Saturday, June 25, 2016

እኔን ነው?! እንዲል እከ!!

"እኔን … ነው? እንዲል…  እከ!!
#ሳteናw

… ይህ እድል ያልገጠማቸውም ሚስኪን እህቶቼ፣ ካሁን አሁን ፖሊሶች መጡብን በሚልና ባለመረጋጋት ስሜት ግራ ቀኛቸውን ይገላምጣሉ። ይህን መሰሉ የፖሊስ ፍራቻ በእነዚህ እህቶቼ ብቻ ሳይሆን በጎዳና ንግድ ላይ በተሰማሩ ወጣቶችም ላይ ይስተዋላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ፖሊስን አይቶ መሸበር የሚገባው ሌባ ብቻ በሆነ ነበር…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  አዉቶቢስ ተራ አካባቢ ታክሲ ውስጥ ተቀምጬ ታክሲው እስኪሞላ በመጠባበቅ ላይ ነኝ። … ሰአት ስለረፈደብኝ ቸኩያለው፣መረጋጋት አጥቻለው። ለነገሩ መረጋጋት የተባለው ነገር በኔ ብቻ ሳይሆን በብዙሃኑ ማህበረሰብ ውስጥ ከታየ  ሳይቆይ የቀረ አይመስለኝም። (ከምር ግን መረጋጋት የተባለው ነገር አልናፈቃችሁም? ይሄ ይሄ ብዬ ባልዘረዝረውም ሁሉም እኮ ጥድፊያ ላይ ነው፣ ለሀቂቃ!! አለ አይደል የትም የማያደርስ ጥድፌያ!!። አልሞላ ባለኝ ታክሲ በመስኮቱ አሻግሬ ምንም የተረጋጋ ህይወት የማይታይበትና የሚዋከበውን አላፊ አግዳሚ ተመለከትሁ… አይኔን ቀና አድርጌ አዲሱ የከተማ ባቡር ድልድይ ላይ የተለጠፈው ፖስተር እንደነገሩ ካየሁት ቡሃላ ነቅዬ ቁልቁል ፈጠፈጥኩት…  የአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የቴሌውና፣ የትንሹ አውቶቢስ መናኸሪያ፣ አጥሮች እንደ ሙዓመር ጋዳፊ በወጣት ሴቶች ታጅበዋል …ለዛውም ቁጥር ስፍር በሌላቸው ሴቶች። ከፊት ለፊታቸው ያለው የባቡሩ ድልድይ ስርም በመደዳ ዘርዘር ብለው በቆሙም ሴቶች ተሞልቷል። ታዲያ እነዚህ እህቶቼ ተሰልፈው የቆሙት ለታክሲ እንዳይመስልህ… ምፅ!! በምን እድላቸው!! በስራና በአማራጭ እጦት በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው መሽኚያቸውን እንደ ሱቅ መተዳደሪያቸው ያደረጉና… ይዟቸው የሚሄድ ወንድ የሚጠብቁ ምስኪን እህቶቼ እንጂ። በፊት በሰባተኛና በሌሎች ጉራንጉር ሰፈሮች ብቻ የነበረው የወሲብ ንግድ ዛሬ ላይ እንደ ካሮት ቁልቁል አድጎ በየጎዳናው ላይ ከሆነ ውሎ አደረ። ከነዚህ እህቶቻችን ውስጥ አብዛኞቹ ታዳጊ ወጣቶች ሲሆኑ የወጣትነት ዘመናቸው ላይ ሃያ አመት የጨመሩም  አሉ። በርካቶቹ ፀጉራቸውን በሂጃብ ጠምጥመው ከስር ገላቸውን እንደ መርፌ በሚጠቀጥቅው ቅዝቃዜ ብጣሽ ጨርቅ ብቻ ጣል ያደረጉ ናቸው። ከላይ የጁምዓ ከስር የቅዳሜ አለባበስ!በለው። ለምን ይሆን ሻሽ (ሂጃብ) የሚጠመጠሙት? ለጊዜው ግምቱ እንጂ እውነቱ ስላልተገለፀልኝ … እንደኔው ገምት። ወጣትነታቸውን በማገባደድ ላይ ያሉት በገፅታቸው ላይ ገበያ ለመሳብ በሚል የተጫረ አርቴፊሻል ፈገግታ ሲያሳዩ…  ታዳጊዎቹ ደግሞ ለገበያቸው ብዙም ጉጉት ሳያሳዩ ቆመው፣
እርስ በእርስ ሲስቁ ሲቀላለዱ፣ ሲላፉ፣ ይታያል… ይህን ሁኔታቸውን ስታይ አንድም ልጅነታቸው አንድም ገና በዚህች ትንሿ  እድሜያቸው እያለፉበት ያለውን መራራ ህይወት ለመርሳት በሚል እንደ ሆነ እንጂ … ደልቷቸው አልያም በስራቸው ደስተኛ ሆነው አንዳልሆነ ስድስተኛው ስሜትህ ይነግርሃል። ሌሎቹ (ቅንዝር አዳማዊያን ማለቴነው) ደግሞ እንደ በግ ገዢ አካላቸውን ከዳበሳ ባልተናነሰ እይታ… ከሚያዩና ዋጋ እንደሚነጋሩ ሁኔታቸው ከሚያስታውቅ ወንዶች ጋር ቆመው ያወራሉ። የተስማሙትም ገንጠል ብለው ተያይዘው ይሄዳሉ።… ይህ በለስ ያልገጠማቸውም፣ ካሁን አሁን ፖሊሶች መጡብን በሚል ግራ ቀኛቸውን ባልመረጋጋት ስሜት ይገላምጣሉ። ይህ የፖሊስ ፍራቻ በእነዚህ እህቶቼ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም ላይ አለ። እንደ እውነቱ ከሆነ ፖሊስን አይቶ መሸበር የሚገባው ሌባ ብቻ በሆነ ነበር
ይህን ትዕይንት ስመለከት ለአፍታ የራሴን ችግር ትቼ በነዚህ እህቶች ዙሪያ ራሴን ስብሰባ ጠራው…

  መቼም እያንዳንዳቸው ህይወት ጀርባ ለዛሬው አስከፊ ህይወት የዳረጋቸው የተለያየ የህይወት ገጠመኝ ቢሆንም። ዞሮ ዞሮ አንድ የሚያደርጋቸው ነጥብ አለ። ችግር !!። በዚህ ቅዝቃዜው ጣት በሚቆረጥም ብርድ፣ እስቶኪንግ ብቻ አስለብሶ፣ የውሸት ፈገግታ አላብሶ፣  ለገበያ ያወጣቸው ነገር ቢኖር ፣ ችግር መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው። ታዲያ ሌላ ስራ አይሰሩም ወይ? ብዬ በውስጤ እንዳልወቅሳቸው፣ ዛሬ ላይ ያደረሳቸውን መንገድ በግልፅ ሳላውቅ መውቀሱ ሞራል አሳጣኝ። ግን አንድ እውነት አለ!! የትኛዋም እህት ወደዚህ ስራ በፍላጎቷ የገባች እንደማትኖር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በዛው መጠን ይሄን አስነዋሪ ስራ አንሰራም ወይም አንሰርቅም ብለው በጎዳና ላይ ንግድ የተሰማሩ ወገኖቸም በአማራጭ እጦት ነው እንጂ በፍላጎቱ ሌባና ፖሊስ መጫዋት ስላማረው ነው የሚል እምነት እንደሌለኝና ይህንንም ሀሳብ እንደምታጋሩኝ አምናለው።  አስነዋሪም ሆነ ህገ ወጥ ስራዎች የሚቀረፉት፣ ብዙ የስራ አማራጮች ሲፈጠሩ ነው። ይህ ሊፈጠር የሚችለው በአስተዳደር በኩል ነገራቶች ሲመቻቹ መሆኑ ለማንም ያልተሰወረ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የስራ አማራጭ ላጣ ህዝብ የሚጠቅመው አማራጮችን ማቅረብ እንጂ አሯሯጮችን አሰማርቶ የአማራጭ መጨረሻቸውን መንፈግና ማስነጠቅ እንዳልሆነ ቅን ልቦና ያለው የሚያውቀው ሀቅ ነው። የሚበላው እስኪያጣ የተቸገረ ህዝብ የፈለገውን ሰርቶ ቢያድር አይፈረድበትም። መቼም ይሄን ሳያውቅ የሚቀር ነጂም ተነጂም እንደማይኖር አውቃለው። እንዲያው ነገሩ ቢጨንቀኝ ቢጠበኝ፣ ነው!! ለአመልህ ድከም ሲለኝ!!

…ግን ደግሞ ይህን ከልቤ ተመኘው!! አለ አይደል ጀሊሉ ብሎልኝ! የዳንጎቴን ወይም የሸሁን ሩብ ሀብት ቢኖረኝ ማለት ነው… [ከልቤ ነው! መርቅኜ ምናምን እንዳይመስልህ!]

  እነዚህንና በመሰል ስራ ላይ የተሰማሩ እህቶቼን ቅድሚያ የስራ እድል የሚሰጥ … ልክ እንደ … ምንድነው እሱ ሚሉት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ!… ምነው ይሄ ዳለቲ ያለው … ስሙ እኮ… ምላሴ ላይ… አለ! … እንደውም… በያመቱ ለዘንዶ ይገብራል እየተባለ የሚታማው… አዎ!! አይካ አዲስ። እንደሱ አይነት!! በተለያዩ ስፍራዎች በተለያዩ አይነት ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ ድርጅት አቋቁሜ፣ የስራ አማራጮች በገፍ እንዲሆኑ  አድርጌ  … ህይወታቸው ከአስነዋሪው ስራ አውጥተው በተመቻቸው የስራ አማራጫቾች በመረጡትና በፈለጉት ስራ ተሰማርተው፣ አንደ ሰው፣ ሰርተው ተቀይረው ሀገር የሚቀይሩ ሀይል  ባደረኳቸው። ብዬ ተመኘው። መቸም ምኞት አይከለከል። የሚሞላው እሱ ነውና።

… የተሳፈርኩበት ታክሲው ሞላና መንቀሳቀስ ሲጀምር… ከሀሳቤም ከምኞቴም ተመለስኩ። አዲሱ የከተማ ባቡር ድልድይ ላይ ተለጥፎ ያየሁትን ፖስተር ድጋሚ ተመለስኩት… ፅሁፉን አነበብኩ። ያነበብኩትን ተጠራጥሬ… የአይኔን ሽፋሽፍቶች በጣቶቼ አሸት አሸት አድርጌ ብሌኔን ወለወልኩና… ድጋሚ ፅሁፉን አነበብኩት…እንዲህ  ይላል።
"…የህዝቦቿን ተጠቃሚነትና አንድነት ያረጋገገጠች ሀገር!!"
"እኔን ነው! አለ እከ!!
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment