Saturday, April 9, 2016

ሰባተኛ ክፍልና ምርቃና የሰሩኝ ጉድ

   ማጥናትና ፣ ልብስ ማጠብ በህይወቴ የምጠላቸው ተግባሮች ነበሩ። በተለይ ማጥናት የሚባልን ነገር። ለዚህም ነበር 7ተኛ ክፍል ላይ እንደ ዲኘሎማ መርሀ ግብር 3አመት የቆየሁት። 7ኛ ክፍል ሶስቴ መድገሜን የታዘቡ አንዳንድ የሰፈሬ ምላሰኛ ልጆች"ሰባት ሰባ ሰባት" እያሉ ይጠሩኝ ነበር። ሰባተኛ ሰፈር የአልጋ ላይ ስራ የሚሰሩ ሴቶች በሰባተኛ የህይወት ቆይታቸው መራር እንደሚሆንባቸው ሁሉ እኔም ሰባተኛ ክፍል መራር አጋጣሚ ሆኖብኝ አልፏል። በዚህ የመጣ 7 ቁጥር ብቻ ሳይሆን ከሱ ጋር የገጠሙ ቁጥሮች ሁሉ መጥፎ ገድነታቸው ገዝፎ ይታየኝ ነበር። ለምሳሌያህል :- የ77ቱ የወሎድርቅ ፣የ87ቱ የመስጊድ ረብሻ ፣ የ97ቱ የፌደራ,,,ጫማ ጥፊ ፣ የ7ኛ ሰፈር መጥፎ ገፅታ,,, ወዘተ ለ7 ቁጥር ያለኝን አመላካከት እውነት አስመስለው ካጋነኑብኝ ምክኒያቶች ነበሩ። እንደኔ እንደኔ የሰይጣን ቁጥር መሆን የነበረበት 666 ሳይሆን 777 ነበር ባይ ነኝ ። :):):)

  በትምህርቴ ደጋግሜ መውደቄ ያሳሰበው አብሮ አደግ ጓደኛዬ ከሱ ጋር በሚኖርበት ቆጥ አብረን እንዳጠና አግባባኝና አብረን ማጥናት ጀመርን። በዚህ ሁኔታ እያለን አንድ ቀን አንድ ሌላ ጓደኛውን አብሮን እንዲያጠና ይዞት መጣ። ጓደኛውን እንደታዘብኩት ከሆነ ከጥናቱ ልምድ ጎን ለጎን ጫት የመቃም ልምድ እንዳለው ታዘብኩ። እኔምከጎበዝ ተማሪ የሚገኝ ማስረጃ ጠቃሚ ነው ብዬ,,,ሲያጠና መቃሙ ምን እንደሚጠቅመው ስጠይቀው በጥናቱ እንደማይሰለቸውና አንዴ ያጠናውን እንደ ማይረሳውና ለዛሬ የትምህርት ውጤቱ የጫቱ ትብብር እንደታከለበት ነገረኝ። ገረመኝ! እኔም እየሰለቸኝ የመጣውን ጥናት ለማዝለቅ የልጁን በቂማ የማጥናት ልምድ ራሴ ላይ ተግባራዊ ለመድረግ አሰብኩ። ማሰብ ብቻ አይደለም መተግበር ጀመርኩ። ቆጧ ላይ ብቻዬን የማጠና ቀን ከደብተሮቼ ሩቡ ያህሉን በእጄ ሩብ ገለምሶ ጫት በጀርባዬ ይዤ የመግባት ልምድ አዳበርኩ። ከጥናቱ ይልቅ የምርቃናው ደስ የሚል ስሜት እየተመቸኝ መጣ። ቀን አልፎ ቀን ሲተካ የጥናቱ ፍቅር ሳይሆን የጫቱ ፍቅር አየለብኝ። አየቃምኩ ማጥናቴ በትምርቴ ሳይሆን በጫቱ ጎበዝ ቃሚ አድርጎኝ ቁጭ አለ። የቆጧ ላይ ቆይታዬ ተከታዩን ይመስል ነበር። ወደ ቆጧ እንደወጣው መጀመሪያ አንድ ሁለት እንጨት ጫት ቀንበጥ ቀንበጡን ቀንጥሼ በጉንጬ የዤ አመነዥጋለው የያዝኩትን ደብተር ማንበብ እጀምራለው ይህ ድርጊቴ ብዙም አይዘልቅም። ይሰለቸኛል። የጫቱ ምርቃና በደም ስሬ ተዛውሮ በመልስ ምቱ ሲያነቃቃኝ እዛው ቆጧ ላይ ያሉ የጓደኛዬን መፅሄቶች እንዳሉ ፊቴ ቆልዬ አንድ በአንድ እየገለፅኩ እያያዛቸዋለው። አዲስዘመን፣ ቃልኪዳን፣ሜዲካል፣ አዲስ አድማስ ገፆቹን እየገላለብኩ በሳበኝ ንባብ ሰምጣለው። በምርቃና የታጀበው የንባቤ ሂደት አንዱ መፅሄት ላይ ስለ ንፅህና አጠባበቅ ሳነብካልሲዬን የማጠብ ሀሳብ ይመጣብኛል!!ስለ አሳዛኝ ፍቅር ሳነብ እንባ ይመጣብኛል!!ስለ ሀገራችን ፖለቲካችን ሳነብ ቃር ይለቅብኛል!!
በእንደዚህ አይነት ከሀሳብ ሃሳብ የመዝለልና የመዋዠቅ ስሜት ውስጥ የተወሰኑ ደቂቃዎች ሳለውቀው ይሄዳሉ። (ፓ! አጥንቼ ሞቻለው)።★አይ ምርቃና! ሰባተኛ ክፍል ያሻግረኛል ለጥናት ያግዘኛል ያልኩት በቂማ ማጥናት የሚዲያ ዳሰሳ እንደሚያቀርብ ጋዜጠኛ ከመፅሄት መፅሄት ያዘልለኝ ጀመር።

አንድ ቀን እንደ ወትሮው ለማጥናት ደብተሬንም ጫቴንም ይዤ ቆጧ ላይ ተሰየምኩ ሽርብትን አልኩ። ቃል ኪዳን የሚለውን መፅሄት ከፍቼ አንድ አሳዛኝ የፍቅር ታሪክ እያነበብኩ ነበር። የምርቃናው የሙቀት ውጤት ፊቴ ላይ ችፍ ያለ ላብ ።የምርቃናው የሆድ አባቢ ስሜት ውጤት አይኖቼ ላይ ችፍ ያለ እንባ ሞጅሮብኛል። "ገለምሶ መጨረሻው ለቅሶ"እንዲሉ አበው lol (ብለዋል እንዴ?)። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ የቆጡ መሰላል ላይ የሚወጣ የኮቴ ድምፅ ሰማው ወዲያው እንባዬን ጠረኩ።

አንድ የሰፈራችን ከቸገረውም ከሰረቀውም ሰው እቃ ገዝቶ የሚሸጥ ቀልቃላ ቃፊር ነበር (እዚህ ምን ያመጣውል እስኪ?) ከቆጡ የወለል በር ጭንቅላቱን እንደ ፍልፈል ብቅ አድርጎ..."ኧሃ,,,ሶል!በርጫ ጀመርሽ እንዴ? አለኝ

"በጫት ዙሪያ ጥናት እያደረኩ ነው"

"አሪፍ ነው! እኔ ምልህ ጀለሱካሽ የለም እንዴ?"

የለም አሁን ወጣ!በሰላም ነው የፈለከው?

"አዎ! አሪፍ ጥቅም የሚያስገኝ እቃ አግኝቼ ነበር ብዛቱ 720 ፍሬ ይሆናል! ላናግረው ፈልጌ ነበር ? "

" ምንድነው እቃው?" አልኩት ብዛቱ ገርሞኝ።

"ፍየል!" አለኝና አስካካ,,,ሊላላጥ እንደመጣ ገባኝ !

"ፍየል ነገር ነህ! አንተ የሆንክ ነጃሳ ብሽቅ ፍልፈል ብዬ ልውርድበት አልኩና የመልስ ምቱ ጫት መቃሜን ይፋ ማውጣት ሊሆን ይችላል ብዬ ስለሰጋው ከአፌ መለስኩት።  ለነገሩ ይሄ ወራዳ እኔ በስድብ ሳልወርድበት ራሱ በመጣበት የቆጥ ጉድጓድ ወረደ። (አያናድም በናታችሁ?ብሽቅ!)ወደ መፅሄቶቹና ወደ ግረባ(ክለሳ) ገባው። ምርቃናው አሁንም ደስ የሚል ስሜት በመላ አካሌ ያንዠቀዝቃል። በዚች ሰዓት ወስጥ የማልችለው የሚያቅተኝ የስራ ዘርፍ አልነበረም። የማስበው ነገር ሁሉ ኩልል ያለና እንቅፋት አልባ ሆነልኝ። የቆጧ ላይ ምርቃና በዚህ የሃሳብ ሩጫ አዋለኝ። ሰማዩ አይን መያዝ ሲጀምር ከቆጧ ወረድኩ። በዚች ሰአት የሚያናደኝ ነገር ቢኖር ከሀሳቤ የሚያደናቅፈኝ ሰው ነው። ምርቃና አስደሳች ስሜቱ ብቻህን ሆነክ ተብሰልሰል ነገር ስለሆነ ማንም ሰው ደስታዬን እንዲነጥቀኝ አልሻም ወይም አልፈለኩም። ለጥንቃቄ ሰው እናዳያገኘኝ የሹራቤን እንደ አንቀልባ ያዘልኩትን ኮፍያ አናቴን ከደንኩት! ሱፐር ማርኬት ለመዝረፍ የተዘገጀ ኒገር ነበር የምመስለው።

★አይ ምርቃና! በክፉም በደጉም አብሮኝ ያሳለፈን ማህበረሰብ እንዳኮርፈው አስገደደኝ። የመረቀኑ ሰዎች ወደው አይደለም ለካ ወሬ የሚጠሉት። ስገባ የነበረው የሰፈሬ የጫጫታና የሰው፣የግርግር ድባብ እንደገረፉት ህፃን አደቡን ገዝቶ አኩርፎ አገኘሁት ይገርማል! ቅድም ስገባ የሰዉ እንደ ሰፈሬ ገራባ ለቃሚ ፍየሎች መቅበዝበዙ አሁን ሰክኗል። አዳሜ ጥግ ጥጉን ይዞ ቆሞ ራሱን አስቸኳይ ስብሰባጠርቶ በምርቃና መርከብ ተሳፍሮ በሃሳብ ማዕበል ይንገላታል።,,,ምፅ,,,! ምስኪን !! አረ!?ምን ሰዉ ብቻ ጀለሶቼ!! ፍየሎቹም ሳይቀር ይህን ቁጥር ስፍር የሌለው የገራባ (የጫት ጥራጊ) ቁልል አፍሰው አፍሰው አላፊ አግዳሚውን ልክ እንደ ሰው በአይናቸው ተቀብለው በአይናቸው ይሸኛሉ። ቅድም እንኳ,,, ይሄ ሳያድግ ያደገበት ወንድነቱን እንደ ቀይ እስክሪቢቶ ቀስሮ እናቱም መንትያ ወንድሙም ላይ ካልወጣሁባቹ እያለ አዛ ሲያደርጋቸው የነበረው ወጠጤ አሁን ጫቱ አኮላሸው መሰል መንጠላጠሉን ትቶ እሱም አድቦ መንገደኛውን በአይኑ ይታዘባል። እንደው ልብ ብዬ እነዚህን ፍየሎች በምርቃናቸው ሰዓት ሳስተውላቸው ከወንድ መንገደኛ ይልቅ ሰፋ ያለ ዳሌ ያላቸውን ሴት መንገደኞች ሲያልፉ አልመዝምዘው ያያሉ ! በቋንቋቸው "ፓ! አቦ ፍዴ!! አየኸው!" የሚባባሉ ይመስላሉ። ምስኪኖች!!

ከሰፈሬ ቅያስ ጫፍ ካለው ሁሴን ሻይ ቤት ሄድኩ። ሁሴን ሻይ ቤት ከግድግዳና ጣሪያ፣ከወንበርና ጠረጴዛ ፣ ከአስተናጋጅና ከቲኘ ፣ ነፃ የሆነ መቀመጫው ከበርጩማ ያጠረ ድንጋይ ጠረቤዛው መሬት፣ ምሰሶው ስልክ እንጨት የሆነ የሜዳ ላይ ሻይ ቤት ነው። የሻይ ቤቱሻይ አፍዪውም፣ ዌይተሩም ፣ ካሼሩም እራሱ ሁሴን ነው። አራት እግር ያለው ድስት የሚመስለው ሻይ የሚጣድበት ምድጃ በአራት መአዘን ከተጎለተቱት የተስተናጋጅ መቀመጫ ድንጋዮች መሀል የተቀመጠ ነው። በዛን ዘመን ሁሴን ለመቀመጫነት ይጠቀምባቸው የነበረው ድንጋዮች ዛሬ ላይ ጥቃቅንና አነስተኞችበጥቃቅኑ ፈላልጠው አንድ ቅያስ የሚሸፍን ኮብልስቶን ይሰሩበታል። ምስጋና የተፈጥሮ ሀብታችንን በሚገባ እንድንጠቀምበት ላደረጉን የልማቱ አጋሮች,,,ህእ,,,!። ሁሴን ሻይ የሚያፈላበት ማንቆርቆሪያ የባልዲ መጠን ሲኖረው ቀን ከሌት ከምድጃው ላይ አለመለየቱ ጥላሸት አጥቁሮት በማንቆሮቆሪያ ቅርፅ የተሰራ እንስራ አስመስሎታል። ሁሴንን ሻይ አስቀድቼው መጠጣት ጀመርኩ። ውስጤን ሻዩ አካሌን የምድጃው ወላፈን በመስከን ላይ የነበረውን ምርቃና ተባብረው መለሱልኝ። ሻዬን ጨርሼ ሂሳብ ከፍዬ ወክ ለማድረግ ከሰፈር ወጣው። እንደ ዔሊ በሲኒማ ራስ በመስጊድ በቢስ መብራት በጎጃም በረንዳ አውቶቢስ ተራ ሰባተኛ አብዶ በረንዳ በምዕራብ ሆቴል ወርጄ በጫተራ አካልዬ ሰፈር ገባው። (የታክሲ ታፔላ አይመስልም?) ረፍዶ ነበር። ብቻዬን ከማድርበት ኦና ቤት ብርድ ልብሴ ደረቱን ገልብጦ በተኛው ፍራሼ ላይ ተጠቅልሎ ተቀምጧል። በሌላ ክፍል ያለው ቤተሰብ ተኝቷል። ምርቃናው ካልሲ እንኳን ማጠብ የማልወደውን ልጅ ብርድ ልብሴን እንዳጥበው ገፋፋኝ። ምድረ ገፍላ!! ብዬ ብርድ ልብሴን ጠቅልዬ ላጥብ ወደ ግቢ ወጣው። ጓሮ ሄጄ ሳፋ አመጣሁና ወገቡ ድረስ ውሃ ሞልቼ ብርድ ልብሴን ዘፈዘፍኩት። ተመልሼ ቤት ገባሁና ጫማዬን አውልቄ ሱሪዬንም ሹራቤንም ወደላይ ሰብስቤ ወጣው። ውሃውን ጨልጦ የጠጣውን ብርድ ልብሱ ማጠብ ለመጀመር ብድግ ላደርገው ስል ከመጀመሪያው ክብደቱ 10 እጥፍ ገዝፎ ጠበቀኝ። እንዴ ይሄ ነገር እንዴት ነው? የዘፈዘፍኩት በውሃ ወይስ በኢጅብት አሚር?። በክብደቱን ብቻ ገና ሳላጥበው ደከመኝ። ይሄ ለማጠብ በማህበር ተደራጅቼ ከሆነ እንጂ በኔ ጉልበት ብቻ እንደ ማይታጠብ ተገለፀልኝ። ይህን ተከትሎም ለብሼ የማድረውም ሌላ ብርድ ልብስ በክፍሌ አለመኖሩም ትዝ አለኝ። ወይኔ ጉዴ!! በድንጋጤ ደርቄ ቀረው። ያለኝ አማራጭ ከዛ ክፍል ብርድ ልብስ መቀበል ነው። ቀስ ብዬ ወደበሩ ተጠጋሁና በቀጭኑ ቀዳዳ ታላቄ እንዳይሰማኝ በሹክሹክታ ድምፅ እህቴን ደጋግሜ ስሟን ተጣራው። "ምን ሆንክ!?" ወይኔ! የፈራሁት ደረሰ ታላቅ ወንድሜ ነበር።

"አይይ,,,ይ ብርድ ልብስ ፈልጌ ነው" አልኩ በፈራና ጫቱ በፈጠረብኝ የተኮኮላተፍ ድምፅ።

"ያንተስ?"በቁጣ ድምፀት።

"ነገ ላጥበው ብዬ ዘፈዘፍኩት"

መኮላተፌና ድርጊቴ ወንድሜ ቅሜ መመርቀኔን አወቀብኝ። ከውስጥ ካለ ሰው ጋር ማውራት ጀመረ!!

"ሰማሺው ይሄ ውሻ! መርቅኖ እኮ ነው!! ጫቱን ሲከተክት ውሎ አፉ ገመድ ሆኗል!"እያለ በብስጭት ለዘለቀ ደቂቃ የስድብ ናዳ አወረደብኝ። በድንጋጤ ቀኑን ሙሉ የለፋሁበት ምርቃና በኖ ጠፋ። ካሁን አሁን በሩን በርግዶ ብርድ የሚያስለቅቅ ካልቾ ይሰጠኛል በሚል ስጋት ተርበትብቻለው። ወንድሜ በሩን ከፍቶ ብርድ ልብሱን ከስድብ ጋር ፊቴ ላይ ወርውሮብኝ ገባ። ኡፍፍፍ,,,አልሃምዱሊላህ!

የዘፈዘፍኩትን ብርድ ልብስ እዛው ትቼ፣ የምለብሰውን ብርድ ልብስ አቅፌ ክፍሌ ገባው። ፍራሹ ብቻውን ተዘርግቶ ጠበቀኝ። ፍራሼ ጆሮ ያለው ይመስል…እንዲህ አልኩት "ምርቃናው አንተንም እንደ ብርድ ልብሱ ቢያዘፈዝፈኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር?"አልኩትና ምርቃና በሰራኝ ጉድ እየሳኩ ተጠቅልዬ ተኛው።

No comments:

Post a Comment