Wednesday, June 8, 2016

ሰላም ያሰፈኑ ዝናቦች

"ሰላም ያወረዱ ዝናቦች"

   ሰኔ 1/1997ዓ/ም ዕለቱ ረቡዕ ነው። ልክ የዛሬ አስራ አንድ አመት። (ጊዜው እንዴት ነው የሚሮጠው በፈጣሪ?)። በማለዳ ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የለቅሶ ድምፅ ሆነ። ከተኛሁበት በድንጋጤ ተነስቼ ወደ ለቅሶው ድምፅ እየሮጥኩ ወጣው። ከአንድ ቀን በፊት የሞተ የታች ሰፈር ሰው ለቅሶ ለመድረስ ከክፍለሃገር የመጡ ሀዘንተኞች በበራችን እያለቀሱ እያለፉ ነበር። ተመልሼ ወደ ቤት ገባሁና ዩኒፎርሜን ለባበስኩ። በእለቱ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከሚፈተኑ ተፈታኞች አንዱ ነበርኩ። ቶሎ ቁርሴን በልቼ እርሳስና መቅረጫዬን ይዤ  ወደ ፈተና ሄድኩ። ሀገሬ በዚህ እለት ከረበባት ሊነሳ ይችላል የሚል የረብሻ ስጋት በተጨማሪ የብሄራዊ ፈተና ብቻ ሳይሆን ከመጀመሪያው አመኔታ አጥቶ የሚጠበቀውን የምርጫ ውጤት የሚገለፅበትና ብዙ ልጆቿን የምታጣበት ቀን ነበር። ጎጃም በረንዳ አካባቢ ከሚገኘው ሜይዴይ አንደኛ ደረጃ የህዝብ ት/ቤት በሰአቴ ደረስኩ። ከመፈተኛው ክፍል  በተሰጠን መፈተኛ ቁጥር መሰረት ወንበር ይዘን ተቀመጥን። ፈታኙ መመህር በቀጥራችን መቀመጣችንን ካረጋገጠ ቡሃላ ከብሄራዊ ፈተና ኤጀንሲ ታሽጎ የመጣውን የፈተና ኪስ ወረቀት እያየነው ቀደደና የፈተና ሽቶችን ለእያንዳዳችን ከፊት ለፊታችን ባለው ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦልን ጨረሰ። የጀምሩ ደውል ሳይደወል ወረቀቱን መንካት እንደማንችል ገልፆልን መጠበቅ ጀመርን።    የፈተናውን መጀመር ከሚያበስረን ደውል በፊት የጦር መሳሪያ ድምፅ ተሰማን። መብራት ሄዶ በተኩስ ድምፅ እንድንጀምር የተተኮሰ አልነበረም። ሊነሳ ይችላል የሚለው ስጋት ስጋ ለብሶ በመከሰቱ እንጂ። ተኩሱ ተደጋገመ በረታ። ለፈተና የተቀመጥነው ተማሪዎች በሽብር ታመስን። በምርጫው ውጤት የመጣ ረብሻ መፈጠሩን ለማወቅ ነጋሪ አላሻንም።

  የተኩሱ ድምፅ አልቆም ሲል የመፈተኛ ክፍሎቻችንን ለቀን መውጣት ጀመርን። በግቢው ውስጥ መጯጯህ  መራበሽ በረታ። የግቢያችን የብረት በር ከውጪ በድንጋይ ተደበደበ። ውጡ የሚል መልዕክት ከአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የተሰጠ መልዕክት ነበር። የፈተና ወረቆተቻችንን በጀርባችን ወሽቀን ዉጪ ከሚረብሸው አካል ለመቀላቀል ወደ በሩ ሮጥን። በሩ ሳንደርስ አድማ በታኝ ፌደራል ፖሊስ ከፊታችን ገርገጭ አለብን። ወደ ላይ አንዴ ዷ… አድርጎ መሳሪያዉን ሲተኩስብን ሩጫችን ወደ ተቃራኒው ሆነ። ከኋላችን ከሚከተሉን ተማሪዎች ፍት ለፊት ተላተምን። ረብሻው በረታ። የመሳሪያው ድምፅ ከዚህም ከዚያም ተንበቀበቀ። ጧ…ጧ… ድድው… ቡው… ቅ…!። የት/ቤቱ  የግቢው በር በአድማ በታኝ ሀይሎች ተያዘ።ተማሪው አስወጡን ቢልም ሰሚ አጣ። ያለው አማራጭ በሩን የያዙትን ሀይሎች የድንጋይ ናዳ ማዘነብ ሆነ። አንዳንዱ ጎበዝ ተማሪ ጥጉን ይዞ ፈተናውን ይሰራል። (የፈተና ወረቀቱን ማን እንደሚቀበለው እንጃ!) ሴት ተማሪዎች ጥግ ጥግ ይዘው የተባራሪ ጥይት ለመሸሽ ተሸጉጠዋል። አብዛኛው ደግሞ ከረብሻው ለመቀላቀል በትጋት ድንጋይ ይወነጭፋል። ከውስጥ የሚዘንበውን የድጋይ ዶፍ ለማቆም አንዱ ፖሊስ በሩን ገርበብ አድርጎ ጭንቅላቱን አስገብቶ ቁልቁል አየ። በአንድ ጓደኛችን የተወረወረ ድንጋይ እየተምዘገዘገ ወደሱ መድረሱን ሲያይ ጭንቅላቱን አውጥቶ አሸሸ ድንጋዩ በሩን ጓ! አድርጎ ወደቀ። የተወረወረበት ፌደራል ፖሊስ የሽጉጡን ቃታ ስቦ በበሩ ላይ ተኮሰ። ጥይቷ የብረት በሩን ቦርድሳና ተወንጭፋ ጓደኛችንን ላይ…  ትረፍ ሲለው ጡንቻውን ብቻ በጨረፍታ አገኘችው። የጓደኛችንን ደም ስናይ ይበልጥ ተደናገጥን።

   በድንጋይና በጦር መሳሪያ የሚደረገው ጦርነት በከፍተኛ ዝናብ ምክኒያት ጋብ አለ። ይህን ዝናብና በሚያዚያ30 1997 በቅንጅት በጠራ  ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የዘነበው ዝናብ ተመሳሰሉብኝ። ፈጣሪ ልጆቹ እንደያልቁበት በመለኮታዊ ሀይሉ ያወረዳቸው። ሰላም ያሰፈኑ ዝናቦች። ይህ ዝናብ ባይዘንብና ሁከቱ ባይቋረጥ ስንት ሰው ሊያልቅ እንደሚችል መገመት ይከብዳል።   በረብሻው ምክኒያት ብሄራዊ ፈተናችን ተቋረጠ። ረብሻውም በዝናብ ምክኒያት ቆመ። ሁከቱ ረገብ ማለቱን ተከትሎ የትምህርት ቤቱ በር ተከፍቶ ተለቀቅን። ወደ ውጪ ስንወጣ አስፓልቱ በድንጋይ ተሞልቶና ከዘነበው ዶፍ ጎርፍ ጋር ተደማምሮ የታረሰ መስክ መስሎ ጠበቀን። ሁላችንም በከፍተኛ ፍርሃትና ሽብር ጥግ ጥጉን ድክም ብሏቸው በቆሙ በተቀመጡ ታጣቂ ሀይሎች መሀል አለፍን፣ ከነሱ በራቅን ቁጥር ሰላማችን ሰፍኖ መሸበራችን እየቀነሰ መጣ። ከጓደኞቼ ጋር እስከ ቅያሳቸው እየሄድን በመጨረሻ ብቻዬን ቀርቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ። ወደ ቤት። ዩኒፎርም መልበሴና የፈተና ወረቀት መያዜ በታጣቂ ሀይሎች ምንም ክፉ ነገር አይገጥመኝም በሚል ራሴን አሳምኜ ተረጋግቼ ብሄድም ከዚህም ከዚያም ቁስለኛም ሬሳም ጭነው ውር ውር በሚሉ አምቡላንሶች (ወግቶ ቅቤ መቀባት ይሉሃል ይሄ ነው) ድምፅ መሸበርና መደንገጤ አልቀረም። መንገድ አሳብሬ ነካሁት።

   ወደ ሰፈሬ ቅያስ የሚያስገባው መንገድ በታንክና በአግአዚ ወታደሮች ከመወረሩ በቀር ምንም የሚታየኝ ነዋሪ የለም። ብቻዬን ነኝ። … በሁለት ታንክ በአንድ ኦራል ዙሪያ ተበታትነው በቆሙ ሰላሳ በሚሆኑ ቀይ ቆብ ለባሽ አግአዚ ወታደሮች መሃል ተማሪ አይነኩም በሚለው በራሴ ሂሳብ ተማምኜ ምንም አይነት የፈርሃት ስሜት ሳይሰማኝ ወደፊት ተጠጋኋቸው። በቋንቋቸው ያወራሉ። መሀላቸውን ሰንጥቄ አልፌ ወደ ሰፈሬ የሚያስገባውን ቀጭን መንገድ ያዝኩ። ከምቅፅበት የሚሰማኝ ድምፃቸው ጠፋና ቋ… ቋ… ቋ የሚለው የራሴ ኮቴ ብቻ ተሰማኝ። ከቅፅበታዊ ፀጥታቸው ጋር ተያይዞ አንዳች የስጋት ስሜት መላ አካሌን ወረረኝ። ሸከከኝ። ቀጭኗን መንገድ ጨርሼ ልታጠፍ ስል ዞሬ አየዋቸው። ጠላታችሁ አንዲህ ክው ይበል!! ልቤ በድንጋጤ ሁለት ቦታ የተሰነጠቀች ነው የመሰለኝ። ለካ ያሁሉ ወታደር ወሬውን ያቆመው ድፍረቴ ገርሞት አፍጥጦ አያየኝ ነበር። ከመካከላቸው አንዱ "በትግርኛ ቅላፄ …እንዳትበላሽ!" አለኝ ሌባ ጣቱን ቀስሮ እያወዛወዘብኝ… ከራቅኩ ቡሃላ  ድንጋይ የምወረውርባቸው መስሎት። እንዴት በሩጫ ቀጭኗን መንገድ እንዳተጠፍኩ አትጠይቁኝ። በሩጫ ታጥፌ ወደ ግቢ በር በሶምሶማ ስጠጋ። ሰው ሁሉ ገብቶ ታላቅ ወንድሜ ሌላ ጊዜ ከት/ቤት የምመለስበት ጎዳና ላይ አይኑን ተክሎ እየተቁነጠነጠ ይመለከታል። ስጠጋው ኮቴዬን ሰምቶ ዞረ። ሲያየኝ ትልቅ እፍይታ እንደተሰማው ከፊቱ ገፅታ ተመለከትኩ። በደንብ ስቀርበው ቀድሞኝ ገባና የግቢያችንን በር ይዞ ጠበቀኝ። ከገባው ቡሃላ በሩን ዘግቶ ተከተለኝ…

  "አንተ አንተ የምን ደም ነው ሹራብህ ጀርባ ላይ?"አለኝ።

"የምን ደም ኧረ እኔንጃ!" አልኩት።

"መቱህ እንዴ?" በድንጋጤ ነው የሚጠይቀኝ።

"አረ በጭራሽ"  አልኩት።

ታዲያ የምን ደም ነው?" ሹራቡን አወለኩ እውነትም ጀርባው ላይ ደም አለ። ምንም የሆንኩት ነገር የለም። ወንድሜ አካሌን ባለማመን ተጠግቶኝ ይመረምራል። ደሙ ት\ቤት ግቢ ውስጥ ጡንቻው በጨረፍታ የተመታው የጓደኛችን መሆኑን ነገርኩ ትና ተረጋጋ።  በዛው ቀን ከምሳ ሰአት ቡሃላ ፈተና እንዳለ ኔትወርክ እንደተለቀቀ ደውዬ አረጋገጥኩ። ሹራብ ቀይሬ ድጋሚ ወወደ ት/ቤት ሄድኩ። በመጠኑም ቢሆን የመረጋጋት ስሜት ሰፍኖ ነበር። የመሳሪያ እሩምታዎችም ከዝናቡ ቡሃላ ቆመው ነበር። ያለ መፈተኛ ቁጥር በዘፈቀደ ተቀምጠን መፈተን ጀመርን። ከሁላችንም ኋላ እንደኛው ለመፈተን የተቀመጡ ሁለት የማናውቃቸው ሰዎች ተቀምጠዋል። አስተያየቱ በሚደብር ፈታኝ እየተፈተንን ሳለን የት\ቤቱ ዳይሬክቶር ወደምንፈተንበት ክፍል ገብቶ ከተማሪዎች እየመረጠ ትከሻችንን እንደመደገፍ እጁን አያስቀመጠብን "ፈተና እንዴት ነው?" እያለ እኔን ጨምሮ ወደ አሰራአንድ ተማሪዎችን ጠየቀን። ነገሩ የተገለፀልኝ ፈተናው ካለቀ ቡሃላ ነበር። ለካ ዳይሬክተራችን ለፈታኛችንና ከኋላችን ለሚፈተኑ ሁለት ሲቪል ፖሊሶች እየጠቆመ ኖሯል። ፈተናውን ጨርሰን መውጣት ጀምርን። በዳይሬክተራችን ከተጠቆምነው ልጆች በምን ተአምር እኔ እንደተረፍኩ ባላውቅም ሌሎቹ በሙሉ እየተያዙ ቤሮ ተቆለፈባቸው። ኦራሉ መኪና ሲመጣ ወደ ዝዋይ ጫኗቸው። በተአምር መትረፌ እየገረመኝ ቶሎ ብዬ ወደቤት ሄድኩ። ዝዋይ የተጫኑ ጓዶቼ የማግስቱ ፈተና ስላመለጣቸው ስምንተኛ ክፍልን ለመድገም ተገደዱ። በረብሻው የተቋረጠው የጠዋቱ ፈተና አማርኛና እነወግሊዝኛ ፈተና ከወር ቡሃላ በድጋሚ ተዘጋጅቶልን ተፈተንን። የሰኔ አንድ 1997 ውሎዬ ይህን ይመስል ነበር።
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment