሸምስ ማን ነች? መልሱን ከአስገራሚው ታሪኳ … ታገኘዋለህ።

   ሸምስ በወጣትነቷ በጣም እልከኛ፣ ሀይለኛ፣ ያሳበችውን ሳታሳካ የማታድር፣ የተሰኘች ብቻ ሳይሆን ሆና የኖረች እንስት ናት ሸምስ። የነዚህ ፀባዮች ባለቤት ብትሆንም በተክለ ቁመናና በመልኳ ደግሞ የተዋበች። አሟልቶ አይሰጥም አንዲሉ። ሀይለኛው ባህሪዋ ከኮረዳነቷ እስከ ብስለቷ ድረስ አብሯት የዘለቀ ቢሆንም፣ እንደ እንከን ተቆጥሮ  ከተፈላጊነት ወይም  ከተወዳጅነት፣ አላገዳትም። እሷን ለትዳር የሚመኝና የሚጠይቀው በርካታ ነው። ለዛ ነው መሰል  ባል ቀያይራ በአራተኛው የፀናችው። ለሶስት ባል ቀይ ካርድ በመስጠት ከእቴጌ መነን  ጋር ምትመሳሰለው ሸምስ መጀመሪያ የተዳረችው ለአንድ ባለ ሀብት ሰው ሁለተኛ ሚስት በመሆን ነበር። አገባች። በትዳር ህይወቷ ቀናት፣ሳምንታት፣ወራት፣ አለፉ። ሸምስ  አ ረገዘች። ሴት ልጅም ወለደች። በአጋጣሚ ሆኖ ጣውንቷም በዛው ሰሞን ነበር ወንድ ልጅ የተገላገለችው። አራሶቹን ለመንከባከብ እንዲመች በሚል ሁለቱም በአንዱ ቤት ተጠቃለው ይታረሱ ጀመር። ሁለት አራስ በአንድ ጊዜ ያስተናገደው ቤት አራስቤት፣አራስ ቤት መሽተቱ አልቀረም። ታዲያ በአንድ ዕለት እንዲህ ሆነ። ሸምስ፣ጣውንቷ ጋር ሁለቱም ህፃኖቻቸውን ታቅፈው ባሉበት፣ ለጥየቃ በመጡ እንግዶች ፊት ባላቸው መጥቶ ቀልድ አዘል ነቆራ ጣል አደረገባቸው። በቀልዱ እንግዳው በሙሉ አስካካ። ሸምስን ቀልዱና፣ሳቁ የንዴት ሞገድ ከእግርጥፍሯ እሰከ ራሷ  ቢያንዘረዝራትም፣ በሰዓቱ ዝም አለች። ጣውንቷ የባሏን ባህሪ ቀደም ብላ በማወቋ ምንም አላለችም። በባሏ ቀልድ ንድድ ያለችው ሸምስ  ምቹ አጋጣሚ ጠብቃ በዛው እለት ገና አጥንቷ ያልጠነከረችው ልጇን ጥላለት ወደ አባቷ ቤት ነጎደች። (ይህን ያህል የአራስ ልጅ አስጥሎ የሚያስኮበልል ምን ቢናገራት ይሆን?) በቃ ልጇን ጥላለት ሄደች። አትንኩኝ ባይነቷና ሀይለኝነቷ የእናትነት አጥር እንኳ አላቆመውም። ድርጊቷ በጊዜው ከነበረው አስተሳሰብና ልማድ ያፈነገጠበት ባል በንዴት ተንጨረጨረ። ጉልበቴን ስማ ትገባታለች ሲል ዛተ። የምትመለስበትን መንገድ በሀይል ሞከረ። አልቻለም። በመጨረሻ  ትመለስ ዘንድ ሽማግሌ ቢልክ፣ አለሆነም።ምን ቢቧጥጥ ወይ ፈንክች ያአባ ቢላዋ ልጅ። ሀይለኛዋ ሸምስ መስሚያዋ ጥጥ ሆነ። ባልም ተስፋውን ቆርጦ ተዋት። የሸምስ ልጅ እንደመንታ የእንጀራ እናቷ ጡት ከወንድሟ ጋር ተጋርታ አየጠባች ማደግ ዕጣ ፈንታዋ ሆነ።

   ሸምስ ሁለተኛ ሚስት ሆኜ  ትዳር አልመሰረትም ስትል ህይወቷ ላይ የምትተገብረው ደንብ አረቀቀች። አግብታ የፈታች መሆኗ ሌላ ባል የማግኘት ዕድሏን አላጠበበውም ነበርና ለሁለተኛ ግዜ ተሞሽራ ተዳረች። ከሁለተኛ ባሏ ጋር ብዙም ሳይቆይ ይኸው ሁለተኛ ባሏ፣ ቅድሚያ ይዛው ከነበረው  አቋሟ የሚፃረር ተግባር ፈፀመ። አልወለደችልኝም በሚል ሰበብ ሳያማክራት እሷ ላይ ሌላ ሚስት አገባ። ሸምስ በንዴት ጦፈች። "ልጅ ስላክወለድኩለት ነው አይደል የደረበብኝ? ቆይ ባልሰራለት ስትል በውስጧ ዛተች። ዝታም አልቀረች። የተደረበችባትን አዲስ ሙሽራ ሀይሎ ጋ ሆ! እያስጨፈረ በዋናው በር ሲገባ። እልኸኛዋ ሸምስ "በል እንግዲህ አልተገናኘንም!" ብላ በጓሮ በር ወደ አባቷ ቀዬ ነካቸው። በቃ! አፍንጫህን ላስ! አለችው። በእልኸኛነቷ ለሁለት ባሎቿ በቢጫ ሳታስጠነቅቅ ቀይ ካርድ አሳይታ ተሰናበተቻቸው። በሁለተኛው ባሏ ሸምሰ በመሄድ ብቻ አልዃ አልበረደም። ከሱ ጋር እሳትና ጭድ የነበረን ሰው አመቻምቻ፣ ለማናደድ ስትል ለሶስተኛ ጊዜ አገባች። ማግባቷ ሳይሆን ጠላቱን ማግባቷ ሁለተኛ ባሏን አሳበደው። ይህን ስታይ የበቀል ጥማቷ ረካ። ያበደው ሆዬ። ሁለቱንም እገድላቸዋለው አለ። ፎከረ ፣ሞከረ፣ በዚሁ የመጣ ሸምስ ከባሏ ጋር ቀዬውን ጥላ ወደ አዲስ አበባ ሸሸች።

  አዲስ አበባን ስትረግጥ ጊዜው በንጉሱ ዘመን መሆኑ ነው። ህይወት በከተማ ተጀመረ። አራት ኪሎ አካባቢ ቤት ተከራዩ። በዛው ቤት ከእለት ጉርስ የማያልፍንግድ ጀመረች። ለስራው አዲስ ስለሆነች ወዲያው ትርፋማ አላደረጋትም ወይንም አላዋጣትም! በዛ ላይ የአራት ኪሎ አካባቢ አብዛኛው ህብረተሰብ ከለመደችው ከኖረችበት ባህል፣ወግ፣ልማድ ሀይማኖት የተለየ በመሆኑ በቀላሉ መላመድ አልቻለችም። አንድ ቀን ለዚሁ ሶስተኛ ባሏ መርካቶ ወንድሞቼ ስላሉ እነሱ ጋር ሄደን ኑሮዋችንን አናሻሽል ሰርተን አራሳችን እንለውጥ ስትል አማከረችው። መልሱ "ሴትዮ አርፈሽ ተቀመጭ  አትንቀዥቀዢ" ነበር። "አርፌ ልቀመጥ? ኧረ! ጣጣህን ቻል!! ብላው ጥላው ወደ መርካቶ። ሸምስ ወንድሞቿ ጋር መርካቶ ገባች። የአይብና ቆጮ ንግድ ጀመረች። (የዛሬው የመርካቶው ቆጮ ተራ ነበር !! አይገርምም።)

እልኸኛዋ ሸምስ ህይወቷን ለብቻዋ ቀጠለች። የሚገርመው ሶስት ባሎቿን ብትፈታም ተተኪ ባል ማግኘት  አልጠጠረባትም። ብዙ ባል እየመጣ እሷን ለትዳር መጠየቅ አልተወም። ያመነችበት ሰላልገጠማት በጄ አላለችም። ከመጀመሪያ ባሏ በተጋባችው እልህ የመጣ የአብራኳን ክፋይ ልጇንን እንኳ ዞር ብላ አላየችም። የእልህኛነቷ ብዛት በአብራኳ ክፋይ እንኳ እንድትጨክን አስገደዳት። በመጨረሻም እዛው መርካቶ ሚስቱ አራት ልጅ አከታትላ ወልዳለት የሞተችበትን ሰው በዘመድ በኩል እንደ አጫት ተነገራት። መልሷ እስኪ ሄጄ አየዋለው ነበር። ጉድ ተመልከት! ሴት ልጅ፣ ወንዱ ቤቷ ሄዶ አይቷትና መርጧት ብቻ በሚያገባበት በዛ ዘመን፣ ሴት ልጅ ማን ያግባት ማን ሳታውቅ ዝም ብላ እንደተመረጠች ተነድታ ወደ ባሏ ቤት መሄድ አግባባዊ ወግ መሆኑ በሚታመንበት በዚያ ዘመን። የሸምስ ድርጊት በተገላቢጦሽ ሆነ።  ያጫትን ሰው ቤቱ ሄዳ አይታው እራሷው እንደሚሆናት እንደማይሆናት ለመወሰን ቀጠሮ አስያዘች። ይህ ድርጊቷ ከአባት ቅድመ አያት ተያይዞ የመጣውን ወግ ልማድ ወደ ጎን ብሎ ተገኘ። የሰማ፣ያየ ሁሉ እንደጉድ መነጋገሪያ ሆነ። በቀጠሮው መሰረት ተደግሶ ወደ አጫት ሰው ቤት ሄደች። ወንድሞቿን እንኳ አስከትላ አልነበረም። ብቻዋን፣ ሄደች ይህ ሁኔታ በራስ የመተማመን መንፈሷ ዘመኑን የተሻገረ መሆኑ ልብ ይሏል። ሰውየን አየቸው! ወዲያው ፎንቃ ጠለፋት! በቃ በአንዴ ወደደችው። እናታቸው ጥላቸው የሞተችውን አራት ህፃን ልጆቹን ስታይ ደግሞ ይብስ ባባች። እሺታዋን እዛው አበሰረች። ድግሱ የተሳካለት ሆነ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ አግባች።እዚህች ጋር  ሸምስን ከሀይለስላሴ ሚስት እቴጌ መነን ጋር የሚያመሳስላት አንድ ጉዳይ ቢኖር በአራተኛ ባሏ መፅናቷ ነው። ስራዋና አቆመች፣ ልጆቹን ማሳደግ ስራዋ አደረገች። ይገርማል!! የራሳን የአብራኳን ክፋይ በእልህ ጥላ የባሏን ልጆች ተንከባክባ በማሳደግ ረገድም የተለየች ያሰኛታል። ፈጣሪ መጀመሪያ ጥላት በመጣችው ልጇ አቄመባት መሰል ጥላት ከሄደችው የመጀመሪያዋ ልጅ ቡሃላ ለሌላ ልጅ አልታደለችም።
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
   በሌላው የህይወት ገፅታ ሸምስ አራስ ቤት ጥላት የመጣችው ልጇ ካሳደገቻት ከእንጀራ እናቷ ጋር ተስማምቶ መኖር ቢያቅታት። ቤቱን ለቃ ጠፋች። የአያቷን ቤት በአንድ አጋጣሚ በእንጀራ እናቷ ጋር ሄዳ አይታው ሰለነበር ወደዛው አመራች። መኮብለልን ከእናቷ ሸምስ በዘር የወረሰችው ይመስላል። ቢሆንም የኗቷን ያህል ሀይለኛ አልነበረችም። የእሳት ልጅ አመድ…። አጠያይቃ አጠያይቃ ከአያቷ ጎጆ ደረሰች። በግቢው ውስጥ የነበሩት አያቷ ረጅሙ ጉዞ አድክሟትና፣ አቧሯ በመላ አካሏ ላይ ረብቦ ሲያዩዋት፣ የወላድ አንጀታቸው ተላውሶ አነቡ፣ አለቀሱ። የሸምስ ልጅ  ከዚህ ቡሃላ ኑሮዋ በአያቷ ጎጆ ሆነ። ልጇም አደገች። ሸምስ አባቷ ቤት የምትሄድበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ከሸሸቸው ረጅም አመት ወደ ሆናት የትውልድ መንደር ነጎደች …
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
…   በአባቷ ቤት ከደረሰች ቡሃላ ትኩረቷን ሰርቃ ስታያት የቆየችው ልጅ አገረድ የራሷ ልጅ መሆኗን አጠገቧ ካለችው ሴት ከሰማች ቡሃላ በድንጋጤ የሳተችው አቅሏ ቀስ በቀስ ተመለሰ። አስታወሰች፣ አዎ! ያቺ ያቺ ምስኪኗ ልጇ፣ የአራስ ቤት ጨቅላ እያለች በእልህ ለአባቷ ጥላት የሄደችዋ፣ የአብራኳ ክፋይ፣ እሯሷ መሆኗን አወቀች። ገና ስታያት ልቧ ትር ትር ያለባት፣ በአይኖቿ ውስጥ መበደሏን የሚገልፅ ስሜቷን ደመነብሷ ሹክ ሲላት ኖሯል ለካ። ዛሬ እንደትላንቱ፣ ሀይለኛዋ፣ በእልከኛነቷ ወደር የሌላቷ ሸምስ አይደለችም። እድሜ ገፍቷል፣ አስተውሎቷ በስሏል፣ በወጣትነቷ  መስሎ ያልታያት ጥፋት ዛሬ ታይቷታል። ሸምስ የተሰበሰበው ሰው እያቆራረጠች ተንደረደረች፣ ከመሬት ላይ ስጋ እንደምትሞጨልፍ  ጭልፊት አሞራ ልቅም አድርጋ ልጇን አቀፈቻት። ያገኘችውን አካሏን ሳመቻት። ጥብቅ ባለ እቅፏ ውስጥ አኑራት ረጅም ሰዓት አዬዬዋን አስነካችው። "እኔ ነኝ ገዳይሽ!" ለቅሷዋን የሚያጅብ ተደጋጋሚ ከሳግ ጋር ተቀላቅሎ ከአንደበቷ የሚወጣ ቃል ነበር። በእልከኝነቷ የፈፀመችው ተግባር ጊዜ ልብ ሰጥቶ ፀፀታት። ፀፀቱ የእግር አሳትት ሆኖ መላ አካሏን ለበለባት። ከስህተት እንደመመለስ፣ ጥፋትን አምኖ እንደማስተካከልስ? ምን መልካም ነገር አለ። ይኸው ሸምስ ዛሬ ጥፋቷን አምናለች። ልጇን ከተማ ከኔ ጋር ትኑር ስትል ሸምስ አቧቷን ብትጠይቅም፣ ቤት ውስጥ ሌላ ልጅአገረድ ሰላልነበር የአባቷ መልስ አይሆንም ነበር። ።ሸምስ ልጇን በርቀት የሚያስፈልጋትን ታሟላላት ጀመር። ምንም እንኳ ለልጇ የቁስ ፍላጎቷን ብታሟላም። የእናትነት ፍቅር ሰጥታ አለማሳደጓ የፈጠረባት የስነልቦና ክፍተት ሊሞላላት አልቻለም ነበር። ይህን ክፍተት በምን ልትሞላው  እንደምትችል የዘወትር ሃሳቧ ሆነ። ልጇም ለአቅመ ሄዋን በመድረሷ ተዳረች። ወለደች። ሁለተኛዋን ልጅ በእናቷ ሸምስ ቤት መርካቶ መጥታ ነበር የወለደቻት። በእናቷ ታረሰች። በዚህ ጊዜ በሸምስ ህሊና እንድ ነገር አቃጨለ። ለአንድያ ልጇ የነፈገቻትን የእናትነት ፍቀር፣ ለወለደቻት ልጅ ሰጥታ ልታሳድግ በልጇ ልትክሳት ወጠነች። ልጇን ጠየቀች። ምንም እንኳ ለእናቷ ሸምስ፣ ሙሉ በሙሉ ይቅርታዋን ባትነፍጋትም በዚህ ጉዳይ አድሜ ልክ እንደምትፀፀ ታውቅ ነበረና፣ሳታቅማማ ተስማማች። የሸምስ ውጥኗ ቢሰምርም፣ የልቧን ሊያደርስላት አልቻለም። እናም እንዲህ አለች… "ልጄ!! በህፃንነትሽ የነፈግኩሽን ፍቅር ዛሬ ለልጅሽ በመስጠት ልክስሽ እንደምሻ ጠይቄሽ አላሳፈርሺኝም፣ እንደጨከንኩብሽ አልጨከንሽብኝም… የለቀቅሶ ሳግ ንግግሯን ገታው…  ከዚህ ቡሃላ የምትወልጂውንም ወንድ ልጅ እንደወለድሺው ለኔው ነው የምትሰጪኝ! ቃል ግቢልኝ አለቻት ስሜት በሚሰረስር ድምፅ። ልጇም ቃሏን እንደምትጠብቅ ምላ ተገዝታ ወደ ቀዬዋ ነካችው። ቃል በተጋቡ በሁለት አመቱ ሴት ልጅ ወለደች። እናቷ ሸምስ ቃል ያስገባቻት ወንድ ልጅ ነበር። ድጋሚ በሁለት አመቱ ወለደች። አሁን ወንድ ሆነ። በቃሏ መሰረት አራት ወር ብቻ ከሷ የቆየውን ወንዱን ህፃን ለእናቷ ሸምስ ሰጠች። እስኪጠነክር አብራው ቆየች። ሸምስ ድስታዋ ወደር አጣ፣ ለልጇ የነፈገችውን እንክብካቤና ፍቅር ለልጅ ልጆቿ ያለ ስስት አፈሰሰችላቸው። ይህ ተግባሯ የስነልቦናዋን ክፍተት ቀስ በቀስ ሞላው። በዚህ በእናትና ልጅ የህይወት ታሪክ ሰበብ በአያት ተቀማጥለው ለማደግ የበቁት የሸምስን የልጅ ልጆች አሁን ላስተዋውቅህ? ሴቷ ታላቄ  shtex ስትሆን ወንዱ እኔው ሳteናw ነኝ!! የናቴ ቃል ኪዳን።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment