Tuesday, April 5, 2016

ፋኖ ነቃን ላረፋ…

መስከረም 12/2008 ዕለተ ረቡዕ ከቀኑ 8:30 አካባቢ የአዲስ አበባ መውጫ በር ለአረፋ ዚያራ በሚሄዱ መንገኞች ተጨናንቋል። ከማለዳው ጀምሮ እስከዚህ ሰዓት ድረስ መንገደኛው እንደጎረፈ ነው። የሚጎርፈው ሰው ብዛቱ ሲታይ ከጠ/ሚንስቴሩ በቀር ባገሩ ሰው የቀረ አይመስልም። ሻንጣ፣ የፕላስቲክ ምንጣፍ ፣ዳንቴል የለበሰ ድፎ፣ ዳንቴል የለበሰ ቴኘ፣ምጣድ ወዘተ... ከሰው ጋር አብረው ከሚግተለተሉ ጓዞች ውስጥ ነበሩ። እኔና ባለ መኪናው ጓደኛዬ በያዝነው ቶዮታ ዶልፊን 15 የሚጠጉ የአገሩን ልጆች ጢቅ አድርገን ጭነናል። ሰባት ያህሉ በወንበሮች ላይ ሲቀመጡ የሚበልጡትን በእቃ ላይ ተቀምጠዋል። ሁሉም ወጣቶች ናቸው። ወንዶቹ ጫት ሲያኝኩ ኮረዶቹ ማስቲካ ያኝካሉ። ከተጨናነቀው የአዲስአበባ መውጫ ጎሮሮ እንደምንም ወጥተን አለምገናደርሰን ወደ ግራ ታጠፍን ዳለቲ፣ አዋሽመልካሳ፣ ጢያ,,,ምናምን አለፍናቸው ። ቡታጀራ እንደ ደረስን ለእረፍት ከአንድ ሆቴል ጊቢ ቆምን። እንደደሌላው ጊዜ ባይሆንም ሀለቷ በመንገደኛ እንደ መሞቅ ብሏል። ቡታጂራ መንገደኞችን የምታሳርፍ የምታስተናግድ ከተማ ነች። በተለይ በአረፋና በመስቀል ጊዜ። ምግብ ስላላሰኘኝ የጀበና ቡና ለመጠጣት ከአንድ በረንዳ ላይ በጀበና አፍልታ።ከምትሸጥ ኮረዳ ጋር በርጩማዋ ላይ ቡና አዝዤ ተቀመጥኩ ።ከልጅቷ ጋር ወሬ ለመጀመር ያህል "ስራ እንዴት ነው?" አልኳት "ዘንድሮ ቀዝቃዛ ነው ባክህ? " "ለምን?" አልኳት ገፅታዋን እያጤንኩ "ወራቤ ባዛር አዘጋጅተዋል መሰለኝ አብዛኛው መንገደኛ ረግጦ ነው የሚያልፈው " አለችኝ ቅር ባለው ገፅታዋ ። ነገሩ ሲገባኝ ወሬውን አስቀይሼ ቡናሽ ይጣፍጣል ድገሚልኝ አንቺም ጠጪልኝ በኔ ግብዣ ብዬ የሶስት ቡና ከፍያት ወደ መኪናችን ሄድኩ፣ ሁሉምመንገደኞች ተሰብስበው እኔን እየጠበቁኝ ነበር። ገብቼ መንቀሳቀስ ስንጀምር ለስላሳ የያዘ ታዳጊ በመስኮት ብቅ ብሎ ጥድድፍ እያለ "ለስላሳ ልስጣችሁ?" ኮካ፣ፔፕሲ፣ሚሪንዳ አለ "ጀላቲ " አለህ አለው አንዱ ተሳፋሪ ተሳፋሪዎቹ በጅምላ ሳቁ ። "የፈላ ነው ለብ ያለ?" ብሎ መለሰ ልጁ ሳቁ ተደገመ የቃላት ጦርነቱን ለማቆም "በቃ ሁሉም ይዟል!" አልኩት። ስላልገዛነው ተናደደ መሰለኝ አንገቱን ወደ ውስጥ አሰግስጎ የተጨናነቀውን ተሳፋሪ ቃኘና "ጉዞው ለበዓል ነው ወይስ ለስደት?" ብሎ አስካካና ሄደ። እውነትም ተሳፋሪውን ድጋሚ ዞሬ ሳየው በኮንቴነር ተገጥግጦ ስደት የሚሄድ እንጂ ለበአል አገሩ ሚሄድ አይመስልም ። ከስልጤ በር ቅበት ደረስን ። ወደ ዞናችን በር መድረሳችን ከእፒከሩ ከሚንቆረቆረው የሞቀ ሙዚቃና የሞቀው ምርቃና ጋር ተደምሮ ነሻጣ ጨመርን ሙዚቃውን ተከትለን አዜምን,,, ♬"ፋኖ ነቃን ላረፋ♬ ♬ፋኖ መጣን ላረፋ ♬ ♬ቦዝ ኢንናስ ከባድ የጥፋ♬ የሚለውን የአሊ ኑር ዜማ♬♬♬ እንደ ባዙቃ በሚወነጨፈው መኪናችን ከአዲስ አበባ 170 ኪሜ የምትርቀውን ሌላዋን አበባ (ወራቤን) ከርቀት ተመለከትኳት ታምራለች። እኛ በፍጥነት ስንቀርባት እሷም ከረጅም ጊዜ ቡሃላ ልጇ እንደምታገኝ እናት ልታቅፈን በፍጥነት ትቀርበናለች ። ፍቆቿ ጎልተው ይታያሉ ፣ መስጊዶቿ በትላልቅ ሚናራዎቻቸው በወታደራዊ ሰላምታ መንገደኞችን "አርሂቡ በፎሌ የምጣ" የሚሉ ይመስላሉ። በናፈቁ እጆቿና በእቅፏ ውስጥ ገባን ከሩቅ ያየሁት ውበቷ ጎላብኝ። ለበአሉ ተሞሽራለች። ጎዳናዎቿ ተውበዋል።በመንገዷ ዳርቻ የተተከሉ ዘንባባዎቿ በውበት ላይ ውበትን ጨምረውላታል ።የመኪናችን ውስጥ ሙዚቃ ደምቋል። ከዞኗ የሚገኝ ብርቱካናማ ቀለም በብሄረሰቡ በባህላዊ የቤት አቀባብ የሚጠቀሙት አይነት የግድግዳ ቀለም ባህላዊ አቀባቡን ቅርፁን ጠብቆ በከተማዋ በተለያዩ ስፍራዎች ተቀብቶ ወራቤ ብርቱካን የዘነበባት መስላለች። እንደ እድሜዋ አይደለችም ወራቤ በፈጣን ሩጫ ላይ ነች። (አኩም የድበል ያሊቄት) ። ሰማዩ ጨለመ። ይህን ተከትሎ የመኪናችንም ፍጥነት ቀነሰ ሰው መርቅኖ ተኮራርፎ መድረጫውን በናፍቆት ይጠብቃል። አልከሶ፣ ሁልባራግ፣ሀርቡቴ በስም እንጂ በገፅታ ብዙም የማይለያዩ ከተሞችን አለፍን። አጫሞ እንደ ደረስን ከግማሽ በላይ ተሳፋሪውን አራግፈን ተጓዝን በላፍቶ ሌንቃ ወደ ቀኝ ታጠፍንና ወደ እመዣር ነካነው ። ግ,, ግ,,ግ,,ግ,,ግ,,ግ የፒስታ መንገዱ መኪናዋን የሚያንገጫግጭ ድምፅ,,,(ምናለ ቢሰሩት እስኪ?) ከምሽቱ3:30 በምስራቅ አዘርነት ወረዳ ዶዶ ገበያ ደረስን። መኪናዋን እዛው አቁምን ጓዛችን አንዠርግገን ከ30 ደቂቃ ነብስ አውጪ የእግር መንገድ በቁጥቋጦ፣በገብስ ማሳ፣ በእንሰት ውስጥ እያቆራረጥን ከጓደኛዬ እናት ቤት ደረስን። በሩ ተከርችሟል በበሩ ስንጥቅ የኩራዙ ፍንጣቂ በሩ ላይወርቃማ መስመር ሰርቶ ይታያል። በር አንኳኳን… "ማኒ" ከውስጥ የልጃገረድ ድምፅ። "ያሮተ ነግዳ" "ዮዴን" ከሚል ምላሽ ጋር በሩ ተከፈተ… እናቱና እህቱ ነበሩ…ጔደኛዬን ሲያዩ በደስታ ጮኹ አቀፉን ሳሙን ጓዛችንን ተቀበሉን። በደከመ መንፈስ ወደ ጎጆው ዘለቅን… ኩራዝና ምድጃው ላይ የሚቀጣጠለው እንጨት ከጭሱ ጋር ተጨምሮ አይን የሚይዝ ብርሃን ፈንጥቀዋል… በጎጆው… አንድ ጎን በኩል… የታሰሩ የጋማና የቀንድ ከብቶች…እንግድነታችን አውቀው ጆሮአቸውን ቀስረው ይመለከቱናል…ሰውና እንሰሳ ተፈተፈቀ ከጎጆ ቤቱ ፊት ለፊት ካለው የተንጣለለ የቆርቆሮ ቤት ሶላር አምፖል በርቶልን ጅባ ተነጥፎልን ጋደም ብለን ወሬ ጀመርን ። እለቱ(የሴቶች አረፋ)የባዐሉ ዋዜማ ስለነበር በአንድ ጣባ ላይ ጎንና ጎን ደቃቅ ጎመንና አይብ ቅቤ ላዩ ላይ ተደርጎበት አይገልፀውም ተደፍቶበት ከጨቦ ቆጮ ጋር ቀረበልን ። ያሰላም ጣዕሙ ልዩ ነው ጢቅ እስክንል አፈስነው ። ከጀለሴ ጋር ከጓሮ ጫት ሰብረን አመጣን ። የጫቱን ነገር አትጠይቁኝ እርጎ በሉት ። ቤቱ ሞቀ እናቱ እንስራ በሚያክል ጀበና ጀነፈል ቡና አፍልተው እየተጫወትን አመሸን ። በእንደዚህ አይነት እንክብካቤ ሁለት ቀን አደርን ። የጓደኛዬ አገር ከባድ የመንገድ ችግር አለበት ። ህብረተሰቡም መንገድ በአስተዳደሩ ስላልተሰራለት ሲያማርር ከአንድም ሁለት ጊዜ ሰምቻለው ። ህብረተሰቡ በብልሹ አስተዳደር ሳቢያ በመንገድ ችግር መሰቃየቱ አሳዘነኝ ። ቀጣይ ጉዞአችን ወደ እኔ ሀገር እነቆር ሌራ አደረግነው ሄድን ከሆዕሳና በሌራ እስከ ወልቂጤ ድረስ የተሰራው የአስፓልት መንገድ ልዩ ነው ። በሬንጅ ሳይሆን በቅቤ የተሰራ ነው የሚመስለው ። ሌራ የጥንት ከተማ እንደመሆኗ መጠን የእድሜዋን ያህል እድገቷ እስከዚህም ነው ። ከሌራ ወደ ዱና ጥርጊያ መንገድ ተያያዝነው ዋው እነቆር የመንገድ ችግር አይታይባትም በማስተር ኘላን የተሰራ ይመስል ሰፋፊ መንገዶች አሏት ።እነቆር የጫት እንጂ የመንገድ ችግር ብዙም የለባትም ። ዱና ገበያ ደረስን ።ዱና የገበያ ቀኗ ሰኞ ስለሆነ ቀዝቀዝ ብላለች ። ትናንሽ መስኮትና ጥቅጥቅ ያለ እቃ ካላቸው ከአንዳንድ ኪዎስኮች በቀር አብዛኛው ዝግ ነበር ። በተከፈቱ ሱቆችና ሻይቤቶች በረንዳ ላይ ወጣቶች ጫት ይቅማሉ ።በዱና ገበያ ጫት ውድ ነው ። ሻጮቹ ለገበሬና ለእንግዳ እኩል አይሸጡም ። ከከተማ ለመጣ እንግዳ መነሻ ዋጋቸው ከ50–100 ብር ነው ። ከዱና ወደ መናጂና መስጊድ አመራን ።የጥንት መስጊድነቱ አሰራሩ ይመሰክራል ። ውስጡ ዘመናዊ የተባለ ምንጣፍ ተንጥፎበታል ። ዋው ያምራል ። ከዛ ወጥተን የጓደኛዬ እህቱ ቤት ለዚያራ አመራን ። እዛም ፍቅር የሆነ መስተንግዶ ተደረገልን ። ክትፎ በአይብ በቆጮ በእንጀራ ጠረግነው ። ቀጣይ ጉዞአችን እኛ ቤት ነበር ። ለመሄድ ስንነሳ እህቱ አድራችሁ ነው የምትሄዱት ሞቼ እገኛለው አለች ። በግ ልታርድልን እያስነዳች ከተቀመጥንበት ክፍል ይዛ መጣች ። ጓደኛዬ ማደሩ ቅር እንዳሰኘኝ ተመልክቶ በስንት ልመና በጉን አስመልሶ ወደ ጃረሞ ሰንቦዬ ከሚገኘው እናቴ ቤት ተጓዝን ። ከዱና ወደ ዋናው አስፓልት ማዞሪያ በሚባለው ሰፈር አስፓልቱን አግድም ሰንጥቀን በአድመና በኩል ጃረሞ ሰንቦዬ ደረስን ከመንገዱ ግራና ቀኝ የበቀሉ ሸንበቆዎች ወደ መንገዱ ዘመም ብለው መንገዱን ጥላማና ነፋሻ ድባብ አላብሰውታል ።ቀዝቃዛው ነፋስ መንፈስ ያድሳል ። በመኪናችን ላይ እየተንጠለጠሉ ያስቸግሩን የነበሩ ልጆችን እያባረርን እያስፈራራን እንደምንም ሰፈራችን ደረስን ። ከጠባቡ የቤታችን አጥር አንድ ሁለቱንነቅዬ መኪናዋን ከጊቢያችን አቆምናት ። ህፃናቱ መኪናዋን እንደ ንብ ወረሯት ። የከተማ ሰው መኪና ገዝቶ የማይደሰተውን ደስታ ህፃናቱ መኪና በማየት ሲደሰቱ አየው ። የወንድሜን ሚስት ሰላም ብለን ወደ ቤት ዘለቅን ። ማዘር አልነበረችም ። ከከተማ የመጣች እህቴ በተዘረጋው ጅባ ላይ ተርግታለች። "ተነሺ ገፍላ " አልኳት እየሳኩ ። ድምፄን ስትሰማ በደስታ ተነስታ ተጠመጠመችብኝ ። "የምትመጣ አልመሰለኝም እኮ? አትደውልም እንዴ? " "እድሜ ለቴሌ! " አልካትና ጓደኛዬን አስተዋወኳት ። ሲሳሳሙ "የኔ እመቤት ዳርዳሩን የልጆች አባት ነው " ስላት እያፈረች ሳቀች "ማዘር የት ሄዳ ነው?" "ትመጣለች! ቁጭ በሉ!" ድንገት ስለ መጣሁባቸው አልተዘገጃጁም ነበርና ድንብርብራቸው ወጣ ። እንደምንም ቤቱን አስተካከሉ ። የሚጣፍጥ አተካኖ ቀርቦልን በላው ። በጀረባችን ተንጋለን እያወራን,,, ከውጪ የናቴን ካካካካካ የሚል የምወደው ሳቋን ሰማው ። በሩን አልፋ ገባች ። ከንፈሯ ጉንጬን አልፎ የሚገባ በሚመስል ሁናቴ አገልብጣ ሳመችን ። ደስ የሚል ምሽት ነበር ። መምጣቴን የሰሙ ጎረቤቶች ቡና አፍልተው ከቁርሱ ጋር ከነሱም አርፍደን እየተሳሳቅን አመሸን ። ጥብስ በእንጀራ ጥብስቅ አደረግነው ። በችኮላ ስለጋገሩት እንጀራው,,, ከማዘር ጋር ትንሽ መጅሊስ ተቀመጥን የዛን ቀን ያፈስኩት ዱዓ በ,,, ለ,,, ው,,,!አላህ ይቀበለን ። አንድ ቀን አድረን ወደ ጓደኛዬ ሚስት ቤተሰቦች አጫሞ ሸሻ ነካነው,,, አገሩ አፈሩ ነጭ (አሸዋማ)ሜዳማና በብዛት ጤፍ የተዘራበት አካባቢ ነው። በረሃም ይመስላል ። በአጫሞም ተመመሳሳይ መስተንግዶ ተደርጎልን ፣ ተደስተን ዱዓ አፍሰን ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ተደስቶብን። የሄድንበትን መንገድ እየገረብን አዲስ አበባ ደርሰን ። አልሀምዱሊላህ ። በመጨረሻም ለመጪው ያበቃን ዘንድ,,, በዚህች ዜማ እለያለው!! ♬ያንብረና ያ ረፋይኮ ሁለጊና ባቆመስና ♬ ♬ያትጉብለና ላረፋይኮ ሁለጊናባቆመስና♬ ♬ያንብረና ያ ረፋይኮ ሁለጊና ባቆመስና ♬ ♬ያትጉብለና ላረፋይኮ ሁለጊናባቆመስና♬

No comments:

Post a Comment