Monday, June 27, 2016

ሰላማዊቷ ሌሊት

" ሰ ላ ማ  ዊ   …   ሌ ሊ ት"
#ሳteናw

… በዛ ውድቅት የረመዳን ሌሊት ከየት መጣ ያላልነው ፍሬን የበጠሰ መኪና፣ እየተንደረደረ… ቀኛችንን ይዘን በቆምንባት በጠባቧና ቁልቁለታማው መንገድ ከላበላያችን መጣብን። መኪናው ወደኛ መኪና ባለው ፍጥነት ሁሉ ይጋልባል… ካለንባት መኪና ወጥተን እንዳናመልጥ መኪናው ደርሶብናል… ሁላችንም ካሁን አሁን ያለንባትን D4D መኪና  ከፊትለፊታችን ወደሚገኘው ገደላማ… ውስጥ ጠራርጎ ይዞን ገባ በሚል ድንጋጤ ከቁጥጥራችን ውጪ የሆነ ጩኸት ለቀቅን… ስናልቅ ላለማየት አይኖቻችንን ጨፈንን… ጓ … ጓ…ገጭ… ግግው…ጓ…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

①እኛ፣ቁርዓንን፣በመወሰኛይቱ፣ሌሊት፣አወረድነው።
②መወሰኛይቱም፣ሌሊት፣ምን፣እንደኾነች፣ምን፣አሳወቀህ?።
③መወሰኛዪቱ፣ሌሊት፣ከሺሕ፣ወር፣በላጭ፣ናት።
④በርሷ፣ውስጥ፣መላዕከቱና፣መንፈሱ፣በጌታቸው፣ፈቃድ፣በነገሩ፣ሁሉ፣ይወርዳሉ።⑤እርሷ፣እስከ፣ጎህ፣ድረስ፣ሰላም፣ብቻ፣ናት።(አል ቀድር)

  ይህቺ በቁርዓን ሰላም የተሰኘችዋ ሌሊት በረመዳን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ውስጥ እንደሆነች በተለይም በጎዶሎ ቁጥር ቀናት በ21/ 23/ 25/ 27 /29 /ውስጥ ልትሆን እንደምትችል በተለይም 27ኛዋ ሌሊት ጥርጣሬው እንደሚልቅ በተጨማሪም ይህች ሰላም የተባለችው ለሌት ብዙ ምልክቶች እንደሚታይባትም ነቢያዊ አስተምህሮት ይገልፃል።
ከነርሱም ውስጥ… ለሊቱ ሞቃታማም ብርዳማም ሳይሆን ሠላም የሆነ ለሊት ከሆነ ምናልባት ዝናብ ሊጥል ይችላል ከዚህም በተጨማሪ በንጋቱ ፀሐይ እንደወጣች ያላት ብርሃን (የጨረር) መጠን ትንሽ ለማይባሉ ደቂቃዎች አይንን ሳይጎዳ ወደ ፀሀይ መመልከት መቻሉ ነው።)

••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  ረመዳን 27 ለይልን ሳስታውስ ሁሌም አምና ረመዳን ያሳለፍኳት ይህቺ ሌሊት ፊቴ ላይ ድቅን ትላለች…

   ጓደኛዬና ሚስቱ (ዘመዴ ነች)፣ በያመቱ ረመዳን ያስለመዱትን ገጠር ሄደው ሰደቃ ለማውጣት እኔና የሚስቱን ወንድም ጨምረው እንደምንሄድ ተነጋግረን። ረመዳን 27 ለይል ከኢሻ መልስ በጓደኛዬ ቤት ተገናኘን። አንድ ቀን በጓዴ ቤት፣አንዱ ቀን በሚስቱ ቤት ሰደቃውን ለማድረግ ታቅዶ ጉዟችን በ27ኛዋ ሌሊት ኢንዲሆን ተወሰነ። ከእራት ቡሃላ ትንሽ ተቀማመጥን፣ መተኛት ቢያሰኘንም መተኛቱን ትተን ተቀመጥን መጨዋወት ያዝን። ምሽት ላይ ትንሽ ዝናብ ጣለ ቢሆንም የአየሩ ሁኔታ የማይሞቅም የማይበርድም ነበር። ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በመካከላችን እርጋታ ሰፍኖኗል። የጓዴ ባለቤት ቡና ከጠጣች ቡሃላ ጉዞ ስንጀምር እንድንቀሰቅሳት ነግራን ሄዳ ደቀሰች። ሌላጊዜ በረባ ባልረባው የምንነታረክ ልጆች በዚህች ቀን አስሬ ዱዓ ስናደርግ፣ የምናውቀውን ቂሳ ስንናገር አረፈድን።  የመሄጃችን ሰዓቱ ሲደርስ… ቀስቅሰናትና… ሱሁር በልተን… የፈጅርን ሰላት መንገድ ላይ ለመስገድ ወስነን …  ጉዞ ጀመርን።

   የሌሊቱ አየር ደስ ይላል ጥርት ባለው ሰማይ ላይ ከዋክብት ብልጭ ድርግም እያሉ ይጠቅሱናል… ከዚህም ከዚያም ይሰሙ የነበሩ የውሾች የማላዘን ድምፅ ደብዛው ጠፍቶ በምናልፍበት መንገድ ሁሉ የመስጂድ ድምፅ ማጉሊያዎች… የለይል ሰላትን ቁርአን ብቻ ያስተጋባሉ። ደስና አርግት ያለ ለሌት ነበር። ከከተማ ሳንወጣ ጓደኛዬ አንድ ገጠር ስትሄድ ትወስደኛለህ ያሉኝ አዛውንት ስላሉ እሳቸውን ፒክ እናድርጋቸው ብሎ፣ መኪናዋን ለሚዘውራት የባለቤቱ ወንድም ነግሮ … ሰውዬው ወደሚገኙበት ሰፈር ሄድን።ደረስን።

    ሰፈሩ ዳገታማና  ወጣ ገባ የሚበዛበት ከመሆኑ የተነሳ የአዲስ አበባ ምድር አይመስልም። በዚህ ወጣ ገባማው መልከአ ምድር ላይ የተገነቡት መኖሪያ ቤቶች አቀማመጣቸውን በርቀት ስታይ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርበው ሰርከስ የሚሰሩ ይመስላሉ። አብሮን ከሚጓዘው ሰውዬው ቤት ከግቢ በር ደረስን። ከአጥሩ ውጪ የቆምንበት ኮብልስቶን መንገድ ሲሆን  ከፊታችን የተዘቀዘቀ ቁልቁለት ከኋላችን ከተወሰነ ርቀት ቡኋላ የሚታጠፍና ደረቱን ገልብጦ የቆመ ዳገት ነበር። ጓዴ ወርዶ ከመንገዱ በስተግራ የሚገኘውን የግቢውን በር አንኴኳ። አፍታም ሳይቆይ የግቢው በር ከውስጥ ባለ ሰው ተከፈተ።  ግቢው ገደላማ ሲሆን፣ መኪናችን ቀኟን ይዛ ብትቆምም  ከመንገዷ ጥበት አንፃር መኪና ውስጥ ቁጭ ብለን ወደ ግቢው ስናይ እንደ ወለል ሆኖ የታየን የቤቶቹ ክዳን ቆርቆሮ ነበር። ከግቢው በር ወደ መኖሪያቤቶቹ የሚያደርሰው ረጅም ደረጃ መሆኑ ባናየውም ያስታውቃል።  የሰውየው ቤተሰቦች ጓዙን ከቤት ውስጥ እያመጡ መኪናችን ላይ መጫን ያዙ። እኛ መኪናዋ ውስጥ ቁጭ ብለን እስኪጨርሱ እንጠብቃለን። የጓዙ መብዛት ይሉኝታ ያሳደረባቸው የተጓዥ ታናሽ ወንድም… ወደ መኪናዋ መስኮት ተጠግተው በቃ አልቋል አንድ እቃ ነው የቀረው በማለት ወደ ጊቢው እንደዘለቁ።… በዛ ውድቅት ሌሊት ከየት መጣ ያላልነው ፍሬን የበጠሰ መኪና፣ ደረቱን ገልብጦ ከቆመው ዳገት… እየተንደረደረ ቀኟን ይዘን በቆምንባት በጠባቧና ቁልቁለታማዋ መንገድ መጣ። መኪናው ወደኛ መኪና ባለው ሁሉ ፍጥነት ይጋልባል… ካለንባት መኪና ወጥተን እንዳናመልጥ ደርሶብናል… ሁላችንም ካሁን አሁን ያለንባትን D4D መኪና ከፊትለፊታችን ወደሚገኘው ገደላማ በሆነው መኖሪያ ቤት ውስጥ ጠራርጎ ይዞን ገባ በሚል ድንጋጤ ከቁጥጥራችን ውጪ የሆነ ጩኸት ለቀቅን… ስናልቅ ላለማየት አይኖቻችንን ጨፈንን…  ጓ…ገጭ… ግግው…ጓ… ገጭ…  እያለና ድንጋይ እያነጠረው በመኪናችንና በግቢው መካከል ባለው ክፈተት የቆርቆሮውን አጥር እየታከከ… የመኪናችንን ጆሮ(ስፔኪዮ፣የጎን መስታወት) ጨርፎና አጥፎ በሚያስደንቅ ፍጥነትና ተዓምር ሽው ብሎ አለፈን። ከድንጋጤያችን ሳንወጣ ሰለጥቂት ስቶን  ቁልቁል የሚንደረደረውን መኪና ተመለከትን። መኪናው ሚኒ ባስ ሲሆን በሚጯጯሁ ተሳፋሪም ተሞቷል። የተጓዥ ቤተሰቦች ከግቢው ውስጥ የጓጓታውን ድምፅ ሰምተው ሮጠው ወጡ። ሚኒባሱ ሄዶ ሄዶ ቁልቁለቱ መሃል ወደ ሚታጠፍ ዳገታማ መንገድ እንደ ዘንዶ አየር ላይ ተምዘግዝጎ ገባ። የሹፌሩን ብቃት ማድነቅ ሳንጀምር ሚኒባሱ ከአይናችን ተሰወረ። ጭንቀታችን ለራሳችን መሆኑ ቀርቶ ሚኒባሱ ውስጥ ስላሉ ሰዎች ሆነ። ከመኪናው ውጪ የነበሩ የተጓዥ ቤተሰቦች የመኪናውን መጨረሻ ለማየት እየጮኹ ተከትለውት ሮጡ። እኛ በድንጋጤ ብዛት በድን ሆነን አንደበታችን ክዶናል። አይናችን ፈጧል።አፋችን ደርቋል። ከየጊቢው የጎረቤት ሰዎች መውጣት ጀመሩ። መኪናውን ተከትለው የሄዱ የተጓዥ ቤተሰብ ለጎረቤቶቻቸው ሁኔታዉን እያስረዱ ተመልሰው ወደኛ መጡ። የሁላችንም ጥያቄ አንድና እንድ ብቻ ነበር። የሚኒባሷና የተሳፋሪዎቹ መጨረሻ። ከአንድ ክምር አፈር ጋር ተጋጭቶ ከፊት ለፊቱ መስታወት ከመሰበር ውጪ ምንም የህይወት አደጋ ሳያደርስ መቆሙን ነገሩን። ከመንገዷ ጥበት አንፃር መኪናው ምንም ሳይነካን የመትረፋችን ነገር ሁሉንም የሰፈሩን ሰዎች አያስደመመ። እዚህ ጋር የአላህ ጥበቃ ባይኖረን ከነደዚህ አይነት ስፍራ መትረፋችን የማይታመን ነበር። አብረውን የሚጓዙ ሰውዬ መጡና እዬዬያቸውን አስነኩት። አስጨርሻችሁ ነበር ልጆቼ በሚል። እኛም ባለተረጋጋው መንፈሳችን እንዲረጋጉ ካደረግን ቡሃላ በድንጋጤ የፈጅርን ሰላት መንገድ ላይ እንሰግዳለን የተባባልነውን ትተን። እዛው ሰፈር ካለው መስጂድ ሰግደን ጉዞ ለመጀመር ወሰንን። ደጋግመን አላህን ስላተረፈን እያመሰገንን፣ ስለ ሁኔታው ደጋግመን እያወራን አዛን እስኪወጣ ጠበቅን። አዛን ብሎ የፈጅርን ሰላት መስጊድ በጀመዓ ሰገድን። መንገድ ስንጀምር ትዕይንቱ በአይነ ህሊናችን እንደ አዲስ እየተመላለሰብን በመካከላችን ፀጥታ ሰፈነ። መኪናችን አለምገናን፣ ዳለቲን እየተወች ትከንፋለች። ሰማዩ ከምስራቁ በኩል ይጠራ ጀመር… ብዙም ሳይቆይ ፀሀይ ድብዝዝ ያለና ለእይታ የማያግድ ጨረሯን እያፈነጠቀች መውጣት ጀመረች።  ይህን የፀሀይ ሁኔታ ስመለከት በጣም ገረመኝ። ያስገረመኝ …  ከላይ በቁርዓንና ሀዲስ ከሺህ ወር በላጭ ናት ተብላ  ስለጠቀሠችው ሌሊት ሊታይባት ይችላል የተባለውን ምልክቶች፣ ባሳለፍነውን ሌሊት እነዚህን ምልክቶቹን ሁሉ ማየቴ ነበር፣ … ዝናብ መጣልና የማይበርድም የማይሞቅም  አየር ፀባይ፣ የተረጋጋ ድባብ፣ አሁን ደግሞ ለእይታ የማያግደው የፀሀይ ሁኔታ፣ ድጋሚ ለጥቂት የተረፍንበት የመኪና አደጋ። የምንሄድበትን ጉዳይ ጨርሰን እስክንመጣ ስለዚህች ሌሊት ደጋግመን መገረማችን ደጋገመን ማንሳታችን አልቀረም። እውነትም ሰላማዊቷ ሌሊት ብያታለው። ከዛን ቀን አደጋ የታደገን አላህ አሁንም ምስጋና ይደረሰው አሁንም ጥበቃው አይለየን።

ለማንኛውም ይህቺ ሌሊት አሁን ያለንባት የረመዳን የመጨረሻ አስር ቀናቶች ክልል ውስጥ ትገኛለች። ከትሩፋቶቿ ለመጎናፀፍ ከመቼውም በበለጠ በኢባዳችን ልንጠነክር ይገባል አላህ ለይለተል ቀደር ይወፍቀን!!! ዱአውም ለጨቋኝ ሀይሎች በግፍ ለታሰሩ ኡስታዞቻችን የሚደርስ ያድርገው!!
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment