Thursday, June 23, 2016

"እ ድ ሜ ለ ማ ር ክ ዙ ከ ር በ ር ግ "

"እ ድ ሜ … ለ ማ ር ክ … ዙckerbueg"
#ሳteናw
ድሮ ድሮ የሀገሬ ኢንተርኔት ቤቶች እንደ ቁጥራቸው ተጠቃሚያቸውም ውስን ነበር። ተጠቃሚዎቹም ወይ ድግሪ ወይ ማስተርስ ያላቸው ጥቂት የተማሩም ሰዎች ነበሩ። በዚህ የመጣ የኢንተርኔት ቤት ወንበሮች በተጠቃሚ እጦት ከሰው ይልቅ በአቧሯ መርግ ይሞሉ ነበር። ድሮ ነው ታዲያ… ዛሬስ? እድሜ ለማርክ ዙከርበርግ የተማረውንም ፣እንደኔ ያለው ቴንኘላስ ምላስ የሆነውም፣ ፊደል የቆጠረውንም በፌስ ቡክ ሰበብ ኢንተርኔት የተባለውን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም፣ ኢንተርኔት ቤቶችን በተጠቃሚም፣ በገቢም እንዲጨናነቅ ላደረገው አሜሪካዊው ጉብል፣ እድሜ… አዋራ አራግፈህ ትጠቀምበት የነበረው የኢንተርኔት ቤት መቀመጫ፣ ዛሬ እንደቆመ ባስ ተሳፋሪ የሚለቀቅ ወንበር ጠብቀህ የመጠቀም ወጉ እንዲደርስህ ላደረገው ወጣት ማርክ።
እርግጥ ነው አልዋሽህም!! ፌስቡክ ፌብሩዋሪ 4/2004 ከመወለዱ በፊት የቀደሙ ማህበራዊ ድህረገፆች እንደነ yahoo… gmail ቢኖሩም ተጠቃሚያቸው እንደ ዛሬው ሰፊው ህዝብ አልነበረም።

[(በነገራችን ላይ የፌስ ቡክ መለያ ቀለም ለምን ሰማያዊ እንደሆነ ታውቃለህ? መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ቀይና አረንጓዴ ቀለም አይቶ የመለየት ችግር ስላለበት ነው። አሉ ነው። ማጣራቱ ያንተ ፋንታ ነው! ለማንኛውም ይህን ምርጥ ልጅ በፌስቡክ ማግኘት ካሰኘህ መደበኛው የፌስቡክ አድራሻ ላይ 4 ቁጥርን ጨምረህ( facebook.com/4 ) ፈልገው ከደማቅ ፈገግታው ጋር ታጅቦ ድቅን ይልልሃል። 5 እና 6 ካስገባህ ደግሞ መስራች ጀለሱካዎቹን ታያለህ)]

ፌስቡክ ከመጣ ወዲህ የኢንተርኔት ተጠቃሚው እንደ አሸን ፈልቶ ቁጥሩም አደገ። አድገ ስልህ የፊስቡክ ተጠቃሚ እንጂ የነብስ ወከፍ ገቢ እንዳልሆነ መቼም አታጣውም። ዛሬ ላይ ህዝቤ የከበደው የፌስቡክ መክፈት ሳይሆን የባንክ አካውንት መክፈት እንደሆነም አይጠፋህም።
የጋራችን አለም ድሃና ሀብታሙን በኑሮ ደረጃ ብትለያየውም፣ ኪስን ሳያይ አንድ አድርጎ ፌስቡክ ሰበሰበው። አብዛኛውን ሰው ይህን ተከትሎ ከፌስቡክና መሰል ድህረገፆች በደንብ ተዋወቀ። ይህን ቀድሞ የባነነው ቴሌም ኢንተርኔትን ወደ የሞባይላችን መስኮት አቀረበው። ግንምን ዋጋ አለው? ፌስቡክ አንድ ቢያደርገን፣ ቴሌ በሞባይል ካርድ ፍጆታ አራራቀን። ድሮስ ጠላት ከሩቅ አይመጣ!!

ፌስ ቡክ የተራራቁ አህጉራትን፣ ለቡና እንደምትጠራራው ጎረቤት አቀራርባል። በተለያየ የአለም ክፍል ያሉ ሰዎችን በአንድ ሰሌዳ አሰባስቧል። አንደኛውን አለም ከሶስተኛው አለም በአየር ላይ ምንኗኗረውን ሌላ አለም ፈጥሯል። የመረጃ ልውውጡም በዛው መጠን አሳድጓል። የአለም ትኩስ ዜናዎችን በየሞባይል እስክሪንህ ላይ ገና የትኩስነት ጭሳቸው እየተንፎለፎለ አንኳኳተው ከች ይሉልሃል።

እናልህ…! ከዚህ ከፌስቡክና መሰል ማህበራዊ ድህረገፆች ጋር መምጣት ተያይዞ ብዙ ለውጥ በሀገራችን መጥቷል። መልዕክት ለመለዋወጥ ፖስታ ቤት የፖስታ ሳጥን ከመክፈት በተንቀሳቃሽ ስልክህን ወይም በዴስክ ቶኘህ inbox ወደ መክፈት አሸጋግሯል። ወጣቱን ፎቶን በዋሌት ቦርሳው ከማስቀመጥ፣ ፌስ ቡክ ላይ ወደ ማስቀመጥ አራቆታል። በዚሁ ሰበብ ጠበሳውም፣ጅንጀናውም ንሯል። ለመጠባበስ የፕሮፋይል ፎቶዎች በእጅ ስራ ጥበብ፣ ተወልውለው፣ተኩለው አምረዋል። ይህን አይተህ፣ከአንዷ ጋር ተቀጣጥረህ በአካል አግኝተህ ስታያት ፎቶው የራሷ መሆኑ ያጠራጥርሃል። ወይም ቀጥረህ ስጠብቃት የውሃ ሽታ ከሆነችብህ ወንድ በሴት አካውንት ተሞዳምዶብህ ይሆናል። በዚህ አላበቃም የአየር ላይ አለማችን፣ ጥንዶችን አየር ላይ ኘ አግባብቶ፣ በገሃዱ አለም አጋብቶ አዋልዷል። በዛው መጠን ሰላማዊ የነበረን ትዳር አበጥብጧል። ተግባብቶ የተጋባውን፣ባለመስማማት ግራ አጋብቶ አፋቷል።

ቺክ ለመጥበስ በፍራቻ ብዛት ቃላት ያጥረው የነበረው ሰውዬ፣ ዛሬ በፌስቡክ ጠበሳ አንድ ፊደል ሲፅፍ የቃላት አማራጭ የሚገጠግጥለት ኪቦርድ ገላግሎታል። በሌላ በኩል በተደረገው ጥናት ኢንተርኔት መሀይምነትን በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል። በፅሁፍ መልእክት ለመግባባት ለግዱ Amharic english የፈደል ገበታ እንዲያጠና አስገድዶታል። በፊት በወር አንዴ የምትጠብቀው ከዘመድ አዝማድ የሚደወል የውጪ ስልክ፣ ዛሬ በየደቂቃው ሆኗል። እድሜ ተያይዘው ለመጡት ለነቫይበር፣ለነ ዋትስ አኘ ና ኢሞ፣ የተጠፋፋውን ወዳጅ አገናኝቷል። የተራራቀን ቤተሰብ አቀራርቧል። የመኝታ ቤት በርህ ሳይንኳኳ፣ ከሳሎን "እራት ደርሷል ና ትባላለህ … በኦን ላይን።

ይህ መልካም ሆኖ ሳለ የነፃነቱ ልክ ወሰን አልፎ ስድ ነገሮችንም፣ ድርቅ ያሉ ውሸቶችንም አቅፏል። ከዌብ ሳይታቸው የሸሸሃቸው አፀያፊ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በጋጠ ወጦች ተፖስቶ ሳትፈልግ በፌስቡክህ ላይ ገጭ ይሉብሃል። ከላይ የሀይማኖት ትምህርት እያነበብክ ከስር ይሄ ጉድ ብቅ ይላል። ቤቱ ተቀምጦ ከልጆቹ ጋር የሚፈነድቀውን ታዋቂ ግለሰብ "ሰበር ዜና! አከሌ አከሌ ዛሬ አረፈ? ይሉሃል። ውሸቱም በዛው ልክ ነው፣ የዜናውን እውነት፣ እንደ ወርቅ ማዕድዕን ከጭቃ እንደሚጣራው አጣርተህ ማረጋገጥን ይጠይቃል።

[(በነገሬ ላይ አፀያፊ ምስሎችን በአካውንትህ ላይ እንዳይለጠፍብህ ለማድረግ setting ግባ timeline and tagiging ግባ who can post your timeline? ግባ only me አደርገው አለቀ።)]
አንድ ሰው ሶስት የፌስ ቡክ አካውንት በመክፈት አንድም ሶስትም መሆንን ችሏል። በዚህ የመጣ ከ8—10 % የሚሆኑት የፌስቡክ አድራሻዎች ፌክ ናቸው። በፌስ ቡክ አንድ ሰው ከፈለገ የሀይማኖት መምህር፣ ልቅና ስድ፣ ደፋ ር ፖለቲከኛ ይሆናል። በገሀዱ አለም አዋቂ ነው ትውልድ የሚያቀና ነው የምትለው ሰውዬ በነ ፌስቡክ ትውልድ የሚያበላሽ ቪዲዮ ይለቅብሃል። አመለ ብልሹ ያልከው በፌስቡክ ላይ የሀይማኖት መሪ፣ እኔ ብቻ አዋቂ የሚል ይሆንብሃል። ማንነትን እንዳሻህ ለመከረባበትም ፌስቡክ ሁነኛ መድረክ ሆኗል። ደግሞ የቤቱን አመል ይዞ ፌስቡክ የሚመጣብህም ሞልቷል።

መች በዚህ በቃ በግልፅ የማታደርጋቸው ድርጊቶ፣ ማህበራዊ ድህረ ገፅ ማድረግ አስችሏል። ማንነትህን ደብቀህ ባለስልጣንን በፔጁ በኩል ብትኮንን፣ ግፋ ቢል አካውንትህን የመሰበር ሙከራ ይደርስበታል እንጂ፣ ማእከላዊ ታጉረህ በዱላ ብዛት እግርህ አይሰበርም። መንግስትን ለመቃወም ከድንጋይ ከመወርወር ወደ ቃላት መወርወር አሸጋግሯል። ይህም ከመንግስት ሀይሎች የሚመለሰውን የጥይት ቃንቄ አስቀርቷል። እንደምታውቀው ሀያል መንግስታት በሶሻል ኔት ሰበብ ተገርስሰዋል ግብፅና ቱኒዚያን መውሰድ ትችላለህ። ይህ ውጤት የሰራው እንደኛ በበነነ ተነነው ለተለያየ ህዝቦች ሳይሆን፣ በአላማ አንድ ለሆነ ህዝብ ነው። እናልህ! … ከአንባገነን መንግስታት የታጣውን በነፃነት ሀሳብን የመግለፅን መብት ፌስቡክ መልሶታል። ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ በላይ ምን የህሊና እረፍት የሚሰጥ ነገር አለ?። ይሄው እኔስ ዛሬ ሃሳቤን ማካፍልህ በዚሁ ፌስቡክ አይደለም? ነው።

እንግዲህ እነዚህንና ዘርፈ ሰፊ ለውጥ በፌስ ቡክ ሰበብ ተፈጥሯል። ይህን ዘርፈ ሰፊ ለውጥ ለበጎም ለክፉም የማዋሉ ስልጣን በመዳፋችን ላይ ነው። በፌስቡክ መማማር፣ ጠቃሚ ሃሳቦችን መለዋወጥ፣ የሚቻለው እንደ አጠቃቀማችን ነው። ለአንድነት፣ ለነፃነት፣ ለመልካም ለውጥ፣ ለተሻለ አስተዳደር ጥቆማ ወዘተ ለማዋል አድርገን የምንዘውረው እኛው ነን። ድንቁ ማርክ ያበረከተልንን በዚህ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ለጋራ ጥቅማችን ቢሆን ድንቅ ይሆናል!! እላለው። ለማንኛውም የፌስ ቡክና መሰል የማህበራዊ ድህረ አጠቃቀማችን ያሳምርልን!! ከማለት ውጪ ምን ማለት ይቻላል? ምንም!!
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment