Sunday, June 12, 2016

" ር ዕ ስ አ ል ባ ው ወ ግ "


#ሳteናw  

  በህይወቴ  አስደሳችም አሳዛኝም ገጠመኞች ያሳለፍኩ ቢሆንም ቅሉ በደስታ ማግስት ስለተከሰተው አሳዛኝ ገጠመኝ ተነበበም አልተነበበ አከትበው ዘንድ መንፈሴ መራኝ…

  የመርካቶ ጎረቤቶቼ  ሴት ልጃቸውን ለመዳር ሽር ጉድ ማለት ጀመሩ። በዚህም ምክኒያት መንደሬ እጅግ ግዙፍ የሰርግ ለማስተናገድ አጋጣሚውን ብታገኝም ለታቀደው ግዙፍ ድግስ  መመጠን ባለመቻሏ መገናኛ 22 ማዞሪያ አካባቢ ትልቅ ቪላ ተከራዩ። ይህ ቤት የግቢው ስፋት ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ የግቢው በር ሲከፈት በብዙ ዛፎች የተሞላና የአስፓልት መንገድ አንጂ ሌላ አይታይህም። እስፓልቱም ተዘርግቶ በዛፎቹ ውስጥ ተጠማዞ ይሰወርብሃል፣ ጭራውን ለመያዝ ተከተልከው ስትሄድ ሴሌሜ ሴሌሜ ካጫወተህ ቡሃላ ዋናው ቪላ በድንገት ከፊትህ ገጭ ይልብሃል። የሆነው ሆኖ በዚህ የቤተመንግስት ስፋት ባለው ቪላ ሰርጉ ተዘጋጀ። ለመትከል ቀናት የፈጀና ተሳቢ መኪና የሚያስዞር ሙሉ በሙሉ ነጭ የሆነ ድንኳን ተጣለ። ከግቢው ትልቅነት የተነሳ እንደ አከንባሎ የተጣለው ድንኳን የያዘው ቦታ ምንም ነበር። የባንድ የዲኮር የምግብ የመጠጡ ነገር አንደ ግቢው በሰፊው ለሰርጉ ተሰናዳ። በሚገርም ሁኔታ ሰርጉ ተከናወነ። ሰርጉ ደምቆ ቢያልፍም በማግስቱ ተያይዘው የመጡ ብዙ አደጋዎች አስከተለ። ወንድሜ ኪያር በዚህ ሰርግ ላይ ቀኑን በተከራየው ዳትሰን መኪና ሲያጅብ ውሎ። ለሌቱን ከጓደኞቹ ጋር ሮንድ ወጡ ለመጨፈር ከክለብ ክለብ ሲዞሩ አገር ሰላም ብላ ጥጓን ይዛ የተኛች ጎዳና ተዳዳሪ ላይ ወጥቶባት ደስታቸው ወደ ሀሰን ዳንሳቸው ወደ ሙሾ ተቀየረ። ታሰረ።በዋስ ተፈታ። የገጫትን ሴት እየተመላለሰ አስታመመ። ጠያቂ ዘመድ የሌላት ብቸኛ ሴት ነበረች። በስንተኛው ቀን ሞተች ይህን በተመለከተ አንድ ቀን ለአይን አባቴ ጋሽ ሼሂቾ ቂማ ላይ ስለገጫት ሴትዮ ይጠየቁት ጀመር…
"ሴትየዋ ሞተች?
"አዎ" አለ ኪያር።
"ወጣት ነች እንዴ?"
"አረ አይደለም አሮጊት ነች። እጅም እግርም የላት! በዛ ላይ አይነ ስውር ነበረች አለ።" ሙሉ ሰው አይደለም የገደልኩት በሚመስል ስሜት።
"ታዲያ መጀመሪይም የሞተች ነው የጨረስኩት አትለኝም።"
አፌን ደፍኜ መሳቅ ቃጥቶኝ በርቼ ፈርቼ ዋጥኩት።

     ሰርጉ በተከናወነ በሁለተኛው ቀን ማለትም ማክሰኞ ምሽት የመልሱ ድግስ ቀጠለ። ከከተማም ከክፍለ ሃግር ወዳጅ ዘመድ መጣ። ከነዚህም ውስጥ ሁሴን የተባለ ከአለታ ወንዶ የመጣው ዘመዳቸው ይገኝበታል። ሁሴን ለደጋሹ ቤተሰብ ቅርብ ዘመድ ስለነበር ከክፍለሃገር ቢመጣም ሲየስተናግድ አመሸ። ሰርገኛ ተበትኖ የተወሰነ ሰው ቀረ። ያትልቅ ቪላ በእንግዳ ሞልቶ  የምንተኛበት ክፍል አጥተን በረንዳ ላይ ተቀምጠን ለማደር ተገደድን። በረንዳ ላይ በተቀመጥንበት ሁሴን በምድጃ ከሰል ይዞ መጥቶ አያይዙልኝ አለ። ከሰሉን አያያያዝንለት። ማደሪያ ክፍል ማግኘቱን ነገረን። ነገር ግን ማንም ከኔ ጋር አይድርም ክፍሉ ቀዝቃዛ ስለሆነ ነው እሳት አቀጣጥዬ የምተኛው አለ። እባክህ አንተ ምታድርበት ክፍል አሳድረን የሚል ተማልኖ ከሁላችን ቢቀርብለት አይሆንም ብሎ ያቀጣጠልንለትን ከሰል ይዞ ሄደ። ሁሴን የሚያድራብት ክፍል ከዋናው ቪላ ማደዶ ተገንጥላ ለብቻዋ በጎጆ ቤት ቅርፅ  በግንብና በቆርቆሮ የተሰራች ቤት ነበረች። ይህቺ ቤት ለሰርጉ ድግስ ለመጡ መጠጦች እነደመጋዘንነት አግልግላለች። ሁሴን ከሰሉን ይዞ ወደዚህች ክፍል። ምድጃውን ከክፍሉ  አማካኝ ቦታላይ አስቀመጠው። የሚተኛበትን መኝታ አነጣጠፈ። ከብረት በሩ ስር የነበረውን ክፍት ሽንቁር ብርድ አንዳይገባ በሚል በጆንያ ዘጋውና ተኛ። እኛም ለሊቱን ስናወራና ስንስቅ ስነጫወት አነጋነው። ጠዋት ሰው መነሳት ሲጀምር።  በተነሳ ሰው ቦታ ላይ ደቀስን።

  … የሙሽሪት እናትና የሰርጉ ዋና ደጋሽ እትዬ አሚና። የሁሴን አርፍዶ መተኛት አሳስቧቸው ወደ ተኛበት የግንብ ጎጆ ሄዱ። በሩን ቆረቆሩ። መልስ የለም። በስሙ ጠሩት አሁንም መልስ የለም። ሰውዬው ምን ነካው? ሁሴን!  ሁሴን! አረ ሁሴን! " አሉት። ወይ ፍንክች። የማታውን የሁሴን ከሰል ይዞ መግባት ጠቆምን። ይህን ሰምተው ሰርግ ደጋሹ ቤተሰብ ተሸበረ። መስኮት ተገንጥሎ ለመግባት ታቀደ።  ይሄ ሁሉ ሲንጓጓ የሁሴን አለመንቃት በህይወት እናገኘዋለን የሚለው የሰው ምኞት ጠፋ። ምናልባት ራሱን ስቶ እናገኘው ይሆናል የሚለው ተስፋ አንሰራርቶ መስኮቱ በስንት ጔጔታ  ለመከፈት በቃ። አንድ ሰው ገብቶ ቢያይ ምድጃው ላይ የነበረው ከሰል ከስሎና አልቆ አመዱ ብቻ ቀርቷል፣ ሁሴንም በተኛበት ክልትው ብሎ ደርቆ ተገኘ። ወዲያው ለፓሊስ ተደውሎ ሪፖርት ተደረገ። ፖሊስ አንቡላስ ይዞ ከተፍ አለ። ካለው ልምድ በመነሳት ሁሴን የገደለው የከሰል ጭስ መሆኑን አስታውቆ ሬሳውን ለምርመራ ብሎ ይዞ ሄደ። ዋዜማውን በመልስ ድግስ በርቸስቸስ ብለው ያደሩ የሙሽሪት ቤተሰቦች። ማግስቱን ከምኒሊክ ሆስፒታል የተረከቡትን ሬሳ ኮንትራት በያዙት ካቻማሌ ጭነው ለሚስትና ለልጆቹ  እረፍቱን ለማርዳት ወደ አለታ ቀንዶ ሄዱ!። የሟች ከአንድ ቀን በፊት በጤንነቱ የተለያቸው ሰው ዛሬ ሬሳው ተጭኖ ሲመጣላቸው ምን ይል ይሆን!!አላህ ለሁሴን ጀነትን ይወፍቀው። ከማለት በቀር ምን ይባላል? በህይወቴ አሳዛኝ ከምላቸው ገጠመኞች ይሄ አንዱ ሆኖ አለፈ።አላህ ከንደዚህ አይነት ደስታ ተከትሎ ከሚመጣ ሀዘን ይጠብቀን።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment