Monday, September 24, 2018

የማንነት ጥያቄ

"የማንነት ጥያቄ"
#ሳteናw
ዛሬ የተፈጠረው ነገር ጄጃን
በቤተሰቡ  ላይ የነበረውን እምነት፣ 
የጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶታል።
እናቱን በአንድ አባት የሚጠሩ
እህት ወንድሞቹን፣ እውን የስጋ
ወንድሞቹ መሆናቸውን
ተጠራጥሯል። 

… ገና ጨቅላ ሳለ ሞቶ እንደተቀበረ
የሚያውቀውና በስሙ የሚጠራበት
አባቱን፣ ዛሬ እንደ አዲስ
ሞተ ተብሎ ከአሳዳጊ ሴት አያቱ
ጋር ለቅሶውን ደርሶ ከመጣ
ቅፅበት ጀምሮ አይምሮው የጥያቄ
ጋጋታዎች የሚተራመሱበት፣ መድረክ ሆኗል።
ይበልጥ  የገረመው ደግሞ የአባቱን ሀዘን
በራሱ ቤት የሚደረሰው ሳይሆን፣
ራሱ በሰው ቤት ሄዶ መድረሱ? 
" ቆይ እሺ ዛሬ የሞተው አባቴ ከሆነ!!
የወንድም እህቶቼስ አባት አይደለም? እና
አያቴ ምን ሆና ነው?  እኔን ብቻ ይዛኝ
ምትሄደው?" ይላል ደጋግሞ ለራሱ።
ለጊዜው ማንነቱ ላይ ፍቺውን ያላወቀው
እንቆቅልሽ እንዳለ ገብቶታል!!
"ኡፍፍፍፍ" አለ ከተጋደመበት ሶፋ ወንበር
ላይ ቀና ብሎ እየተንጠራራ።

ተመልሶ ወደ … ሀሳቡ ገባ።
ለዚህ ሁሉ ውዝግብ ያበቃውን የዛሬውን
ገጠመኝ ውሎ አንድ በአንድ በህሊናው
ይከልሰው ጀመር …

… የአስራሁለት አመቱ ጄጃን፣
ከትምህርት ቤት ለምሳ እደተለቀቀ፣
የቀትሩ ፀሀይ መሀል አናቱን እንደድሪል
ቦርቡሮ ሳይበሳው ከሰፈሩ ደረሰ።
ወደ ቤት ዘው ብሎ ሲገባ፣ ከእናቱ በላይ
የሚያፈቅራቸው አሳዳጊ ሴት አያቱ ያለ
ወትሮው ገፅታቸው ላይ የሀዘን ስሜት
አነበበና።

"እማ ምን ሆነሽ ነው? ሲል ጠየቃቸው?"
ገና ደብተሩን ሳያስቀምጥ፣ በፍጥነት
ከጎናቸው መደቡ ላይ እየተቀመጠ።

ጄጃን የእናቱን እናት አያቱን ከወላጅ
እናቱ በላይ ያፈቅራቸዋል! ምክንያቱም
ነብስ ሳያውቅ ጀምሮ በእናትነት ፍቅር
አሳድገውታል። የአያቱን ልጆች ማለትም
አጎት አክስቶቹንም ወንድሜ እህቴ እያለ
ከማደጉም በላይ፣ የሚጠራውም በወንድ
አያቱ ስም ነበር።

  ጄጃን ብዙ ሚስቶች ያለው ወላጅ አባቱን
አይቶት አያውቅም። ስለሱ ሲወራም
አልሰማም። እናቱ አንዳንዴ እናቷ ዘንድ
ስትመጣ ቢያያትም አብሯት ስላላደገ፣እሷ
የእናትነት ፍቅር ልትሰጠው ብትሞክርም
ወላጅ እናቱ እንደሆነች ብትገልፅለትም፣
እሱ ግን የእናትነት ፍቅር ሊሰጣት
አልተቻለውም። ጄጃን የእናትነት ፍቅር
መስጠት የቻለውለአሳዳጊ አያቱ ብቻ
ነው።

"ምንም አልሆንኩም? ዛሬ ከሰዓት
ትምህርት ቤት እንዳትሄድ የምንሄድበት
ቦታ አለ" አሉት አያትየው ፣ አጠገባቸው
የተቀመጠው የልጅ ልጃቸውን ፀጉሩን
እየዳበሱ …
ጥያቄም ልመናም በመሰለ ቃና።

"የት ነው የምንሄደው  እማ?" አለ።
"አንድ የምንደርሰው ለቅሶ አለ" አሉት።
ሌላ ጥያቄ እንዳያስከትልባቸው እየሰጉ።
በአያት ተቀማጥሎ በነፃነት ያደገው ጄጃን።
ሌላ ጥያቄውን በግርምት አስከተለ።

"እንዴ እማ ከኔ ጋር ለቅሶ ሄደን እኮ
አናውቅም። ዛሬ ምን ተፈጠረ?
ደግሞ ማን ነው የሞተው"ጥያቄ ላይ፣
ጥያቄ እደራረበ።

"በቃ እንሄዳለን አልኩህ!" አሉት ትንታኔ
ውስጥ ላለመግባት ጫን ባለ ቃላቸው።

"ጄጃን ከአያቱ አጥጋቢ ምላሽ ባያገኝም፣
ማብራሪያውን ለጊዜው ሊነግሩት
እንዳልፈለጉ ገባውና ዝምታውን መረጠ።
አንደበቱ ዝም ይበል እንጂ፣ አይምሮው
ብዙ ነገር ያወጣል ያወርዳል። የቀረበለትን
ምሳ ከአወዛጋቢ ሀሳቡ ጋር እያላመጠ
አበቃ።

    በአያቱና በጎረቤት እናቶች ታጅቦ ወደ
አላወቀው ለቅሶ ቤት መሄድ ጀመሩ።
በተሳፈሩበት ውይይት ታክሲ ውስጥ፣
የጎረቤት ሴቶች ከዚህቀደሙ ለየት ባለ
የሀዘኔታ አስተያየት ሲያዩት… የበለጠ
ድንግርግር አለው። ከታክሲ መውረጃው
ደረሱ። በአያቱ መሪነት ጥቂት የኮሮኮንች
መንገድ እንደተጓዙ በቆርቆሮ አጥር
የታጠረና በሩ ገርበብ ካለ ጊቢ ደረሱ።

ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሁሉም ሴቶች
የተመካከሩ ይመስል ለቅሷቸውን
በጅምላ  እየለቀቁት ገቡ …
(በሀዘን ቤቱ፣ብዙ ሰው አለመኖርና፣
ጭርታው፣  አንድ ሁለት ቀን ያለፈው
ለቅሶ  ይመስላል።)
አያቱን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች ለሀዘንተኛ
በተደረደው ወንበር ላይ ተደርድረው
ሲቀመጡ ፣እሱም ተከትሎ ከአያቱ
አጠገብ ባለ ክፍት ወንበር ላይ ተቀምጦ
የሚያለቅሰውን ሰው አንድ በአንድ
ይመለከት ጀመር። አጠገቡ ያሉት አያቱ
አልቅስ እንጂ በሚል ይጎሽሙታል።

  ጄጃን የሞተው ማን ይሁን ምን
በማያውቅበት ሁኔታ ማልቀስ አልቻለምና
የአያቱንን ፍላጎት ማሟላት አልሆነለትም።
ዘለግ ካለ ለቅሶ ሁሉም ጋብ ሲል፣
የሀዘንተኛው ሁሉ አይን እሱ ነው።
ነገሩ ከአይምሮው በላይ ሆኖበት ቢጮህና
እውነቱ ቢነገረው በወደደ …  ከአያቱ ጋር
ባደገበት ሰፈር፣ አይነ ደረቅ የሚባልለት
ጄጃን  ያ ሁሉ አይን ሲያርፍበት ሳይፈልግ
በግዱ አይንአፋር ሆነ።

በለቅሶና በሀዘን እጅግ የተጎሳቆሉና፣ ከዚህ
ቀደም አይቷቸው የማያውቅ ሁለት ወጣቶች
(የሟች ልጆች) ከተቀመጡበት ተስፈንጥረው
መጡና… "ቁጭ እራሱን እኮ ነው የሚመስለው"
እያሉ በፍፁም ፍቅር አገላብጠው ይስሙት
ገቡ።"

ጄጃን ከሟች ጋር የሚያገናኘው አንዳች
ነገር  እንዳለ ጠረጠረ። ቆይ ሟቹ ማን
ነው?  ከኔስ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ
ምንድነው? የልጅ አይምሮው ሊፈነዳ ደረሰ።
ቢጨንቀው ወደ አያቱ ዞረና አያቸው።
አያቱም በጭንቀት አዩትና ከሳሙት
ወጣቶች ጋር ለሁሉም የሚሰማ
ወግ ጀመሩ…

"በመጨረሻው ሰዓት ልጆቼን አደራ እያለ፣
ነበር!" ከሳሙት ወጣቶች አንዱ።
… በተለይ የአባት ፍቅር ሳልሰጠው
ከእናቱ እናት ጋር ያደገውን ጄጃንን
አደራ እኔ የነፈኩትን ፍቅር
እናንተ ስጡት፣ እኔን አያውቀኝም፣
እናቱንም እንደዛው፣ ገና ጡት
ሳይጥል ነው ሴት አያቱ ጋር   ማደግ
የጀመረው… እያለ ነው ያረፈው።"
አለ ሳግ በተናነቀው ድምፅ።

ጄጃን  አንድ ነገር መነገንዘብ ቻለ።
ሟቹ ወላጅ አባቱ መሆኑን።
ነገር ግን በአያቱ ቤት እየሰማና
እያመነበት ከኖረው እውነታ ጋር ነገሩ
ተጋጨበት።

  ከዛ ቡሃላ ምን እንደተወራ፣ ከለቅሶው መች
ወጥተው ቤቱ እንደደረሱ ሳያውቀው ራሱን
ካደገበት ቤት አገኘው።

   … የአያቱ ወንድ ልጅ ታላቅ ወንድሙ
ነስሪ ወደቤት መጣ። ቀን የተፈጠረውን
ነገር ሰምቶ በጣም ተቆጣ። በሌላ
ክፍል ውስጥ ከአያቱ ጋር ለምን
ተነገረው? ትልቅ ሲሆን አይደርስም
ነበር ወይ?  በሚል ሲጨቃጨቁ
ይሰማዋል።

አያቱና ነስሪ ጄጀን ካለበት ክፍል መጡ።

ሌላ ጊዜ ቤቱን በአንድ እግር የሚያቆመው
ጄጃን ዛሬ ሶፋው ላይ ትክዝ ጥቅልል
ብሎ ሲያየው ነስሪ ሆዱ ብርዝ አለበት…
እንደምንም ስሜቱን ተቆጣጥሮ …

"ጄጃን" ብሎ ጠራው ። በጥልቅ
ሀሳብ ተክዞ የተቀመጠውን ጄጃን።
"አቤት" አለው በሰጠመበት ዝምታ
እየነቃ።
"አባታችን ማን ነው?" ሲል ጠየቀው።
"እንዴዴዴ!! ያሲን ነዋ አለ" የሚጠራበት
የወንድ አያቱን ስም። በቃ ዛሬም ነገም
ሁሌም አባትህ ያሲን ነው አለው።
ጄጃን በነስሪ ንግግር ትንሽ ቢሆንም
ውስጡ ተረጋጋ።

ቀናቶች ሲፈራረቁ…
ሳምንታት፣ ወር ሲወልዱ… ዕድሜው
እየጨመረና እየበሰለ ሲሄድ ጄጃን
አንድ እውነት ግን መገንዘቡ አልቀረም።
በስሙ የሚጠራበት ያሲን ወላጅ አባቱ
ሳይሆን አያቱ፣ እነነስሪ ወንድሞቹ
ሳይሆኑ አጎት አክስቶቹ መሆናችውን።
(አቦ!! ግን ይሄ ነስሪ ዛሬ የት ሄደ?)

ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment