Saturday, June 18, 2016

"ምክርና ቡጢ"

"ም ክ ር ና  …   ቡ ጢ "
#ሳteናw

  ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው" ይባላል።  ልክ ነው! ሁለቱም የሚከብዱት ለተቀባይ እንጂ ለሰጪው አይደለም። ግን በሰላም አገር ለምን ስለ ቡጢ? ባይሆን ስለ ምክር ጠቀሜታነትና ጉዳት እንዳስስ። ደግሞ ምክር ምን ጉዳት አለው? የሚል ጥያቄ ከመድረኩ ከተነሳ። ለመጥፎ ነገር መመከርና ያለ ቦታና ጊዜው የተሰጠ መልካም የምትለው ምክር እንደ ቡጢው አካልን ባይጎዳ ስነልቦና የሚጎዳበት አጋጣሚ አለ። እንዴት ለሚለው ጥያቄ መልሱን ወረድ ስትል ታገኘዋለህ። የሂፖቶምንስትሮስስኩፔዳሊኦ ፎቢያ ተጠቂ ከሆንክ ግን እዚህ ጋር ወራጅ ብለህ ልትወርድ ዲሞክራሲያዊው መብትህ ነው። ሂፖቶምንስትሮስስኩፔዳሊኦ ፎቢያ ምን እንደሆነ ባነንክ? (ረጅም ፅሁፍ የማንበብ ፎቢያ) ተጠቂ ማለት ነው። የስያሜው ርዝመት እራሱ የተገለፀውን ፎቢያ አላመጣብህም?  ካላመጣብህ የፎቢያው ተጠቂ ስላልሆንክ … አብረን እንዝለቅ…

   ☞ ምክር በእጅህ ሳይሆን በምላስህ የምትሰጠው መልካም ነገር ነው። ኪስህ ሳትገባ በንግግር ምታበረክተው ገፀ በረከት! በለው። ምክር ኪስ ሳትገባ ብታበረክተውም በዘመናችን ኪስ የሚሞላ ስራ ሆኗል። በከተማህ ጎዳናዎች ውር ውር ስትል አከሌ አከሌ የአማካሪ ባለሞያ የሚሉ ፖስተሮችን ሳታነብ የቀረህ አይመስለኝም። ታዲያ በመንደርህ እንደሚመክርህ ማህበረሰብ በነፃ የሚመክርህ መስሎህ ዘለህ ጥልቅ ስትል ከፊት ለፊትህ "ደረሰኝ ሳይቀበሉ አይክፈሉ" የሚለው ማስታወቂያ የንግድ ድርጅት መሆኑን ይገልፅልሃል። (አስበው ለምክር ሄደህ tin numbur) ስትጠየቅ… ህእ!)።

ወደ እነዚህ አማካሪ ድርጅቶች ምክር ፈልገህ ስትሄድ። በቅድሚያ ያለብህን ችግር ትናዘዛለህ። ችግርህን ያገናዘበ መፍትሔ የሚሰጥህን ምክር ታገኛለህ።… ልክ ሳይካትሪስት ጋር … ሄደህ ምንህን እንደሚያምህ ገልፀህ ህክምናውን እንደምታገኘው) በአማካሪ ድርጅቶች ምክር ተጠቅሞ ተስፋው ያንሰራራ ህይወቱ የተለወጠ ፣ትዳሩ ከመበተን የተረፈ እንዳሚኖር ሁሉ… ያለ ቦታና ጊዜው ችግርህን ሳያገናዝብ የተሰጠ ምክር ተስፋ ያጨልማል።

   ምክር ገፀበረከት የሚሆንልህም በአስፈላጊው ቦታና ጊዜ ስታበረክተው ነው።በዛውም መጠን ለሰጪው ቀላል ቢሆንም ወደ ተግባር ለሚለውጠው ተቀባይ ሊከብድም ላይከብድም ይችላል። ምክር በምላስ ብቻ ሳይወሰን በቻሉት ልክ ለተመካሪው በተግባር ማበርከትም የምክርን መልካምነት ያልቃል። በተመክሮ ህይወት ትለወጣለች። ተስፋ ታንሰራራለች። በተቃራኒው የተመካሪን ሁኔታ ያላገነዘበ መካሪ በሚሰጠው ምክር የበለጠ ተመካሪን የሚጎዳበት፣ተስፋ የሚያዳሽቅበት፣ ሞራል የሚገድልበት ሁኔታ አለ። እንደዚህ አይነቱ ከምክርነት አልፎ ቡጢ ይሆናል። እንዴት አትልም? በምሳሌ እንይ… በገንዘብ ችግር ረሃብ የተጠበሰ ሰው ባንተ ተስፋ ጥሎ ገንዘብ ትሰጠኛለህ ብሎ በጣም በይሉኝታ እንደራበው ብቻ ነገረህ እንበል… አንተ መራቡን እንጂ ማጣቱን ሳትረዳለት ምን ገዝቶ መብላት እንዳለበት… ብታማክረው ላንተ የመከርክ ቢመስልህም ለተመካሪው ከባድ መርዶ ነው… ተስፋ የሚያስቆርጠው ነው። ለዚህም ነው ምክር በጊዜው በቦታው ልክ ነው ጠቀሜታነቱ የምልህ።

  ሌላ ምሳሌ… በገንዘብ እጥረት መክሰር  ላይ ላለ ነጋዴ ሄደህ የተዳደከመ ሱቁን አንዲሞላ ይሄን እቃ አምጣ ይሄን መደርደሪያ አሳምረው… የዕቃ አማራጮችን በካሽ እንዲገዛ መምከርም ልክ እንደዛው ምክር ሳይሆን ስላቅ ይሆናል። ምክኒያቱስ በብር እጥረት  መክሰሩን እያየህ… በካሽ እቃ ገዝተህ አምጣ በማለት ችግሩን ያላገናዘበ ምክር ሰጥተህ በቁስሉ እንጨት ሰደህ አቆሰልክው እንጂ መከርከው አይባልም።ዛሬ ይህን ሁሉ ለፈላሰፍና ልነዘንዝህ የቻልኩበት የራሴ ምክኒያት አለኝ። መዘርዘሩ አሰፈላጊ ስላልሆነ ዘልየዋለው። (መፅሀፉስ ዝለለው ይልህ የለ?)ዝለለው።ለማንኛውም በህይወታችን ሂደት ውስጥ መካሪ የምንሆንበት አጋጣሚ ተፈጥሮ የምክር ገፀ በረከት ለማበርከት ስንፈልግ… የተመካሪን  ነባራዊ ሁኔታዎችን አገናዝበን በሚገባ ተረድተንይገባል። እደግመዋለው!! የፅሁፉ ዋና አላማ ይከው ነው። ከመምከራችን በፊት የተመካሪን ሁኔታን በሚገባ ተገንዝበን መመከር አለብን ነው። አለዚያ ያለ ቦታው ምክር ለተመካሪው ቡጢ ሊሆን ይችላልና እንጠንቀቅ ነው። ካጠፋው ልጥፋ፣ ደግሞ አፉ በሉኝ!!
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment