Saturday, April 9, 2016

"ደቡብ ምድረ ገነት"

" <<…በአዋሳ ከተማ በግራጫማው መንገዶቿ የወንድሜን ልጅ ይዤ ስሮጥ ስጫወት ሳይክል፣ስጋልብ መርካቶአዊ ባህሪዬ ከአዋሳ ልጆች ሲያደባድብ… ሲያስማማ… ሀይቅ… ስሄድ… አሞራ ገደል… አሳ ተጠብሶ… ስበላ…(ያሳለፍኩት ገጠመኝ እራሱ ሌላ ፅሁፍ ይወጣዋል፣ምናልባትም አንድ ቀን ከነሸጠኝ እቸከችከው ይሆናል)…>> ብዬ ነበር ይከው ነሽጦኝ ቸከቸኩት። ከሸገር በ278 ኪሜ በምትርቀውን ከተማ… አዋሳ እገኛለው… እስክደርስ ልቤ በጉጉት ሊፈነዳ የደረሰባቸው አዋሳንና የወንድሜን ልጅ አገኘዋቸው። አዋሳ አረብ ሰፈር የሚኖሩት የወንድሜ ሚስት ቤተሰቦች ከአያቴ ተደውሎ በተነገራቸው መሰረት… አ/አ ታክሲ በአይናቸው ከርቀት እንደሚጠብቁ ሰዎች በጉጉት ሲጠብቁኝ ደረስኩ። የወንድሜ ልጅ አብዱሬ የአራት ወይም የሶስት አመት ከምናምን ጨቅላ ቢሆንም እኔን ለመለየት ጊዜ አልወሰደበትም። ከሩቁ ሲያየኝ እየሮጠ መጥቶ እንደ ፋርማሲ ማስታወቂያ እባብ ተጠመጠመብኝ። ትንሹ አጎቴ መጣ በሚል በደስታ ፈነደቀ። እጄን እየጎተተ ከፊት ከፊቴ ድክ ድክ እያለ በጉጉት የሚጠብቁኝ የእናቱ ቤተሰቦች ጋር ወሰደኝ። እነሱም በወንድማዊ ፍቅር ተቀበሉኝ። ከሻይ ቤታቸው ጀርባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት ገባን። አብዱሬ እርጎና ዳቦ ከሻይ ቤቱ ይዞልኝ መጣ። አቀባበል አደረገልኝ። የናፈቀኝን የአዋሳ እርጎ አጣጣምኩት። እርጎው ሞቆህ ደክሞህ ስትጠጣው አንዳች ጣፋጭ አነቃቂ ስሜት ያላብስሃል። ጥያቄ ይጎርፍልኝ ጀመር። እንዴት ከአያቴ ጠፍቼባት እንደመጣው። በመልሴ ሲስቁ ወይ የመርካቶ እሳት! እያሉ ተደነቁ። አብዱሬ…አሁንም እጄን ይዞ እየመራ ወደ ጓሮአቸው ወሰደኝ። ጓሮው በተለያዩ እፅዋት በፓፓዬ በአቡካዶ በካዝሚር… ዛፎች ተሞልቶ ከአእዋፋት ዝማሬ አንዳች አረጋጊና አስደሳች ስሜት መንፈስን ይመግባል። መርካቶ ውስጥ ፍራፍሬ ሻጭ አዟሪ ነጋዴ በሚያንጠለጥለው ሳጠራ ላይ የማውቃቸውን ፍራፍሬዎች አዋሳ ላይ በየዛፉ እንደቀልድ ተንጠልጥለው እንቁልልጬ ሲሉኝ ገረመኝ። የመርካቶ ልጅ እንዲህ ዛፍና እአዋፍ የበዛበት ስፍራ ለማየት ከፈለገ ብሄረ ፅጌ ወይም መናፈሻ መሄድ ፍራፍሬዎችን ከነ ቅጠላቅጠላቸው ለማየት ከፈለገ የኢትፉሩት መሸጫ ሱቅ መሰለፍ ግድ ሲለው። የአዋሳ ልጆች ይህን ለማየት የቤታቸውን የመስኮት መጋረጃቸውን መግለጥ ብቻ በቂያቸው ነው። እኔን በማግኘቱ ደስታው ወደር ያጣው አብዱሬ የተለያዩ ፍራሬዎች ይዞ አስታቀፈኝ። እናቱ ሳራ በወቅቱ አልነበረችም። ለህክምና ናዝሬት መሆኗን ተነገረኝ። የሳራ ወንድምና እህቶች መግለፅ በሚቸግር እንክብካቤ አደረጉልኝ። መሸትሸት ሲል የአዋሳን (ፒያሳ) ለማየት ከሳራ ወንድም ጋር ወጣን። ግሎ የሚውለው የአየሩ ፀባይ አመሻሽ ላይም የማይቀዘቅዝ ተስማሚ ነው። ቀኗም ሌሊቷም ሞቃት ነው። እዚህ አገር ላይ ብርድ ልብስ ነጋዴ በሳምንቱ ከስሮ አገሪቷን የሚለቅ ይመስለኛል። የአዋሳ ፒያሳ እንደ ሸገሩ ፒያሳ የሚበዛባት ካፌ ሳይሆን ዛፍ ነው። በጎዳናዎቿ ላይ ሞተራቸው የሰው ጉልበት የሆኑ ሳይክሎችና የሚኒባስ ግልገል የሚመስሉ ባጃጆች ያለ ማቋረጥ ውር ውር ይላሉ። ጎዳናውን ተከትዬ ቁልቁል ስመለከት እይታዬን የሚቋጨው አድማሷ የአዋሳ ሀይቅ ወርቃማ ሆና ከኋላ ኪሷ ፀሀይን ስትሸጉጥ አየዋት። አቦ እንዴት አባቱ ይማርካል። ሌዊ ካፌ ገብተን ምርጥ በርገር ጋበዘኝ። ደስ የሚለውን የአየር ፀባይና እፁብ ድንቅ ማራኪ ድባብ እያጣታምን በእግር ጉዞ እያወራን ተዟዟርን። የሳራ ወንድም በድንገት… "አዙሪት" ታውቃለህ? አለኝ። "የሚጥል በሽታ" አልኩት። "አይደለም" "እና ምንድነው? " "አዋሳ ላይ አዙሪት የሚባለው ምን መሰለህ… እምም… እንግዳ ሆነህ በእግርህ ወደ ሀይቁ አካባቢ ከሄድክ አዙሪት ድንገት አቅልህን አስቶህ በራስህ እግር አየመራህ ሀይቅ ወስዶ የሚያሰምጥህ ዛር ነው።" "አረ ባክህ?" እያልኩ ተጠጋሁት። ዛሩ ከሱ ነጥሎ ወስዶ በሀይቁ እምብርት የሚያጠልቀኝ እየመሰለኝ ። "አዎ… ግን ድሮ ነበር አሁን ብዙም የለም እናም አንተ እንግዳ ስለሆንክ ለብቻህ ወደ ሀይቅ እንዳትሄድ አለኝ። መፍራቴ ገብቶት። (ከአያቴ "ቀዥቃዣ ነው" አደራ ስለተባሉ በዘዴ እግሬን እያሰረኝ ነበር)። መሽቶ ቤት ገባን። አብዱሬ ተኝቷል። ምርጥ እራት በልተን ተኛን። ሌሊት በድንገት ስነቃ ባልጠራ እይታዬ በመረብ ተከብቤ አየው። እንዴ! ስታዲየም የጎል መረብ ውስጥ ነው ያደርኩት? ብዬ ብዥታዬን አትኩሬ ስመለከት የወባ መከላከያ አጎበር ነውየከበበኝ። ለካ ማታ ከተኛው ቡሃላ በአጎበር ወባ እንዳይነድፈኝ ከልለውኝ ኖሯል። የትኛው የኳስ ፍቅሬ ነው የጎል መርብ ውስጥ የሚያስተኛኝ ? ብዬ በሀሳቤ ፈገግ አልኩ። ተመልሼ ተኛው። ጠዋት አላርም ሆኖ እያባበለ የቀሰቀሰኝ የፈረስ ጋሪዎች የቃጭል ድምፅና የአእዋፋት ፂውፂውታ ነበር። መርካቶ እንደ አላርም ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስህ የከባድ መኪና ሞተርና የሰዎች አስደንባሪ ጩኸት እንጂ እንደ አዋሳ ማራኪ የአእዋፍ ዝማሬ አይደለም። ከመኝታዬ አጎበሩን ገልጬ አይኔን እያሻሸው ወጣው። በግቢው ውስጥ የፈነጠቀው ማራኪ የማለዳው የፀሀይ ብርሃን እንደ ጨቅላ ህፃን እርቃንህን ቅባት እየተቀባባህ መሞቅ ያሰኛል። ከሳራ ወንድም ጋር አሞራ ገደል ሊያስጎበኘኝ ሄድን። አሞራ ገደል የአዋሳ ሀይቅ የቅፅል ስም ይሁን የዳቦ ስም ለጊዜው መረጃው የለኝም። በእድሜ ጠገብ ዋርካዎች በተለያዩ ዛፎችና ሳር የተሞላ አረንጓዴ የሀይቁ በረንዳ ነው። በየዛፎቹ ላይ ጉሬዛና ጦጣዎች እንደጉድ ይፈነጩበታ። አእዋፋት ይዘምሩበታል። ቁራዎች እንደ ጎረምሳ በጎረነነ ድምፃቸው ያንቋርሩበታል። በማለዳ መምጣታችን እንጂ ቀትር ላይ ቢሆን በየዋርካው ጥላ ስር የአዋሳ ስቄ ጫት እየቃሙ በሚስቁ ወጣቶች እንደሚሞላ አስጎብኚዬ ነግረኝ። ደናማውን ሳር ለበስ መሬት ሲያልቅ… ረግገጋማው ምድር ላይ ከውሃው ሾልከው የበቀሉ ረጃጅም ሳሮች ይታያሉ። ሀይቁ ላይ የተለያዩ ስዕሎችና ጥቅሶች የተፃፉባቸው ጀልባዎች ወዲያ ወዲህ ይቀዝፋሉ። ጀልባዎቹ ላይ ከተፃፉ ጥቅሶች ውስጥ… አዋሳ ምድረገነት፣አዋሳ የፍቅር ሀይቅ፣ዳኤ ቡሹ፣ ውቢቷ ኢትዮጲያ፣ ደቡብ ኢትዮጲያ የሚሉ ይገኙበታል። አሳ እዛው ተጠምዶ እዛው በስሎ እአሳ በቅቅልና በጥብስ መልክ ከምትመገብበት…ስፍራ መድረሴን የአሳው ሽታ አበሰረኝ። በተጣደ ምጣድ አሳ በዘይት እየተጠበሰ ሲንቸፈቸፍ። በመካከለኛና አሮጌ ድስት አሳ ሲቀቀል… ቡልቅ ቡልቅ ሲል… ሸማቾች ለመሸመት ሲዋከቡ። የሸመቱት ገለል ብለው ሲመገቡ ተመለከትኩ። ከተመጋቢዎቹ ማዶ የደረቀ ጫት እንጨት የመሰሉ እግሮች ያሉት አንገቱ ላይ ከረጢት መሰል ነገር ያንጠለጠለ አባኮዳ የተባለ የአእዋፍ ዝርያ ምግብ ቤት ውስጥ እንዳሉ ድመቶች የሚጣልላቸውን ቡሌ ይጠብቃሉ። የተወረወረላቸውን እንደ ጎበዝ በረኛ በመንቁራቸው ይቀልባሉ። ይህ ትዕይንት አሳ ተመጋቢ ሰው ስንጥብ እንዳይሰነቀርብት በጥንቃቄ የሚመገበውን አጅሬ አባኮዳ ያለምንም ስጋት ሲሰለቅጥ ሲታይ "አሳ መብላት በብልሃት" የሚለው ተረት ለአባኮዳ እንደማይሰራ ያስገነዝባል። ለበሳል እዕምሮ እድገት ታላቅ ሚና ይጫወታል የሚባልለትን አሳ ቀን በቀን ያለማቋረጥ የሚሰለቅጠው አባ ኮዳ ምሁር አለመሆኑ ያስገርማል። በዛው ሰሞን ከአረብ ሰፈር የእድሜ እኩዮቼ ልጆች ጋር ተግባባን። ብዙ የጫወታ ልምዶች ተለዋወጥን። በብዙ ነገር መርካቶንና አረብ ሰፈር ወክለን ተፎካከርን። እኔ ፑሽ አኘ 30 ያለማቋረጥ በመምታትና እግርን በመበልቀጥ(split)በልጬ ስገኝ እነሱ በጭንቅላት በመቆምና በመገለባበጥ በቡድን ከኔ በልጠው ተገኙ። መርካቶን ወክዬ የቀረብኩት እኔ ብቻ ስሆን አረብ ሰፈርን የወከሉት ዳኛውን ጨምሮ ሶስት ነበሩ። በውጤቱ መሰረት እነሱ በለጡ(አለ ዳኛው)። ኢፍትሃዊ ነው ብዬ ተቃወምኩ። የውድድሩ አይነት ተቀየረ። በጀት አገጫጭተን መደብን ፓስታ በሹካ መብላትና እኩል መጠን ያላቸው ሸንኮራዎች ቀድሞ በጨረሰ ውድድር ለማድረግ ሁለቱም ምግቦች ቀረቡ። በሹካ ጠቅልሎ መብላት ልምድ ስለነበረኝ እኔ በፓስታው ሳሸንፍ የአረብ ሰፈሩ አቻዬ ጥርሱ ከሸንኮራ መጭመቂያ ማሽን ባላነሰ ፍጥነት ኮረሻሽሞ በሸንኮራ አሸነፈ። መርካቶ ያለው መስሎኝ ተረቤን ጣል አደረኩ። "የአዋሳ ልጆች ስኳር ፋብሪካ ብትቀጠሩ ያዋጣችኋል ስል። ዳኛውን ጨምሮ የመልስ ምታቸው ዱላ ሆነ። በዚህ የተነሳ ውድድሩ አሸናፊው ሳይለይ ተጠናቀቀ። ይህ በሆነ ቀን ማታውን ቤት ቁጭ ብዬ ቲቪ ስመለከት ሁሴን ይጠራካል ተባልኩ።(ሁሴን በሰፈሩ የሚፈራ የሳራ ወንድም ነው) ተነስቼ ወጣው። ስደርስ ቀን የተጣሉኝን ልጆች መጥረጊያ እንጨት ላይ አንበርክኮአቸው ደረስኩ። ልጆቹ ሲያዩኝ አንገታቸውን ደፉ። ምንም እንኳን የመቱኝን ልጆች መበቀል ቢያስደስተኝም ቅሉ ከልብ አሳዘኑኝ። "እንዴት ለሶስት ሲመቱህ ዝም ትላለህ ለምን አልነገርከኝም? ሲል በቁጭት እያዘነ ተቆጣኝና "በል… ቀን እንደመቱህ ምታቸው" አለኝ ሁሴን። ይህን ማድረግ አልፈለኩም። እንደውም…ሽምግልና ገባው… "ሁሴን በጨዋታ መካከል ተጣልተን ነው ደግሞ እኔ በምላሴ ሶስቱንም በጅምላ ስለመታዋቸው ነው አፀፋውን ቦክስ ያደረጉት። እናም ጥፋቱ የኔ ስለሆነ ለዛሬ እለፋቸው አልኩት። ይህ መልሴ ሁሉንም አስደነቀ። ሁሴን ይሄን ሚስኪን ትመታላቹ? ብሎ መጅ እጁን ሊመርግባቸው ሲቃጣው። ያዝ አደረኩት። ድርጊቴ ልባቸውን ስለነካው ያለምንም ጫና ከልባቸው ይቀርታ ጠየቁኝ። በይቅርታው ሰበብ እኚህ ልጆች አዲስ አበባ እስክመለስ ድረስ በፍቅር ተንከባከቡኝ… ሳሱልኝ ወደዱኝ። ይቅርታ ከምንም ይበልጣል። ይቅርታ ባላደርግና አጋጣሚውን ተጠቅሜ ብበቀላቸው ኖሮ… ይህን ፍቅር ባላገኘው ነበር። እደግመዋለው… ይቅርታ ከምንም ይበልጣል።

No comments:

Post a Comment