Monday, April 25, 2016

ቀዩዋ ፖፖ…

    የ3 አመቷ የጎረቤቴ ልጅ ለይላ (አበሩ) እጇን በእናቷ ተይዛ ከመዋዕለ ህፃናት ስትመለስ ሳያት…አየችንና ሮጣ መጣች… ጉንጯን ስሜያት የት እንደምትማር ጠየኳት። የምትማርበትን አፀደ ህፃናት ስትነግረኝ ፈገግ አልኩ። ምክኒያቱም ከ 24 ዓመት በፊት እኔም በዚሁ አፀደ ህፃናቱ  ተምሬበታለውና… ወደ ድሮው ትውስታ በሀሳብ ነጎድኩ … ከአፀደ ህፃናቱ መዋያ በፊት በአይነ ህሊናዬ የሚታዩኝ ትውስታዎች የሚከተሉት ነበሩ…

  መርካቶ በሚገኘው መኖሪያ ቤታችን ግቢ ውስጥ ቢጫ ቁምጣዬን ለብሼ ስሮጥ ፣ስዘል፣ ሰፈራችን ላይ በቆመ ከባድ መኪና መውጣት ተስኖኝ ጎማው ስር ስርመሰመስ … ከጓደኛዬ አብርሃም ሰርጉ ጋር… "ደርግ ያሳደገው ሌባ ፣ ኢህዴግ ይቀጣዋል" እያልን ስንዘምር፣ ደግሞ ስንሯሯጥ "ጩሎ ትትሰበራ!" የሚለው የአያቴ የማስጠንቀቂያ ድምፅ። ከ ጓደኛዬ አብርሃም ና ጀማል ጋር ከቀዩ አፈር ግድግዳ ላይ አፈር እያረጋገፍን ስንቅም ፣ከሌላ ጓደኛዬ ከሄኖክ ጋር ስንደባደብ ሲያሸንፈኝ መልሰን ስንሻረክ… ከቤት ስላክ "አልሄድም ሀምዱ ይመታኛል!" ስል (ሀምዱ እያነበብክ ነው?)  ደግሞ ያቺ ቀዩዋ ፖፖዬ ላይ በእግሬ እየተጫወትኩ ለእዳሪ ስቀመጥ…

ወይኔ! ቀዩዋ ፖፖዬ… (እሷን ያስጣለኝ… የጳውሎስ ኞኞ ትዕንግርት የሚለው መፅሄት ነበር…መፅሄቱ እንዴት እንዳስጣለኝ መጨረሻ ላይ እመለስበታለው።)

የመዋዕለ ህፃናቱ ትውስታዬ የሚጀምረው ከዚህ ነው…

   በአይን አባቴ ጋሽ ሼሂቾ ስፖንሰርነት ከትልቋ እህቴ (መይሙና) ጋር ሄጄ መዋዕለ ህፃናት ተመዘገብኩ። ትምህርት በተጀመረ ቀን እህቴ (መይሙና) አንድ እጄን ይዛኝ … በአንድ እጄ የምሳ እቃ አንጠልጥዬ ፣ በጀርባዬ ቦርሳ አንጠልጥዬ ፣ ደረቴ ላይ በመርፌ ቁልፍ የተያዘ መሀረብ አንጠልጥዬ፣ ከህፃናት መዋያው በር ደረስኩ። መግቢያ በሩ "እንቢ! አንገባም!"  በሚሉ ቁጫጭ ህፃናት ሁካታና ጫጫታ ተቀውጧል። (ነገርየው የግዞት እስር ቤት ነው እንዴ?) የህፃናት መዋያው ጥበቃ (ትዝ ይለኛል አውራጣቱ ቆራጣ ነበር!!) አንገባም ያሉ ቁጫጮችን እየዘገነ ወደ ቅጥር ግቢው ይወረውራቸዋል። ይህን ሳይ የመግባት ሞራሉን አጣውና ፈራው! አልገባም! ብዬ  ልቀውጠው አልኩና የሚገጥመኝን በቆራጣ እጅ የመወርወር ዕጣ ፈንታ አስታውሼ… በከፍተኛ ድብርት እንደ ኤሊ እየተንቀራፈፍኩ ወደ በሩ ተጠጋው በር ጋር ስደርስ። ከኋላዬ ራቅ ብላ የቆመችው እህቴ "ቡሃላ አስረስ መጥታ ትወስድሀለች እሺ!" አለችኝ። ምን አማራጭ አለኝ በሚል እይታ አይቻት ወደ ውስጥ ዘለኩ።

  … ግቢው በምድረ ዉሪ ተሞልቷል። ነባር ተማሪዎች አንድ አይነት የኑፎርም ለብሰዋል እንደኔ አዳዲስ ተማሪዎች ደግሞ የክት ልብሳቸውን ለብሰው በረድፍ ረድፍ ተሰልፈዋል። የምሰለፍበትን ረድፍ በአስተናባሪ መምህራን ተጠቁሜ ከአንዱ ሰልፍ ተቀላቀልኩ። ከሰልፋችን ፊት ለፊት ከፍ ባለ ቦታ ላይ (መድረክ መሆኑ ነው) ሙሉ ልብስ የለበሰ ሰው ንግግር አደረገ … ቀጥሎ አስቂኝ የአሻንጉሊት ትርዒት እንደሚቀርብ አስተዋውቆ ወረደ። አስቂኝ አሻንጉሊት የተባለው ነገር መድረኩ ላይ ወጣ። በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍርሃት ጋር የተዋወኩት በዚህች ቅፅበት ሆነ… ጠላታችሁ እንደዚህ ክው ይበል! እቤት ሳስቸግራቸው "ጭራቅ መጣልህ" እያሉ የሚያስቦኩኝን ጭራቅ ስጋ ለብሶ ከፊቴ ቆሞ በአይኔ በብረቱ ያየው መሰለኝ ፈራው።

  ወ ተተኘኘረዞቀ
@… ለአይኑ ብቻ ቀዳዳ ባለው ጥቁር ጨርቅ ከአናቱ ጀምሮ ቁመቱን እስካስረዘመበት እንጨት ድረስ የተከናነበ ሰው ነበር። ፈጣሪ ይይላቸውና! ይሄንን ነበር እንግዲ ለኛ ለደቂቅ ህፃናቱ አስቂኝ ነው ያሉን አሻንጉሊት።  አንደዛ ሆኖ ሲኮምክ ከማሳቅ ይልቅ እኔን ጨምሮ ብዙሃን ህፃናቱን በፍርሃት አሳቀቀን!። እኔማ ቢጨንቀኝ ቢጠበኝ ማሳቀቁን ጨርሶ እስኪወርድ አይኔን ከሱ ላይ አሸሸው። ጨርሶ ወረደ። ኡፍፍ ግልግል!!። እዚህ ያመጣችኝ እህቴን መውቀስ ቃጣኝ…  አሳቅቀው ከጨረሱን ቡሃላ ወደየ ክፍሎቻችን ገባን። ክፍሉ ውስጥ  እንደራሳችን ትንንሽ የሆኑ ወንበርና ጠረጴዛዎች ተቀበሉን። የክፍሉ ግድግዳ ዙሪያ በጣውላ በተሰራ መደርደሪያ ላይ አለፍ አለፍ ብሎ አሻንጉሊቶችና መጫወቻዎች ተደርድረዋል። መደርደሪያው እጅግ ከፍ ተደርጎ ስለተሰራ አሻንጉሊቶቹን ልናያቸው እንጂ ልንዳስሳቸው አንችልም ነበር። አንዱን ወንበር መርጬ ተቀመጥኩ… የተለያዩ መምህራን እየተፈራረቁ ራሳቸውን አስተዋወቁን…  በየአንዳንዳቸው… ሀሁሂሃ… 1234… ABCDE… በተራ ተራ ተማርን።

  እማማ ጅማቴ (የህፃናት መዋያው የፅዳት ሰራተኛ) እጃቸው ላይ… ኪሊሊሊሊሊ…  የምትል ቃጭል አንቃጭለው የእረፍት ሰአት መድረሱን አወጁልን። ከክፍል ወጣው… ከምንም አይነት ተማሪ ስላልተግባባው ለጊዜው ብቸኛ ሆንኩ። ደበረኝ! ምናልባት ከቤተሰብ ተለይቼ ስውል የመጀመሪያዬ ቀን ስለሆነ ይሆናል። ከግቢው አንድ ጥጌን ይዤ እንደ ሁሉም አዲስ ተማሪዎች በእንግዳነት ስሜት ሁኔታውን እታዘባለው። እንደልባቸው የሚሯሯጡት የሚጫወቱት የሚዘሉት ነባር ተማሪዎች ብቻ ናቸው። ከውሃ ቧንቧው አቅራቢያ የተወሰኑ ህፃናት በማይታየኝ ነገር ላይ እየተጠቋቆሙ ሲያሾፉና ሲስቁ አየው። ምን ይሆን ብየ ለማየት ሄድኩ…። ልብሳቸው ላይ እዳሪ ያመለጣቸው ቁጫጮች በእማማ ጅማቴ ቂጣቸውን እየታጠቡ ነበር። ልጆቹን እንደዛ ያሳቃቸው ቂጥ ማየታቸው መሆኑ ገረመኝ … (ያሳቃቸው እብደት ወይስ … ፍደት ?) ሳቅ ብዬ አይኔን ወደሌላ አቅጣጫ ወረወርኩ። በፍርግርግ ብረት በር የተቆለፈበት ህፃናት መዋያው ውስጥ ያለ ሌላ ግቢ ተመለከትኩ። በሩ አካባቢ አጮልቀው የሚያዩ ልጆች አሉ። ተጠግቼ ሳይ በሳር በአበባ አና በልጆች መጫወቻ የተሞላ መናፈሻ ነው…! ዥዋዥዌ ፣ሸርተቴ፣ መሸከርከሪያ ምናምን (የኛ ዘመን ኤድናሞል በሉት)። መዋያው ከገባው ለመጀመሪያ ጊዜ የተደሰትኩት በዚህች ቅፅበት ነበር። ደስታዬ ብዙም አልቆየም የመጫወቻ ግቢው የተቆለፈበትን ቁልፍ ሳይ ለመጫወት የነበረኝ ጉጉት በኖ ጠፋ…በመዋያው በቆየሁበት ሁለት አመታት ውስጥ መጫወቻዎችና አሻንጉሊቶች ከማየት ባለፈ በተግባር መጫወት አልቻልንም።  ለምን አንደሆነ ዛሬም ድረስ መልስ ያጣሁለት እንቆቅልሽ ነው።

ከዕረፍት መልስ ትንሽ ተምረን በእማማ ጅማቴ ቃጭል ብስራትነት ለምሳ ተለቀቅን። የምሳ ዕቃዎቻችንን ከሚቀመጡበት ስፍራ የራሴን እንስቼ  በግቢው ጥላማ ቦታዎች አንዱ ጋር ተቀምጬ ምሳዬን በላው። ከምሳ ቡሃላ ባለው ጊዜ መተኛት እንጂ መማር የለም። ጠዋት ደብተር አስደግፈን በተማርንበት ጠረጴዛ ላይ ከሰዓት ቡሃላ ከደረታችን በላይ ያለ አካላችንን አስደግፈን እንተኛበታለን። (የዛሬ ዘመኖቹ ፍራሽ አላቸው አሉ!)።ህፃናት  መዋያው መዋል በጀመርኩ የተወሰኑ ቀናቶች ውስጥ ትንሽ ትንሽ ተላመድኩ። ዛሬ ላይ ማላስታውሳቸው ጓደኞችንም ያዝኩ።

  አንድ ቀን በምሳ ሰዓት ላይ ችግር ገጠመኝ። ምሳዬን ለመብላት የምሳ እቃዬን አንስቼ ከለመድኳት ስፍራ ተቀምጬ። የምሳ አቃ ክዳኑን ለመክፈት አሽከረከርኩት ከወትሮው ጠበቅ አለብኝ። ሀይል ጨምሬ በትግል ከፈትኩት። ውስጡ ያለውን እንቁላል በዳቦ ሳይ ደነገጥኩ። ያስደነገጠኝ እንቁላል ተቋጥሮልኝ ስለማያውቅ አልነበረም። የዛን ዕለት ጠዋቱን ግን  እህቴ የቋጠረችልኝ እንቁላል እንዳልነበር ስላወኩ እንጂ። አይ በቃ እህቴ ደስ እንዲለኝ በመሃል መጥታ ምግቡን በእንቁላል ቀይራልኝ ይሆናል ብዬ። በእህቴ እንክብካቤ እየተደሰትኩ። ቡሃላ ሳገኛት እንዴት አቅፌ ጉንጯ ላይ  እንደምስማት እያሰላሰልኩ እንቁላሉን መከትከት ጀመርኩ። ጉድና ጅራት ከኋላ ነው እንዲሉ ከዚህ ቡሃላ ነበር ጉዱ የተከሰተው። እየበላው ሳለ … አንድ ተማሪ ከአንድ መምህር ጋር ወደኔ አቅጣጫ ሲመጡ አየው። ተማሪው የኔን አይነት የምሳ እቃ በእጁ አንጠልጥሏል። የዚህን ጊዜ ነበር አንድ ስህተት መፈጠሩን ደመነብሴ ሹክ ያለኝ። አጠገቤ ሲደርሱ ከአይኔ ብቻ ቀና ብዬ አየዋቸው።

ልጁ "ይሄ ነው የኔ ምሳ ዕቃ ብሎ" ወደ ምበላበት የምሳ እቃ ጣቱን ቀሰረ። (እናቱንና! ጣቱን ብነክሰው ደስ ባለኝ።)

"ለምን የሰው ምሳ እቃ አነሳህ?" አለችን መምህሯ። ድንብርብሬ ወጣ!

"የራሴ መስሎኝ ነው!" አልኩ አፌን ዳቦ በእንቁላል በሞላሁበት አንደበቴ እየተኮላተፍኩ።

  እርግጥ ነው የምሳ እቃዎቹ መመሳሰል እንደ አህያ ለመለየት የሚቸግር ነበር። ይህን የተረዳችው መምህሯም "ለሌላ ቀን ሁለታችሁም ስማችሁን ፃፉበት" ብላ። ያጋመስኩትን ምሳ እቃ አንስታ የኔን አስቀምጣ ሄደች። ምሳ ዕቃዬን ለመክፈት ወኔው ጠፋብኝ። እንቁላል እንዳልተቋጠረልኝ ባውቅም በሆነ ተዓምር እንቁላል እንዲሆንልኝ ተመኘው። ከአንቁላል ወደ እንጀራ በወጥ ወደ ኋላ መመለሱ እየሸከከኝ ክዳኑን ሳሽከረክረው ሳያታግለኝ ተከፈተ። አይ በቃ! እንጀራ ነው እንቁላል ቢሆን በደንብ አጥብቃ ትዘጋው ነበር…  የፈራሁት አልቀረም እንጀራ በወጥ… ሆኖ ተገኘ። ከባድ የአፒታይት መቆለፍ ተከሰተብኝ። አሳይቶ መንሳት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተረዳው።

☞ ቅድም እህቴን እንዴት ጉንጯን እንደምስማት ያቀድኩትን ዕቅድ!…  እንዴት አድርጌ ጉንጯን እንደምነክሳት በማቀድ … ቀየርኩት!! Kkkkk

   • ስለ ቀዩዋ ፖፖዬና በሷ መቀመጥን ስላስተወኝ የጳውሎስ ኞኞ ትዕንግርት መፅሄት ልንገራችሁና እትትዬን ልቋጭ።

   በልጅነቴ የግሌ ንብረት ከምላቸው ቁሶች ውስጥ አንዷ ቀዩዋ ፖፖዬ ነበረች። በዚህች ፖፖዬ ስቀመጥ ደስ ይለኛል። ነፃነት የተባለ ሁሉ በመዳፌ ያለ ያህል ይሰማኛል።በዙፋን ላይ የተሰየምኩም ጭምር…  ይሄ ስሜት ያለ ምክኒያት አልተከሰተም። በእሷ  ከተቀመጥኩ "ና ይሄን እቃ" ይዘህ "ና ሼኪ ሱቅ ሂድ" የለ መላላክ የለ። ለዚህም ነበር ቶሎ ልፋታት ያልቻልኩት። ይሄን ፖፖ የሙጥኝ ማለቴን የሚያውቀው ታላቅ ወንድሜ(ከድር) አንድ ቀን በዚህችው ዙፋኔ ላይ በተቀመጥኩበት በአይኑ ገርምሞኝ አልፎኝ ወደ ቤት ገባ። ሲመለስ እጁ ላይ ትዕንግርት የተሰኘውን የጳውሎስ ኞኞን መፅሄት ይዞ ነበር። (ይህ መፅሄት እስከ ቅርብ ጊዜ እጄ ላይ ነበር)። አጠገቤ ደርሶ ሊያሳኝ የፈለገውን ገፅ እየገላለጠ መፈለግ ጀመረ። የሚፈልገው ገፅ ሲደርስ…

መፅሄቱን እያቀበለኝ "ይህን ፎቶ ተመልከተው…! አለኝ።

  በተቀመጥኩበት ተቀብዬው ፎቶውን አየሁት። ፍቶው (አንድ ድመት በሽትቤት መቀመጫ ሴራሚክ  ላይ ተቀምጣ)ነበር። በአፍረት አንጋጥጬ በአፍረት አየሁት

"ድመት እንኳ ሽንትቤት በምትጠቀምበት ዘመን! አንተ ዘላለም አለምህን ፖፖ ላይ ትቀዝናለህ? ቀሽም!" ብሎኝ ብቻ ሄደ።

  በድመት መበለጤ ከነከነኝና ከዛን ቀን ቡሃላ  ከፖፖዬ ጋር ተለያየን። የታላቅ ወንድሜ ሳይኮሎጂ ሰራ። ፖፖዬ ስራ ፈታች። ጊቢ ውስጥ ተጥላ ተጉላላች… ይህን የተመለከተች መካከለኛዋ እህቴ (ሽትዬ ወድሻለው) አነሳቻትና አፈር ሞልታ አበባ ተከለችባት። አይ ልጅነት!!

No comments:

Post a Comment