Wednesday, April 20, 2016

"የመጨረሻው ሳምንት" እውነተኛ ታሪክ

     ጊዜው ከ12 አመት በፊት ነበር…በኮልፌ የእስላም መካነ መቃብር ለቀብር ዚያራ ሄድኩ። ጊቢው ውስጥ… ከቀኝና ከግራ የተዘረጋውን ደናማ መካነ መቃብር ከዋናው በር ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሰንጥቆ የሚዘልቀውን አስፓልት መንገድ ይዤ ተጓዝኩ። ወደ 30 ሜትር ወደ ውስጥ እንደዘለቅኩ ዛሬ "ሳይሰገድብህ ስገድ" የሚል አስጠንቃቂ ማስታወቂያ ከተለጠፈበት እድሜ ጠገብ ዛፍ አካባቢ ስደርስ ወደ ቀኝ ታጠፌ ግንቡ ጫፍ ያለውን የአያቴ ቀብር ደረስኩ።

ሞት ለሰው ልጅ ጊዜውን ጠብቆ የሚገጥምና ፈፅሞ የማይቀር ፅዋ ነው። ለሞት እጁን ማይሰጥ ለሞት የማይንበረከክ ለሞት የማይበገር ህያው ፍጡር የለም። በዚህም መሰረት የአያቴ ጊዜዋ ደርሶ ከሙታን ማህበር ተቀላቅላለች። ከሳምንት በፊት አያቴን ስንቀብር  ከቀብሩ አለፍ ብሎ የነበረው ባዶ መሬት በአዳዲስ ቀብር መሙላቱ አስገረመኝ … ከምኔው ሞላ? …ጉድ!በሚል ተገርሜ… በልጅ ልሳኔ ለአያቴ ብሎም ለሁሉም ሟቾች ፀሎቴን ለራሴ ብቻ በሚሰማ ድምፅ አደረስኩ…

አያቴ ቀብር ዙሪያውን በአምስት የህፃናት ቀብር መከበቡን  የታዘብኩት በዚያች ቅፅበት ነበር። ይህን ስመለከት…በአያቴ ለቅሶ ላይ አንዲት ጎረቤታችን ለለቀስተኛው ሰው አያቴን በተመለከተ አየሁ ብላ የተናገረችው ህልም ፊቴ ላይ ድቅን አለብኝ። ህልሟና አያቴን የከበበው የህፃናት ቀብር እጅጉኑ ተመሳሰለብኝ አስገረመኝም አስደነቀኝም። …ጎረቤታችን አየሁት ያለችው ህልም በአጭሩ እንዲህ ነበር…"አያቴ በሚያለቅሱ ህፃናት ተከባ በተራ በተራ እያቀፈች ፣ስታባብላቸው ስታጫውታቸው… ዘወተር እሮብ እንደምታደርገው አተካኖ ስታበላቸው…"ነበር።

☞(አያቴ ዘወትር እሮብ ወይ ሀሙስ ነጭ ቶቧን ለብሳ፣ አተካኖ ወይም ቆጮና አይብ ሰርታ ፣ እንስራ በሚያክል በግድንግድ ጀበና ቡና በቅቤ አፍልታ ፣መላ ጎረቤት ተጠርቶ እየተበላ ቡና የሚጠጣበት… በቡናው ያልተገኘ ቋሚ ታዳሚ ሰው ድርሻው ሳይነካ የሚቀመጥለት… ሲመጣ ድርሻውን የምትሰጥበት የቡና ሴሬሞኒ ልምድ ነበራት)

በአምስት ህፃናት ተከባ የሚለው ህልም በአምስት የህፃናት ቀብር ቀብሯ መከበቡ የሚያመሳስለው ነገር እንዳለው መቼም ግልፅ ነው… ሚስጥሩ ግልፅ ባይሆንልኝም ይህ ነበር ያስገረመኝ። እዛው ቀብር ቆሜ… የህልሙ ግርምት ወዳለፈው የአያቴ የመጨረሻ ሳምንት በትዝታ ወሰደኝ…

የሳምንቱ እረፍት በሆነ እሁድ ቀን እንደ እናት ካሳደገችኝ አያቴ ጋር አስኮ ከምትኖረው ታላቅ እህቴ ቤት ውለን ወደ መርካቶ ስንመለስ። ከወትሮው በተለየ እርጋታ እንደ ትልቅ ሰው ያየችውን ህልሟንና ተከትሎ የመጣውን ሀሳቧን ታማክረኝ ገባች። በጊዜዉ እኔ እድሜዬ የአስራዎቹ አጋማሽ ስለነበርና ልጅነት ስለነበረብኝ እና ያን ያህል ለቁምነገር ብቁ ስላልነበርኩ ከዚህ ቀደም እንደ አዋቂ አወያይታኝ አታውቅም ነበር… የዛን እለት ግን። እኔን ለቁም ነገር አጭታ ማወያየቷ ገርሞኛል። በውስጤ አዋቂ ሆንኩ ማለት ነው ብዬ የአዋቂነት ስሜት ከደስታ ጋር ተሰምቶኝ የምትለውን በፅሞና አዳምጣት ጀመር…

"ሰሞኑን ህልም አይቻለው…"ካቻምና የሞተው ልጄ በመኪናው አንድ ስፍራ ድረስ ወስዶኝ መኪናውን አቆመና <<ያንቺ ቦታ እዚህ ነው ውረጂ>> ብሎ ከመኪናው አውርዶኝ ሲሄድ አየሁ አለችኝ።
ህልሙ በሚስጥር አንዳች መልዕክት ያስተላለፈላት ይመስል… በዚህ ሁለት ቀን ገጠር ልጄ ጋር(እናቴን ማለቷ ነው) ደርሼ እመጣለው ማስተካክልላት ነገሮች አሉ ስለዚህ የቤቱን አደራ!" አሁን ልጅነት የለም…ትልቅ ሁነካል ብላ ከዚህ ቀደም ብላኝና  አድርጋ የማታውቀውን አደራ ጣለችብኝ። ለነገሩ በቤቱ እኔና አያቴ ብሎም የምግቤቱ ሰራተኞች ብቻ ነበር የምንኖረው። ቢሆንም ከዚህ ቀደም ገጠር ለመሄድ ስትነሳ ከሰራተኞቹ ዋናዋን ነበር አደራ ብላ የምትሄደው።

  በሁለተኛው ቀን ማክሰኞ እንዳለችውም ወደ ገጠር ሄደች። በአያቴ አደራ መሰረት የዛን ሰሞን የቤቱ ጥበቃ በእጄ ላይ ወደቀ። በዚህ አጋጣሚ አያቴ ስትመጣ ሰርኘራይዝ ላድርጋት በሚል ቤቱን አፀዳዳው። ልብሶችን በሙሉ አሳጠብኩ። አንዳንድ ቁሶችን ቦታ በመለዋወጥ የቤቱን ይዘት አሰፋሁት አሳመርኩት። ቤቱ የተለየ ድምቀት ተጎናፀፈ። ብርሃነን በብርሃን ሆነ።  የአያቴን አልጋ ዙሪያውን በትልቅ መጋረጃ ጋረድኩት። ለምን እንደዛ እንዳደረኩ አላውቅም። ይህን ሳደርግ… እህቴና የወንድሜ ሚስት ተያይዘው ወደ ቤትገቡ። ከሰላምታ ልውውጥ ቡኋላ…

"እንዴ ቤቱ እንዴት ሰፋ አማረ? ደግሞ መጋረጃው ምንድነው? "ሲሉ አደናቆትና ጥያቄ አከታተሉብኝ።

"እማዬ ሰሞኑን ሙሽራ ነች!"ለዛ ነው የጋረድኩት ብዬ በመቀለድ ያላሰብኩትን መልስ ሰጠዋቸው።

"አረ ይደብራል አንሳው"!አሉኝ። እሺ አልኩ ነገር ግን አላነሳሁትም።

መጋረጃውን በተመለከተ በርካታ ሰዎች ቢጠይቁኝም። መልሴ "እማዬ ሰሞኑን ሙሽራ ነች!" የሚለው ብቻ ሆነ። ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው እንደዛ መልስ እመልስ የነበረው እኔ ሳልሆን… የአያቴን የዛን ሳምንት ዕጣ ፈንታ ያወቀ አንዳች ነገር በኔ ምላስ የመለሰው መልስ ይመስለኛል። የመልሴ ሚስጥር ግልፅ የሆነልኝ ከሳምንት ቡሃላ ነበር። በዛን ሰሞን የአያቴ አደራ ለመጠበቅ የምግቤቱን ሂደትና ሂሳብ በቅርበት ለመከታተል አብዛኛውን ሰአት ቤት ውስጥ አሳልፍ ነበር። ከአንድም ሁለት ሶስት ሰው አያቴን ፈልጎ ቤት ድረስ መጣ። እንዴ ሰው ምን ሆኖ ነው ሰሞኑ አያቴን አጥብቆ የፈለገው?  ወይስ እኔ ሳላውቅ አያቴ ህጋዊ ጠበቃ ወይም የምክር አገልግሎት መስጠት ጀምራለች? ብዬ ለራሴ በጥያቄ መልክ …ቀለድኩ።

(ከጊዜ ቡሃላ ነበር ሰዎች አያቴን ፈልገው መጥተው የነበረው … ሁሉም ስለ አያቴ አስጊ ህልም አይተው ሊነግሯትና ዱዓ አድርጉ ሊሏት መሆኑን ያወኩት)

  አያቴ አርብ ከቀትር ቡሃላ ከገጠር ጓዝ ሳታበዛ ቀለል ባለ ሁኔታ መጣች። የተለየ እርጋታዊ ሞገስ ይታይባታል። ጎረቤት በመላ እየዞረች ሰላም አለች።(ከዚህ ቀደም ከገጠር ስትመጣ ይህ በገጠመኝ እንጂ ሆን ብላ በየቤቱ ዞራ ሰላም አትልም ነበር) ስትመጣ ለብሳው የነበረውን ልብስ አውልቃ አሁኑኑ ይታጠብ አለች። ቡና ተፈልቶ ቤቱ ደመቅመቅ አለ። ስለ መጋረጃው  ጠየቀችኝ። እንደተለመደው። "ሰሞኑን ሙሽራ ነሽ" እኮ ስላት ፈገግ አለችና… እራት ቀረበና ተበልቶ መጨዋወት ጀመርን … ገጠር ስላሳለፈችው ሁኔታ ያሰበችው እንዳሳካች እንዳስተካከለች … እናቴ አንድ ቀን እደሪ ብላ ብትለምናትም አይሆንም ብላ መምጣቷን…ሌላም ሌላም ነገር ተጨዋወተን ለመኝታ መዘገጃጀት ጀመርን። አያቴም በመጋረጃ ከጋረድኩላት አልጋዋ ተኛች። ሁላችንም በየመኝታችን ደቀስን። ከመጋረጃው ውስጥ የአያቴ ድምፅ ተሰማኝ"የበላችው እራት እንዳልተስማማት ተናገረች" ምን እንደሆነ ያልተረዳሁት ፍርሃት ፍርሃት አለኝ።

የሌሊቱ ፅልመት መጥራት በሚጀምርበት ማለዳ…ላይ አያቴ ትን እንደማለት ሲላት ሴቶቹን ቀስቅሳ የሚጠጣ ውሃ ስጡኝ ብላ ከአልጋዋ ወርዳ  ምንጣፍ ላይ ተቀመጠች። ሴቶቹ በፍጥነት ሁሃ አምጥተው አቀበሏት… የጠጣችው ውሃ አልወርድ አላት… ልጄን ጥሩት ልጄን ጥሩት ብላ ወደተኛሁበት አመለከተች… የሴቶቹ የህበረት ጥሪ ከእንቅልፌ አባነነኝ…ቀና ብዬ ስመለከት አያቴ በተጨነቀ ገፅታ … በእጇ ና ና…ቶሎ በል… በማለት ጠራችኝ። እየሮጥኩ ሄጄ ደግፌያት በድንጋጤ"እ… እማ ምን? ምንሆንሽ? " ስላት… ልትነግረኝ የፈለገችውን ለመናገር አንደበቷ ከዳት… መናገር አለመቻሏን ከፊቷ ገፅታ ተረዳው… የእስትንፋሷ ማመላለሻ ትቦ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መዘጋቱን የመጨረሻው  ክርርር የሚለው የትንፋሿ  ድምፅ አረዳን…ያለምንም ህመምና ጣር በሚስጥራዊ ህልም ጋጋታ ብቻ የተጠናቀቀው የአያቴ የምድር ቆይታ የመጨረሻ ሳምንት  ትውስታው ይሄን ይመስላል።

አላህ ጀነተል ፊርደውስ ይወፍቃት!

No comments:

Post a Comment