Thursday, May 12, 2016

የአባድር ት/ቤት የትውስታ ቅንጭብ

#ሳteናw
☞ የታች አባድር ትውስታዬ
ከ1ኛ አስከ 6ተኛ ክፍል ብቻ ወደሚያስተምረው ታች አባድር ለመመዝገብ ስሄድ… በቀበሌ 18 አፀደ ህፃናት ኬጂ ተምሬ የጨረስኩበትን የምስክር ወረቀት ይዤ ብሄድም መዝጋቢው ኡስታዝ አህመድ ከዜሮ ክፍል መጀመር እንዳለብኝ ለሴት አያቴ አሳውቀው መዘገቡኝ። ትምህርት ቤቱ ማስተማር የጀመረ እለት ቀደም ብዬ ከቅጥር ጊቢው ደረስኩ። የታች አባድር ት/ቤት ከልሙጥ ቆርቆሮው የግቢው በር እንዳለፍኩ ዙሪያውን መስኮት እንጂ መስታወት የሌላቸው መማሪያ ክፍሎች ተቀበሉኝ። በለው! የጊቢው ስፋት የጦጣ ግንባር በሉት!። ሜዳው ከስፋቱ ጋር በማይመጣጠኑ ትልልቅ ድንጋዮች እንደ ኮብልስቶን ተገጥግጠው የተነጠፉበት ነው። የድንጋዩ ሜዳ በክረምቱ ከተማሪዎች ኮቴ እፎይ ስላለ ነው መሰለኝ ከንጣፍ ድንጋዮች ሰርጥ አምልጠው ሳሮች በቅለውበታል። ከግቢው በር ጎን ከሚገኘው ቢሮ በረንዳ… የእንጨት ምሰሶ ላይ የከባድ መኪና ጎማ ተቀባይ ብረት ተንጠልጥሏል። ምንድነው? ብዬ ጠቀሜታውን ሳላሰላስል … ጥበቃው ጋሽ ስራጅ እንዝርት የመሰለ ብረት በቀኝ እጃቸው ይዘው የተንጠለጠለውን ብረት በያዙት የእንዝርት መዶሻ አንኳኩት…ኪው ኪው ኪው… ወዲያው ተማሪው ሲራወጥ ደወል መሆኑ ገባኝ። ለብሄራዊ መዝሙር ተሰለፍን፣ የመዘገቡኝ ኡስታዝ አህመድ እንደ ጦር ጀነራል ከተማሪው ሰልፍ ትይዩ ቆመው የሰልፉን ስነ ስርዓት መሩ።።…አሳርፍ፣ ከንዳ ፣ ተጠንቀ…ቅ…1… 2… 3 (ቢስሚ ካላሁ በለድ…) አረብኛ መዝሙር አዘመሩን (ማለቴ ነባር ተማሪዎች ዘመሩ) ቀጥሎ ብሄራዊ መዝሙር…አዘመሩን።
ወደ ክፍል እንደገባው፣ ወንዶች በግራ ሴቶች በቀኝ ረድፍ በእንጨት ዴስክ ላይ ተቀመጥን። በተሰባበረው የተማሪ መማሪያ ዴስክ ላይ ከድሬና፣ እንድሪስ (አላህ ይርሃመው) ካቦ ለመሆን መራኮት ጀመሩ። ትችለኛለህ? እያሉ እያንዳንዱን ተማሪ ግብግብ መያያዝ ጀመሩ … አብዛኛውን ተማሪ "አልችልህም" አስባሉ። እኔ ጋር ሳይደርሱ የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ አረብኛ አስተማሪ ኡስታዝ ሱልጣን ገቡ። ሲተራመስ የነበረው ቁጫጭ አደበ። በእጃቸው መፅሀፍት ቾክና ቀጭን ጎማ ይዘዋል። በተሰባበረው የተማሪ መማሪያ ዴስክ ለሞላነው ውሪዎች ብላክ ቦሩድ ላይ በአረብኛ ፊደል ቃላትን ፃፉ። ደብራተችንን ገልጠን ለመፃፍ እንታገል ጀመር። እኔማ የፃፍኳት (አሊፍ) የተሰበረ እግር ትመስል ነበር። ቀጥለው የፃፏቸውን ቃላት በመግረፊያ ጎማቸው እየጦቀሙንና ጮክ ብለው እያነበቡልን እኛንም በህብረት ድምፅ አስደገሙን… ዘሀባ…አኛ ዘሀባ… ወቀፋ… እኛም… ወቀፋ … ጃለሳ…ጃለሳ። ቀን አልፎ ቀን ተተካ እንዚህንና በርካታ የአረብኛ ቃላት ቃላት እንደሸመደድን… ያለ ቲቸር ሱልጣን አስባይነት በመጠቆም ብቻ ማንበብ ጀመርን ዘሀባ… (ኬ!ቲቸሩ) … ወቀፋ…(ሚን) ጃለሳ… በሞራል ቃላቱን እንድንደግም ኡስታዝ ሱልጣን ጆሮአቸውን በአልተሰማኝም ስታይል ወደኛ ይገፉታል … እኛም ድምፅ ጨምረን … ዘሀባ… (ኬ) ወቀፋ…(ሚን) ጃለሳ… (አላህ ይማራቸው ኡስታዝ ሱልጣን)።
በጋሽ ስራጅ ሰው መራሽ ደወል ለእረፍት ስንለቀቅ የጊቢው በር ተበርግዶ ይከፈት ነበር። ጠፍጣፋና ክብ ብስኩት፣ እንደ ቃጫ የተጠመለለ ብስኩት፣ የበሶ ጀላቲ፣ የወተት ጀላቲ፣ የተድበለበለ ሰሊጥ፣ ቀጭንና ረጅም ቾክ የሚመስለው አሊ ከረሜላ ወዘተ… የሚሸጥበት ከጊቢው ውጪ ላይ ጊዚያዊ ገበያ ይደራል። ጀላቲ የመቀማማቱም ነገር እንደዛው። ታማኝ የነበርነው ተማሪዎች በእረፍት የትም ብንሄድ ተመልሰን እንመጣለን።
ሌላኛው ትዝታዬ 8 ብር የነበረውን ወርሃዊ ክፍያ ሳንከፍል ካሳለፍን ደግሞ፣ ቲቸር አህመድ ትልቅዬ መዝገቡን ይዞ አየተማርን ዘው ብሎ ይገባል። አስተማሪው ማስተማሩን ያቆማል። ቲቸር አህመድ መዝገቡን ገልጦ
"አከሌ አከሌ"
አቤት!
"ቀጥል" በእጁ ወደ ውጪ እያመለከተ።
"አከሌ አከሌ"
አቤት!
"ቀጥል"
አያለ በመጥራት ከትምህርት ገበታችን ወደ ቤታችን ያባረናል።
ታች አባድር እስከ 6ተኛ ያስተማሩኝን አስተማሪዎች በወፍ በረር እንቃኛቸው።
☞የት/ቤቱ ዳይሬክቶር ሶፊያ፣ ሁሌም ፊቷ ላይ ሲሪየስ ገፅታ የሚነበብባት ነበረች። በተማርኩበት አመታት ስትስቅ አይቻት አላውቅም። ሌላው የሚታወሰኝ ድርጊቷ አስተማሪ ሲያስተምረን ድምፅ ሳታሰማ መስታወት በሌላቸው መስኩት ቆማ የምትሰልለን ነገር። የረበሸን ተማሪ ጆሮ ስትመዘልግ።
☞ሳይንስ አስተማሪያችን ኑርሁሴን ወፍራምና ራሰ በራ! ነገር ነበር። በትንሽ ነገር ቱግ ይላል… በሚንተባተበው አንደበቱ "አንተ እናትክን እጠፈጥፍሃለው!" ማስጠንቀቂያ ያዘወትራል። ስተንተኛ ክፍል እንደሆነ እንጃ የክፍል ሀላፊያችን ሆኖ በመጨረሻው አመት መፅሀፍ ስናስረክብ፣ ተረክቦ ከደረደረው መፅሀፍ በከድሬ ጆካ አማካኝነት እየሰረቅን ደግመን ስናስረክው በመጨረሻ ጎድሎበት ሲወዛገብ አስታውሳለው።
☞አጭሩና ሱዳኒ የሚመስለው … ቲቸር አብዲ ህብረተሰብ አስተማሪ ነበር። ልዩ ባህሪው አስቸጋሪን ተማሪ በመታገስ የሚያክለው አልነበረም። ትግስቱ ያበቃ ጊዜ ግን እሱን አያርገኝ በረባሹ መቀመጫ ላይ ያሉ ተማሪዎች ሁሉ ከቅጣቱ አያመልጥም። ባስ ሲልበትም ዴስኩ ላይ ቆሞ እንደ አረም በያዘው ጎማ ይጨፈጭፈን ነበር። የሚገርመው ከ17 አመት በፊት የማውቀው ቲቸር አብዲ አሁንም እራሱ ነው።
☞ኮራ ኢንግሊሽ ቲቸር፣ የማይፈራው ተማሪ አልነበረም።
☞የወጣት ተክለ ቁመናው በጉልምስናው ወቅት ያልከዳው ኡስታዝ አብዱላሂ ሙሉ ሽበትና ሉጫ ፀጉሩ ህንዳዊ ያስመስሉት ነበር …ምን አስተማሪ እንደነበር ዛሬ ላይ ባላስታውስም። በተፈሪነቱ ውስጥ ተወዳጅ አስተማሪ እንደነበር አይረሳኝም (አላህ ይርሀመው)።
☞ቀጭንና ጠጪ፣ሱሴ አይኑ ሁሌም በርበሬ ከመሰለው ቲቸር አጥናፉ ቡሃላ አማርኛ አስተማሪዬ የነበሩት አዛውንቱ አርዓያ ነበሩ። ከሳቸው ክፈለ ጊዜ ትዝ የሚለኝ። አንድ ቀን ሲያስተምሩን በ "አ" ፊደል ቃል የሚሰራ ብለው ተማሪዎችን ማሳተፍ ጀመሩ። አጠገቤ ይቀመጥ የነበረው ሞኛሞኝ ነገሩ አድል እጁን አወጣ። አድሉን ሰጡት።
"አር!" አለ። ሁላችንም ሳቅን። ቲቸር አርአያ (ባልጠፋ ቃል አር) በሚል ገፅታ ገርምመውት አርን ፃፏት።
☞ሂሳብ አስተማሪ ቀጭን ረጅሙ ኤልያስ፣ በሚነፋነፈው ድምፁ አስታውሰዋለው። አብረውኝ ከተማሩ ተማሪዎች ከድሬ፣ መሀመድ ኑር፣ ወንድማማቾቹ ሙስጠፋናቢላል፣ አይዳ ኢንቲሳር፣ሂክማ፣ ሀናን… ያልፃፍኳቸው ብዙ ተማሪዎች አሉ።
☞የላይ አባድር ትውስታዬ
7ተኛ ክፍል ላይ አባድር ስማር… ቁሌታም ነገሩ አስተማሪ መሀመድ ሱልጣን፣…(የላይ አባድር ትውስታዬ በሌላ ቀን እመለስበታለው)
የኔን የታች አባድር ትውስታ አንድ በአንድ ብቸከችከው ማሰልቸት ስለሚሆን አስኪ የናንተን የታች አባድርን ትውስታ አካፍሉን።

No comments:

Post a Comment