Sunday, July 10, 2016

"አስመራ ናፈቀችኝ"

"አ  ስ  መ  ራ…  ና  ፈ  ቀ  ች  ኝ!! "
#ሳteናw

… በቀይ ባህር ዳርቻ አሸዋው ላይ ባዶ እግሬን ወክ እያደረኩ የንፋሱ ሽውታ፣ በከፊል ቁልፉን  የከፈትኩት ሸሚዜንና ቁምጣዬን…  እያርገበገበው…  የተፈጥሮን ውበት ሳጣጥም… ከማዶ ደግሞ… ፀጋዬ ሀይለማርይምና የአስመራዋ ቆንጆ! ፊያሜታ ጊላይ  ሲያወጉ፣ ሲሳሳቁ፣ በሰበብ አስባቡ ሲነካኩ … ሲሸፋ*ዱ… እሷ  አየሳቀች "ዋእ! አባቴ ይሙት ደደብ ነህ" ስትለው…
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••

  የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም እንዴ? እርግጠኛ ነኝ መልስህ አዎ ነው። እኔ ግን አልሃለው።  አይቻት የማላውቀውን ሀገር በስዕላዊ ብዕር እንድናፍቅ ሆኛለው። የቷ ሀገር ነች ሳታያት የናፈቀችህ ካልከኝ? መልሴ አስመራ ይሆናል። የቀድሞ ክፍለ ሀገራችን፣የዛሬ ጎረቤት አገራችን አስመራን… ።

አዎ! ተዓምረኛው ብዕረኛ ለናፍቆት የሚያደርሰው ያዩት ሀገር ብቻ ሳይሆን፣ በአይን በብረቱ ያላዩትንም ሀገር፣ በስዕላዊ ብዕር አሳይቶ ማስናፈቅ እንደሚቻል አስመስክሯል!! ይገርምሃል ብዕሩን ከሁሉም አቅጣጫ እንደሚቀርፅ ዲጂታል ካሜራ ተጠቅሞ፣ 3D መነፅር አድርጌ ስክሪን ላይ የምሾፋት እስኪመስለኝ ድረስ አስመራን አሳይቶኛል።

ማን ነው እሱ? ማንነቱን ከመግለፄ በፊት ያስደነቀኝ ስዕላዊ ብዕሩን በስሱ እንየው…

  … እንደ ምላስ ንፁህ የሆኑ አውራ ጎዳናዎቿ ላይ በወታደራዊ ሰልፍ ቀጥ ብለው የቆሙ የሚመስሉ አሸብሻቢ ዘንባባዎቿን፣ የገበያዋን ትርምስ፣ዮሃንስ አራተኛ አየር ማረፊያን፣ አይሮፕላኖቹ ሽቅብ ሲያኮበኩቡ፣ ቁልቁል አፍንጫቸውን አዘቅዝቀው መሬት ሲስሙ፣ የሀዝሀዝን የሴቶች እስርቤት ውጪያዊ ገፅታ፣

   የአስመራን ቆንጆዎች ከሹሩባቸው ጋር ውበት ፈሶባቸው፣ የደሀ ቦርጭ በሚያካክሉ በወርቅ ጌጦቻቸው ተጊጠው በፅዱ ጎዳናዎች ሲተላለፉ፣… በነጭ ወረቀት ላይ የሰካካቸው ስዕላዊ ቃላት… ንባብ ላይ መሆኔን አስዘንግቶ… እነዚህ የአስመራ ቆንጆዎች መርካቶ ውስጥ በአጠገቤ የሚያልፉ መስሎኝ "ናይ አስመሪና ፅብቅቲ" ብዬ… ላደንቃቸው በዘመኑ ቋንቋ (ልለክፋቸው) እስኪቃጣኝ… ድረስ ነው ትረካው መስጦ  የሸወደኝ። (ሳፈላ ነው)።

3ዲው ብዕር… በአስመራ ቤተመንግስት፣ መሰብሰቢያ፣ አዳራሽ ውስጥ፣ በመንግስቱ ሀይለማሪያም የተመራውን የቀይ ኮከብ ዘመቻ ስብሰባ ላይ፣ የተገኙ የደርግ ጄነራሎች፣ ኘሮቶኮል ከጠበቀው አለባበሳቸው፣ አንስቶ እስከ አድርባይነት መሽቆጥቆጣቸው ድረስ ያሳዩትን እንቅስቃሴ … በራሱ እይታና ትዝብት የተወከልኩ የስብሰባው ታዳሚ አድርጎ አስሹፎኛል

   ደግሞ በመሃል አስመራ ታዋቂውን በፓራዲዞን ቡና ቤት ውስጡ፣ ቆሜ… የብርጭቅቆች ግጭጭት፣ ቢራ ሲከፈት (ፕስስስ) ሲል ፣የተስተናጋጆች ጫጫታ፣ ሳቅ፣ትዕዛዝ ቡና ቤቷን ሲያዋክባት… ደግሞ  አንዱ ወንበር ላይ የሻዕቢያ ሰላይ የነበረውን ስዕላይ በራኺ ከነ ሸረኛ መልኩ ተቀምጦ በተመስጦ ሲጋራዉን እየመጠጠ ጀሌዎቹን ሲጠብቅ… በቡና ቤቱ ምድር ውስጥ ለውስጥ እንደ ሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ተፈልፍሎ የተሰራውን የሻዕቢያ ህዋስ ሚስጥራዊ ፅህፈት ቤትን፣ … በሻወር ቤት ውስጥ በማያስነቃ መልኩ የተገነባውና፣ መታጠቢያው ገንዳ ተንሸራቶ ሲከፈት ወደ ፅ/ቤቱ የሚያስገባ በጨለማ የተዋጠ ደረጃዎች የሆነውን… ሚስጥራዊን መግቢያ በር እየመራና… እያስደነቀኝ…  በዚህ ዋሻ ውስጥ ይኖራል ተብሎ የማይገመት እጅግ ዘመናዊነት የተላበሱ፣ ከዳር እስከዳር በተነጠፉ ቀይ ንፁህ ምንጣፎች የተንጣለሉባቸውን፣ ምቹ ወንበር የተሞሉባቸውን ቢሮዎች… ከነ ገለፃው…  ደግሞ
… በቀይ ባህር ዳርቻ አሸዋው ላይ ባዶ እግሬን ወክ እያደረኩ የንፋሱ ሽውታ፣ በከፊል ቁልፉን  የከፈትኩት ሸሚዜንና ቁምጣዬን…  እያርገበገበው…  የተፈጥሮን ውበት ሳጣጥም… ከማዶ ደግሞ… ገፀ ባህሪያቱ ፀጋዬ ሀይለማርይምና የአስመራዋ ቆንጆ! ፊያሜታ ጊላይ  ሲያወጉ፣ ሲሳሳቁ፣ በሰበብ አስባቡ ሲነካኩ … ሲሸፋ*ዱ… እሷ  አየሳቀች "ዋእ! አባቴ ይሙት ደደብ ነህ" ስትለው… የአንደበቷን ለዛ ሳይቀር … ከመሀከላቸው ተገኝቼ በአካል ድባቡን በእውን የምታዘብ… እጄን የኋሊት አጣምሬ በጭንቅላቴ ንቅናቄ አዎንንታዊ ምላሽ እየሰጠሁት የሚያስጎበኘኝ አስጎብኚ እስኪመስለኝ ድረስ ነው በስዕላዊ ብዕሩ እየመራ በምናብ፣ አስመራን ያስከለመኝ… ታዲያ ብናፍቅ ትፈርድብኛለህ?
መፅሀፉ አስመራን በአካል ሄጄ ባላያትም በአይነ ህሊና አሳይቶ … አስናፈቀኝ። እንዲህም ስል…  አስመኘኝ…
ምን ነበር? የኤልሞሌ ወላጆች ድንበሩን ከመስበራቸው በፊት ሰላም ወርዶ ቢሆን ኖሮ? ምነው ይህቺ አስመሪና ከኢትዮጲያ ባለተገነጠለች ኖሮ ?…  ግን ማን ያውቃል? አንድ ቀን… ስንሰለጥንና የአንድነት ሀይል ሲገለጥልን እንደ አውሮፓ በአንድ ፓስፖርት የምንጠቀም ሀገሮች እንሆን ይሆናል!!

እመነኝ ኦሮማይን ሳነብ የንባቡ ሂደት የፈጠረብኝ ምስል… ልክ አንደዚህ ነው… ብዕሩ፣ እንደ ተንቀሳቃሽ ምስል ሆኖ፣ የማላውቃትን ሀገር አስመራን እንድናፍቅ ያደረገኝ…ግን ማነው ደራሲው? በዚሁ መፅሀፍ የመጣ ህይወቱን የከፈለና እስከዛሬ አሟሟቱ በግልፅ ያልታወቀው ድንቁ ብዕረኛ በአሉ ግርማ ነው(ነብስይማር)። ኦሮማይን ካላነበብከው አንብበው እልሃለው!!)
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment