Sunday, August 26, 2018

አ ሰ ብ ት መ ለ ስ ል ን

"አሰብ ትመለስልን "
#ሳteናw

… እኛ ኢትዮጲያዊያን ከሶስት አስርት አመታት በፊት ከ1500 ኪሜ በላይ የሚረዝም የባህር በር እንዳልነበረን ሁሉ፣ ዛሬ ላይ በታሪካዊ ስህተት የባህር በር የማጣታችን ነገር ፣ እንደ አንዳች ነገር ይከነክነኛል፣ ይቆጨኛል፣…  በተለይ በተለይ ለወደብ ሲሉ ደማቸውን የገበሩ ጀግና አባቶቻችንን ሳስብ… ሲያልፍም ሀገሬ በየቀኑ ለወደብ ኪራይ  የምታወጣው ሚሊዮን ዶላሮች፣ እንደቀልድ ያጣነው የባህር በር ኖሮ ቢሆንና ፣ ይህ ለሀገር ውስጥ ልማት ቢውሉ ኖሮ ብዬ ሳስብ። ያሰላም እርርርር ጭስስስስ!!

ይህንን ስሜት አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ወገኔ የሚጋራኝ ይመስለኛል። ለዛሬው የባህር በር ማጣታችን ብዙ ምክኒያቶች መደርደር ቢቻልም፣ በዋናነት ግን በመጨረሻው ዘመን የተደረገው የአልጀርሱ  ስምምነት ይመስለኛል። አዎ በዛ ስምምነት ላይ ኢትዮጲያን "የወከሉት ልኡካን፣ ምን ልኡካን ባንዳ እርግማን ልበላቸው እንጂ!!  በድርድሩ ላይ  ለኢትዮጲያ የባህር በር ማግኘት  ለዘብተኛ አቋም ባይኖራቸው ኖሮ በጊዜው  ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጲያ የባህር በር የማግኘቷ ዕድል ሰፊ እንደነበር በዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም የተፃፈው አሰብ የማን ናት በሚለው መፅሃፍ በዝርዝር ተቀምጣል።

በመሰረቱ  ወደብ አልባ ያደረገን የአልጀርሱ ስምምነት፣ አፄ ሚኒሊክ በጣልያን ተፅዕኖ እጃቸውን ተጠምዝዘው ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ በተዋዋሉት ውል ተንተርሶ የተደረገ ነው። በመሆኑም የኢትዮጲያን ጥቅም ያስጠበቀ አልነበረም። ይህን ያወቁ የኢትዮጲያ ተዋዋዮች ጠበቆች፣ ምን አይነት የኢትዮጲያዊነት ስሜት እንዳላቸው ግልፅ ባይሆንም ሙሉ በሙሉ ኢትዮጲያን የባህር በር ያለምንም ክርክርና  ይግባኝ አስረክበው እጃቸውን እያጨበጨቡ በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ ዘመን አይሽሬ  የበደል በደል የግፍ ግፍ ፈፅመው መጥተዋል።

እርግጥ ነው ከ1500 ኪሎ ሜትር በላይ የነበረው የቀድሞ የኢትዮጲያ የባህር በር ና ቀይ ባህር፣ስትራቴጂክ የሆነ ስፍራ በመሆኑ  በተለያዩ ዘመናትት የውጭ ወራሪዎች በማፈራረቅ ለማስተናገድ ተገዷል። ከወራሪዎቹም  ውስጥ ግብፅ፣ ቱርክ እንግሊዝና ጣልያን በዋናነት ይጠቀሳሉ። ከቅርብ ጊዜ ታሪክ ብንጀምር እንኳ ጣልያን ለ50 አመት፣ እንግሊዝ ለ10 አመት ገዝተዋታል የጥንቷን ሀማሴን የዛሬዋን ኤርትራ!!
ይህም የባንዳ መፈራረቅ በስፍራው ይኖሩ በነበሩ ኢትዮጲያዊያን ላይ የኢትዮጲያዊነት ስሜታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረምና የመገንጠል ፅንሰ ሀሳብ ተፀንሶና ተወልዶ እውን መሆኑ አልቀረም።

ሌላው የባህር በር ለማጣታችን ምክንያት አንዱ የአድዋ ጦርነት ነው።

እምዬ ምኒሊክ በአድዋው ድል  ፣ መረብን አለመሻገራች ለተባራሪው ፋሺሽት ጦር ቀይ ባህር ከመስጠም አዳነው። ሃምሳ አመት ከመረብ ማዶ ባለችው የጥንቷ ሐማሴንና፣  ከአንድ አፋራዊ ግለሰብ የተከራያትን አሰብን  ሰፍቶ ኤርትራ የሚል የሚል ስያሜ አውጥቶ፣ ለሃምሳ አመት ቅኝ ገዛ፣ በሃምሳ አመት ውስጥ በራሱ ስዕብና የተገነባ ትውልድ ተፈጠረ። በዚህ ረጅም ዘመን  ያለፈው የአርትራ  የቀድሞው  ትውልድ በኢትዮጲያዊነት ላይ ምንም ጥያቄ ባይኖረውም በአዲሱ ትውልድ ዘንድ ኢትዮጲያዊነቱ መሸርሸሩ አልቀረም። 
አይ እምዬ ሚኒሊክ ምን ነበር  መረብን ተሻገረው ነጫጭባውን መንጋ ቀይ ባህር ባሰመጡልን ኖሮ።

ሌላኛው አመክኒዮ የፌዴሬሽኑ መፍረስ ነው። በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን ኤርትራ ከኢትዮጲያ ጋር በፌዴሬሽን እንድተዳደር በአለም መንግስታት ተፈርዶ ፌዴሬሽኑ ተግባር ላይ ቢውልም። የኢትዮጲያዊነት ስሜቱ የሚያይልበት የኤርትራ ህዝብ ግን " ለምን በፌዴሬሽን?  ኤርትራ እንደ አንድ የኢትዮጲያ ክልል ትተዳደር " የሚሉ ጥያቄዎች ማንሳታቸው አልቀረም። በኤርትራ ፓርላማ ኤትዮጲያዊ አንድነት አቋም ባላቸው አባላት የድምፅ ብልጫ፣ ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ ተደረገ።

በዚህ የተቃወሙ ሃይላት፣ በኢትዮጲያ ታሪካዊ ጠላቶች ትብብር ጀብሃ የሚባል ታጣቂ ተፈጠረ። አላማውም ኤርትራን ነፃ አውጥቶ በራሳ የምትተዳደር ሃገር ለመመስረት ነበር። ይህ ድርጅት በሃይለስላሴ መንግስት ላይ የራስ ምታት ሆነ። ጀብሃአብዛኛውንና ቆላ የሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚወክል በመሆኑ በደጋውና በክርስትያኑ ህዝብ መካከል ክፍተት ተፈጠረ። ይህንን ክፍተት በመጠቀም የሃይለስላሴ መንግስት ከራሱ ከጀብሃ አባሎች ተገንጥሎ ሻዕቢያ የሚባ ለውን ድርጅት፣ ጀብሃን እንዲያዳክመለት በሚል፣ እንቋቋም ያላሰለሰ ጥረት አደረገ። የአፄው መንግስት ተምኔቱ ሳይሰምር  ቀረ።  ጀብሃን ይሸረሽርልኛል፣ የኢትዮጲያንና የኤርትራን አንድነት  ያስጠብቅልኛል የተባለው ድርጅት ሻዕቢያ፣ ነገሩ ተገላቢጦሽ ሆነና  ለረጅም ዘመናት ለኢትዮጲያ የእሳት አሎሎ ከሆነ ቡሃላ ኤርትራን ከኢትዮጲያ ለመገንጠል፣ በቃ። "አይዋስ ቢዋሰኝ ከባለዕዳ ባሰኝ " ይሉሃለ ይሄ ነው። እነዚህ አመክኒዮዎች እንዳሉ ቢሆንም መግቢያ ላይ በጨረፍታ የተገለጠው  የአልጀርሱ ኢፍትሃዊ ስምምነት ሀገሬን የባህር በር በማሳጣት ረገድ የአንበሳውን ድረሻ ይወስዳል። እንግዲህ የባህር በር ጉዳይ በወፍ በረር ሲቃኝ  ከላይ ያለፈውን ይመስላል።

ያለፈው አልፏል። የአሁኑ ትውልድ ግን በዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ መንገድ ኢትዮጲያን የባህር በር እንድታገኝ ያላሰለሰ ጥረት ሊያደርግ ይገባናል፣ አለበለዚያ የባህር በር ላለማጣት የወደቁ የአባቶቹ አጥንት ይፋረደናል!!

ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment