Friday, May 20, 2016

የትም ተወለድ መርካቶ እደግ

#ሳteናw

"የትም ተወለድ መርካቶ እደግ"

"የትም ተወለድ መርካቶ እደግ" የሚለው ብሂል ያለነገር አልተባለም። ይህን አባባል ዛሬ ፌስ ቡክ ላይ መርካቶን አውጥተው የሰፈራቸውን ስም በመተካት የሚፖስቱትን ስታይ ለየትኛው ሰፈር እንደተባለ ግር ብሎህ ይሆናል! አይዞህ ግር አይበልህ ከዚህ ፅሁፍ ንባብ ቡሃላ ግን አባባሉ ለማን እንደተባለ በራስህ ፈራጅነት ታረጋግጣለህ።

ለአንድ ሰው ዛሬ ለተላበሰው ስብዕና አስዳደጉ ወሳኝ ሚና መሆኑን ማስታወስ አይጠበቅብኝም። የዛሬ ማንነት የአስተዳደግ ፍሬ ነው። መርካቶ ሰፊ የገበያ ስፍራ በመሆኑ የማይረግጠው የማይጎበኘው የሰው አይነት የለም። አዋቂው፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ አስተማሪው፣ ተማሪው፣ ቱሪሰቱ፣ ለማኙ ፣ቀማኙ … በዚህም ሳቢያ የመርካቶ ልጅ በአስተዳደጉ ከማይገናኘው የሰው አይነት የለም እልሃለው። ይህም መስተጋብር በአስተዳደጉ የህይወትን ውጣ ውረድ ብዙ እንዲያይ፣ብዙ እንዲታዘብ፣ብዙ እንዲያውቅ ያደርገዋል የመርካቶን ልጅ።

ሌላ ሰፈር ያደገንና የመርካቶን ልጅን አቅርበህ ብታነጋግር በንቃተ ህሊናም ሆነ ብዙ አዲስ ነገር በማወቅ ረገድ የመርካቶ ልጅ ልቆ እንደምታገኘው ጥርጥር አይግባህ። ከከተማችን ሰፈሮች ሁሉ የመርኬ ልጅ በንቃተ ህሊናው ልቆ መገኘቱ ይሄው አስተዳደጉ ነው። በሌላ ስፍራ ገና ዳይፐር የሚቀያየርለት ህፃን የመርካቶ እኩያው ዳይፐር ሲሸጥ ታየዋለህ። ገና በጨቅላነቱ የኢኮኖሚ የተግባር ባለሞያ ይሆናል፣ የትኛው እቃ በየትኛው ወቅት እንደሚሸጥ ያለምንም አለማዊ እውቀት ይገነዘባል።  በልጅነቱ የህይወትን የተለያየ ገፅታ አይቶና አውቆ ያድጋል። በያንዳንዱ እንቅስቃሴው ምን ማድረግ እንዳለበት ለመርካቶ ልጅ መምከር ጊዜ ማጥፋት ነው።

በኪነ ጥበብ ዘርፍ ብትል የመርካቶ ልጅ ከ18 ቀበሌው ከሂሩት ቪዲዮ ቤት አንስቶ በዘመኑ ዘመናዊ እስከነበሩት ሲኒማ ራስ፣ አዲስ ከተማ ሲኒማ፣ የፊልምና የትያትር ጥበቦችን ገና ከህፃንነቱ አጣጥሞታል። ሀይመኖተኛነትን እንደ የእምነቱ በከበቡት ቤተ አምልኮዎች ይስተማራል። የተለያዩ እምነቶችን አስማምቶ አፋቅሮና አዋዶ እንዲያድግ … ያለማንም ኘሮፖጋንዳና አስተማሪ የራጉኤልና የአንዋር መስጊድ የጉርብትና አጥር ብቻ ማየት በቅቶታል። ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት ባሉ መንደሮች ያደገ ክርስቲያን ወጣት ከቁርአን ክፍል ፋቲሃን ቅራ ብትለው ሳያዛንፍ ያንበለብልልሃል። በተክለ ሀይማኖት ቄስ ትምህርት ቤት ተምሮ ያለፈ ሙስሊም ህፃንም የጠዋትና ማታ የዳዊትን ፀሎትን ያንቸለችልልሃል። የመርኬው ፈላ !

ይህ ብቻ አይደለም ሁለቱን የህይወት ጎኖች ማግኘትንና ማጣትን ገና ከጨቅላነቱ በከበቡት ባለ ሀብት ነጋዴዎች፣ በሌሊት ከእዳሪ ቡሃላ  መርካቶ በሚደርሱ የኔ ቢጤዎች አማካኝነት ጠንቅቆ ያውቃል። የችግርን መራራነት ለመረዳት በችግር ውስጥ ሳያልፍ በማየት ብቻ ይረዳዋል።የህይወት ዑደቷ በተለያዩ አጋጣሚዎች ህይወታቸውን የለወጠ ስብዕናዎችን በሰባተኛ ጉራንጉር፣ በአውቶብስ ተራ የምሽት ተሰላፊ እህቶች፣ በአሜሪካ ጊቢ በአልጋ ተራ ሴቶች አይቶ ግንዛቤ ይኖረዋል። አለነገር የትም ተወለድ መርካቶ እደግ አልተባለም። ፀጋዬ ገ/መድህን በቅኔው  የተቀኘለት… አብዱ ኪያር በዜማው ያቀነቀነለት… መርካቶ። ከየትኛውም ስፍራ መርካቶ የማደግን ልዩነት ይበልጥ ለማስገንዘብ በጥቂቱ መርካቶንና ክፍለ መርካቶዎቿን በስሱ ላስታውስህ

መርካቶ፣ አውቶቢስ ተራን ጎጃም በረንዳን ከራስጌው ፣ ከተክለሀይማኖት እስከ አብነት ከግርጌው አኑሮ ሰፍሯል።
ከአፍሪካ በትልቅነቱ ግንባር ቀደም መርካቶ ምንም አይነት ሰው እንደማታጣ ሁሉ ምንም አይነት ሸቀጥም እንደማታጣ ስነግርህ ከልቤ ነው። ዋና ዋናዎችን ሸቀጥ ትተህ በዙሪያህ ምንም አያገለግሉም ብለህ የፈረድክባቸው ቁሶች መርካቶ ስራ ላይ ሲውሉ ትታዘባለህ

… አገልግሎቱ አብቅቷል ብለህ በግቢህ ውስጥ ለልብስ ማጠቢያ ምጣድ ማስደገፊያነት ብቻ የምትጠቀመው የመኪና ጎማ፣ በጎማ ተራ እጆች… ወደ በረባሶ ጫማ፣ ልብስ ማጠቢያ የጎማ ሳህን፣ ዘመን የማይበጥሰው ገመድ… ወዘተ ሲሆን በአይንህ በብረቱ አይተህ በመርካቶ ጎማ ተራ ልጆች ፈጠራ ትደነቃለህ። የጥፍር ቀለም ጠርሙስ፣ የቅባት ጠርሙስ፣ አሮጌ ጫማዎች፣ የተቀዳደዱ ልብሶች፣ የተበጣጠሱ ፌስታሎች፣ የኘላስቲክ ውጤቶች፣ ብትንትናቸው የወጣ ካርቶኖች… የለስላሳ  ቆርቆረሮዎች ብታምንም ባታምንም መርካቶ የሚሸጡ እቃዎች ናቸው። ትላንት እህቶቻችን ተጠቅመው የጣሉት የጥፍርና የቅባት ቀለም ጠርሙስ ዛሬ አንዱ ምግብ ቤት የደቃቅ ጨው ወይም የቅመማ ቅመም ዕቃ የሆኑት በመርካቶ ውስጥ አልፈው ነው። ጠብሽ ከንቶህ ለቁራሌው የሸጥከው የዘይት ቆርቆሮ ወንፊት፣ ላቀች ምድጃ፣ ቀፈሻ፣ ወዘተ… አድርጎ መልሶ ለማዘርህ የሸጠልህ የመርካቶ ቀጥቃጭ ሰፈር ልጅ ነው። በስፍራው ማደጉ አይረባም የተባለን ነገር መልሶ አገልግሎት ላይ የማዋልን እሳቤ በተግባር ይማራል።የተበጣጠሱ ፌስታሎችና ስብርብራቸው የወጣ የኘላስቲክ ውጤቶች ለኘላስቲክ ፋብሪካዎች ለጥሬ እቃነት ግብዓትነት በመርካቶ እንደሚሰበሰቡ ብነግርህስ። ተሰብሯል ብለህ የጣልከው ባልዲ በሪሳይክል ኘሮሰሰህ ጆክ ሆኖ የምትጠቀመው የመርካቶ ነጋዴ ለፋብሪካዎች አስረክቦ ነው። ከየትኛውም አህጉር፣ ሀገር፣ ሰፈር ወደ ከተማህ የሚገቡ… ሸቀጣ ሸቀጦች መዓከላቸው መርካቶ ነው። ወይ መርካቶ!

አብዶ በረንዳ አለልህ ደግሞ… የከተማችን የጫት ፍጆታ በገፍ የሚያቀርብልህ የጫት ገበያ። በቅጡ ያልተነገረለት፣ ከመርካቶ የገበያ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ነው። አብዶ በረንዳ ስያሜው ከምን ከማን እንደመጣ ባይታወቅም… አብዶ በተሰኘ ሰው እንደተመሰረተ መገመት አይከብድም። ከሰባተኛ በስተቀኝ የሚገኘው አብዶ በረንዳ በጫት ቆጮና የሸክላ ውጤቶች የሚገበይበት ቦታ ነው። 24 ሰዓት ጫትና እብድ ብትፈልግ አታጣም! አብዶ በረንዳ።

ከአብዶ በረንዳ አጠገብ ወራባ ተራ አለልህ። አላቂ ምግብ ነክ ዕቃዎች በጅምላ የምትገበይበት። ወራባ በስልጢኛ፣ በሀደሪኛ በሶማሊኛ (ጅብ) ማለት ነው። ጅብ ተራ ብለህ ተርጉምልኝ ወራባ ተራን። ስፍራው ይህን ስያሜ ያገኘው ድሮ በግንትር  እቃዎች በመታወቁ ነው። ዛሬ ባይኖርም በፊት በፖሊስና ህብረተሰብ ኘሮግራም ላይ ሸክላ ፈጭተው በርበሬ፣አንዳች ነገር ጨምቀው ዘይት፣ ሙዝ አቡክተው ቅቤ ብለው ሲሸጡ ተይዘዋል ሲል ያሳወቀህ ወንጀለኞች… መሠረታቸው ከዚህ ስፍራ መሆኑንም አልዋሽህም።

ቦንብ ቦንብ የሆኑ ነጋዴዎች፣ ከዱባይ፣ ከቻይና… ሸቀጥ፣ ሀገርህ የሚያመርታቸውን ዕቃዎች አስመስለው አሰርተው አስመጥተው የሚያከፋፍሉት በመርካቶ ቦንብ ተራ መሆኑን ሳልገልፅልህ አላልፍም። ይሄንንና መሰል ሁኔታዎች ታዝቦ ማደግ ቀልድ አይደለም። ለዚህም ነው የመርካቶ ልጅ አዲስ የሚሆንበት ጉዳይ የለም ምልህ… አለ የተባለ የዘመኑ ምርጥ ምርጥ ሞዴል ሞባይልና ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ተያይዞ ለሚመጡ ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎች ቅርብነቱ ምንም ጥርጥር የሌለው ሀቅ ነው። የመርካቶ ልጅ ሀረር ሳይሄድ ስለ ሀረር ይተነትንልሃል።

ለምሳሌ:- አንተ የአምር አብዱላሂን ሀገር ሐረር ሄደህ ግንቧን ማየት ባትችል፣ የሀደሬዎችን የቤት አሰራራቸውን፣ የመጅሊስ መደቡን፣ የግድግዳ ላይ ጌጦቻቸውን፣ የእደ ጥበብ ውጤታቸውን አይተህ ለማድነቅ ባይሳካልህ፣ የፍቅር ሀገር ድሬን የአኗኗር ገሯምነቷን መጎብኘት እጅ ቢያጥርህ… ና ወደ መርካቶ። በብዛት የብሄሩ ተወላጆች የሰፈሩበት ሀደሬ ሰፈር ፣ የሀረርጌና የድሬ ፍቅርና አኗኗር ዘይቤ ድባብ በናሙናነት ቁልጭ ብሎልህ  ታገኘዋለህ።ሀረርና አጎራባቾቿ አፈራሽ የሆኑ የጫት ዘሮችን መቃም ቢያሰኝህ ሀረር ሳትሄድ እዚሁ አለልህ በመርካቶ ሀደሬ ሰፈር። ትንሽ ወረድ ብለህ… ፎዴ ተራ ግባ ደግሞ የተለያዩ ሰልባጅ ጫማዎችና ፣ የሸክላ ውጤቶች በገፍና በቅናሽ ዋጋ … ታገኛለህ፣ ካልባነንክ ትገነተራለህ።በፊት ከፊት ለፊቱ ሜዳ ሆቴል የሚሰኝ የሜዳ ላይ ምግብ ቤት ነበረ። ከአንድ ጉርሻ አንስተህ እስከፈለከው ድረስ የሆቴል፣ የኬክ ቤት የደሀን፣የሀብታምን፣ የክርስትያን፣ የሙስሊም፣ ምግቦች በአንድ ማዕድ በፍቅር ተሰባስበው ሲሸጡ ከመመልከትህ ባሻገር ልዩነት አልባ አንድነትን ትማራለህ በመርካቶ ጉርሻ ገበያ። 

  ከሀብታም መልስ ላይ ታድመህ፣ የሙሽራና የሚዜዎቹ ባህል ልብስ ውበቱ ካስደመመህ አትጠራጠር! ጥጡ ከአፋር ቢለቀምም፣ በምንጃር ተወላጅ ተፈትሎ በእንዝርት ቢሾርም ፣ በዶርዜ ልጆች ተሸምኖ ጥለቱ ቢያምርም፣ ድንቅ አድርጎ ሰፍቶ የሸጠላቸው የመርካቶ ሸማ ተራ ባለ ሱቅ ነው።

መርካቶ እንደ ቃሉ ቀላል ስፍራ አይደለም… የሌለበት ጉድ፣ የለም በዚህ ሁሉ መሀከል ማደግ ቀልድ አንዳልሆነ አሁን የተረዳህ ይመስለኛል። ሌላው ደግሞ መርካቶ ያላፈራቸው አይነት ሰዎች የሉም። ከከባድ ነጋዴዎች ጀምረህ በተለያዩ የህይወት ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ለሀገርህ እጅግ አስፈላጊ የምትላቸው ሰዎች ሞልተዋል። ከትልቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአዛውንት እስከ ጨቅላ፣ ከባለ ሀብት እስከ መናጢው፣ ከጤነኛው እስከ እብድ… ሁሉንም የህብረተሰብ ስብዕናዎች ሁሉንም አይነት ብሄር ብሔረሰቦች ጠቅልሎ የያዘ አንድ ክልል ቢኖር መርካቶ ሰፈሬ ነው።
በቃ አልነዝንዝህ እንደ ብሂሉ እኔም እደግምልሃለው… "የትም ተወለድ መርካቶ እደግ"ብዬ ተሰናብቻለው!
ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment