Sunday, September 4, 2016

ሸምስ ቡሴር

" ሸ ም ስ      ቡ ሴ ር "
#ሳteናw

   ሸምስ … ከረጅም አድካሚ ጉዞ ቡሃላ አቧቷ ቀዬ ደረሰች። ለሷ አቀባበል ለማድረግ በቅድም አያቴ ጎጆ ቤተሰብ፣ጎረቤት ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ተሰብስቦ ለቡና በተቀመጠበት ነበር… የሸምስን ቀልብ አንዲት ህፃን ልጅ የሳበችው። ሸምስ… ህፃኗን ባየች ቁጥር ልቧ ድንግጥ ድንግጥ ትር ትር ይልባት ገባ። ቢጨንቃት ቢጠባት "ያቺ አይነ ትልልቋ ልጅ  ማን ነች? ስትል አጠገቧ የነበረችውን ሴት ጠየቀች"።"ሴትየዋም እስኪ በደንብ እያት!"። አለቻት። ሸምስ አንዳች ነገር ጠረጠረች። ግን እርግጠኛ ስላልሆነች ጥርጣሬዋን ዘላ ወዸ ጥያቄዋ ገባች "እባክሽን አታስጨንቂኝ ማነች?" "እንግዲየውስ እርምሽን አውጪ ያንቺው ልጅ ነች።"……
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

እስከማውቀው ድረስ በምድር ላይ ከሰማዋቸው የእናቶች ታሪክ የአብራኳን ልጅ በእልህ ጥላ የእንጀራ ልጆቿን በእንክብካቤ ያሳደገች እናት ብትኖር የእናቴ እናት አያቴ ሸምስ ቡሴር ነች።

   አያቴ በወጣትነት ዘመኗ ለምታምንበት አቋሟ ምንም ማንም ሀይል የማይበግራትና በጣም እልከኛ በባህሪዋም ሀይለኛ የተሰኘች ነበረች። ይህ ባህሪዋና እልከኛነቷ ከኮረዳነቷ እስከ ብስለቷ ድረስ አብሯት የዘለቀ ባህሪይ ነበር። በተወረደልኝ የታሪክ መረጃ መሰረት ሀይለኛ ነች!! በሚል ምንም ባል ያላጣች ስትሆን የፈለገችውን ነገር በፈለገችው መልኩ የራሳ የማድረግ ብቃት ከመላበሷ ባሻገር በተክለ ቁመናና በመልኳ የተዋበች ነበረች።   ይህችው ሀይለኛዋ አያቴ ለእናቴ አባት ሁለተኛ ሚስት ሆና ከቤቱ ገባች። እሷና ጣውንቷ በተመሳሳይ ጊዜ ወለዱ፣ አያቴ እናቴን ፣ ጣውንቷ አጎቴን። ሁለት አራስ በአንድ ጊዜ ያስተናገደው የአያቶቼ ቤት አራስ አራስ መሽተቱ አልቀረም። አንድ ዕለት እንዲህ ሆነ። አያቴ ሸምስ በአራስነት ጊዜዋ ከአራስ ጣውንቷ ጋር እየታረሰች ባለችበት ሁኔታ ባሏ መጥቶ ቀልድ አዘል ነቆራ ጣል አደረገባቸው።  ጣውንቷ ምንም አላለችም። አያቴ ግን አፍንጫህን ላስ! አለችውና ገና አጥንቷ ያልጠነከረችው እናቴን ጥላለት ወደ አባቷ ቤት ነጎደች። ታምናለህ በቃ ልጇን ጥላ ሄደች። የእናቴ አባት ትመለስ ዘንድ ሽማግሌ ቢልክ፣ ምን ቢቧጥጥ። ሀይለኛዋ አያቴ መስሚያዋ ጥጥ። እናቴ ከአጎቴ ጋር እንደመንታ የእንጀራ እናቷ ጡት አየጠባች አደገች። አያቴ ሁለተኛ ሁለተኛ ሚስት ሆኜ ባል አላገባም! በሚል አቋሟ ፀንታ በአባቷ ቤት ከሀይለኝነቷ ጋር መኖራን ቀጠለች። ለሁለተኛ ጊዜ ተኩላ ተሞሽራ ተዳረች። ብዙም ሳይቆይ ይኸው ሁለተኛ ባሏ፣ በምታምንበት አቋም የሚፃረር ተግባር ፈፀመ። እሷ ላይ ሌላ ሚስት አገባ። "ልጅ ስላክወለድኩለት ነው አይደል የደረበብኝ ?" ብላእልህ ተናነቃት። በሆዷ ላንተ እልህ የማደርገውን እኔ አውቃለው ብላ ጠበቀች። ሁለተኛው ባሏ አዲሷን ሙሽራ ሀይሎ ጋ ሆ እያስጨፈረ በዋናው በር ሲያገባ። እልኸኛዋ አያቴ "በል እንግዲህ አልተገናኘንም!" ብላ። በጓሮ በር ነካቸው። በቃ! አፍንጫህን ላስ! አለችው። ድጋሚ  ወደ አባቷ ቤትገባች። የባል ገዷ ለሱ እልህ፣ከሱ ጋር ማይስማማ የነበረን ሰው። ለሶስተኛ ጊዜ አገባች። ሁለተኛ ባሏን በሶስስተኛ ባሏ አሳበደችው። እገድላቸዋለው አለ። በዚሁ የመጣ ከዚሁ ባሏ ጋር ለኑሮ  ወደ አዲስ አበባ መጡ።   እንግዲህ ጊዜው በንጉሱ ዘመን መሆኑ ነው። ህይወቷ በአዲስ አበባ ቀጠለች። አራት ኪሎ አካባቢ በነበረው በባሏ ቤት የሻሜታ ንግድ ጀመረች። አላዋጣትም! የአራት ኪሎ አካባቢ ኑሮም አልተመቻትም።(ለፖለቲካ ቅርብ ስፍራ ስለነበር ይሆን?) እንጃ ብቻ አልደላትም። አንድ ቀን ለዚሁ ሶስተኘ ባሏ መርካቶ ወንድሞቼ ስላሉ እነሱ ጋር ሄደን ኑሮዋችንን አናሻሽል ስትል አማከረችው። አይሆንም አላታ። እሷም አፍንጫህን ላሳታ! ብላ። ሶስተኛወንም  ጥላ ወደ መርካቶ ነካቸው። ወንድሞቿ ጋር ገባች። የግሏን ስራ መስራት ጀመረች። አያቴ ሶስት አግብታ ብትፈታም ባል አልጠጠረባትም። ብዙ ባል እየመጣ እሷን ለትዳር መጠየቅ አልተወም። ያመነችበት ሰላልገጠማት በጄ አላለችም። ከመጀመሪያ ባሏ በተጋባችው እልህ የመጣ የአብራኳን ክፋይ ልጇንን እንኳ ዞር ብላ አላየችም። የእልህኛነቷ ብዛት በአብራኳ ክፋይ እንኳ እንድትጨክን አስገደዳት።  በመርካቶ የአይብና የቆጮ ንግድ ጀመረች። (የዛሬው የመርካቶው ቆጮ ተራ በአያቴ ዘመንም ነበር አይገርምም።) እልኸኛዋ አያቴ ህይወቷን ለብቻዋ ቀጠለች። በመጨረሻም እዛው መርካቶ ሚስቱ አራት ልጅ አከታትላ ወልዳለት የሞተችበትን ሰው በዘመድ በኩል እንደ አጫት ተነገራት። መልሷ እስኪ ሄጄ አየዋለው ነበር። ተመልከትልኝ ጉዷን! ሴት ልጅ፣ ወንዱ ቤቷ ሄዶ አይቷትና መርጧት ብቻ በሚያገባበት በዛ ጊዜ፣ ማን ያግባት ማን ሳታውቅ ዝም ብላ እንደተመረጠች ተነድታ ወደ ባሏ ቤት በምትሄድበት ዘመን።  አያቴ በተገላቢጦሽ ያጫትን ሰው ቤቱ ሄዳ አይታው እራሷው እንደሚሆናት ለመወሰን ቀጠሮ አስያዘች። ይህ አድራጎቷ ተያይዞ የመጣውን ወግ ልማድ ወደ ጎን ብላ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ (አቦ ጀግና!)። አያቴ ስለሆነች አያሽቃበጥኩላት ወይም እየሞላውህ እንዳይመስልህ የምተረተርልህ ሀቅ ነው። ከፈለክ ድንጋይ ነክሼ እምልልሃለው።( አረ ሲያምርህ ይቅር ከፈለክ አትመን…ህእ)

   በቀጠሮው መሰረት ተደግሶ ወደ አጫት ሰው ቤት ሄደች። አየቸው! ወዲያወ ፎንቃ! በቃ በአንዴ ወደደችው። እናታቸው ጥላቸው የሞተችውን አራት ህፃን ልጆቹን ስታይ ደግሞ ይብስ ባባች። እሺታዋን እዛው አበሰረች። ድግሱ የተሳካለት ሆነ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ አግብታ ህይወትን  ቀጠለች። የራሳን የአብራኳን ክፋይ በእልህ ለባሏ ጥላ የባሏን ልጆች እንደ ልጆቿ በእንክብካቤ አሳደገች።   አያቴ ፈጣሪ መጀመሪያ ጥላት በመጣችው ልጇ አቄመባት መሰል ከእናቴ ቡሃላ ለልጅ አልታደለችም።

  አራስ ቤት ጥላት የመጣችው ልጇ(እናቴ) ከእንጀራ እናቷ ጋር ተስማምቶ መኖር ቢያቅታት። ወደ እናቷ አባት ቤት ጠፍታ መጣች።(በማን ትውጣ?)

   እናቴን ሲያዩዋት በወንድ አያቷ አለቀሱ። እናቴ ከዚህ ቡሃላ  በአያቷ እጅ ህይወቷ ቀጠለች። ከዘመን ቡሃላ አያቴ አባቷ ቤት የምትሄድበት አጋጣሚ ተፈጠረ። የልጇን ወደ አባቷ ቤት መምጣት የማውታቀው አያቴ አባቷ ቤት ገጠር ሄደች። በአባቷ ቤት … ቤተሰብ ሁሉ ተሰብስቦ በተቀመጠበት የአያቴን ቀልብ አንዲት ልጅ ሳበቻት። ባየቻት ቁጥር ልቧ ድንግጥ ድንግጥ ይልባት ገባ።"ያቺ አይነ ትልልቋ ልጅ  ማን ነች?" ስትል አጠገቧ የነበረችውን ሴት ጠየቀች።"ሴትየዋም እስኪ በደንብ እያት!"። አያቴ አንዳች ነገር ጠረጠረች። ግን እረግጠኛ ስላልሆነች ተወችውና።"እባክሽን አታስጨንቂኝ ማነች?" "እንግዲየውስ እርምሽን አውጪ ያንቺው ልጅ ነች።"   አያቴ በተሰበሰበው በሰው መኻል ተንደርድራ ሄዳ ልጇን አቀፈቻት። ረጅም ሰዓት እንዳቀፈቻት። አዬዬዋን አስነካችው። "እኔ ነኝ ገዳይሽ!" "አኔ ነኝ ገዳይሽ!"። ረጅም ሰዓት እናቴን አቅፋ አነባች። ትላንት በጉርምስናዋ የፈፀመችው ተግባር ዛሬ ልብ ስትገዛ ፀፀታት። ፀፀቱ የእግር አሳትት ሆኖ መላ አካሏን ለበለባት። እናቴን ከተማ ወስዳ ለማሳደግ አቧቷን ጠየቀች። ቤት ውስጥ ሌላ ልጅአገረድ ሰላልነበር አባቷም የአባቷም ሚስት በጄ አላሉም።   አያቴ ከዛ ቡሃላ ለእናቴ በርቀት የሚያስፈልጋትን ታሟላላት ጀመር። የቁስ ፍላጎቷን ማሟላቷ፣ የእናትነት ፍቅር ለልጇ አለመስጠቷ የፈጠረባት የስነ ልቦና ክፍተት ሊሞላላት አልቻለም። ዘመን አልፎ ዘመን መጣ። ልጇም (እናቴ) ተዳረች። ወለደች። ሁለተኛዋን ልጅ በእናቷ ቤት መርካቶ መጥታ ነበር  የወለደቻት። ከዚህ ቡሃላ አያቴ እንድ ነገር አሰበች። ለአንድያ ልጇ የነፈገቻትን የእናትነት ፍቀር ለልጅ ልጇ ልትሰጥ። ሲፀፅታት የኖረውን በልጇ ልትክሳት። የልጅ ልጇን ለማሳደግ እዛው መርካቶ አስቀረች። ይህም አያቴን አላረካትም። እናቴ ልጇን እናቷ ዘንድ ትታ ለመሄድ ስትሰናዳ። አስቀምጣ እንዲህ አለቻት። "ልጄ በህፃንነትሽ የነፈግኩሽን ፍቅር ዛሬ ለልችጆሽ በመስጠት ልክስሽ እሻለው። ይህች ልጅ እኔው ጋር ታድጋለች። ከዚህ ቡሃላ የምትወልጂውንም ወንድ ልጅ እንደወለድሺው ለኔው ነው የምትሰጪኝ! ብላ ቃል አስገባቻት። እናቴ ቃሏን እንደምትጠብቅ ምላ ተገዝታ ወደ ቀዬዋ ነካችው። ቃል በተጋቡ በሁለት አመቱ እናቴ ሴት ልጅ ወለደች ይህቺ ልጇ ከሳ ጋር ታድጋለች። እናቷ የገባቸው ቃሏ ወንድ ልጅ ነው። ድጋሚ በሁለት አመቱ ወለደች። አሁን ወንድ ሆነ። በቃሏ መሰረት የአራስነት ጊዜዋን እንደጨረሰች ወንዱን ህፃን ልጇን ለእናቷ ሰጠች። በደንብ እስኪጠነክር አብራው ቆየች። በመሃል ከሱ ተለይቼ መኖር አልቻልኩም ብላ መልሳ ገጠር ወሰደችው። ከተማ ለምዶ ገጠር አልስማማ አለው። ድጋሚ ይዛው ከተማ መጣች። ቀድሞ የነበረው ወዙ የገጠሩ አየር አሟጦት ነበር… በመጨረሻም ለእናቷ ጥላው ሄደች። ህፃኑም በአያቱ ማደጉን ቀጠለ። ህፃኑ ማን እንደሆነ ልንገርህ? እኔው ነኝ። በአያቴ እጅ ማደግ እጣ ፈንታዬ የሆነበትን መንስኤ አሁን የገባህ? ይመስለኛል!!
ወገሬት!!   

No comments:

Post a Comment