Monday, May 2, 2016

ዘመነ ገንዘብ

ዘመነ ገንዘብ!

ቀስ በቀስ የጦር መሳሪያ ከግለሰቦች እጅ እየወጣ በመንግስት እጅ መጠራቀም ጀመረ። ጦርነት እየቀነሰ ሰላም እየነገሰ መጣ። ከጦር ሰፈሮች ይልቅ ባንኮች መበራከት ጀመሩ።ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፍልስፍና ተወለደ። ብር በቁም ነገር ተወሰደ።ግብር ማብላት ቀርቶ ሆቴል መክፈት ተለመደ። እንጀራ የሚሰጥ መሆኑ ቀርቶ የሚሸጥ ሆነ።እነ እቴጌ ጣይቱ የግብር ድንኳናቸውን አፍርሰው ሆቴል ከፈቱ። ከለውጡ ጋር መራመድ ያቃተው ሁላ አሮጌ በገናውን ድር ከለበሰ ግድግዳ አውርዶ

<<እቴጌ ጣይቱ እጅግ ተዋረደች፣
ሁቴሏን አቁማ እንጀራ ነገደች>> እያለ አዘነ።

እየሰነበተ ቁርጡን ሲያውቅ ግን "እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም " ተብሎ ተዘፈነ። ገንዘብ ያለው ሰው ጠብመንጃ ሳይሆን ባለ ጠብመንጃ መግዛት ቻለ። "ወይ ጉዴ ላግባሽ አለኝ ነጋዴ" የሚለው ቀርቶ "መልበስ አረንጓዴ ማግባት ነው ነጋዴ" ተብሎ ተቀነቀተ። በዘመነ መውዜር የሰርግ ዘፈን በግዳይ ላይ ያጠነጠነ ነበር። በዘመነ ብር "አረ ሚዜው ደሃ ነው ሽቶው ውሃነው" ተብሎ ተዜመ። ወላጅ ልጁን በኢኮኖሚ ዙሪያ የሚያጠነጥን ስም ሰየመ። እነ ሽፈራው ቀርቶ እነ ብሩ እነ ሚሊዮን መጡ። ካርል ማርክስ የተባለው ሊቅ "(በቡርቭዋ ስርዓት ውስጥ) ገንዘብ የመልካም ነገር ሁሉ ቁንጮ ነው። ስለዚህ ባለ ገንዘቡ መልካም ሆኖ ይታያል"  ብሎ ፅፏል።

ማርክስ ከነመፈጠሩ የማያውቁ አባቶቻችን "ያለው ማማሩ ከነ ነውሩ" በማለት የገንዘብን ተዓምር አሳምረው ገልጠውታል። ሀብታም ሰው ወራዳ ህይወት ቢኖርም የገንዘብ አቅም ባይናችን ፊት ክቡር ሆኖ እንዲቆም ያደርገዋል። እናም "የገንዘብ ደግነቱ ታስሮ ማስፈታቱ" ተብሏል። ገንዘብ ነውረኛውን ክቡር፣ እስረኛውን ነፃ የማድረግ አቅም እንዳለው ተደርሶበታል።

ዛሬ ገንዘብ ሰዎችን የማያደርጋቸው ነገር የለም። ሰዎች ለገንዘብ ሲሉ የማይሆኑት ነገር የለም። የይሉኝንታን የስነ ምግባርን አጥር የገንዘብን ፈተና የመገደብ አቅም የለቸውም። ጥንት ወተትና ቅቤ በስጦታ በችሮታ እንጂ በሽያጭ የሚቀርቡ ነገሮች አልነበሩም። ዛሬ ሰዎች ለገንዘብ ብለው የገማ ሙዝ ቅቤ ነው ብለው ይሸጣሉ። መንገደኛ ተቀብሎ በብላሽ ማሳደር የተለመደ ነበር። ዛሬ ሰዎች መንገደኛን ገድለው ኩላሊቱን የሚሸጡበት ዘመን ላይ ደርሰናል። የተፈጥሮ ውበታቸውን ሸጠው ሰው ሰራሽ መዋብያ ይገዛሉ፣ ድንግልናቸውን ይሸጣሉ፣ ወላቆች ጥርስ ይገዛሉ፣ ተካዞች ሳቅ ይከራያሉ፣ መላጦች ፀጉር ይሸምታሉ፣ ጃንደረቦች ሙርጥ ይገዛሉ። ገንዘብይኑር እንጂ አሮጊቶች ጨምዳዳ ቆዳቸውን አስገፍፈው የኮረዳ ልስልስ ገላ ይለብሳሉ።ሰዎች እንቅልፋቸውን ጨቁነው ባፈሩት ገንዘብ የእንቅልፍ ክኒን ይሸምታሉ። ከየትኛውም ስኬት ጀርባ ከየትኛውም ውድቀት ጀርባ ከየትኛውም ቀውስ ጀርባ ከየትኛውም ሰላም ጀርባ ኤልሻዳይ ገንዘብ ቆሟል።

ያም ሆኖ፣ አቤቱ የእለት መቶ ብራችንን አትንፈገን!

ምንጭ:- ከአሜን ባሻገር ከበዕውቀቱ ስዩም

No comments:

Post a Comment