Wednesday, June 29, 2016

"የ ቄ ሳ ር … እ ን ባ"

  ወይኔ መንጌ መጨረሻዬ ይህ ሆነ? ለደቂቃዎች በዝምታ ተዋጡ። እንጥላቸው ዱብ… ሀሞታቸው ፍስስ… ቅልጥማቸው ድቅቅ… ወገባቸው ዛለ… ጉልበት ከድቷቸው ተንገዳገዱ። ራቅ ብሎ አንድ ድንጋይ ታያቸው። ሄደው ቁጭ አሉበት። እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም… ፈሰሰ። በጉንጫቸው ተንሸራትቶ ሱሪያቸው ላይ ተንጠባጠበ። አብረዋቸው የነበሩ ባለስልጣናት በብዙ ልመና ከተቀመጡበት አስነሷቸው። እንዳቀረቀሩ ወደ ሄሌኮኘተራቸው ገቡ። … ሄሊኮፕተሯ እንደተነሳች ተቀምጠውባት የነበረው ድንጋይ በዙ 50 ካሊበር አውቶማቲክ መሳሪያ ፍርክስክሷ ወጣ። "ነው እንዴ…? አሉ መንግስቱ ሀይለማሪያም!! "ይሄ ፈፅሞ የጠላት ጥይት አይደለም። የጄኔራል ገዝሙ ስራ ናት!!" ተስፋ መቁረጥ በደማቸው ተሰነቀረ። ከዚህ ቡሃላ የግል ህይወታቸውን ማትረፍ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ታያቸው። ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። በሚቀጥለው ቀን ጧት ወደ ዚምባብዌ የሚበር ቻርተር አውሮፕላን አዘዙ። ••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••• አርብ ሚያዚያ 11/1983 ኮ/ል መንግስቱ ሀይለማሪያም፣ ብሄራዊ ሸንጎ የተባለውን አካል አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ። በዚህ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ የሀረሩ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ንግግር ቆሽቴያቸውን አሳረረው… "…ክቡር ኘሬዝዳንት፣ በዚህ አዳራሽ ዳግም የምንገናኝ አይመስለኝም፣ … እርስዎም 50 ሚልዮኑን የኢትዮጲያን ህዝብ በደም ባህር ማግደው፣ ቆስቁሰው… ለእሳት ዳርገው።… የቴዎድሮስን ፅዋ ከመጠጣት በቀር ሌላ የለዎትም። ይሄን እንዳማያበላሹትም አምናለው…! ይሸሻሉ የሚል እምነት የለኝም። እግዚአብሄር ምስክሬ ነው! መንጌ! እዚያችው እተቀመጡባት ወንበርዎ ላይ ቋንጣ ሆነው እንደሚቀሩ አምናለው። እግዚአብሄር ምስክሬ ነው! ይህን ባያደርጉ ግን ታሪክ ይፋረድዎታል። ኮሎኔል መንግስቱ ለጳጳሱ በሆዳቸው መልስ ሰጡ። "ወይኔ መንጌ፣ እንዲህ ልደፈር? የማን አባቱ ቀልቃላ ደብተራ ነው? እስኪ ያማከርኩት አይመስልም? ቴዎድሮስ ራሱን ያጠፋው በዘመኑ አይሮኘላን ስላልነበረ መሆኑን መረዳት እንዴት ያቅትሃል? ወዳጄ ለዚህ ልግምተኛ ህዝብ ብዬ ትርጉም አልባ ሞት እንድሞት ያምርሃል? በፍፁም አልሞትም!!" …ኮ/ል መንግስቱ ከስብሰባው ቡሃላ ወደ ቤተመንግስት ቤታቸው አመሩ። ባለቤታቸው ወይዘሮ ውባንቺና ልጆቻቸው ቅዝዝ ብለው ተቀምጠው ደረሱ። … በተቀመጡበት የሳቸውን መምጣት ሲያዩ ነቃ ነቃ አሉ። አምባሳደር አስራት ሀይሌም ነበሩ። መንግስቱ የተለመደውን ሰላምታ ሰጥተው ወደ መልበሻ ክፈላቸው አመሩ። ልብሳቸውን ቀይረው ከተመለሱ ቡሃላ ሶፋው ላይ በትካዜ ተቀመጡ። አሁን የድሮው ወሬ አልነበረም። የቤቱ ድባብ ያስፈራል። አምባሳደሩ አንዳች ነገር መናገር የፈለጉ ይመስላሉ። መንግስቱ ለመስማት ፍቃደኛ አልነበሩም። ለውጦቹን አንድ በአንድ እያነሱ መጣል ጀመሩ። በበታቾቻቸው መደፈራቸው፣ የሚያምኑት የሚታዘዛቸው ሰው መጥፋት… " ወይኔ መንጌ መጨረሻዬ ይህ ሆነ! ግንፍል ብሎ የመጣ እንባ ተናነቃቸው። …ከሁሉ ከሁሉ የነደዳቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመፈንቅለ መንግስት ተይዘው የነበሩ ጄነራሎች መረሸን መቃወምና፣ የሳቸውንም ፎቶ ማቃጠላቸውን ሲሰሙ ነበር። መረጃውን ያደረሱላቸውን ኮ/ል ተስፋዬ ወልደስላሴ ነበሩ። "ይሄ መንጋ ተሽካላ… የድሃ ልጅ!! ብስጭት አሉ። "እሱ ተምሮ ሀገር ሊቀይር? ምን ያድርግ ያጠገብኩት እኔ!! እናቱ አሳይታው የማታውቀውን ምግብ ሲውጥ እንዴት አይጥገብ?" መንጋ ያላዩ ልጅ ሁላ!!" መንግስቱ በስሜት ተውጠው ስልክ አነሱ። ለኢሰፓ አንደኛ ተጠሪ ሻለቃ እንዳለ ተሰማ ደወሉ። "ጓድ!! ረብሻ ያነሱ ቀንደኛ ተማሪዎችን አጣርታችሁ በሁለት ቀናት ውስጥ እርምጃ ትወስዳላችሁ።"ስልኩን ዘጉት። በሶስተኛው ቀን እነዚሁ ባለስልጣናት ተመልሰው መንግስቱ ቢሮ መጡ። ቀንደኛ የተባሉትን 25 ተማሪዎች፣ ስም ዝርዝራቸውን አቀረቡ። መንግስቱ የተማሪዎቹን ስም የያዘውን ወረቀት በአይናቸው ከመረመሩ ቡሃላ "የማጣራት ሂደቱን ከጨረሳችሁ ጓድ ተስፋዬ ትቀጥላህ!! ባለፈው እንደተነጋርነው እርምጃ ትወስድባቸዋለህ። "የእጃቸውን ትሰጣቸዋለህ!! ማለት ነው። ባለስልጣናቱን አሰናበቱ። ቀጥለው ቢሮቸው የገበቱ ኮ/ል ፍሰሃ ደስታና ኮ/ል ተካ ቱሉ ነበሩ። መንግስቱ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው አዮዋቸው። …የውድቀት ዜና አምጥተው ይሆን? ምንም ይሁን ግድ አልነበሯቸውም። ምን ያልወደቀ ነገር አለና? አድሜ ለዚህ መንጋ በርሜል…ሁሉ "ኮ/ል ፍሰሃ የመጡበትን መናገር ቀጠሉ…"ጓድ መንግስቱ፣ አንድ ነገር ልንለምንህ ነው አመጣጣችን ትላንት ጄኔራሎቹን ገደልን፣ በዚህ በተከበብንበት ወቅት፣ ለጋ ተማሪዎችን ብንገድል ህዝብ ምን ይለናል?…ባይሆን እንደ አባት መክረን ዘክረ… መንግስቱ አላስጨረሱትም ድንገት ቱግ አሉ…" አጣርታችሁ እርምጃ ውስዱ አልኩ እንጂ… መች ይገደሉ አልኩ? ቆይ ምንድነው ነገሩ? ብብቴ ስር እየተሴረብኝ ያለው ሴራ? ጠረጴዛውን በቡጢ ነረቱት… "ጓድ እንደሱ ከሆነ ችግር የለም። ለደህንነትዎ አስበን ነው። ብለው ኩምሽሽ እንዳሉ ተያይዘው ከቢሮ ወጡ።" ጊዜው በሮ የግንቦት ወር ገባ። … ከሎኔል መንግስቱ ከዚህ ቡሃላ አንድ ታላቅ ዘመቻ ወጠኑ። በሳቸው የሚመራ ሰራዊት አከማቹ። ማዘዣ ጣቢያው ከሪሙ ላይ አቆሙ። በመሃል ለአስቸኳይ ስራ፣ አሰብ ደርሰው ከቀናት ቡሃላ ሲመለሱ ከሪሙ ያዘጋጁት ጦር በቦታው አልነበረም። ተበሳጭተው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ። ሌላ አስደንጋጭ ዜና ጠበቃቸው። የወሎው ማዘዣ ጣቢያ ነቅሎ ደብረብርሃን ሰፍሯል። ቢሆንም በፊት እሳቸው ሳያውቁት አይሞከርም ነበር። የኢአዴግ ሰራዊት የአንቦን ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ተቆጣጥሮ… ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ጉዞ ጀምረዋል። መንግስቱ ይህን ጉዞ ለመግታት አንድ ታላቅ ጦርነት ለማንሳት ተነሱ። ሁኔታዉን ለመረዳ በሄሊኮፕተር አንድ ኮረብታ ላይ አረፉ። ወርደው ቁልቁል ተመለከቱ። ሠራዊታቸው ወደ አዲስ አበባ ይተማል። አስራ ሰባት አመት ሙሉ ያቆሙት እልፍኝ ሲፈርስ… ፍርስርስ ማለቱን ውስጣቸው ቁልጭ አድርጎ ነገራቸው። ወይኔ መንጌ መጨረሻዬ ይህ ሆነ? ለደቂቃዎች በዝምታ ተዋጡ። እንጥላቸው ዱብ… ሀሞታቸው ፍስስ… ቅልጥማቸው ድቅቅ… ወገባቸው ዛለ… ጉልበት ከድቷቸው ተንገዳገዱ። ራቅ ብሎ አንድ ድንጋይ ታያቸው። ሄደው ቁጭ አሉበት። እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም… ፈሰሰ። በጉንጫቸው ተንሸራትቶ ሱሪያቸው ላይ ተንጠባጠበ። አብረዋቸው የነበሩ ባለስልጣናት በብዙ ልመና ከተቀመጡበት አስነሷቸው። እንዳቀረቀሩ ወደ ሄሌኮኘተራቸው ገቡ። … ሄሊኮፕተሯ እንደተነሳች ተቀምጠውባት የነበረው ድንጋይ በዙ 50 ካሊበር መሳሪያ… ድው!?… ፍርክስክሷ ወጣ። "ነው እንዴ…? አሉ መንግስቱ ሀይለማሪያም!! ሽቅብ ይዛቸው በምትወጣው ሄሊኮፕተር መስታወት ቁልቁል እያዩ … "ይሄ ፈፅሞ የጠላት ጥይት አይደለም። የጄኔራል ገዝሙ ስራ ናት!!" አሉ። ተስፋ መቁረጥ በደማቸው ተሰነቀረ። ከዚህ ቡሃላ ጥያቄው የግል ህይወታቸውን ማትረፍ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ታያቸው። ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። በሚቀጥለው ቀን ጧት ወደ ዚምባብዌ የሚበር ቻርተር አውሮፕላን አዘዙ። ወ/ ሮ ውባንቺና ልጆቻቸው ጓዝ ጥቅለላ ይጣደፋሉ። አምባሳደር አስራት የመንግስቱን ዋና ዋና ንብረቶች ያዘጋጃሉ። መንግስቱ ጥድፊያቸውን ያላዩ መስለው አለፏቸው። ጥቁር ገፃቸው ከሰል መስሏል። የቤተመንግስት ምግብ አብሳይ ሴቶች እየሰሟቸው ምፅ! ብለው ከንፈር ይመጣሉ። ከሁሉም የመረራቸው ይኸው የሰዉ የሀዘኔታ አተያይ ነበር። ከቁርስ ቡሃላ አራት ጠባቂዎቻቸውንና ሻለቃ ደመቀ ባንጃውን አስከትለው በሁለት ሽፍን መኪናዎች ተሳፍረው በ10ኛው በር በኩል ወጡ፣ ወደ ቦሌ። በመኪናው ጥቁር መስታወት አሻግረው ወደ ውጪ ተመለከቱ። አዲስ አበባ በቁሟ አንቀላፍታለች። ከግንባር ሸሽቶ የመጣው ሰራዊት ጠመንጃዉን ያለ ወጉ ይዞ ከልተም ከልተም ይላል። ሰዎች እየከበቡ በጥያቄ አሳራቸውን ያበለሏቸዋል። "መንጋ አዛባ … ቂጡን ቆልፎ አይዋጋ ይሸሻል። ይኸው ለዚህ ውርደት አበቃኝ። እስቲ ኢትዮጲያ የኔ ሀገር ብቻ እንደሆነች ይረከባት። ይሄ ወረኛ ህዝብ እንደ አለት ተጋግሮ ዝም ያለው እኔ ብቻ የምጎዳ መስሎት ከሆነ ይቅመሰው። … አስጎንብሶ በጉማሬ ሲዠልጠው ያኔ መንጌ መንጌ ይላል!!ኢትዮጲያን ፈርሞ አስረክቦኛል እንዴ?"! መኪናዎቹ ተከታትለው ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ገቡ… ምንጭ ፣= (የቄሳር እንባ (ሀብታሙ አለባቸው) ነው።) ወገሬት!!

Monday, June 27, 2016

ሰላማዊቷ ሌሊት

" ሰ ላ ማ  ዊ   …   ሌ ሊ ት"
#ሳteናw

… በዛ ውድቅት የረመዳን ሌሊት ከየት መጣ ያላልነው ፍሬን የበጠሰ መኪና፣ እየተንደረደረ… ቀኛችንን ይዘን በቆምንባት በጠባቧና ቁልቁለታማው መንገድ ከላበላያችን መጣብን። መኪናው ወደኛ መኪና ባለው ፍጥነት ሁሉ ይጋልባል… ካለንባት መኪና ወጥተን እንዳናመልጥ መኪናው ደርሶብናል… ሁላችንም ካሁን አሁን ያለንባትን D4D መኪና  ከፊትለፊታችን ወደሚገኘው ገደላማ… ውስጥ ጠራርጎ ይዞን ገባ በሚል ድንጋጤ ከቁጥጥራችን ውጪ የሆነ ጩኸት ለቀቅን… ስናልቅ ላለማየት አይኖቻችንን ጨፈንን… ጓ … ጓ…ገጭ… ግግው…ጓ…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

①እኛ፣ቁርዓንን፣በመወሰኛይቱ፣ሌሊት፣አወረድነው።
②መወሰኛይቱም፣ሌሊት፣ምን፣እንደኾነች፣ምን፣አሳወቀህ?።
③መወሰኛዪቱ፣ሌሊት፣ከሺሕ፣ወር፣በላጭ፣ናት።
④በርሷ፣ውስጥ፣መላዕከቱና፣መንፈሱ፣በጌታቸው፣ፈቃድ፣በነገሩ፣ሁሉ፣ይወርዳሉ።⑤እርሷ፣እስከ፣ጎህ፣ድረስ፣ሰላም፣ብቻ፣ናት።(አል ቀድር)

  ይህቺ በቁርዓን ሰላም የተሰኘችዋ ሌሊት በረመዳን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ውስጥ እንደሆነች በተለይም በጎዶሎ ቁጥር ቀናት በ21/ 23/ 25/ 27 /29 /ውስጥ ልትሆን እንደምትችል በተለይም 27ኛዋ ሌሊት ጥርጣሬው እንደሚልቅ በተጨማሪም ይህች ሰላም የተባለችው ለሌት ብዙ ምልክቶች እንደሚታይባትም ነቢያዊ አስተምህሮት ይገልፃል።
ከነርሱም ውስጥ… ለሊቱ ሞቃታማም ብርዳማም ሳይሆን ሠላም የሆነ ለሊት ከሆነ ምናልባት ዝናብ ሊጥል ይችላል ከዚህም በተጨማሪ በንጋቱ ፀሐይ እንደወጣች ያላት ብርሃን (የጨረር) መጠን ትንሽ ለማይባሉ ደቂቃዎች አይንን ሳይጎዳ ወደ ፀሀይ መመልከት መቻሉ ነው።)

••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  ረመዳን 27 ለይልን ሳስታውስ ሁሌም አምና ረመዳን ያሳለፍኳት ይህቺ ሌሊት ፊቴ ላይ ድቅን ትላለች…

   ጓደኛዬና ሚስቱ (ዘመዴ ነች)፣ በያመቱ ረመዳን ያስለመዱትን ገጠር ሄደው ሰደቃ ለማውጣት እኔና የሚስቱን ወንድም ጨምረው እንደምንሄድ ተነጋግረን። ረመዳን 27 ለይል ከኢሻ መልስ በጓደኛዬ ቤት ተገናኘን። አንድ ቀን በጓዴ ቤት፣አንዱ ቀን በሚስቱ ቤት ሰደቃውን ለማድረግ ታቅዶ ጉዟችን በ27ኛዋ ሌሊት ኢንዲሆን ተወሰነ። ከእራት ቡሃላ ትንሽ ተቀማመጥን፣ መተኛት ቢያሰኘንም መተኛቱን ትተን ተቀመጥን መጨዋወት ያዝን። ምሽት ላይ ትንሽ ዝናብ ጣለ ቢሆንም የአየሩ ሁኔታ የማይሞቅም የማይበርድም ነበር። ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በመካከላችን እርጋታ ሰፍኖኗል። የጓዴ ባለቤት ቡና ከጠጣች ቡሃላ ጉዞ ስንጀምር እንድንቀሰቅሳት ነግራን ሄዳ ደቀሰች። ሌላጊዜ በረባ ባልረባው የምንነታረክ ልጆች በዚህች ቀን አስሬ ዱዓ ስናደርግ፣ የምናውቀውን ቂሳ ስንናገር አረፈድን።  የመሄጃችን ሰዓቱ ሲደርስ… ቀስቅሰናትና… ሱሁር በልተን… የፈጅርን ሰላት መንገድ ላይ ለመስገድ ወስነን …  ጉዞ ጀመርን።

   የሌሊቱ አየር ደስ ይላል ጥርት ባለው ሰማይ ላይ ከዋክብት ብልጭ ድርግም እያሉ ይጠቅሱናል… ከዚህም ከዚያም ይሰሙ የነበሩ የውሾች የማላዘን ድምፅ ደብዛው ጠፍቶ በምናልፍበት መንገድ ሁሉ የመስጂድ ድምፅ ማጉሊያዎች… የለይል ሰላትን ቁርአን ብቻ ያስተጋባሉ። ደስና አርግት ያለ ለሌት ነበር። ከከተማ ሳንወጣ ጓደኛዬ አንድ ገጠር ስትሄድ ትወስደኛለህ ያሉኝ አዛውንት ስላሉ እሳቸውን ፒክ እናድርጋቸው ብሎ፣ መኪናዋን ለሚዘውራት የባለቤቱ ወንድም ነግሮ … ሰውዬው ወደሚገኙበት ሰፈር ሄድን።ደረስን።

    ሰፈሩ ዳገታማና  ወጣ ገባ የሚበዛበት ከመሆኑ የተነሳ የአዲስ አበባ ምድር አይመስልም። በዚህ ወጣ ገባማው መልከአ ምድር ላይ የተገነቡት መኖሪያ ቤቶች አቀማመጣቸውን በርቀት ስታይ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርበው ሰርከስ የሚሰሩ ይመስላሉ። አብሮን ከሚጓዘው ሰውዬው ቤት ከግቢ በር ደረስን። ከአጥሩ ውጪ የቆምንበት ኮብልስቶን መንገድ ሲሆን  ከፊታችን የተዘቀዘቀ ቁልቁለት ከኋላችን ከተወሰነ ርቀት ቡኋላ የሚታጠፍና ደረቱን ገልብጦ የቆመ ዳገት ነበር። ጓዴ ወርዶ ከመንገዱ በስተግራ የሚገኘውን የግቢውን በር አንኴኳ። አፍታም ሳይቆይ የግቢው በር ከውስጥ ባለ ሰው ተከፈተ።  ግቢው ገደላማ ሲሆን፣ መኪናችን ቀኟን ይዛ ብትቆምም  ከመንገዷ ጥበት አንፃር መኪና ውስጥ ቁጭ ብለን ወደ ግቢው ስናይ እንደ ወለል ሆኖ የታየን የቤቶቹ ክዳን ቆርቆሮ ነበር። ከግቢው በር ወደ መኖሪያቤቶቹ የሚያደርሰው ረጅም ደረጃ መሆኑ ባናየውም ያስታውቃል።  የሰውየው ቤተሰቦች ጓዙን ከቤት ውስጥ እያመጡ መኪናችን ላይ መጫን ያዙ። እኛ መኪናዋ ውስጥ ቁጭ ብለን እስኪጨርሱ እንጠብቃለን። የጓዙ መብዛት ይሉኝታ ያሳደረባቸው የተጓዥ ታናሽ ወንድም… ወደ መኪናዋ መስኮት ተጠግተው በቃ አልቋል አንድ እቃ ነው የቀረው በማለት ወደ ጊቢው እንደዘለቁ።… በዛ ውድቅት ሌሊት ከየት መጣ ያላልነው ፍሬን የበጠሰ መኪና፣ ደረቱን ገልብጦ ከቆመው ዳገት… እየተንደረደረ ቀኟን ይዘን በቆምንባት በጠባቧና ቁልቁለታማዋ መንገድ መጣ። መኪናው ወደኛ መኪና ባለው ሁሉ ፍጥነት ይጋልባል… ካለንባት መኪና ወጥተን እንዳናመልጥ ደርሶብናል… ሁላችንም ካሁን አሁን ያለንባትን D4D መኪና ከፊትለፊታችን ወደሚገኘው ገደላማ በሆነው መኖሪያ ቤት ውስጥ ጠራርጎ ይዞን ገባ በሚል ድንጋጤ ከቁጥጥራችን ውጪ የሆነ ጩኸት ለቀቅን… ስናልቅ ላለማየት አይኖቻችንን ጨፈንን…  ጓ…ገጭ… ግግው…ጓ… ገጭ…  እያለና ድንጋይ እያነጠረው በመኪናችንና በግቢው መካከል ባለው ክፈተት የቆርቆሮውን አጥር እየታከከ… የመኪናችንን ጆሮ(ስፔኪዮ፣የጎን መስታወት) ጨርፎና አጥፎ በሚያስደንቅ ፍጥነትና ተዓምር ሽው ብሎ አለፈን። ከድንጋጤያችን ሳንወጣ ሰለጥቂት ስቶን  ቁልቁል የሚንደረደረውን መኪና ተመለከትን። መኪናው ሚኒ ባስ ሲሆን በሚጯጯሁ ተሳፋሪም ተሞቷል። የተጓዥ ቤተሰቦች ከግቢው ውስጥ የጓጓታውን ድምፅ ሰምተው ሮጠው ወጡ። ሚኒባሱ ሄዶ ሄዶ ቁልቁለቱ መሃል ወደ ሚታጠፍ ዳገታማ መንገድ እንደ ዘንዶ አየር ላይ ተምዘግዝጎ ገባ። የሹፌሩን ብቃት ማድነቅ ሳንጀምር ሚኒባሱ ከአይናችን ተሰወረ። ጭንቀታችን ለራሳችን መሆኑ ቀርቶ ሚኒባሱ ውስጥ ስላሉ ሰዎች ሆነ። ከመኪናው ውጪ የነበሩ የተጓዥ ቤተሰቦች የመኪናውን መጨረሻ ለማየት እየጮኹ ተከትለውት ሮጡ። እኛ በድንጋጤ ብዛት በድን ሆነን አንደበታችን ክዶናል። አይናችን ፈጧል።አፋችን ደርቋል። ከየጊቢው የጎረቤት ሰዎች መውጣት ጀመሩ። መኪናውን ተከትለው የሄዱ የተጓዥ ቤተሰብ ለጎረቤቶቻቸው ሁኔታዉን እያስረዱ ተመልሰው ወደኛ መጡ። የሁላችንም ጥያቄ አንድና እንድ ብቻ ነበር። የሚኒባሷና የተሳፋሪዎቹ መጨረሻ። ከአንድ ክምር አፈር ጋር ተጋጭቶ ከፊት ለፊቱ መስታወት ከመሰበር ውጪ ምንም የህይወት አደጋ ሳያደርስ መቆሙን ነገሩን። ከመንገዷ ጥበት አንፃር መኪናው ምንም ሳይነካን የመትረፋችን ነገር ሁሉንም የሰፈሩን ሰዎች አያስደመመ። እዚህ ጋር የአላህ ጥበቃ ባይኖረን ከነደዚህ አይነት ስፍራ መትረፋችን የማይታመን ነበር። አብረውን የሚጓዙ ሰውዬ መጡና እዬዬያቸውን አስነኩት። አስጨርሻችሁ ነበር ልጆቼ በሚል። እኛም ባለተረጋጋው መንፈሳችን እንዲረጋጉ ካደረግን ቡሃላ በድንጋጤ የፈጅርን ሰላት መንገድ ላይ እንሰግዳለን የተባባልነውን ትተን። እዛው ሰፈር ካለው መስጂድ ሰግደን ጉዞ ለመጀመር ወሰንን። ደጋግመን አላህን ስላተረፈን እያመሰገንን፣ ስለ ሁኔታው ደጋግመን እያወራን አዛን እስኪወጣ ጠበቅን። አዛን ብሎ የፈጅርን ሰላት መስጊድ በጀመዓ ሰገድን። መንገድ ስንጀምር ትዕይንቱ በአይነ ህሊናችን እንደ አዲስ እየተመላለሰብን በመካከላችን ፀጥታ ሰፈነ። መኪናችን አለምገናን፣ ዳለቲን እየተወች ትከንፋለች። ሰማዩ ከምስራቁ በኩል ይጠራ ጀመር… ብዙም ሳይቆይ ፀሀይ ድብዝዝ ያለና ለእይታ የማያግድ ጨረሯን እያፈነጠቀች መውጣት ጀመረች።  ይህን የፀሀይ ሁኔታ ስመለከት በጣም ገረመኝ። ያስገረመኝ …  ከላይ በቁርዓንና ሀዲስ ከሺህ ወር በላጭ ናት ተብላ  ስለጠቀሠችው ሌሊት ሊታይባት ይችላል የተባለውን ምልክቶች፣ ባሳለፍነውን ሌሊት እነዚህን ምልክቶቹን ሁሉ ማየቴ ነበር፣ … ዝናብ መጣልና የማይበርድም የማይሞቅም  አየር ፀባይ፣ የተረጋጋ ድባብ፣ አሁን ደግሞ ለእይታ የማያግደው የፀሀይ ሁኔታ፣ ድጋሚ ለጥቂት የተረፍንበት የመኪና አደጋ። የምንሄድበትን ጉዳይ ጨርሰን እስክንመጣ ስለዚህች ሌሊት ደጋግመን መገረማችን ደጋገመን ማንሳታችን አልቀረም። እውነትም ሰላማዊቷ ሌሊት ብያታለው። ከዛን ቀን አደጋ የታደገን አላህ አሁንም ምስጋና ይደረሰው አሁንም ጥበቃው አይለየን።

ለማንኛውም ይህቺ ሌሊት አሁን ያለንባት የረመዳን የመጨረሻ አስር ቀናቶች ክልል ውስጥ ትገኛለች። ከትሩፋቶቿ ለመጎናፀፍ ከመቼውም በበለጠ በኢባዳችን ልንጠነክር ይገባል አላህ ለይለተል ቀደር ይወፍቀን!!! ዱአውም ለጨቋኝ ሀይሎች በግፍ ለታሰሩ ኡስታዞቻችን የሚደርስ ያድርገው!!
ወገሬት!!

Saturday, June 25, 2016

እኔን ነው?! እንዲል እከ!!

"እኔን … ነው? እንዲል…  እከ!!
#ሳteናw

… ይህ እድል ያልገጠማቸውም ሚስኪን እህቶቼ፣ ካሁን አሁን ፖሊሶች መጡብን በሚልና ባለመረጋጋት ስሜት ግራ ቀኛቸውን ይገላምጣሉ። ይህን መሰሉ የፖሊስ ፍራቻ በእነዚህ እህቶቼ ብቻ ሳይሆን በጎዳና ንግድ ላይ በተሰማሩ ወጣቶችም ላይ ይስተዋላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ፖሊስን አይቶ መሸበር የሚገባው ሌባ ብቻ በሆነ ነበር…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  አዉቶቢስ ተራ አካባቢ ታክሲ ውስጥ ተቀምጬ ታክሲው እስኪሞላ በመጠባበቅ ላይ ነኝ። … ሰአት ስለረፈደብኝ ቸኩያለው፣መረጋጋት አጥቻለው። ለነገሩ መረጋጋት የተባለው ነገር በኔ ብቻ ሳይሆን በብዙሃኑ ማህበረሰብ ውስጥ ከታየ  ሳይቆይ የቀረ አይመስለኝም። (ከምር ግን መረጋጋት የተባለው ነገር አልናፈቃችሁም? ይሄ ይሄ ብዬ ባልዘረዝረውም ሁሉም እኮ ጥድፊያ ላይ ነው፣ ለሀቂቃ!! አለ አይደል የትም የማያደርስ ጥድፌያ!!። አልሞላ ባለኝ ታክሲ በመስኮቱ አሻግሬ ምንም የተረጋጋ ህይወት የማይታይበትና የሚዋከበውን አላፊ አግዳሚ ተመለከትሁ… አይኔን ቀና አድርጌ አዲሱ የከተማ ባቡር ድልድይ ላይ የተለጠፈው ፖስተር እንደነገሩ ካየሁት ቡሃላ ነቅዬ ቁልቁል ፈጠፈጥኩት…  የአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የቴሌውና፣ የትንሹ አውቶቢስ መናኸሪያ፣ አጥሮች እንደ ሙዓመር ጋዳፊ በወጣት ሴቶች ታጅበዋል …ለዛውም ቁጥር ስፍር በሌላቸው ሴቶች። ከፊት ለፊታቸው ያለው የባቡሩ ድልድይ ስርም በመደዳ ዘርዘር ብለው በቆሙም ሴቶች ተሞልቷል። ታዲያ እነዚህ እህቶቼ ተሰልፈው የቆሙት ለታክሲ እንዳይመስልህ… ምፅ!! በምን እድላቸው!! በስራና በአማራጭ እጦት በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው መሽኚያቸውን እንደ ሱቅ መተዳደሪያቸው ያደረጉና… ይዟቸው የሚሄድ ወንድ የሚጠብቁ ምስኪን እህቶቼ እንጂ። በፊት በሰባተኛና በሌሎች ጉራንጉር ሰፈሮች ብቻ የነበረው የወሲብ ንግድ ዛሬ ላይ እንደ ካሮት ቁልቁል አድጎ በየጎዳናው ላይ ከሆነ ውሎ አደረ። ከነዚህ እህቶቻችን ውስጥ አብዛኞቹ ታዳጊ ወጣቶች ሲሆኑ የወጣትነት ዘመናቸው ላይ ሃያ አመት የጨመሩም  አሉ። በርካቶቹ ፀጉራቸውን በሂጃብ ጠምጥመው ከስር ገላቸውን እንደ መርፌ በሚጠቀጥቅው ቅዝቃዜ ብጣሽ ጨርቅ ብቻ ጣል ያደረጉ ናቸው። ከላይ የጁምዓ ከስር የቅዳሜ አለባበስ!በለው። ለምን ይሆን ሻሽ (ሂጃብ) የሚጠመጠሙት? ለጊዜው ግምቱ እንጂ እውነቱ ስላልተገለፀልኝ … እንደኔው ገምት። ወጣትነታቸውን በማገባደድ ላይ ያሉት በገፅታቸው ላይ ገበያ ለመሳብ በሚል የተጫረ አርቴፊሻል ፈገግታ ሲያሳዩ…  ታዳጊዎቹ ደግሞ ለገበያቸው ብዙም ጉጉት ሳያሳዩ ቆመው፣
እርስ በእርስ ሲስቁ ሲቀላለዱ፣ ሲላፉ፣ ይታያል… ይህን ሁኔታቸውን ስታይ አንድም ልጅነታቸው አንድም ገና በዚህች ትንሿ  እድሜያቸው እያለፉበት ያለውን መራራ ህይወት ለመርሳት በሚል እንደ ሆነ እንጂ … ደልቷቸው አልያም በስራቸው ደስተኛ ሆነው አንዳልሆነ ስድስተኛው ስሜትህ ይነግርሃል። ሌሎቹ (ቅንዝር አዳማዊያን ማለቴነው) ደግሞ እንደ በግ ገዢ አካላቸውን ከዳበሳ ባልተናነሰ እይታ… ከሚያዩና ዋጋ እንደሚነጋሩ ሁኔታቸው ከሚያስታውቅ ወንዶች ጋር ቆመው ያወራሉ። የተስማሙትም ገንጠል ብለው ተያይዘው ይሄዳሉ።… ይህ በለስ ያልገጠማቸውም፣ ካሁን አሁን ፖሊሶች መጡብን በሚል ግራ ቀኛቸውን ባልመረጋጋት ስሜት ይገላምጣሉ። ይህ የፖሊስ ፍራቻ በእነዚህ እህቶቼ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም ላይ አለ። እንደ እውነቱ ከሆነ ፖሊስን አይቶ መሸበር የሚገባው ሌባ ብቻ በሆነ ነበር
ይህን ትዕይንት ስመለከት ለአፍታ የራሴን ችግር ትቼ በነዚህ እህቶች ዙሪያ ራሴን ስብሰባ ጠራው…

  መቼም እያንዳንዳቸው ህይወት ጀርባ ለዛሬው አስከፊ ህይወት የዳረጋቸው የተለያየ የህይወት ገጠመኝ ቢሆንም። ዞሮ ዞሮ አንድ የሚያደርጋቸው ነጥብ አለ። ችግር !!። በዚህ ቅዝቃዜው ጣት በሚቆረጥም ብርድ፣ እስቶኪንግ ብቻ አስለብሶ፣ የውሸት ፈገግታ አላብሶ፣  ለገበያ ያወጣቸው ነገር ቢኖር ፣ ችግር መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው። ታዲያ ሌላ ስራ አይሰሩም ወይ? ብዬ በውስጤ እንዳልወቅሳቸው፣ ዛሬ ላይ ያደረሳቸውን መንገድ በግልፅ ሳላውቅ መውቀሱ ሞራል አሳጣኝ። ግን አንድ እውነት አለ!! የትኛዋም እህት ወደዚህ ስራ በፍላጎቷ የገባች እንደማትኖር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በዛው መጠን ይሄን አስነዋሪ ስራ አንሰራም ወይም አንሰርቅም ብለው በጎዳና ላይ ንግድ የተሰማሩ ወገኖቸም በአማራጭ እጦት ነው እንጂ በፍላጎቱ ሌባና ፖሊስ መጫዋት ስላማረው ነው የሚል እምነት እንደሌለኝና ይህንንም ሀሳብ እንደምታጋሩኝ አምናለው።  አስነዋሪም ሆነ ህገ ወጥ ስራዎች የሚቀረፉት፣ ብዙ የስራ አማራጮች ሲፈጠሩ ነው። ይህ ሊፈጠር የሚችለው በአስተዳደር በኩል ነገራቶች ሲመቻቹ መሆኑ ለማንም ያልተሰወረ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የስራ አማራጭ ላጣ ህዝብ የሚጠቅመው አማራጮችን ማቅረብ እንጂ አሯሯጮችን አሰማርቶ የአማራጭ መጨረሻቸውን መንፈግና ማስነጠቅ እንዳልሆነ ቅን ልቦና ያለው የሚያውቀው ሀቅ ነው። የሚበላው እስኪያጣ የተቸገረ ህዝብ የፈለገውን ሰርቶ ቢያድር አይፈረድበትም። መቼም ይሄን ሳያውቅ የሚቀር ነጂም ተነጂም እንደማይኖር አውቃለው። እንዲያው ነገሩ ቢጨንቀኝ ቢጠበኝ፣ ነው!! ለአመልህ ድከም ሲለኝ!!

…ግን ደግሞ ይህን ከልቤ ተመኘው!! አለ አይደል ጀሊሉ ብሎልኝ! የዳንጎቴን ወይም የሸሁን ሩብ ሀብት ቢኖረኝ ማለት ነው… [ከልቤ ነው! መርቅኜ ምናምን እንዳይመስልህ!]

  እነዚህንና በመሰል ስራ ላይ የተሰማሩ እህቶቼን ቅድሚያ የስራ እድል የሚሰጥ … ልክ እንደ … ምንድነው እሱ ሚሉት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ!… ምነው ይሄ ዳለቲ ያለው … ስሙ እኮ… ምላሴ ላይ… አለ! … እንደውም… በያመቱ ለዘንዶ ይገብራል እየተባለ የሚታማው… አዎ!! አይካ አዲስ። እንደሱ አይነት!! በተለያዩ ስፍራዎች በተለያዩ አይነት ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ ድርጅት አቋቁሜ፣ የስራ አማራጮች በገፍ እንዲሆኑ  አድርጌ  … ህይወታቸው ከአስነዋሪው ስራ አውጥተው በተመቻቸው የስራ አማራጫቾች በመረጡትና በፈለጉት ስራ ተሰማርተው፣ አንደ ሰው፣ ሰርተው ተቀይረው ሀገር የሚቀይሩ ሀይል  ባደረኳቸው። ብዬ ተመኘው። መቸም ምኞት አይከለከል። የሚሞላው እሱ ነውና።

… የተሳፈርኩበት ታክሲው ሞላና መንቀሳቀስ ሲጀምር… ከሀሳቤም ከምኞቴም ተመለስኩ። አዲሱ የከተማ ባቡር ድልድይ ላይ ተለጥፎ ያየሁትን ፖስተር ድጋሚ ተመለስኩት… ፅሁፉን አነበብኩ። ያነበብኩትን ተጠራጥሬ… የአይኔን ሽፋሽፍቶች በጣቶቼ አሸት አሸት አድርጌ ብሌኔን ወለወልኩና… ድጋሚ ፅሁፉን አነበብኩት…እንዲህ  ይላል።
"…የህዝቦቿን ተጠቃሚነትና አንድነት ያረጋገገጠች ሀገር!!"
"እኔን ነው! አለ እከ!!
ወገሬት!!

Thursday, June 23, 2016

"እ ድ ሜ ለ ማ ር ክ ዙ ከ ር በ ር ግ "

"እ ድ ሜ … ለ ማ ር ክ … ዙckerbueg"
#ሳteናw
ድሮ ድሮ የሀገሬ ኢንተርኔት ቤቶች እንደ ቁጥራቸው ተጠቃሚያቸውም ውስን ነበር። ተጠቃሚዎቹም ወይ ድግሪ ወይ ማስተርስ ያላቸው ጥቂት የተማሩም ሰዎች ነበሩ። በዚህ የመጣ የኢንተርኔት ቤት ወንበሮች በተጠቃሚ እጦት ከሰው ይልቅ በአቧሯ መርግ ይሞሉ ነበር። ድሮ ነው ታዲያ… ዛሬስ? እድሜ ለማርክ ዙከርበርግ የተማረውንም ፣እንደኔ ያለው ቴንኘላስ ምላስ የሆነውም፣ ፊደል የቆጠረውንም በፌስ ቡክ ሰበብ ኢንተርኔት የተባለውን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም፣ ኢንተርኔት ቤቶችን በተጠቃሚም፣ በገቢም እንዲጨናነቅ ላደረገው አሜሪካዊው ጉብል፣ እድሜ… አዋራ አራግፈህ ትጠቀምበት የነበረው የኢንተርኔት ቤት መቀመጫ፣ ዛሬ እንደቆመ ባስ ተሳፋሪ የሚለቀቅ ወንበር ጠብቀህ የመጠቀም ወጉ እንዲደርስህ ላደረገው ወጣት ማርክ።
እርግጥ ነው አልዋሽህም!! ፌስቡክ ፌብሩዋሪ 4/2004 ከመወለዱ በፊት የቀደሙ ማህበራዊ ድህረገፆች እንደነ yahoo… gmail ቢኖሩም ተጠቃሚያቸው እንደ ዛሬው ሰፊው ህዝብ አልነበረም።

[(በነገራችን ላይ የፌስ ቡክ መለያ ቀለም ለምን ሰማያዊ እንደሆነ ታውቃለህ? መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ቀይና አረንጓዴ ቀለም አይቶ የመለየት ችግር ስላለበት ነው። አሉ ነው። ማጣራቱ ያንተ ፋንታ ነው! ለማንኛውም ይህን ምርጥ ልጅ በፌስቡክ ማግኘት ካሰኘህ መደበኛው የፌስቡክ አድራሻ ላይ 4 ቁጥርን ጨምረህ( facebook.com/4 ) ፈልገው ከደማቅ ፈገግታው ጋር ታጅቦ ድቅን ይልልሃል። 5 እና 6 ካስገባህ ደግሞ መስራች ጀለሱካዎቹን ታያለህ)]

ፌስቡክ ከመጣ ወዲህ የኢንተርኔት ተጠቃሚው እንደ አሸን ፈልቶ ቁጥሩም አደገ። አድገ ስልህ የፊስቡክ ተጠቃሚ እንጂ የነብስ ወከፍ ገቢ እንዳልሆነ መቼም አታጣውም። ዛሬ ላይ ህዝቤ የከበደው የፌስቡክ መክፈት ሳይሆን የባንክ አካውንት መክፈት እንደሆነም አይጠፋህም።
የጋራችን አለም ድሃና ሀብታሙን በኑሮ ደረጃ ብትለያየውም፣ ኪስን ሳያይ አንድ አድርጎ ፌስቡክ ሰበሰበው። አብዛኛውን ሰው ይህን ተከትሎ ከፌስቡክና መሰል ድህረገፆች በደንብ ተዋወቀ። ይህን ቀድሞ የባነነው ቴሌም ኢንተርኔትን ወደ የሞባይላችን መስኮት አቀረበው። ግንምን ዋጋ አለው? ፌስቡክ አንድ ቢያደርገን፣ ቴሌ በሞባይል ካርድ ፍጆታ አራራቀን። ድሮስ ጠላት ከሩቅ አይመጣ!!

ፌስ ቡክ የተራራቁ አህጉራትን፣ ለቡና እንደምትጠራራው ጎረቤት አቀራርባል። በተለያየ የአለም ክፍል ያሉ ሰዎችን በአንድ ሰሌዳ አሰባስቧል። አንደኛውን አለም ከሶስተኛው አለም በአየር ላይ ምንኗኗረውን ሌላ አለም ፈጥሯል። የመረጃ ልውውጡም በዛው መጠን አሳድጓል። የአለም ትኩስ ዜናዎችን በየሞባይል እስክሪንህ ላይ ገና የትኩስነት ጭሳቸው እየተንፎለፎለ አንኳኳተው ከች ይሉልሃል።

እናልህ…! ከዚህ ከፌስቡክና መሰል ማህበራዊ ድህረገፆች ጋር መምጣት ተያይዞ ብዙ ለውጥ በሀገራችን መጥቷል። መልዕክት ለመለዋወጥ ፖስታ ቤት የፖስታ ሳጥን ከመክፈት በተንቀሳቃሽ ስልክህን ወይም በዴስክ ቶኘህ inbox ወደ መክፈት አሸጋግሯል። ወጣቱን ፎቶን በዋሌት ቦርሳው ከማስቀመጥ፣ ፌስ ቡክ ላይ ወደ ማስቀመጥ አራቆታል። በዚሁ ሰበብ ጠበሳውም፣ጅንጀናውም ንሯል። ለመጠባበስ የፕሮፋይል ፎቶዎች በእጅ ስራ ጥበብ፣ ተወልውለው፣ተኩለው አምረዋል። ይህን አይተህ፣ከአንዷ ጋር ተቀጣጥረህ በአካል አግኝተህ ስታያት ፎቶው የራሷ መሆኑ ያጠራጥርሃል። ወይም ቀጥረህ ስጠብቃት የውሃ ሽታ ከሆነችብህ ወንድ በሴት አካውንት ተሞዳምዶብህ ይሆናል። በዚህ አላበቃም የአየር ላይ አለማችን፣ ጥንዶችን አየር ላይ ኘ አግባብቶ፣ በገሃዱ አለም አጋብቶ አዋልዷል። በዛው መጠን ሰላማዊ የነበረን ትዳር አበጥብጧል። ተግባብቶ የተጋባውን፣ባለመስማማት ግራ አጋብቶ አፋቷል።

ቺክ ለመጥበስ በፍራቻ ብዛት ቃላት ያጥረው የነበረው ሰውዬ፣ ዛሬ በፌስቡክ ጠበሳ አንድ ፊደል ሲፅፍ የቃላት አማራጭ የሚገጠግጥለት ኪቦርድ ገላግሎታል። በሌላ በኩል በተደረገው ጥናት ኢንተርኔት መሀይምነትን በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል። በፅሁፍ መልእክት ለመግባባት ለግዱ Amharic english የፈደል ገበታ እንዲያጠና አስገድዶታል። በፊት በወር አንዴ የምትጠብቀው ከዘመድ አዝማድ የሚደወል የውጪ ስልክ፣ ዛሬ በየደቂቃው ሆኗል። እድሜ ተያይዘው ለመጡት ለነቫይበር፣ለነ ዋትስ አኘ ና ኢሞ፣ የተጠፋፋውን ወዳጅ አገናኝቷል። የተራራቀን ቤተሰብ አቀራርቧል። የመኝታ ቤት በርህ ሳይንኳኳ፣ ከሳሎን "እራት ደርሷል ና ትባላለህ … በኦን ላይን።

ይህ መልካም ሆኖ ሳለ የነፃነቱ ልክ ወሰን አልፎ ስድ ነገሮችንም፣ ድርቅ ያሉ ውሸቶችንም አቅፏል። ከዌብ ሳይታቸው የሸሸሃቸው አፀያፊ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በጋጠ ወጦች ተፖስቶ ሳትፈልግ በፌስቡክህ ላይ ገጭ ይሉብሃል። ከላይ የሀይማኖት ትምህርት እያነበብክ ከስር ይሄ ጉድ ብቅ ይላል። ቤቱ ተቀምጦ ከልጆቹ ጋር የሚፈነድቀውን ታዋቂ ግለሰብ "ሰበር ዜና! አከሌ አከሌ ዛሬ አረፈ? ይሉሃል። ውሸቱም በዛው ልክ ነው፣ የዜናውን እውነት፣ እንደ ወርቅ ማዕድዕን ከጭቃ እንደሚጣራው አጣርተህ ማረጋገጥን ይጠይቃል።

[(በነገሬ ላይ አፀያፊ ምስሎችን በአካውንትህ ላይ እንዳይለጠፍብህ ለማድረግ setting ግባ timeline and tagiging ግባ who can post your timeline? ግባ only me አደርገው አለቀ።)]
አንድ ሰው ሶስት የፌስ ቡክ አካውንት በመክፈት አንድም ሶስትም መሆንን ችሏል። በዚህ የመጣ ከ8—10 % የሚሆኑት የፌስቡክ አድራሻዎች ፌክ ናቸው። በፌስ ቡክ አንድ ሰው ከፈለገ የሀይማኖት መምህር፣ ልቅና ስድ፣ ደፋ ር ፖለቲከኛ ይሆናል። በገሀዱ አለም አዋቂ ነው ትውልድ የሚያቀና ነው የምትለው ሰውዬ በነ ፌስቡክ ትውልድ የሚያበላሽ ቪዲዮ ይለቅብሃል። አመለ ብልሹ ያልከው በፌስቡክ ላይ የሀይማኖት መሪ፣ እኔ ብቻ አዋቂ የሚል ይሆንብሃል። ማንነትን እንዳሻህ ለመከረባበትም ፌስቡክ ሁነኛ መድረክ ሆኗል። ደግሞ የቤቱን አመል ይዞ ፌስቡክ የሚመጣብህም ሞልቷል።

መች በዚህ በቃ በግልፅ የማታደርጋቸው ድርጊቶ፣ ማህበራዊ ድህረ ገፅ ማድረግ አስችሏል። ማንነትህን ደብቀህ ባለስልጣንን በፔጁ በኩል ብትኮንን፣ ግፋ ቢል አካውንትህን የመሰበር ሙከራ ይደርስበታል እንጂ፣ ማእከላዊ ታጉረህ በዱላ ብዛት እግርህ አይሰበርም። መንግስትን ለመቃወም ከድንጋይ ከመወርወር ወደ ቃላት መወርወር አሸጋግሯል። ይህም ከመንግስት ሀይሎች የሚመለሰውን የጥይት ቃንቄ አስቀርቷል። እንደምታውቀው ሀያል መንግስታት በሶሻል ኔት ሰበብ ተገርስሰዋል ግብፅና ቱኒዚያን መውሰድ ትችላለህ። ይህ ውጤት የሰራው እንደኛ በበነነ ተነነው ለተለያየ ህዝቦች ሳይሆን፣ በአላማ አንድ ለሆነ ህዝብ ነው። እናልህ! … ከአንባገነን መንግስታት የታጣውን በነፃነት ሀሳብን የመግለፅን መብት ፌስቡክ መልሶታል። ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ በላይ ምን የህሊና እረፍት የሚሰጥ ነገር አለ?። ይሄው እኔስ ዛሬ ሃሳቤን ማካፍልህ በዚሁ ፌስቡክ አይደለም? ነው።

እንግዲህ እነዚህንና ዘርፈ ሰፊ ለውጥ በፌስ ቡክ ሰበብ ተፈጥሯል። ይህን ዘርፈ ሰፊ ለውጥ ለበጎም ለክፉም የማዋሉ ስልጣን በመዳፋችን ላይ ነው። በፌስቡክ መማማር፣ ጠቃሚ ሃሳቦችን መለዋወጥ፣ የሚቻለው እንደ አጠቃቀማችን ነው። ለአንድነት፣ ለነፃነት፣ ለመልካም ለውጥ፣ ለተሻለ አስተዳደር ጥቆማ ወዘተ ለማዋል አድርገን የምንዘውረው እኛው ነን። ድንቁ ማርክ ያበረከተልንን በዚህ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ለጋራ ጥቅማችን ቢሆን ድንቅ ይሆናል!! እላለው። ለማንኛውም የፌስ ቡክና መሰል የማህበራዊ ድህረ አጠቃቀማችን ያሳምርልን!! ከማለት ውጪ ምን ማለት ይቻላል? ምንም!!
ወገሬት!!

Monday, June 20, 2016

"ጓ ዴ ሌላኛው ፓፒዮ"

"ጓዴ (ሌላኛው ፓፒዮ)"
#ሳteናw
መግቢያ
     በጓዴ መኪና አዲስ የሰራውን  ቤት ምርቃቱ ላይ ፣(ተሰርቶ እስከሚያልቅ ተመላልሼ ባየውም) የድግሱ ታዳሚ ለመሆን አብረን እየሄድን ነው። ጓዴ ዛሬ በደንብ መሰረቱ የረገጠ ህይወት ከመጎናፀፉ በፊት ያሳለፈውን የህይወት ውጣ ውረድ አንድ በአንድ በአይኔ ላይ ይታየኝ ጀመር… ቀጥሎ የምተረተርልህም ይህንኑ ነው። የህይወት ስንክሳር ለሱ ብቻ የተመደበለት ይመስል የወጣትነት ዘመኑን በመከራ ጋጋታ አስተናግዶ በስተመጨረሻ የተረጋጋ ህይወት ስለገጠመው የቅርብ ጓደኛዬን ታሪክ። (ጓደኛዬ ስልህ እንደኔ ወጠጤ እንዳይመስልህ የአስር አመት ልዩነት በመካከላችን አለ)። ልቸከችክልህ ያነሳሳኝ የሱን የህይወት ውጣ ውረድ ለብዙ ሰው እንደ ፈረሳዊው ፓፒዮ ምርጥ ምሳሌ ሊሆን የፅናትን መጨረሻና ተስፋ ያለመቁረጥን ያማረ ውጤት …  ለሌላው መማሪያነት በሚል እሳቤ ነው ። (በነገራችን ላይ የፖፒዮን ታሪክ አንብበከዋል? ካላነበብከው እመነኝ ታድለሃል!! እንዴት ማለት ጥሩ! አየህ ስለሱ ታሪክ የተተረጎመውን መፅሃፍ በአዲስ መንፈስ ተመስጠህ ታነበዋለህ። የታሪኩ አወራረድ ልብህን እንዴ ሲያንጠለጥል አንዴ ሲያረጋጋህ አንዴ ሲጥል አንዴ ሲያነሳ በራሱ ሪትም እያወዛወዘ እያስተማረህ …  ይዞህ እስከመጨረሻው ይጓዛል። መጨረሻውን ሳታውቅ ለማንበብ አድሉ ስላለህ ነው ታድለሃል ማለቴ። አሁን ግን በግሌ የፅናት ምሳሌ አድርጌ ወደ ምወስደው ጓዴ (ሌላኛው ፓፒዮ) ታሪክ ላሳፍርህ…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 1
… ሀቅ ያወጡልኛል ፍትህ ያስገኙልኛል ብሎ ተስፋ ጥሎበት የነበረው የሽምግልናው ሂደት ለካደው ባለ ሀብት ካደላ ቡሃላ። ያደረገው ተስፋ ቆርጦ ትላንት እንደ ባለቤት ሙሉ ጊዜውን ሰውቶ ይሰራበት የነበረውን ሱቅ ለካደው ለባለሀብቱ አጎቱ ትቶ ቤሳቤስቲን ሳይዝ ጥሎ ወጣ…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
  ምዕራፍ 2
     ጓዴ ፓፒዮ አዲስ አበባን የረገጠው በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር። በእናቱ ወንድም ምክኒያት። አጎቱ በመርካቶ ክልል አነስተኛ ሱቅ የነበረው ሲሆን። ሱቁን ቀጥ አድርጎ የሚያስተዳድርለት ታማኝ ሰው አጣና ጓዴ ፓፒዮን  ከገጠር አስመጣው። ጓዴም ወደ ከተማ እንደ ደረሰ ቀጥታ ወደ አጎቱ ሱቅ ገብቶ ስራውን ጀመረ። አየዋለ ሲያድር ስራውን በሚገባ ለመደ። ከዚህም አልፎ በስራው የተመሰገነ ሆነ በአጎቱ። ከነበረው ንቃተ ህሊና ተጨማምሮ ብዙ ደንበኞችን ለአጉቱ ሱቅ አስተዋወቀ። በዚህ ሁኔታ ረጅም አመት እንደሰሩ በፐርሰንት የራሱን ድርሻ የሚያገኝበትን አሰራር ከአጎቱ ጋር ተወያይተው አፀደቁ። የስራው ሁኔታ ተሻሻለ። የሰራበትን ሳይቀበል አለኝ በሚለው ሂሳብ ዝም ብሎ መስራቱን ቀጠለ። መቼም ሰው ሆኖ የማይጣላ የለም። ከአጎቱ ጋር አለመግባባት ተፈጠረና ተጣሉ። እሺ እስከዛሬ የሰራሁበትን ስጠኝና የራሴን ስራ ልስራ አለው ለአጎቱ! ምስኪኑ ጓዴ ፓፒዮ። የምን ብር ነው የምሰጥህ?  እስከዛሬ የተጠቃቀምክበት ለእናትህ በየ አመት በዓሉ የላከው ገንዘብ ከአገልግልትህ ክፍያ በላይ ነው። የሚል መልስ ከአጎቱ ያገኛል። በዚህ ቢል በዛ አጎት ተብዬ ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ሆነ። ትላንት በስራው ያመሰገነውን የእህቱን ልጅ ዛሬ ካደው። አለም አንዲህ ነች ሙንሙጥ። እንደ ልጥ የምትልመጠመጥ። ትላንት ባስቀመጥካት፣ ዛሬ ማትቀመጥ። ቁንጥንጥ።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 3
    በእናቱ ወንድም እንደ ማይጠቅም እቃ በድንገት የተጣለው ጓዴ ፓፒዮ። የሀገሩን ተወላጅ ሽማግሌዎች ሰብስቦ አቤት አለ። ሁኔታውን አስረዳቸው። እስከዛሬ እንደራሱ ሲሰራበት የከረመውን ድርሻ ያሰጡት ዘንድ ወደ አጎቱ ላካቸው። ባለሀብት የሆነው አጎት ሽማግሌዎቹን በደስታና በግብዣ ተቀበለ። በግብዣ የታወሩ ሽማግሌዎች ቀጣጥፎ የሚነግራቸውን ሁሉ አምነው ተቀበሉ። ወደሱም አደሉ። ለጓዴ መጥተው እንደውም ብር አንተ ጋር ስላለው ስጠው የሚል ተስፋ አስቆራጭ መልስ ነገሩት። ድሮስ ከሌለህ ማን ላንተ ያደላል?። ።ጓዴ ፓፒዮ ምድርና ሰማይ ተደበላለቁበት፣ መግቢያ ቀዳዳ ጠፋበት። ትላንት አንደራሱ ከሰራበት ሱቅ እንደባዶ ካርቶን በቀልድ ወርውሮ ጣለው። ከናቱ ጉያ ወጥቶ ሲመጣ ሱቅ አዘጋጅታ የጠበቀችው ከተማ ዛሬ ፊቷን አዞረችበት። ምንም አላለም ተበደልኩ ብሎ ለማንም አልተነፈሰም። እንደዘመኑ ሰው በእልህ ለበቀል ተነሳስቶ ቃልቻና ደብተራ ጋር ሄዶ መርፌና ኮረሪማ  አላሰቀለም። በደሉን ለፈጣሪ አስረክቦ ፊቷን ወዳዞረችበት አለም ስንክሳር ሀ ብሎ ፊቱን አዙሮ ግብግብን ጀመረ። የህይወትን ውጣ ውረድ ከዚህ ጀመረ። ከመንከራተት በዘበኝንት ከአንድ ሀብታም ጊቢ ተቀጠረ። አንገቱን ደፍቶ በመስራት አምስት አመታትን አስቆጠረ። ደመዎዙንም አጠራቀመ። አምስት ሺህ ብር ሲደርስለት መርካቶ ትንሽ መደብ ተከራይቶ መስራቱን ጀመረ። ካለው ልምድ ጋር ተጨማንሮ ወዲያው ስራው ለመደለት ትርፋማም ሆነ። ቤት ተከራየ። ቀጥሎ ሚስት አገባ። በአመቱ አንድ ልጅ ወለደ። የመጀመሪያ ልጁ በተወለደ ማግስት ድጋሚ ለኪሳራ ተዳረገ። ዛሬ ቢከስር ቢደላው ብቻውን አይደለም። የሱን እጅ የሚጠብቁ የሁለት ነብሶች ሀላፍትና ጫንቃው ላይ ተጭኖበታል። ከአጎቱ ክህደት ማግስት ጀምሮ በተደጋጋሚ የተጋረጠበት የችግርን ፅዋ መቅመሱ ከፍተኛ ልምድ ሆኖታል። በምንም ነገር ያሳበውን ሳያሳካ ተስፋ እንዳይቆርጥ አድርጎ አስተምሮታል። ጓዴ ፓፒዮ ምንም ሳያዝን ሳይተክዝ የቀረ ገንዘቡን ለሚስትና ለልጁ መቆያ ትቶላቸው… ደላላ ወደ አገኘለት የጉድጓድ ውሃ አውጪ ድርጅት ውስጥ በጉልበት ስራ ተቀጠረ። መላ አካልን ሬንጅ  በመሰለ ዘይት የሚያጨማልቀውን ስራ ሳይጠየፍና ጉልበቱን ሳይሰስት ገበረ። የሚሰራበት ድርጅት ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ ገጠር ስለነበር ለሚስትና ልጁም ገንዘብ እየላከ ለተወሰነ አመት ከአይናቸው ርቆ ቆየ። በስራው ታታሪነት ታወቀ። ድርጅቱ  በየአመቱ ባስለመደው ታታሪ ሰራተኛን የመሸለም ስነ ስርአት የአስራ አምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነ።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 4
   ጓዴ በታታሪነቱ የተሸለመውን ብር ይዞ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ መርካቶ ገባ። ረጅም ጊዜ ልምድ ያካበተበትን የንግድ ስራውን  ጀመረ። ባሁኑ እንኳ በዱቤ እቃ የሚሰጡት ነጋዴዎች ስላገኘ ስራው በጣም ሞቀ። በእጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ በትርፍ ሆነ። ከኪራይ ቤት ተላቆ የራሱን ቤት የጨረቃም ቢሆን ገነባ። ሚስቱንና ልጁን ይዞ ወደ ገነባው ቤት ገባ። ስራውም እንደሞቀ ቀጠለ። ብዙ ገዥና ሻጭ ነጋዴዎች ለግባባት ቻለ። ህይወቱ እንደ አዲስ ደመቀች። ሆኖም በዚህ አልቀጠለችም። ድጋሚ ህይወት ወጥመዷን አጠመደችበት ለዛውም ሁለት ወጥመድ።  የገነባው የጨረቃ ቤት በመንግስት ግብረ ሀይል ህገ ወጥ ነው በሚል ፈረሰ። ወደ ክራይም ቤት ተመለሰ። በዚህ አላበቃም። በመርካቶ በሱቁ አቅራቢያ በተነሳው የእሳት አደጋ ወደነሱ ሱቅ ደርሶ ሙሉ ንብረቱ በአንድ ምሽት በእሳት ተደመሰሰ። ወደ ችግር ኑሮ ተመለሰ።  አሁን ግን ወደ ጉልበት ስራ አልተመለሰም…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 5
    ጓዴ ፓፒዮ  ቤቱ ህገወጥ ነው ተብሎ በፈረሰ ሰሞን… የንግድ ቤቱ በእሳት አደጋ መደምሰሱን አይተናል። ጓዴ ከዛስ ቡሃላ ምን ገጠመው? እንዴትስ ሆነ? ተመልሶ ወደ ጉልበት ሰራ ተሰማራ? ለሚለው ጥያቄ መልስ እነሆ …

ከእሳት አደጋው ቡሃላ ወደ ጉልበት ስራ አልተሰማራም። ምክኒያቱም በመርካቶ የንግድ ቤት ሲቃጠል በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ አደጋው ለደረሰበት አካል መልሶ የሚቋቋምበትን የገንዘብ እርዳታ የማድረግ ልምድ አለ(ነግ በኔ ነዋ)። በዚህ መሰረት ለነ ጓዴ ፓፒዮ ከተሰበሰበው የእርዳታ ገንዘብ  የድርሻው ተሰጥቶት መልሶ ለመቋቋም በቃ። ስራውን ቀጠለ። በዱቤ ወስዶ በእሳት የነደደበትን የንብረት እዳ አየከፈለ እየከፈለ አጠናቀቀ። ይህም ለእድገቱ ማዝገም ምክኒያት ሆነ። ሚስቱ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች። ህይወት እንደገና በደስታ ይመራት ጀመር።  ••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 6
  የጓዴ የህይወት ስንክሳሩ ገና አላበቃም። ከእሳት አደጋው አገግሞ ሁለተኛ ልጅ ተወልዶለት። ራሃ የሆነ ህይወት በመምራት ሳለ… ሁለተኛ ልጁ ከዚህ አለም በሞት ተለየው። አሁንም አላበቃም… በቀድሞው መሬት ላይ  ድጋሚ የሰራውም ቤት ድጋሚ ፈረሰ። ደግሞ ይግረምህ ብታምንም ባታምንም ለሁለተኛ ጊዜ ሱቁ በተመሳሳይ አደጋ በእሳት ወደመ። እርዳታውም ተደግሞ አሁንም ስራውን ጀመረ። በተከታታይ አደጋ ምክኒያት የተሸከመው እዳ ለተዳከመ ሱቁ መንስኤ ሆነ። የበፊቱን እዳ ሳይከፍል ሌላ እቃ የሚያገኝበት መንገድ ጠበበ። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ መኖሩን ተያያዘው። አልሞተምም  አልጠፋምም የሆነ አይነት ላይፍ።

  የጓዴን የህይወት ውጣ ውረድ ስታነበው እራሱ ጨነቀህ አይደል። እኔ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ብለህ አላሰብከውም?። እኔ በግሌ የማብድ ነበር የሚመስለኝ። ግን ደግሞ አንድ እውነት ልንገርህ። አንዳንዴ ለማይችል አይሰጠውም ይባላል። ታሪኩን የምነግርህ ጓዴ በሚደርስበት መከራ ልክ የመቻያ ጥበቡን አፍስሶበታል። እንተ ስታነበው ያስጨነቀህ እሱ ተውኖት እንዳንተ አልተጨነቀም። ከምሬን ነው። ብረት የሰው ብረት። ትላንት ባለሱቁ ሆኖ ዛሬ የጉልበት ስራተኛ ሲሆን ምንም የስነልቦና ጫና የማያድርበት የሰው ብረት ነው። ከዚህ ቡሃላ ጓዴ ፓፒዮ  ከኔ ጋር በስራ የሚያስተሳስረን ሁኔታ ተፈጠረ። ከዚህ ቡሃላ እስከተወሰነ ድረስ ያለው ታሪኩ ከኔው ጋር የተሳሰረ ስለሆነ አንድ ላይ ለተርከከክልህ…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 7
     እኔ የጓዴን በዝምድናም ጭምር የመጣ የህይወቱን እርምጃ በቅርበት በማየት ጠንቅቄ አውቅ ነበር። ትምህርት ጨርሼ ቀጥታ ወደስራው አለም ስሰማራ ጓዴ ሰራ ያለማምደኝ ዘንድ በደንብ ቀረብኩት። ከቤት በብድር መልክ በቀፈልኳት ብር እቃ እየገዛው ለሱ ሱቅ ማቅረብ ጀመርኩ። ቅርበታችን ጠበቀ። ስራውም ሞቀ። በዚህ መሃል አማከረኝና አትርፎ ለመሸጥ መሬት ገዛ። የኔም ሆነ የሱም ገንዘብ መሬቱ ላይ አደረ። ከዛሬ ነገ ይሸጣል ያልነው መሬት ገግሞ ቁጭ አለ። በዚህ የመጣ ስራ ፈታን። ቁጭ ብሎ መዋል። ቁልጭ ቁልጭ ብቻ ሆንን። እኔም ከቤት የወሰድኩት ብር ከምን ደረሰ(ይኼኔ ቀረጣጥፈህ ቅመኻት ነው) የሚለው ጭቅጭቅ ሲበረታ እውነቱን ነግሬ፣ እኔም አረፍኩ እነሱም አረፉት። መሬቱ አሁንም አልተሸጠም። የጓዴ ፓፒዮ መደብ የኔም ኪስ ኦና ሆነ። ከኔ ይልቅ የሱ ችግር ባሰ። ምክኒያቱም ብዙ እሱን የሚመለከቱ ሀላፍትናዎች ስለነበሩበት። ሶስተኛ የወለደው ወንድ ለጁም ድክድክ ማለት ጀመረ። በዛው ሰሞን ውጬ ከነበረችው እህቱ ገንዘብ ተላከለት። የላከችው ገንዘብና የእኔ በመሬቱ ላይ የዋለው ገንዘብ መጠን እኩል ነበር። ከቤት እንደተጨቀጨኩ ያውቅ ስለነበር አንስቶ ሰጠኝ። መቀበል አልሆነልኝም። እሱ መደቡ ባዶ ሆኖ፣ ሚስት ልጆቹ እጁን እየተጠበቁ ባለበት በዚህ ወቅት ያገኛትን ገንዘብ መውሰዱ ለህሊናዬ ጎረበጠኝ። ይሄን ገንዘብ መደቡን እቃ ሙላበት አልኩት የኔን መሬቱ ሲሸጥ ትሰጠኛለህ አልኩት። በደስታ የሚያደርገው ጠፋው። ወዲያው መደቡን ሞላ ስራውን ቀጠለ። እኔም መሬቱ እስኪሸጥ በትዕህስት መጠባበቁን ያዝኩ። ከእልህ አስጨራሽ ቆይታ ቡሃላ መሬቱ ተሽጦ ብሩን ለቤት ወስጄ ሰጠው። ጓዴ ከዚህ ቡሃላ የደረሰበትን ብዘረዝረው በወደድኩ ነገርግን ማሰልቸት ስለሚሆን ወደ ማጠቃለያው ልግባ ነገር ከዚህ ቡኋላ አንድ ጊዜ የመክሰርና 3 ጊዜ ቤት እንደፈረሰበት አልዋሽህም!! እንዴት የሚፈርስ ቤት ደጋግሞ ይገነባል? የሚል ጥያቄ ካነሳህ። ከላይ ያሰበውን ካላሳካ ምንም ተስፋ አይቆርጥም ብዬህ አልነበር ለዛ ነው።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 9
  ጓዴ ፓፒዮ በሚሰራበት ሱቅ እኔም ድጋሚ ብር ቀፍዬ መደብ ተከራይቼ መስራት ጀመርኩ። ሁለት አመት ከምናምን እንደሰራን ከምንሰራበት ሱቅ ሁላችንም እንድንለቅ ተደረገ። መደብ ላይ የነበረኝን ሸቀጥ ጭኜ ካደጉበት ጊቢ ውስጥ ደርድሬ መሸጥ ጀመርኩ። ጓዴ ፓፒዮንም ከኔ አጠገብ እንዲሰራ አደረኩት። ያለ ሱቅ ኪራይ ጊቢው ውስጥ ንግዱ ለመደልን። የጓዴም ባለቤት የስራ ቦታው እየቆመች እሱ ውጪ ውጪ ሌላ ስራ መስራት ጀመረ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በግቢው ውስጥ ስራ እኔ ከስራው ጨዋታ በኪሳራ ስወጣ። ጓዴ ውጪ ዉጪ በሚሰራው ስራ ያልታሳበ ለውጥ አመጣ። አንድ ሁለት ሰዎችን ጨምሮ በስማቸው ፌስታል ማስመረት ጀመሩ። የፌስታሉ ስራ እንደሮኬት ተኮሳቸው። ያርግላቸው!! እኔም ወደሌላ ፊልድ ተዛወርኩ። ጓዴ በእልህ ደጋግሞ የፈረሰበትን ቤት ሰራ። ቤቱ እራሱ በህጋዊነት ፀደቀለት። መኪናም ገዛ። ህይወቱ በአጭር ጊዜ  ተለወጠች። ለረጅም አመት ያንከራተተችው ህይወት እጅ ስላልሰጠላት ዛሬ እጅ ሰጠችው። ባለ ሀብት ከሚባለው ደረጃ ደረሰ። ከራሱ አልፎ ለኔም በቃ። ከረጅም አመት ቡሃላ አጎቱን ጠየኩት። መክሰሩን ኑሮው እንደድሮ አለመሆኑን። ባጠፋውም ጥፋት ለይቅርታ ሽማግሌ እንደላከበት፣ እሱም ይቀርታውን እንዳልነፈገው… እያጫወተኝ አዲስ በሰራው ቤት ምርቃት ላይ በደስታ አሳልፍን። በችግርም በደስታ ሳይለየን ለዚህ ላደረሰን አላህ ምስጋናችንን ይድረሰው። ከዚህ ጓዴ እኔ ብዙ ነገር ተምሬያለው። ምን ቢጨልም መንጋት እንደማይቀር የጓዴ ፅናት ምርጥ ማሳያ ነው። አንተም የተስፋ አለመቁረጥን ፍሬ ከጓዴ ፓፒዮ የተማርክ ይመስለኛል… ካሰለቸውህ አፉ በለኝ!! ለማንኛውም ትርተራዬተፈፅሟል ።
ወገሬት!!