Monday, June 20, 2016

"ጓ ዴ ሌላኛው ፓፒዮ"

"ጓዴ (ሌላኛው ፓፒዮ)"
#ሳteናw
መግቢያ
     በጓዴ መኪና አዲስ የሰራውን  ቤት ምርቃቱ ላይ ፣(ተሰርቶ እስከሚያልቅ ተመላልሼ ባየውም) የድግሱ ታዳሚ ለመሆን አብረን እየሄድን ነው። ጓዴ ዛሬ በደንብ መሰረቱ የረገጠ ህይወት ከመጎናፀፉ በፊት ያሳለፈውን የህይወት ውጣ ውረድ አንድ በአንድ በአይኔ ላይ ይታየኝ ጀመር… ቀጥሎ የምተረተርልህም ይህንኑ ነው። የህይወት ስንክሳር ለሱ ብቻ የተመደበለት ይመስል የወጣትነት ዘመኑን በመከራ ጋጋታ አስተናግዶ በስተመጨረሻ የተረጋጋ ህይወት ስለገጠመው የቅርብ ጓደኛዬን ታሪክ። (ጓደኛዬ ስልህ እንደኔ ወጠጤ እንዳይመስልህ የአስር አመት ልዩነት በመካከላችን አለ)። ልቸከችክልህ ያነሳሳኝ የሱን የህይወት ውጣ ውረድ ለብዙ ሰው እንደ ፈረሳዊው ፓፒዮ ምርጥ ምሳሌ ሊሆን የፅናትን መጨረሻና ተስፋ ያለመቁረጥን ያማረ ውጤት …  ለሌላው መማሪያነት በሚል እሳቤ ነው ። (በነገራችን ላይ የፖፒዮን ታሪክ አንብበከዋል? ካላነበብከው እመነኝ ታድለሃል!! እንዴት ማለት ጥሩ! አየህ ስለሱ ታሪክ የተተረጎመውን መፅሃፍ በአዲስ መንፈስ ተመስጠህ ታነበዋለህ። የታሪኩ አወራረድ ልብህን እንዴ ሲያንጠለጥል አንዴ ሲያረጋጋህ አንዴ ሲጥል አንዴ ሲያነሳ በራሱ ሪትም እያወዛወዘ እያስተማረህ …  ይዞህ እስከመጨረሻው ይጓዛል። መጨረሻውን ሳታውቅ ለማንበብ አድሉ ስላለህ ነው ታድለሃል ማለቴ። አሁን ግን በግሌ የፅናት ምሳሌ አድርጌ ወደ ምወስደው ጓዴ (ሌላኛው ፓፒዮ) ታሪክ ላሳፍርህ…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 1
… ሀቅ ያወጡልኛል ፍትህ ያስገኙልኛል ብሎ ተስፋ ጥሎበት የነበረው የሽምግልናው ሂደት ለካደው ባለ ሀብት ካደላ ቡሃላ። ያደረገው ተስፋ ቆርጦ ትላንት እንደ ባለቤት ሙሉ ጊዜውን ሰውቶ ይሰራበት የነበረውን ሱቅ ለካደው ለባለሀብቱ አጎቱ ትቶ ቤሳቤስቲን ሳይዝ ጥሎ ወጣ…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
  ምዕራፍ 2
     ጓዴ ፓፒዮ አዲስ አበባን የረገጠው በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር። በእናቱ ወንድም ምክኒያት። አጎቱ በመርካቶ ክልል አነስተኛ ሱቅ የነበረው ሲሆን። ሱቁን ቀጥ አድርጎ የሚያስተዳድርለት ታማኝ ሰው አጣና ጓዴ ፓፒዮን  ከገጠር አስመጣው። ጓዴም ወደ ከተማ እንደ ደረሰ ቀጥታ ወደ አጎቱ ሱቅ ገብቶ ስራውን ጀመረ። አየዋለ ሲያድር ስራውን በሚገባ ለመደ። ከዚህም አልፎ በስራው የተመሰገነ ሆነ በአጎቱ። ከነበረው ንቃተ ህሊና ተጨማምሮ ብዙ ደንበኞችን ለአጉቱ ሱቅ አስተዋወቀ። በዚህ ሁኔታ ረጅም አመት እንደሰሩ በፐርሰንት የራሱን ድርሻ የሚያገኝበትን አሰራር ከአጎቱ ጋር ተወያይተው አፀደቁ። የስራው ሁኔታ ተሻሻለ። የሰራበትን ሳይቀበል አለኝ በሚለው ሂሳብ ዝም ብሎ መስራቱን ቀጠለ። መቼም ሰው ሆኖ የማይጣላ የለም። ከአጎቱ ጋር አለመግባባት ተፈጠረና ተጣሉ። እሺ እስከዛሬ የሰራሁበትን ስጠኝና የራሴን ስራ ልስራ አለው ለአጎቱ! ምስኪኑ ጓዴ ፓፒዮ። የምን ብር ነው የምሰጥህ?  እስከዛሬ የተጠቃቀምክበት ለእናትህ በየ አመት በዓሉ የላከው ገንዘብ ከአገልግልትህ ክፍያ በላይ ነው። የሚል መልስ ከአጎቱ ያገኛል። በዚህ ቢል በዛ አጎት ተብዬ ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ሆነ። ትላንት በስራው ያመሰገነውን የእህቱን ልጅ ዛሬ ካደው። አለም አንዲህ ነች ሙንሙጥ። እንደ ልጥ የምትልመጠመጥ። ትላንት ባስቀመጥካት፣ ዛሬ ማትቀመጥ። ቁንጥንጥ።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 3
    በእናቱ ወንድም እንደ ማይጠቅም እቃ በድንገት የተጣለው ጓዴ ፓፒዮ። የሀገሩን ተወላጅ ሽማግሌዎች ሰብስቦ አቤት አለ። ሁኔታውን አስረዳቸው። እስከዛሬ እንደራሱ ሲሰራበት የከረመውን ድርሻ ያሰጡት ዘንድ ወደ አጎቱ ላካቸው። ባለሀብት የሆነው አጎት ሽማግሌዎቹን በደስታና በግብዣ ተቀበለ። በግብዣ የታወሩ ሽማግሌዎች ቀጣጥፎ የሚነግራቸውን ሁሉ አምነው ተቀበሉ። ወደሱም አደሉ። ለጓዴ መጥተው እንደውም ብር አንተ ጋር ስላለው ስጠው የሚል ተስፋ አስቆራጭ መልስ ነገሩት። ድሮስ ከሌለህ ማን ላንተ ያደላል?። ።ጓዴ ፓፒዮ ምድርና ሰማይ ተደበላለቁበት፣ መግቢያ ቀዳዳ ጠፋበት። ትላንት አንደራሱ ከሰራበት ሱቅ እንደባዶ ካርቶን በቀልድ ወርውሮ ጣለው። ከናቱ ጉያ ወጥቶ ሲመጣ ሱቅ አዘጋጅታ የጠበቀችው ከተማ ዛሬ ፊቷን አዞረችበት። ምንም አላለም ተበደልኩ ብሎ ለማንም አልተነፈሰም። እንደዘመኑ ሰው በእልህ ለበቀል ተነሳስቶ ቃልቻና ደብተራ ጋር ሄዶ መርፌና ኮረሪማ  አላሰቀለም። በደሉን ለፈጣሪ አስረክቦ ፊቷን ወዳዞረችበት አለም ስንክሳር ሀ ብሎ ፊቱን አዙሮ ግብግብን ጀመረ። የህይወትን ውጣ ውረድ ከዚህ ጀመረ። ከመንከራተት በዘበኝንት ከአንድ ሀብታም ጊቢ ተቀጠረ። አንገቱን ደፍቶ በመስራት አምስት አመታትን አስቆጠረ። ደመዎዙንም አጠራቀመ። አምስት ሺህ ብር ሲደርስለት መርካቶ ትንሽ መደብ ተከራይቶ መስራቱን ጀመረ። ካለው ልምድ ጋር ተጨማንሮ ወዲያው ስራው ለመደለት ትርፋማም ሆነ። ቤት ተከራየ። ቀጥሎ ሚስት አገባ። በአመቱ አንድ ልጅ ወለደ። የመጀመሪያ ልጁ በተወለደ ማግስት ድጋሚ ለኪሳራ ተዳረገ። ዛሬ ቢከስር ቢደላው ብቻውን አይደለም። የሱን እጅ የሚጠብቁ የሁለት ነብሶች ሀላፍትና ጫንቃው ላይ ተጭኖበታል። ከአጎቱ ክህደት ማግስት ጀምሮ በተደጋጋሚ የተጋረጠበት የችግርን ፅዋ መቅመሱ ከፍተኛ ልምድ ሆኖታል። በምንም ነገር ያሳበውን ሳያሳካ ተስፋ እንዳይቆርጥ አድርጎ አስተምሮታል። ጓዴ ፓፒዮ ምንም ሳያዝን ሳይተክዝ የቀረ ገንዘቡን ለሚስትና ለልጁ መቆያ ትቶላቸው… ደላላ ወደ አገኘለት የጉድጓድ ውሃ አውጪ ድርጅት ውስጥ በጉልበት ስራ ተቀጠረ። መላ አካልን ሬንጅ  በመሰለ ዘይት የሚያጨማልቀውን ስራ ሳይጠየፍና ጉልበቱን ሳይሰስት ገበረ። የሚሰራበት ድርጅት ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ ገጠር ስለነበር ለሚስትና ልጁም ገንዘብ እየላከ ለተወሰነ አመት ከአይናቸው ርቆ ቆየ። በስራው ታታሪነት ታወቀ። ድርጅቱ  በየአመቱ ባስለመደው ታታሪ ሰራተኛን የመሸለም ስነ ስርአት የአስራ አምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነ።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 4
   ጓዴ በታታሪነቱ የተሸለመውን ብር ይዞ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ መርካቶ ገባ። ረጅም ጊዜ ልምድ ያካበተበትን የንግድ ስራውን  ጀመረ። ባሁኑ እንኳ በዱቤ እቃ የሚሰጡት ነጋዴዎች ስላገኘ ስራው በጣም ሞቀ። በእጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ በትርፍ ሆነ። ከኪራይ ቤት ተላቆ የራሱን ቤት የጨረቃም ቢሆን ገነባ። ሚስቱንና ልጁን ይዞ ወደ ገነባው ቤት ገባ። ስራውም እንደሞቀ ቀጠለ። ብዙ ገዥና ሻጭ ነጋዴዎች ለግባባት ቻለ። ህይወቱ እንደ አዲስ ደመቀች። ሆኖም በዚህ አልቀጠለችም። ድጋሚ ህይወት ወጥመዷን አጠመደችበት ለዛውም ሁለት ወጥመድ።  የገነባው የጨረቃ ቤት በመንግስት ግብረ ሀይል ህገ ወጥ ነው በሚል ፈረሰ። ወደ ክራይም ቤት ተመለሰ። በዚህ አላበቃም። በመርካቶ በሱቁ አቅራቢያ በተነሳው የእሳት አደጋ ወደነሱ ሱቅ ደርሶ ሙሉ ንብረቱ በአንድ ምሽት በእሳት ተደመሰሰ። ወደ ችግር ኑሮ ተመለሰ።  አሁን ግን ወደ ጉልበት ስራ አልተመለሰም…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 5
    ጓዴ ፓፒዮ  ቤቱ ህገወጥ ነው ተብሎ በፈረሰ ሰሞን… የንግድ ቤቱ በእሳት አደጋ መደምሰሱን አይተናል። ጓዴ ከዛስ ቡሃላ ምን ገጠመው? እንዴትስ ሆነ? ተመልሶ ወደ ጉልበት ሰራ ተሰማራ? ለሚለው ጥያቄ መልስ እነሆ …

ከእሳት አደጋው ቡሃላ ወደ ጉልበት ስራ አልተሰማራም። ምክኒያቱም በመርካቶ የንግድ ቤት ሲቃጠል በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ አደጋው ለደረሰበት አካል መልሶ የሚቋቋምበትን የገንዘብ እርዳታ የማድረግ ልምድ አለ(ነግ በኔ ነዋ)። በዚህ መሰረት ለነ ጓዴ ፓፒዮ ከተሰበሰበው የእርዳታ ገንዘብ  የድርሻው ተሰጥቶት መልሶ ለመቋቋም በቃ። ስራውን ቀጠለ። በዱቤ ወስዶ በእሳት የነደደበትን የንብረት እዳ አየከፈለ እየከፈለ አጠናቀቀ። ይህም ለእድገቱ ማዝገም ምክኒያት ሆነ። ሚስቱ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች። ህይወት እንደገና በደስታ ይመራት ጀመር።  ••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 6
  የጓዴ የህይወት ስንክሳሩ ገና አላበቃም። ከእሳት አደጋው አገግሞ ሁለተኛ ልጅ ተወልዶለት። ራሃ የሆነ ህይወት በመምራት ሳለ… ሁለተኛ ልጁ ከዚህ አለም በሞት ተለየው። አሁንም አላበቃም… በቀድሞው መሬት ላይ  ድጋሚ የሰራውም ቤት ድጋሚ ፈረሰ። ደግሞ ይግረምህ ብታምንም ባታምንም ለሁለተኛ ጊዜ ሱቁ በተመሳሳይ አደጋ በእሳት ወደመ። እርዳታውም ተደግሞ አሁንም ስራውን ጀመረ። በተከታታይ አደጋ ምክኒያት የተሸከመው እዳ ለተዳከመ ሱቁ መንስኤ ሆነ። የበፊቱን እዳ ሳይከፍል ሌላ እቃ የሚያገኝበት መንገድ ጠበበ። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ መኖሩን ተያያዘው። አልሞተምም  አልጠፋምም የሆነ አይነት ላይፍ።

  የጓዴን የህይወት ውጣ ውረድ ስታነበው እራሱ ጨነቀህ አይደል። እኔ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ብለህ አላሰብከውም?። እኔ በግሌ የማብድ ነበር የሚመስለኝ። ግን ደግሞ አንድ እውነት ልንገርህ። አንዳንዴ ለማይችል አይሰጠውም ይባላል። ታሪኩን የምነግርህ ጓዴ በሚደርስበት መከራ ልክ የመቻያ ጥበቡን አፍስሶበታል። እንተ ስታነበው ያስጨነቀህ እሱ ተውኖት እንዳንተ አልተጨነቀም። ከምሬን ነው። ብረት የሰው ብረት። ትላንት ባለሱቁ ሆኖ ዛሬ የጉልበት ስራተኛ ሲሆን ምንም የስነልቦና ጫና የማያድርበት የሰው ብረት ነው። ከዚህ ቡሃላ ጓዴ ፓፒዮ  ከኔ ጋር በስራ የሚያስተሳስረን ሁኔታ ተፈጠረ። ከዚህ ቡሃላ እስከተወሰነ ድረስ ያለው ታሪኩ ከኔው ጋር የተሳሰረ ስለሆነ አንድ ላይ ለተርከከክልህ…
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 7
     እኔ የጓዴን በዝምድናም ጭምር የመጣ የህይወቱን እርምጃ በቅርበት በማየት ጠንቅቄ አውቅ ነበር። ትምህርት ጨርሼ ቀጥታ ወደስራው አለም ስሰማራ ጓዴ ሰራ ያለማምደኝ ዘንድ በደንብ ቀረብኩት። ከቤት በብድር መልክ በቀፈልኳት ብር እቃ እየገዛው ለሱ ሱቅ ማቅረብ ጀመርኩ። ቅርበታችን ጠበቀ። ስራውም ሞቀ። በዚህ መሃል አማከረኝና አትርፎ ለመሸጥ መሬት ገዛ። የኔም ሆነ የሱም ገንዘብ መሬቱ ላይ አደረ። ከዛሬ ነገ ይሸጣል ያልነው መሬት ገግሞ ቁጭ አለ። በዚህ የመጣ ስራ ፈታን። ቁጭ ብሎ መዋል። ቁልጭ ቁልጭ ብቻ ሆንን። እኔም ከቤት የወሰድኩት ብር ከምን ደረሰ(ይኼኔ ቀረጣጥፈህ ቅመኻት ነው) የሚለው ጭቅጭቅ ሲበረታ እውነቱን ነግሬ፣ እኔም አረፍኩ እነሱም አረፉት። መሬቱ አሁንም አልተሸጠም። የጓዴ ፓፒዮ መደብ የኔም ኪስ ኦና ሆነ። ከኔ ይልቅ የሱ ችግር ባሰ። ምክኒያቱም ብዙ እሱን የሚመለከቱ ሀላፍትናዎች ስለነበሩበት። ሶስተኛ የወለደው ወንድ ለጁም ድክድክ ማለት ጀመረ። በዛው ሰሞን ውጬ ከነበረችው እህቱ ገንዘብ ተላከለት። የላከችው ገንዘብና የእኔ በመሬቱ ላይ የዋለው ገንዘብ መጠን እኩል ነበር። ከቤት እንደተጨቀጨኩ ያውቅ ስለነበር አንስቶ ሰጠኝ። መቀበል አልሆነልኝም። እሱ መደቡ ባዶ ሆኖ፣ ሚስት ልጆቹ እጁን እየተጠበቁ ባለበት በዚህ ወቅት ያገኛትን ገንዘብ መውሰዱ ለህሊናዬ ጎረበጠኝ። ይሄን ገንዘብ መደቡን እቃ ሙላበት አልኩት የኔን መሬቱ ሲሸጥ ትሰጠኛለህ አልኩት። በደስታ የሚያደርገው ጠፋው። ወዲያው መደቡን ሞላ ስራውን ቀጠለ። እኔም መሬቱ እስኪሸጥ በትዕህስት መጠባበቁን ያዝኩ። ከእልህ አስጨራሽ ቆይታ ቡሃላ መሬቱ ተሽጦ ብሩን ለቤት ወስጄ ሰጠው። ጓዴ ከዚህ ቡሃላ የደረሰበትን ብዘረዝረው በወደድኩ ነገርግን ማሰልቸት ስለሚሆን ወደ ማጠቃለያው ልግባ ነገር ከዚህ ቡኋላ አንድ ጊዜ የመክሰርና 3 ጊዜ ቤት እንደፈረሰበት አልዋሽህም!! እንዴት የሚፈርስ ቤት ደጋግሞ ይገነባል? የሚል ጥያቄ ካነሳህ። ከላይ ያሰበውን ካላሳካ ምንም ተስፋ አይቆርጥም ብዬህ አልነበር ለዛ ነው።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ምዕራፍ 9
  ጓዴ ፓፒዮ በሚሰራበት ሱቅ እኔም ድጋሚ ብር ቀፍዬ መደብ ተከራይቼ መስራት ጀመርኩ። ሁለት አመት ከምናምን እንደሰራን ከምንሰራበት ሱቅ ሁላችንም እንድንለቅ ተደረገ። መደብ ላይ የነበረኝን ሸቀጥ ጭኜ ካደጉበት ጊቢ ውስጥ ደርድሬ መሸጥ ጀመርኩ። ጓዴ ፓፒዮንም ከኔ አጠገብ እንዲሰራ አደረኩት። ያለ ሱቅ ኪራይ ጊቢው ውስጥ ንግዱ ለመደልን። የጓዴም ባለቤት የስራ ቦታው እየቆመች እሱ ውጪ ውጪ ሌላ ስራ መስራት ጀመረ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በግቢው ውስጥ ስራ እኔ ከስራው ጨዋታ በኪሳራ ስወጣ። ጓዴ ውጪ ዉጪ በሚሰራው ስራ ያልታሳበ ለውጥ አመጣ። አንድ ሁለት ሰዎችን ጨምሮ በስማቸው ፌስታል ማስመረት ጀመሩ። የፌስታሉ ስራ እንደሮኬት ተኮሳቸው። ያርግላቸው!! እኔም ወደሌላ ፊልድ ተዛወርኩ። ጓዴ በእልህ ደጋግሞ የፈረሰበትን ቤት ሰራ። ቤቱ እራሱ በህጋዊነት ፀደቀለት። መኪናም ገዛ። ህይወቱ በአጭር ጊዜ  ተለወጠች። ለረጅም አመት ያንከራተተችው ህይወት እጅ ስላልሰጠላት ዛሬ እጅ ሰጠችው። ባለ ሀብት ከሚባለው ደረጃ ደረሰ። ከራሱ አልፎ ለኔም በቃ። ከረጅም አመት ቡሃላ አጎቱን ጠየኩት። መክሰሩን ኑሮው እንደድሮ አለመሆኑን። ባጠፋውም ጥፋት ለይቅርታ ሽማግሌ እንደላከበት፣ እሱም ይቀርታውን እንዳልነፈገው… እያጫወተኝ አዲስ በሰራው ቤት ምርቃት ላይ በደስታ አሳልፍን። በችግርም በደስታ ሳይለየን ለዚህ ላደረሰን አላህ ምስጋናችንን ይድረሰው። ከዚህ ጓዴ እኔ ብዙ ነገር ተምሬያለው። ምን ቢጨልም መንጋት እንደማይቀር የጓዴ ፅናት ምርጥ ማሳያ ነው። አንተም የተስፋ አለመቁረጥን ፍሬ ከጓዴ ፓፒዮ የተማርክ ይመስለኛል… ካሰለቸውህ አፉ በለኝ!! ለማንኛውም ትርተራዬተፈፅሟል ።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment