Sunday, September 4, 2016

ኢቲቪና ሙዓመር ጋዳፊ

"ኢቲቪና ጋዳፊ"

  ኢቲቪ ድሮም ለኢትዮጲያ ህዝብ አልተፈጠረም። ቶምሰን በተባለ የእንግሊዝ ድርጅት አገዛ በ1957 ጋዳፊና የወቅቱ አንባገነኖች ደስ እንዲላቸው ሲባል ክቡርነታቸው የአፍሪካ አንድነትን ለማድመቅ ሲሉ ወለዱት። እድሜ ለጃ!። ይኸው ኢቲቪ ከጋዳፊ እኩል ኢትዮጲያን ላለፉት አርባ ምናምን አመታት የሙጥኝ እንዳለ አለ።

   አንድ ተውኔት መድረክ ላይ ሲተወን ትያትር ይባላል። ተውኔቱ ደጅ ተቀርፆ በሲኒማ ቤትና በቴሌቪዥን ስታየው ፊልም ተብሎ ይጠራል። አንድ ደረቅ ኘሮፖጋንዳ ባላዋቂ ጋዜጠኛ ወይም በአዋቂ "ዋሽቶ አደር" በሰፊ ብራና ሲፃፍ "አዲስ ዘመን" ይባላል። ያው! ፕሮፖጋንዳ ጥሩ የትወና ብቃት ባላቸው ጋዘጠኞች ተቀርፆ ሲቀርብ "ኢቲቪ" ተብሎ  ይጠራል።"ኢቲቪ"ና "አዲስ ዘመን" የእድሜ ዘመናቸው ረጅም ነው። ሁለቱም እድሜ ያጎበጣቸው አዛውንቶች ናቸው፣ ተከብረው ግን አያውቁም።

"አዲስ ዘመን" ሞኝ ሰውነት ስላለው ኩሸት ሲበዛበት ዝም ብሎ ወደ ጎን ይለጠጣል። በአንፃሩ ኢቲቪ ውሸትና ኩሸት እያሸማቀቀው በየቀኑ ይከሳል። ስንት ዲያስፖራዎች 21‘ ኢንች ቲቪ እየገዙ ወደ አሜሪካና አውሮፖ ሄደው አመት ቆይተው ሲመለሱ የገዙት ቲቪ 14’ ኢንች ሆኖ ጠበቃቸው መሰለህ።ይህ ነገር ቀልድ ሆኖ ይወራል እንጂ የየቤቱ እውነት ነው። ብዙ የኢትዮጲያ ቲቪዎች በውሸት እየተሸማቀቁ ከስተዋል። ተመሳሳይ የበሽታው ምልክቶችም በአስመራ ቲቪዎችም ላይ ይስተዋላል።

ዕድሜዬ እየገፋ ነው። የኢቲቪን ውለታ ዛሬም ድረስ አልረሳውም። በአባባ ተስፋዬ ተረቶች መልካም ስብዕናን እንድገነባ ረድቶኛል፣ አዝናንቶኛል፣ በአፍሪካ ዋንጫዎች አስቦርቆኛል። ማራዶና የተባለ የኳስ ንጉስ እንዳለ አሳይቶኛል። ጥላሁን ገሠሠ የሚባል የሙዚቃ ንጉስ ተስረቅራቂ ድምፁን አሰምቶኛል፣ እንባውን ሳይቀር አሳይቶኛል። ማይክል ጃክሰንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየኝ ኢቲቪ ነው። አለምን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት በኢቲቪ መሆኑን መቼም አልክድም። ኢቲቪ በሁሉም መልኩ አሳድጎኛል። ለዚህም አመሰግነዋለው።

  ኢቲቪ በልጅነቴ አይንና ጆሮዬ ነበር። አሁን አይንና ጆሮዬ በገዛ አገሬ በይፋ ታሽገውብኛል። ይህ የእኔ አቻ ትውልዶች ሁሉ የሚጋሩት ሀቅ ነው። እንዲያውም የኢቲቪ ውሸት ያንገሸገሻቸው ወጣቶች በማህበራዊ ድህረገፅ "I HATE ETV" የሚባል የፌስቡክ ቡድን አስከማቋቋም ደርሰዋል። ይህ ንቅናቄ… በርካታ አባላት አሉት። የአገሪቱ ዝነኛ ሰዎችም በዚህ ድህረ ገፅ ኢቲቪ እንዳንገሸገሻቸው ይናገራሉ። አንድ ወጣት በዚህ የማህበረሰብ ድህረ ገፅ ላይ እንዲህ ፅፎ አነበብኩ "ኢቲቪ እናት ኢትዮጲያ ላይ ያለ ትልቅ እባጭ ኾኖ ይሰማኛል"
ኢቲቪ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ይዋል!!
ረጅም እድሜ እንዲህ በነፃነት እንድንፅፍ ላበቃን ህገ መንግስታችን!
ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር!!

ምንጭ– ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ በመሀመድ ሰልማን

No comments:

Post a Comment