Sunday, June 5, 2016

"ቀ ል ጠ ው…   የ ቀ ሩ ት … የ እ ና ቴ …ጥ ር ሶ ቼ"

   አያቴ አያቴ፣መርካቶ መርካቶ እያልኩ አዛ አደረኩህ አይደል? ግድ የለም ዛሬ ስለ አያቴም ስለመርካቶም አልነዘንዝህም። ባይሆን ስለእናቴና ታናሽ ወንድሜ አስቂኝ ወግ ዘብ ላድርግልህ። የኢባዳ ግዜህን የሚሻማ ከሆነ ተወው እንዳታነበው በኔ ማሳበብ አይሰራም። እንኳን ባንተ ወንጀል በራሴም ወንጀል ሸክም በዝቶብኛል። ወደ ጉዳዩ…

    የታናሽ ወንድሜና የእናቴ ቅርርብነት በጣም ከምቀናባቸው ነገሮች አንዱ ነው። ቅርርብነታቸውን ላየ ሰው ወንድምና እህት እንጂ እናትና ልጅ መሆናቸውን ዲ ኤን ኤ ካላስመረመረ በቀር ለማመን ይቸገራል። እናቴ በተፈጥሮዋ ነገርን ቀለል አድርገው ከሚመለከቱ ወይም ከማያካብዱ ሰዎች ትመደባለች። በአጭሩ ጣጣ የላትም ልበልህ። የእናትነት ወግና ክብሯን ያልጣሰ ለዛ ያለው ቅርርብነታቸው መሀል የሚፈልቁት ቀልድና አስቂኝ ቁም ነገሮች የዘመናችንን ኮመዲዎችን የሚያስከነዳ ሳቅ ይፈጥሩልኛል። ይሄ ሳቅ ሲናፍቀኝ ወይ ሲከፋኝ እናቴ ጋር ሄጄ በሁለቱ መካከል የሚደረገውን ቀልድ ቁምነገር ነክ በሆነው ጨዋታቸው መሳቅና የተከፋሁበት ነገር መርሳት የአልፎ አልፎ ተግባሬ ነው። ሁሌም እናቴ ቤት ስሄድ ዚያራ ብቻ ሳይሆን ተዝናንቼ እንደምመጣ አልዋሽህም። ለምን ይሆን ከኔ ወይም ከሌሎች ልጆቿ ገር እንደ እሱ ማንቀራረበው? ስል ብዙ ጊዜ ራሴን እጠይቃለው። በቅናት አይደለም አለ አይደል ለማወቅ ያህል። (ለነገሩ እኔ ከአያቴ እንጂ ከሷ ስላላደኩ ይሆናል እንደሱ ያልተቀራረብነው።)

    እናቴና ወንድሜ ህብረት ፈጥረው ዘና ካደረጉኝ ጭውቴዎች አንድ ላካፍልህ (ምናልባት እኔ ዋና ሀሳቡን እንደነሱ ቀልዳዊ ለዛ ሳልቀላቅል ስለፃፍኩት ላያስቃችሁ ይችላል። ከዚህ በፊት እናቴ እንዴት ትንሽ የተነቃነቀ አንድ ጥርሷን በራሷ እጅ ሁለት አድርጋ እንደነቀለቸው እየተቀባበሉ ሲነግሩኝ … በሳቅ አንብቻለው "የናቴ የፊተኛውት አንድ ጥርሷ ወልቆ የተነሳቸውን ፎቶ ውጪ ላለችው እህቴ ላኩላት። በዚህ ያዘነችው እህቴ በቃ እኔ አስተክልልሻለው ስትል ቃል ገባችላት። በቃሏ መሰረት እዚህ ከምታጠራቅመው ብር ላይ ተወስዶ እንዲተከልላት የእናቴ እህትና የወንድሟ ሚስት…ነገረች። እነሱም ለእናቴ ይህን ዜና ይዘው መጡ።እናቴም ከተነቀለው ጥርሷ አጠገብ ያለው ጥርስ በስሱ መነቃነቁን ስትነግራቸው። በቃ የማስነቀያ  ወጪ ለመቀነስ  የተነቃነቀውን ጥርስ እራስሽ እያባበልሽ ንቀዪው፣ ከዛ በሚቀጥለው አስራአምስት ቀን ወስደን እናስተክልልሻለን ይሏታል። በዚህም መሰረት እናቴ ጥርሳን  ለመንቀል ትሸቀሽቀው ጀመር … ከሱ አጠገብ ያለውም ጥርስ ተነቃነቀና አንድ ላይ ሁለቱንም ጥርሶች በቀናቶች ውስጥ ነቅላ መጠበቅ ጀመረች። አስራ አምስቱ ቀን ሳይገባደድ ፓስፖርቷ በመጥፋቱ ያለ ህጋዊ መንገድ ትሰራ የነበረችው እህቴ መያዟን ጓደኞቿ ደውለው አረዱን እስከዛሬ የላከችውም ብር እሷ ሳትመጣ እንዳይነካ ማለቷንም ጨመሩ። ቤተሰቡ በእህቴ መታሰር ገብቶ የእናቴ ይተከላል የተባለው ጥርስ ተረሳ። እናቴም ልጇ ታስራ ስለ ጥርሷ የማንሳቱ ሞራል የናት ወጓ ስላልፈቀደላት በዝምታ ተወችው። አይዞሽ አንድ ቀን እኔ አስተካክልልሻለው ብዬ ቃል ገባሁላት (አላህ ያሳካው!!) ይሄን እየተቀባበሉ እናቴና አብዲ ሲነግሩኝ ሆዴን እስኪያመኝ የሳቅኩት።

   ባለፈው ሳምንት አንዱ ቀን በሆነ ጉዳይ ሙዴ ተጦለበና ውዝግብግቤ ሲወጣ። በዛው ቀን እንደልማዴ ዘና ፈታ ለማለት… እናቴ ጋር ሄድኩ… ከሄድኩ ረጅም ጊዜ ስለነበር በናፍቆት… ጥብቅብቅ ካለ… ሰላምታ ቡሃላ…"አብዲ የለም እንዴ?" ስል ጠየኳት።ለስራ ክፍለ ሀገር እንደሄደ ነገረችኝ። ከእራት ቡሃላ ቡና እየጠጣን ከናቴ ጋር። ጨዋታችንን ማድራት ጀመርን…"ዳዳ(በፊት በስሟ እጠራት ነበር አሁን ዳዳ ብዬ ነው የምጠራት)"ዬ(አቤት)" "አንድ ሰሞን አብዲ ግድግዳውን በጥቅሶች መዓት ሞልቶት አይቼ ነበር አሁን ማን አነሳው?" "እህትህ ክፍለ ሃገር መሄዱን ስታውቅ ጨርሳ ገነጣጥላ አነሳችው" አለችኝና… ያን ሁሉ ጥቅስ ለምን ሊፅፈው እንደቻለ ዛሬ ስለሌለ ከመሰረቱ ትነግረኝ ገባች።(እናቴ  በስልጥኛ ነው ትነግረኝ የነበረው ወደ አማርኛ ለውጨው ነው።)

   ከዚህ በፊት ስራ የፈታ ሰሞን… እዚሁ ግቢ ውስጥ አላቂ እቃዎችን አምጥቶ ለመሸጥ በማሰብ ከአክስቱ የተወሰነ ብር ተበድሮ መጣ"። "እሺ"  "አንድ ሁለት እያለ ስራው ለመደለት። እዳውን ለመክፈል ዛሬ አምስት ነገ አስር እያለ በትንሽ ሳጥን ውስጥ ማጠራቀም ጀመረ። ብሩ ትንሽ ጠርቀም ሲል እና ውጪ የነበረችው እህትህ ትመጣለች የሚለው ወሬ ተገጣጠመ።" "እሺ" አልኳት። ወሬዋ መስጦኝ አየተመቻቸው።"በዚህ ጊዜ አቶ አብዲ ሆዬ እዳውን ዲያስፖራ እህቴ ትከፍልልኛለች ብሎ ተስፋ በማድረግ… የነበረውን ብር አውጥቶ ጋላክሲ ሞባይል ሊገዛ አሰበና ከዚህ ቀደም "ስመጣ አመጣልሃለው" ያለችውን አስታውሶ ጋላክሲውንም ታመጣልኛለች ብሎ… በግማሹ ብር ከስራው ጎን ለጎን  ጫት አምጥቶ ለመሸጥ ማሰቡን ነገረኝ።"
"እሺ"።
" ተው አንተ ልጅ እዚህ ሰፈር ለቃቃሚ እንጂ ቃሚ የለም ጫቱ አይሸጥልህም ብለው አልሰማ ብሎኝ የጫቱን ስራ ጀመረ። በዚህ መሃል እህታችሁም በሰላም መጣች። አንድ ሁለት ቀን ካሁን አሁን ጋላክሲ ግራንድ ካመጣችው ሻንጣ ውስጥ አውጥታ ትሰጠኛለች እያለ በተከፈተ ቁጥር ልቡም አብራው ትከፈት ጀመር። ከአልባሳት በስተቀር ከሻንጣው ጋላክሲ የውሃ ሽታ ሆነ። በድንገት ያሰበችውን ያህል ሳታሳካ በመምጣቷ የኔም ጥርስ ተነቅሎ እንደቀረው የሱንም ስልክ እንዳላመጣችለት ባውቅም በሁኔታው ከመሳቅ በቀር  እራሷ ትንገረው ብዬ አልነገርኩትም የሆነ ቀን ደፈር ብሎ ጨክኖ ቢጠይቃት! "በድንገት አይደል እንዴ ታስሬ የመጣሁት?" ስትለው ቆረጠለት። በእልህ እዳዬን እከፍለዋለው ብሎ ያጠራቀመውን በር ግማሹን ጫት ጀምሮበት ብር አልነበር?"አዎ" "ከሱ የተረፈውን ገንዘብ ላይ ሌላ ተበድሮ ጨምሮ ጋላክሲ የሚባለውን ስልክ ሊገዛ! ሊሄድ ሲል… እሺ ስትገዛ እሱ አይቶልህ ያጋዛህ (እኔን) ሂድ ብለውም አልሰማ ብሎኝ። ሄዶ ገዝቶ መጣ። ይህን ተከትሎ። የጫቱ ገበያ ሞተ። ከሚሸጠው ይልቅ የሚያድረው ሲበዛ፣ ከሚከስር እያለ ያደረውን ጫት ከጠዋት ጀምሮ እስከማታ መጨፍጨፍ ያዘ።አረ ባክህ አንተ ልጅ? ያልለመደብህን ነገር አታድርግ" ብዬ ሳቄን እያፈንኩ ብቆጣው። "ባክሽ! አትጦልቢኝ!" አለኝ። በል እሺ አልጦልብህም ብዬ ተውኩት።

በተደራረበበት ብስጭት ምክኒያት በየቀኑ ያደረውን ጫት ቅሞ ቅሞ ሲመረቅን ጥቅሶችን ፅፎ እያመጣ ግድግዳው ላይ  መለጠፍ ጀመረ!።
"አረ ይሄ ነገር አልበዛም ወይ?" ብለው። ቦታ ይዞ ቤት አጠበበብሽ?። ብሎ ኩም ሲያደርገኝ አሁንም ተውኩት። "እሺ… አልኳት የሳቅ ብዛት ሆዴን እያሳመኝ ጫወታዋን እንድትቀጥልልኝ።"የፃፈውን ጥቅስ አንብቤ መረዳት ባልችልም፣ በሰው አስነበብኩ…""ምን ይል ነበር?"። ባነበውም ከሷ መስማት ፈልጌ። " ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው!" እስኪያልፍ ያለፋል! ሰውን ማመን ቀብሮ! አሁን ረሳሁት ብዙ ነበር… እና እንዳልኩህ ከሚሸጠው ጫት አደሮበት የሚቅመው በዝቶ መክሰር ጀመረ። በዚህ ቢበቃው ምን ነበረበት?።" እናቴ ካ በሚለው ሳቋ ታጅባ ነበር የምትነግረኝ። ሳቋ እኔንም እያሳቀኝ።"ደግሞ ምን ሆነ…?"

  አንድ ቀን እንደልማዱ ያደረበትን ጫት ቅሞ እቃውን አገባብቶ፣ ጥቅሱን ለጣጥፎ ከጨረሰ ቡሃላ፣ ቻርጅ ላይ ሰክቶ ያዋላትን ሞባይል ሊከፍታት ቢታገል ቢታገል ጭጭ ምጭጭ አለችበት። ከምርቃናው ጋር ተጨማምሮበት በድንጋጤ ላብ ሲያጠምቀው ይታየኛል። አሳዘነኝ። ሁኔታው ደግሞ በጣም ሊያስቀኝ ታገለኝ። ምን ሆነብህ ብዬ ከጠየኩትም ይበሳጭብኛል ብዬ ፈራሁት። ቢጨንቀኝ  በተቀመጥኩበት ብርድልብሴን ተከናንቤ ሳቄን ለማፈን ስታገል… ከግድግዳ ጋር የተጋጨ የስብርባሪ ድምፅ ሰማው። ደንግጬ ክንብንቤን ገልጬ ባየው በንዴት ሞባይሏን ከግድግዳው ጋር አላትሟታል። እንደምስቅ ስላወቀ ቶሎ ከቤት ወጣ።" ብላኝ የምወደው ሳቋን ለቀቀችው። አብሬያት በመሳቅ ቤታችንን የሳቅ መድረክ አደረግናት። ዕለቱን ያናደደኝን ነገር በናቴ ጫወታ ስቄ አገባደድኩት።

አላህ ለእናቶቻችን ረጅም እድሜ ይወፍቅልን!።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment