Saturday, April 30, 2016

ጃ ያስተሰሪያል!

  ጃ ያስተሰሪያል… ጃ ያስተሰሪያል… የሚለውን የቴዲ ዜማ የወጣው  በጉርምስናዬ መጀመሪያ አካባቢ ነበር። ዜማው በፖለቲካ ውጥረቱ ሰሞን ብርቅ ሆኖብኝ አስሬ እየደጋገምኩ እቤት በሶፋ ወንበር ላይ እንዳህያ እየተንከባለልኩ በስሜት አይኔን ጨፍኜ ተመስጬ አብሬ አዜማለው። ሲዲውን ያቅሙ ወሰን ድረስ በለቀጥኩት… ሙዚቃ እንኳን ለራሴ ለመንደሬ በቂ ነበር። ይህ ተደጋጋሚ ደርጊቴ ያበሳጨው ታላቅ ወንድሜ … በአካባቢው አለመኖሩ ጠቅሞኛል … (ወንድሜ ሲቆጣ በቀልድ እያዋዛ ሲሆን በሚቆጣበት ጊዜ የሚያሳየው ድምፅና እንቅስቀሴ አለመሳቅ ያልፈለገን ሁሉ በግድ ያስቃል) ካሁን አሁን መጣብኝ እያልኩ ዘፈኑን አብሬ አዜማለው ከዜማው ከያንዳንንዱ ስንኝ ጋር የራሴን ስዕላዊ ምናብ አየፈጠርኩ በስሜት ማድመጤ ቀጥያለው… ስፒከሩ ይጮሃል…እኔም ከስፒከሩ በላይ ድምፄን ለማጉላት ፎቴው ላይ እየተንደባለልኩ እዘፍናለው አይገልፀውም… እሰነጠቃለው…!

ግርማዊነታቸው ከዚህ ሰረገላ
ወደ ዋገን ወርደው ሲተኩ በሌላ
በዛውንቶች ራስ ስድሳ ጉድጓድ ምሳ
አብዮት ሞላችው የተማሪ ሬሳ

ዘንድሮ ፈርቻለው በተማሪ ሬሳ ታሪክ ተረኛው እኛ እንዳንሆን ብቻ። ሰግቻለው!! ቢሆንም ዜማውን አብሬ አዜማለው… ግጥሙን ከምኔው በቃሌ እንደያዝኩት ለራሴም ገርሞኛል። ምናል እንደዚህ ትምህርት ቢያዝልኝ? ሰባተኛ ክፍል ፈተናው በዜማ ቢሆን ኖሮ እንኳን ሶስቴ ልወድቅ ከሴክሽን አንደኛ ነበር ምነቀንቀው። ለምን የትምህርቱ አሰጣጥ በዘፈን መልክ አይኮንልንምግን? ኪኪኪ አስበው እስኪ ቲቸር ታመነ ፊዚክስ እየዘፈነ ቢያስተምረን? በራሴ ሃሳብ በጣም ሳኩ። የስምንተኛ ክፍል ፊዚክስ አስተማሪዬ ታመነ ምን አይነቱ ባለ ውቃቤ ወይ ደብተራ መተቱን እንደደገመበት አይገባኝም። ያለ ስራ መቀመጥ የማይችል ፍጡር ቢኖር ቲቸር ታመነ ነው። ሌላው ቲቸር ታመነን በተሰተካከለ አለባበስ ማየት ዘበት ነው። ወይ ኮሌታው ተዛንፏል ወይ የጫማ ክሩ ተፈቶ እያንዘላዘለ ወይ ያለካልሲ ጫማ ተጫምቶ ማየት የተለመደ ነው። እረፍት ቡሃላ የሚያስተምረው ክላስ ካለው የደውሉ ማብሪያ መጥፊያ ካለበት ስፍራ ዳስተሩን ቾኩንም ማስተማሪያ መፅሀፉንም አቅፎ አስሬ ሰአቱን እያየ ለመደወልና ለማስተማር የሚቁነጠነጥ አስተማሪ ነበር።ይህ ድርጊቱ እንኳን ለኛ ለተማሪዎች ለሌሎች አስተማሪዎችም ሳቅ የሚያጭር ባህሪው ነበር። ከዚህ ባህሪው ጋር እየዘፈነ ሲያስተምረን በአይነ ህሊናዬ ሳየው ነበር ሳቄን መቋቋም ያቃተኝ። ትኩረቴን… ወደ ዜማው ተመለስኩ…

ጃ ያስተሰሪያል… ጃያስተሰሪያል…

<<አንተ እብድ አረ ቀንሰው>> አለችኝ ፈቲያ የወንድሜ ባለበቤት።

<<ፈቱ የመጨረሻ ነው ይኼ ብቻ ይለቅ>> አልኳት በልምምጥ።

<<ምን አገባኝ! አሁን ከድር መምጫው ደርሷል!!>> ብላኝ ሄደች።

ቴዲ ያቀነቅናል እኔም አብሬው…

ይሄም በጥላቻ ይሄንን ሲወቅሰው
መለየት አቃተን የሚበጀንን ሰው።

ቴዲ አሁን በማ ሞት የሚመርጠውን መለየት አቅቶት ነው? ማንን ለመሸወድ ነው? የአልበሙን ፖስቸር ላይ የተነሳው ፎቶ አቋቋሙ (ሁለት እጆቹን ቀበቶ ማሰሪያው ላይ አሳርፎ ጭንቅላቱን ወደ ቀኝ ዘመም አድርጎ)  "ቅ" ፊደል  ሲሰራ ቅንጅትን የሚመርጥ መስሎኝ ነበር? ለካ ማንን እንደሚመርጥ ተወዛግቧል? እኔ ግን መለየት አላቃተኝም…ምመርጠውን  ለይቻለው…የምርጫ ካርድ ልወስድ ቀበሌ ስሄድ 18 አመት አይሞላህም አለኝ የመዝገብ ሹሙ…

<<የቁመቴ ማጠር አይተህ ነው? ቁመቴ የእርግማን ብዛት እንጂ የእድሜ አለመድረስ አይደለም>> ብዬ…አሳስቄ በስንት መከራ ነው ካርድ ያወጣሁት… መቼም ለካርዱ ይሄ ሁሉ ግብ ግብ የፈጠርኩት ያለውን አገዛዝ ለመምረጥ እንደሆነ ለናንተ መንገር አያሻኝም! ህእ!።

አቤት ስቃይ አቤት ጠኔ!
ሰማይ ጨክኖ በወገኔ።
ስንት አሳለፈንን…

ቴዲ ጠኔ ሲል በዛው ሰሞን ከጎረቤት ልጆች ጋር በአበላል አንተ ትበልጥ አንተ ትበልጥ እያልን የተከራከርነው ታወሰኝ።እኛ ቤት ቁጭ ብለን ስንከራከር ወንድሜ ከድር መደብ ላይ ቁጭ ብሎ እየቃመ ነፃት ጋዜጣን ያነባል።

<<አንተ ደረቅ በአበላል ከናንተ አልለይም ትላለህ? እንደውም አንድ ምክር ልስጥህ ሆድህ ውስጥ ፌስታል ይዞ የቆመ ደረሳ ሳይኖር አይቀርም  ሄደህ ሆድህን ተመርመር>> አለ አዚዝ ከደማቅ ሳቁ ጋር

<<ልክ ነው ተመርመር መቼ ለት ጉዱን ለማየት ሶስት ክትፎ ሰባህ ቤት አዝዤ አውድሞታል እኮ!!>>

<<የሰባህ ቤት ክትፎ ብዙ ኘሆኑ ነው?ቆርኪ በሚያክል ጣባ የሚያቀረቡትን ክትፎ ብዙ ነው ትላለህ? ብየ የመልስ ምቴን ቀጠልኩ… ስማ አንዋር !አዚዝ ከናንተ ጋር መከራከር የደንቆሮ ለቅሶ ነው ካላመናቹ ይኸው ከድርን ጠይቁት! ከናንተ የተለየ አበላል እንደሌለኝ ይንገራችሁ >>አልኳቸው።

<ህእ! ደረቅ በሚል ገፅታ አየኝ>> ወንድሜ ከድር።

<<አረ ከድር ስማው! አፒታይቴ ዝግ ነው ቆለፈኝ ይላል ወንድምህ!ባለፈው >> አለ አንዋር።

<<አረ በአላህ ከድር! ሀቁን አንተ አሳምንልኝ። ለሀቅ እኔ እበላለው? >> ስለው።በብርሃን ፍጥነት ከመደብ ላይ ዘሎ አጠገቤ ደረሰና። ሁለት እጆቹን እንደ ጉርሻ ወደ አፌ አስጠግቶ።

<<ከዚህ በላይ እኔን ልትላኝ ነው?  ና! ብላኛ ና!>>ሲለኝ።የተሳቀው ሳቅ መቼም አይጠፋኝም።

ከቴዲ ጋር አብሬ ማዜሜ ቀጥሏል።  (ይህቺ ፓርት ስሜቴን ስለምትኮረኩረው ድምፄን ጨምሬ በጩኸት አዜምኩ)

አልቅሰን ሳናባራ ብለይን ወይኔ!!
እዚህ ጋር ደግሞ ሌላ ትኩሳት…

ብዬ ሶፋው ላይ እየተንከባለልኩ በስሜት ባለኝ ድምፅ ሁሉ… ስቃጠል ወንድሜ … ገና ግቢ ሲገባ በስፒከሩ ድምፅ ተናዶ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ከች።

…ወገኔ አለቀ በወሲብ እሳት…
እሳት… እሳት…

በሩ በወንድሜ ተበረገደ…

<<አረ ባክህ አላህ እሳት ይልቀቅብህ አንተ ሰውዬ እሳት አትሁንብኝ!!>> ብሎ በምሬት ጮኸብ። ንዴቱ መልሱ በጣም አስቆኝ እየተንደፋደፍኩ ተነስቼ ሲዲውን እንዴት እንዳጠፋሁት አላውቅም። ፀጥ… ረጭ…!!

No comments:

Post a Comment