Saturday, June 4, 2016

ወአንድነት ወመሰሎ ወቀስተደመና

  ወ አ ን ድ ነ ት… ወ መ ሰ ሎ…  ወ ቀ ስ ተ ደ መ ና!!
<=================================>
#ሳteናw

  የርዕሱ ቋንቋ ግዕዝኛ፣ ይሁን ኧማራይክ እኔም አላውቀውም። ብቻ የአንድነትንና የቀስተደመናን… መመሳሰል ለመግለፅ የተጠቀምኩት ነው። ለማንኛውም… አሁን ይሄ አያሳስብህ ትኩረትህን ሰብሰብ አድርግልኝና … የጋራ ጥቅማችን ወደ ሆነው … ሀሳብ… እንግባ… 

…  አንድነት ከምወዳቸውና ደስ ከሚሉኝ ስሞች ውስጥ አንዱ ነው። ለምን? አትለኝም… ለምን ማለት ጥሩ!! አንድነት ከስያሜ ያለፈ ዘርፈ ሰፊ ትርጉም ስላለው ነው። አንድነት ሀይል ነው፣ አንድነት ውበት ነው፣ አንድነት ሰላምነው፣ ደግሞ ይግረምህ አንድነት ፍቅር ነው፣ አንድነት የድል ቁልፍ ነው፣ አንድነት የጥንካሬ መገለጫ ነው። አንድነት ይሄ ሁሉ ነው።
ለምን አንድነትን እንደምወደውና ደስ እንደሚለኝ አሁን የተረዳኸኝ ይመስለኛል። በአንድነት የማይፈርስ ተራራ፣ የማይንኮታኮት ቋጥኝ፣ የማይደመሰስ ሀይል የለም። በአብዛኛው ትልቅ የምትለው ነገር ሁሉ የተለያዩ ነገሮች ድምር ውጤት ነው።

… የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም ሲባል ሰምተሃል አይደል? አንድነት ግን ያላየሃትን ሀገር እንድትናፍቅ ያደርግሃል። የአንድነት ሀይል እስከዚህ ድረስ ነው። በጆሮህ ብቻ በፍቅሯ ተለከፈህ በያመቱ ዲቪ (diversity visa lottery) ሎተሪዋን አሰፍስፈህ የምትጠብቀውን አሜሪካንን ውሰድ አማላይነቷ ያጎሉት ሀምሳ ምናምን ስቴቶች በአንድነት ተሰባስበው ነው። ዘ ዩናይትድ እስቴትስ ኦፍ አሜሪካ። አየኸው ስሟ እራሱ አፍ ሲሞላ?! የአንድነት ውጤት ነዋ። ሀይል የሚኖርህ በአንድነት ነው። ጀግኖች አባት አርበኞቻችን የጣሊያንን ፋሺሽት ወራሪን እግሩንም፣ ቅስሙንም ሰብረው ቾር ያሉት (ያባረሩት) አንድ በሆነ ሀገራዊ ስሜት ተውጣጥተው ነው። ደግሞ አንድነት ሰላም ነው። የሰፋ ልዩነት ከሌለ ፀብ ምን ማደሪያ አለው። የትኛውንም የጦርነት የታሪክ ድርሳን ብትመለከት አንድ የማያግባባ ነጥብ በመፈጠሩ የተከሰተ ነው። እና እልሃለው! ከመሬት ተነስቼ አይደለም አንድነትን መውደዴ። አንፍነት ብዙ ነገር ነው።

… ለምሳሌ መርካቶን ውሰድ… (ይሄ ደግሞ! መርካቶን እንደ ቅመም በወጎቹ መሃል ሁሉ ጣል ካላደረገ አይሆንለትም እንዴ? ብለህ በውስጥህ እንደምትቦጭቀኝ አውቃለው። ምን ላርግ!! መርኬ።ሰፈሬ ለምሳሌነት ሁሉ ምቹ ሁና ስለማገኛት ነው።) መርካቶን የአፍሪካ አንደኛ ማርኬት ያሰኛት ምንድነው? ካልከኝ። መርካቶ የተለያዩ ስያሜ ባላቸው ስፍራዎች የወል ስም ነው እልሃለው። መርካቶ በእቅፏ ያሉ ስፍራዎች በርካታ ናቸው። ለመጠቀስ ያህል…አመዴ ገበያ፣ ሲዳሞ ተራ ሸማ ተራ፣ ጠላ ሰፈር፣ ሲኒማ ራስ፣ መስታወት ተራ ፣ ጆንያ ተራ፣መፅሀፍ ተራ፣ዱባይ ተራ፣ ጎማ ተራ፣ በርበሬ በረንዳ፣ ምናለሽተራ፣ ጋዝ ተራ፣ ዶሮ ተራ፣ ሎሚተራ፣ ቄጠማ ተራ፣ ቧንቧ ተራ፣…  ወዘተ …ይጠቀሳሉ… የነዚህ ስፍራዎች ስብስብ ነው የመርካቶ ትልቁ ህልውና እና ውበቷ። አሁንም … ከርዕሳችን አልወጣንም፣ አንድነት።

  በሌላ በኩል አንድነት ውበት ነው። ልብ ብለህ ተመልክተህ ከሆነ… የቀስተዳመና ውበት የተለያዩ ቀለሞች ስብጥር ነው። ውበቱን ያጎሉት ቀለማቱ እንደ መልካቸው በእኩል ደርዝ  በመገጥገጣቸው ነው። አንዱ ቀለም ሰፍቶ አንዱ ቢጠብ  የቀስተደመናው ውበት ሙሉ አይሆንም። በመካከላቸው ክፍተት መፍጠርም የውበቱን ማራኪነት ብዥታ ያለብሰዋል። ስለዚህ ለተሟላው የቀስተዳመናው ውበተ-ነፀብራቅ  የእያንዳንዱ ቀለም በእኩል የመደርደር ውጤት ነው። እንቀጥል…  ቀና በልና የሰንደቅ አላማህን ግርማ ሞገስና ውበት ተመልከተው… ጀግንነት! ሀይል!ወኔ! የሀገር ፍቅር… ስሜት የሚያሳይህ አንዱ ቀለም ካንዱ ስለበለጠ አይደለም! ትኩረት የሚስበው ህብረቀለማቱ እንጂ ነጠላው ቀለም አይደለም።

   የኢትዮጲያዊነታችን ውበትም ልክ እንደዚሁ የሁላችንም ድምር ውጤት ነው።… የተለያየ ብሄር መሆናችና በኢትዮጲያዊነት ክበብ መታቀፋችን ነው። ለየትኛውም አለም ትኩረት የሚስበው ህብረብሄሩ እንጂ ነጠላው ብሄር አይደለም።(ይህን አረፍተ ነገር አስምርበት) ስለዚህ የኢትዮጲያዊነት ውበተ ነፀብራቅ ያለ አንዳችን ሙሉ አይሆንም። ነጥቡ አራት ነው። ከዚህ ውጪ… እኔ ያከሌ …ፀዴ ዘር ነኝ። እኔ የዚህኛው አባል ነኝ። እኔ ጂኒ… ነኝ… እኔ… ቁልቋል… ነኝ አቦ እንዴት እንደሚደብረኝኝኝ…። ኢትዮጲያዊ መሆን በቂ ነው አለቀ። ተፈጥሮ በቸረችህ ገፅታ ኢትዮጲያዊነትህ ተገልፇል። ዋናው ነጥቤም ይኸው ነው። በብሔር ባንመፀዳደቅስ? … የማን ዘር ወርቅ የማን ዘር አፈር ነው…? ሁሉም ሰው ነው። የልዩነት ክበብን ማስፋት መጨረሻው ራስህን ባይተዋር ከማድረግ ውጪ ሚፈይድልህ ነገር የለም። ልዩነት አይኖርም ማለት አይደለም። በተለያየ  አመለካከት፣እምነት፣ ወዘተ… ልዩነት ይኖራል… ነገር ግን የኢትዮጲያዊነት አንድነት እንደ ፋሲካ በግ የሚሰዋ መሆን የለበትም።

የሚገርምህ ደግሞ የልዩነት ወሰን የማስፋት አባዜ ብቻህን እስክትቆም ድረስ አይቆምም። የብሄር ክበብ ለየህ…ትቀጥላለህ … የጎሳ… ቀጥለህ… የቤተሰብ… ቀጠልክ…ብቻህን ቀረህ። ብቻህን ቆምክ ማለት ደግሞ እመነኝ ምንም ነህ። ከመንጋዋ እንደተነጠለችው በግ የቀበሮ ሲሳይ…ከመሆን ውጪ። ቀበሮዋም አንዱን ለመነጠልም የተለያዩ አማራጮች ትወስዳለች… ህልውናዋን የምትቀጥለው ከመንጋው የሚነጠለውን በግ በመብላት ነዋ። ስለዚህ ያንዣበበውን የቀበሮዋን እድሜ ለመቋጨት ከመንጋው አለመነጠል በቂ ነው። ለብቻህ ማትገፋው ቋጥኝ በህብረት ጢባጢቤ ትጫወትበታለህ። በብቸኝነትህ ያቅራራብህ ምንም ሀይል በህብረትህ ይሸማቀቃል። ተንኮታክቶ አፈር ከድሜ ይግጣል።

   ሀገር ማለት መልከዓምድሩ፣ ወንዙ፣ ጋራ፣ ሸንተረሩ ብቻ አይደለምሀገር ማለት ህዝብም ነው። የህዝብ ፍቅር ተንሰራፋ ማለት የሀገር ፍቅር ኖረ ማለት ነው። የእነዚህ ውጤት አንድነትን ይፈጥራል። ልክ ነው የሀገር ፍቀርና አንድነት ከመሬት ተነስቶ አይከሰትም። ስታስበው ከባድ ይመስላል እንጂ ድካም አይጠይቅም። የሚጠይቅህ ቅንነትና ፍላጎትን ብቻ  ነው። እነዚህን ካሉህ የሀገር ፍቅር እንዲከሰትልህ ሩቅ መሄድ አያሻህም። በግልህ ከየትኛውም ኢትዮጲያዊ ሰው ከየትኛውም ብሄር አባል የሆነ ጎረቤትህ ፍቅር ይኑርህ፣ መግባባትህ ይዳብር፣ ይቅርባይነት ይከተልህ፣ የዛኔ አንድነትህ በመዳፍህ … ሁሉም ነገርህ በደጅህ። ስለዚህ የሚጠቅመን ኢትዮጲያዊ  አንድነትን መጠበቅ እንጂ ልዩነት ማስፋት አይደለም። ልዩነት ውበት ነው። አንዳችን ያለ አንዳችን ሙሉ እንደማንሆን ሁሉ… የተለያዩ ቀለማት በቀስተደመና እንደተቋጩ ሁሉ፣ የልዩነት ወሰንህም ኢትዮጲያነት ይቋጨው። እልሃለው፣ ደግሞ ቦተሊካ ቦከተክ ብለህ እንዳታቀሳስረኝ አደራ!! ለማንኛውም እኝኝኝ ካበዛሁብህ አፉ በለኝ።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment