Tuesday, June 7, 2016

የ ደ ር ጉ = ወ ታ ደ ር !!

የ ደ ር ጉ  =  ወ ታ ደ ር !!
<===============>
ሳteናw

… የቤታችን ክዳን ቆርቆሮ በታጣቂው የደርግ ወታደር ተከታታይ ተኩስ ወንፊት ከሆነ ቡሃላ… በድንጋጤ ተደብቆ የነበረው የግቢው ሰው ከያለበት ወጥቶ…  ሰአት የሰረቀውን ሌባ ይዘው እንደ ሚያስረክቡት ቃል ገብተው አረጋጉት። ወታደሩን።

… ታላቅ እህቴ መይሙና የወታደሩን መረጋጋት ተከትላ፣ የቤት ውስጥ ስራዋን ለማከናወን፣ ማድ ቤት… ወደ ዱቄቱ በርሜል ሄደች። ሁሌም በርሜሉ ላይ ዳንቴል እንደለበሰ የሚቀመጠው መሶብ ተዘበራርቆና የበርሜሉ ክዳን ገርበብ ብሎ ስታገኘው…  (ከፍቼው ነበር እንዴ?) ብላ ራሷን በመጠራጠር እየጠየቀች ክዳኑን ከፈተችው። በርሜሉ ውስጥ ዱቄት ብቻ ሳይሆን… ዱቄት ለብሶ ቁጢጥ ብሎ የተቀመጠ ሰዉ አገኘች… በድንጋጤ ጆሮ በሚሰነጥቅ ድምፅ እሪሪሪሪሪሪ ብላ ጩኸቷን ለቀቀችው……………………

   1983 ዓ/ም የደርግ ወታደር በኢህአዴግ እንደተከነተ ካምፑን እየለቀቀ ወደ ከተማ መትመም ጀመረ። ከተማችን አዲስ አበባ በተሸነፉ የደርግ ወታደሮች ተጥለቀለቀች። ካጥለቀለቁን የደርግ ወታደር አንዱ መሳሪያውን እንደታጠቀ የእጅ ሰአቱን  ለመሸጥ ወደ ሰፈራችን መርካቶ መጣ። ወታደሩም ሰአቱን የሚገዙትን ቃፊሮች አገኘ። (ቃፊር በመርካቶ ቋንቋ ከቸገረውም ከሰረቀውም እቃ እየገዛ የሚሸጥ ጥቃቅንና አነስተኛ ደላላ ማለት ነው።) ወታደሩ ቃፊሮቹ ሰአቱን ለመሸጥ በመደራደር ላይ ሳለ አንዱ ጭልፊት የመርካቶ ሌባ ሰአቱን ከእጁ ነጥቆት ሮጠ። ወታደሩ ቃፊሮቹን ትቶ ሰአቱን መንትፎ የሚሮጠውን ሌባ መከተል ጀመረ። ቢጫ ሱሪ ለብሶ በጥግ ጥግ የሚሮጠውን ሌባ እንዲቆም መሳሪያውን ወደ ላይ ደጋግሞ ተኮሰው። ከዚህ ተኩስ ቡሃላ በገበያተኛ ግርግር ተዋክባ የነበረችው ሰፈሬ ሰው ምን እንደዋጠው የት እንደገባ ሳይታወቅ ፀጥ ረጭ ያለ ምድረበዳ ሆነች። ወታደሩ አሁንም ባለ በሌለው ሀይል እየሮጠ አየተኮሰ ሌባውን ተከተለው። ሌባው እኛ ጊቢ ዘሎ ገብቶ ተሰወረ። ወታደሩም ሌባውን ተከትሎት ገባ።

  ጊቢያችን …  ወንበሮች ወዳድቀው፣ ጠረጴዛ ተንጓሎ፣ ሻሽ… ሻርኘ… እንድ… እግር ጫማ… ኮፍያ… ምናምን መሬቱ ላይ ተንጠባጥቦበት ደረሰ። ወታደሩ ባየው ነገር  ካለው ወታደራዊ ልምድ በመነሳት ግቢው ውስጥ የሰው ዘር ከአፍታ በፊት እንደ ነበረበትና አሁን በፍራቻ እንደተደበቀ ተረዳ። የግቢያችን ነዋሪ ከተኩሷ ጀምሮ ግማሹ አልጋ ውስጥ ግማሹ ሻንጣ ውስጥ በሩን ዘግቶ ተደብቋል። ወታደሩ ግቢው ውስጥ ግራ ቀኙን ቢያማትር ሌባውን ጨምሮ የሚጠይቀው ሰዉ የተባለ ዘር አጣ። "ተኩስ የደበቀውን ተኩስ ያወጣዋል" ብሎ ነው መሰለኝ። ወዲያው ያነገበውን መሳሪያ አወለቀና ከፊት ለፊቱ ያለውን የቤታችን ቆርቆሮ ጠርዙ ላይ ካካካካካካካካ እያደረገ የጥይት መዓት አርከፈከፈበት ከቆርቆሮነት ወደ ወደ ወንፊትነት ሲለወጥ ተኩሱን አቆመ። ቤት ውስጥ ተደብቆ የነበረው ሰው ውጣ መባሉ ገብቶት ቀስ በቀስ እየፈራ ወጣ። ቀድሞ የወጡት ቡና ነጋዴው የአይን አባቴ ጋሽ ሼይቾ ነበሩ። የደርጉ ወታደርም  እንዳይደነግጡ የሽጉጡን አፈሙዝ ወደ መሬት መልሶ "እዚህ ጊቢ ቢጫ ሱሪ የለበሰ ሌባ ሰአቴን ነጥቆኝ ሲገባ አይቻለው አሁኑኑ ሌባውን አውጡት አለዚያ እያንዳንድሽን አንድ በአንድ እቆላሻለው" አለ።  ይህን የሰማችው አያቴ ቢጫ ሱሪ ሲል በድንጋጤ ልጄ ቢጫ ሱሪ ነው የለበሰው አለች ። የሚገርመው ልጇ ቢጫ ሱሪ አለበሰም። ወታደሩም ወደ ተጠቆመው ልጇ ቢመለከት ሌላ አይነት ቀለም ነው የለበሰው አያቴ በድንጋጤ እንደዛ እንዳሉ ገባውና። እሱ አይደለም ሌባውን አይቸዋለው ብሏቸው። በቁጣ ወደ አይን አባቴ ዞረ። ጋሽ ሸሂቾም ወታደሩን ተጠግቶ ማረጋጋትና ማግባባት ያዙ። ከፈለገም ብርም ተሰብስቦ እንደሚሰጠው ነገሩት። "እኔ ለማኝ አይደለሁም! የማንንም መፅዋት አልፈልግም፣ ጊዜ ጣለኝ እንጂ ለአብዮት የታገልኩ የኢትዮጲያ ልጅ ነኝ። አሁን ቢጫ ሱሪ የለበሰውን ሌባ ብቻ አውጡልኝ" አለ። የግቢው ሰው የህይወቱ መቀጠል ዋስትና በሌባው መገኘት ላይ ሆነ። ሁሉም ሌባውን በመፈለግ ተሰማራ፣ ያልተፈተሸ ያልተነሳ ኮተት የለም፣ አልጋ ውስጥ ሰው ተገኘ። አልጋ ውስጥ የተገኘው ግን ሌባው አልነበረም። የሽጉጡን ድምፅ ሰምተው የተደበቁ የሰፈሬ ጎረምሶች እንጂ። ወታደሩ መረጋጋቱ በስንት መሀላ ተረጋግጦላቸው ከአልጋ ውስጥ ወጡ። አሁንም ሌባውን ለማግኘት ፍለጋው ጦፈ። ወታደሩም ቀስ በቀስ ተረጋግቶ በግቢው ውስጥ በግርግሩ ወድቆ የነበረው ወንበር ላይ ተቀምጦ ሌባው እስከሚገኝ መጠበቅ ጀመረ።

…  በዚህ ቅፅበት ከአንደኛው መኖሪያ ቤት የታላቅ እህቴ ጩኸት ተሰማ። በፍለጋ የተሰማራው የግቢው ነዋሪ እሪታው ወደ ተሰማበት አቅጣጫ ተግተለተለ። ሲደርሱ መላ አካሉ በዱቄት የተሸፈነውን ሌባ በርሜሉ ውስጥ ሲቁለጨለጭ አገኙት። እሱን ያልመታ ውሻ ይውለድ የተባለ ይመስል በሁሉም ሰው የዱላ ውርጂብኝ ወረደበት። ከበርሜል ውስጥ የጀመረው ድብደባ ወታደሩ ጋር እስኪደርስ አልቆመም ነበር። ከብዙ ድብደባ ቡሃላ የለበሰው ዱቄት በኖ ተነሳ። መቶ በመቶ የሌባው ማንነት የተረጋገጠው ከዚህ ቡሃላ ሆነ። በዱላ ብዛት የለበሰው ዱቄት ተራግፎ በመነሳቱ የለበሰው ቢጫ ሱሪ መሆኑ ተለየ። እጁን ተጠፍሮ ወታደሩ ዘንድ ቀረበ። ወታደሩ ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ተነሳና ሊጨርሰው ሲል ብልጡ ሌባ ሰአቱን አውጥቶ ሰጠው። ወታደሩም ሰአቱን ከተቀበለው ቡሃላ ይቅርታ አድርጎለት ከጊቢያችን ወድቆ ሄደ።  የግቢው ሰው ግን ወታደሩ ከሄደም ቡሃሏ ሌባውን እን ቀልድ አልቀቀውም። "አስጨርሰኸን ነበር አን አንቡላ!?" አያለ እየሰደበው በእልህ …ሁለተኛ እዚህ ግቢ አይደለም ተባሮ በሰላሙም ጊዜ እንዳይገባ አደርጎ ምላስና ብብቱ ሲቀር መላ አካሉ ተቀጥቅጦ ከግቢ ውጪ ተጣለ። ነብሱ የተመለሰችው ሌባ ተነስቶ እያነከሰ ሄደ። የሚገርመው ይሄው ሌባ ከሶስት ቀን ቡሃላ ከግቢያችን ውጪ ተገድሎ ተገኘ። ድመት መንኩቀሳ አመሏን አትረሳ! ይባላል። ይህ ላቦሮ እንደ ደርጉ ወታደር በይቅርታ የሚታለፍ መስሎት ወደ ሌብነቱ  ወዲያው ተሰማራ፣ በሌሊት ሰርቆ ሲያመልጥ በሴት ታጋይ ወታደር ጭንቅላቱ ላይ በጥይት ተመቶ አዛው እኛ ግቢ በር ላይ ሞቶ ተገኘ። ግቢያችን ውስጥ በይቅርታ ቢታለፍ፣ አልመከር በማለቱ ግቢያ በር ላይ ህይወቱ አለፈች። ምከረው ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው!!

☞ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment