Sunday, June 12, 2016

" ያ ል ተ መ ለ ሰ ው …… ረ መ ዳ ን"


#ሳteናw

   … የተኛበትን የሆስፒታል አልጋ ግርጌው ላይ ተቀምጬ እግሩን አያሻሸው እንዲያወራኝ እንባ በተጋገረበት አይኔ እለማመጠው ያዝኩ። መልስ ሊሰጠኝ ቢፈልግም አልቻለም። አጠገቡ በተቀመጥኩበት አንድ  የቤተሰብ አባል ከራስጌው መጥቶ ተቀመጠ። የዚህኔ ታላቅ ወንድሜ ጎታ ሁለት ቃላት ከአንደበቱ በስንት ትግል ሲወጡለት ሰማው። "ሳራን አደራ" (ባለቤቱን ማለቱ ነው) …  ቃላቶቹን ስሰማ እንደማይተርፍ ገብቶት ተስፋ መቁረጡን አወኩ። ቀድሞውንም ዳር ዳር ሲለው የነበረው እንባዬ ተንቧቧ። ሮጬ ከክፍሉ ወጣው። በዛው በሸከከኝ ስሜት ተይዤ ወደ ቤት ተመለስኩ…
★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★

ቀጥሎ የማስነብብህ በ93ና በ94 ዓ/ም አስደሳችም አሳዛኝም ገጠመኝ ያሳለፍኩትን የህይወቴ ቅንጭብ ታሪክ ነው!! የማንበብም ያለማንበብም መብትህ የተጠበቀ ነው!!

  በ93 ዓ/ም ስድስተኛ ክፍል ደረስኩ። ታላቅ እህቴ ሽቱ ዘጠነኛ ክፍል ደርሳ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ገባች። ትልቋ እህቴ መይሙና ከስምንት አመት የጅዳ ቆይታ ቡሃላ ለሀገሯ በቃች። የሷን መምጣት ተከትሎ ቤታችን ሽቅርቅር አለች ሶፋ፣ ብፌ ፣ ብዙ ዘመናዊ የተባሉ ቁሳቁሶች ተሟሉላት። በእህቴ ሽቱ ጋዝ ይቀባ የነበረው የቤታችን የእንጨት ወለል ሰም መቀባት ጀመረ። መቀባቱስ ባልከፋ። የሰሙ መቀባት አያቴን ለወጪ እኔን ለነፃነት ማጣት ዳረገን። ይህን መሰረት ያደረገው ከታላቅ እህቴ ሽቱ የተሰጠኝ ዛቻ ተካታዩ ሆነ። 

"ታዲያ እንደ በፊት አስሬ ገባለው ወጣለው ብትል ኩርኩሜን ታቃታለህ አይደለ? የሚያስገባህ አስገዳጅ ነገር ከተፈጠረ በርኖስ አለ በሱ ላይ እየተንሸራትክ ገብተህ ትወጣለህ።"

  ያለኝ አማራጭ አለመግባት ወይም ሰሙ የሚቀባበትን በርኖስ ረግጭና ከወለሉ አጣብቄ በሱ እየተንሸራተትኩ መንቀሳቀስ ሆነ። ግን ምን ዋጋ አለው እግሬን እያንፏቀቅኩ በመንሸራተት መሄድ አልሳካልህ አለኝ። ከአንዴም ሁለት ሶስቴ በአፍጢሜ ተደፍቼ ጥርሴን ከመትፋት ለጥቂት አመለጥኩ። አያቴም ቀድሞውኑ የወጪውም ነገር ስላልተስማማት
"ልጄን ልትገዩው ነው እንዴ?" በሚል ሰበብ ሰም ለመግዛት የመደበችውን ባጀት አቆመች። ወለላችን ወደ ጋዝ፣ እኔ ወደ ነፃነቴ ተመለስን።

  ዲያስፖራ እህቴን  መይሙናን ከኤርፖርት እኔና ታላቀወ ወንድሜ ጎታ ሆነን ተቀበልናት ከያዘችው በርካታ ሻንጣና ካርቶን ጋር ይዘን ቤት ገባን። ከዚህች ቅፅበት ቡሃላ ቤታችን ለተወሰነ ግዜ የአረብ ቤት የአረብ ቤት ሸተተች። የሚሰሩ የምግብ አይነቶች ወደ አረቡ አለም ያደሉ ሆኑ። ሽቱና መይሙና በጋራ ቤታችንን ከውጪ ከመጣው ቁሳቁስ ጋር በሁሉም ረገድ ለወጧት። የቤታችን መለወጥ በርካታ የጎረቤት ጎረምሶችን ሳበች።

   የቤተሰብ አይሱዙ ሹፌር የነበረውና  ከአንድ አመት በፊት ያገባው ወንድማችን ጎታ በሚስቱ ቤተሰቦች በተዘጋጀው መልስ ለመገኘት ወደ አዋሳ ሄድን። የመርካቶ ጓደኞቹ አንድ ሳይቀሩ ተከተሉት።የመልሱ ድግስ እራት ስለነበር ቀኑን ከሙሽሮቹ ጋር በአዋሳ ሀይቅ በመዝናኛ ቦታዎቿ ስንዞር ፍቶ ስንነሳ በጀልባ ስንሄድ አሳለፈን ወደ ድግሱ ቦታ ደስ በሚል እጀባና የመኪና ክላክስ ታጅበን ደረስን። ቆንጆ ድግስ ሆኖ አለፈ። ሁላችንም ወደ አዲስ አበባ ተመለስን። ከዚህ ቡሃላ እኛም ጎታን መልስ መጥራታችን የሚጠበቅ ስለሆነ። የመልስ ዝግጅት ተጀመረ። የመርካቶ ጊቢያችን በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ድል ያለ ሰርግ አሰተናገደች። ግቢው ሙሉ በሙሉ በዲኮር ደመቀች።የመልሱ ፕሮግራም በደመቀ ሁኔታ ተጠናቀቀ። አያቴ በመይሙና በተነደፈው  ስትራቴጂ መሰረት እቀድ ስራ አስፈፃሚነት ተይዛ  ቢዚ ሆና አሳለፈች።

ይህ በንዲህ አንዳለ የረመዳን ወር ገባ። የዚህ አመት ረመዳን ካለፉ የረመዳን ወሮች በቤተሰባችን ለየት የሚያደርገው። የእህቴ መይሙና እና የወንድሜ ጎታ ከነሚስቱ እና መላው ቤተሰብ በአንድ ማዕድ ተሰባስበን ማሳለፈችን ሆነ። ፣ ለአፍጥር የሚሰሩ ምግቦች ብስኩትና የጭማቂ መጠጦች ከዚህ ቀደም በቤትም ሆነ በጎረቤት ያልታዩ ነበሩ።  የታላቅ ወንድሞቻችን ባልንጀሮች ከአፍጥር ቡሃላ እስከ ኢሻ ድረስ በኛቤት መሰባሰብ ወዘተ…  ካለፉት የረመዳን ፆሞች ለየት ያደረጉት ሆኑ። በንደዚህ አይነት ሁኔታ የረመዳኑ ፆም ደማቅ ትውስታ ፈጥሮ ይህን መሰሉ ፆም በቤተሰቡ ላይመለስ ሄደ። ፆሙ አይደለም ያልተመለሰው። ቤተሰቡ ተሟልቶና በደማቅ ሁኔታ ማሳለፉ እንጂ። ያልተመለሰው ረመዳን ብየዋለው።

  ከተወሰኑ ጊዜያት ቡሃላ  ወንድሜ ጎታ ላይ የአቋም ለውጥ ማየት ጀመርኩ። ሰውነቱ ቀን በቀን መቀነስ፣ አብዛኛውን ጊዜ ለብቻው ማሳለፍ፣ እንደበፊት መሳቅ መጫወቱ መደብዘዝ ጀመረ። በዚህ አላቆመም መኪናዋን ኪያር እንዲነዳት አድርጎ እሱ ገቢና መቀመጥ ጀመረ።

94 ዓ/ም  ገባ። ዘጠና ሶስት ቤታችንን ደስታ በደስታ እናዳደረጋት ሁሉ። 94 የቤታችን ደስታ ላይ የሀዘን ጥላውን ያጠላበት ገባ። ወደ ሰባተኛ ክፍል መግባቴን ተከትሎ ከታች አባድር ወደ ላይ አባድር ዛወርኩ። በዚሁ አመት እህቴ ሽቱ ወደ አረብ አገር ሄደች። ቤታችን የጭርታ ፅልመት ገና በሄደች ቀን አለበሰው። በዚህ ቀን ምሽት እንዲህ ሆነ።

(ለሊት እኔና አያቴ በተኛንበት ድንገት ነቃው። ደብዛዛው ዜሮ አምፖል በርቷል። የሽቱን መኝታ ሳየው ባዶውን አገኘሁት። አንዳች ሀዘን አንጀቴቴን አላወሰው ስቅ ስቅ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ። ለቅሶ ዬ አያቴን ቀሰቀሰ። ያለቀስኩበት ምክኒያት ስለገባት ታባብለኝ ገባች። በማባበል ሂደቱ አልገፋችበትም አቅፋኝ ለቅሶዬን ተቀላቀለች። አልቀሰን አልቅሰን ሲደክመን እንቅልፍ ወሰደን።)

  ወንድሜ ጎታ ባላወኩት ምክኒያት ሙሉ በሙሉ ስራውን ለኪያር ሰጥቶ ቤት ተቀመጠ። ለረጅም ወር ድምፁም ጠፋብን። በመጨረሻ ሚስቱ ሳራ ደወለች። ጎታ በጣም አሞታል አለችን። ታላቄ ጨቦ ወደ አዋሳ ሄደ። በማግስቱ ጎታን ሳራን የአመት ልጁ አብዱረህማንን ይዞ ኪያር በመኪናው ይዟቸው መጣ። ደግፈው እቤት ሲያስገቡትና ቀድሞ በተዘጋጀለት ቦታ ሲያስተኙት… ጎታን ሳየው ዘይኔን ማመን አልቻልኩም። ከሰውነት ውጪ ሆኗል። መናገር አይችልም  ይህን ሳይ ወትሮውም ለእንባ ቅርብ የሆነው ትልቁ አይኔ የእንባ እንክብሎች ዘረገፉ።

   አያቴ በእንባ አላበቃችም ተነስታ እንደ ጦስ ጎታን ተሽከረከረችው "እያነባችና እኔ ጦስህ ልውጣልህ" በማለት። ይህ ድርጊቷ መላ ቤተሰቡን በእንባ አጠበው። ያችን ለሊት በለቅሶ ካነጋን ቡሃላ። አያቴ እንደወትሮዋ ዱዓ ለጎታ ለማስደረግ ቢላንቢሎ ሰርታ ወደጅ ዘመዶቿን ጠርታ ድኧ አስደርጋ ዋለች።  ማምሻውን ጨቦ ጎታን ወደ ሆስፒታል ወሰደው። ቤተ ዛታ ክፍተኛ ክሊኒክ ሳርቤት አልጋ ተያዘለት። በህመሙ ጊዜ አጠገቡ የነበረው ኪያር ከሱ ጋር አደረ። በማግስቱ እሁድ በጠዋት ተነስተን ልናየው ሄድን። ቤት አይቸው ከነበረበት ሁኔታ ግሉኮስና ኦክስጂን ከመደረጉ ውጪ ምንም ለውጥ አላየሁበትም። አሁንም ማውራት አልቻለም። ከሆስፒታል አይቼው ወጣው

  … ሳራን አደራ የሚለው የወንድሜ ጎታ ቃላቶች በጆሮዬ እያንቃጨለብኝ እቤት ስደርስ  ቤታችን የረበበው የፍራቻ ፅልመት በርትቶ ሌሊቱን አሳለፍን። በሌሊት ኪያር ደወለ። ሳራና አንድ ሰው ተያይዘው ሄዱ። ሳራ ተመልሳ ስትመጣ ወደግቢ የገባችው በለቅሶ ነበር። ምንድነው ምን ሆነ ብዬ ስጠይቃት። ደክሟል ሂድና እየው ብላ የታክሲ ሰጠችኝ። ልቤን ፍርሃት ፍርሃት እየተሰማው ጊዜ ሳላጠፋ ወደ ሳር ቤት ሄድኩ። ሆስፒታሉ ጊቢ ስደርስ ኪያር እያለቀሰ ደረስኩ። ጎታ ወደተኛበት ክፍል ብሄድም ዶክተሮቹ አላስገባ አሉኝ። በጓሮ በኩል ዞሬ በመስኮት ተንጠልጥዬ አየው። ወንድሜ ጎታ በጀርባው እንደተጋደመ አይኑ ኮርኒሱ ላይ ፍጥጥ ብላለች። በይህይወት ያለ ይመስላል። መሞቱን የተረዳሁት ግን  ነርሷ ጉልኮሱን ነቃቅላ የተንተራሰውን ትራስ አንስታ ፍራሹ ላይ ጭንቅላቱን አኑራ ፍጥጥ ብላ የቀረችው አይኑን ሽፋሽፍቱን ከድና  ከላይ የለበሰውን አንሶላ ፊቱ ድረስ ሸፍና ስታለብሰው ነበር። ከማንም በላይ የምወደው ወንድሜ ጎታ ሰርገን በደገስንለት በአመቱ ከዚህች አለም ተለየ። ወንድሜ ቃልህንስ ጠብቀን ይሆን?  አላህ ጀነተል ፊርደውስ ይወፍቅህ።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment