Thursday, May 12, 2016

መሳይ

  #ሳteናw

  የሳሎንም የማዕድ ቤትም ሚና በምትጫወተው ጠባቧ የጓደኛዬ እናት መኩ ቤት ምንጣፍ ከተነጠፈበት ፍራሽ ላይ በጎኔ ተኝቼ ትራስ ተደግፌ … በሞባይሌ ኢንተርኔት ከፍቼ የተለያዩ ድህረገፆችን እያገላበጥኩ ነው። ድህረ ገፆችን ሳገላብጠጥ ርሃብም ሆዴን እያገላበጠው ነበር።ከፊቴ የጓደኛዬ እናት መኩ እራት ፍርፍር ለመስራት ጉድ ጉድ ትላለች። በምታፈረፍረው ፍርፍር ከቁሌቱ ጀምሮ ጣል እስከተደረገው ቅቤ  ቃና … ድረስ … ሆዴ  ኡኡኡኡ ድረስልኝ አያለ እየጮኸብኝ ነው። አይኔ ሞባይል ስክሪኔ ላይ ቢሆንም በርሃቤ ሚናነት ልቤ በማፈርፈሪያው ድስት ውስጥ ነበር። ድሰቱ ውስጥ የሚንከራተተው ልቤን ወደ ኢንተርኔቱ መሰብሰብ ቢያቅተኝ።

"ለምን ካርዴ ይክሰር ልጄ!" ብዬ ኢንተርኔቱን አጠፋሁት። ልቤንም እንዳሻት ታድርገው ብዬ ሙሉ በሙሉ ለመኩ ተውኩላት። መኩ ማቁላላት ስትጀምር አብሮ ሲቁላላ… እንጀራውን ስታፈረፍር አብሮ ሲፈረፈር… አዚህ ደግሞ ሆዴ ሲያንቋርር…  በስንትና ስንት መከራ የማይደርስ የለም… ረጅም ሰዓት ያሻፈደኝ ፍርፍር … ደረሰ።

  እራት ቀረበና በላን… ስነጀምር አጎራረሴ ፈረስ መዘለል የማይችለው ቋጥኝ የሚያክል ጉርሻ እያነሳው የሚያንቋርረው ጨጓራዬ ላይ ላይ በላይ ስተገትግበት  ጋሼ ጨጉሯ ከፍርፍሩ ጋር መላወስ ጀምሮ ቢዚ ሆነ መሰለኝ መጮሁን አቆመ። ደግሞ እንዴት እንደሚጣፍጥ። ማን ነበር? ሁሌም እየጣፈጠው የሚበላው ደሀ ብቻ ነው ያለው?። ማንም ይበለው ማን ነገሩ ልክ ነው! ደሀ ሁሌ ርቦት በሚበላበት ምድር እያጣፈጠው ባይበላ ነበር የሚገርመኝ። ርሃቤ ጋብ ሲል ልቤ ከፍርፍሩ ወጥቶ ፍልስፍና ውስጥ ገባ! ጨጓራዬ ስራ ስለፈታ ነበር እንዴ እሪሪሪ ኡኡኡ እያለ ሲጮህ የነበረው!? መጮህ የስራ ፈቶች ድርጊት ነው እንዴ? ብዬ ራሴን ጠየኩ።ሌላው ማንነቴ መልስ ሰጠ።

"… አይደለም! ምክኒያቱም በመጮህ የሚተዳደሩ ሰራተኞች አሉ … ለምሳሌ የታክሲ ወያሎች፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ወያሎች እንዲሁም የኢቲቪ ወያሎች… አያለ መልስ ያለውን ሲያንበለብብኝ …

"ሆሆ! ወንድሜ ልኑርበት… ከጉዳዮቹ ጋር አታነካካኝ! … ብዬ አቋረጥኩትና… ሀሳቤን ወደ ፍርፍሩ መለስኩት።

☞"አየህ አይደል ችግራችሁ የዘመኑ ልጆች"

☞"ምንድነው? ምን ሆንክ ደግሞ" አልኩት።

☞ ፈሪና ቦቅባቆች ናቹኋ። ችግርን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ ባልሰማ ባላየ ሙድ ከችግሩ ጋር መላመድ ትሻላችሁ። ያለምንም ጥረትና ትግል ምቾትን ትናፍቃላቸሁ። ፍላጎታችሁ… የበሰለ መመገብ ብቻ!! አሁን አንተ በስሎልህ እደምትመገበው… 

☞"ታዲያ በማብሰል ሂደቱ ራቅ ብልም ልቤ ድስቱ ውስጥ እንደነበር ረሳህ …? አልኩት።

☞"ልብህ ድስቱ ውስጥ ቢሆንም እጅና እግርህ ተጣጥፎ  ስራፈቶ አልነበር እንዴ? ደግሞ እወቅ ለተግባር ዋናው  አንቀሳቃሾቹ እጅና እግር  እንጂ ልብ ብቻ የተግባር መሳሪያ አይደለም !ገባህ? ልብ አመላካች ነው። እጅና አግር አድራጊ ናቸው። አንተ የመብላት ፍላጎትህ ወርውሮት ልብህ ድስቱ ውስጥ ቢሆንም… ለፍላጎትህ መሟላት ደግሞ እጅና እግርህ ተጣጥፈው ምንም አስተዋፅኦ አላበረከቱም?!ግና ተነስተህ መኩን… በተግባር አግዘሃት ቢሆንስ ኖሮ? የርሃብ የስቃይ ዘመንህ ያጥር … በመመገቡም ረገድ ያንተ አስተዋፅኦ ስለታከለበት በደስታና በእርካታ ትመገበው ነበር። ይሄን በምሳሌ ላሳይህ ፈልጌ እንጂ… በማህበረሰባዊ ፖለቲካዊ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ላይ የራሳችሁን የተግባር አሻራ አኑራቹ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ሀገራችሁ ዴሞክራሲ ከሰፈነባችው ጥቂት ሀገራት ተርታ ትመደብ ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው የዘመኑ ልጆች እንዲህ እንዲያለ ነገር አልፈጠረባችሁ። 

☞ ጀለሴ ፖለቲካህን አታራግብብኝ። እኛ ከፖለቲካ ውጪ ነን። ከ97 ቡሃላ ከፖለቲካ እጃችንን አውጥተናል።ፖለቲካ ፖለቲካ ብለን ያተረፍነውም የኑሮ ውድነትና የሞራል ውድመትን ነው።

☞ ከፖለቲካ ውጪ ነን ብትሉም ቅሉ የህይወት ኡደት እራሷ ከፖለቲካ ታነካካለች። ማንም ከፖለቲካ ንክኪ አይድንም… እያለ ሊተረተር ሲል  አቋረጥኩት። 

☞ ቱልቱላ ነገር ባክህ እራቴን አስጨረስክብኝ። ብዬ ወደ ፍርፍሩ ዞርኩ። ሌላው ማንነቴ ባነሳው የፖለቲካ አጀንዳ ባስቆመውም በምርጫ 97 የሆነ ልዩ ትውስታ ትዝ አለኝ። 

   • ምርጫ 97ትን ተከትሎ በመራጩ ህዝብና በመንግስት መካከል  <<ድምፅ የሰጠሁበትን ኮሮጆ ቀይረሻል! አልቀየርኩም>> የሚል ሀገራዊ ወዝግብ ተከሰተ። ይህ አለመግባባት ቀስ በቀስ የምርጫ ውጤት ይገለፅበታል በተባለበት ዕለት ማለትም ሰኔ 1 ቀን 1997  የተጭበረበረ ውጤት አንቀበልም ባለው ህዝብ ከባድ ተቃውሞና አደገኛ ረብሻ አስከተለ …  በረብሻው ወጣቱ  አውቶብስ ሰበረ ፣ የህንፃዎች መሰታወት ተከሸከሸ…

   በወጣቱ ድርጊት የተናደደው መንግስት በስናይፐር ታጣቂዎቹ የወጣቱ አናት አነደደው። ማታውን በቴሌፍጀን ዜና በረብሻው የተሰው… ወጣቶች በየስማቸውና በእድሜያቸው ላይ አስር አመት ተጨምሮላቸው ተገለፀ። ስለ እድሜያቸው መጨመር ለተነሳው ጥያቄ አንዳንድ ልማታዊ ነዋሪዎች(የ20 ወጣት ሲሞት በአንድ ቀን የ10 አመት ዕድሜ ይጨምራል) ብለው ለህብረተሰቡ ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ መልስ አብራሩ… አሉ። አሉ ባልታ ነው።

  "እያንዳንድሽ ከአሁን ቡሃላ በሁለት ጣቶቼ እቀሳሰራለው ብትዪ ውርድ ከራሴ!!… ታጣቂዎቼ ላይ ድንጋይ ናዳ አራግፋለው ብትዪ እንደ ቃሪያ አራግፍሻለው…ምድረ የሲኒ ላይ መዓበል…" የሚል ኮሜዲም ትራጄዲም መሰል ነገር ተሰማ አሉ …

  ወጣቱ በሌሊት ከየቤቱ ተለቅሞ ወደ ዝዋይ እስር ቤት በኦራል መኪና ተጋዘ። ይህ አመፅ ትንሽ ጋብ አለ። በመራጭ ህዝብና በመንግስት መካከል የነበረው አለመግባባት መልሶ የረመዳን ፃም ላይ ጥቅምት 22/23 1998 ላይ  "ዶክተሮቼን ፍቺ " በሚል ድጋሚ ሁከቱ አገረሸ። በተቃውሞው ረብሻ ላይ የአውቶብስ ተራ ልጆች አውቶቢስ፣ የጎማ ተራ ልጆች ጎማ፣ የቆሼ ሰፈር ልጆች ቆሻሻ እያቃጠሉ ተቃወሙ። ወጣት የተባለ ሁሉ መተላለፊያ መንገድ ዘግተው በመንግስት ታጣቂዎች ላይ የድንጋይ ናዳ ሲያዘንቡ ዋሉ በአፀፋው የመንግስት ታጣቂዎች ወጣቱ ላይ የጥይት ቃንቄ አዘነቡበት። አዲስ አበባ በየሰፈሩ የተለያየ አይነት ተቃውሞ በተለያየ መልኩ ቢገለፅም የበርበሬ በረንዳ አካባቢ (የከረዩ) ልጆች  በርበሬ በማቃጠል ሳይሆን በድንጋይ ውርወራ ከሁሉ ልቀው ታጣቂውን ሀይል እንደ ቆላ  በርበሬ አቃጠሉት። ይህን ተከትሎ የመንግስት ታጣቂዎችም ከየትኛውም ሰፈር በላቀ መልኩ በሰፈሩ ወጣት ላይ ሀይላቸውን አላቁ። ወጣቶቹም አለቁ። ዲሞክራሲያዊ መብቴ ነው ብሎ የጮኸው ህዝብ ደምበደም ሆኖ ተስፋ ቆርጦ ቤቱ ገባ። ሁከቱ ከበረደም ቡሃላ በቀንም በሌሊት ወጣቱ  በታጣቂዎች እየታፈሰ ወደ ዴዴሳ ይጫን ጀመር። የዛን ሰሞን የረመዳን ፆም ስለነበር ፆመኛ ነኝ ያለ ወጣት ወይም ሙስሊምነቱን በአለባበሱ የሚገልፅ ወጣት ወደ ዴዴሳ ያለመጫን እድሉ ትንሽ ሰፋ ይል ነበር።

ይህን የተረዳው የበርበሬ በረንዳ ወጣት ያለ ሀይማኖቱ ኢስላማዊ አለባበስ ጀለቢያ ለብሶ  ይንቀሳቀስ ጀመር። ከነሱም ውስጥ ከአስተማሪ አባቱና መሰረተ ትምርት ከተማሩ እናቱ ጋር የሚኖረው መሳይ የተባለው ወጣት ይገኝበታል…  ዋናው ትውስታዬ መሳይ ነው።

   መሳይ አንድ ቀን ጀለቢያውን እንደለበሰ በቁምሳጥኑ መስታወት እራሱን ሲመለከት ሌላ ሰው የተመለከተ እስኪመስለው ድረስ በአለባበሱ ደነገጠ። ያስደነገጠው ምን እንደሆነ ውስጠ ሚስጥሩን ባያውቀውም ጀለቢያው የተለየ ግርማ እንዳላበሰው ታዝቦ ተደነቀ። ሙስሊም ለመምሰል በመሞከሩ እንዲህ ሞገስ  ያላበሰው ሙስሊም መሆን ሲጨመርበት ደግሞ ምን ያህል እንደሚሆን ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም። በጀለቢያው ምክኒያት መሳይ ስለ እስልምና ለማወቅ ፍላጎት አደረበት። በየአጋጣሚው ስለ እምነቱ መጠየቅና ማወቅ ጀመረ። ፍላጎቱም ወደር ስላልነበረው የሀይማኖት ንፅፅር መፅሀፍትን ገዝቶ ያነብ ጀመር… ቀድሞ በነበረበት እምነት ያጣቸውን ብዙ መልሶች ከኢስላም ማግኘቱ ወደ ኢስላም ልቡ ተማረከ። በጀለቢያ ሰበብ ኢስላምን ለመቀበል አላህ መንገዱን አገራለት። ቤተሰቦቹ ሳያውቁ በአቅራቢያው ከሚገኘው መስጊድ ኢስላምን ተቀበለ። አብደላህ ተባለ። ቤተሰቡ የልጃቸው በባህሪይ መለወጥ ስርዓት መያዝ ሳያስገርማቸው አልቀረም። የድሮ አስቸጋሪነቱ ጠፍቶ ፍፁም መልካም ስነምግባር መላበሱ ቢያስደስታቸውም ቅሉ የለውጡን መንስኤ አለማወቃቸው እንቆቅልሽ ሆነባቸው። መሳይም ጊዜው ሲደርስ ያውቁታል በማለት በዝምታው ፀና። መሳይ በኢስላም ከመማረኩ የተነሳ የግዴታ አምልኮ ብቻ ሳይሆን የውዴታ አምልኮዎችን ይተገብር ጀመር። ከነዚህም ውስጥ በውድቅት ሌሊት መስገድ (ሰላተለይል)፣ ሰኞና ሀሙስ መፆም ነበር።    አንድ ቀን በሌሊት ተነስቶ ውዱዕ ሲያደርግና ክፍሉ ገብቶ ሲሰግድ እናቱ በመስኮት ተመለከቱት። በማግስቱ ቤተሰብ የመሳይን ሙስሊም መሆን አወቀ። አበዱ ተንጨረጨሩ ሰደቡት ወቀሱት… ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ! … ሽማግሌ ቢላክ ግዴለም ተመለስ ቢባል አልሆነም። ቀጥሎ እናቱ የተጠናወተው ክፉ መንፈስ ይሆናል ብለው ፀበል አመጡለት ሳያውቅ አጠጡት የቀረውን ከደጅ አስቀመጡት መስሚያው በኢስላም ብቻ የተማረከው መሳይ ይባስ ብሎ በፀበሉ ሳያውቅ ውዱዕ ሲያደርግበት አዩት። ይሄኔ እናትም ፀበል ያልበገረው እኔ በምን አቅሜ ብለው ሳይወዱ በግድ መሳይ መስለሙን ተቀበሉ። ሁኔታው በማስገደድ እንደማይሆን የተገነዘቡ አባቱም ቁጭ አድርገው ያነጋግሩት ጀመር። መሳይም የሚጠይቁትን ጥያቄ እየመለሰ እየጠየቀ…ብዙ ተነጋገሩ አባት በውይይታቸው ልጃቸው ልክ መሆኑን ቢያውቁም እሳቸው እውነታውን ለመቀበል ልማድና ፍላጎታቸው እንደ ግድግዳ ሆኖ ጋረደባቸው። አላህ የሻውን ይመራል። የመሳይ ሙስሊም መሆን ያለምንም አታካሮና ተግደርዳሮት በውይይት ፀደቀ። (የተማረ ይግደለኝ)። መሳይ ከቤተሰቡ ቢስማማም በአካባቢው አብሮ አደግ ጓደኞቹ መገለል ደረሰበት። ሙስሊም ጓደኞቹ ብቻ ያቀርቡት ጀመር። ያገለሉትም ቀን አልፎ ቀን ሲተካ በመልካም ስነምግባር ማርኮ እንደቀድሞው ሆኑለት። አሁን መሳይ ነፃነቱን አገኘ። ነፃነቱ ይበልጥ ወደ እምነቱ ለመዝለቅ በሩን አሰፋለት። መሳይ በኢስላም ባህር በፍቅር ሰመጠ። ለአላህ በመተናነስ ሰገደ። ነቢዩን(ሰዐወ) ከልቡ አፈቀረ። የሚገርመው 500 ጊዜ ሰለዋት ሳያወርድና ዚክር ሳያደርግ አይተኛም። ረሱልን (ሰዐወ) ከማፍቀሩ የተነሳ መሀመድ ለተባለ ማንኛውም ሰው ወንበር ይለቃል። አሉ የተባሉ የኢስላም ምሁራን ዘንድ ተመላለሰ።   መሳይን መጀመሪያ በዝና አወኩት። ጓደኛዬ ጓደኛው ነበር። ስለሱ የፃፍኩትን መረጃ አስተዋዋቂ ጓደኛዬ የነገረኝ ነው። ጓደኛዬን መሳይን እንዲያስተዋውቀኝ ጠየኩት። ስራ ቦታዬ ይዞት መጣ ተዋወኩት። መሉ ጀለቢያ ለብሷል። መላ አካሉ አንዳች ብርሃን ፈሶበት በሙሉ አይንህ ልታየው…ያሳፍርሃል። አይህን ትሰብራለህ። ሲተዋወቅህ ደስ በሚል ለዛና ፈገግታ ነው። ወንበር ሰጥቻቸው ተቀመጡ። ንግግሩ ሁሉ ጣፋጭ ነው። በድንገት መሀመድ የሚባል ሰው መጥቶ ተቀላቀለን።  መሳይ ቀድሞ  "አሰላሙ አለይኩም" ብሎ ስሙን ነገረው።  መሀመድም "ዋአለይኩም ሰላም" መሀመድ እባላለው አለ።  "ሰዐወ" በማለት መቀመጫውን ለቆ እንዲቀመጥ ጋበዘው። አስከትሎም ከአስደናቂ ፈፈግታ… ጋር "መሀመድ ቆሞ እኔ ልቀመጥ" አለ። ስለሱ የሰማሁት እውነት መሆኑን አረጋገጥኩ። ሌላው ስለሱ ያስገረመኝ ተከታዩ ሁኔታ ነበር።     አንድ ቀን መሳይ ጓደኛዬን ይዞ ሀጂ መሀመድ ራፊዕን ሊዘይራቸው ቤታቸው ሄደ።(ሀጂ መሀመድ በእስልምና እውቀት አንቱ የተባሉ ዛሬ በህይወት የሌሉ ድንቅ አሊም ነበሩ) የሀጂ መሀመድ ራፊዕ ባለ አንድ ክፍል የቀበሌ ቤታቸው በኪታቦች ተሞልቶ ቤተ መፅሀፍት እንጂ መኖሬያ ቤት አይመስልም። ሚስትም ልጅም የላቸውም። በጊዜው ሸኹ ታመው አልጋ ላይ ከከተሙ ውሎ አድሯል። መሳይ ሀጂን ከሚንከባከቡ ወጣቶች አንዱ ነበር። መሳይ… ግንባራቸውን ስሞ ጓደኛውን አስተዋውቆ ሀጂን እግራቸውን በአበት ሶዳ እያሸላቸው ዱዓ እያደረጉለት…ሳለ  በመሀል መሳይ አንድ ሰው በህልሙ ማየቱን ነገራቸው። ሀጂም አንተ ልጅ አላህ ይወድሃል በህልምህ ያየኸው ረሱልን(ሰዐወ) ነው" አሉት። ይህንንም የነገረኝ አብሮት ሀጂ ቤት የሄደው ጓደኛዬ ነበር። የመሳይን ነገር ብፅፈው ሙሉ መፅሀፍ አይገድበኝም እዚህ  ጋር ላቁም። መሳይ በረብሻው ላለመታፈስ ባደረገው ጀለቢያ ሰበብ ኢስላምን ተቀብሎ ነቢዩን (ሰዐወ) በህልሙ ለማየት የበቃ ለሀቅ ታላቅ ክብር ያለው ለወጣቱ ሞዴል የሚሆን ወጣት ነው። አላህ ይጨምርለት።  ይህን ድንቅ ወጣት ማሻ አላህ አትሉትምን?

No comments:

Post a Comment