Tuesday, April 5, 2016

ጋሼ

☞ በእሳት አደጋ ምክኒያት ሱቁ የወደመበት የቤተሰብ ሀላፊ ግለሰብ ነው። የቤተሰቡንም የራሱን ህይወት ወደ ቀድሞ ይዞታው እንዲመለስ ካለው ፅኑ ፍላጎት በመነሳት ከደረሰበትን አደጋ ይታደጉት… መልሰው ያቋቁሙት ዘንድ የሚማፀናቸው ሀብታም የተባሉ ሰዎች 20 እና 30ብር በዛ ካለ 50 ብር ይሰጡታል። ሰውየውም የተሰጠውን በደስታ አያመሰገነ አሁንም ይዞራል…  እነዚህ ብሮች በዛ ደግ ዘመን ትልቅ ብር ነበሩ። የቤተብህን የወር ወጪ የምትሸፍንበት… ሀይል ነበራቸው። …  ይህ ሰው በዚህ መልኩ የእርዳታ እጆች እንዲዘረጉለት ሲኳትን እግሩ የቸርነት አባት ተብሎ ከሚታወቀው ዘመዱ ዘንድ አደረሰው። ቦታው ሲኒማ ራስ ጃቢር ጫት ቤት ነበር… ሰውየው የደረሰበትን አደጋ ለቸር ዘመዱ ጋሼ… ተናግሮ ሳይጨርስ … ነበር … ጋሼ መዳፉ ላይ የታሰረ 10,000 ብር ያስጨበጠው። አላመነም…  ለኔ ነው ብሎ አልጠረጠረም… የሚቀለድበትም… መሰለው… አይኑን አንከራተተ …

"ጋሼ ምን ላድርገው?  ለኔ ነው? ጋሼ… ተንተባተበ… ተርበተበተ… ይህ ብር ከወደመበት ንብረት ሁሉ ይልቃል። የጠፋውን መመለስ ብቻ ሳይሆን አሻሽሎ ማቋቋም የሚያስችለው ነበር።

"አዎ ላንተ ነው ይዘህ ሂድ" አለው ጋሼ።

ሰውየው ላንተ ነው የሚለውን ቃል ሲሰማ በድንጋጤ ይሁን በደስታ እግሩ ተብረከረከ … ከግንብ ጋር ተጋጨ … ተንገዳግዶ በድጋፍ ቆመ … ምስጋናውን በአንደበቱ መግለፅ ተቸገረ …ቃላት አጠሩት… ስሜቱ ተደበላለቀ…ምስጋናውን በከዳው አፉ መግለፅ  ቢቸግረው አይኖቹ የእንባ እንክብሎች አርከፈከፉ … በስፍራው የነበሩ ሁሉ ስሜታቸው ተነካ … የጋሼ ቸርነትና… የችግረኛው ሰው ደስታውን የገለፀበት ሁኔታ… (በጋሼ… ድርጊት አላህ እንኳን እንዴት እንደሚደሰትበት ልብ በሉ)…  ጋሼ…

   ስለ ቸርነት ሲወራ ሁሌም በአይነ ህሊናዬ የሚመጣ ሰው ቢኖር ቡና ነጋዴ የነበረው እውነተኛው ሀብታም  ጋሼ … ነው። የጋሼ ቸርነት ከላይ ለምሳሌ ባየነው እውነታ መልኩ… ለተቸሪው ሰው ቆሌ የሚያስገፍፍ ቸርነት ነበር። ባደኩበትና በምኖርበት አካባቢ ከትንሽ እስከ ትልቅ ከደሃ እስከ ሀብታም ከሙስሊም እስከ ክርስቲያን… ብቻ በአጠቃላይ የጋሼ… የቸር እጅ አልደረሰኝም የሚል ካለ እጅግ በጣም ውሸታም እለዋለው። ጋሼ የስንቱን ቤተሰብ በአል እንደሚያደምቅ። ለስንቱን ችግር እንደደረሰ ለስንቱ ቤተሰብ ገበና ሽፋን እንደነበር ቤቱ ይቁጠረው። ጋሼ… የቸገረውን ሰው አይቶ መለየት የሚችልበት ልዩ ተሰጥኦ አላህ ችሮት ነበር። ጋሼ እውነተኛ ሀብታም ነው። ጋሼ … ችግርህን አውጥተህ መግለፅ አፍረህ ስትጨነቅ ስትጠበብ … ጋሼ ካየህ…ሳትነግረው አውቆልሀል…  በቃ …  ደርሶልሃል። ይህ ነበር ጋሼ!!

   ጋሼ ለስንቱ ጭንቅ ላንቆራጠጠው ሰው እንደ ደረሰ… ስለሱ ቸርነት በተነሳበት ሁሉ የምሰማው ሀቅ ነው። እንደዛውም አላህ ለሱ ዱኒያን በእግሩ ስር እንድትገዛ ገርቶለት ነበር። ጋሼ ባደኩበት ጊቢ ውስጥ ከብዙ መጋዘኖች ውስጥ አንድ መጋዘን ስለነበረው በግቢያችን ብሎም በአካባቢያችን ነዋሪዎች…ሁሉ  የታወቀ ነው። …ጋሼ ሁሌም በክፉም በደጉም ከህብረተሰቡ ጎን አለ። በአካባቢው  የውሃ ፍሳሽ ትቦ ይግባ… ሽንት ቤት ይቆፈር … መሬቱ በሲሚንቶ ይለሰን… ከተባለ… ግንባር ቀደሙ ተሳታፊ ጋሼ ነበር… ጋሼ የሽንት ቤት ችግር ኖሮበት አይደለም… (ባለ 1 ፎቅ መኖሪያ ቤት እጅግ ብርቅ በነበረበት በዛ ዘመን… ዛሬም ድረስ ዲዛይኑ የሚያስደምም ባለ 3 ፍቅ ቤት ነው የነበረው … ከአብነት ወደ አዲስ ከተማ ወደላይ ስትወጣ አሁን አትላስ ከፍተኛ ክሊኒክ የተከራየውን ፎቅ ቤት አወከው እሱ ነበር መኖሪያ ቤቱ)… ከኛ የተወላከፈ መንደር ለሽንት ቤት ግንባታ በሰፊ ድርሻ ይሳተፍ የነበረው…  ከነበረው ቅንነት… ቸርነት በመነሳት እንጂ… ለራሱ ሲል አልነበረም… ምንም በማይጠቀምበት… አይመለከተውም በምትለው ልማት ሁሉ ከፍተኛው ወጪ በጋሼ ይሸፈናል።

በሌላ በኩል ጋሼ… የአይን አባቴ ነበር። "እንኳን ለራሴ ለሰው ይዘፍናል አንገቴ" እንዲሉ ነገር ነበር … ጋሼ ለኔ። እንኳን ሲገረዝ አይኑን ለያዘው ልጅ የአይን አባት ሆኖ ይቅርና የአይን አባት ላልሆነውም … ጋሼ ቸርነቱ ገደብ የለውም። ጋሼ ለኔ በልጅነቴ እንደ ሀብታም ልጅ ያደረገልኝን ውለታ ቆጥሬም መልሼም አልዘልቀውም።… 1 መቶ ብር የአንድ ጥሩ ደሞዝተኛ ደሞዝ በነበረበት ወቅት ለኢድና ለአረፋ በዓላት ለአልባሳት ብቻ 500 ብር ይለቅብኝ ነበር። ለኔ ብቻ ነው ያልኩህ። እንደኔ የሚያደርግላቸው ልጆችም በርካታ ነበሩ። በየ አጋጣሚው  ባገኘኝ ቁጥር የሚያደርግልኝንና የት/ቤት የሚከፍልልኝ እንዳለ ሆኖ። ሌላው ልጅ እያለው ትዝ የሚለኝ … በግቢያችን ባሉ መጋዘኖች ውስጥ በላብ አደርነት የሚሰሩ ልጆች ስራ ከፈቱ… ድብርት ተጫጭኗቸው ካየ… በግ… ተገዝቶ… አሳርዶ …ስጋው… ተከትፎ… ተጠብሶ… ለላብ አደሮቹ የሚጋብዝበት አጋጣሚዎች…  ለቁጥር ይታክቱኛል።

  ደግሞ ረመዳን ሲደርስ… ዘይት በበርሜል … ዱቄት በኩንታል…ገዝቶ… ለያንዳንዱ ቤተሰብ እንደፍጆታው ይሰጣል። እየነገርኩህ ያለሁት በግልፅ ሲሰጥ በእኔ ትንሿ እድሜዬ ያየሁትን ብቻ ነው። ዛሬ ላይ ቆመህ ታዲያ ይሄ ምን ያስገርማል? ትል ይሆናል… ልብ ማለት ያለብህ… በዛ ዘመን… ሰው ስለ እምነት ያለው እውቀት ውስን በሆነበት… መቶ ብር ብርቅ በነበረበት… ቸገረኝ ላለ ሰው 10,000 ብር ድረስ ሰጥቶ… በደስታ የሚያስነባ… ቸር ሰው… በማያገባው በማይመለከተውና በማይጠቀምበት ነገር   ሁሉ… ለሰዎች ምቾት መዋለ ንዋዩን ያለስስት የሚያፈስ… የያንዳንዱን ጎረቤት የችግር ቀዳዳ… እያንኳኳ የሚደፍን ሰው እንደልብ ማግኘት ዘበት እንደነበር ነው። ይህ የጋሼ ቸርነት ትውስታዬ 1% ነው። ያላየሁት ያልደረስኩበትን ያልሰማሁት 99% ቸርነቱን… የደረሰላቸው ያደረገላቸው ልቦና ውስጥ ተቀብሮ የሚኖር ነው።

እውነተኛ ሀብታም ማለት ብዙ ብሮች ብቻ ያሉት ሰው ሳይሆን ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችሉ ነገሮች ያለው ሰው ነው… ፍቅር፣ ክብር ወዘተ… ጋሼ እውነተኛ ሀብታም ነው የምልህ ለዚህ ነው የጋሼ ሀብት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን በቀናነቱ… የሰው ፍቅር… የሰው አክብሮት… የሚቸረው እውነተኛ ሀብታም ነበር።

  ዛሬ ጋሼ ሸሂቾ ሽፋ በህይወት የለም። አላህ የሰራውን ቸርነት በከይር ይመዝግብለት። በርካታ ቤተሰቦች እንዳስደሰተ ከነ መላ ቤተሰቡ በጀነተል ፊርደውስ በእዝነቱ አስገብቶ ያስደስትው …

No comments:

Post a Comment